Saturday, 22 December 2012 10:07

“ወይ አነ! እድለይ ከምዚ ይኹን”?

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(4 votes)

ተስፋውን የተነጠቀው ሐፍቶም ግደይ
ሐፍቶም ሶስተኛውን ራስን የመግደል ሙከራ ካደረገ በኋላ ማን ወደ ሰንአ ማዕከላዊ ሆስፒታል እንደወሰደው ዛሬም ድረስ አያውቀውም፡፡ ለነገሩ እሱም ጠይቆ አያውቅም፡፡ ራሱን ማወቅ የቻለው ወደዚህ ሆስፒታል ከገባ ከሳምንት በኋላ ነበር፡፡ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ሁለት ወር ከአስራ ስምንት ቀን ሲታከም ከቆየ በኋላ ማገገም በመጀመሩ ወጣ፡፡ ለሶስት ጊዜ ያደረገው ራስን የመግደል ሙከራ ተጨማሪ ስቃይ ከማትረፍ በቀር ሊሳካለት ባለመቻሉ “ሞት እንኳ ሊሳካልኝ ያልቻለው ምናልባት በሰኞ ቀን ባልወለድ ይሆናል” ብሎ ሙከራውን ሁሉ እርግፍ አድርጐ ተወው፡፡ መቼም ህይወት ካለ ምንም ቢሆን ተስፋ መኖሩ አይቀር፡፡ ነገ ይዞት የሚመጣውን እጣ ፈንታ ማን ያውቃል?

አንድ አይነት ክንፍ ያላቸው ወፎች በአንድነት ይበራሉ እንደሚባለው፣በየመን ያሉ የእኛ ሰዎችም አንድነት አላቸው ወይም ሊመሰርቱ ይችላሉ ተብሎ በቀላሉ ሊገመት ይችላል፡፡ ሆኖም 
በአስቸጋሪና ማለቂያ በሌላቸው ፈተናዎች ከተሞላው የሀፍቶም የህይወት ስንክሳር ውስጥ አንድ ምዕራፍ እንኳ የማይሞላውን ይህን ተደጋጋሚ ራስን የማጥፋት ሙከራ ቅንጫቢ ታሪክ የሰሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከእሱ ጎን አልቆሙም፡፡ እኒህ የእሱ ቢጤ ስደተኞች ከመከራው እንዲጽናና እና ጫንቃው እንዲደነድንለት ከማገዝ ይልቅ “ድመት” የሚል ተጨማሪ ቅጥያ ስም ያወጡለት ሲሆን “እንደ ድመት ዘጠኝ ነፍስ ያለው ነው” እያሉ ይዘልፉትም ነበር፡፡
ሀፍቶም ግደይ የስደተኞች ስድብ ከሚያደርስበት ስቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል ያደረጋቸውን ሙከራዎችና ጥረቶች ሁሉ እያሰበ ሲቆዝምና ሆድ ሲብሰው፣ ፊቱን ከተኮራመቱ እግሮቹ መሃል ይቀብርና “ወይ አነ! ወይ አነ! እድለይ ከምዚ ይኹን?” (ወይ እኔ! እድሌ እንደዚህ ይሁን?) እያለ ያማርራል፡፡ ወዲያውም “ማማየ! ማማየ!” እያለ ወንድ ልጅ እንደዚህ ሊያለቅስ ይችላል ተብሎ በማይገመትበት ሁኔታ፣ መላ ሠውነቱ እየተንዘፈዘፈ ፊቱና ፊቱን የቀበረባቸው ጉልበቶቹ በእንባውና በንፍጡ እስኪዝረከረኩ ድረስ ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል፡፡ “ማማየ! ማማየ! ማሀረኒ!”
