አሳ ሁልጊዜ በመረብ ብቻ አይጠመድም፡፡ የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራሙ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ውጤት በማስመዝገብ ሲከሸፍ፣ ብዙዎቹ ቤተእስራኤሎችና እነሱን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእስራኤል መንግስት ቤተእስራእሎችን ለማዋሀድ በሚል የቀረፃቸውን ሌሎች ፕሮግራሞች የአፈፃፀማቸውን ጉዳይ መለስ ብሎ ለመገምገም አረፍ የሚልበት ታዛና የጥሞና ጊዜ ያገኛል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የድሩዝ ማህበረሠብ አባላት ተለይተው ከሚታወቁበት ነገሮች አንዱ ለሚኖሩበት ሀገር መንግስት ያላቸው የማያወላውል ታማኝነት ነው፡፡ በድፍን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስጥ በሀገሬ የሚኖሩ ድሩዞች የተቃውሞ ድምፃቸውን አሠሙብኝ ወይም ደግሞ በአመጽ ተነሱብኝ ብሎ ስሞታውን ያሠማም ሆነ የሚያሠማ መንግስት ለመድሀኒትም ቢሆን ተፈልጐ አይገኝም፡፡ በ1970ና 80ዎቹ የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የራሳቸውን ሚሊሻ በማቋቋም ነፍጥ አንስተው ውጊያ የገጠሙት ህልውናቸዉን አደጋ ላይ ከጣሉት ታጣቂ የሚሊሻ ቡድኖች ጋር እንጂ ከሊባኖስ መንግስት ወታደሮች ጋር አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤሎችም በእስራኤል የሚኖሩ “ድሩዞች” አይነት ነበሩ፡፡

እግራቸዉ የእስራኤልን መሬት ገና ከመርገጡ ጀምሮ የሂብሩ ጋዜጦች መብታቸውንና ነፃነታቸውን የሚጋፋ፣ ሠብአዊ ክብራቸዉንም የሚያንቋሽሽ አስከፊ የጥላቻ ዘመቻ ሲከፍቱባቸው፤ ያይጥ ምስክር ድንቢጥ እንዲሉ ጋዜጦችንም ተከትለው የተለያዩ የእስራኤል ተቋማት፣ የተለያዩ የእስራኤል የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት መሪዎችና የማህበረሠብ አባላት ተዘርዝሮ የማያልቅ የዘረኝነት በደል ሲፈጽሙባቸው በእስራኤል መንግስት ላይ የነበራቸው ተስፋና እምነት እንደተጠበቀ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎቹ ለእስራኤል መንግስት የነበራቸውን ክብርና እምነት እንዲህ በቀላሉ እሰየው ብለው ለድርድር የሚያቀርቡት ጉዳይ ጨርሶ አልነበረም፡፡ የተስፋዋ ሀገራችን በሚሏት እስራኤል ይሆናል፤ ያጋጥመናልም ብለው ጨርሰው ባልገመቱት ሁኔታ ያ ሁሉ ግፍና በደል ወደው እስኪጠሉ ድረስ ሲፈራረቅባቸው የእስራኤል መንግስት በወቅቱ የሠጣቸዉ መልስ አልነበረም፡፡ በዘርና በቀለማቸው የተነሳም ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ እንኳ ማንም ብሏቸው ወይም ጠርቷቸው የማያውቀውን “ኩሽም” (ባሪያ) የሚል መዘባበቻ ሲሆኑ የእስራኤል መንግስት ግን ተፈልጐም እንኳ ሊገኝ አልቻለም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቤተእስራኤላውያን ከተጣዱበት የዘረኝነት መጥበሻ ላይ እንዳሉ በፀጥታ መገላበጥን እንጂ በሚያምኑትና በሚያከብሩት የእስራኤል መንግስት ላይ ልባቸውን ለማሻከርም ሆነ ፊታቸውን ለማጥቆር ጨርሶ አልሞከሩም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በዚያን ወቅት በእስራኤል መንግስት ላይ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አንጀት አልነበራቸውም ነበር፡፡

እንደ እስራኤል ድሩዞች ተደርገው መቆጠር ጀምረው የነበሩት ቤተእስራኤሎች ማንም ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ ባልገመተው ሁኔታ በእስራኤል መንግስት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃውሞ አደባባይ በመውጣት የእየሩሳሌምንና የሌሎችም የእስራኤል ታላላቅ ከተሞች ለአንድ ወር በዘለቀ ጠንካራ የተቃውም ስብሠባና ሠልፍ ቀውጢ ያደረጉት ሀይማኖታቸውን በተመለከተ በከፍተኛ ሀፍረት ላይ የጣላቸውና በእጅጉ ያሸማቀቃቸው በደል ከደረሠባቸው በኋላ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎች ከዚህ በፊት በከፍተኛ ትዕግስትና ሆደ ሠፊነት ይዘዋቸው የነበሩት የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ እንዲያገኙ የእስራኤል መንግስትን ሳያሠልሱ መወትወት የጀመሩትና አልፎ አልፎም የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሠማት የጀመሩትም ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ የእስራኤል መንግስት ግን የቤተእስራኤሎችን ችግር የተረዳው ገልብጦ በተቃራኒው ነበር፡፡ ለእስራኤል መንግስት የቤተእስራኤሎች ችግር እውነተኛ ችግር ሳይሆን እነሱን ለማዋሀድ በሚል የሚያደረግላቸው መጠነ ሠፊ እርዳታ ስለበዛባቸው ከመቅበጣቸው የተነሳ የመጣ ችግር አድርጐ ነበር፡፡ እናም በየጊዜው የሚያቀርቡትን የመፍትሄ አቤቱታ ለማዳመጥ የሚያስችል ጊዜውም ሆነ ልቦናና የመስሚያ ጆሮ አልነበረውም፡፡

ይልቁንስ ነገሩ ሁሉ የምግብ ፍላጐት ከመብላት ጋር ይመጣና ይጨምራል እንደሚባለው ሆኖበት ነበር፡፡ እናም አንዱ ጥፋት በጊዜ የመታረም እድል ማግኘት ሳይችል በሌላኛው ላይ እየተደራረበ ሄዶ፣ ቤተእስራኤሎቹን ከተቀረው የእስራኤል ማህበረሠብ ጋር በሚገባ ለማዋሀድ በሚል በእስራኤል መንግስት ተደግሶ የነበረውን “የቅልቅሉን” ድግስ የተጠሩት እንግዶች ሊቀምሱት እንዳይችሉ አድርጐ በአሳዛኝ ሁኔታ እንጀራውን አሻገተው፣ ወጡን እጅ እጅ እንዲል አደረገው፡፡ የእስራኤል መንግስት ቤተእስራኤሎች የራሳቸውን ቤት መግዛት እንዲችሉ ለማበረታታት በሚል በሠጣቸው ብድር አማካኝነት እስከዛሬ አስር አመት ድረስ አስር ሺ አምስት መቶ የሚሆኑ ቤተእስራኤላውያን አብዛኞቹ ባለ አንድ መኝታ ቤት የሆኑ አፓርታማዎችን ወይም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመግዛት ችለዋል፡፡ ከተቀሩት ውስጥ አብዛኞቹ በመንግስት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ፣ ከዛሬ አስር አመት ወዲህ ወደ እስራኤል የመጡት ደግሞ ዛሬም ድረስ በመጠለያ ጣቢያዎችና በተንቀሳቃሽ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ለቤተእስራኤሎች ተዘርግቶ የነበረው የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራም እንደተገለፀው የተወሰኑትን የቤት ባለቤት ሊያደርጋቸው ቢችልም የሚፈለገውንና ቀድሞውኑ የታሠበለትን ውጤት ሳያመጣ እንደከሸፈ በእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ተመስክሮበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእስራኤል መንግስት ሌላ በተጠያቂነት ቀርቦ ቃሉን ሊሠጥ የሚችል ተጠያቂ አካል ሊኖር አይችልም፡፡ እንዴት ቢባል… የእስራኤል መንግስት ይህን የብድር ፕሮግራም የጀመርኩት ቤተእስራኤሎችን ለመርዳት በሚል “ቅን” መንፈስ ነው በማለት ሞቅ ያለ ፕሮፓጋንዳውን ቢለቅም ለፕሮግራሙ አፈፃፀም ሙሉ ቀልቡንና ልቡን ጨርሶ አልሠጠም ነበር፡፡ ፕሮግራሙን ለማስፈፀም የተጠቀመባቸው ስትራተጂዎች በሙሉ የተንጋደዱና አቅም ባላቸው ባለሙያዎች የተያዙና የተመሩ ጨርሶ አልነበሩም፡፡ የፕሮግራሙ ጠቅላላ አሠራርም የግብር ይውጣ ነበር፡፡

ይህን የብድር ፕሮግራም አሠራር በትኩረት በመከታተል አፈፃፀሙን በደንብ መገምገም የቻሉ የማህበራዊ ኑሮ ጥናት ባለሙያዎች፤ የእስራኤል መንግስት ቀድሞውን ቢሆን የእስራኤል “ኩሽም” የሆኑትን ቤተእስራኤሎች ከተቀረው “ናሽም” (ነጭ) የእስራኤል ማህበረሠብ ተለይተው በአንድ አካባቢ ብቻ ተከማችተው እንዲኖሩ ለማድረግ እጅግ በረቀቀ መንገድ ነድፎ ያዘጋጀው ፕሮግራም ነው እያሉ በሰላ ትችት ሲያብጠለጥሉት ኖረዋል፡፡ ይህን የባለሙያዎች ትችት ትክክል ነውም አይደለምም ብሎ መከራከሩ አጨቃጫቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የእስራኤል መንግስት በፈለገው አይነት አላማ ቢያዘጋጅም የመጨረሻው ውጤቱ ግን ከቀረበው ትችት ጋር አንድ አይነት ነበር፡፡ የመኖሪያ ቤት ለመግዛት ብድር የወሰዱ ቤተእስራኤሎች አብዛኞቹ ስራ አጥ ነበሩ፡፡ ስራ አላቸው የሚባሉትም ቢሆን እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ በሚያስገኙ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ እናም ከወሰዱት ብድር ላይ ትንሽ ጨምረው በተሻሉና መካከለኛ ገቢ አላቸው ወደሚባሉትና ሁሉም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች በተሟሉባቸው አካባቢዎች ውስጥ ቤት ለመግዛት የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ሁሉም በብድር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው ያመሩት ርካሽ የመኖሪያ ቤቶች ወደሚሸጡባቸው፣ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ባልተዘረጉባቸው ኋላቀርና ጭራሹኑ ወደተዘነጉት አካባቢዎች ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ በድህነት የተቆራመዱ፣ በጨለማ የተዋጡና፣

ከሌላው የእስራኤል ህብረተሠብ በእጅጉ የተጉላሉ “የኩሽም ቤተእስራኤሎች” የመኖሪያ ጌቶዎች እንዲመሠረቱ ዋነኛ ምክንያት ለመሆን በቃ፡፡ የማታ ማታ አፍላ፣ ኪርያት ጋት፣ ኦር ይሁዳ፣ ኪርያት ማላኪህና የመሳሠሉት በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ሠፈሮች “ናሽም” እስራኤላውያን ዝር የማይሉባቸዉ ወይም ዝር ሊሉባቸው በጣም የሚፈሯቸው የቤተእስራኤሎች መኖሪያ ጌቶ ሠፈሮች በመሆን አለም አቀፍ እውቅናን ለመጐናፀፍ ቻሉ፡፡ አሳ ሁልጊዜ በመረብ ብቻ አይጠመድም፡፡ የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራሙ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ውጤት በማስመዝገብ ሲከሸፍ፣ ብዙዎቹ ቤተእስራኤሎችና እነሱን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእስራኤል መንግስት ቤተእስራእሎችን ለማዋሀድ በሚል የቀረፃቸውን ሌሎች ፕሮግራሞች የአፈፃፀማቸውን ጉዳይ መለስ ብሎ ለመገምገም አረፍ የሚልበት ታዛና የጥሞና ጊዜ ያገኛል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህንን ተስፋ ያደረጉትም “አንዴ የተሸነፈ ሁለት ጊዜ ያፍራል” የሚለው እድሜ ጠገብ የማስተዋልና የብልሀት አነጋገር መቼም ቢሆን ለእስራኤል መንግስት አይጠፋውም ከሚል ግምታቸው በመነሳት ነበር፡፡ ቶማስ ሐንዴ የተባለ ደራሲ “Mr. Nicholas” በሚል ርዕስ በ1952 ዓ.ም ባሳተመው መጽሀፍ፤ አደጋን ለመጋፈጥ የማይፈልጉ ቦቅቧቃ ሰዎች፤ ምንም ቢያደርጉ ምን በአስደናቂ ነገሮች የተሞላ ህይወት ለመኖርና አስደናቂ ውጤቶችን ለመቀዳጀት ከቶውንም አይችሉም ይላል፡፡ ይህ የቶማስ ሒንዴ አባባል በቀላልና አጭር አገላለጽ ሲቀመጥ “ጀብዱ ለጀብደኞች፣ (Adventure is for fare adventurous) ማለት ነው፡፡ ከ1973 ዓ.ም የዬም ኪፑር ጦርነት ድል ማግስት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በወይዘሮ ጐልዳ ሜየርም ሆነ በቤንጃሚን ናታንያሁ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመራው የእስራኤል መንግስት ወታደራዊ የሆነውን ነገር ለጊዜው ትተን ማህበራዊ ጉዳዮችን ብቻ በተመለከተ የወሠዳቸውን የተለያዩ የፖሊሲም ሆነ ሌሎች እርምጃዎችን በስሱ በመገምገም ብቻ የእስራኤል መንግስት ጀብዱ (Adventure) አድናቂና ጀብደኛ (Adventurous) መንግስት እንደሆነ ለመገንዘብ ምንም አይነት የአዕምሮ ብሩህነትን አይጠይቅም፡፡

አሳዛኙ ነገር ግን እነዚያ ቤተእስራኤሎችና የቤተእስራኤል ድርጅቶች ይህንን በወጉ መገንዘብ አለመቻላቸው አሊያም ጨርሰው መዘንጋታቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የእስራኤል መንግስት፤ የመጀመሪያው ውሸት ወደ ሁለተኛው ውሸት ይመራል እንደሚባለው አይነት ከመጀመሪያው ስህተት ወደ ሁለተኛው ተሸጋገረ፡፡ የእስራኤል መንግስት ቤተእስራኤሎችን ለማዋሃድ በነደፈው ማስተር ፕላን፣ የስራ እድልን በተመለከተ ያስቀመጠው ዋነኛው ግቡ ለቤተእስራኤሎች የሙያና የክህሎት ስልጠና መስጠት የሚል ነው፡፡ በዚህ መሠረት የእስራኤል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለቤተእስራኤሎቹ በቂያቸው ነው ብሎ የመረጠላቸው የሙያና የክህሎት የስልጠና መስኮች የብረታብረት፣ የእንጨት ስራ፣ የነርሲንግ፣ የሆቴል መስተንግዶና፣ የልብስ ስፌት ናቸው፡፡ የእውነት ለመናገር ባለእጅነትን አምላክ ሁልጊዜ ለቤተእስራኤሎች ብሎ የጣፈው ሙያ ይመስላል፡፡ ይህ ላይ ላዩን ሲያዩት አሪፍ ነገር ይመስላል፡፡ ነገር ግን ቤተእስራኤሎች አስቀድሞ በተመረጠላቸውና በተወሰነባቸው በእነዚህ የስልጠና መስኮች የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅትም ሆነ ከዚያ ቀደም ብሎ እነዚህ የስራ መስኮች በፍልስጤማውያንና በሌሎች ዜጐች ከአፍ እስከደገፋቸው ተይዘው ነበር፡፡ እናም ቤተእስራኤሎቹ እንደታሰበው ሰልጥነው ቢወጡም፣ በእስራኤል የስራ እድል መድረክ ላይ ተወዳድረው ስራ ማግኘት በእጅጉ አዳጋች ሆነባቸው፡፡ በመጨረሻም ያተረፉት ነገር የእስራኤልን አውራጐዳናዎች ማጽዳት፣ መናኛ ስራዎችን እጅግ መናኛ በሆነ ክፍያ መስራትና የእስራኤል የአዲስ መጤዎችና የውህደት ሚኒስቴር የሁልጊዜም የእርዳታ ጥገኛ ሆኖ መቅረትን ነበር፡፡ በትምህርትና በሌሎች የማህበራዊ ዘርፎች የተገኘው ውጤትም ከዚህ ጨርሶ የተለየ አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤላውያን በተሻለ ተዋህደውበታል ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ተቋም ቢኖር የእስራኤል የጦር ሀይል ብቻ ነው፡፡

ቤተእስራኤሎች እውነተኛ እስራኤላዊ መሆናቸውንና ለእስራኤል ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት የህይወት መስዋዕትነትም ቢሆን በመክፈል ለማሳየት ቁርጠኛ አላማ የያዘና ለዚህም የምራቸውን የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊትን በገፍ የተቀላቀሉትም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ተቋምም ቢሆን ያጋጠማቸው የዘረኝነት መድልዎ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ የእስራኤል መንግስት ችግሮቹን በጊዜ ለመፍታት ባለመቻሉ ሳይሆን ፈጽሞ ባለመፈለጉ የተነሳ በሁሉም ነገር የመጨረሻውን ዝቃጭ ደረጃ የያዘ አንድ የእስራኤል ማህበረሠብ ለመፍጠር ቻለ፡፡ ቤተእስራኤሎችም የማታ ማታ ከመላው የእስራኤል ማህበረሠብ ተለይተው የዘረኝነት ጥቃትና መድልዎ ሰለባ ሆነውና የመጨረሻውን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ይዘው ራሳቸውን አገኙት፡፡ ይህም ሁኔታ የአብዛኞቹን ቤተእስራኤሎች ቤተሠብ ክፉኛ አመሠቃቀለው፡፡ በእድሜ የገፉት ለከፍተኛ ግራ መጋባት ሲዳረጉ፣ ወጣቶቹ ደግሞ በከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ በመውደቃቸው “ራስታ” ለመሆን ባዘኑ፡፡ እነዚሁ ቤተእስራኤሎች በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ስለወደቁ፣ በወንጀል ድርጊት መሳተፍ፣ የወንጀል ቡድን አባል መሆን፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀምና ማዘዋወር ድርጊት ውስጥ መሳተፍ ጀመሩ፡፡

በዚህም የተነሳ የቤተእስራኤል ወጣቶች የእስራኤልን እስር ቤቶች ማጨናነቅ ተያያዙት፡፡ ለህይወት ጉጉት ማጣታቸውና ከህይወት ትግል ማፈግፈጋቸውም መገዳደልንና ራስን ማጥፋትን እንደ ዋነኛ የችግር መገላገያ መፍትሄ አድርገው ይቆጥሩት ጀመር፡፡ የተቀረው የእስራኤል ህዝብ በአባታቸው ኖህ እንደተባረኩት ልጆች እንደ ሴምና ያፌት ናቸው፡፡ ማርና ወተቱን እለት ተዕለት እየተቆጣጠረ የቆዳ ስልቻቸውን የሚሞላላቸው የራሳቸው አሳላፊ አላቸው፡፡ የቤተእስራኤሎች ኩባያ ግን ባዶ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሀገሪቱ የማርና የወተት ሠልፍ የእነሱ ተራ ከሁሉም የመጨረሻው ስለሆነ ነው፡፡ አሁን እነሱ ለአምላካቸው እያቀረቡት ያለው ፀሎት አንድ ብቻ ነው፡፡ አምላካቸው የራሳቸውን ነህምያ (ነቢይ) እንዲሠጣቸው!! አሜን ያድርግላቸው!

