Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 December 2012 13:57

“በወተት ብቻ አይደለም ያደግሁት፤ በቡናም ነው” - አቶ አሊ ሁሴን Featured

Written by 
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ነው ለሽልማት የበቃችሁት?
አልፎዝ ከ95 በመቶ በላይ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ነው የሚታወቀው፡፡ ለሽልማት የበቃነው የንግድ ስራ ሂደታችን ተገምግሞ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የቡናና የግብርና ምርቶች ወደተለያዩ አገራት በመላክ ለአገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገባታችን ነው፡፡በዚህም ከንግድ ሚኒስቴር ድርጅታችን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ከቡና ሌላ ምንድን ነው ወደ ውጭ የምትልኳቸው ምርቶች?

በቀዳሚነት ቡና ቢሆንም ሰሊጥና የተለያዩ ቅመማቅመሞችንም እንልካለን፡፡ በእርግጥ በአገር ደረጃም ትልቁ ምርትና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘው ቡና ነው፡፡ አሁን ድርጅታችን እንደውም ወደ ቡና ልማቱ ገብቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ልማቱ ላይ አልነበርንም፡፡ ቡናውን ከአነስተኛ ገበሬዎች ላይ እየሰበሰብን ነበር ለዓለም ገበያ የምናቀርበው፡፡ አሁን ግን በኦሮሚያና በደቡብ ክልል በሰፊው ልማቱ ውስጥ ገብተናል፡፡
በአገራችን ሰፋፊ የቡና ልማት እርሻዎች የሉም፡፡ ከተለያዩ ትናንሽ እርሻዎች ላይ የተሰበሰበው ነው ለገበያ የሚቀርበው፡፡
በዓመት አንድ ጊዜ ነው የሚተከለው፡፡ ቡና አቅራቢ የሚባል አለ፡፡ ቡናውን ከየገበሬዎቹ አሰባስቦ ወደ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ያመጣልናል፡፡ ኤክስፖርተሮች ደግሞ ቡናውን ገዝተን በራሳችን ዘመናዊ መሣሪያ አዘጋጅተንና ጥራቱን ጠብቀን ወደሚፈለግበት አገር እንልካለን፡፡
በአለፈው አስር ዓመት ከቡና ጋር በደንብ ተዋውቀናል፡፡ እውቀቱን ስናጐለብት ነው የቆየነው፡፡ የቡና ልማት ትልቅ ስራ ነው፡፡ እኛ ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ገዢዎች አሉን፡፡
እናም ስለ ቡና መናገር፣ ማስተዋወቅ ጀምረናል፡፡ ያን ስናደርግ ደግሞ የራሳችን የቡና ልማት ያስፈልገናል ብለን ቡናው ላይ በስፋት ስራ ጀምረናል፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ በቂና ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርትን አላት?
ለዚህም ነው ትላልቅ የቡና እርሻ እንደሚያስፈልገን አስበን በቡና ልማቱም ላይ በመግባት አቅማችንን ለማሳደግ እየሠራን ያለነው፡፡ የአገራችን የቡና ገቢ አሁን ባለበት ሁኔታ መቀጠል የለበትም፡፡ በትላልቅና ሰፋፊ እርሻዎች መልማት አለበት፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከቆምን አለም አቀፍ የቡና ገቢያችን ይወርዳል፡፡ አለም ላይ የቡና አቅርቦት ፍላጐቱ አለ፡ እኛም በሰፊው ማልማት ጠቀሜታ እንዳለው ስላመንን ነው ወደ ቡና እርሻ የገባነው፡፡ በደቡብ ክልል ቦንጋ፤ በኦሮሚያ ጅማ አካባቢ በ2ሺ ሄክታር መሬት ላይ የቡና እርሻ ልማት ጀምረናል፡፡ ተጨማሪ የመሬት ጥያቄዎችን በደቡብ ክልልም በኦሮሚያም ጠይቀናል፡፡ ከገባንበት አይቀር በስፋት ማልማት ነው የምንፈልገው፡፡ ችግሩ ግን ለቡና ልማት የሚሆን መሬት የለም፡፡ በአብዛኛው ለቡና የሚመቸው መሬት በደን የተሸፈነ ነው፡፡ በደቡብም በኦሮሚያም መሬት ስንጠይቅ በደን የተያዘ ነው፤ ለቡና ልማት የለም የሚባል ነገር አለ፡፡ ደኑን ቢሰጡን ቡናውንም እያለማን ደኑን መጠበቅ እንችላለን፡፡
ለቡናው ልማት የሚመቹ አካባቢዎች ደግሞ እነዚህ የጠቀ ስኳቸው ከክልሎች ናቸው፡፡
በደቡብና በኦሮሚያ ክልል ባሉት የቡና እርሻ ልማቶች ላይ ስንት ሰራተኞች ተቀጥረዋል?
