Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 16 September 2011 05:30

አርቲስቶችና የአዲስ ዓመት ምኞታቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በኪነጥበቡና በፖለቲካው ዘርፍ ጉልህ ሚና ያላቸው ባለሙያዎች 2003 ዓ.ምን እንዴት እንዳሳለፉትና በ2004 ለአገራቸው የሚመኙትን ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹ አርቲስቶች ባሳለፍነው ዓመት የጥበቡ ዘርፍ እንዳደገ ቢስማሙም እየናረ የመጣው የኑሮ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰው የተሻለ ዘመን እንዲመጣ ተመኝተዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በበኩላቸው ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እያደር መቀነሱንና ዲሞክራሲያዊ ሂደቱ መቀጨጩን ይገልጻሉ፡፡ የፖለቲካውን ዕጣ ፈንታ ለመተንበይም ተቸግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ በተለይ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በህዝቦች መካከል መግባባትና መነቃቃት እንደፈጠረ ገልጾ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ግብዓት የመሰብሰብ ሥራ እንዳከናወነ ይገልጻል፡፡ በ2004 ዓ.ም. ተቃዋሚዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው አርቲስቶቹንና ፖለቲከኞቹን አነጋግራ የአዲስ ዓመት መልዕክታቸውን እንደሚከተለው አቅርባለች፡፡


..የዓመቱ አስቸጋሪ ነገር የኑሮ ውድነቱና ረኀኀብ ነው..
በኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ሁለት ነገሮች ተሻሽለዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንደኛውና የምናፍቀው የመድረክ ሙዚቃዎችን ተመልክተናል፡፡ ከስቱዲዮ ተቀርፀው ስንሰማቸው የነበሩትንና  በመድረክ ማየት የምንፈልጋቸውን በየሳምንቱ በጃዝ አንባ እያገኘናቸው ነው፡፡ የናይት ክለብ ጨዋታዎች በዲሲፕሊን እየተሠሩ ነው፡፡ ሁለተኛው መንግሥት ለጥበቡ አክብሮት እና ትኩረት እንዲሰጠው እንፈልግ ነበር፡፡ ከመንግሥት ጋር ያደረግነውም ውይይት ውስጡ ችግር ቢኖረውም ውጤት ያመጣና ቢያንስ በሦስት ጉዳይ ላይ መልስ እንዲሰጠን ያስቻለ በመሆኑ በጐ ነገር አይቻለሁ፡፡ ለጥበቡ ዕድገት ያደረኩትን አስተዋጽኦ ስገመግመው ከላይ ባስቀመጥኩት መልኩ ለውይይቱ የሚሆን ሰነድ በማዘጋጀት ጥሩ ነገር ሠርቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በ2003 ዓ.ም በአገሪቷ ላይ የነበረው አስቸጋሪ ነገር የኑሮ ውድነትና ረኅብ ነው፡፡ ጤፍ ከጐጃም እንደምናመጣ እያወቅሁኝ ከውጭ የምናስገባ ይመስል፣ በጣም መወደድ የሚያስገርም ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ ቀጥተኛ ለውጥ ካልመጣ በተለይ የመንግሥት ሠራተኛው ይቋቋመዋል ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም በቁጥር  ጥቂት ነው የሚባለውን የሲቪል ሰርቪስን ሠራተኛ ከ80 በመቶ ያላነሰ ገበሬ ሠርቶ ማብላት አለመቻሉ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ሌላው ፓርላማ ውስጥ ወንበሩ ከቻሌንጅ (ተግዳሮት) ውጭ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ የሚቀርበው ሐሳብ ይርባም አይርባም የልዩነት ሐሳብ መድረክ ነውና በክርክር የዳበሩ ሐሳቦች መፍለቅ ሲገባቸው ከዚህ ውጭ በሆነ መልኩ መድረኩ ራቁቱን ሆኖ ያየሁበት ዓመት ነው፡፡ አስደሳቹ ነገር ትውልዱ እየተቀየረ ነው፡፡ ሌላው አባይን የማልማቱ ሐሳብ ስንፈልገው የነበረ ነው፡፡ ሁኔታው ዱብ ዕዳ ቢሆንብንም የትም ሀገር ሥልጣኔ የራሱ ቻሌንጅ (ፈተናዎች) እንዳሉት ማወቅ አለብን፡፡
ዘመነ ዮሐንስ ጦርነትን ያሸነፍንበት ነው ሲባል እሰማለሁ፡፡ ስለዚህ መጪው 2004 ዓ.ም ሁሉን የምናሸንፍበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የተጀማመሩት ነገሮች ከፍጻሜ ከደረሱ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሰርፀ ፍሬ ስብሀት
የሙዚቃ ባለሙያና የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህር


..ኢትዮጵያ ጠግባ የምታድር ሀገር እንድትሆን ምኞቴ ነው..
በ2003 ዓ.ም የሥነጥበብ ሞያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ክብር ያገኘበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ የአገር መሪ የኪነጥበብ ሰዎችን ..ችግራችሁ ምንድነው? ችግራችሁን እንፍታ?.. በሚል ያወያዩን ጊዜ ነበር፤ ይሄ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ትልቅ ሥራ እንዲሠራ የተዘረጋ ነገር በመሆኑ አንድ ለየት ያለ ክንውን ያደርገዋል፡፡ ሌላው ባሳለፍነው ዓመት በርካታ ትልልቅ ፊልሞች ተሠርተዋል፡፡ ለእኔ ግን በዓመቱ ከተከናወኑ ክንውኖች ዋናውን ቦታ የሚይዘው መንግሥት ለጥበቡ ትኩረት መስጠቱ ነው፡፡ ጥበቡ እንዲያድግ አንድ እርምጃ ተሄዷል ማለት ነው፡፡ በበኩሌ ለኪነጥበቡ ያደረኩትን አስተዋጽኦ በሚመለከት በመደበኝነት ሥራዬን ከመሥራት ጐን ለጐን ለበርካታ ዓመታት በአዕምሮዬ ሳመላልሰው የነበረውን ..ሔሮሺማን.. ፊልም ሠርቼ ሠጥቻለሁ፡፡ የአገሪቱ መሪ የኪነጥበቡን አካላት እንዲያነጋግሩ በተደረገ ጊዜ የሕዝብ ግንኙነት ሆኜ በርካታ ሥራዎችን ሠርቻለሁ፡፡ ገና ሌላም ነገር እሠራለሁ፡፡ በ2003 ዓ.ም አሳዛኝ የሆነ ነገር ጃፓን ላይ የተፈጠረው አደጋ ነው፡፡
በአረቡ አለም በተፈጠሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የእኛንም ጨምሮ በርካታ ዜጐች መጐዳታቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ሌላው በዘፈንና በፊልም ስናነሳው የነበረው አባይ ለልማትና ለሥራ መነሳቱ አስደሳች ነገር ነው፡፡
በ2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር የምትሆንበትን ነገር ጀምራለች፡፡ የሥራና የጀርባ አጥንት ላይ የሚቆምና ተፍ ተፍ የሚል ትውልድ ያለባት በመሆኑ የተሻሉ ነገሮች ይከሰታሉ፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ጠግባ የምታድር ሀገር እንድትሆን ምኞቴ ነው፡፡
ሠራዊት ፍቅሬ
የማስታወቂያ ባለሞያ፣ የፊልም ፀሐፊና ተዋናይ