Published in ከአለም ዙሪያ

“ቱሪዝም በኢትዮጵያ” በተሰኘ በጥናት የተደገፈ መጽሐፋቸው ጌታቸው ደስታ የጥምቀት እንዲሁም የቃና ዘገሊላ ሚካኤል ክብረ በዓላትን አስመልክተው “በጐንደር በተለይ አፄ ፋሲለደስ መታጠቢያ ተገኝቶ የጥምቀት በዓልን ማክበር እጅግ በጣም ጐብኚዎችን የሚያስደምም ትርዒት ነው” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ በዓለ ጥምቀት መዲና የሆነችው ጐንደር፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶችንም ጭምር ተመልከቱልኝ ትላለች፤ ጥምቀቷን አስታካና ከዚያም ውጪ ባሉ ቀናት፡፡ ጥምቀትን ተንተርሰው በከተማይቱ አስተዳደርና በሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ከተዘጋጁት ፌስቲቫሎች አንዱ ባለፈው ሳምንት ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው “ኢትዮጵያን በጐንደር የባህል ፌስቲቫል” ነው፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ከጐበኘሁአቸው ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ከቋራ ወጥተው የኢትዮጵያን ታሪክ ለመለወጥ የጣሩ አንዲት ትልቅ ሴት ይገኙበታል፡፡ በ18ኛው ክፍለዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ፣የነገሥታት ልጆች ታስረው ከሚጠበቁበት ለንግሥና የበቁት አፄ በካፋ ሁለተኛ ሚስታቸውን ያገቡት እንደተራ ሰው መስለው በሄዱበት ሲታመሙ በወላጆቿ ፍቃድ አንዲት ልጃገረድ አስታማቸዋለች፡፡ ከሕመማቸው ያገገሙት በካፋም ንግሥት አደረጓት፡፡

የንግሥትነት ዘውድ የተቀዳጀችው የያኔዋ ብርሃን ሞገሳ ወይም ወለተ ጊየርጊስ በኢትዮጵያ ታሪክ የምትታወቀው “ቋረኛዋ እቴጌ ምንትዋብ” በሚል ስሟ ነው፡፡ እንደ ንግሥቲቱ ሁሉ ከቋራ የፈለቁት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ አንድነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አምና በጐንደር ከተማ እምብርት ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ትተውት ከሄዱት ታሪክ ውጭ በጐንደር እንደቀደምት ነገሥት ቤተመንግሥት ያልተውት አፄ ቴዎድሮስ ያህልም ባይሆን ቋረኛዋ እቴጌ ምንትዋብ በዘመናቸው የነበረችይቱን ኢትዮጵያ በዙፋን እና ከዙፋን ጀርባ መርተዋል፡፡ ምንም እንኳ ከባላቸው አፄ በካፋ የተጀመረ አመራራቸው እስከ ልጅ ልጃቸው ተፍፃሜተ - መንግስት አፄ ኢዮአስ ቢደርስም የንግሥና ዘመናቸው በራስ ስዑል ሚካኤል ቀታሌ ንጉሥ ሲያበቃ የተዳከመች ኢትዮጵያን ጥለው አልፈዋል፡፡ እኒሁ ንግሥት ከተዋቸው መንፈሳዊ ቅርሶች አንዱ ራሳቸው ያሰሩት የቅድስት ቁስቋም ማርያም ቤተክርስትያን ናት፡፡ ቤተክርስትያኗ የንግሥቲቱን፣ የልጃቸውን የቋረኛ አፄ ኢያሱን እና የልጅ ልጃቸውን አፄ ኢዮአስን አጽም ጨምሮ በርካታ ቅርሶችን ይዛለች፡፡ ከነዚህ ቅርሶች መካከል የታላቁ አባይ ወንዝን መነሻ ለማጥናት ብሎ አስቴር የተባለች ኢትዮጵያዊት ያገባው ስኮትላንዳዊው አሳሽ ጀምስ ብሩስ መኖሪያ ቤት ፍርስራሽ አለ፡፡

ከዚሁ ጐን ንግሥቲቱ በአደፍ ወቅት የቤተክርስትያን አገልግሎት የሚሳተፉበት ቤት እና ጳጳሱ ወይም በማዕረግ ከፍተኛ የሆነው ካህን “እግዚአብሔር ይፍታሽ” የሚሉባቸው ከፍታ ቦታም ይገኛል፡፡ ከሱ ባሻገር የሚገኘው ደግሞ እቴጌ ምንትዋብ ካህናቱንና ሌሎች እንግዶች ግብር የሚያገቡበት ወይም በዘመኑ አጠራር ምግብ የሚያበሉበት አዳራሽ ይገኛል፡፡ አዳራሹ የንግሥት እና የካህናት ብልሃት የተወዳደረበት አንድ ታሪክም አለው፡፡ ቋረኛዋ ምንትዋብ መንገዶቻቸው ቢለያዩም እንደ ቋረኛው ካሳ አፄ ቴዎድሮስ ሁሉ ካህናቱን በእጅ ለማስገባት ያደረጉት ጥረት፣ ንግሥታዊ ምንጣፋቸውን የሽንት ጨርቅ አድርጐባቸዋል፡፡ ካህናት ሁሌ ያሸንፉኛል፡፡ ዛሬ ግን እኔ አሸንፋቸዋለሁ ብለው የተነሱት ንግሥት፣ እጅጉን ጨው የበዛበት ምግብ ለካህናቱ በማስቀረብ የወይን ጠጅ በገፍ እንዲንቆረቆር አደረጉ፡፡ የግብር አዳራሾቹ በሮች እንዲዘጉ ጥብቅ ትእዛዝም አስተላለፉ፡፡ በቆይታ ብዛት ፊኛቸውን የቀበተቻቸው ካህናት የሚያደርጉትን አጡ፡፡ የተፈጥሮ ግዴታቸውን ለመወጣት ባለመቻላቸውም ማውጠንጠን ጀመሩ፡፡ አስበው አስበውም አለቃ ኢሳይያስ በተባሉ ቄስ አንድ ሃሳብ አመነጩ፡፡ አለቃም በላቀ ዘዴ ንግሥቲቱን ጠየቁ፡፡ “እቴጌ አምስት መቶና አምስት መቶ ስንት ነው?” “”ሺነዋ!” አሉ እቴጌ ምንትዋብ፡፡

“እቴጌ ካሉስ እሺ!” አሉና አለቃ ኢሳይያስ እጀጠባባቸውን ከፍ ዝቅ በማድረግ ሽንታቸውን ሸኑ፡፡ ሌሎቹም ተከተሏቸው፡፡ የእቴጌ ምንትዋብ ውድ የአበባ ምንጣፎች በሽንት ራሱ፡፡ እቴጌም በአለቃው መላ በመገረማቸው ሸለሟቸው፡፡ አዳራሹም እስካሁንም ድረስ “ሽነዋ አዳራሽ” ይባላል፡፡ ከዚህ አዳራሽ እልፍ ብሎ የእቴጌይቱን ዘመን የሚያስታውስ አነስተኛ ቤተመዘክር ተቋቁሟል፡፡ ቤተመዘክሩ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን አጽሞች ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊና አለማዊ ቅርሶች ይዟል፡፡ ከነዚህም መካከል ነጋሪት፣ መጽሐፈ ግንዘት፣ ስዕለ አድህኖ፣ እቴጌይቱ በአንባቸው ርስራስ አሰሩት የተባለው ስዕለ መርቆሬዎስ፣ ተደራራቢ ጠፍር አልጋ፣ ልብሰሐዋርያት፣ ግብረ ሕማማት፣ የመጾር መስቀል፣ ነገረ ማርያም፣ ማህሌተ ጽጌ፣ ተዐምረ ማርያም፣ ድጓ፣ ግንዘት፣ ስንክሳር፣ ዐርባዕቱ ወንጌል፣ ታሪክ ነገሥት፣ መጽሐፈ ቅዳሴ፣ ተዐምረ ኢየሱስ እና የወርቅ ሚዛን ይገኙበታል፡፡ በእድሜ ጠገብ ጥዶች የተከበበ ይህንን ቤተመዘክር እና ቤተክርስትያኑን ለመጐብኘት ለኢትዮጵያዊ 10 ብር፣ ለውጭ ሀገር ዜጋ 50 ብር፣ ለቪዲዮ ካሜራ 75 ብር መክፈል የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ጐብኚዎች በርካታ ሆነው በመጡበት ጊዜ አንድም አስጐብኚ አልነበረም፡፡ በዚያ ምትክ የግቢው ጥበቃ ናቸው ገለፃ ሲያደርጉ የነበሩት፡፡ አስጐብኚ ተብለው የመጡት መነኩሴም አንዳንድ ማብራሪያዎቻቸው እርግጠኝነት የማይታይባቸውና በ”መሠለኝ” የተሞሉ ነበሩ፡፡

ለቅርሶቹ በቂ ጥገና ባለመደረጉም በተለይ ሕንፃዎቹና ፍርስራሾቹ ለበለጠ ጉዳት እየተጋለጡ ነው፡፡ ግቢው ተቆጣጣሪ ስለሌለውም በጀምስ ብሩስ መኖሪያ ቤት ፍርስራሽ ላይ በቀይ ቀለም “በአቶ አባተ መልኬ ፈረሰ” የሚልና ሌሎች አልባሌ ጽሑፎች የታሪክ መፈራረሱን እያፋጠኑት ይመስላሉ፡፡ በዚህ መልክ እየፈራረሱ ካሉት ቅርሶች መካከል የባልትና መምህርቷ እቴጌ ምንትዋብ ጥልፍ፣ ቅመማ፣ ወዘተ ማስተማርያ አንዱ ነው፡፡ ራሷ ቅድስት ቁስቋም ቤተክርስትያንም ተከታታይ ጥገና ካልተደረገላት ነገ የሚታይም ሆነ የሚነገር ታሪክ አይኖራትም፡፡ የ”ሽነዋ” አዳራሽ ጥገና ተጀምሮ እንደተቋረጠ በዐይን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እንዲህ የተጀመረ ጥገና መቋረጡና ጭራሽ ትኩረት አለመሰጠቱ አነጋጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ቤተክህነትና የከተማዋ አስተዳደር “የኔ ነው የኔ ነው” በሚል የባለቤትነት ውዝግብ የተነሳ እየተጐዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም የስብከተወንጌል ኃላፊ አባ ጽጌማርያም ጥበቡ፣የቤተክርስትያኑ ጣራ ክረምት ክረምት በማፍሰሱ በውስጡ ያሉ መቀደሻዎችና ሌሎች ቅርሶች ጉዳት እንዳገኛቸውና ያለከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ፈቃድ መጠገን እንደማይቻል እንዲሁም የአዳራሹን ጥገና እያካሄዱ ያሉ ሠራተኞች በቅጡ ባለመስራታቸው የበለጠ የቅርስ ጉዳት መኖሩን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የጐንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ ስለዚሁ ጠይቀናቸው፣ “ቅርሶቹ በተመሳሳይ ጊዜ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ቅድሚያ ሰጥተን የምንጠግናቸው አሉ፣ ቤተክህነቷም የምትጠግናቸው አሉ፡፡ በቤተክህነትና በአስተዳደራችን መካከል የጥቅም ግጭት የለም፡፡ ቁስቋም ማርያም ድረስ በጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገድና መፋሰሻ እየሰራን ነው፡፡” ብለውናል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 26 January 2013 16:09

ሐምሊን - የአዋላጆች ኮሌጅ...

“ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ” በአገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን የተመሰረተውም በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ኮሌጁ ተማሪዎችን በዲግሪ ደረጃ የሚያስመርቅ ሲሆን በማስተማር ሂደቱም ከፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስር ጋር በትብብር የሚሰራ ነው፡፡ ሐምሊን የአዋላጆች መማሪያ ኮሌጅ የተከፈተው እንደውጭው አቆጣጠር በ2007/ ዓ.ም ሲሆን እስከአሁን ባለው ሂደትም ከመቶ በላይ አዋላጆችን በዲግሪ ከፊሉን ያስመረቀ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ሲመሰረት አላማው አዋላጆች ለእያንዳንዱዋ ሴት ያስፈልጉዋታል የሚል ነው፡፡ ኮሌጁ ተማሪዎችን በምን መንገድ እንደሚቀበል እንዲሁም ቀጣይ የስራ ተግባሩ ምን ሊመስል እንደሚችል የኮሌጁ የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መላኩ ተድባበ አብራርተውልናል፡፡ ከአቶ መላኩ ማብራሪያ በማስቀደም የአንዲት ተማሪንና የኮሌጁን ኒውስ ሌተር ውይይት እናስነብባች ሁዋለን፡፡
***
“...ወደ ኮሌጁ የመጣሁት ከትግራይ መስተዳድር ከመቀሌ ማለትም ከአዲስ አበባ ወደ 780 ኪሎ ሜትር ርቀት ነው፡፡ እድሜዬም 19 አመት ነው፡፡ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርን ያጠናቀቅሁት ከመቀሌ 30 ኪሎ ሜትር ወጣ ባለች የገጠር ከተማ ነው፡፡ የመሰናዶ ትምህርን በመቀሌ ከተማ እንዳጠናቀቅሁ ወደ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ በ2012 ዓ.ም ለመግባት ችያለሁ”
ጥ/ ስለፌስቱላ የምታውቂው ወይንም ያየሸው ምን ልምድ አለሽ?
መ/ እኔ እራሴ የፌስቱላ ታማሚ ነበርኩ፡፡ ቤተሰቦቼ በግብርና የሚተዳደሩ ስለሆኑ እንደሀገሩ ልማድ በልጅነ ነው የተዳርኩት፡፡ ገና ሰውነ ሳይጠና በማርገዜ ልጅ ከመውለድ ጋር ተያይዞ በምጥ ምክንያት ችግሩ አጋጥሞኛል፡፡ ከዚያ በሁዋላም የ14/አመት ልጅ ሆኜም ወደመቀሌ ሄጄ ስለነበር የኤፍ ኤም ሬድዮ ስለፌስቱላ ሲናገር ስለሰማሁ እና በአካባቢው ሆስፒታሉ መኖሩንም ስለአወቅሁ ወደዚያ ሄጄ ታክሜአለሁ፡፡ አኔ መማር ብፈልግም ብዙ እንዳልማር የሚያደርጉኝ ችግሮች ገጥመውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በሕክምናው እና በሁዋላም ለመማር ባደረግሁት ጥረት የረዱኝን ሰዎች በጣም እያመሰገንኩ እነሆ ለውጤት በቅቻለሁ፡፡
ጥ/ በሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ለመማር በመብቃትሽ ምን ስሜት አለሽ?
መ/ እኔ የፌስቱላ ሕመም ማለት ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በየገጠሩ እንደእኔ ያሉ ሴት ሕጻናት ምን ያህል እንደሚሰቃዩ ሳስብ ይህንን ትምህርት መማሬና ችግሩ ወዳለበት አካባቢ በመሄድ ሴቶች ወደችግር እንዳይገቡ አስቀድሜ ለማዋለድ በመታደሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ከምረቃዬ በሁዋላ በገባሁት ቃል መሰረት ወደገጠሪቷ ኢትዮጵያ ተመድቤ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡
ምንጭ /The Hamlin College of Midwives/volume 1 issue 8/
***
ኢሶግ፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ለምን ተቋቋመ?
መላኩ፡ ኮሌጁ በዋነኛነት የተቋቋመበት ምክንያት የፌስቱላን ሕመም ለመከላከል ከሚያስችሉት ምክንያቶች ዋነኛው እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይል መውለድ መቻላቸው በመሆኑ ለዛ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በማስተማር ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ ነው፡፡ ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ይህንን ኮሌጅ እንዲከፈት ሲያደርግ .....አዋላጅ የህክምና ባለሙያዎች ለእያንዳንዱዋ ሴት..... በሚል መሪ ሀሳብ ነው፡፡ ብዙ ሴቶች በየገጠሩ በተለያዩ ምክንያቶች በሰለጠነ ሰው መውለድ ባለመቻላቸው ምክንያት ከ4/ ቀን ላላነሰ ጊዜ በምጥ ስለሚሰቃዩ እና ገላቸው ባለመጠንከሩ ምክንያት በማህጸን አካባቢያቸው የሰውነት መቀደድ ስለሚደርስባቸው ፌስቱላ ለተባለው የከፋ ሕመም ይጋለጣሉ፡፡ ስለዚህ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምሩቃንን ለሕብረተሰቡ በማቅረብ በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ ማድረግ ዋነኛ አላማው ነው፡፡
ኢሶግ፡ የተማሪዎች ቅበላ ስርአቱ ምን ይመስላል?
መላኩ፡ ኮሌጁ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም እንደውጭው አቆጣጠር ከ2007/ ጀምሮ
በተለይም ለፌስቱላ ሕመም የተጋለጡ አካባቢዎችን በማስቀደም ተማሪዎችን እየተቀበለ በዲግሪ ያስመርቃል፡፡
ተማሪዎቹ እንደሌላው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኮሌጁን የመግቢያ መስፈርት እንዲያሙዋሉ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ኮሌጁ የሚያወጣውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ የሚቀበላቸው ተማሪዎች በሙያው ለመስራት ፈቃደኞች የሆኑትን፣ በተለይም ተመልምለው ወደመጡበት የገጠር ክፍል ተመልሰው ለመስራት የሚፈርሙትንና ቃል የሚገቡትን ይመርጣል፡፡ ምናልባትም የመሰናዶ ትምህርትን አጠናቀው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የሚገቡት ተማሪዎችና ወደ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ከሚገቡት ተማሪዎች የሚለዩት በተጠቀሱት መመዘኛዎች ነው፡፡
ኢሶግ፡ ተማሪዎቹ በጾታ ይለያሉ?
መላኩ፡ ተማሪዎቹ በሙሉ ሴቶች ናቸውምክንያቱም በአብዛኛው እናቶች ችግራቸውን ሙሉ በሙሉ ገልጸው ለመናገር ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ይመርጣሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለሙያዎቹም ሴቶች ቢሆኑ የችግሩን ምንነት ለመረዳት ይበልጡኑ ቅርብ ይሆናሉ የሚል ግምት አለ፡፡ ተማሪዎቹ ከተመረቁ በሁዋላ የሚሰሩት በገጠሪቱዋ አካባቢ በመሆኑም በአካባቢው ላሉ አባወራዎችም ስሜት ከወንዶቹ ይልቅ ሴቶቹ እናቶቹን ቢያዋልዱ እንደሚመርጡም አንዳንድ ማሳያዎች አሉ፡፡ ወደ ኮሌጁ ስንመለስ የተሰራው የመኖሪያ አካባቢ ወንድና ሴትን በተለያየ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የማይመች ስለሆነ ተማሪዎቹ ሴቶች ብቻ እንዲሆኑ ተወሰነ፡፡
ኢሶግ፡ ምሩቃኑ ወደ ስራቸው የሚሰማሩት በምን ሁኔታ ነው?
መላኩ፡ ከመንግስት ጋር የትብብር ስምምነት አለ፡፡ ኮሌጁ ቢያስተምርም ወደስራ የሚመድባቸው
መንግስት ነው፡፡ ቀጣሪያቸው እና ደመወዝ የሚከፍላቸው መንግስት ነው፡፡ በማንኛውም ረገድ በመንግስት ሕግ የሚተዳደሩ ሰራተኞች ናቸው፡፡ በእርግጥ ለስራ ሲመደቡ ችግሩ ወደባሰበት እና ወደታወቁ አካባቢዎች ማለትም ምሩቃኑ ወደመጡበት አካባቢ እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡
በገቡት ቃል መሰረት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚገደዱት ለተወሰነ ጊዜ ሲሆን ይህንን ግዴታ ሳይፈጽሙ ተግባራቸውን ቢያቋርጡ ግን በስምምነቱ መሰረት ዶክመንታቸው የሚያዝባቸው ሲሆን በተጨማሪም ለትምህርታቸው የወጣውን ዋጋ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡
ኢሶግ፡ ተማሪዎቹ ከተመረቁ በሁዋላ በምን ሁኔታ ስራቸውን እንደሚያከናውኑ የሚታወቅበት የክትትል ዘዴ አለ?
መላኩ፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ የተማሪዎችን ምልመላና ምደባ እንዲሁም የስራ ሁኔታ የሚከታተል አንድ ክፍል አለው፡፡ ተማሪዎችን ከአራቱ መስተዳድሮች ትግራይ ፣ኦሮሚያ ፣ደቡብ እና አምሀራ ከመጡ በሁዋላ ወደትምህርቱ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ተምረው ከተመረቁ በሁዋላ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን የወር፣ የሶስት ወር እና የስድስት ወር እንዲሁም አመታዊ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምሩቃኑ የኮሌጁን አርማ ለብሰው በሚሰሩበት የገጠር አካባቢ ላሉ የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን ስለምናደርግና እጥረት የሚኖርበት ሁኔታ ካለ የማሟላት ስራ ስለምንሰራ ባለሙያዎቹ የት ነወ ያሉት ብቻ ሳይሆን ምን እየሰሩ ነው ? የሚለውንም ጭምር ኮሌጁ ያውቃል፡፡
ኢሶግ፡ የሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ግብ ምንድነው?
መላኩ፡ ግቡ ፌስቱላን መከላከል ብሎም ማስቆም ነው፡፡ እንደውጭው አቆጣጠር 2015 ዓ/ም ድረስም 50/ ሚድዋይፎችን በ25/የጤና ጣቢያዎች ማሰማራት ከመነሻው የተጠቀሰ ግብ ነው፡፡ እንደስራው አካሄድ ግን እስከአሁን በተደረገው የስልጠና ሂደት በአራቱ መስተዳድሮች ወደ 34/አዋላጆች ተመድበው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አሁኑ ወቅት ከሰባ ያላነሱ ተማሪዎች በኮሌጁ ሙያውን በመቅሰም ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለሙያዎቹ በየመስተዳድሩ በተመረጡ ባለሙያዎችን መመደብ ብቻ ሳይሆን አምቡላንስም በማቅረብ ከእነርሱ አቅም በላይ የሆነ ችግር ሲፈጠር እናቶች ከፍ ወዳለ ሕክምና እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ አምቡላንሶቹ ክረምት ከበጋ ታካሚዎችን በነጻ በማመላለስ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ ከህብረተሰቡም ምስጋን ይደርሳቸዋል፡፡ ስለዚህ ፌስቱላን ለመከላከል በተነደፈው እቅድ መሰረት ኮሌጁ በመስራት ላይ ያለው ስራ እናቶች ለፌስቱላ እንዳይጋለጡ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎአል ብለን እናምናለን፡፡