ኩባንያው የቀን ሰራተኞችን ጨምሮ እስከ 2ሺ ሠራተኞች ቀጥሮ ያስተዳድራል፡፡ ገና ድርጅታችንም እየሰፋና እያደገ ስለሚሄድ የበለጠ ሠራተኞችንም ቀጥረን የማሰራት ፍላጐቱ ነው ያለን፡፡
እንዴት ነው ወደዚህ ስራ የገቡት?
የኤክስፖርቱን ስራ በጣም ነው የምወደው፡፡ ከብዙ ዓለም ጋር ያገናኛል፡፡ ገበያ ለማፈላለግ፣ የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት ብዙ ቦታ ያስኬዳል፡፡ በዛ ምክንያት ስራውን እወደዋለሁ፡፡
እስከሰራሁ ድረስ ደግሞ አገሬን የምጠቅምበትን መንገድ ነው የማስበው፡፡ ማንኛውንም ስራ ስሰራ ገንዘብ ለማግኘት ነው፣ ችግር የለውም ገንዘብም ይገኝበታል፡፡ ግን ገንዘብም እያገኘሁ አገሬን መርዳት ፣ ህብረተሰቡን ማገዝ የምችልበትን ነገር ነበር የምመኘው፡፡ ጥቃቅን ገበሬዎች ቡና አልምተው ገበያ ፈልገው መሸጥ የለባቸውም፡፡ ከእነሱ የሚመጣውን ምርት ወደ ገንዘብ መለወጥ መቻል እኔን ያስደስተኛል፡፡ ስሸጥ ገበሬውን እረዳለሁ፤ የውጭ ምንዛሬ ለአገሬ አስገባለሁ፤ እኔ ራሴም አድጋለሁ፡፡ ተጠቃሚ ነኝ፡፡ የምሠራውን ስራ ከብዙ አቅጣጫ ነው የማየው፡፡ በዚህ ስራ ከተሰማራሁ ከአስር ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡
ከልጅነቴ ጀምሮ ከቡና ጋር ሰፊ ትስስር አለኝ፡፡ እናቴ ስትነግረኝ ልጅ ሆኜ ታላላቆቼ ቡና ሲጠጡ ነጥቄያቸው ነበር የምጠጣው፡፡ በወተት ብቻ አይደለም ያደግሁት፤ በቡናም ነው፡፡ መልኬንም ጠየም ያደረገው እሱ ሳይሆን አይቀርም (ሳቅ)፡፡ አሁንም ጠዋት ከቤት ስወጣ ቡና ሳልጠጣ አልወጣም የፔርሙዝ ቡና አይደለም፡፡ በኢትዮጵያዊ መልክ ተቆልቶ እየጨሰ አጠገቤ ቡናው ሲሸተኝ ነው ደስ የሚለኝ፡ለምሳም ወደ ቤቴ ስገባ ቡና ይፈላል፡፡ ማታም እንደዛው፡፡ ማታ ቡና ከጠጣሁ እንቅልፍ አይወስደኝም የሚሉ አሉ፡፡ አሁን ታላቅ ወንድሜ ቡና ላይ ነው የሚሠራው፡፡ ከአስር ሰዓት በኋላ ቡና አይጠጣም፤ እንቅልፍ አይወስደኝም ነው የሚለው፡፡ እኔ ግን ቡና ጠጥቼም መተኛት ከፈለግሁ እተኛለሁ፤ ለቡና ለየት ያለ ፍቅር አለኝ፡፡ ለዚህ ነው ቡና ላይ በትጋት የምሰራው፡፡
ቤተሰብዎ ቡና ላይ ይሰራ ነበር?
አባቴ ቡና እያለማ ይነግድ ነበር፡፡ አያቴም እንደዚሁ የቡና ትላልቅ ባለሀብቶች ከሚባሉት አንዱ ነበር - በሃይለስላሴ ጊዜ፡በደርግ ተወረሱ፡፡ ትላልቅ የቡና ልማቶች ነበሯቸው፡፡ ያው ሳድግ ጀምሮ ከቡና አልተለየሁም፡፡ ከመሞቱ በፊት “ቡናን ትልቅ ነገር አድርገህ መስራት አለብህ፤ የሰው ልጅ ስራ ቡና ነው” እያለ ይመክረኝ ነበር፡፡
የርስዎ አባት የቡና ንግድ በአገር ውስጥ ነው ወይስ ውጭ?