የሰው ልጅ ተወልጄ ያደግሁበት፣እትብቴ የተቀበረበት ነው ስለሚለው አካባቢ ያለው ስሜት ጥልቅ የመሆኑ ሚስጥር ድንቅ ነገር ነው፡፡ ከመሬት የተቀበረው እትብቱ ከዚያች መሬት ጋር ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነቱና ስሜቱ የተሳሠረበት የዝንተአለም ገመድ ነው፡፡ የማይጨው ከተማ ሀፍቶም ግደይ ተወልዶ ያደገባትና እትብቱ የተቀበረባት ከተማ ናት፡፡
ማይጨው የሀፍቶም ቤተሠብ፣ የእሱም የልጅነትና የለጋ ወጣትነት እድሜው ጠቅላላ ታሪክ የተፃፈባት መዝገብ ናት፡፡ እናም እትብቱ ለተቀበረባት የማይጨው ከተማ ያለው ፍቅርና ስሜት እጅጉን ረቂቅና ጥልቅ ነው፡፡ ማንም ቢሆን የሃፍቶምን የህይወት ታሪክ ድር ልምዝዝ ቢል መነሻውን የሚያገኘው ከዚህችው የማይጨው ከተማ ብቻ ነው፡፡
የዛሬ ሠላሳ አምስት አመት ገደማ በማይጨው ይገኙ ከነበሩት አነስተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች አንዱ የሀፍቶም አባት ነበር፡፡ እናቱ አደይ እግዚሐራ የቤት እመቤት ሲሆኑ አባቱ የሱቋ ዋና አንቀሳቃሽና ነጋዴ ነበሩ፡፡ ሀፍቶም አባቱ ከመጀመሪያ ሚስታቸው የወለዷቸው ሶስት እህቶቹና ሁለት ወንድሞቹ ሳይቆጠሩ ከእናቱ ከአደይ እግዚሀራ የተወለዱ ሠባት ወንድሞችና አምስት እህቶች አሉት፡፡
የእነዚህ ሁሉ ታላቅ ወንድምም እርሱ ነው፡፡ የአባቱ የንግድ ገቢ የሚያወላዳ ስላልነበረ ያንን ሁሉ ቤተሠብ በወጉ መመገብ ጨርሶ የማይቻል ነበር፡፡ ለሀፍቶምና ለተቀሩት ወንድምና እህቶቹ በምግብ እጥረት ከሚደርስባቸው ረሀብ ይልቅ ትልቁና ከባዱ ችግራቸው ልብስ ነበር፡፡
ጫማ ከበፊቱኑ የሚያስቡት ነገር ስላልነበር እንደ ችግር ቆጥረውት አያውቁም፡፡ የልብስ ነገር ግን ከፈተናዎቻቸው ሁሉ የላቀው ፈተና ነበር፡፡ የእሱ ታናናሽ እህቶች ከላያቸው ላይ ነትቦ ያለቀው ልብሳቸውና የተራቆተው ገላቸው በፈጠረባቸው መሳቀቅ የተነሳ፣ወደ ውጭ ለመውጣትና በተለይ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡
ሀፍቶም እንደ በኩር ልጅነቱ አባቱን ለማገዝ የተቻለውን ያህል ቢፍጨረጨርም የቤተሠቡን አስከፊ የድህነት ኑሮ ለማሻሻል አልቻለም፡፡ ትምህርቱን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጦ ያገኘውን አይነት የቀን ስራ እየሰራ በሚያገኛት ትንሽ ገቢ እናቱን መደጐም ቢችልም፣ መላ ቤተሠቡን ሊያጠግብ የሚችል እንጀራ ቢያንስ ለአንድ ቀን እንኳ በእናቱ ሌማት ውስጥ ማስቀመጥ እንደ ሰማይ ራቀው፡፡ በእንዲህ አይነት ሁናቴ ሀያ ሁለት አመት እስኪሞላው ድረስ አስከፊውንና ፈታኙን የድህነት ህይወት በማይጨው ከተማ ውስጥ ተጋፈጠ፡፡
በ1990 ዓ.ም ጥር ወር ውስጥ ግን እናቱ አባቱን ሲያገቡ ለጥሎሽ የተሠጣቸውንና የክፉ ቀን መውጫ ይሆናል ብለው ያስቀመጡትን የወርቅ ጌጥ ሰርቆ፣ እዚህ ሄድኩ ብሎ ሳይናገርና እንዲያ የሚወዳቸውን እናቱን “ደህና ዋይ” ብሎ ሳይሠናበት፣ ስራ ፍለጋ ማይጨው ከተማን ለቆ ወደ ደሴ ተጓዘ፡፡ በደሴ ከተማ ከእናቱ የሰረቀውን ወርቅ በመሸጥና የቀን ስራ እየሰራ በሚያገኛት የእለት ገቢ ህይወቱን ለመግፋት የተቻለውን ያህል እየለፋ፣ ለአምስት አመታት ያህል ዘለቀ፡፡ በ1995 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ግን ደሴን ለቆ የተሻለ ስራ ይገኝባታል እየተባለ ይወራላት ወደ ነበረችው ኮምቦልቻ ተዛወረ፡፡