Published in ላንተና ላንቺ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ክስተቱ ታሪካዊ መስሏል፡፡ ገና በጅምሩ የብሔራዊ ቡድኑ ተሳታፊነት በአስደናቂ ሁኔታዎች እና ድባቦች የታጀበ ሆኗል፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ በተለይ በጆሃንስበርግና የምድብ 3 ጨዋታዎች በሚደረጉባት ሬልስፕሪት አረንጔዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን በመልበስ፣ ፀጉራቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን በመቀባት፣ የብሔራዊ ቡድኑን ዋልያዎችና የአገሪቱን ባንዲራ ያጀቡ አልባሳትን በተለያዩ ዲዛይኖች ሠርተው ለገበያ በማቅረብና በመልበስ ከፍተኛ ድምቀት ፈጥረዋል፡፡
ውድድሩ ከሳምንት በፊት ጆሃንስበርግ በሚገኘው የሶከር ሲቲ ስታድዬም በአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችው ኬፕቨርዴ መካከል ሲጀመር ስታድዬም በገቡ ኢትዮጵያውያን ውድድሩ ድምቀት ተላብሷል፡፡
በሶከር ሊቲ ስታድዬም የተለያዩ ክፍሎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማልያ የለበሱና ያነገቡ ኢትዮጵያውያን ብዛት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡
ከኢትዮጵያና ከዛምቢያ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አምበሎች እዚያው ቦምቤላ ስታድዬም መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የነበረው አጠቃላይ ድባብ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ1 እኩል ውጤት ቢደመደምም ዛምቢያ እንዳሸነፈች ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች ነበር የተቆጠረው፡፡ ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ለአምበሉ አዳነ ግርማ ከተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን የዛምቢያና የናይጀሪያ ጋዜጠኞችም ይገኙበታል፡፡ ከ10 በላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በታደሙበት መግለጫ ላይ አንድ ሁለት ጋዜጠኞች የኢትዮጵያ አሰልጣኝ እና አምበሉ ተሰናብተው የተቃራኒ ቡድን አሰልጣኞች መግለጫ ሲሰጡ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ልክ እንደ ጆሴ ሞውሪንሆ ከጋዜጠኞቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አስገራሚና አጭር አረፍተነገሮች በመጠቀም ምላሽ መስጠት ችለዋል፡፡
አሰልጣኙ ስለቀጣዩ ተጋጣሚዎች ምን እንደሚያስቡ ለአሰልጣኙ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ለተቃራኒ ቡድን ጠንካራ ግምት ይዘው እንደሚገቡ ገልፀዋል፡፡ በስታድዬሙ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ቩቩዜላ እና የውሃ መጠጫ ላስቲኮች ለምን ወረወሩ ሲባልም ደጋፊዎቹ እኛን በመቃወም ያን ተግባር አልፈፀሙም ብለዋል፡፡
በመግለጫው የኢትዮጵያ አሰልጣኝና አምበል ማብራሪያ ሲያበቃ እዚያ ለነበርን የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሁለት ነገር ገርሞን ነበር፡፡ የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል አዳነ ግርማ የአማርኛ ማብራሪያ በእንግሊዝኛ ትርጉም የሰጡት የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብቃት ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፕሬስ አታሼ የሆኑት የፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በመግለጫው አብረው መድረኩ ላይ ቢገኙም የአዳነ ግርማን የአማርኛ ማብራሪያ አለመተርጐማቸው ነበር፡፡ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ አሰልጣኝና አምበል መግለጫቸውን ጨርሰው ሲሄዱ እኝህ የፕሬስ አታሼ ቀጣዩን የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና አምበል መግለጫ እንደመከታተል እሳቸውም አብረው ውልቅ አሉ፡፡ የሚያናድደው እኝህ የፕሬስ አታሼ የዛምቢያው አሰልጣኝ ሄሮሼ ሬናልድ፡፡

“ብሔራዊ ቡድኑ ሩብ ፍፃሜ ይገባል”
ስለሺ ይማም
ደቡብ አፍሪካ ከገባሁ ስምንት ዓመት ሆኖኛል፡፡ የተወለድኩት በአዲስ አበባ አሮጌ ቄራ አካባቢ ነው፡፡ ትምህርቴን እስከ 9ኛ ክፍል ተምርያለሁ፡፡ ሙያ አልነበረኝም፤ አዘውትሬ ኳስ እጫወት ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ በንግድ ስራ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ ጐን ለጐን በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ የእግር ኳስ እንቅስቃሴዎች ብዙ እንሳተፋለን፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኦሎምፒክ ማጣርያ እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ጋር በተገናኘ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብና በማስተባበር ብዙ ስራዎችን አከናውነናል፡፡
ዋና አላማችን ብሔራዊ ቡድኖቻችን ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ጨዋታዎቻቸው ተመልካች እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ከ29ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ከራሳችን ወጭ አድርገን እንዲሁም ከህዝብም አሰባስበን በጆሃንስበርግና በየክፍለሀገሩ ፖስተሮችን በመለጠፍ፣ በራሪ ወረቀቶቼን በመበተንና ተንቀሳቅሰናል፡፡ ገንዘብ የሌላቸውንም እየደገፍን ኳሱን እንዲከታተሉ አስችለናል፡፡
ማንኛውም ተግባራችን ከፖለቲካ ጋር አይገናኝም፣ አይያያዝም፡፡ የምንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች በደቡብ አፍሪካ ብለን ነው፡፡ በምድብ 3 ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር በኔልስፕሪት ላደረገችው ጨዋታ እያንዳንዳቸው ከ60 በላይ ተመልካቾች የሚይዙ 11 አውቶብሶችን በማስተባበር 400 ኪ.ሜ ተጉዘን ብሔራዊ ቡድኑን ደግፈናል፡፡
ከ7ሺ በላይ ትኬቶችን ሸጠናል፡፡ በኔልስፕሪት በሚገኘው የሞምቤላ ስታድዬም የኢትዮጵያን ጨዋታ ለመከታተል ስታድዬም የገባው ህዝብ ብዛት በጣም ይገርማል፡፡ የኢትዮጵያ ጊዜ መምጣቱን እያስመሰከሩ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን ማንንም መፎካከር የሚችል ሆኗል፡፡ በደጋፊዎች፣ በተጨዋቾች ብቃትም አስተማማኝ ሆኗል፡፡ በእርግኛነት ሩብ ፍፃሜ እንገባለን፡፡
በእርግጠኛነት ስምንት ውስጥ እንገባለን፡፡
ምንተስኖት ደስታ (አቡሽ)
የትውልድ ስፍራዬ የጌድዮ ዞን ዋና ከተማ ዲላ ናት፡፡ የብሔራዊ ቡድናችን አጥቂ ጌታነህ ከበደ የዲላ ልጅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመጣሁ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፡፡
ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርቴን በማጠናቀቅ ዲፕሎማዬን አግኝቻለሁ፡፡
ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣሁበት ምክንያት በዚህ ከሚኖሩ ቤተሰቦቼ ጋር ለመስራት ነው፡፡ ቤተሰቦቼ በደቡብ አፍሪካ ከ11 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ አሁን በቤተሰቦቼ የንግድ ሱቅ እየሠራሁ ነኝ፡፡ ቤተሰቤ ባለ 5 ፎቅ ህንፃ አለው፡፡ ህንፃውንም አስተዳድራለሁ፡፡
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ከገመትኩት በላይ ሆኖብኛል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ቡድኑ ሲጫወት በሜዳው የሚወዳደር ይመስላል፡፡ ይህ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ያው እንግዲህ ኢትዮጵያኖች በጣም እግር ኳስ እንወዳለን፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት ሁላችንም ሰርፕራይዝ ሆነናል፡፡ በእርግጠኝነት ሩብ ፍፃሜ እንገባለን፡፡ እኛ የምንሰራበት አካባቢ “ታውን” ይባላል፡፡ በዚያ የሚሠሩ የደቡብ አፍሪካ፣ የናይጀሪያ፣ የማሊ ዜጐች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እጅግ ተደንቀዋል፡፡ ስለአፍሪካ ዋንጫው ስናወራ በሩጫ ብቻ የሚያውቋት ኢትዮጵያ በእግር ኳስም ምርጥ መሆኗን መገንዘባቸው አስገርሟቸዋል፡፡
አብረውን ከሚሠሩት የናይጀሪያ ዜጐች ጋር ስናወራ ለኢትዮጵያ የናይጀሪያ ቡድን ከባድ እንደሚሆንበት ነግረውናል፡፡ ሩብ ፍጻሜ እንደምንገባም ራሳቸው ነግረውናል፡፡ዳዊት ሰለሞን (ግራኝ)
የትውልዴ ስፍራ ኮልፌ ቀበሌ 11 ነው፡፡ በተለምዶ ጅማ ሰፈር የሚባለው አካባቢ ኳስ ተጨዋች ነበርኩ፡፡ የጀመርኩት በባንክ “ቢ” አንድ ዓመት፤ መብራት ኃይል አንድ “ቢ” አንድ ዓመት ፣ በኦሜድላ ዋና ቡድን እና በሊያ፣ (አንዋር ያሲን በነበሩበት ጊዜ) ገብቼ ለአንድ ዓመት ተጫውቻለሁ፡፡ ከባንክ “ቢ” የወጣሁት በበጀት ምክንያት ክለቡ ሲፈርስ ነበር፡፡
ከዚያ መብራት ኃይል ሄጄ በመጨረሻም ኦሜድላ ገባሁ፡፡
ባንኮች በኦሜድላ አንድ ዓመት እንደተጫወትኩ ባንኮች እኛ ያሳደግነው ልጅ ነው ብለው ወደ ክለቡ መለሱኝ፡፡ ያኔ የባንክ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ አሸናፊ በቀለ ነበር፡፡ በባንኮች ክለብ ለአምስት ዓመት ተጫወትኩ፡፡
ሁለገብ ተጨዋች ነበርኩ፡፡ በተለይ ግን ግራ ተመላላሽ እና አማካይ ስፍራ ላይ እሰለፍ ነበር፡፡ ከባንኮች በኋላ አየር መንገድ ለአንድ ዓመት፣ ከዚያ በኋላ በጉና እና በትራንስ ክለቦች እያንዳንዳቸው ለሁለት ዓመት ተጫወትኩ፡፡ ከዚያ ኳሴን አቆምኩ እና የአሰልጣኝነት ኮርስ ወሰድኩ፡፡ በትምህርቱም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የክብር ተመራቂ ሆንኩ፡፡ “ሮሃ ራይዚንግ” የተባለ እና የጐዳና ተዳዳሪ ልጆችን በእግር ኳስ የሚያሳትፍ ፕሮጀክት አቋቁሜ በአሰልጣኝ ታምሬ ተፈራ (ፑፒ) አማካኝነት ከአንድ ዓመት በላይ ሠራን፡፡ እግር ኳስ መጫወት ያቆምኩት በዕድሜ ምክንያት አልነበረም፡፡ ከክለብ ተገቢውን መልቀቂያ ላገኝ ባለመቻሌ ነው፡፡
የፕሮጀክቱን ስራ በድንገት አቆምኩት፡፡ ምክንያቱም ወደ ደቡብ አፍሪካ መጥቼ ከዚያም ወደ አሜሪካ ለመሄድ ነበር፡፡ እዚህ በነበረኝ ቆይታ ኑሮን ለማሸነፍ መስራት ስለነበረብኝ ወደ ንግድ ስራ ገባሁ፡፡
ላለፉት ሰባት ዓመታት የንግድ ስራውን ሳከናውን ቆይቻለሁ፡፡ እግር ኳሱን ደግሞ በትርፍ ሰዓት ኤደን ቪል የሚባል የሶከር አካዳሚ ባለቤት የሆነ ብራዚላዊ ጋር እያሰለጠንኩ ሰራሁ፡፡ እድሜያቸው ከ10-12 የሆኑ የብዙ አገር ዜጐች ህፃናትን ለአንድ ዓመት አሰልጥኛለሁ፡፡
ደቡብ አፍሪካ ገብቼ ሦስት ዓመት ከኖርኩ በኋላ የልጅነት ጓደኛዬ (ሃና ቀፀላ ትባላለች) ወደአለሁበት እንድትመጣ አደረግሁ፡፡
ከዚያ ትዳር መሰረትን፣ ቤተሰብ ጀመርን፡፡ አንድ ልጅ አፈራን፡፡ ቅዱስ ይባላል፡፡ የተወለደው ደግሞ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫን ባዘጋጀችበት ዓመት የመክፈቻው ዕለት ነበር፡፡
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጠበቅሁት በላይ ብቃት አሳይቷል፡፡ የብቃታቸው ምስክርና ቁልፍ የተጨዋቾቹ በስነልቦና ከፍተኛ ጥንካሬ ማሳየታቸው ነው፡፡ እኔ ባሳለፍኩት የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ የነበረው ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ቢሆንም ግብ የማስቆጠር ብቃቱ ላይ ደካማ ነበር፡፡ ውጭ ወጥቶ ተሸንፎ ነው የሚመጣው፡፡
ጐል አያገባም፣ ሀገር ውስጥ ሲጫወት ያሸንፋል ግን 1ለ0 ነው፡፡ ይህ አጥቂዎቹ ከተቃራኒ ቡድኖች ጋር ተጋፍጦና ጐል አስቆጥሮ የመጫወት ብቃት እንደሌላቸው የሚያመለክት ነበር፡፡
አሁን ያሉት ልጆች ግን ሀገር ውስጥ ከ2 እና ከ3 በላይ ጐል ያገባሉ፡፡ ከአገር ውጭም ውጤት የሚቀይር ጐል አግብተው ይመላለሳሉ፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ ለውጥ ነው፡፡
በእኔ ግምት የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ሩብ ፍፃሜ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ለዚህ ደረጃ መብቃትና በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ኢትዮጵያ መታየቷ፣ ለመጭው ትውልድ አፍሪካ ዋንጫ መግባትን ሳይሆን ዋንጫ መብላትን እንዲያልሙ ያደርጋቸዋል፡፡

መልክአ፣ ኢትዮጵያ ፪

አሁንም ከአትላንታ ጆርጅያ አልወጣኹም፡፡ ባለፈው ሣምንት ጽሑፌን ለዛሬ ያቆየኹት በራቁት ዳንስ ቤት (Strip Club) ውስጥ በአግራሞት ስለተመለከትኋት ሐበሻዊ - መልክ - ራቁት - ደናሽ ልተርክላችኹ ቀጠሮ ይዤ ነበርና ከዚያው ልቀጥልላችኹ፡፡ ዓርብ እና ቅዳሜ የአሜሪካኖቹ የመዝናኛ ዕለታት ናቸው፡፡ ማታ ወጥቶ መዝናናት የሚያሰኘው ካለ ዓርብ እስኪመጣ መጠበቅ ግዴታው ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ባሉት ቀናት ወደ ምሽት መዝናኛ ቤቶች ጐራ ማለት የብርዳም (ቁራጭ) ምሽቶች ሰለባ ያደርጋል። መዝናኛ ቤቶቹ ዐይነታቸው ለየቅል ነው። የአትላንታ ምሽት ቤቶችም እንደ ሌሎቹ የአሜሪካ ከተሞች ሁሉ ዓርብን መስለዋል። መኪና ማቆሚያዎች በተሽከርካሪዎች፣ መግቢያ በሮች ደግሞ በሰው ተጨናንቀዋል። በከተማው ይገኛሉ ሲባል ከሰማኋቸው ራቁት ዳንስ ቤቶች ሁሉ እኔ አሁን ያለሁበትን መርጫለኹ፡፡ ሐበሻዊ መልክ ያላት ደናሽ በዚህ ቤት ትገኛለችና፡፡ ቀናት በፈጀ ልመና ቦታውን ሊያስጐበኙኝ ፈቃደኛ ሆነው ያካሄዱኝ ሦስት ወንድ ጓደኞቼ ዓርብ እና ቅዳሜ ተመራጭ ቀናት መሆናቸውን በመጠቆም ይዘውኝ የወጡት በአንዱ ዓርብ ነው፡፡ ከቦታው ደረስን፡፡