..የሥልጣኔና የጥጋብ ዘመን እንዲሆን ምኞቴ ነው..
ካለፉት ጊዜያት አንፃር 2003 ስገመግመው ሥራዎች በጥራትና በብዛት እየተስፋፉ ነው፡፡ ሕዝቡ ትያትሮችን እየተመለከተ እና እየወደደ  መምጣቱ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ በእኔ በኩል በ2003 ዓ.ም በድርጅቴ የሠራሁት ..የሚስት ያለህ.. ትያትርን ነው፡፡ ከየካቲት ወር ጀምሮ በብሔራዊ ቲያትር እየታየ ነው፡፡ በፊልም ደረጃ ደግሞ ..ሔሮሺማ.. ላይ ሠርቻለሁ፡፡ ይሄንን በማድረጌ ለጥበቡ እድገት አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ እላለሁ፡፡ በጽሑፍና በትወና የምሳተፍባቸው ሥራዎች ደግሞ በ2004 ይቀጥላሉ፡፡
በ2003 ዓ.ም ካየሁት አስገራሚ ክስተት የአረቡ ዓለም ንቅናቄ ነው፡፡ ነፃነትን ማግኘት ደስ የሚል ነው፡፡ በጣም ያስደሰተኝ ደግሞ ግብጽ ውስጥ ከአመፁ በኋላ ከተማዋን ያፀዱት ነገር ከልቤ ቀርቷል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ መጽሐፍቶችን በአገራችን እንደልብ ማግኘታችን ሌላው ደስ እንዲለኝ ያደረገ ነገር ነው፡፡ በአገራችን ተከስቷል የምለው አስቸጋሪ ነገር የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ሰው እንዴት እንደሚኖር እየተገረምኩ ያለሁበት ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር የተሻለ ቀን እንዲያመጣ እናፍቃለሁ፡፡ ለምግብ የሚሆኑ ነገሮችን ለመግዛት መሠለፍ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ወዴት እየሄድን እንደሆነ አስባለሁ፡፡
በ2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ የጥጋብ ዓመት፣ የሥራ ውጤታማነት የሚታይበት፤ ወጣቱ የሥራ ፈጠራና የሥራ ተነሳሽነትን የሚያሳይበት ቀናነት የነገሰበት የሥልጣኔ፣ የጥጋብ ዘመን እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡
አዜብ ወርቁ
ደራሲና ተዋናይ


..ጥበብ በደንብ አድጓል..
በ2003 ዓ.ም ጥበብ በደንብ አድጓል፡፡ በሞያው ስላደረኩት አስተዋጽኦ ከእኔ ይልቅ ሰው ቢናገረው ይሻላል፡፡ በአጠቃላይ  በርካታ ሥራዎች በመሠራታቸው ግን ማደጉን እያየን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ስኬታማ የሆንበትን ጥሩ የቴሌቪዥን ድራማ ሠርተናል፡፡ እየሠራንም ነው፡፡
በዓመቱ አስቸጋሪ የምለው የኑሮ ውድነቱን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ2004 ዓ.ም ሠላም የሠፈነባት፤ ኑሮ ተስተካክሎ ከሠላም ጋር የምናያት ኢትዮጵያ እንድትሆን እመኛለሁ፡፡  
ሙሉአለም ታደሰ
የማስታወቂያ ባለሙያ እና ተዋናይ


..ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ትባላለች..
በ2003 ዓ.ም በቂ በሆነ ሁኔታ ጥበብ አድጓል፡፡ እኔ በግሌ ..አባይ ወይስ ቬጋስን.. ሠጥቻለሁ፡፡ ለእኔ በ2003 ዓ.ም አስቸጋሪ ወቅት የነበረው ..አባይ ወይስ ቬጋስ.. ፊልም ለማሳየት የተፈጠረው የአዳራሽ ግርግር ነበር፡፡
አስደሳቹ ደግሞ መሳካቱ ሲሆን ሌላው ሰባት ወር ደክሜ የሠራሁት ፊልም ከእነላፕቶፔ መሠረቁ አሳዛኙ ነገር ነው፡፡ በአገር ደረጃ አስደሳቹ የአባይ ግድብ መገንባቱ ነው፡፡
በአጭር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከምዕራባያውያን ቀድማ ቁጥር አንድ ትባላለች ብዬ አስባለሁ፡፡ መልካም ምኞቴ ይህ ነው፡፡
ቴዎድሮስ ተሾመ
የፊልም ዳሬክተር እና ተዋናይ

