Saturday, 24 September 2011 09:43

አዲሱን የታክሲ ታሪፍ ባለንብረቶቹ እና አሽከርካሪዎቹ አልተቀበሉትም

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

የታክሲ ባለንብረቶችን አቤቱታ ተከትሎ የከተማ ታክሲዎች ላይ የታሪፍ ማስተካከያ  ቢደረግም የንብረቱ ባለቤቶችና ተቀጣሪ አሽከርካሪዎች ማስተካከያው በቂ አይደለም ይላሉ፡፡  አሽከርካሪዎቹ ታፔላው እንዲቀር ሲጠይቁ ባለንብረቶቹ ተመችቶናል ይላሉ፡፡ አቶ ፍቃዱ ይልማ የተባሉ የታክሲ አሽከርካሪ፤ አዲሱን የታክሲ ታሪፍ ጭማሪ  አስመልክቶ አስተያየቱን ሲሰጥ 30 ሳንቲም ጭማሪ ከማድረግ ይልቅ ታፔላ ማስለጠፉ እና የቀ-ና ስምሪቱ እንዲቀር ቢደረግ አዋጪ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የሚያስቀምጠው፤ በታፔላ በቀጣና የሚመደቡ ታክሲዎች ይዞታቸውን ያገናዘበ ባለመሆኑ ዳገት መውጣት የሚሳናቸው ተሽከርካሪዎች ዳገት ወዳለበት አካባቢ እንደሚመደቡ ተናግሯል፡፡ በዚህም አደጋ መከሰቱን እና ለኪሳራ መዳረጋቸውን ይገልፃል፡፡ ታክሲዎች በተገቢው ሁኔታ ኅብረተሰቡን ማገልገል እንዲችሉ ከታሪፉ ይልቅ ታፔላ እንዲቀር ይጠይቃል፡፡

የባለንብረቶች ማኅበር ሊቀመንበሮች በበኩላቸው፤ መኪኖቻቸው እንዳይጐዱ እና አሽከርካሪዎቹN ለመቆጣጠር የቀጠናን ሥራ እንደመረጡት ይናገራሉ፡፡ የንስር ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ይበልጣል አባተ እንደሚሉት፤ ማንም በቀጠና ሠርቶ የተጐዳ ሹፌር የለም፡፡ ሕገወጥ አሠራሮችን ለመሥራት ካልፈለጉ በስተቀር.. ይላሉ፡፡ አሽከርካሪዎቹ በደሞዛቸው አነስተኛነት ምክንያት በየቀኑ በሚያገኙት ውሎ አበል ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስተዳድሩ የገለፀው ይርጋለም ፀሐይ፤ ..ገቢያችን በማነሱ ቤተሰብ እየተጐዳብን ነው.. ይላል፡፡ የታሪፍ ጭማሪው ፋይዳ የሌለው ነገር መሆኑን በመግለጽ፡፡
በዋናነት የሹፌሮቹ ጥያቄ የታፔላ መነሳትን ነው፡፡ ታሪፉ ባይጨምርም እንደ ፈለጉት ተዘዋውረው ቢሠሩ ለውጥ እንደሚመጣ ይገልፃሉ፡፡ ..የታሪፉ መጨመር ዋጋ ቢስ ነው..  አዲሱን የታክሲ ዋጋ ታሪፍ ያጣጥላሉ፡፡
የአዲሱ ታሪፍ በኪሎ ሜትር የሚገለጽ ሲሆን ይህም ቀድሞ ከነበረው የታክሲ ታሪፍ አብዛኛዎቹ ቀንሰዋል፡፡ በጥቂቶቹ ላይ ጭማሪ ቢኖርም፡፡ እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር ድረስ በቀድሞ አሠራሩ ብር ከ70 ሳንቲም ብር ከ85 የነበረው አሁን ወደ ዝቅ ያለ ሲሆን በሌሎቹም ላይ እንደ የኪሎ ሜትራቸው ቅነሳ የተደረገባቸው አሉ፡፡ ይህም ሰው በልማድ ሲከፍልባቸው የነበረ ሲሆን ይህም በኪሎ ሜትር ሲሰላ ዋጋቸው መቀነሱን ለማሳወቅ ችለናል፡፡      
..ጭማሪው ሁለትና ሶስት ብር ቢሆንም አያዋጣም..