ከፊት ለፊታችን በተንጣለለው የመኪና ማቆሚያ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መኪኖች ተደርድረዋል። ዙሪያ ገባውን በተደረገ ፍለጋ እንደምንም አንድ ማቆሚያ ተገኘ፡፡ መኪናችንን ግራና ቀኙን ጠብቆ ያለምንም ስሕተት ለማቆም የሁሉም ሰው ርዳታ አስፈልጐ ነበር፡፡ ቀድመው ቦታ ይዘው በቆሙት መኪኖች ላይ ጭረት ማሳረፍ በቀላሉ የሚታለፍ ጥፋት አይደለም፡፡ በፊልም እና በማስታወቂያ የማውቃቸው የዓለም ውድ ሞዴል መኪኖች በመኪና ማቆሚያው ከተደረደሩት መካከል ቀላል የማይባለውን ቁጥር ይዘዋል፡፡ የቤቱ መለዮ የኾነው ማስታወቂያ ከሩቅ ይጣራል፡፡ በዐሥራ አምስት ደረጃዎች ከፍታ በተሠራ የቪላ ቤት ቅርጽ ግዙፍ ቤት አናት ላይ “Pink Pony” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎበታል፡፡ በታላላቅ ፊደላት የተቀረጸ ሲሆን ሮዝ መልክ ባለው መብራት ያሸበረቀ ነው፡፡ በሁለቱ ቃላት መካከል ፊቷን ያዞረች ራቁት ደናሽ ሴት ምስል ተጣምሮ ተሰቅሏል። ወደ መግቢያው ስንጠጋ ሁለት ሙሉ ጥቁር የፖሊስ ልብስ የለበሱ ነጭ ጠባቂዎች ዙሪያቸውን መሣሪያ ታጥቀው ወደ ዳንስ ቤቱ የሚገቡት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች አለመሆኑን መታወቂያ እያገላበጡ በማየት የይለፍ ምልክት ይሰጣሉ። ተራችንን ጠብቀን የይለፍ ማኅተሙን እጃችን ላይ ካስመታን በኋላ ተራ በተራ ፍተሻችንን እያጠናቀቅን የመግቢያ ክፍያ ወደሚከፈልበት ቦታ ሄድን፡፡

ለአንድ ሰው መግቢያ 15 ዶላር ይከፈል ነበርና ለአራታችን ለመክፈል ወደ ሒሳብ ተቀባዩዋ ስንጠጋ፣ ወደኋላ ቀርቶ የነበረው ታክሲ አሽከርካሪ ጓደኛችን ለሒሳብ ተቀባዩዋ የሆነ ምልክት አሳያት፤ የገባት አልመሰለኝም፤ ምን እንደሚል ደግማ ጠየቀችው፡፡ ባለታክሲ መሆኑንና ደንበኞችን ይዞ መምጣቱን ጠቆማት፡፡ “ገባኝ” በሚል ስሜት እየተፍለቀለቀች የኛን ወስዳ የሱን መለሰችልን፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለታክሲዎች ደንበኛ ይዘው ወደዚህ ቤት ከመጡ መግቢያ ሳይከፍሉ ገብተው ይታደማሉ ወይም ደግሞ ኮሚሽን ይቀበላሉ፡፡ በአሜሪካ ከአምስት ኢትዮጵያውያን ጋር የመገናኘት ዕድል ቢገጥማችሁ አንዱ ባለታክሲ መሆኑ ግድ ነውና እዚህ ቤትም አብረውኝ ከመጡት ጓደኞቼ አንዱ ባለታክሲ ነው፡፡ እንዲህ ላለው የከተማ ወሬ ከእነሱ የቀረበ ስለማይኖር ጥያቄዬን ለሱው መወርወር ጀመርኹ፡፡ “የዳንስ ቤቱ ጠባቂዎች ይህን ሁሉ ሽጉጥ የታጠቁት ለምንድነው?” ስል ጠየቅኹት፡፡ “የትኞቹ? በር ላይ ያለፍናቸው ነው? ፖሊሶች ናቸዋ” አለኝ፡፡ እንደገና ወደኋላ ተመልሼ መታወቂያቸውን መጠየቅ አማረኝ። በራቁት ዳንስ ቤት መግቢያ በር ላይ ፖሊሶች ቆመው በትጋት ይቆጣጠራሉ። “ለዐቅመ አዳምና ሔዋን የደረሳችሁ እንደፍጥራጥራችሁ” በሚል ስሜት ወደ ውስጥ ያሳልፋሉ፡፡ የቆረጥነውን ትኬት ሁለተኛው በር ላይ ላገኘነው ተቆጣጣሪ ሰጥተን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ በሩ ወለል ብሎ ሲከፈት ድፍረቴ ጥሎኝ ጠፋ፡፡ ሰውነቴ በላብ ተዘፈቀ፡፡ ከወደፊት ይልቅ ወደኋላ የመመለስ ፍላጐቴ ጨመረ፡፡ የደም ግፊት እንዳለበት ሰው የጭንቅላቴን የኋለኛ ክፍል ጨምድዶ ያዘኝ። በድንጋጤ ክው ብዬ ቀረኹ፡፡ ወድጄ እና ፈቅጄ የመጣሁ ሳይሆን የሆነ ሰው በሲዖል ደጃፍ አምጥቶ የጣለኝ መሰለኝ፡፡

ዐይኔ ለጊዜው ማስተዋል የቻለው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እጅግ ሰፊ በሆነው ዳንስ ቤት ውስጥ ርቃናቸውን የሆኑ በርካታ ሴቶች ይርመሰመሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ውስጥ በጐበኘኋቸው “ስም ያወጡ” ራቁት ዳንስ ቤቶች ውስጥ የተመለከትኋቸው ኢትዮጵያውያን እንስቶች “በስንት ጣዕማቸው?” አሰኘኝ፡፡ ጡታቸውን እና ሃፍረተ -ገላቸውን በእራፊ ጨርቅም ቢሆን ሸፈን ያደርጉታል፡፡ ያኔ ይህን ቢዝነስ ሠለጠኑ ከተባሉት አገሮች ቀድተው አዲስ አበባ ያመጡትን የዳንስ ቤት ባለቤቶች ረግሜያቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ለእራፊ ጨርቃቸውም ቢሆን አመሰገንኋቸው፡፡ ያጋነንኹ ካልመሰላችሁ እውነቱን ልንገራችኹ፡፡ ከቆምኹበት ብንቀሳቀስ የምወድቅ ስለመሰለኝ አንገቴን ወደ መሬት ቀብሬ ትንሽ ትንፋሽ ወሰድኹ፡፡ ጐትቼ ያመጣኋቸው ወዳጆቼ ወኔ ሲከዳኝ ሲያዩኝ ተሣሣቁብኝ፡፡ ከፊል እርቃኗን የኾነች አስተናጋጅ ፊቷን እንደ ጸዳል አብርታ በሚያብረቀርቅ ፈገግታ “ቁጥራችሁን ንገሩኝና ቦታ ልስጣችሁ?” ስትል ጠየቀች። ባይሆን ከለል ያለ ቦታ እንዳለ ለማየት እንደምንም ተጣጥሬ ቀና አልኹ፡፡ የቤቱ ስፋት በአንድ ጊዜ ይህን ለመቃኘት አያስችልም፡፡ ቀና ማለቴ ከፈራኋቸው ራቁት ሰውነቶች ጋር መልሶ አገጣጠመኝ፡፡ “የቱ ጋር እንቀመጥ?” በሚል ጠያቂ አስተያየት ሁሉም ወደ እኔ ተመለከቱ “ያስመጣሽን አንቺ ነሽ፤ እንግዲህ ተወጪው ይመስልባቸዋል፡፡ ከለል ያለ ቦታ ካገኘን ብዬ ከእነድንጋጤዬ ጠየቅኋቸው፡፡

ባለታክሲው ወዳጄ “ለዚች ልብሽ ነው እንዴ?” ሲል በድንጋጤዬ ላይ አላገጠብኝ፡፡ በቤተኝነት ስሜትም ከቤቱ መግቢያ በር በስተቀኝ በኩል ካለው የመጠጥ መሸጫ ክብ ባንኮኒ ላይ እንድንቀመጥ ወደዚያው ወሰደን፡፡ በዙሪያ ገባው ምን እየተከናወነ እንደሆነ የማየት አቅም ለጊዜው ስላጣሁ ዐይኔን በክቡ ባንኮኒ ውስጥ ቆመው መጠጥ በሚሸጡት ሴት እና ወንዶች ላይ ተከልኹ፡፡ አማራጭ ማጣት ኾኖብኝ እንጂ እኒህም የሚታዩ ሆነው አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ በውስጥ ሱሪ እና በጡት ማስያዣያ፣ ከፊሎቹ አጭር ቁምጣ በተጣበቀ አላባሽ፣ ከሰውነታቸው ከፊሉን አራቁተው ለማሻሻጫነት የቆሙ ናቸው፡፡ የአዲስ አበቦቹን “ከፊል ራቁት ደናሾች” ከእራፊው ጨርቅ በመለስ ያለውን ገላቸውን አጋልጠው ለሽያጭ በማቅረብ በቀጫጭን ብረቶች ታግዘው፣ ሰውነታቸውን ከወሲብ ቀስቃሽ ሙዚቃ ጋር አዋሕደው እየተገለባበጡ የሽልማት ገንዘብ ሲሰበስቡ ሳይ “አይ ድህነት አያደርገው የለ” ስል ለእንስቶቹ ሆዴ ተላውሶላቸው ነበር፡፡ በርካቶች ሥራ ፍለጋ በሚሰደዱባት የዓለም ቁንጮ በሆነችው ሀገረ አሜሪካ፣ ገላቸውን ለሽያጭ ላቀረቡት ወጣት እንስቶችስ “አይ የእንጀራ ነገር” ስል ደረቴን ልድቃላቸው ይሆን? ጉዳዩ የእንጀራ አይመስልም፤ እናም ደረት የመድቃቱ ነገር አስፈላጊ አልመሰለኝም፡፡ ቀስ እያልኹ የቤቱን መብራት እና ድምፅ ተላመድኹት፡፡ አቀማመጤን አስተካክዬም ሰረቅ እያደረግሁ ቀረብ ካሉት “የገላ ነጋዴዎች” ቅኝቴን ጀመርኹ። የቤቱ አጠቃላይ ስፋት በግምት ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እጅግ ሰፊ ወጥ አዳራሽ ነው፤ ግን ደግሞ በተለያየ መንገድ ተከፋፍሏል፡፡ አራት መዓዝን ቅርጽ ያላቸው ሰፋፊ የመጠጥ መሸጫ ባንኮኒዎች፣ በርካታ የመደነሻ መድረኮች አሉት፡፡

ነጭ እና ጥቁር ቀለም ያላቸው ሴቶች ተራ በተራ ወደ መድረኩ እየመጡ የዕርቃን ትርኢት ያሳያሉ፤ ጨርሰው ሲወርዱም ግብዣ ያቀረበላቸውን ሰው ይዘው በአንደኛው የቤቱ ኮርነር በርከት ብለው ወደተደረደሩትና የመኝታ ያህል ተለጥጠው የሶፋ መቀመጫዎች ይዘው እየሄዱ ሥራቸውን በግል ይቀጥላሉ። ልዩ ክፍያ የሚከፍል ደግሞ ሴቶቹን ወደውስጠኛው ክፍል ይዞ እንዲገባ ይፈቀድለታል፡፡ “እዚህ ቤት ግን በርግጥ ኢትዮጵያውያን ይመጣሉ?” - ቀደም ሲል የሰማሁትን መረጃ ተጠራጥሬ እንደገና ለማረጋገጥ ለባለታክሲው ያቀረብኹለት ጥያቄ ነው፡፡ በርግጥ ጥያቄው የሞኝ ይመስላል፡፡ በአዲስ አበባዎቹ የምሽት ዳንስ ቤቶች ውስጥ ተገኝተው በአዳጊ እንስቶች የውስጥ ሱሪ ገንዘብ እየጨመሩ የሚዝናኑ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያ ምድር አይቼ እንዲህ በዘመነች አገር የኢትዮጵያ ልጆች ታዳሚ መሆናቸውን መጠየቅ በርግጥ “ሞኝነት” ነው፡፡ ግን ደግሞ የቤቱን አስነዋሪነት ስመለከት በዚህ ቦታ የሀገሬ ልጆች ተሳታፊም ታዳሚም ናቸው መባሉን አምኖ መቀበል ከባድ ኾነብኝ፡፡ መብሰክሰኬ ብዙም ሳይቆይ ከጓደኞቼ የአሻግረሽ ተመልከቺ የቀስታ ጥቆማ ደረሰኝ። በቀላሉ አልታይ አለኝ፡፡ ከተቀመጥኹበት ረጅሙ የባንኮኒ ወንበር ተንጠራርቼ ዐይኔን አሻገርኹ፡፡ ከፍ ካሉት የመደነሻ መድረኮች ዝቅ ብለው ከተደረደሩት መቀመጫዎች ላይ አንዲት ሴት እና ሁለት ወንዶች ተቀምጠው እንቅስቃሴውን ፈዘው ያስተውላሉ፡፡ በመጠጥ ጭምር እየተዝናኑም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ያየኋቸው ከርቀት ቢሆንም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መለየት አላስቸገረኝም፡፡ ባያውቁኝ ባላውቃቸውም እዚያ ቦታ ቁጭ ብዬ በሌላ የሀገሬ ሰው በመታየቴ ብቻ ሃፍረት ተሰምቶኝ ለመደበቅ ሞከርኹ፡፡ እነርሱ እኔ የተሰማኝ ስሜት የተሰማቸው አልመሰለኝም፡፡ ማንም በዚያ ቦታ ቢኖር ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡ እንደ ውጭ አገር ዜጐቹ ሁሉ እነርሱም ተራ በተራ እየተነሡ ዶላር ይሸልማሉ፡፡

በቃል ያልተመለሰው ጥያቄዬ በተግባር ተመለሰልኝ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በዚያ ቤት ነበሩ፡፡ ባለታክሲው ወዳጄም፤ “የኛ አገር ልጆች በብዛት የዚህ ቤት ደንበኛ አይደሉም። አልፎ አልፎ የእኔ ቢጤ ባለታክሲ ደንበኛ ይዞ ይመጣል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ እንዳንቺ እንግዳ እና አዲስ ሰው ከሀገር ቤት ሲመጣ አሳዩኝ ይልና ለማየት ይመጣል፡፡ ግን ከአንድ ቀን በላይ እዚህ ቤት የሚመጣ ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ነው፡፡ አንዳንዱ እዚህ በመምጣቱ ብቻ ራሱን እንደረከሰ ሰው ቆጥሮ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ጠበል ይጠመቃል አትላንታ ካለው ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ቁጥር የሚይዙ ሰዎች ግን የቤቱ ደንበኞች ናቸው፡፡እንዲህ ያለ ቤት ስለመኖሩ የማያውቁ ደግሞ በርካቶች ናቸው፤” አለኝ። የቤቱን ታዳሚዎች ኹኔታ በግምታዊ አኅዝ ለማስቀመጥ 300 በሚሆኑ እንግዶች መካከል ከ70 በላይ የሚሆኑ እርቃን ሴቶች ይርመሰመሳሉ፡፡ ከእኔ ጥያቄ እና ከባለታክሲው ወዳጄ መልስ ውጪ በመካከላችን ጸጥታ ሰፍኗል፡፡ ሁለቱ አገጫቸውን እጃቸው ላይ አስደግፈው ጸጥ ብለዋል፤ ተፋፍረዋልም፡፡ እውነት ነው፤ እንዲህ ያለውን ነገር አንድ ላይ ኾኖ መመልከት በራሱ ያስተፋፍራል፡፡ በቤቱ እንደምትሠራ የተነገረኝ አበሻዊ መልክ ያላት ደናሽ አለመምጣት ካሰለቸኝ ከአንድ ሰዓት በኋላ “መጣችልሽ፣ መጣችልሽ!” አለኝ ባለታክሲው ወዳጄ፡፡ ክንፍ ያለኝ ይመስል አኮበኮብኹ፤ ልጅቱን ፍለጋ አንገቴን አንቀዠቀዠኹት፡፡ መካከል ላይ ወዳለው መድረክ የምታመራ፣ ያማረ ተክለሰውነት ወዳላት ወጣት አሳየኝ፡፡ ወደ መድረኩ እየሄደች ስለሆነ ፊቷን ማየት አልቻልኹም፡፡ የሚታየኝ ጀርባዋ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እንዳየኋቸው ሴቶች ከእራፊ በላይ በሆነ ጨርቅ ሰውነቷን ሸፍናለች፡፡ ጡቶቿን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ጡት ማስያዣ እና ሣሣ ያለም ቢሆን ታፋዋ ድረስ የሚሸፍን ቁምጣ መሰል ነገር ለብሳለች፡፡ ትልቅ ተረከዝ ያለው ቡትስ ጫማም ተጫምታለች፡፡ መድረኩን አስቀድማ ስትደንስበት ከነበረችው ባለነጭ ገላ ሴት ተረክባ የተከፈተላትን የሙዚቃ ምት ተከትላ፣ ቀስ እያለች ወደ መድረኩ ወጣች። ዙሪያውን ከበው የተቀመጡት ታዳሚዎች የቀደመችውን በጭብጨባ ሸኝተው እሷንም በጭብጨባ ተቀበሉ፡፡ የእኔ ዐይን እንዳፈጠጠ ነው፡፡ ጭንቅላቷ በአርተፊሻል፣ ፀጉር ቢሸፈንም መልኳ ሐበሻዊ መሆኑን ለመለየት ነጋሪ አላስፈለገኝም፡፡ በዝግታ የጀመረችውን ዳንስ እያፈጠነችው መጣች፡፡ ሰውነቷ በከፊል የተሸፈነ መሆኑን ስመለከት፣ ምናልባት አንዳች ማኅበረሰባዊ ሞራል በጥቂቱም ቢሆን ተጭኗት ሊሆን ይችላል ስል ጠረጠርኩኹ፤ ግን ደግሞ በቤቱ ውስጥ ከደናሾቹ እንደ አንዷ ኾና መድረክ ላይ ከወጣች በኋላ፣ ሰውነትን በእራፊ ጨርቅ መሸፈኑ ትርጉም አልባ ሆነብኝ፡፡ መጀመሪያውኑ ተወልቆ የተጣለ ነገር ነውና። ልጅቱ እንቅስቃሴዋን ቀጥላለች፡፡

ከመድረኩ ጀምረው ወደላይ የቤቱን አናት እንደምሰሶ ደግፈው የያዙትንና ለዚሁ አገልግሎት ተብለው የተዘጋጁትን ቀጫጭን ብረቶች እየተጠቀመች ስሜትን ለወሲብ በሚቀሰቅስ እንቅስቃሴ ለደቂቃዎች ስትናጥ ቆየች፡፡ ቀጠለችና አንዱን ብረት በአንድ እጇ እንደያዘች የአንድ እግር ጫማዋን አወለቀች፤ አስከትላም ሁለተኛውን ደገመች። በመድረኩ የጽዳት እና የዶላር ሽልማት ሰብሳቢ ሠራተኛ አማካኝነት የወለቀው ጫማ ተነሣ፡፡ ዳንሱ በባዶ እግር ቀጠለ፡፡ ቆየት ብላ የጡት ማስያዣዋን ፈታ ጥላ ከወገቧ በላይ እርቃኗን ሆነች፡፡ “ኦ! አምላኬ! የፈጣሪን ስም ጠራሁ። ሸላሚዎች ተነሡ፡፡ መጠኑ ስንት እንደሆነ መለየት ባልችልም ዶላር ይዘንብላት ገባ፡፡ ቆየት ብዬ እንደተረዳሁት ከቤቱ ደንበኞች ውስጥ ከዐሥር እስከ 100 ዶላር የሚሰጡ ባይጠፉም አብዛኛው ደንበኛ ግን ዘርዝሮ ይዞ አጠገባቸው ይቆምና በተለያየ ስልት እየስደነሰ ዶላሩ አምስት እና ዐሥር ላይ ሲደርስ ቦታው ሄዶ ይቀመጣል፡፡ በቤቱ ውስጥ ራቁት ደናሾቹ በመድረኩ ላይ እያሉ እያዩ ከማስደነስ ውጪ ቀርቦ መንካት የተከለከለ ነው፡፡ ልጅቷ ዳንሷንም እራፊ ጨርቋንም ከሰውነቷ ላይ እያነሣች መጣል ቀጥላለች፡፡ ሥሡን ቁምጣዋን አውልቃ ጥላ በውስጥ ሱሪ ብቻ ቀርታለች፡፡እየተዟዟረች ሽልማቷን ትሰበስባለች፡፡ አዲስ አበባ ላይ ደናሾቹን ባገኘሁ ጊዜ ዳንሱን ሥራ ብለው የያዙት አማራጭ ከማጣት ተነሥተው እንደሆነ አንጀት በሚበላ የችግር ታሪካቸው አዋዝተው ተርከውልኝ ነበር፡፡

