Saturday, 22 December 2012 10:36

“ክትትል በጤና ጣቢያ ... ወሊድ ብሾፍቱ ሆስፒታል ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

“...ጤና ጣቢያዎች ወይንም ኬላዎች ላይ እናቶች የማይወልዱ እና ለመውለድ ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ከሆነ በዚያ የሚገኙ ባለሙያዎች ምን ሰርተው ነው የሚበሉት? ስለዚህ እያንዳንዱ/ዷ አዋላጅ ነርስ ወይንም የጤና ባለሙያ ባላቸው የስራራ ሰአት ወይንም ወቅት የተወሰኑ እናቶችን ማዋለድ ይጠበቅባቸዋል፡፡” ዶ/ር ዎድሮስ አድሀኖም /የቀድሞው የኢፊድሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር/
ዶ/ር ጀምበር መስቀሉ
ከላይ የተገለጸው አባባል የተነገረው ካለምክንያት አይደለም እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የእርግዝና ክትትል ቢያደርጉም ለመውለድ ግን የሚሄዱት ወደሆስፒታል መሆኑ የሚያስከትለውን የስራ ጫና እና በትክክልም በሆስፒታል ሊረዱ የሚገባቸውን እናቶች እድል የሚያጣብብ መሆኑን የሚመለከት ነው፡፡

የቀድሞው የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ሚኒስትር ዶ/ር ዎድሮስ አድሀኖም እንደተናገሩትም በቢሾፍቱ አካባቢ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና በሆስፒታሉ መካከል ያለው የታካሚዎች ቅብብል Referral ችግር እንዳለበት ለመመልከት ችለናል፡፡ እናቶችና ጨቅላ ሕጻናት በምን ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ የሚለውን ዳሰሳ ለመመልከት በሆስፒታሉ በተገኘንበት በውጭው አቆጣጠር ኦክቶበር /2012 ምንም የእናቶች ሞት በሆስፒታሉ ያልተመዘገበ ሲሆን ይልቁንም እንደ እንደ ችግር የተነሳው እናቶች በራሳቸው መንገድ ወደሆስፒታል እየመጡ የሚወልዱ ስለሆነ ጤና ጣቢያዎቹ ተገቢውን እርዳታ አላደረጉም የሚል ነው፡፡ በሆስፒታሉ በጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ጀምበሩ መስቀሉ እንደሚሉት...
“ብዙ እናቶች ጤና ጣብያ ላይ የቅድመ ወሊድ ክትትል ካላቸውና ጥቂት እናቶች በጤና ጣቢያው የሚወልዱ ከሆነ የቅድመ ወሊድ ክትትሉ የጥራት ችግር አለው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አንዲት እናት የት መውለድ እንዳለባት መወሰን ወይንም ቦታውን መምረጥ ያለባት በቅድመ ወሊድ ክትትል ጊዜ ነው ፡፡ አንዲት እናት የምትወልድበትን ቦታ መምረጥ ብቻ ሳይሆን የስነልቡና፣ የገንዘብ፣ የምግብ፣ የትራንስፖርት... ዝግጁነት እንዲሁም ምናልባት እንኩዋን በምትወልድበት ጊዜ ድንገተኛ ነገር ቢፈጠር ደም የሚሰጣት ማን እንደሆነ ጭምር ለይቶ እስከማወቅ ድረስ ዝግጅት ማድረግ ያለባት በእርግዝና ክትትል ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ስራዎች በጤና ጣቢያዎች በትክክል ስለማይሰሩ እናቶች የእርግዝና ክትትላቸውን በጤና ጣቢያ አድርገው ለመውለድ ግን ወደ ቢሾፍቱ ሆስፒታል መምጣታቸው ብዙ የሚያስቸግር ሁኔታን ፈጥሮአል፡፡ ምክንያቱም የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ የቆዩት ሌላ ቦታ ስለነበር በሆስፒታሉ ምንም ተመዝግቦ የሚገኝ ታሪክ የላቸውም፡፡ ስለዚህ የማዋለድ ተግባሩን ውስብስብ የሚያደርግ ሁኔታ በእጅጉ ይስተዋላል፡፡ እናትየው ለመውለድ በምጥ ላይ ሆና ምርመራው እንደ አዲስ ይሰራል፡፡ ሴትየዋ በምጥ ላይ ስለሆነች የሚደረገው ምርመራም መሰረታዊው እንጂ ሁሉን ነገር ለማወቅ የሚያስችል አይሆንም፡፡ ነገር ግን የእርግዝና ክትትል ስታደርግበት የነበረበት ጤና ጣቢያ ብትወልድ ወይንም ከጤና ጣብያው አቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞአት ወደሆስፒታሉ ከነታሪክዋ ብትተላለፍ የሚያክማት ባለሙያ በቀላሉ ከተጻፈው መረጃ በማየት እናትየውን በአፋጣኝ በተገቢው ሁኔታ መርዳት ይችላል”