ኮምቦልቻን ከደሴ ከተማ ጋር ሲያወዳድራት የተሻለች ከተማ ትሁንለት እንጂ ኑሮው ያው በቀን ስራ የሚገኝ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ነበር፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ለአምስት አመታት ኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ ከኖረ በኋላ፣ በ2000 ዓ.ም መስከረም እንደጠባ ኮምቦልቻን ለቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡
ወደ አዲስ አበባ ለመምጣቱ ዋነኛው ምክንያት የሚገፋው ኑሮ ከእጅ ወደአፍ መሆን ብቻ ሳይሆን ከእናቱ የሰረቀው ወርቅ ፀፀቱ መቆሚያና መቀመጫ ስለነሳው፣የተሻለ ስራ አግኝቶ ለመተካት ነበር፡፡ ሊነጋ ሲል ይጨልማል፡፡ ሀፍቶም ይህንን አባባል መጀመሪያ ማን እንደተናገረው አያውቀውም፡፡ ቁጥሩን ለይቶ ለማያውቀው ጊዜ የተለያዩ ሠዎች እየደጋገሙ ሲናገሩት ግን በሚገባ አዳምጧል፡፡ አባባሉ የዛሬው አስቸጋሪ ፈተናና ችግር የነገውን ስኬት አመላካች ነው ለማለት እንደሆነም ገብቶታል፡፡ ስለዚህም እሱም ሊነጋ ሲል ይጨልማል እያለና ስሜቱን በተስፋ ሞልቶ እያሟሟቀ፣አዲሱን የአዲስ አበባ ህይወት ብቻ ለብቻ መጋተሩን ቀጠለ፡፡
መርካቶ፣ ጐጃም በረንዳ፣ ቄራ፣ ኮተቤ፣ አቃቂ፣ ቃሊቲ ወዘተ--- ያገኘውን የጉልበት ስራ እየሰራ ኖሮባቸዋል፡፡ የሚያገኘው ገቢ ግን እንኳን የእናቱን ወርቅ ሊተካለት ይቅርና የቀን ቀለቡን እንኳ የሚችልለት አልነበረም፡፡ ግን መታገሉንና ከእለት ተዕለት የህይወት ፈተናዎቹ ጋር ግብግብ መግጠሙን አላቋረጠም፡፡ ሊነጋ ሲል ይጨልማል እያለ፡፡ ሀፍቶም በዚህ አይነት ሁኔታ ለሁለት አመት ታገለ፡፡ ይሁን እንጂ እንዲያ በተስፋና በታላቅ ትዕግስት የጠበቀው ንጋት የውሀ ሽታ ሆነበት፡፡
ብዙ ጭስ ግን ትንሽዬ እሳት፡፡ አንድ ቀን ጐጃም በረንዳ በሁለት የጭነት መኪናዎች ከጅቡቲ ተጭኖ የመጣ የወለልና የግድግዳ ንጣፍ ሴራሚክስና የባኞ ቤት እቃዎችን ከሌሎች ሠባት የቀን ሠራተኞች ጋር እያራገፈ ነበር የጭነት መኪናዎቹ ረዳቶች ወደሚያወሩት ነገር ጆሮውን ጣል ያደረገው፡፡
ረዳቶቹ ከዚህ በፊት እንደነሱ የጭነት መኪና ረዳት የነበረ፣አሁን ግን ጅቡቲ ውስጥ ሱቅና “የአበሻ ምግብ ቤት” ስለከፈተ ጓደኛቸው አንስተው በአድናቆት ሲያወሩ ሰማ፡፡
ወሬው ቀልቡን ለምን እንደሳበው ጨርሶ ባይረዳውም፣ መላ ስሜቱ በሙሉ በተለየ ሁኔታ ተነቃቃ፡፡ እናም ረዳቶቹ የሚያወሩትን ወሬ ስራዬ ብሎ እያዳመጣቸው መሆኑን እንዳያውቁበት የተቻለውን ያህል ተጠንቅቆ የተቻለውን ያህል ለማዳመጥ ሞከረ፡፡ ረዳቶቹ የዚያን እለት ሌላ ጊዜ ሲገናኙ ከሚያወጉት ወሬ የተለየ ነገር አላወጉም፡፡ በዚህ የተነሳም ፈረሳቸውን ለለማኙ ነዳይ መስጠታቸውን ልብ አላሉትም ነበር፡፡ ሀፍቶም ግን ከዚያን ቀን ጀምሮ ልቡ ወደ ጅቡቲ ሸፈተበት፡፡ ጅቡቲ የቀን ቅዠቱ የሌሊት ህልሙ ሆነችበት፡፡ እንዳሻው የሚጋልበው አዲስ ፈረስ አገኘ፡፡ ነገሩ ፈረሱን ለለማኙ ነዳይ ስጠው፣እርሱም ልቡ ፈንድቶ እስኪሞት ድረስ ይጋልበዋል እንደተባለው አይነት ነበር፡፡ ከመጠን ያለፈ ጥድፊያ ከመጠን ያለፈ መዘግየትንና መጓተትን ያስከትላል፡፡ ሀፍቶም ወደ ጅቡቲ ለመሄድ አለመጠን ቢጣደፍም ባሠበው ፍጥነት መጓዝ አልቻለም፡፡
