Saturday, 22 December 2012 10:10

ቻው! ቻው! News week

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ላለፉት 79 ዓመታት በፖለቲካና በንግድ፣በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጥበብና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዜናዎችን፣ትንተናዎችንና አስተያየቶችን ባማረና ጥልቀት ባለው ሁናቴ ለመላው ዓለም አንባቢዎቹ ሲያቀርብ የኖረው ሳምንታዊው የኒውስዊክ መጽሔት፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ (ታህሳስ 22 ቀን) በሚያቀርበው የመጨረሻ እትሙ የሕትመትን ዓለም ለዘላለሙ ይሰናበታል፡፡
ኒውስዊክ መጽሔትን በየሳምንቱ እየተቀበሉ የሚያትሙ፣ የሚያሽጉ፣ የሚጭኑና በመላው ዓለም ላሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎቹ የሚያሠራጩ ኩባንያዎች ከመጽሔቱ አሳታሚ ጋር የነበራቸው የሥራ ውል ከፈረንጆቹ የ2013 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ይቋረጣል፡፡ አሳሚታዎቹ የመጽሔቱን የወረቀት እትም ለማቋረጥ የወሠኑት ኒውስዊክን ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሮኒካዊ በሆነ ቅርጽ ብቻ እንዲቀርብ በመፈለጋቸው መሆኑ ታውቋል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ በመላው ዓለም ተሰራጭተው የሚገኙ የኒውስዊክ ደንበኞችም ከእንግዲህ መጽሔቱን የሚያገኙት እንደወትሮው በመጻሕፍት መሸጫ ወይም በፖስታ አድራሻቸው በኩል ሳይሆን በተንቀሳቃሽ ኮምፒውተሮቻቸው ወይም በእጅ ስልኮቻቸው መስኮት ብቻ ይሆናል፡፡ መጽሔቱን በዘመናዊ የዲጂታል ቅርጽ ብቻ እንዲወጣ ያስገደደው በቴክኖሎጂ እየተለወጠ ያለው ዓለም መሆኑን አዘጋጆቹ ይናገራሉ፡፡ 
ኒውስዊክ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ሲጓዝ ስለኖረ፣ ለመጽሔቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አዲስ አይደለም፡፡ ለዚህም አብነት የሚሆነው nesweek.com በተሠኘው ድረ አምባ (web site) አማካኝነት ከአንባቢያን ጋር ሲገናኝ ከአሥር ዓመት በላይ ያስቆጠረ በመሆኑ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በድረ ገፆቹ ለአንባቢዎቹ ይቀርቡ የነበሩት በመጽሔቱ የወረቀት እትም ላይ ለወጡ መጣጥፎች ተጨማሪ የሆኑ ድምጽና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ነበሩ፡፡
በኋለኛው ጊዜ ደግሞ መጽሔቱ ራሱ በዲጂታል ቅርጽ ተሰርቶ ከተጨማሪ ታሪክ እንዲሁም ድምጽና ተንቀሳቃሽ ምስል ጋር ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
ይህ አንጋፋ መጽሔት የተቋቋመው በአሜሪካ ሲሆን ባለቤቱና መሥራቹም የTime መጽሔት የውጭ ዜናዎች አርታኢ የነበረው ቶማስ ጄ ሲ ማርቲን ነበር፡፡ ማርቲን (News) እና (Week) የተሰኙት ሁለት የእንግሊዝኛ ቃላትን በሰረዝ አገናኝቶ News-week የተባለ መጽሔት መሠረተ፡፡ የመጽሔቱም የመጀመሪያ እትም እ.ኤ.አ የካቲት 17 ቀን 1933 ገበያ ላይ ዋለ፡፡ ኒውስዊክ በጊዜው ጠቅላላ አወቃቀሩን (Layout) የወረሰው በዘመኑ የ10 ዓመት ታላቁ ከነበረው ከ Time መጽሔት ነበር፡፡