በተለይ አንዲት 18 ዓመት በቅጡ የማይሞላት አዳጊ፤ “በትምህርቴ ብዙም ሳልገፋ እናት እና አባቴ ሁለት ታናናሾች ጥለውብኝ ሞተው እነሱን አስተምራለሁ፡፡ የምንኖረው በቀበሌ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ረኀብ እና ጥማት ተራ በተራ እየተፈራረቀ ችግር የቤታችን አባል ቢሆንብኝ አንዷን ጐረቤት ተከትዬ ገላዬን ለመሸጥ ጐዳና ወጣሁ፤ ጓደኛዬ እዚህ የመቀጠር ዕድል ሲቀናት ለእኔ ደግሞ መንገዱን አሳየችኝ፤ ከመራብ ገላን መሸጥ፣ ገላን ከመሸጥ ደግሞ አሳይቶ ገንዘብ ማግኘት አይሻልም?” ስትልም ጠይቃኝ ነበር፡፡ ያን ጊዜ “መራብ ይሻላል” እንዳልላት እሷ ሥራውን የመረጠችው መራብ ባስከተለባት መዘዝ እንደሆነ ነግራኛለች። መራብ የሚያመጣውን መዘዝ ደግሞ ምን እንደሚያስታውሰን አላውቀውምና ዝም አልኋት፡፡ የጀመርሽው መንገድ የተሻለ ነው እንዳልል ደግሞ ድርጊቱ አስነውሮኛል። እናም ያኔ ከንፈሬን በሐዘኔታ መጥጬ በደንብ ዝም አልኳት፡፡ ይቺኛዋን ግን ምን ልበላት፡፡ እኔ እሷን እያየሁ ሐሳቤን ሳነሣ ስጥል፣ እርሷ ልብሷን ጥላ ጨርሳ በመጨረሻም እርቃን ገላዋን፣ መለመላዋን ቀርታለች፡፡ አሁን እኔም ኢትዮጵያዊ እንዳትሆን አጥብቄ ተመኘሁ። ይኼኔ እኮ እንዲህ ሆና የምታገኘውን ዶላር ከምትልክላቸው ቤተሰቦቿ ውስጥ አንዱ ወንድሟ እየፈነጨበት ይሆናል ስል አሰብኹ፡፡ የተቀመጡትም የቆሙትም ወንዶቹ በራቁት ገላዋ አፋቸውን ከፍተዋል፡፡ በዛ ሰዓት የሚደንሰው ራቁት ሰውነት የእርሷ ብቻ አልነበረም፡፡ በርካቶች ሥራ ያሉትን እርቃን ዳንስ ተያይዘውታል፡፡

ምን ያህል ሰዓት መድረክ ላይ እንደቆየች ለማስተዋል ባልችልም ሲበቃት ወረደች፡፡ መጨረሻዋን ለማየት በዓይኔ ተከተልኳት፡፡ እንደ ባልደረቦቿ እሷም የመድረኩን ካበቃች በኋላ የግሏን ጀመረች። ተጠርታ መሰለኝ ከወንዶች ጋር ተቀምጣ ስታያት ወደ ነበረች ወጣት ፈረንጅ ሴት ሄዳ ትደንስላት ጀመረች። የዳንሱ እንቅስቃሴ መተሻሸትንም ይጨምር ነበር፡፡ ሲላት ደግሞ ትቀመጥበታለች። ልጅቷን ከዛ በላይ ተከታትሎ መመልከት ለእኔ ሕመም ሆነብኝ፡፡ እንደምንም ብዬ ላነጋግራት ሞከርኩ፡፡ በጉዳዩ ላይ ከወዳጆቼ ጋር ተወያየሁ፡፡ ለማነጋገር ያለው አንድ አማራጭ ለዳንስ መጋበዝ ብቻ ሆኖ ተገኘ። ማነው የሚጋብዘው? ደፋር ከመካከላችን ጠፋ፡፡ እንደምንም ለትንሽ ደቂቃ ብዬ ባለታክሲውን አግባባሁት፡፡ በአንዷ አስተናጋጅ አማካይነት ጥሪ ተላለፈላት፡፡ ቆየት ብላ በውስጥ ሱሪ እና በጡት ማስያዣ መጣች፡፡ ቁርጥ ሐበሻ። እንደመጣች ባለታክሲውን እየተሻሸች መደነስ ጀመረች፡፡ ከየት እንደመጣች ለማወቅ በአማርኛ ሰላምታ ሰጠኋት። በማውቃቸው ጥቂት ትግርኛ ቋንቋ ሞከርኋት፡፡ አሁንም ዝም አለች፡፡ ባለታክሲው እየቀፈፈው መጣ፤ ሊታገሠኝ አልቻለም፡፡ ለመገፍተር የዳዳው ይመስላል። ሰላምታውን በፈረንጅ ቋንቋ አደረግሁና “የሀገሬ ልጅ መስለሽኝ ነው” አልኋት፡፡ ዳንሷን ሳታቋርጥ “የት ነው ሀገርሽ?” አለች። “ኢትዮጵያ”፣ አንገቷን በማወዛወዝ ምላሽ ሰጠችኝ፡፡ እኔ ከዛ አይደለሁም ማለቷ ነበር፡፡ “ከአሥመራ?” አሁንም አንገቷን አወዛወዘች፡፡ “መልክሽ ግን የኛን አገር ሰው ይመስላል” አልኋት፤ ዝም ብላ መወዛወዟን ቀጠለች፡፡ “ይውለቅልህ” ለባለታክሲው ጥያቄ አቀረበችለት፡፡ ያችኑ እራፊ ጨርቋን ልታወልቅ መሆኑ ነው፡፡ “አልፈልግም፤ አልፈልግም” አለና ተቻኩሎ ከኪሱ ካወጣቸው ዶላሮች መካከል አምስት ዶላር ሰጣት አሜሪካን ሀገር ባለታክሲን ከሌላው ሰው ለየት የሚያርገው በርካታ ዝርዝር ዶላሮች በኪሱ መያዙ ነው፡፡

እንደ ሌላው ሰው በየማሽኑ ላይ ካርድ ሲጭር አይውልም። “ዐሥር ዶላር ነው” ስትል አምስት ዶላር ጭማሪ ጠየቀችው፤ እንዲያቆያት በዐይኔ ብለማመነውም ፈቃደኛ አልሆነም። ዐሥር ዶላር ጨመረላትና እንድትሄድለት “አመሰግናለሁ” አላት፡፡ ምስጋናውን በፈረንጅ ቋንቋ ነበር ያቀረበላት፡፡ እሷም ዶላሩን ተቀብላው “አመሰግናለሁ” አለችው። መልሱ ግን በአማርኛ እንጂ በፈረንጅኛ አልነበረም።ሁለታችንም በድንጋጤ “እንዴ?” የሚል ቃል አወጣን፡፡ እኔማ ከተቀመጥኹበት ተነሥቼ ይዤ ላስቀራት ምንም አልቀረኝም። ፈገግ ብላ “ያቐንየለይ” ስትል ምስጋናውን በትግርኛ ጨምራልን፣ አረማመዷን አፍጥና ግራ አጋብታን ወደመጣችበት ተመለሰች፡፡ ዳንስ ቤቱን ለማየት ከመሄዴ በፊት ስለሐበሻዊ መልኳ ደናሽ የነገሩኝ ኢትዮጵያውያን ልጅቷ ኤርትራዊ ስለመሆኗ ሳይጠራጠሩ ነበር ያወሩኝ፡፡ ኤርትራውያን ባገኘሁ ጊዜም ስለዚችው ልጅ ጠይቄያቸው ኢትዮጵያዊ ስለመሆኗ ነው ያወሩኝ፡፡ አብረውኝ የመጡት ልጆችም ልጅቱ ኤርትራዊ ስለመሆኗ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡ሁለቱም ከኛ ወገን አይደለችም ሲሉ፤ እዚያ እና እዚያ አሽቀንጥረው ሊጥሏት ይሞክራሉ፡፡ ዋናው ምክንያታቸው ደግሞ በድርጊቱ ማፈራቸው ነው፡፡ የልጅቷ ዜግነት የማወዛገቡ ሌላው ምክንያት ራሷ ልጅቷ መሆኗ ገባኝ። በሁለቱም ቋንቋ ትናገራለች፤ መልኳም የሐበሻ ነው፡፡ ለእኔ ግን መምጫዋ አላስጨነቀኝም፡፡ እሷ ከየትኛውም ትምጣ፤ ከሁለቱም ሀገር ቀያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች፤ ወይ በትምህርት፣ በፖለቲካ ጉዳይ አሊያም ሥራ ፍለጋ ነው፡፡ “እንጀራ ፍለጋ 15 ሺሕ ኪሎሜትር ተጉዞ ገላን በአደባባይ አራቁቶ ለሰፊ ሕዝብ መሸጥን ምን አመጣው?” አላናገረችኝም እንጂ ይህችንም እንደ አዲሳባዎቹ ልጠይቃት ያሰብኹት ጥያቄ ነበር፡፡

ምናልባትም “ከምራብ ብዬ” ነው ትለኝ ይሆናል፡፡ የሷ ግን እንደአዲሳባዎቹ መልስ አልባ አያደርግም፤ “ስንት እንጀራ ለመብላት ነው?” እላት ነበር፡፡ ለእኔ ሰቅጣጭ ከሆነብኝ ከዚህ ቤት ወጥተን ያመራነው ወደ ኢትዮጵያውያን ጭፈራ ቤት ነበር። መቼም “ከሺሻ እና ከዳንስ ቤት አትወጪም ወይ?” እንዳትሉኝ እኔ ያየሁት እንዳይቀርባችሁ ከሚል እሳቤ ነው!! ሌላ ሌላውንም ያየኹትን፣ የታዘብኹትን ያህል ቀስ እያልኹ አወጋችኋለሁ፡፡እናም በዚህ ጭፈራ ቤት በመጠጥ ተሟሙቀው፣ሲያሻቸው እየተሻሹ ሲላቸው እየተሳሳሙ፣ሲላቸው እየቆሙ፣ሲፈልጉ ደግሞ ተቀምጠው ሺሻቸውን እያጨሱ፤በጭሱ ደግሞ ታፍነው ልባቸው እስኪጠፋ በሀገራቸው ዘፈን እየጨፈሩ ያየኋቸው ጥንዶች እጅግ ጨዋ ሆነው ታዩኝ። የአስነዋሪ እና የአኩሪ ተግባር መለኪያው ጠፋብኝ፡፡ በአሜሪካ ቆይታዬ በአገሬ የማውቀውን የአስነዋሪ እና የአኩሪ ታሪክ መለኪያ ካጠፋብኝ ሌላው የጥቂት ኢትዮጵያውያን ተግባር አንዱ ደግሞ የግብረሰዶማውያን ነገር ነው፡፡ለአሜሪካኖቹ ሳይቀር አስጨናቂ በሆነው ግብረሰዶማዊነት ተዘፍቀው ያየኋቸውና ታሪካቸውን የሰማሁት ኢትዮጵያውያን እስካሁን አስጨንቀውኛል። ጎዳና የወጡ ኢትዮጵያውያንን ማየት እነዚህኞቹን እንደማየት አልከበደኝም፡፡ ግብረሰዶማዊነት በአሜሪካ መባባሱ እና ቀስ በቀስ በተለያዩ ግዛቶች ለጋብቻም እየተፈቀደ መሄዱ የኢትዮጵያንም ራስ ምታት ሆኗል። አንዲት እናት ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ልጇ “ማሚ ጓደኛዬን ላስተዋውቅሽ” ሲል በሰጣት ቀጠሮ ስላጋጠማት ነገር ያወጋችኝን ደግሞ እስቲ ልንገራችሁ። (ይቀጥላል)

Published in ባህል

በገና በዓል ዋዜማ ወደተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ባንክ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች … የሄዱ ሰዎች በዋናው መግቢያ በር ወይም በእንግዳ መቀበያ ክፍል ቀልባቸውን የሳበና በተለያየ አንፀባራቂ ነገሮች የተጌጠ የገና ዛፍ ስለማየታቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ወቅትን ጠብቀው የልብስ አሰቃቀላቸውን የሚያሳምሩት ቡቲኮችም የገና አባትን ልብስ ሰቅለው በብዛት ታይተዋል፡፡ በመስቀለኛ መንገዶች ቀይ መብራት ያስቆማቸው መኪኖች ስር እየተሽለኮለኩ “የአባባ ገና”ን ልብስ ለብለው ተመሳሳዩን ግዙን የሚሉ ወጣቶችም ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አልነበረም፡፡ ባለፈው ሳምንት ባየው ነገር የተገረመ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ትዝብቱን የገለፀው “አባባ ገና እማማ ገናን እየጨቆናት ነው” በሚል ነበር፡፡ ድንቅ ነው፣ ልዩ ነው፣ በሌሎች ዘንድ አይገኙም … የሚባሉትና ኢትዮጵያዊ መልክ ካላቸው የበዓል አከባበሮች መካከል አንዱ የገና በዓል ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች የሚታየው ጅማሬ መላ አገሪቱን ይወክላል ማለቱ ቢከብድም በመዲናችን እየታየ ያለው የገና በዓል አከባበር ግን “አባባ ገና” ያሳደረብን ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ጠቃሚ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ዛሬ የምናከብረው የጥምቀት በዓል አገራዊ የአከባበር መልክና ሥርዓቱን እንደያዘ አሁን ላይ ከመድረሱም ባሻገር በተለይ የብሔር ብሔረሰብ አልባሳትን በመልበስ ወጣቶች በማንነታቸው እንደሚኮሩ ማሳያ መድረክ እየሆነም መጥቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ እንደታየው በየጥምቀተ ባህሩ በተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ አልባሳትና የፀጉር አሰራር አጊጠው ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት እየፈጠሩ ያሉ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሚከበሩት በሁለቱ በዓላት ውስጥ የሚታየው እውነት በተቀላቀለ መስመር ላይ መሆናችንን ያሳያል፡፡ በአንድ በኩል በማንነት መኩራትና ማንነትን የማስጠበቅ ተግባር ሲታይ፤ በሌላ ጎን የራስን ጥሎ የሌላውን የማንሳት ፍላጎት ይንፀባረቃል፡፡ በተቀላቀሉት ነገሮች ውስጥ ባለው ትግል ማንኛው ያሸንፋል? አሸናፊው ምን ጠቃሚ ነገር ያስገኝልናል? የሚያስከትልብን ጉዳትስ ምንድነው? በትግሉ ተሸንፎ ከሚጠፋውስ ምን ጠቃሚና መልካም ነገርን እናጣለን? የሚሉ ጥያቄዎች ያስነሳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሰራውን ጥናት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ “መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም፤ በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ” በሚል ርዕስ በቀረበው ጥናት ላይ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት እንዲወያዩበት ተደርጓል፡፡ ጥር 3 ቀን 2005 ዓ.ም በራስ ሆቴል በተሰናዳው መድረክ ላይ የጥናቱ ባለቤትና በሥራው የተሳተፉ ባለሙያዎች ስለ ባህልና ልማድ ምንነት፤ መጤ ልማድና ባህሎች በማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚያስከትሉት አደጋ፤ለመጤ ድርጊቶች መስፋፋት ግሎባላይዜሽን፤መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ መረቦች ስላላቸው አስተዋጽኦ፤በተለያየ አተገባበር ተፈፃሚ የሚሆኑት መጤ ልማድና ባህሎች በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ እንዳለና ችግሩን ለመከላከል ያሉት ዕድልና አማራጮች ምን እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ማብራርያ ሰጥተውበታል፡፡

መጤ ባህልና ልማዶች በአዲስ አበባ ከተማ ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዙ ሱስ አስያዥ ዕፅ ተጠቃሚው መበራከቱን፣የቀንና የምሽት የራቁት ጭፈራ ቤቶች መብዛታቸውን፣ ግብረሰዶማዊነት መስፋፋቱን፣ “እኔን ይመቸኝ እንጂ ለሌላው ግድ የለኝም” የሚል የግለኝነት ስሜት እየጨመረ መምጣቱንና ሌሎች መሰል ችግሮች ዙሪያ ገለፃ ከተሰጠ በኋላ መድረኩ ለአስተያየትና ጥያቄ ክፍት ሆነ፡፡ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” የሚለውን ብሂል አስቀድመው አስተያየት መስጠት የጀመሩት የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ነበሩ፡፡ የግብረ ገብ ትምህርት መቋረጡ ለችግሮቹ መከሰት አንድ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ውብሸት፣ብዙ ዜጎቻችን የኤችአይቪ/ኤድስ ሰለባ ከሆኑ በኋላ ጥናቱ ተሰርቶ የቀረበው መንግሥት ወይም የሚመለከታቸው አካላት የት ከርመው ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ በጥናቱ ወረቀት የቀረበው ቀደም ብለን እንሰማው የነበረን ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣የነገ አገር ተረካቢ ወጣት ትውልድን ለመታደግ እንዲህ ዓይነት ጥናት፣ የተግባር እንቅስቃሴና እሳት የማጥፋት ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ናዝሬት፣ ሐዋሳ፣ ባህርዳርና በመሳሰሉት ከተሞችም በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡ “ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጥልን ማነው ብለን በተጨነቅንበት ሰዓት፤ የዘገየ ቢሆንም ይህ ጥናት መሰራቱ አስደሳች ነው” በማለት ንግግር የጀመረው ደግሞ ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ ነው፡፡ “ማርፈድን ባላበረታታም ከመቅረት ማርፈድ ይሻላል” እንደሚባለው ዘግይቶ የቀረበው ጥናት፣ ሕብረተሰባችን እየተፈራራ እንዲሄድ ያደረጉትን ችግሮች ይቀርፉለታል” በሚል ምሳሌዎችን ሲያቀርብ “ዛሬ ጋብቻ ለመመሥረት ፍርሐት ላይ ባንወድቅም ልጅ መውለድ ግን የብዙዎች ፍርሐት ሆኗል፡፡