ከጅማ አዲስ አበባ ጭኖ እየመጣ ይሸጥ ነበር፡፡ ለውጭ ቡና ላኪዎች፡፡ ልጅ ሆኜ የሚሸጥበት ቦታ አብሬ ሄጄ ሲያስረክብ አይ ነበር፡፡ ከመኪና ላይ ሲወርድ ልጅ ነው ብለው ማንም ከጉዳይም አይጥፈኝም፡፡ ግን ሳልታዘዝ ከመኪና የሚወርደውን የቡና ኩንታል አንድ፣ ሁለት… ብዬ እመዘግብ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ እንደተለመደው ቡናውን ከመኪና አውርደው ሲጨርሱ ስህተት ተፈጥሮባቸው ግራ ተጋቡ፡፡ በኋላ ግን እኔ ይሄው ቆጥሬያለሁ ብዬ ሰጠኋቸው፡፡ በኋላ ቼክ ሲደረግ እኔ ልክ ነበርኩ፡፡ አባቴ በጣም ተደነቀ፡፡ ትምህርት ቤትም ሆኜ ንግድ በጣም እወድ ነበር፡፡
ንግድ ስልሽ ሰርቶ ማትረፍ ነው፡፡ አባቴ አንድ ጊዜ ከአዲስ አበባ መጫወቻ ገዝቶልኝ ነበር - ፊልም እየቀያየረ አጉልቶ የሚያሳይ ካሜራ ነው፡፡ መጫወቻውን ካሜራ ፍራንክ እየተቀበልኩ ለሰዎች አሳይበት ጀመርኩ፡፡ ብዙ ሳንቲም አጠራቀምኩ፡፡ እቤት “የሳንቲም ማስቀመጫ ባንክ ስሩልኝ” ብዬ ተሠራልኝ፡፡ በርካታ ሳንቲም ካጠራቀምኩ በኋላ አውጥቼ ሳየው ብዙ ሆኗል፡፡ የምትወልድ ፍየል ይገዛልኝ አልኩና ተገዛልኝ፡፡ ፍየሏ ወልዳ ወልዳ ከተማውን አጥለቀለቀችው፡፡
“የሁሴን ሃጂ ፍየሎች ከተማውን ሞሉት፤ አጥለቀለቁት” በሚል ክስ መጣ፡፡ እኔ ልጅ ስለነበርኩ ሁኔታውን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ በዚህ የተነሳ ፍየሎቹ ተሸጡብኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ንግድ ተሰጥኦዬ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይኸው ዛሬ የልጅነት ህልሜ እውን ሆነ፡፡
የትምህርትስ ነገር፤ የንግድ ተሰጥኦዎን በትምህርት ለማዳበር ሞክረዋል?
በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን ከ12ኛ ክፍል በኋላ በትምህርቴ መቀጠል አልፈለግሁም፡፡ የንግድን ሥራዬን የሚያሳድግልኝ አጫጭር ኮርሶችን ወስጃለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ሳለሁ በሂሳብ ትምህርት በጣም ጎበዝ ነበርኩ፡፡ የተሰጠኝን የክፍል ስራ ከክፍል ልጆች ቀድሜ ሰርቼ አሳርም ነበር፡፡
ለቤተሰቦችዎት ስንተኛ ልጅ ነዎት?
አስር ወንድምና እህቶች አሉኝ፤ እኔ ሶስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ትንሽ ደፈር ስለምል ት/ቤትም ሆኜ ጓደኞቼ አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ ውሎዬ ከትልልቆቼ ጋር ነበር፡፡ አስተማሪዎች ፈተና ሲያርሙ አብሬያቸው ሆኜ አየዋለሁ፡፡ በልጅነቴ እንኳን ከእኔ የተሻለ ሰው ጋር ነበር የምውለው፡፡ ከእነሱ ማወቅ መማር የምፈልገው ነገር ነበር፡፡ ከእኔ በታች ያለውን መርዳት፤ ከእኔ በላይ ያለውን ወዳጅ ማድረግ እወድ ነበር፡፡ በቅርቡ ክቡር ፕሬዚዳት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ቢሮ የጃፓን ኢንቨስተሮችን ይዣቸው መሄድ ነበረብኝ፡፡ የአገራቸው ሚዲያዎችን ይዘው ነበር የመጡት፡፡ ከፕሬዚደንቱ ጋር ስንወያይ እሳቸው “He is my friend” እያሉ ያወራሉ - ወደ እኔ እየጠቆሙ፡፡ ጃፓኖቹ በፕሬዚደንቱ ንግግር በጣም ተደንቀው ነበር፡፡ በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ የስራ ሰው ነው፤ ጐበዝ ነው፤ አገር ወዳድ ነው›› ለማለት ፈልገው ነው፡፡
እድሜዎት ስንት ነው? ወደ ቢዝነስ የገቡት ከቤተሰብ በወረሱት ገንዘብ ነው ወይስ…?