ዶ/ር ደረጀ መልካ የቢሾፍቱ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው ፡፡ የእርግዝና ክትትል በየጤና ጣብያዎቹ የሚያደርጉ እናቶች በራሳቸው ፈቃድ ለመውለድ ወደሆስፒታል መምጣታቸው በአሰራር ምን አይነት ችግር እንደሚያስከትል አጋጣሚያቸውን አስታውሰዋል፡፡
“አንድ ጊዜ የተፈጠረ አጋጣሚ ነው፡፡ እናትየው ክትትል የምታደርገው በጤና ጣብያ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ለማዋለድ ሲቀበሉዋት የልጁን ትንፋሽ ማግኘት ስላልቻሉ ለባለቤትዋ ምንም ነገር ሳይነግሩ ወደ ቢሾፍቱ ሆስፒታል ያስተላልፉዋታል፡፡ ቢሾፍቱ ሆስፒታል እንደደረሰችም እንድትገላገል ሲደረግ ልጁዋ ግን በሕይወት አልነበረም፡፡ ባልተቤትዋ ልጁ የሞተው በሆስፒታሉ ሲወለድ ነው ብሎ ለእራሱ ስለተረዳ ትልቅ ጸብ ተፈጠረ፡፡ መጨረሻ ላይ ግን የሪፈራልየተላለፈችበት ወረቀቱ ሲታይ ልጁ ሕይወት እንዳልነበረው ተጽፎ ተገኘ፡፡ ጤና ጣብያዎቹ ወላድዋን ወደሆስፒታል ሲልኩዋት ምክንያቱን ለባልተቤትየው እንኩዋን ቢያስረዱ ኖሮ ችግሩ አይፈጠርም ነበር፡፡ ስለዚህም እንደዚህ ያሉ ችግሮች እንዳይደገሙ ለመነጋገር ሞክረን ለወደፊቱ እንደሚያስተካክሉ ቃል ገብተዋል፡፡ ሌላው ችግር ሁኔታው በሆስፒታሉ ባለሙያዎች ላይ ጫና ማስከተሉ ነው፡፡ የእርግዝና ክትትል በየጤና ጣቢያዎቹ አድርገው ነገር ግን ለመውለድ በቀጥታ ያለምንም የጤና ችግር ወደቢሾፍቱ ሆስፒታል መምጣታቸው በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን የስራ ጫና ከማክበዱም በላይ የጤና ባለሙያዎቹን እረፍት የሚነሳ በመሆኑ ብዙ ሐኪሞች ስራውን እየለቀቁ መሄዳቸው አንዱ ችግር ነው፡፡ ሌላው... በየጤና ጣቢያዎቹ የሚኖረው ችግር ለማዋለድ የሚጠቀሙባቸው እንደ ቫኪዩም የመሳሰሉ መርጃዎች እጥረትም ቢስተካከል ምናልባትም ለመውለድ ወደ ሆስፒታል የሚመጡ እናቶችን በጤናጣቢያዎቹ በማዋለድ ጫናውን ሊቀንስ ይችላል፡፡ በእርግጥ ብዙዎቹን የተጉዋደሉ ነገሮች ለማሟላት ከጤና ጽህፈት ቤቱ ጋር እየተነጋገርን ሲሆን በቅርብ ይስተካከላል ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እራሳቸውን ወደ ሆስፒታል ሪፈር እያደረጉ የሚመጡትን ወላዶች የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ ወደቆዩበት ጤና ጣብያ ተመልሰው እንዲሄዱ ማድረግ ስለማይቻል የስራ ጫናውን ተቋቁመን ስራውን በመስራት ላይ እንገኛለን”
በሆስፒታሉ የጤና መኮንን የሆኑት አቶ ዎድሮስ ደስታ እንደሚገልጹት