ኒውስዊክ ከአራት ዓመት በኋላ Today ከተሰኘ መጽሔት ጋር ውሕደት ሲፈጽም በመጽሔቱ ስም መካከል የነበረው ሠርዝ ወጥቶ መጠሪያው እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀውን Newsweek የሚል ቅርጽ ያዘ፡፡
መጽሔቱ በተሻሻለ አቀራረብና በጠለቀ የትንተና ብቃት መታወቅ የጀመረው ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ከነበረው ጊዜ ወዲህ ነበር፡፡ በተለይ በዚህ ጦርነት ወቅት ባህር ማዶ ለዘመቱ የአሜሪካ ወታደሮች የተዘጋጀው በኪስ የሚያዝ እትም መጽሔቱ ከአሜሪካ ድንበር ውጪ እንዲታወቅ በር ከፍቶለታል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ ኒውስዊክ በየጊዜው ያልተቋረጠ መሻሻል ሲያሳይ በመቆየት፣ እ.ኤ.አ ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ ንብረትነቱ የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ አሳታሚ ሆነ፡፡
ከአዲሱ ባለቤቱ የወረሰው የጎለበተ የጋዜጠኝነት ልምድም የመጽሔቱን የአቀራረብ፣ የዘገባና የትንተና ብቃት ከፍ ወዳለ ደረጃ ስላሸጋገረው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአሜሪካ ቀዳሚ የዜና መጽሔቶች ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡
መጽሔቱ በዋሺንግተን ፖስት ባለቤትነት መተዳደር ከጀመረ ወዲህ ከመደበኛው የአሜሪካ እትሙ በተጨማሪ ለአውሮፓ አንባቢዎች በፈረንሳይ፣ ለእስያ አንባቢዎች ደግሞ በጃፓን እየተዘጋጀ በመቅረብ የተነባቢነት ሽፋኑን ከፍ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም ደግሞ ከመደበኛ የእንግሊዝኛ እትሙ ሌላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጃፓንኛ እትም አውጥቷል፡፡ በተከታታይም የስፓኒሽ እና የኮርያ ቋንቋ እትምችን በማሠራጨት እውነተኛ ዓለም አቀፍ መጽሔት ያሰኘውን ቅጽል ተጎናፅፏል፡፡
እነዚህና ሌሎቹ ገድሎቹ ተጨማምረው ኒውስዊክን በአሜሪካ ታትመው ከሚሠራጩትና (The Big Three) በሚል ቅጽል ከሚታወቁት ከTime መጽሔት እና የUS News & World Report ጎን በዐብይ የዜና መጽሄትነት ሊያሰልፉት በቅተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም አሜሪካዊው ባለጸጋ ሲድኒ ሃርማን እስከገዛው ጊዜ ድረስ መጽሔቱ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በዋሺንግተን ፖስት ባለቤትነት ሲተዳደር ቆይቷል፡፡
ኒውስዊክ በአዲሲ ባለቤቱ በሲድኒ ሃርማን እጅ ከገባ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም THE DAILY BEAST ከተሰኘውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎች ካሉት የዜና፣ የትንተናና የሐተታ ድረ አምባ ጋር ውሕደት ፈጸመ፡፡ አዲሱ ጥምረትም The Newsweek /Daily Beast Company የሚል ሥያሜ የያዘ ሲሆን የመጽሔቱ መጠሪያ ግን ሳይቀየር እንዳለ ቀጥሏል፡፡
ይህ ከዚህ ድረ አምባ ኩባንያ ጋር የተፈጸመ ውህደት፣ ኒውስዊክ መጽሔት ከዘመናዊ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጋር እንደፈጸመው ጋብቻ ሊቆጠር ይችላል፡፡ የመጽሔቱ ህትመት መቋረጥም በከፊል የዚህ ውህደት ውጤት ነው፡፡ ዴይሊ ቢስት ከኒውስዊክ ጋር ከመዋሀዱ አስቀድሞ በድረ ገጽ ብቻ በሚያቀርበው ዜናና ትንተና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎች ያፈራ እንደመሆኑ፣ መጽሔቱ ሕትመትን ተሰናብቶ ጓዙን በመጠቅለል ከዲጂታዊ መጽሔቶች አምባ እንዲገባ ተጽእኖ ለመፍጠር እንዳስቻለው ይታመናል፡፡