እንግዲህ ወደ 40ዎች አካባቢ ይሆነኛል፡፡ የሚገርምሽ ከአባቴ አምስት ሳንቲም ቆጥሬ አልወሰድኩም፡፡ ዕውቀትና ልምድ ነው የወረስኩት፡፡ ሶስተኛ ትውልድ (third generation) የሚል አባባል አለኝ፡፡ ከአያቴ፣ ከአባቴ፣ ወደ እኔ የወረደ የስራ ጥበብን ለማሳየት ነው ገንዘባቸውን አይደለም የወረስኩት፡፡
ዕውቀታቸውን ልምዳቸውን ነው፡፡ ወንድም እህቶቼ አስር ነን፡፡ አባቴ ሲሞት ዘጠኙ ብቻ ናቸው ንብረት እንዲወስዱ ያደረግሁት፡፡ እኔ አንድ ብር አልወሰድኩም፡፡ መስራት መታገል እንዳለብኝ አምን ነበር፡፡
በቀጥታ ወደ ቡና ንግድ ነው የገቡት?
አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ከተለያዩ አገሮች ስፔር ፓርቶችን እና ሌሎች እቃዎችን ማምጣት ጀመርኩ፡፡ ግን ህልሜ በቡና ስራ መሰማራት ነበር፡፡ ሰዎችን ማግኘት ማውራት፣ መንገዶችን ማጥናት ነበር የመጀመሪያ ስራዬ፡፡ የኤክስፖርት ሥራ ለመጀመር ወደ ውጪ መሄድ ነበረብኝ፡፡ እናም ወደ ሳዑዲ አረብያ ሄድኩና የመኪና መለዋወጫዎችና አንዳንድ ጨርቃጨርቆች፣ አልባሳት ማምጣት ጀመርኩ፡፡ ከገበያው ጋር መተዋወቅ ጀመርኩ፡፡ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ከገመገምኩ በኋላ የልጅነት ህልሜ የሆነውን የቡና ንግድ ለመጀመር ዝግጅቴን አጠናቀቅሁ፡፡ ወደ ሳዑዲ አረብያ እየሄድኩ ሳለ አውሮፕላን ውስጥ ከአንድ ባለሀብት ጋር ተዋወቅሁ፡፡ ገንዘብ ስላለኝ ወይንም ስለሌለኝ አይደለም፡፡ ሁልጊዜ አውሮፕላን ውስጥ ቢዝነስ ክላስ ነበር የምቀመጠው፡፡ ያን የማደርገው ጉዞዬን እንደ አንድ የስራ አካል ስለምቆጥረው ነው፡፡ ከሰው ጋር እንደሚያገናኘኝ አስብ ነበር፡፡ ቢዝነስ ክላስ ለእኔ አዳዲስ የቢዝነስ እድሎች የሚፈጠሩበት መድረክ ነው፡፡ በዚህ የሚጠቀሙት ባለስልጣናትና በአብዛኛው ደግሞ የቢዝነስ ሰዎች ናቸው፡፡ ቡናን ‹‹አጀንዳዬ›› ብዬ ስለያዝኩት ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ገለፃ አደርጋለሁ፡፡ ቢዝነስ ክላሱ ውስጥ ያገኘሁት የሳዑዲ ባለሀብት፤ ጋር ስንጨዋወት ፍላጐቱን አወቅሁኝ፡፡ ከኢትዮጵያ የስጋ ምርት መውሰድ ይፈልግ ነበር፡፡ ከሰዎች ጋር መስራት ጀምሮ አልተሳካለትም፡፡ እና እየተበባጨ ነገረኝ፡፡ ስለ ንግድ ከተጨዋወትንና ከተግባባን በኋላ ‹‹እባክህ እንስራ›› አለኝ፡፡
‹‹እኔ ገና ኤክስፖርት ስራ አልጀመረኩም፤ ግን የመስራት ፍላጎት ስላለኝ በደንብ እሰራዋለሁ›› አልኩት፡፡ ተስማማን፡፡ ተግባብተን በሚገርም ሁኔታ በደንብ ሰራነው፡፡ እኔ አቅራቢ፤ እሱ ተቀባይ ሆኖ፡፡ 24 ሰዓት ነበር የምሰራው፡፡ ከልቤ ስለምሰራ ውጤት አገኘሁበት፤ በመንግስትም ተሸለምኩ፡፡ ከሳዑዲ ባለሀብቱ ጋር ጥቂት አመት ከሰራን በኋላ ‹‹በቃኝ አንተ መስራት ከፈለግህ ቀጥል›› አለኝ፡፡ ‹‹እኔማ አላቆምም›› ብየው ስራውን ቀጠልኩ፡፡ የኤክስፖርት ስራ መስመሩን ይዣለሁ፤ የገበያውን ውል አግኝቼዋለሁ፡፡ በመሃል ግን ቡናዬ ናፈቀችኝ፡፡ ቀዩን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማምጣት የቡና ማበጠሪያ ቦታ ጅማ ውስጥ ተከራየሁ፡፡ ሁለት ኮንቴነር ቡና (36 ሜትሪክ ቶን) አዘጋጀሁና ለመሸጥ ወደ አዲስ አበባ በመጣው ገበያ እምቢ አለ፡፡ የሚገዛኝ አጣሁ፡፡ ቡና ለእኔ ወንድሜ ነው፡፡ ቡና በወንድሙ አይጨክንምና አይጨክንብኝም ብዬ ጠረቴን ቀጠልኩ፡፡ የምሸጠውን የቡና አይነት ቋጥሬ የገዥዎችን ስም ዝርዝር ይዤ ከሃገር ወጣሁ፡፡ ወደ ሳዑዲ ሄድኩ - የቡና ገዥዎችን በር ማንኳኳት ጀመርኩ፡፡ አንድ የሳዑዲ ባለሀብት ቢሮ ቀጠሮ አስይዤ ገባሁ፡፡ ከፍተኛ የቡና ኤክስፖርተር ነኝ ብዬ አላወራሁም፡፡ እጄ ላይ ይሄን የመሰለ ቡና ይዤ ገዥ አጣሁ፤ አግዘኝ” አልኩት፡፡