“እናቶች በብዛት የሚወልዱት በብሾፍቱ ሆስፒታል መሆኑን የሚያሳየው በአንድ ወር ከ200 /ሁለት መቶ በላይ ወሊድ መመዝገቡ ነው፡፡ የዚህን ምክንያት ለመረዳት ከቢሾፍቱ ጤና መምሪያ ጋር ለመነጋገር ሞክረናል፡፡ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ በከተማው ውስጥ ያሉት የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞችና ነርሶች በየቤቱ እየዞሩ ያሉትን እርጉዝ ሴቶችን በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ ይህም ጤና ጣቢያ ላይ ክትትል እንዲያደርጉና ክትትል ባደረጉበት ጤና ጣቢያ እንዲወልዱ ሁኔታዎች ለማመቻቸት እንዲሁም ለእናቶቹ ለማስረዳት ወይንም ለማሳመን ነው፡፡ ይህንን ሀላፊነት ማዘጋጃ ቤቱም በመውሰዱ ችግሩን ለመፍታት ሁኔታዎችን እያመቻቹ ይገኛሉ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ የቢሾፍቱ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የብዙ አንባቢዎች ችግር መሆኑን የሚያሳየው በአንድ ወቅት የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ተዎድሮስ አድሀኖም የተናገሩት እማኝ ነው፡፡ እሳቸውም እንደተናገሩት...ጤና ጣቢያዎች ወይንም ኬላዎች ላይ እናቶች የማይወልዱ እና ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ከሆነ በዚያ የሚገኙ ባለሙያዎች ምን ሰርተው ነው የሚበሉት? ስለዚህ እያንዳንዱ/ዷ አዋላጅ ነርስ ወይንም የጤና ባለሙያ ባላቸው የስራ ሰአት ወይንም ወቅት የተወሰኑ እናቶችን ማዋለድ ይጠበቅባቸዋል... ባሉት መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሆስፒታል መውለድ የሚፈልጉት ምናልባት እንኩዋን ችግር ቢፈጠር ብቃታ ያላቸው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች መኖራቸውን ስለሚያውቁ ሲሆን ይህንን ግን ክትትል በሚያደርጉበት በጤና ጣቢያው ለመውለድ ፈቃደኞች ቢሆኑ ምናልባት የሚያስቡት ችግር ቢፈጠር እንኩዋን ወደሆስፒታል የሚተላለፉ መሆኑን በሚገባ ሊነግሩዋቸው ይገባል”
በስተመጨረሻ ዶ/ር ጀምበሩ መስቀሉ እንደገለጹት፡-
“እናቶቹ ክትትል በሚያደርጉበት ጤና ጣቢያ መውለዳቸውን ትተው ወደሆስፒታል የሚመጡት በቤታቸው ለመውለድ ከሚቀሩት በጣም የተሸሉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሕይወታቸውን ለማዳን ተገቢውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ክትትል ወዳደረጉበት ጤና ጣቢያም ሆነ ወደሆስፒታል የማይመጡት እና በቤታቸው የሚቀሩት ምን ያህል እናቶች እንደሚጎዱ መገመት አሰቸጋሪ ይሆናል፡፡ የጤና ጣቢያዎቹ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በሚደረጉት ውይይቶች የጥራትን ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ አብዛኛውን የቅድመ ወሊድ ክትትል መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አንዲት እርጉዝ ሴት ክትባት ማግኘት አለባት፡፡
መሰረታዊ የሆኑ ምርራራዎችን ማግኘት አለባት
ለወሊድ ለእራራስዋ ቅድመ ዝግጅት እንድታደርግ ንቃትዋን ማዳበር ይገባል፡፡ ትራራንስፖርት...ገንዘብ... ወዘተ
የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ጤና ጉዳይ ትኩረት እንደሚገባው ቢታመንም እየተሰራ ያለው ግን በልማዳዊው አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጤና ጣቢያ ክትትል ስታደርግ የቆየች እናት በዚያ የተመዘገበው ታሪክ ምንም ሳያስጨንቃት ለመውለድ እራስዋን ወደሆስፒታል ማስተላለፍ ወይንም ለመውለድ በቤትዋ መቅረት ትክክለኛ እርምጃ አለመሆኑን እና አስቀድሞ ሲከታተላት ወደነበረው የጤና ተቋም በመሄድ መውለድ እንደሚገባቸው ለእናቶች ምክር መለገስ ይገባል፡፡

Read 4504 times