በጭማሪው ህዝቡ የተደናገረ ይመስለኛል፡፡ ህዝቡ ቤንዚን ሲጨምር አምስትና አስር ሳንቲም ሲጨምር ነው የሚያውቀው፡፡ ነገር ግን የእኛ ስራ ዋጋ መጨመር አይደለም፡፡ በሌላ ንግድ የተሠማራ በሚያዋጣው መንገድ ትርፉን አስቦ ጨምሮ ይሸጣል፡፡ የእኛ ስራ እንደዛ አይደለም፡፡ የመለዋወጫ እቃ ጨምሯል፤ ሦስት መቶ ብር የምንገዛው ጐማ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ደርሷል፡፡ አጠቃላይ እቃዎቹ በአስር እጥፍ ጨምረዋል፡፡
እኛ ግን የታሪፉ ዋጋ የሚሻሻልን ቤንዚን በጨመረ ጊዜ ነው እንጂ ከስፔር ፓርትና ከመኪና ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የመጣ የዋጋ ጭማሪ አልነበረም በዚህ ደግሞ የትራንስፖርቱ አገልግሎት እየሞተ በመምጣቱ ለማንሳት የአዲስ አበባ እና የፌደራል መንገድ ትራንስፖርት ከማህበሩ ጋር በጋራ ጥናት አድርጓል፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡን ታሳቢ ያደረገ መነሻ የዋጋ ማስተካከያ ተሠርቷል፡፡ ከወጪያችን ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ግን አይደለም፡፡ ሁለትና ሶስት ብርም ቢባል አያዋጣም፤ ግን የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት  የተጨመረው ትንሽ ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱን መንግስት ለማረጋጋት ሸቀጦችን ያቀርባል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የታክሲ ባለንብረትን መደጐም ቢችል ኩፖን ተዘጋጅቶ ቤንዚን ገበያው ላይ 21 ብር ከሆነ ለእኛ 15 ብር ቢሸጥ፣ ስፔር ፓርቶችንም ሆነ መኪና ከውጪ ማስመጣት ብንችል የትራንስፖርቱN እጥረት ለመቀነስ እንችላለን፡፡ መንግስት ካስቀመጣቸው በጐ ስራዎች አንዱ በቀጣና ማሰማራቱ ነው፤ ይሄ ትንሽም ቢሆን የመኪኖች መጐዳትን ይቀንሳል፡፡ ለሹፌሮች ላይጥማቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የትም ተሯሩጠው እንዳይሠሩ ይሆናል፤ ስለሚያግዳቸው ባለንብረቱ ግን ንብረቱን ለመቆጣጠር ይችላል፤ ነገር ግን ገቢ ላይ ይጐዳልም ይጠቅማልም፡፡ ይሄ ለቀጣና ብቻ ሳይሆን አዲሱ ታሪፍንም ይመለከታል፡፡ ለረጅም መንገድ ይጐዳል፡፡ ለአጭሮቹ ግን ይጠቅማል፡፡ የቀጠና ስምሪት ያስከተለውን የገቢን መቀነስ ለመቋቋም ነው ታሪፍ የጨመርነው፡፡ ከሁለት ወር በኋላም ጥናት አድርገን የዋጋ ማስተካከያ እናደርጋለን፡፡ አንበሳ የከተማ አውቶቢስን መንግስት ይደግፋል፡፡ የታክሲውም የመንግስት አካል ባይሆኑም ድጐማ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ስራ ይሞታል ህዝቡ ይጐዳል፡፡
አቶ አበባው ካሳ ተሠማ
(የፀሐይ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሊቀመንበር)
..የታሪፍ ጭማሪው መምጣቱ የድሮ ዋጋውን ቀንሶታል..