በቀድሞ ዘመን ልጅን ለጎረቤት በአደራ ሰጥቶ የመሄድ መልካም ባህል ነበር፡፡ ዛሬ ልጄን ጠብቅልኝ ብሎ ለጎረቤት የሚሰጥ ሰው ካለ፣ልጄ ምንም ሳይሆን መልሼ አገኘሁ ይሆን? ከሚል ፍርሃትና ስጋት ጋር ነው፡፡” የመንግሥት መዋቅርና የልማት አካሄድ ሰውን ትኩረት ያደረገ አይመስልም ያለው ጋዜጠኛው፤ መገናኛ ብዙኃን የሕብረተሰቡን የእኔነት ስሜት ሲገድሉ ይታያል፡፡ ማንቼና አርሴ ለእኛ ሕብረተሰብ ምንድን ናቸው? ሲልም ጠይቋል፡፡ ሕብረተሰቡ ማንነቱን እንዲያጣ የከበቡት ችግሮች በጥናት ወረቀት ከቀረበውም በላይ ሰፊና ጥልቅ ነው ያለው ጋዜጠኛ በፍቃዱ፣ ተተርጉመው እየቀረቡልን ያሉት የፍልስፍና መፃሕፍት አስተሳሰባችንን እያናጉትና ብዙዎችን የትም ወድቀው እንዲቀሩ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡ የመፃሕፍት የፊት ገፅ ሽፋን የሴቶችን እርቃን ገላ የሚያሳይ መሆኑ፣ ስለ መሳሳም ጥበብ፤ ሴትን በፍቅር ስለማንበርከክ፤ የወንዶችን ትኩረት ስለመሳብ ችሎታ … በሚል የሚቀርቡት መፃሕፍትም የከበበን አደጋ አንዱ ማሳያ ናቸው ያለው ጋዜጠኛው፣ “ሕብረተሰቡ ይሄ የእኔ ጉዳይ አይደለም ብሎ ራሱን እስኪከላከል ድረስ የሚጠብቀው ያስፈልገዋል” ብሏል፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ተስፋዬ ማሞ በበኩሉ፣ በኑሮ አስገዳጅነት ብዙ ወላጆች በቀን ከ12 ሰዓት በላይ በሥራ ላይ ከመቆየታቸው ጋር በተያያዘ የወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የመገናኘት ዕድል እየጠበበ መምጣቱን የራሱን ገጠመኝ ሲያቀርብ “በሳምንቱ ውስጥ ልጆቼን የማገኝበት ጊዜ ስደምረው ከ20 ሰዓት እንዳማይበልጥ አስተውያለሁ” ካለ በኋላ ትውልዱ ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል፡፡

ካፒታሊዝም ሁሉንም ነገር እየሸጠ ሁሉንም ነገር የሚያጠፋ ሥርዓት ነው ያለው አቶ ተስፋዬ፣ በስመ ኢንተርናሽናል ሥም በከተማችን እየተስፋፉ የመጡት ትምህርት ቤቶች አንዱ የችግር ምንጭ ሆነዋል ብሏል፡፡ ለዚህ ችግር ከመንግሥት ባልተናነሰ ማህበራዊ ኃላፊነትን መሸከም የሚችል የኪነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ያስፈልጋል፡፡ ሕብረተሰብ ተለይቶ የማይታወቅ ነገር ስለሆነ የወላጆች ካውንስል በአገር አቀፍ ደረጃ በማቋቋም መንግሥት ሕጉ እያለ ማህበረሰቡን መከላከል ያልቻለበትን ምክንያት መሞገት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡ “የተበላሸው ነገር ብዙ ነው፡፡ ያልተበላሸው ነገራችንን ለማዳን ብንሰራ የሚል ሀሳብ አለኝ” ያለችው የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ የምወድሽ ስዩም በበኩሏ፣ በዚህ ዓላማ መሰረት እሷ የምትመራው ማህበር ስላከናወናቸው ተግባራት፤ በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይና ገጠመኞቿ ዙሪያ እርሷም በግሏ ስላከናወነቻቸው ተግባራት ማብራሪያ ከሰጠች በኋላ፣ ስለ ኒውዮርክ ያቀረበችው ምሳሌ እኛስ ወዴት እየሄድን ነው? የሚያስብል ነው፡፡ “ኒውዮርክ በዓለማችን ትንሿ የሲኦል ምሳሌ ናት፡፡ አገሪቱ እናትና ልጅ ባል የሚቀማሙባት በመሆኗ ክስተቱ የውይይት ርዕሰ ነገር ሆኖ በቶክ ሾው ይቀርባል፡፡ ባል ሴት ፍለጋ፣ ሚስት ወንድ ፍለጋ አገልግሎቱን ወደሚሰጡ ተቋማት በሄዱበት ይገናኛሉ፡፡ በእኛስ አገር አሁን የሚታየው ጅማሬ በዚያ ደረጃ አያድግም ወይ?” ብላለች - የምወድሽ፡፡ አርቲስት ፈለቀ ጣሴ በበኩሉ፣ “ከጥቂት ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶች ግቢ መኖሪያ ቤት ያላቸው ሰዎች ጠላ ንግድ መጀመራቸው አነጋጋሪ ነበር።

ዛሬ የዕፀ-ፋሪስ ተጠቃሚዎች መበራከት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የዛሬ 20 ዓመትም በአዲስ አበባ ከተማ የእርቃን ዳንስ ቤቶች ነበሩ፡፡ልዩነቱ አሁን ተበራክተዋል፡፡ በጥናት ከቀረበው በላይ የግል ሚዲያዎች በችግሩ ዙሪያ በስፋት ሰርተዋል፡፡ ከእናንተም በተሻለ እነሱ መረጃው አላቸው፡፡ ዕፀፋሪስ በመርፌ የሚወሰድባቸው አካባቢዎች አሉ። የእናንተ ጥናት ይህንን የደረሰበት አይመስልም፡፡ በጥናታችሁ የተቀመጠው የሱስ አስያዥ ስሞችና የመሸጫ ዋጋ አሁን በከተማው ካለው ጋር በጣም ይለያያል። ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ በተለያየ ጊዜ ሕግና መመሪያዎች ወጥተዋል። ሕጉ ግን ችግሩን ሲቀርፍ ሳይሆን ሕግ አስፈፃሚዎችን ሲጠቅም ነው የታየው” ብሏል፡፡ ከፊልም ሰሪዎች ማህበር የመጡት አቶ ደሳለኝ ኃይሉ፣የዓለም ኀያላን መንግሥታት ዛሬ በኢኮኖሚ ያልበለፀጉ አገራትን የሚወሩት እንደ ቀድሞ ዘመን ጦር በማዝመት ሳይሆን በቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆኑን እንደማሳያ ያቀረበው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መመልከት ትቶ ወደ ዲሽ ስርጭቶች ትኩረት ያደረገውን ሰው ብዛት በመጥቀስ ነው። ስለዚህ የመንግሥት ትኩረትም ሆነ ልማት ሰውን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ሲል አስተያየቱን አቅርቧል፡፡ ጥናቱን ያሰራውና መድረኩን ያሰናዳው ቢሮ፤ችግሮቹን ለመቅረፍ ከማንም በተሻለ የኪነጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ ሚናና ድርሻ ይኖራቸዋል በሚል እምነት መድረኩን ማሰናዳታቸውን በማጠቃለያቸው አስምረውበታል - አቶ ደሳለኝ፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ ስዩም “የተበላሸውን ለማስተካከል ያልተበላሸውን እንጠብቅ” እንዳለችው በእጅ ያለውን ወርቅ ማክበር በኋላ ከመቆጨት ያድናል፡፡ አባባ ገና ጭቆና የደረሰባት እማማ ገናን ነፃ ለማውጣት ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የአባባ ጥምቀት ጭቆና ያላረፈባት እማማ ጥምቀትን መጠበቅ ግን ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ በየጥምቀተ ባህሩ በብሔር ብሔረሰብ ልብሶቻቸው ተውበው የሚመጡትን ወጣቶች ማድነቅ ተገቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 26 January 2013 15:16

ኢቴቪ እና የአፍሪካ ዋንጫ

“በድብቅ አላስተላለፍኩም፤ በድርድር ላይ ነን” ኢቴቪ አለማየሁ አንበሴ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘውን 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በቀጥታ እያስተላለፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስርጭቱን በድብቅ ሲያስተላልፍ እንደነበረ በይፋ ከተነገረ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶችና ወቀሳዎች እየቀረቡበት ሲሆን ድርጅቱ በበኩሉ ጨዋታው እየተላለፈ ያለው በድብቅ አለመሆኑን እና እስከ አሁን ድረስ ድርድር እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዕለቱ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በድብቅ እያስተላለፈ መሆኑን በሚመለከት በቴሌቪዥን ስክሪኑ ላይ የተጻፈው እና በኳስ ተንታኞች የቀረበው ተደጋጋሚ ወቀሳ ድርድር ላይ ያለው ድርጅት አቋም ነው ወይስ የጋዜጠኛው የሚለውን እያጠራ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ኢቴቪ ውድድሩ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ከቴሌቪዥን ባለመብቱ ኩባንያ ጨዋታውን የማስተላለፍ መብት ለማግኘት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ መጠየቁን አስታውቆ የተጠየቀው ክፍያ ተገቢ አይደለም በሚል ራሱን ጨምሮ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መቃወማቸውንና በድርድር ላይ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለም ከመክፈቻ ሥነስርዓቱ ጀምሮ ሲያስተላልፍ ቆይቶ የኢትዮጵያና የዛምቢያ ጨዋታ በሚታይበት ወቅት የኢትዮጵያ ቡድን ጐል ማስቆጠሩን ተከትሎ ጨዋታው ይተላለፍበት የነበረው “አፌኔክስ” የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በስክሪኑ ላይ “ይህን ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ያለፍቃድ እያስተላለፈ ነው” የሚል የእንግሊዝኛ ጽሑፍ መልቀቁ ይታወቃል፡፡ ጽሑፉ ከተለቀቀ በኋላም በወቅቱ ጨዋታውን ሲዘግቡ የነበሩት ተንታኞች በተደጋጋሚ “ይህን ጨዋታ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያለፍቃድ እያስተላለፈ ነው፡፡ ምናልባትም በሕግ ሊጠየቅ ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ጣቢያው በሕግ መጠየቅ እና ቅጣትም እንዳለው እያወቀ ያለፍቃድ ማስተላለፉ ሳያንስ ፍቃድ በሌለውና ክፍያ ባልተፈፀመበት ፕሮግራም ላይ ስፖንሰር ሰብስቦ ማስተላለፍ ተገቢ አለመሆኑን አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ የቴሌቪዥን ተከታታዮች ተናግረዋል፡፡ የቴሌቪዥን ፍቃድ ሳያወጡና ግብር ሳያስከፍሉ ተጠቃሚ መሆን በሕግ ያስቀጣል እያለ ራሱ ለሕግ ተገዢ አለመሆኑ አሳፋሪ ነው” የሚሉ መልዕክቶችም በማኅበራዊ ድረገፆች ላይ ሲተላለፉ ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የመዝናኛና የስፖርት ዘርፍ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ፍቅር ይልቃል ስለተፈጠረው ሁኔታ ለአዲስ አድማስ ሲያብራሩ፤ የጨዋታውን በቴሌቪዥን የማስተላለፍ መብት ከገዛው መቀመጫውን ቤኒን ካደረገው “LC2-Lancia” ድርጅት ጋር የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት እየተደራደረ ቀደም ሲል የተከናወኑትን አምስት የአፍሪካ ዋንጫዎች በደንበኝነት አብረው ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ፍቅር ቀደም ሲል የነበሩትን ድርድሮች በማሳያነት ሲጠቅሱም፣ ከድርጅቱ ጋር ሲሠሩ በነበረበት ወቅት መጀመሪያ አካባቢ ድርጅታቸው ይከፍል የነበረው 50ሺሕ ዩሮ (1ሚ.200 ሺ ብር) ሲሆን መጨረሻ ላይ ደግሞ የከፈለው 75ሺህ ዩሮ (1ሚ.800ሺ ብር) ነበር፡፡ በዚኛው ጨዋታ ግን ቀደም ሲል ከነበሩት ከ10 እጥፍ በላይ በመጨመር 750 ሺህ ዩሮ እና የአየር ሰዓት ክፍያ 250 ሺህ ዩሮን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 1 ሚሊዮን ዩሮ (24ሚ.ብር) መጠየቁን አብራርተዋል፡፡ ዋጋው በዚህ መልኩ ሊጨምር የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል የግል አስተያየት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ፍቅር፤ ቀደም ካሉት ክፍያዎች በሚያስገርም ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት የድርድር ሂደቱ ሊራዘም እንደቻለ እና ጉዳዩ ዕልባት ሳያገኝ ጨዋታው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸውም መልዕክቱ እስከተላለፈበት ጊዜ ድረስ እና አሁንም ጭምር (በትናንትናው ዕለት) በድርድር ላይ መሆናቸውን፣ ወደ መስማማቱም እየተጠጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ጨዋታውም ከድርጅቱ ዕውቅና ውጪ በድብቅ ይተላለፍ የነበረ ባለመሆኑ ድርጅታቸው ላይ የሚደርስ የሕግ ተጠያቂነት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ድርጅታቸው እስከዛሬ ይካሄዱ የነበሩ 10 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን ሲያስተላልፍ ቆይቶ አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሰለፈበትን ጨዋታ ሳያስተላልፍ መቅረት የአድማጭ ተመልካቹን ፍላጎት አለማሟላት ነው ያሉት አቶ ፍቅር፤ እስከመጨረሻው ድረስ ተደራድረው ክፍያ በመፈፀም ኢቴቪ ጨዋታውን ማስተላለፉን እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 26 January 2013 15:13

“እንደ አቅሜ አኑረኝ…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ከጥቂት ወራት በፊት የሆነ ሠርግ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ…እንዲህ ለአብዛኛው ሰው ውሉ እየጠፋ ባለበት ዘመን ሰዎቹ ድንኳን ጥለው ከአቅማቸው በላይ ተጋባዥ ጠርተዋል፡፡ ሁለቱም የመንግሥት ደሞዝተኞች ናቸው፡፡ ታዲያላችሁ…ከዘመድም፣ ከቁጠባ ማህበርም በመከራ በተሰበሰበች ገንዘብ የተዘጋጀችው ምግብ ለግማሹ ሰው እንኳን ሳትዳረስ ማለቅ! እዛ ላይ ነገሩ ቢያልቅ ጥሩ ነበር፡ ግፋ ቢል “ምግብ አለ ብዬ ባዶ ሆዴን ሄጄ ጦሜን የሰደዱኝ እግዜሐር ይይላቸው…” ምናምን አይነት ነገር ቢኖር ነው፡፡ (እኔ የምለው…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ለምንድነው ሠርግ ምናምን በመሳሰለው ግብዣ በቂ ምግብ ያላገኘነውም፣ እምብርታችን እንትን እስኪል ‘የዋጥነውም’ እኩል “በእነሱ ቤት ጋብዝው ሞተዋል!” እያለ መሄዱ…በቃ ‘ኮምፐልሰሪ’ ሆነ ማለት ነው! እናላችሁ…በቆልቲ ጋብዛችሁ ወይም አሮስቶ ዲቢቴሎ… “ድንቄም ተጋበዘ!” መባል እንደማይቀርላችሁ እወቁማ!) እናላችሁ…ምግቡ ተሟጦ ሰዉ ፍጥጥ ሲል የወንድና የሴት ቤተሰብ ግርግር ፈጥረው ድንኳኑን ቀወጡት አሉ፡፡ ሙሽሮች በዓቨናቸው ዕንባ ግጥም ብሎ ነበር ተብሏል፡፡

እኔ የምለው መጀመሪያ ነገር…እዚሀ አገር በቃ አቅሚቲን የማወቅ ነገር ተረሳ ማለት ነው! ብዙ ነገሮች ላይ ከአገር ጀምሮ እስከ እኛ ተራዎቹ ድረስ…ሁላችንም አቅማችንን እየረሳን ነገርዬው ሁሉ እኮ ግራ የሚያጋባ እየሆነ ነው! ስሙኝማ…መአት መሥሪያ ቤቶች ዕቅዳቸውን ሲያሳውቁ ትሰሙልኛላችሁ አይደል… በዓመቱ መጀመሪያ ላይ… “በዚህ ዓመት ምርታችንን በመቶ ምናምን ፐርሰንት ለማሳደግ በጥናት የተደገፈ ዕቅድ ተይዟል…” ምናምን ይባላል፡፡ ድንገት የአንድ እርከን ዕድገት ወይም ቦነስ አገኛለሁ ብሎ የቋመጠ ሠራተኛ አዳራሹን በጭብጨባ ያናጋላችኋል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ እኛው መቶ ምናምን ፐርሰንት ያሉት ሰውዬ ተመልስው መድረክ ላይ ይወጣሉ፡፡ “በተለያዩ ምክንያቶች የዘንድሮው ዕድገት ቀደም ብሎ በዕቅድ ከተያዘው ሃያ ስምንት ፐርሰንት ሆኗል…” ምናምን ይሉላችኋል፡፡ እናላችሁ…የመጀመሪያው የመቶ መናምን ፐርሰንት ፉከራ ለዜና አመቺ ሆነና…“ይህን ያህል የምታሳደጉት በየትኛው አቅማችሁ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ ስሙኝማ…እዚህ አገር ምን የተለመደና ‘የማያስጠይቅ’ ነገርም አለ መሰላችሁ…ማጋነን! በሁሉ ነገር በዓለም ምናምነኛ የተለመደው እኮ ማንም ሰው “በምን ላይ ተመስርተህ ነው እንዲህ ልትል የቻልከው?” “የትኛው ተቋም ነው አጥንቶ እዚህ ላይ የደረሰው?” ምናምን ብሎ የሚጠይቅ ስሌለ አቅሚቲን ባይኖርም የተፈለገውን ነገር አደርጋለሁ ምናምን ማለት ይቻላል፡፡

በተለይ አንዲት ጫፏ የምትያዝ ነገር ከተገኝችማ…ምን አለፋችሁ… “ዓለም ሳይቀር ያደነቀው…” የምንላት ‘ስታንድ አፕ’ ኮሜዲ ከፊት ወይም ከኋላ ትገባለች፡፡ “ዓለም ሳይቀር ማድነቁን በምን አረጋገጥክ?” ተብሎ የመጠየቅ ስጋት ስሌለ የሌለንን አቅም “አለን” ማለት እንደ ሺሻ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሱስ እየሆነብን ነው፡፡ እናማ…ነገራችን ሁሉ “የእከሊት ልጅ ድል ባለ ሠርግ አግብታ የእኔ ልጅ ያለሠርግ የምትገባው ምን በወጣት!” እየተባለ ሦስተኛ ዲቪዥን ሆኖ “እንደ ፕሬሚየር ሊግ ካልሆንኩ ከምላሴ ጸጉር…” አይነት ነገሮች የብዙዎችን ጎጆ ወጪዎች ኑሮ እያናጉ ነው፡፡ ፍቺዎች በዙ ምናምን የሚባለው ነገር…አለ አይደል… ብዙ ጊዜ ችግሩ የጀመረው ገና የሠርጉ ጊዜ ይሆናል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሆሊዉድ ነው አሉ…እናላችሁ ሙሽርዬዋ የሆሊዉድ ተዋናይት ነች፡፡ እናማ…ሙሽራው ሆዬ ወደ እሷ እየሄደ ባለበት ጊዜ መንገዱ በመኪና ተጨናንቆ እንደልቡ መንቀሳቀስ ስላልቻለ አርፍዷል፡፡ ታዲያላችሁ…ሞባይል ደውሎ ምን አላት መሰላችሁ…ወዳንቺ እየመጣሁ መንገዱ በትራፊክ ተጨናንቆ ነው በሰዓቱ ያልደረስኩት፡፡ ብቻ አደራሽን… እስከደርስ ድረስ ሌላ ሰው አግብተሽ እንዳትጠበቂኝ…” ሆሊዉድ እንዲህ ነዋ! (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሙሽራው ባረፈደ ቁጥር ሙሽርዬዎቹ ሌላ ‘ቤንች ላይ’ የተቀመጠ ‘የሚያገቡ’ ቢሆን ኖሮ የአገራችን ‘እጩ ሙሽራ’ ሁሉ አጨብጭቦ ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር፡፡) አቅምን ያለማወቅ ነገር በዝቷላ! እናማ በአቅም መኖር እያቃተን ብዙ ነገራችን ውሉ እየጠፋ ነው፡፡ በየቡና ቤቱ እየተጋፋን መጠጥ ስንገለብጥ የምናመሸው አብዛኞቻችን…አለ አይደል… አቅሙ ኖሮን ሳይሆን ነገርዬው “ከማን አንሼ…” አይነት ነገር ነው፡፡