በመሆኑም ከመጪው የአውሮፓዉያኑ አዲስ ዓመት ከጃንዋሪ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኒውስዊክ የወረቀት እትም ወደ ዲጂታል ቅርጽ ተለውጦ፣ አንባቢዎች መጽሔቱን ለማግኘት የሚችሉት በኢንተርኔት አማካይነት በኮምፒውተር እና ድረ ገጽ በሚያስተናግዱ የእጅ ስልኮቻቸው ብቻ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ ታህሳስ 31 ቀን 2012 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የሚወጣው የኒውስዊክ መጽሔት እትምም በመጽሔቱ የ79 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመጨረሻው ቅጂ ይሆናል፡፡ የዴይሊ ቢስት መስራችና አሁን የኒውስዊክ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆነችው ቲና ብራውን ለመጽሔቱ እትም መታጠፍ መንስኤውን ስትናገር፣ የዘመናዊ ንባብ ልማድ በመለወጡ የተነሳ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ አንባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዲጂታል ወደሆኑ የንባብ አማራጮች እየተሳቡ መምጣታቸውን የጠቆመችው ቲና ብራውን፤ እኛ አንባቢዎቻችንን እየተከተልናቸው እንጂ እየመራናቸው አይደለም ብላለች፡፡
ዲጂታል የሆኑ ምንጮችን የማንበብ ልማድን አስመልክቶ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ 39 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን የዜና ምንጫቸው ኢንተርኔት ሲሆን፤ ከአምስቱ አሜሪካውያን ሁለቱ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን የሚያነቡት በተንቀሳቃሽ ኮምፒውተሮች ወይም በሞባይል ስልኮቻቸው አማካይነት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህም ሌላ በአሜሪካ 70 ሚሊዮን የሚደርስ ታብሌት ኮምፒውተር ተጠቃሚ ያለ ሲሆን ቁጥሩ በየጊዜው እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል፡፡
እነዚህ ጥናቶች የቲና ብራውንን አስተያየት የሚያጠናክሩ ከመሆናቸውም ሌላ በእርግጥም ዲጂታል እትሞች የመጪው ዘመን ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደሚሆኑ የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው፡፡ አሁን ብዙዎቹ ጋዜጦችና መጽሔቶች ዲጂታል እትሞቻቸውን በማውጣት ከወረቀት እትሞቻቸው ጋር መሳ ለመሳ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ሲሆኑ ይህም ወደፊት ለማይቀረው የዲጂታል ብቻ እትም የአንባቢዎቻቸውን እጅ በመያዝ እየመሩ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል፡፡
ከወረቀትና ከቀለም ወደ ዲጂታል አምባ የሚደረግ ሽግግርን ያጠኑ ተመልካቾች፤ በዲጂታል እትሞች ከሚደሰቱ አንባቢዎች በላይ የሚረኩት አሳታሚዎቻቸው ናቸው ይላሉ፡፡ ይኸውም ዲጂታል ሕትመት እንደ ወረቀት እትም ከማተሚያ ቤት ጋር መጓተት፣ ማሸግ እና በተለያየ የዓለም ክፍል ለሚገኙ አንባቢዎች የማሠራጨት ወጪና ድካም የሌለበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የዲጂታል እትም በረከትም ወደፊት ብዙ አሳታሚዎች የወረቀት እትሞቻቸውን እንዲያጥፉ እንደሚያበረታታ ይገመታል፡፡