የታሪፍ ጭማሪው የባለንብረቱን ጥቅም ያገናዘበ ስሌት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም በአጭር መንገዶች ላይ ያለው ዋጋ ሲጨመር በረጅሙ ላይ ደግሞ ዋጋ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ይሄ የኪሎ ሜትር ስሌት ላለፉት ሠላሳ አመታት ያልተቀየረ ነው፡፡ ያኔ የሞተር እድሳት በሦስት ሺህ ብር ይጠናቀቅ ነበር፡፡ አሁን ሃያ አምስት ሺህ ብር ይደርሳል፡፡ የእቃ ዋጋዎች ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ ስለዚህ የታሪፍ መስተካከሉ ባለንብረቱን ያስደሰተ አይደለም፡፡ ይሻላል ለማለት እንጂ አሁን ያሉት መኪኖች በሊትር ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ አይሄዱም፡፡ ስለዚህ ዋጋው ገቢያችንን ያማከለ አይደለም፡፡ በፊት የተለመዱት ዋጋዎች ተቀንሰዋል፡፡ ለምሳሌ ከቦሌ ሜክሲኮ ሦስት ብር ከሰባ ሳንቲም ነበር፡፡ አሁን ግን 2.85 ሆኗል፡፡ ከመገናኛም እንደዚሁ ሆኗል፡፡ ስራው አላዋጣም ስላላቸው ሶማሌ ተራ የሚበተኑ ታክሲዎች በዝተዋል፡፡ የማስተካከያ ገንዘብ ስለሌላቸው ማለት ነው፡፡ ዘርፉ አዋጪ ስላልሆነ ወደዚህ ስራ የሚገባ የለም፡፡
እና የጠቀመን ቀጣና ነው፤ ይሄም ባለሀብቱ መኪናው የት እንዳ ሊያውቅ ይችላል እንጂ የገቢ ለውጥ አያመጣም፡፡ ምናልባትም በህገወጥ መንገድ ለመክበር የፈለገ ካልሆነ በስተቀር ቀጣናው ጠቅሞናል፡፡
አዋጪ መስመር ይዘው አያዋጣም ብለው አንዳንድ ሹፌሮች ባለንብረቱን ለማታለል ይሞክራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀጣናውን እንደ ችግር የሚወስዱ አሉ እንጂ የተጐዳ የለም፡፡ የሹፌር ስራ ከፍተኛ ጫና እንዳለው እናምናለን፡፡
ደሞዛቸው በአሁኑ የኑሮ ውድነት ያኖራቸዋል ብዬ አላስብም፤ ረዳቱንም ጭምር፡፡ ሆኖም ሹፌሩን ሊጐዳ የሚችል መስመር የለንም፡፡ ነገር ግን ይሄ አካል ጥቅም አያግኝ አንልም፡፡ ስነምግባር የሌላቸው አንዳንዶች ሹፌሮች እንዳሉ ሁሉ ለማገልገል ቀና ደፋ የሚለውን ሹፌር አይጠቀም አንልም፡፡ ይሄ ሁሉ እንዲሆን መንግስት የተለያዩ ነገሮችን ማመቻቸት አለበት፡፡ አንድ መኪና በሊትር 5 ኪሎ ሜትር እየሄደ አንድ ሊትር 21 ብር እየገዛ፣ የሹፌርና የረዳት ቁርስ ምሳና እራት ችሎ የቀን ውሎ አበል ችሎ፤ ለባለቤት የሚገባው ገቢ ከቀነሰ መኪናውን ለማሳደስ በቂ ገንዘብ አይኖርም፡፡ የመኪናው መቆም የስራ አጥነትን ያባብሳል፡፡ በታሪፍ ጭማሪው የተጠቀመው ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ በልማድ ሲከፍል የነበረው የሠባት ኪሎ ሜትር ታሪፍ ቀንሷል - ወደ 2.85 ወርዷል፡፡ ህዝቡ ይሄንን አያውቅም፡፡ በዚህ ላይ ተነጋግረን ዋጋው እንዲሻሻል ጠይቀናል፡፡ ህዝቡ ግን አሁንም ጉዳቱን ነው የሚያስበው፡፡ ግን በታሪፍ ጭማሪው የተጠቀመው ህዝቡ ነው፡፡
አቶ ይበልጣል አባተ
የንስር የታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሊቀመንበር
***
..ገቢ ለማስገባት በጭንቀት
ነው የምንሰራው..
ከበፊቱ አሠራር ላይ በመጀመሪያ የታፔላ መለጠፍ ከፍተኛ ችግር አምጥቷል፡፡ ከቤት በባዶ ስንወጣ ለህዝብ አዝነን ስንጭን እንቀጣለን፡፡ እኛ የምንመጣው በነዳጅ ነው፤ በፊት ቢሆን ተሯሩጠን እንሞላለን፡፡ ሌላው የታሪፍ ጭማሪ ለእኛ ምንም የጠቀመን ነገር የለም፡፡ ረጅም መንገድ ስንሰራ ይጐዳናል፡፡ ምክንያቱም ለሠባት ኪሎ ሜትር ታሪፉ 2.85 ነው የተደረገብን፡፡ በፊት ሦስት ብር ከሰባ ነበር፡፡ አሁን ያሉት መኪኖች አብዛኛው የተጐረጐሩ በመሆናቸው ነዳጅ ይበላሉ፡፡ ለምሳሌ ከፒያሳ ቦሌ ደርሶ መልስ አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ነው፡፡ በአዲሱ ታሪፍ ሰማንያ ብር ደርሶ መልስ ቢገኝ ነዳጅ የሚወስደው ደግሞ አምስት ሊትር ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ ትርፉ ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ ለባለቤትም ገቢ ለማስገባት በጭንቀት ነው የምንሠራው፡፡ እኛ መኪናችንን አቁመን ሰው እንጠብቃለን፡፡ ሰው መኪናችንን ተደግፎ ሌላ መኪና ይጠብቃል፡፡ በፊት ሰው ባየንበት ስለምንሄድ የተሻለ ነበር፡፡ የታሪፍ ጭማሪም መፍትሔ አይሆንም ነገር ግን ማቆራረጥ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ መንገድ ትራንስፖርት ቢሠራ ይሻላል፡፡
ይርጋለም ፀሐይ - የታክሲ ሹፌር
ከወሎ ሰፈር ቄራ
***
..ታሪፍ ጭማሪው አይጠቅመንም..