የምር… ከማን አንሼ ያፈረሰው ቤት ሩቡን ያህል እንኳን ‘ለልማት’ ተብሎ አልፈረሰም፡፡ እናማ…ያለ አቅም ‘የሚሞከሩ’ ሠርጎች አብዛኞቹ የዚሁ የ“ከማን አንሼ” ነገር ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሰውዬው ጓደኛውን ምን ይለዋል መሰላችሁ… “አንድ አምስት ሺህ ብር አንተ ጋ ታስቀምጥልኛለህ?” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም “ለምን?” ይለዋል፡፡ ምን ብሎ ይመልስላችኋል…“ገና ትናንት ነው ያገባሁት፡፡” ይሄኔ ጓደኝዬው… “ታዲያ ገንዘብህን ቤትህ ለምን አታስቀምጠውም?” ሲለው ጓደኝዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…“የማላውቃት ሴት እቤቴ ገብታማ አምኜ ገንዘቤን እቤቴ አላስቀምጥም!” ሠርጉ ላይ ተጠርቶ የመጣው ሰው ሁሉ በውሀ ጥም ጉሮሮው ደርቆ…አለ አይደል… “ለክርስትና እንመጣለን ገና…” የሚለው አሽሙር ስለሚመስል ይቅርልንማ፡፡ ልክ ነዋ… ሙሸሮቹ እንዴት እንደ ሠረጉ ብናውቅ ኖሮ እኮ ዘፈንዬው ተለውጦ “ለማጽናናት እንመጣለን ገና…” ምናምን የሚል አዲስ ሪሚክስ ይሆን ነበር፡፡ እናማ…በሠርጋቸው ማግስት ወደ እናቶቻቸው ሮጠው ስለሄዱ ሙሽሮች ሰምተናል፡፡ (እኔ የምለው… አንዳንድ ሙሽሮች ‘ትዋይላይት’ ላይ እንደምናያቸው ሰዎች ያደርጋቸዋል እንዴ! አሀ…“ለዘላለም ገባች” የተባለች፣ ሙሽርዬው “የጠቅላይ ተሰካልኝ” ያለላት እንትናዬ በማግስቱ እግሬ አውጪኝ ስትል ግራ ይገባናላ!) እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሰውየው ለሚስቱ ብዙም ፍቅር የለውም አሉ፡፡

እናላችሁ… አንድ ቀን ለጓደኛው “ሚስቴ እኮ ጥላኝ ጠፋች…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ… “እስቲ ትንሽ ቀን ጠብቃትና በዛው ከቀረች ብርችንችን ብለን እናከብረዋለን፡፡” ሌላው ሰውዬ ደግሞ ምን አለ… “ሚስቴ ጥዬህ እሄዳለሁ እያለች እየፎከረችብኝ ነው…” ብሎ ለጓደኝዬው ሲነግረው ጓደኝዬው ምን አለ መሰላችሁ…“ፉከራ አይደለም ጥዬህ እሄዳለሁ ብለሽ ቃል ግቢልኝ በላት…” ሰውዬው የእሱ ቤት ጭቅጭቅ ሰፍኖ የጓደኛው ቤት ሰላም መሆኑ ግርም ስለሚለው ይጠይቀዋል፡፡ “እንዴት ነው እኔ መከራዬን እያየሁ አንተ ቤት ሰላም የሆነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም ምን ብሎ ይመልሳል መሰላችሁ…“ሚስቴ የገንዘብ ሚኒስትር ነች፣ እናቷ የጦር ሚኒስትር ነች፣ ምግብ አብሳይ ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ነች…” ጓደኝየው በማብራሪያው ግራ ይገባውና “ታዲያ በዚህ መሀል አንተ ምንድነህ?” ሲል ይጠይቀዋል። ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“እኔ ግብር ከፋዩ ሰፊው ህዝብ ነኝ፡፡” ዓለም ላይ የለየለት አምባገነን ማን እንደሆነ ታውቃለህ ሲባል ምን አለ መሰላችሁ… “አንተ እንዴት አወቅህ… እኔ አይደለሁ እንዴ ያገባኋት!” አለና ቁጭ አለላችሁ፡፡ አስተማሪው ተማሪውን “አባትህ ሦስት መቶ ብር ቢኖረውና ግማሹን ለእናትህ ቢሰጣት እናትህ ምን ይሰማታል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“በድንጋጤ ልቧ ቀጥ ይላል፡፡” በድንጋጤ ልባችን ቀጥ ከማለት ያድነንማ! “እንደ አቅሜ አኑረኝ” ማለት ይልመድብንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 26 January 2013 15:06

ያልተገላገሉት ምጥ!

የእርግዝናዋን መጨረሻ ሣምንታት ያሣለፈችው በጭንቅ ነበር፡፡ የበላችው ምግብ አለመርጋት፣ ከፍተኛ ራስ ምታትና ከባድ የወገብ ህመም በእርግዝና መጠናቀቂያ ሣምንታት አካባቢ የገጠሟትና ለከፍተኛ ሥቃይ የዳረጓት በሽታዎች ነበሩ፡፡ እርግዝናዋን የምትከታተልበት ጤና ጣቢያ ውስጥ ያገኘቻት የጤና ባለሙያ ችግሩ በአብዛኛው በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ችግር መሆኑንና በሒደት እንደሚተዋት ስለነገረቻት፣ ህመሟን ችላ የምትወልድበትን ቀን መጠባበቅ ጀመረች፡ ይህ እርግዝና ከእሷ ፍላጐት ውጪ የተከሰተ በመሆኑ ደስተኛ አልነበረችም፡ቀደም ሲል የወለደቻቸው የስምንት፣ የሰባት፣ የአምስት፣ የሶስትና የአንድ ዓመት ከአራት ወር ዕድሜ ያላቸው ልጆቿ ለእሷ ቤተሰብ ከበቂ በላይ እንደሆኑ ታምናለች፡ ባለቤቷ መርካቶ ውስጥ በአንድ የልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ ተቀጥሮ የሚያገኘው ወርሃዊ ደመወዝ እነዚህን ልጆቿን እንኳን በአግባቡ ለማሣደግ እንዳላስቻላት ታውቃለች፡፡

በየወሩ እየጨመረ የሚሄደው የሸቀጦች ዋጋ ናላዋን ሲያዞራት፤ ከግለሰብ ተከራይተው የሚኖሩባት ሁለት ክፍል ቤት የኪራይ ዋጋ በየሶስት ወሩ እያደገ አቅሟ ከሚቋቋመው በላይ ሆኖባታል፡፡ አራት ወንድሞችና ሶስት እህቶች ያሉት ባለቤቷ፤ የልጆቹን ቁጥር የእሱ ወላጆች ከወለዷቸው ልጆች ቁጥር ማነስ እንደሌለበት በማመኑ፣ የባለቤቱን የወሊድ መከላከያ ልጀምር ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጐታል፡፡ “እያንዳንዱ ልጅ የራሱን እድል ይዞ ነው የሚወለደው” ባይ ነው - ባለቤቷ፡፡ በየዓመቱ ለመስቀል ወላጆቹን ለማየትና በዓሉን ለማክበር ወደ አገሩ ሲሄድ አዳዲስ ልጅ፣ አዳዲስ ፊት ለወላጆቹ ማሣየት ይፈልጋል፡፡ ቢያንስ ባለቤቱ እርጉዝ ሆና ቤተሰቦቹ እንዲያዩዋት ይመኛል፡፡ የባለቤቷ እናት /አማቷ/ ሴት ልጅ ሌጣ ትሆን ዘንድ አይገባም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ሆዷ ገፋ ብሎ ወይም ህፃን እያጠባች ካላዩ “ምነው ሥራ ፈታሽ … የሴት ሆድ እኮ ባዶ አያድርም” ይሏታል፡፡ የእነሱን ቃል ለማክበርና የባለቤቷን ፍላጐት ለማሟላት በዓመት በዓመት የወለደቻቸው አምስት ልጆቿ ለእሷ ከአቅሟ በላይ ናቸው፡፡

አሁን በሆዷ ይዛ ጭንቅ ውስጥ የገባችበት ልጅ ስድስተኛዋ መሆኑን የነገረቻት የጤና ጣቢያ ነርስ፣ የአለምን ችግር አልተረዳችላትም፡፡ “ይበልሽ የራስሽ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ልጅ በዚህ ዕድሜሽ መፈልፈልሽ ምን ይሁን ብለሽ ነው” ብላ ወሽመጧን በጥሳዋለች፡፡ በራሷ ፍላጐትና ምርጫ ያደረገችው ይመስል፡፡ ይህቺው የጤና ባለሙያ አለም ስለቤተሰቦቿ በተለይም ደግሞ ስለባለቤቷ በእሷ የወሊድ መከላከያ መጠቀም አለመጠቀም ላይ ያለውን አቋም የነገረቻትን ሰምታ ባለቤቷን ጠርታ ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልነበረም፡፡ ብቻ ለእርግዝና ክትትል ወደ ጤና ጣቢያው በሄደችባቸው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ሁሉ አለምን ታመናጭቃታለች፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍል ከተማ፣ በተለምዶ አንፎ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለዓመታት የኖረችው አለም፤ ወደዚህ ሠፈር የመጣችው የቤት ኪራይ ዋጋ ቅናሽ በመሆኑ ነበር፡፡ አለም ባንክ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ እሷ ወደምትኖርበት አንፎ ለመሄድ በእግር ከ40-50 ደቂቃ ይወስዳል፡፡ ስድስተኛ ልጇን እርጉዝ የሆነችው አለም፤ አንድ ሌሊት ለዘጠኝ ወራት ሲያስጨንቃት የኖረውን ፅንስ ትገላገል ዘንድ ምጧ መጣ፡፡ በቤቱ ውስጥ ከባለቤቷ፣ ከህፃናት ልጆቿና ለዓይን ህክምና ከገጠር ከመጡት የባለቤቷ እናት ሌላ ማንም አልነበረም፡፡የእናታቸው ድንገተኛ የሌሊት ጩኸት ከእንቅልፋቸው ያባነናቸው ህፃናት፣ ልጆቿ የተኛችበትን አልጋ ከበው በጭንቀት የምትወራጨውን እናታቸውን ያዩዋታል፡፡ አዲሱን የልጅ ልጃቸውን ለማየት የጓጉት የባለቤቷ እናት፤ ሰውነቷ በላብ ተነክሮ እንደእሣት የምትፋጀውን አለም ሆዷን በቫዝሊን ያሻሉ፡፡ ጭንቋ እየበዛ ሲሄድና የሰውነቷ ትኩሣት ሲጨምር ባለቤቷ ተደናገጠ፡፡

ከዚህ በፊት ከወለደቻቸው ልጆቿ መካከል አራቱን በቤት ውስጥ በሠላም ነበር የተገላገለችው፡፡ አምስተኛዋንና ትንሿን ልጇን ብቻ ነበር በኮልፌ ጤና ጣቢያ የተገላገለችው፡፡ ጐረቤቷ የነበሩ ሴቶች ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ለእርግዝና ክትትል ደብቀው ጤና ጣቢያ ወስደዋት ነበር እነዚሁ ሴቶች ህመሟና ጭንቋ ሲበረታ ወደ ሃኪም ዘንድ መሄድ እንዳለባት በመወትወታቸውና የእሷም ፍላጐት መሆኑ ሲበዛበት ባሏ ጤና ጣቢያ እንድትሄድ ፈቅዶ እዚያ ተገላገለች፡፡ ግን ሁሉንም ልጆቿን ስትወልድ እንዲህ እንደ አሁኑ አይነት ድካምና ላብ፣ እንዲሁም ትኩሣት ፈፅሞ አይቶባት አያውቅም፡፡ ባለቤቷ ተጨነቀ፡፡ ዓይኑ እያየ ቤት ውስጥ ከምትሞትበት ወደ ሃኪም ዘንድ ሊወስዳት መሆኑን ለእናቱ ነገራቸው፡፡ ምን ሲደረግ አሉ እናቱ፡፡ እኔ ስምንት ልጅ የወለድኩት ከቤቴ ነው፡፡ ምን ሆና ነው ሃኪም ዘንድ የምትወስዳት? አይደረግም! ብለው ተሟገቱት፡፡ ዓለም በደከመ ዓይኗ ለመነችው፡፡ የሚስቱ የጭንቅ ድረሱልኝ ጩኸት እንዲወስን አደረገው፡፡ ብድግ ብሎ ጐረቤቱ የሆነውን ባለጋሪ ሊቀሰቅሰው ሄደ፡፡ አንፎ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለከተማው እጅግ በቀረበና አለም ባንክ በተባለው ሰፈር አዋሳኝ ቢሆንም ትራንስፖርት የለውም፡፡ አለም ባንክ ከተባለው ሰፈር አንፎ ለመድረስ በ3 ብር የጋሪ ትራንስፖርት መሄድ የግድ ነው፡፡ መንገዱ ወጣ ገባና አስቸጋሪ በመሆኑ እንኳንስ በምጥ ጭንቅ የተያዘች ሴትን ቀርቶ እኔ ነኝ ያለ ጐበዝን ይፈትናል፡፡ ግን አማራጭ የለም፡፡ ጐረቤቷ ባለጋሪ ተጠርቶ መጣ፡፡ አስፋው ሚስቱን ከባለቤቱ ጋር ተጋግዞ ጋሪው ላይ ጫናትና ህፃናት ልጆቹን ለእናቱ አደራ ሰጥቶ ወደጤና ጣቢያው ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፡፡ ከአለም ባንክ ታክሲ ማዞሪያ ማለፍ ያልተፈቀደለት ባለጋሪ፤ እነ ዓለምን ለአንድ የኮንትራት ሚኒባስ አሣልፎ ሰጥቶ ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ ሌሊቱ ወደ ንጋቱ ተቃርቧል፡፡ ከዓለም ባንክ ኮልፌ ጤና ጣቢያ ለመድረስ ለሚኒባሱ 180 ብር ከፍለውታል፡፡ ጤና ጣቢያው ሲደርሱ ዓለም አቅሟም ድምጿም ደክሞ ነበር፡፡ በክሊኒኩ በራፍ ላይ ባገኘው አግዳሚ ወንበር ላይ ዓለምን አስተኝቶ ካርድ ለማውጣት ወደ ካርድ ክፍል ሄደ፡፡ ሠራተኛዋ አልነበረችም፡፡ ለደቂቃዎች ቆሞ ጠበቃት፡፡

ሠራተኛዋ መጥታ ካርድ ወጥቶ አለም ምርመራ ወደሚያደርግላት ሐኪም ዘንድ ለመቅረብ ከአንድ ሰዓት በላይ ጊዜ ወስዶባታል፡፡ የመረመራት ሃኪም ያለችበትን ሁኔታ ሲመለከት ደነገጠ፡፡ የደም ግፊቷ 190/240 ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ዓለም ልጇን በምጥ መገላገል እንደማትችል የተረዳው ሃኪም፤ በኦፕሬሽን መገላገል ትችል ዘንድ ወደ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ሪፈር አላት፡፡ጤና ጣቢያው የራሱ አምቡላንስ ቢኖረውም ዓለምን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ግን አልፈቀደም፡፡ ባለቤቷ በኮንትራት ታክሲ ዓለምን ይዞ ወደ ሆስፒታል በረረ፡፡ በመንገድ ግንባታ ሰበብ የፈራረሱና የተዘጉ መንገዶች፣ የተጨናነቀው የትራፊክ ፍሰት እንደልብ አላስኬድ ያለው ባለታክሲ፤ ጥቁር አንበሣ ሲደርስ ዓለም ትንፋሿ ፈፅሞ ደክሞ ነበር፡፡ በባሏ ሸክም ከታክሲ ላይ ወርዳ ስትሬቸር ላይ የተኛችው ነፍሰ ጡር እና በምጥ ጭንቅ ላይ የነበረችው እናት፤ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ውስጥ ምርመራ ሊያደርግላት በተዘጋጀው ሐኪም ዘንድ ስትደርስ እቅታዋን ዋጠቻት፡፡ እኩለ ሌሊት ላይ የጀመረው የዓለም የምጥ ጭንቅ እኩለ ቀን ከመድረሱ በፊት በሞት ተጠናቀቀ፡፡ አሣዛኟ እና ከ10 ዓመት በታች የሆኑ አምስት ልጆቿን በትና፣ የረባ ህክምና እንኳን ሣታገኝ በሆዷ እስከተሸከመችው ፅንስ ለዘለዓለሙ አንቀላፋች፡፡ የዚህችን አሣዛኝ እናት ታሪክ ያጫወተኝ ባለቤቷ አቶ አስፋው ዘርጋ ነበር፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ያረገዘችውን ፅንስ እንኳን ሣትገላገል በሞት ለተለየችው ባለቤቱ ሞት ምክንያት የሚያደርገው ወደ ሆስፒታል ይዟት ለመሄድ መሞከሩን ነው፡፡ እናቴ ያለችኝን ሰምቼ ቢሆን ኖሮ፣ ሚስቴ እዚሁ ቤቷ በሰላም ትገላገል ነበር፡፡ የእናቴን ቃል ረግጬ ይዣት ሄጄ በመንገድ መንገላታት ለሞት አበቃኋት ባይ ነው፡፡ ሐኪሞቹ ለሚስቱ ሞት መንስኤው ከፍተኛ የደም ግፊት እንደሆነና ገና ምጡ እንደጀመራት ህክምና ብታገኝና በኦፕሬሽን እንድትገላገል ቢደረግ ኖሮ፣ የእሷንም ሆነ የፅንሱን ህይወት ለማትረፍ ይቻል እንደነበር ነግረውታል፡፡

አሁን አስፋው እናታቸውን ያጡ አምስት ልጆችን የማሳደግ ከፍተኛ ሃላፊነት ወድቆበታል፡፡ ከምዕተ አመቱ ግቦች አንዱ የሆነውንና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሚዲያ ያለውን ሚና ለማጐልበት ታስቦ ሰሞኑን በጤና ጠበቃ ሚኒስቴር ለሚዲያ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ በነበረው አውደ ጥናት ላይ እንደተገለፀው፤ በአገራችን በየአመቱ 2.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ያረግዛሉ፡፡ ከእነዚህ ሴቶች መካከል በሰለጠነ ባለሙያ ማለትም በነርስ፣ በአዋላጅ ነርስ፣ በጤና መኮንን ወይም በሀኪም ታግዘው የሚወልዱት 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 90 በመቶ የሚሆኑት ማንም ሳይረዳቸው በቤታቸው የሚወልዱ ናቸው፡፡ በአገራችን ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68 ሴቶች፣ በየሰአቱ ደግሞ 3 ሴቶች ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የአብዛኛው እናቶች ሞት የሚከሰተው በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከ85 በመቶ በላይ ለሚሆነው የእናቶች ሞት ዋንኛ መንስኤዎች የደም መፍሰስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የተራዘመ ምጥ ኢንፌክሽንና ውርጃ ናቸው፡፡ እንደ ጤና ጥበቃው መረጃ መሰረት፤ እያንዳንዱ እርግዝና ለሞት የሚዳርግ ችግር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ይህንን ችግር አስቀድሞ መተንበይ አይቻልም፡፡ ስለዚህም ማንኛዋም ነፍሰ ጡር ሴት ምጥ እንደጀመራት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ወደ ህክምና ተቋማት የሚደርሱት ዘግይተው በመሆኑ ህይወታቸውን መታደግ ሳይቻል ቀርቶ ለሞት ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ነፍሰጡር ሴቶች የራሳቸውንና የህፃኑን ህይወት ከሞት ሊታደግ የሚችል በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎትን እንዳይጠቀሙ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ዋንኞቹ ሦስቱ መዘግየቶች እየተባሉ ይጠቀሳሉ፡፡