..የሚደርሰኝ አስተያየት አበረታች ነው..
የእኔ ሥራ ሁልጊዜ መሥራት ነው፡፡ ለእኔ የሚገባኝ በመሥራቴ ትምህርት እየተማርኩ እንዳለሁ ነው፡፡ ለሙያው ያደረኩትን አስተዋጽኦ በሚመለከት የሚያውቀው ተመልካቹ ነው፡፡ የሚደርሰኝ አስተያየት ደግሞ አበረታች ነው፡፡ ለእኔ ይሄንን ማግኘቴ በጣም ደስ የሚያሰኘኝ እና ወደ ተሻለ ነገር የሚገፋፋኝ ነው፡፡  እኔ እንደ ባለሞያ ዕድገቱን ሳይ ለምሳሌ ሔሮሺማ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ነው፣ ተመልካችም ጥሩ አስተያየት ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ሙያው ማደጉን ያሳያል፡፡
በዓለም ላይ የተከሰቱት የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድርቅ እና የተፈጥሮ አደጋዎች አሰቃቂ ክስተቶች ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሁሉም ሰው የሚደሰትባት፣ የሚጠግብባት ፍቅር እና ሠላም የሠፈነባት፤ አንድም ሰው ዳቦ አጥቶ የማይራብባት ኢትዮጵያን እመኛለሁ፡፡
መሠረት መብራቴ ተዋናይ
..ሁሉም የሥራውን ፍሬ የሚያገኝባት ሀገር እመኛለሁ..
በ2003 ዓ.ም ጥበብ አድጓል አላደገም የሚለውን ለመናገር ብዙ ነገሮች ያስፈልጋል፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው በርካታ ፊልሞች በመሠራታቸው ከሆነ፣ በብዙ መንገድ በርካታ ፊልሞች እየወጡ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ሙያው ትኩረት እየተሰጠው እያደገ መሆኑን እናያለን፡፡ ተዋናዩ የተሻለ ነገር የሚያሳይና ተዋናዩን ያከበረም ነው፡፡ ይሄንን ዕድገት ለማስቀጠል በበኩሌ እኔ ፕሮዲዩስ የማደርገው የራሴ ድርሰት ለማቅረብ፣ ከጓደኞቼ ጋር አዲስ ፊልም ለማበርከት እየተሯሯጥኩ ነው፡፡ በአገሪቱ ተከሰተ የምለው አስደሳችና አስቸጋሪ ለይቼ የማየው የተለየ ነገር የለም፡፡ በ2004 ዓ.ም መልካም ወሬ የሚወራባት፤ ሰው አብሮ ተባብሮ በቀናነት የሚተያይባት፤ ሁሉም የሥራውን ፍሬ የሚያገኝበት፤ የተሻለ ለውጥ የምናይበት ሀገር እንድትሆን እመኛለሁ፡፡
ሜሮን ጌትነት
ገጣሚ እና ተዋናይ


..ሥራ አጥ የማይኖርባት አገር እመኛለሁ..
የሙዚቃ ሙያው አድጓል፤ ጥሩ ባንዶች እየተቋቋሙ ነው፡፡ ቀደም ሲል በኪቦርድ ብቻ ይሠራ የነበረው አሁን  በቡድን በደንብ የሚጫወቱትን ሳይ ደስ ይለኛል፡፡
ገና ብዙ ነገሮች ቢቀሩትም መንግሥት በቅጂ መብት ዙሪያ ያደረገው ጥበቃ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ በግሌ ለሞያው አስተዋጽኦ እያደረኩ ነው፡፡ ለአዲሱ ዓመት ..የበረሀ ስደተኛ.. የሚል ነጠላ ዜማ ለቅቄያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ቴዲ አፍሮ ተጨምሮበት ዘፈኑን አሳድገን ክራር እና ማሲንቆ ጨምረን እንዲያስጨፍር አድርገን፣ በቆንጆ ሁኔታ ሁለት ሆነን ሠርተነዋል፡፡ ለብዙ ዘመን ሁለት ሰው መሥራት ቆሞ ነበር፤ አሁን ግን ከታላቁ ከማከብረው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ጋር ሠርቻለሁ፡፡
በ2003 ዓ.ም በኖርንበት አሜሪካ የደረሰው የተፈጥሮ አደጋ፤ ባልተለመደበት በቨርጂኒያና በዲሲ መድረሱ ያስፈራል፡፡ በሀገራችን የሚታየው የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት በጣም ያስከፋል፡፡ አስደሳቹ በአገራችን መንገድ እና በርካታ ቤቶች መሠራታቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ እግዚአብሔር የቀደሳት፤ ሕዝቡ አብሮ ተዛዝሎ እና ተቃቅፎ የሚኖርባት አገር ናት፡፡ እኔም በ2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ስራ አጥ የማይኖርባት፤ የትምህርት ቤት ጥራት የሚያድግባት፤ የተማረ ሥራ ሠርቶ የሚኖርባት አገር እንድሆን እመኝላታለሁ፡፡
ኩኩ ሰብስቤ
ድምፃዊ