ዋናው ማነቆው ለመጓጓዣ የሚሆን “ቅርሺ” ለማግኘት እጁ ማጠሩ ነበር፡፡ እጣ ፈንታ የምትወደው ደግሞ ለስላሶችንና አንገት ደፊዎችን ሳይሆን አመፀኞችን ብቻ ነው፡፡ ሀፍቶምም በኪሱ የቋጠራትን አንድ መቶ አስራ ሁለት ብር ብቻ እንደያዘ ለአፍታም እንኳ ልቡ ሳይመነታበት ቀልቡን ወጥራ ወደያዘችው ጅቡቲ ወደፊት! አለ፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጅቡቲ ለመግባት ያደረገው ጉዞ፣ራሱን የቻለና በአስገራሚ ትዕይንቶች የተሞላ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ረጅሙንና አስቸጋሪውን ጉዞ የጀመረው ከአዲስ አበባ በአውቶቡስ ተሳፍሮ ቀጥታ ወደ ደሴ በመሄድ ሲሆን ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ ያመራው ግን በእግሩ በመጓዝ ነበር፡፡
ኮምቦልቻ ከደረሰ በኋላ ለሶስት ቀናት ወደ አፋር ክልል የሚሄዱ መኪኖችን ሁሉ እስከቻሉት አካባቢ ድረስ እንዲወስዱት በመለመን ከባዘነ በኋላ፣በመጨረሻ የለስላሳ መጠጦች ጭኖ የሚጓዝ የጭነት መኪና ሹፌር ተባብሮት ሚሌ ድረስ ሸኘው፡፡ ሚሌ ከደረሰ በኋላ ግን እንደ ኮምቦልቻው መኪና በመለመን ጊዜውን ማጥፋት አልፈለገም፡፡ ልክ እንደ እብደት በሚቆጠር ውሳኔ ከሚሌ እስከ ሎጊያ ያለውን ረጅም ርቀት በዚያ በረሃ በእግሩ አስነካው፡፡ ሎጊያ ሲደርስ ለሶስት ቀናት እረፍት ካደረገ በኋላ እስከ ጅቡቲ ያለውንም መንገድ በእግሩ ለመሄድ እንደተያያዘው፣የወጪ ንግድ ሸቀጥ ጭነው በተከታታይ የራሳቸውን ቅፍለት ሠርተው የሚጓዙ በርካታ የጭነት መኪናዎችን አየ፡፡
እጁን እያውለበለበ እንዲያሳፍሩት ቢጠይቅም ከጉዳይ የጣፈው አሽከርካሪ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ማጣት ህግና ደንብን አያውቅም፡፡ እናም ሀፍቶም ወሰነ፡፡ ያመቸኛል ያለውን የጭነት መኪና መረጠና ከአሽከርካሪውና ከረዳቱ እይታ ተከልሎ ተንጠላጠለ፡፡ በጭነት መኪናው ላይ ተንጠላጥሎ ረጅም ርቀት ለመጓዝ ቻለ፡፡ ሰአታት ከፈጀ ጉዞ በኋላም አንድ አነስተኛ ከተማ ወለል ብሎ ታየው፡፡ በከተማው መግቢያ ላይ በርካታ የጭነት መኪናዎች ተሰልፈው ወደ ከተማው ለመግባት ተራቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ ሀፍቶም የከተማውን ስም ባያውቀውም ጅቡቲ እንደደረሰ ገመተ፡፡
ልቡ በደስታ ፈነደቀ፡፡ የተንጠላጠለበት የጭነት መኪና ተራው ደርሶ ወደ ከተማው መግቢያ ኬላ ሲቃረብ “አሊሳቢየህ” የሚል ጽሑፍ የተፃፈበት የብረት ታፔላ አየ፡፡ “ልክ ነው ጅቡቲ ነው፡፡ ጅቡቲ ደርሰናል” አለ፡፡ በደስታ ስሜት ልቡ የቆመ መሰለው፡፡ ራሱን አዞረው፡፡ ልቡንና ቀልቡን ከግራና ቀኝ ሠቅዛ ይዛው የቀን ቅዠትና የሌሊት ህልሙ ሆና የከረመችው ጅቡቲ እነሆ አሁን ከፊት ለፊቱ ተንጣልላ ተኝታለች፡፡ ሀፍቶም ከዚህ በኋላ ጨርሶ ጊዜ ማባከን አልፈለገም፡፡
የተሳፈረበት መኪናው መፈተሽ ሲጀምር ከተንጠላጠለበት ወደ መሬት ዱብ ብሎ ወረደ፡፡ ሚዛኑን ተቆጣጥሮ ልቡ በደስታ ስሜት እንደተሰለቀ፣ወደ ከተማዋ ለመግባት ሊሮጥ ቀና ሲል ግን ከአንድ ሰው ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠመ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 2556 times