የመጀመሪያው መዘግየት ተብሎ የሚጠራው እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ በሰለጠነ ባለሙያ ታግዘው ለመውለድ በጊዜ ውሳኔ ላይ አለመድረስ ነው፡፡ ይህም በገንዘብ እጥረት፣ በባህል ተፅእኖ፣ በግንዛቤ እጥረት ሊከሰት ይችላል፡፡ የፅሁፋችን መነሻ የሆነችው ሴት ታሪክ እንደሚያሳየን፣ ምጡ በጀመራት ጊዜ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለባት ወይስ የለባትም በሚለው ጉዳይ ባለቤቷና የባለቤቷ እናት ሲወዛገቡ ነበር፡፡ በዚህ ውዝግብ ሳቢያም አለም በጊዜ ወደ ጤና ተቋሙ እንዳትሄድ ሆናለች፡፡ ሁለተኛው መዘግየት የሚባለው ደግሞ እናቲቱ ወደ ጤና ተቋሙ እንድትሄድ ከተወሰነ በኋላ ከቤቷ ተነስታ ጤና ተቋሙ እስክትደርስ ድረስ የሚኖረው መዘግየት ነው፡፡ በተለይ በገጠራማውና ትራንስፖርት ፈፅሞ በማይኖርባቸው አካባቢዎች ችግሩ የጐላ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ውስጥም አንዳንድ እናቶች የዚህ ችግር ሰለባ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ የባለታሪካችን አለም ባለቤት ሚስቱ ወደ ጤና ተቋሙ እንድትሄድ ከወሰነ በኋላም ከቤቱ ጤና ጣቢያ ድረስ የሚወስዳት ትራንስፖርት ባለመኖሩ በጋሪና በኮንትራት ታክሲ ሲጉላላና ሲቸገር ቆይቷል፡፡ ይህም ሚስቱ በጊዜ እርዳታ የሚያደርግላት ሃኪም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ ሦስተኛው መዘግየት የምንለው ደግሞ እናቶች ጤና ተቋማት ከደረሱ በኋላ የሚገጥማቸው መዘግየት ነው፡፡ ይህም በባለታሪካችን አለም ላይ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የተለያዩ መሰናክሎችንና እንቅፋቶችን አልፋ ጤና ተቋሙ የደረሰችው አለም፤ የካርድ ክፍል ሠራተኛዋ አልገባችም በሚል ምክንያት ለደቂቃዎች የህክምና እርዳታ ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ይህም አለም በወቅቱ እርዳታ እንዳታገኝና ህይወቷ ለመትረፍ እንዳትችል አድርጓታል፡፡

እነዚህ ሶስት መዘግየቶች በርካታ እናቶችን ያለ አግባብ እንድናጣቸው የሚያደርጉን ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ማንኛዋም ነፍሰ ጡር ሴት በእርግዝና ወቅት ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የእይታ ብዥታ፣ የእጅና የፊት ማበጥ፣ ከፍተኛ የሆድ ህመም፣ የደም መፍሰስ፣ ከምጥ በፊት የሽርት ውሃ መፍሰስና ትኩሳት ካጋጠማት ወይንም ከእነዚህ ምልክቶች አንዱን እንኳን ካየች በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የህክምና እርዳታ ማግኘት ይገባታል፡፡ ምልክቶቹን እያዩ ቸል ማለት ወይንም ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት እንደ አለም ያለ አሳዛኝ ሞትን ያስከትላልና ፈፅሞ ልንዘናጋ አይገባም፡፡ ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ ያለውን ጠቀሜታ አውቆ፣ ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄድ የሚደረገውን ቅስቀሳ ያህል በጤና ተቋማቱ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎትና የባለሙያዎችን ስነ ምግባርም ዞር ብሎ ማየትና መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ማንኛዋም እናት ህይወት ለመስጠት ህይወቷን ማጣት የለባትምና!!

Published in ዋናው ጤና

ፈጣሪ ከፍጡራኑ ጋር ለመገናኘትና መለኮታዊ ህጉንና መልእክቱን ለማስተላለፍ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልደት ድረስ አንድ መቶ ሃያ አራት ሺህ ነብያት ልኳል፡፡ ታድያ ነብዩ መሐመድ የመጨረሻውና መደምደምያው ነብይ ናቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ ሰ.ዐ.ወ አልተማሩም፡፡ ነገር ግን አላህ መልአኩ ጅብሪል (ገብርኤል) አማካኝነት መለኮታዊውን ዕውቀት በውስጣቸው አስርፀዋል፡፡ ስለ ነብዩ መሐመድ መልካም ስብዕና፣ ጥሩ ጸባይ፣ ፍርድ አዋቂነት፣ ርህራሄና ይቅር ባይነት ብዙ ነገር መግለፅ ቢቻልም የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ እሳቸው የሰሩትን እና ያሳዩትን ተአምራት መግለፅ ብቻ ስለሆነ እሱን አልፈዋለሁ፡፡ ነብዩ መሐመድ የተገኙበት የአረቡ ማህበረሰብ በወቅቱ በከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የነበረ ሲሆን ማህበረሰቡ በባዕድ አምልኮ፣ በስካርና በቁማር የተዘፈቀበት ወቅት ሲሆን ዑመር ኢከኑ ኸጣብ፣ ከባዕድ አምልኮ ወደ እስልምና ከተመለሱ በኋላ የተናገሩትን መጥቀስ በጊዜው የነበረውን እውነታ ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡ “አንድ ነገር ያስቀኛል፡፡ አንድ ነገር ደግሞ ያስለቅሰኛል፡፡ የሚያስለቅሰኝ ከጣፋጭ የተሰራ ጣኦት ይዘን በበረሃ ውስጥ ስንጓዝ ራበንና በላነው፡፡” በማለት ቅድመ ኢስላም የነበረው ማህበረሰብ ለፈጣሪ የነበረውን አመለካከት ሲገልፁ፤ የሚያስለቅስዎትስ ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ፤ “ከጦርነት ስመለስ ሚስቴ ሴት ልጅ ወልዳ ጠበቀችኝ፡፡

እንደ አገሩ ባህል መሰረት ከነህይወቷ መቅበር ነበረብኝ፡፡ ልቀብራት ጉድጓድ ስቆፍር “አባቴ አባቴ” እያለች ጺሜ ላይ የነበረውን አቧራ ታራግፍልኝ ነበር፡፡ እንደዚያ እያለች ቀበርኳት” በማለት ማህበረሰቡ በወቅቱ ለሴት ልጅ የነበረውን አመለካከት ገልጸዋል፡፡ ሴትን እንደንብረት ማየት፣ የአባትን ሚስት መውረስ፣ ሚስትን በቁማር ማስያዝ፣ ሴት ልጅ ስትወለድ ከነህይወቷ መቅበር ቅድመ እስልምና የነበረ የወቅቱ የዘቀጠ አስተሳሰብ ሲሆን በዚህ የጀህልያ (የድንቁርና) ዘመን ነበር፡፡ ነብዩ መሐመድ ነውየተወለዱት፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላኩት ተአምራት ለመስራትና ለማሳየት አልነበረም፡፡ የታላቁንና መለኮታዊውን ሐይል የአላህን ትዕዛዝ ለማስተላለፍ እንጂ፡፡ ይህ ሲባል ግን ምንም ተአምራት አላሳዩም ማለት አይደለም፡፡ ያሳዩዋቸውን ተአምራት ከመዘርዘራችን በፊት ዋናው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተአምራት ለሳቸው የተሰጠው ወይም በጅብሪል አማካኝነት በስርፀት ወደሳቸው የገባው ቁርአን ወይም የአላህ ቃል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አላህ በገለጸላቸው መሰረት የተናገሩት “ሐዲስ” ሲሆን በጊዜው ሊታወቁ ቀርተው ሊታሰቡ የማይችሉትን እውነቶች በአንደበታቸው መናገራቸውና እነዚህን እውነቶች ሳይንስ በቅርቡ ያረጋገጣቸው መሆናቸው ናቸው፡፡ ከነዚህ የቁርአንና የሐዲስ እውነቶች ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡ “እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መሆናችንን አያውቁምን? ህያው የሆነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን፡፡ አያምኑምን? (አል፤ ነንብያ 30) እንግዲህ ይህ የቁርአን አንቀጽ የሚያሳየው ስለ (big bang) ቲዎሪ ሲሆን ከ13.7 ቢሊዮን አመታት በፊት መላው ዩኒቨርስ በአንድ ነጠላ አቶም ውስጥ ታምቆ እንደነበርና በከባድ ፍንዳታ እንደተለያየ ሳይንስ በቅርቡ ደርሶበታል፡፡

እንግዲህ ከ14 አመት በፊት የነበሩ ማንበብና መፃፍ የማይችሉት ነጋዴዉ መሐመድ፤ ይህንን ሳይንሳዊ እውነት እንዴት ሊያውቁት ቻሉ ብለን ስንጠይቅ መልሱ አንድና አንድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አላህ ገልጾላቸው፡፡ ከአቡ ሰላማ በተወራ ሐዲስ መሰረት፤ በእርሳቸውና በተወሰኑ ሰዎች መካከል በአንድ ቁራጭ መሬት ሰበብ ጭቅጭቅ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ ለምዕመናን እና ዓኢሻ (ረ.ዓ) ሲነግሯት፤ “አቡ ሰላማ ሆይ! ከሰዎች ምንም አይነት መሬት ያለ አግባብ እንዳትወስድ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ከአንድ ሰው አንድ ስንዝር መሬት በጉልበቱ ወይም በብልጠት ተጠቅሞ የወሰደ ሰው፤ እስከ ሰባት ምድር ድረስ (በወሰደው መሬት ልክ) በአንገቱ ላይ ይጠመጥምበታል፡፡ ሳሌም አባቱን ጠቅሶ ባወራው ሐዲስ፤ ነብዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ከሰዎች ቁራጭ መሬት በጉልበት (በስልጣን) ያለ አግባብ የወሰደ ሰው በፍርዱ ቀን ሰባት ምድር ድረስ (ውስጥ) ይሰምጣል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሐዲሶች የሚነግሩን አላህ ግፍና ጭቆናን ምን ያህል ከባድ ወንጀል አድርጐ እንዳስቀመጠው ሲሆን ሰባቱ ምድር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፡፡ የሥነ-ምድር (Geology) ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ምድር ከሰባት ክበቦች (Zones) የተሰራች ስትሆን እነርሱም ከውስጣዊው ክፍል ጀምሮ እስከ ውጫዊው ድረስ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡ 1. ጠጣር የሆነው (ታችኛው) ውስጣዊ የምድር ክፍል (Core) ይህ የምድር ክፍል ጠጣር ሲሆን የተሰራውም 90% ከብረትና 9% ከኒኬል ነው፡፡ እንዲሁም ካርቦን ፎስፈረስ ሲልከን ኦክስጂን በድምሩ 1% ብቻ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የክበቡ አጋማሽ (Diameter) በግምት 2402 ኪ.ሜ እንደሆነ ይገመታል፡፡

ይህ ሰባተኛው የምድር ክፍል መሆኑ ነው፡፡ 2. ፈሳሽ የሆነው ላይኛው ውስጣዊ የምድር ክፍል (Core) ይህ ፈሳሽ የሆነው የምድር ክፍል ውስጣዊውንና ጠጣሩን የምድር ክፍል አክቦ የያዘ ሲሆን ውፍረቱ 2275 ኪሜ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ይህ አካል ስድስተኛው የምድር ክፍል ነው፡፡ 3. ዝቅተኛው ማንትል (Lower Mantle) ይኸኛው ጠጣር የሆነና ቀላጭ (Molten) የሆነው የውስጠኛው የመሬት ክፍል (Liquid outer core) የሚያከብብ፣ ውፍረቱ 2215 ኪሜ እንደሆነ የሚገመት አምስተኛው የምድር ክፍል ነው፡፡ 4. መካከለኛው ማንትል (Middle Mantle) ጠጣር የሆነ የመሬት ክፍል ሲሆን ውፍረቱ ወደ 270 ኪሜ እንደሆነ ይታሰባል - አራተኛው የምድር ክፍል፡፡ 5. የላይኛው ማንትል (Upper Mantle) ይህ የመሬት ክበብ ከፊል ቀላጭ (Semi Molten) ሲሆን በአንፃራዊነት ከፍተኛ እምቅታ (Density) ያለው ነው፡፡ ውፍረቱ ከ65-120 ኪሜ ሲሆን ሦስተኛው የምድር ክፍል መሆኑ ነው፡፡ 6. ዝቅተኛው አለታማ የመሬት ክበብ (Lower Rockey Crust) ውፋሬው በደረቅ መሬት የብስ ከ40-60 ኪሜ ሲሆን ባህሮችና ውቅያኖሶች ክፍሎች ከ60-80 ኪ.ሜ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ይህ ክበብ ሁለተኛው የምድር ክፍል ነው፡፡ 7. ላይኛው አለታማ የመሬት ክበብ (Upper Rockey Crust) ውፍረቱ ከ5-8 ኪሜ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሆኖም በባህሮችና በውቅያኖሶች ስር ከሆነው ከ60-80 ኪሜ በአማካይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የላይኛው የመርሰ ምድር ንጣፍ፣ በአብዛኛው ከጥቁር ድንጋይ የተሰራ ሆኖ በላዩ ላይ ወፍራም የአለት ንጣፎች ያሉት አንደኛው የመሬት ክፍል ነው፡፡

እስካሁን ያየነው ትንታኔ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሁለት ሐዲሶች በተለይም ደግሞ በፍርድ ቀን ሰባት ምድር ድረስ ይሰምጣል ከሚለው ጋር እንደሚስማማ ሲሆን በሚከተሉት የቁርአን ምዕራፎች እንዴት እንደሚታገዝ እንመልከት፡፡ “ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን፣ ሰማያትም (እንደዚሁ) አንድ አሸናፊ ለሆነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለፁበትን ቀን (አስታውሱ) “አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፡፡ ከምድርም መሰላቸውን (ፈጥሯል) በመካከላቸው ትእዛዙ ይወርዳል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ቻይ መሆኑን፣ አላህም በነገሩ ሁሉ በእውቀት ያከበበ መሆኑን ታውቁ ዘንድ (ይህንን አሳወቃችሁ፡፡) (አል-ጦለቅ 12) አነስ ኢብን ማሊክ (L.O) እንዳወሩት፤ የመካ ሰዎች ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተአምር እንዲያሳዩዋቸው ጠየቅዋቸው፤ እርሳቸውም ጨረቃ ተገምሳ በሁለት ቦታ እንድትወድቅ በማድረግ አሳዩዋቸው፡፡ በመካከሉም የሂራ ተራራ በግልፅ ይታይ ነበር፡፡ ይህ ሐዲስ በብዙ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች የተረጋገጠ ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ አብደላህ ኢብን ዑመርና አብደላህ ኢብን አበስ እንዲሁም ሌሎች ይገኙበታል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ፕሮፌሰር ዘግሉል አል ነጂር፤ ዌልስ በሚገኘው የከርዲፍ ዩንቨርስቲ የህክምና ፋከልቲ ገለፃ እያደረገ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ መስሊም በሱራ አል ቀመር (በጨረቃ ምዕራፍ) መጀመርያ ላይ ስላለውና ስለጨረቃ መገመስ ስለሚተርከው ጉዳይ ጠየቀው፡፡ ሰውየው የፈለገው ይህ የቁርአን ምዕራፍ የያው ሃሳብ እንደሳይንሳዊ መረጃ ሊወሰድ ይችል እንደሆነና ይህን ክስተት የሚደግፍ ሌላ ሳይንሳዊ መረጃ ይገኝ እንደሆነ እንዲገልፅለት ነበር፡፡ ናሳ የተባለው የአሜሪካ የህዋ ምርምር ማህበር፤ ሰዎችን ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ ሳይንቲስቶች በጨረቃ ላይ የያዩትን ለብዙ ሰዎች ቢገልፁም የሚያምናቸው አላገኙም፡፡ ይህም ጨረቃ ከብዙ አመታት በፊት ለሁለት ተገምሳ የነበረና መልሳ የተገጣጠመች የሚመስሉና የሚያመለክቱ ጠንካራ ማስረጃዎች እንዳሉ ነው፡፡

ኢማም አድዱይለሚ በ”አልፈርድወስ” ኢማም አስሲዩጢ በ”ጀሚዕ አልጀማዋዕ” መፅሐፍታቸው ላይ እንደገለፁት፤ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡፡ “አላህ አራት የተባረኩ ነገሮችን ከሰማይ ወደ መሬት አውርደዋል፡፡ እነርሱም ብረት፣ እሳት፣ ውሃና ጨው ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ይህ ሐዲስ ደካማ ከሚባሉት ሐዲሶች የሚያስመድበው ቢሆንም ታላቅ የሆነ ሳይንሳዊ ሐቅን የያዘ በመሆኑ ወደጐን ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በነበሩበት ጊዜ የነበሩ ሰዎች፤ የእሳት የውሃንና የጨውን ከሰማይ መውረድ ቢገነዘቡም የብረትን ጉዳይ ግን ብዙም አልተረዱትም ማለት ይቻላል፡፡ ሰፋፊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የከዋክብት ህይወት ኡደት (Life cycle) ብዙ እርከኖችን እንደሚያልፍ ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ደረጃዎች ከዋክብት በጣም በሚያንቦገቡጉት ጊዜ በሳይንሳዊው አጠራር “Novas” እና “Supernovas” የሚል ሲሆን የክዋክብቱ ውስጣዊ (core) የሚኖረው የሙቀት መጠን በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የእነዚህ ኖቫስ እና ሱፐር ኖቫስ የሚሰኙ የክዋክብት ደረጃዎች ተወርዋሪ ኮከብ የምንላቸው በውስጣቸው የኒኩልየር መዋሃድ ይከናወንባቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው እነዚህ የህዋ አካላት ሙሉ በሙሉ ወደ ብረትነት እስኪቀየሩ ድረስ ነው፡፡ በዚህ ሽግግራዊ ሂደት አጠቃላዩ የከዋክብቱ ሃይልና ጉልበት (Energy) ወደ ፍንዳታ (Explosion) እስኪደርሱ ድረስ እየገፋቸው ሄዶ በመጨረሻም ተፈረካክሰው በመላው ዩኒቨርስ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በእኛም ፕላኔት ምድርም የተለያዩ ተወርዋሪ የጠፈር አካላት (ሙሉ ለሙሉ ብረታማ የሆኑ) ወደ መሬት ከባቢ አየር በሚወድቁበት መንገድ ነው ብረት ወደ መሬት የሚወርደው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ እንግዲህ የቁርአንና የሐዲስ መለኮታዊነት በሳይንስ ሲረጋገጥ ከማያሳየው ከብዙው በጣም በጥቂቱ ሲሆን አንባቢ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ጐግል ዌብሳይት ውስጥ ያሉትን የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ተአምራቶች በተመለከተ የተፃፉትን፡- Splitting of the Moon Food Multiplication Water Multiplication Supplication for Rain Light to guid companions Crying of the stem of the date – palm free Glorification of Allah by the prop het’s heals The expulsion of a liar’s corpse by the earth The speech of the wolf The prophets Night journey to Jerusalem and ascent to the Heavens የሚሉትን ክሊክ አድርገው ቢያዩ የበለጠ መረጃ ለማወቅ እንደሚረዳቸው አምናለሁ፡፡ ምንጭ - ሳይንሳዊ ተአምራት በነብዩ ሐዲሶች

Published in ህብረተሰብ
Page 1 of 11