“የያዝከው ቡና በጣም ጥሩ ቡና ነው፤ እንደዚህ አይነት ቡና ገዝተን አናውቅም አዲስ ቡና ገበያው ቶሎ አይለምድልንም፤ የአንተ ሁኔታ ስለተመቸኝ ግን እገዛዋለሁ” አለኝ፡፡ ዋጋ ጠየቀኝ፤ ያልኩትን ገንዘብ ተቀበለኝ፡፡ ወደ ሃገሬ በርሬ መጣሁ፡፡ የኤክስፖርት ፈቃዴን አወጣሁና ስራውን ጀመርኩ፡፡ የእኔ ቡና በመርከብ ተጭኖ ሄደ፤ ለዚህም በቃሁ ብዬ ደስ አለኝ፡፡ በዚህ አይነት ነው ወደ ስራው የገባሁት፡፡
ስለ ንግድ ሰራዊት እድገት ይንገሩን… ውጣ ውረዱ ምን ይመስል ነበር?
አሁን ያሸለመኝም 12 ሺህ ሜትሪክ ቶን ልኬ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ውስጥ ስትሰሪ ሙሉ ስራውን ማወቅ አለብሽ፡፡
በቡና ውስጥ ያሉትን ስራዎች በሙሉ አውቄ መገኘት አለብኝ የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ስለቡና ማወቅ፣ ማጥናት ገበያው ምን ይመስላል የሚለውን መንገዶቹን መሰለል ጀመርኩ፡፡ መጀመርያ ላይ ለማልማት አቅም አልነበረኝም፡፡ አሁን በጥናት እርሻውን ጀምሬዋለሁ፡፡ የለማውን ቡና ለመላክ ፕሮሰስ ስላለው በ1997 ዓ.ም የቡና ማደራጃና ማከማቻ አዲስ አበባ ላይ ከፈትኩ፡፡ 30 ሺህ ቶን ቡና ማዘጋጀት በሚችል ዘመናዊ መሳሪያ እየታገዝኩ ቡናውን መላክ ጀመርኩ፡፡ ሐረር ላይ ደግሞ 7 ሺህ 5መቶ ቶን ማምረት የሚያስችል መሳሪያ ተከልኩ፡፡ ሳዑዲ የሐረር ቡና ነው የሚፈለገው፡፡ እናም ኢትዮጵያ ውስጥ የተቆላ፣ የተፈጨ፣ የታሸገ እና እሴት የተጨመረበት ቡና ማምረት አለብኝ ብዬ ተነሳሁ፡፡ በወቅቱ የመንግስትም ድጋፍ ነበር፡፡ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶና ታሽጎ ሲላክ የተሸለ ገንዘብ እናገኝበታለን በሚል በሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ድጋፍ ይደረግልኝ ነበር፡፡ ሌላ የቡና ገበያ አማራጮችም እየተፈጠሩ መጡ፡፡
በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ነው?
አዎ፡፡ ጃፓኖች የሚፈልጉት የቡና ጥራት ጥያቄ ከባድ ነበር፡ ከእነሱ ጋር ገበያ ተመቻቸ፡፡ ምርቱ በኮንቴነር ወደ ጃፓን ሄዶ ጃፓን ሼልፍ ላይ የኢትዮጵ ቡና ተብሎ ተቀመጠ፡፡ ገረመኝም ደስ አለኝም፡፡ ለእኔ ስኬት ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያ ውስጥ ታሽጎ መጣ” ሲባል በጣም ነበር የተደሰትኩት፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ተቀባዬ ኩባንያ የራሱ ችግር ገጠመው፡፡ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶ፣ ታሽጎ የሚላከው ቡና ጥያቄ ውስጥ ስለነበር ግሪን ኮፊው ከፍተኛውን ድርሻ ያዘ፤ ገበያው የተመቻቸ ስለሆነ በስራው ለመቀጠል መታገል ጀመርኩ፡፡
ቡናውን ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጐ ወደ ጃፓን የመላኩ ስራ ቆመ ወይስ?
የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የሀገር ልማት ስለሚያሳስባቸው 5 ዶላር ያመጣልኝን ሰው በጣም አደንቃለሁ ብለው ነበር፡ ኢንቨስተሮችን ያበረታታሉ፡፡ ሄዳችሁ አሳምናችሁ የውጪ ምንዛሬ ማምጣታችሁ የሚደነቅ ነው ይሉን ነበር፡፡ ትግሉ ብዙ ስለሆነ ነው፡፡ በጃፓን የተካሄደ ኤግዚቢሽን፤ ጠ/ሚ መለስ ደግሞ ለስብሰባ እዛ ነበሩ፡፡ ጊዜያቸውን እንደምንም አብቃቅተው ባረፉበት ሆቴል እንድናነጋግራቸው ፈቀዱልን፡ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶና ታሽጎ ወደ ጃፓን የምንልከውን ቡና ተቀባይ የነበረው ኩባንያ የገንዘብ ኪሳራ እንደገጠመው አጫወትኳቸው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ቡና ተቀባይ የነበረው ኩባንያ ጥሩ ተስፋ ነበረው፤ ጃፓን ውስጥ ከመቶ በላይ ሱፐር ማርኬት አለው፤ የእኛ ምርት በመደብሮቹ ውስጥ መደርደራቸው ለእኛ ትልቅ ፕሮሞሽን ነው፡፡ የጃፓኑ ኩባንያ ከገጠመው ችግር ተላቆ እስኪወጣ ድረስ ያስቀመጠወን አማራጭ ሃሳብ እንስማው›› አልኳቸው የጃፓኑ ኩባንያ ባለቤቶች በተገኙበት ተማከርን፡፡ በመንግስት በኩል የምንረዳችሁ ነገር ካለ እንደግፋችኋለን በርቱ አሉን፡፡ ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ የሚበጀውን መላ ጠ/ሚ ጠቆሙንና ሂደቱ ቀጠለ፡፡ ከሚኒስትሮችም ጋር በየወሩ ግምገማ ይደረጋል፡፡ “ማን ላከ? እንዴት ነው?” የሚለው ነገር ይጠናል፡፡
በባንክ በገንዘብ በኩል ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚባሉ ችግሮችም እየተነሱ መፍትሄ ይበጅላቸዋል፡፡የንግዱ ማህበረሰብ የንግድን አካሄድ እና ቢሮክራሲ በደንብ ያውቃል፡፡ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የሚሰሩ የመንግስት ቢሮዎች አካባቢ ያሉ ግን በሹመትና በስልጣን ወይንም በትምህርት የሚመጡ ናቸው፡፡ በሌሎች ሃገሮች ግን ከንግድ ነክ ነገሮች ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ አካላት ከንግድና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሰሩና በትምህርትም የዳበሩ ናቸው?
በእርግጥ ነገሮች አልጋ በአልጋ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሌሎች ሃገሮች ስንሄድ ከምናየው የምንቀስመው ትምህርት ይኖራል፡፡
የበለፀጉ አገራትን ልምድ ቀስመን መጠቀም እንችላለን፡፡ ለምሳሌ መንግስት የሚያደርግላቸውን እገዛ በመግለፅ ተመክሮ እናጋራለን፡፡ ብዙ እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ቢኖሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ የልምድ ልውውጥ የምናደርግበት፤ የምንመካከርበት ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ይህን የምለው ከሀገር ስወጣ ራሴን እንደ አምባሳደር አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ ከአገር ስወጣ አሊ ሌላ ሰው ነው፡፡ ንግዴን ለመስራት ነው የምሄደው፡፡ ለሃገሬ ልሰራ ነው የምሄደው፡፡ እዛ ውስጥ እኔ አልጠቀምም እያልኩ አይደለም፡፡ ውጭ ሃገር ስሄድ የማወራው ስለ ኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች በሙሉ ነው፡፡
ስለ ኤክስፖርት ነው የማወራው፡፡ ስለ ሀገሪቷ የኤክስፖርት ምቹነት ነው የምናገረው፡፡ ቡናን ብቻ አላወራም፡፡ ከመንግስት ተልከህ ነው የመጣኸው ይላሉ፡፡ ስለ ሃገሬ ባህል፣ ወግ፣ ስርዓት... ምን ልበልሽ ብዙ አወራለሁ፡፡ የውጪ ኢንቨስተሮች እዚህ ሲመጡ ግን ነገሮች ከባድ መሆን የለባቸውም አሰሪ በሆነ መልኩ ሊመቻች ይገባል፡፡
በንግድ ስራ ሂደት ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው?
