አውቶቡሶቹ የቴሌቪዥን ስክሪን ያላቸው፣ የመንገደኛውን ምቾት የሚጠብቁና ለአገራችን አየር በሚስማማ መልኩ የተገጣጠሙ መሆናቸውንም አቶ አዲል ገልፀዋል ፡፡ ድርጅቱ በመጀመሪያው ዙር ሃያ አምስት አውቶቡሶችን ወደ አገር ውስጥ ያስገባ ሲሆን በቀጣዮቹ አራትና አምስት ወራት ሌሎች ሃያ አምስት አውቶቡሶችን ለማስገባት እንዳቀደ ተገልጿል፡፡
አውቶቡሶቹ የሚሰማሩበት መስመርና የትራንስፖርት ዋጋው በቀጣዩ ሣምንት ይፋ የሚደረግ ሲሆን የአገልግሎት ክፍያው የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበና ድርጅቱንም አትራፊ በሚያደርግ መልኩ እንደሚተመን የተናገሩት አቶ አዲል፤ ዋጋው ከሃይገር ባስ ከፍ ያለ፣ ከታክሲ ያነሰ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
አሊያንስ ትራንስፖርት ሰርቪስ አክስዮን ማህበር ከአመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር የመቅረፍ አላማ አንግቦ የተቋቋመና ታዋቂ ባለሀብቶችና አርቲስቶች የሚገኙበት አክሲዮን ማህበር ነው፡፡
በአዲስ አበባ በተለይ በስራ ሰዓት መግቢያና መውጪያ ላይ ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም የተነሳ ነዋሪዎች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