..ሙዚቃውም አድማጩም ያደገበት ዓመት ነው..
ያለፈውን 2003 ዓ.ም ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው አንፃር እንዴት እንዳለፈ ስገመግመው፤ አድማጩ ጥራት ያለውን ሥራ የሚመርጥበት ጊዜ በመሆኑ የሙዚቃ ሞያውም አድማጩም ያደገበት ነው፡፡ ነገር ግን የቅጂ መብት ጥሰት በየቦታው በመንሠራፋቱ እና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች አጠቃላይ ኢንዱስትሪው ማደግ በሚገባው መጠን ሊያድግ አልቻለም፡፡ ከሞያው አንፃር እያበረከትኩ ያለሁትን አስተዋጽኦ በሚመለከት ከተጠየኩ ለ2004 ዓ.ም መግቢያ አዲስ የሙዚቃ አልበም አበረክታለሁ ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እና ከቅጂ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አዲስ ዓመትን ተሻግረዋል፡፡ ከዓመቱ በአንዱ ወር ግን እነዚህ አዳዲስ ሥራዎቼን ለሕዝብ ጆሮ አደርሳለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡  በሌላ በኩል ክለብ ውስጥም በሙዚቃው ዘርፍ በርካታ ጥሩ ነገሮችን ለመሥራት እየጣርኩ ነው፡፡  በ2003 ዓ.ም ቀን በቀን ጤነኛ ሆኜ ማሳለፌ አስደሳች ትውስታዬ ነው፡፡ ቴሌቭዥን በከፈትኩ ቁጥር የምሠማው የዓለም አለመረጋጋትና ችግር እንዲሁም በኢትዮጵያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት 2003ን በአስቸጋሪነቱ የሚያስታውሱኝ ክስተቶች ናቸው፡፡ 2004 ዓ.ም እርስ በእርስ መዋደድ ያለባት፤ ሰላም የበዛባት፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት እመኛለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም አዲስ ዓመት፡፡
ሸዋንዳኝ ኃይሉ
ድምፃዊ


..አስደሳቹ ጤና ኖሮኝ እየሮጥኩ መሆኑ ነው..
የ2003 ዓ.ም የሙያ ደረጃን ለመገምገም ጥናት ያስፈልጋል፡፡ በግሌ ያየሁት ነገር ከ2002 ዓ.ም አሁን ያለው ነገር የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለምሳሌ የቲያትር ተመልካች ሙሉ በሙሉ የጠፋበት ወቅት ነበር፡፡ ትኩረቱም ወደፊልም ነበር፡፡ አሁን ግን በትያትርም በፊልምም ተመልካች አለ፡፡ ዘፈንን በተመለከተ ከቅጅ መብት አኳያ ውጤታማ ነው ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ መጽሐፍትን በተመለከተ በሳምንት ሁለትና ሦስት መጽሐፎትን ያገኘንበት ዓመት ነበር፡፡ ጥበብ እንዲያድግ ያደረኩት አስተዋጽኦ ፀሎት ነው፡፡  ሌላው እኔ ከወጣትነቴ ጀምሮ ባለኝ አቅም በዘፈን፣ በትያትር፣ በፊልም በሁሉም መስክ ላይ እየሳተፍኩ ነው፡፡ ፍሬሽ ማንን የመሰለ ትያትር ተመልካች መሬት ላይ ተቀምጦ እያየ ነው፡፡ ይሄንን ሁሉ የምናደርገው ለጥበቡ ማደግ በሚደረገው አስተዋጽኦ ብቻ ሳይሆን ወጣቶችን በማበረታታትም ረገድ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም የዳቦ፣ የሽንኩርት የቲማቲም የነዳጅ ዋጋ እና የመሳሰሉት ነገሮች ዋጋ መወደድ አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ አስደሳቹ ጤና ኖሮኝ እየሮጥኩ መሆኑ ነው፡፡
በ2004 ዓ.ምን ለምለም ኢትዮጵያ ከሀገር አንስቶ እስከ ግለሰብ የታቀዱት ሐሳቦች ተከናውነው የምናይበት ዓመት ያድርገው፡፡
አዳነች ወልደገብርኤል
ተዋናይ ዳሬክተር




..ዓመቱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚደሰቱበት ይሁን..
ባሳለፍነው ዓመት ብዙ አዳዲስ ሙያተኞች በመምጣታቸው ፊልም ቤቶች ከውጭ ፊልሞች ይልቅ ለሀገር ውስጥ ፊልሞች በራቸውን እየከፈቱ ነው፡፡ ከኋላዬ የመጡትን በማበረታታትና በማድነቅ ጥሩ መንገድ የማሳየት፣ ባህል ጠብቀው ሀገር ወዳድ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታዬንም ቀጥዬበታለሁ፡፡ የቲቢ በሽታን ለመከላከል የተሰጠኝ ኃላፊነት ከ2003 ዓ.ም የደስታ ምንጮቼ አንዱ ነው፡፡ ብዙ መሥራት በሚችሉበት ዕድሜ ድንገት ያሸለቡ ሞያተኞች ያሳዝኑኛል፡፡ 2004 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚደሰቱበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም

..አኩሪ ባህሎቻችንን የምንጠብቅበት ይሁን..
የ..ሰው ለሰው.. ተከታታይ የቴሌቭዢን ድራማ መጀመርና ከሰለሞን ቦጋለ ጋር የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የክብር አምባሳደር መባላችን፣ ከዓመቱ አስደሳች አጋጣሚዎቼ ተጠቃሽ ነው፡፡ የቴሌቪዢን ድራማው ባተሌ ስላደረገኝ ከእነሙሉዓለም ጋር ልሠራ የነበረው ፊልም፣ አመለጠኝ ከምላቸው አሳዛኝ ገጠመኜ አንዱ ነው፡፡ የአባይ ግድብ ጉዳይ ከሀገሪቱ ትልቅ አጀንዳዎች ይሰለፋል፡፡ 2004 ዓ.ም መተሳሰባችንን አዳብረን አኩሪ ባህሎቻችንን የምንጠብቅበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
ሰለሞን ዓለሙ ፈለቀ
አርቲስት


..አዲሱ ዓመት የንባብ ዘመን ይሁን..
ዓለምአቀፍ የአፍሪካ ደራስያን ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱና ሐፍቱ የሀገራችንን የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ሥፍራዎች መጎብኘታቸው የዓመቱ የዘርፉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የአንጋፋ ሐፍትን ለምሳሌ የጋሽ ፀጋዬን እና የአብዬ መንግሥቱን ሥራዎች ማሳተሙ ሌላው ስኬት ነው፡፡ ለደራስያኑ ጉባኤ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ሐፊነቴ፣ በአስተባባሪነት የራሴን አስተዋዖ አድርጌአለሁ፡፡ በወረቀት ዋጋ መናር በርካታ ሥራዎች አለመቅረባቸው የቀረቡትም በኑሮ ውድነት የተጠበቀውን ያህል ገዢ አለማግኘታቸው ዓመቱን አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ በግል ሕይወቴ ከማፈቅራት እሌኒ መስፍን ጋር ጋብቻ መፈፀሜ እጅጉን አስደስቶኛል፡፡ አምና በዚህ ወቅት አርቲስት ፀሐይ ዮሐንስ ያለውን ደግሜ ልዋስና 2004 ዓ.ም የንባብ ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
እንዳለጌታ ከበደ
ደራሲ

 

Read 4835 times Last modified on Friday, 16 September 2011 05:54