እንግዲህ ቡና ማልማት ነው ፍላጎታችን፡፡ መሬት መመቻቸት አለበት፤ሌላ ሰው ያለማውን ብቻ ይዘን ኤክስፖርተር ነን ማለት ተገቢም አይደለም፡፡ በተለይ የቡና ልምድ ያላቸው እናልማ ብለው ሲነሱ መንግስት ገፋፍቶ ሊያሳድጋቸው ይገባል፡፡
እኛ መቸገር የለብንም፡፡ በርግጥ መንግስት አብሮን እየሰራ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጀምሮ… ንግድ ሚኒስቴር “ምን ጋ ናችሁ” ይለናል እለት በእለት፡፡
አንዳንድ ጊዜ መላክ ነው የሚቀራቸው፡፡ ባንኮች ብድር ለራሳቸው ሲሉ ነው የሚሰጡት፡፡ ምክንያቱም ሰርተን አምጥን እኮ እንከፍላቸዋለን፡፡ በነጻ የሚሰጠን እኮ የለም፡፡ ባንኮችን እባካችሁ የሚል ነገር ጠይቄ አላውቅም፤ አሁንም ወደ ፊትም አልጠይቅም፡፡ ፓርትነር ሆኜ ነው የምሰራው፡፡ ለነገሩ በተቻለኝ መጠን ብዙ መበደርም አልፈልግም፡፡ በገንዘብ እጦት ምክንያት ስራው እንዳያልፈኝ እወስድና ቶሎ መመለስ ነው የምፈልገው፡፡ ስወስደው ደስ አይለኝም፤ ደስ የሚለኝ ስመልሰው ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በዓለም ላይ የቡና ገበያ የመንገጫገጭ ሁኔታ ገጥሞት ነበር፡፡ ድርጅታችሁ እንዴት ተወጣኸው?
በርግጥ በእኛም ሃገር በዓለም ላይም የቡና ገበያ የመንገጫገጭ ሁኔታ ገጥሞት ነበር፡፡ ባለፈው ሶስት ዓመት ከነበሩት በአንድ ጊዜ ዝቅ ሲል በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ እንደ ሀገር ከባድ ነበር፡፡ ቡና ከሀገር ውስጥ መውጣት አልቻለም፡፡ በውድ ዋጋ የተገዛ ነበር፡፡ ችግሩን መዋጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት በቡናው ስራ የነበርን ሰዎች በቆራጥነት መወጣት አለብን የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ቡና በባህሪው ለምን አምና እንደዚህ ሆነ፤ ካቻምና እንደዚህ ሆነ የሚል ነገር የለውም፡፡ በየቀኑ የሚቀያየር የራሱ የሆነ አካሄድ አለው፡፡ የቡና ስራ በጣም ያስፈራል ብዬ ሌሎችን አስፈራርቼ፣ ሌሎች እንዳይገቡበት መናገር አልፈልግም፡፡ ትልቅ ኪሳራ ሲመጣ ያስደነግጣል፡፡ ትልቅ ትርፍም ሲመጣ ያስደነግጣል፡፡
በአለም ላይ ያለ የቡና ገበያ እንደ ቁማር ነው የሚባለው ለዛ ነው?
እንደ ቁማር ሊባል አይችልም፤ እንደ ማንኛውም ንግድ ነው፡፡ ማንኛውም ንግድ ሪስክ ነው፡፡ ሪስክ ያንሳል ይበዛል ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ መነገድ ማለት ሪስክ ማኔጅመንት ነው፡፡
ስለዚህ ቡናም ተመሳሳይ ነው፡፡ ግን የቡና ሪስክ ከፍተኛ ነው፡፡ በብዙ ምክንያቶች ከፍና ዝቅ ይላል፡፡ ይሄ ለሁሉም የማይታወቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለቡና ነጋዴዎች አስፈላጊነቱን እንዴት ይገልፁታል?