የኒውስዊክ ባለቤት የሆነው The Newsweek/Daily Beast ኩባንያ መጽሔቱን ለማሳተም፣ እንዲሁም በመላው ዓለም ለሚገኙ አንባቢዎቹ ለማከፋፈልና ለማሠራጨት በየዓመቱ ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግን ኩባንያው አሁን የሚያቀርበውን አዲሱን ዲጂታል የኒውስዊክ እትም በየትኛውም የዓለም ክፍል ላሉ አንባቢዎቹ በትንሽ ገንዘብ፣ በፍጥነትና በአንድ ጊዜ ለማድረስ ስለሚያስችለው ወጪውን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስለታል፡፡
ዘመናዊው የዲጂታል ዓለም ከላይ ከተመለከቱት ጥቅሞቹ በተጨማሪ በመደበኛ የወረቀት ሕትመት ውስጥ የማይገኙና አንባቢዎችን የሚያጓጉ ጸጋዎች አሉት፡፡ ይህም የዲጂታል ሕትመት ጸጋ ድምጽንና ተንቀሳቃሽ ምሥልን ከጽሑፍ ጋር ያለ ችግር አካትቶ ለማውጣት መቻሉ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ የዲጂታል ሕትመት አንባቢዎች፣ አስተያየታቸውን ባነበቡበት ቅጽበት ማቅረብ መቻላቸው ደግም ሌላው የዲጂታል እትም በረከት ነው፡፡
አዲሱ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የሆነ የኒውስዊክ መጽሔት በመላው ዓለም ላሉ አንባቢያኑ የሚቀርበው መጽሔቱ የ80ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በሚያከብርበት ዋዜማ ላይ ነው፡፡ አዲሱ ዲጂታል መጽሔት የሚጠራው Newsweek Global በተሠኘ አዲስ ስም ሲሆን ለአንባቢያኑ የሚቀርበውም እንደወረቀት እትሙ ሁሉ በክፍያ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለአንድ ዓመት የመጽሔት ደንበኝነት የሚጠየቀው ዋጋ (52 ቅጂዎች) ለአይፓድ ከሆነ 25 ዶላር፤ በፕሪንተር ለመታተም የሚችል ሆኖ በላፕቶፕ ወይም በኮምፒውተር እንዲነበብ የሚዘጋጅ “እትም” ደግሞ የ40 ዶላር ዋጋ ተተምኖለታል፡፡
የኒውስዊክን ከህትመት ውጪ መሆን አስመልክታ የመጽሔቱ ዋጋ አዘጋጅ ቲና ብራውን በጥቅምት ወር ለሮይተርስ ስትናገር “… የወረቀት እትም ማውጣት ያረጀ ያፈጀ ዘዴ መስሎ ይታየኛል፡፡ ምንም እንኳን ለህትመት መጽሔት ያለኝ ፍቅር ያልቀነሰ ቢሆንም፣ አሁን የጋዜጠኝነት የሥራ ውጤትን ለማቅረብ ግን የወረቀት እትም ትክክለኛው ዘዴ ነው ብዬ አላምንም” ብላለች፡፡
አሁን የደረስንበት ጊዜ የወረቀት ሕትመት ፍጻሜ ዋዜማ እና የዲጂታል እትም መባቻ ላይ ይመስላል፡፡ ኒውስዊክ ከሕትመት ውጪ የመሆን ውሣኔ ሲወሰንበት የመጀመሪያው መጽሔት አይደለም፡፡ የወረቀት እትሞቻቸው ታጥፈው ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አምባ ከተቀላቀሉ በዓለም የታወቁ የሕትመት ውጤቶች መካከል ሊበርቲ መጽሔት፣ ሳተርዴይ ኢቭኒንግ ፖስት እና ዳንዲ የኮሚክ መጽሔት ይገኙበታል፡፡ በመጪዎቹ ጊዜያት ሌሎች የሕትመት ውጤቶችም የኒውስዊክን መንገድ እንደሚከተሉ ይገመታል፡፡ ኒውስዊክ መጽሔት መልካም ዘገባዎቹን፣ ትንተናዎቹንና አስተያየቶቹን ከትዝታዎቹ ጋር ትቶልን ከሕትመት መድረክ ይሰናበታል፡፡ የመጽሔት ወዳጆች በቅርቡ ከሕትመት ለመለያየት ፍላጎት እንደሌለው በገለጸው Time መጽሔት ጊዜያዊ መጽናናትን ለማግኘት ይችሉ ይሆናል፡፡ የሚሄድን መሸኘት፣ የሚመጣን መቀበል የኖረ የሰዎች ልማድ ነውና እኛም አሮጌውንና የለመድነውን ኒውስዊክ መጽሔትን ደህና ሰንብት እያልን፤ አዲሱን ኒውስዊክ ግሎባልን ደግሞ እንኳን ደህና መጣህ እንለዋለን - በወረቀት እትም ባናገኘውም፡፡

Read 3031 times