የታሪፍ መጨመሩ ጥቅሙ አይታየኝም፤ መጀመሪያም በቀጠና ሲያደርጉ ችግር ነበረው፡፡ የሚጠቀመውም የሚጐዳውም ተሳፋሪው ነው፡፡ መቆራረጥ የመጣው እንደውም አሁን ነው፡፡ በፊት በአንድ ታክሲ ረጅም መንገድ ልንሄድ እንችላለን፡፡ እኔ ሶስት መቶ ብር ደሞዝ አለኝ፡፡ በግለሰብ ቤት አምስት መቶ ብር ተከራይቼ ነው ከባለቤቴና ከልጄ ጋር የምኖረው፡፡ የታሪፍ አወጣጡ የረዳትና የሹፌሮችን ጥቅም ያላገናዘበ ነው፡፡ አብዛኛው መኪና ደርሶ መልስ መቶ ብር ይሠራል ቢባል ነዳጅ አምስት ሊትር ይበላል፡፡ ስለዚህ በኪሳራ ደርሶ መልስ እንሠራለን፡፡ ሌላው ታፔላው ከቤታችን ስላራቀንና እንደልብ ቤታችን ገብተን መመገብ ስላልቻልን መንገድ ለመብላት ተገደናል፡፡ ሌላ ወጪ ማውጣት ሆኗል፡፡ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ስለማይቻል በባዶ ነው የምሄደው ይሄ ደግሞ ቤንዚን ይበላል፡፡ ወረፋ ጠብቆ በመጫን ሰአታችንን እንገድላለን፡፡ ይሄ ገቢያችንን ደካማ ያደርጋል፤ ለእኛ የታሪፍ መጨመር ዋጋ የለውም፡፡
ሲሳይ ግርማ ሹፌር
(ከቦሌ ሚካኤል መርካቶ ጣና ገበያ)
***
ሃያ ሳንቲም ጨምሮ ህዝቡን ከማንገላታት ታፔላ ቀርቶ ታሪፍም እንደ ድሮ ቢሆን ይሻላል፡፡ በርካታ ሰው ቆሞ እኛ ዝም ብለን ተደርድረን ብናያቸው ምን ይጠቅማል፡፡ ስርአት የሚያስይዙ የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ለመቅጣት ከሚቸኩሉ ይሄንን ህዝብ አገልግሉ ቢሉን ነው የሚሻለው እንጂ የሌለ ታሪፍ ማውጣት ጥቅም የለውም፡፡
ሀይሌ ብርሃኑ ሹፌር
(ከመብራት ኃይል ሠፈራ)
***

..ታፔላው ከመጣ ጀምሮ እንቅልፍ ተለይቶኝ
አያውቅም..
አዲሱን ታፔላ ለመቀየር ነበር አመጣጤ ሶስት ቀን ሆኖኛል፡፡ ማህበሩ ስራው ልክ እንደ ታፔላው የተዘበራረቀ ነው፡፡ እኔ ታፔላው ከመጣ ጀምሮ እንቅልፍ ተለይቶኝ አያውቅም፡፡ መኪናው ውስጥ ለረጅም ጊዜ ነው የምተኛው፡፡ ከአንድ ሰአት በላይ ወረፋ ለመያዝ ነው የምንቆመው፤ ይሄ ደግሞ ህዝቡን አማሯል፡፡ የታሪፍ ጭማሪ ከሚባል ቢቀነስ ነው የሚሻለው፤ ሰላሳ ሳንቲም ተጨምሮ አንድ ብር ተቀንሶብናል፡፡ በዚህ አሠራር እንዴት ገቢ ይገኛል፡፡
በፊት በስድስት ቢያጆ ደህና ነገር ይያዝ ነበር፤ አሁን አስራ ሁለት ጊዜም ቢሠራ አያዋጣም፤ ስለዚህ ለህዝቡም ለእኛም ያልጠቀመንን ታፔላ መንግስት ያስቁመው፡፡
ረመዳን ከማል
(ከቡናና ሻይ ኤርፖርት)

Read 3870 times