ዘመናዊ የግብይት ስርዓት መኖሩ መልካም ነው፡፡ በቀድሞ አሰራር ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ ወደ አዲስ ነገር ሲገባ በአንድ ጊዜ መቀበል ያስቸግራል፡፡ በየጊዜው እየተስተካከሉ መሄድ አለባቸው፡፡ ለመረከብ ወደ ተለያየ ዞን ስለምንሄድ ለእኛ ሰፊ የስራ ጫና ፈጥሮብናል፡፡
በፊት ከገዛን በኋላ እዚህ እየመጣ ነበር የምንረከበው፡ ስንረከብ ጎድሎ ይመጣል፤ ከሾፌሮች ጋር እንጣላለን፡፡ “የታሸገ ነው የተሰጠኝ፤ እኔ የማውቀው ነገር የለም” ይላል፡፡
ጥራት ላይ ደረጃ 4 ገዝቼው ሲደርሰኝ ደረጃ 6 ሊሆን ይችላል፡፡ ዝቅ ያለ ጥራት ይገጥመኛል፡፡ ግን አንድ ነገር ሲሰራ ችግሮች አይጠፉም፤ ስለዚህ አብሮ መታገል ነው፡፡ አሁን እንደውም ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ እሱን ቢያፈጥኑልን ለእኛ እሱ እንደውም መልካም ነው፡፡
በድርጅታችሁ ምን ያህል መጠን ያለው ቡና በየቀኑ ወደ ውጪ ትልካላችሁ?
አዲስ አበባ ባለው ኩባንያችን ከ4-5 ኮንቴነር ቡና ማበጠር እንችላለን፡፡
የማዘጋጀት አቅማችንን ነው የምነግርሽ፡፡ ድሬዳዋም ላይ በተመሳሳይ ባለን ዘመናዊ መሳሪያ በዓመት ወደ ሰላሳ ሺህ ቶን ቡና ይዘጋጃል፡፡
ሰፊ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ሐረር ያለው ቡና በዓመት ከ15-16 ሺህ ቶን ነው የሚያዘጋጀው፡፡
የቡና ልማቱን ታሳቢ በማድረግ ነው ድሬዳዋ ያለውንም የሰራነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የአካባቢው ገበሬም የተሻለ ነገር ተፈጥሮልኛ ብሎ ልማቱ ላይ እንዲገፋ በማሰብ ነው፡፡
ወደ ፊትስ የርስዎ ራዕይ ምንድን ነው?
ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ኮሪያና አውሮፓ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አሁን እኛ እየገባን ነው፡፡ በተለይ መንግስት በጀት መድቦ የበለጠ የማስተዋወቅ ስራውን በጋራ ብንሰራ የበለጠ ውጤት እናመጣለን፡፡ አንዳንድ ሃገሮች ቡናውን ያውቁታል፤ ይሰማሉ፤ የማየት እድሉን ያላገኙ አሉ፡፡ እነዛን ሃገሮች እየሰረሰርን ብንገባ የበለጠ ገበያ እናመጣለን፡፡
የተወሰኑ ሃገሮች ላይ ብቻ መንጠልጠል አስፈላጊ አይደለም፡፡ ገበያ ሲጠፋ ሲወርድ ያሉትን ውጣ ውረዶች ያስተካክለዋል፡፡ ኩባንያውን በደንብ ስላጠናከርኩ ጊዜውም ስላለኝ ተጨማሪ ዕውቀቶችንና ልምዶችን ለመቅሰም እጥራለሁ፡፡ በሀገሬ ላይ ድህነትን ማጥፋትና የበለጠ እንድታድግ መስራት ነው የወደፊት ራዕዬ፡፡
በተለይም እኛ ኢንቨስተሮች ሀገራችን የምንኮራባት ናት፡፡ የገንዘብ ችግር እንጂ የአየር ንብረትዋ፣ የህዝቧ ጥሩነት የሚያሰራ ነው፡፡ በሄድኩበት የስራ አጋጣሚ ሁሉ አገሬን አጉልቶ ማሳየት የዘወትር ስራዬ ነው፡፡
የውጪ ባለሀብቶች ወደ ሃገራችን መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የበኩሌን ጥረት እያደረግሁ ነው፡፡ ሁላችንም ይህም ስናደርግ በፍጥነት ከድህነት እንወጣለን፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት ሃላፊነቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የእኛም ጭምር ነው፡፡
ባሳለፉት የስራ ዘመን ድህነትን ከሀገር ለማጥፋት ምን የተለየ ነገር ሰሩ?
ለሀገር ልማት እድገት አበረከትኩት የምለው በርካታ ነገር ባይኖርም ለስራ በተንቀሳቀስኩባቸው አካባቢዎች የሀገሬ አምባሳደር ሆኜ ስለ ኢትዮጵያ እሰብካለሁ፡፡
በተጨማሪ ለአባይ ግድብ ቃል ከገባነው 5 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ሌላ 5 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ አስር ሚሊዮን ብር አበርክተናል፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ እቅዶች አሉን፡፡ እሱን ወደፊት የምንገልፀው ይሁን፡፡
ቤተሰብ አፍርተዋል?
አዎ ሶስት ልጆች አሉኝ፡፡ ልጅና ብር አልጠግብም (ሳቅ) ይቀጥላል፡፡

br /

Read 9366 times Last modified on Wednesday, 19 December 2012 07:36