Print this page
Saturday, 15 December 2012 13:31

ፍቅር በሞባይል

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(93 votes)

የጓደኛዬ ጓደኛ ነው፡፡ ባህርዳር መጥቶ ተዋወቅን፡፡ በጓደኛችን ግብዣ ነው የመጣው፡፡ ለነገሩ ለጉብኝት ነው አልኩኝ እንጂ የተጋበዘው ጓደኛው የሚኖረውን ጥሩ ኑሮ (የሚባል) አይቶ ሄዶ የትውልድ ቦታው እንዲያወራ ነው፡፡
እኔ እንደዛ ነው የገባኝ፡፡ በጣም ፈጣን ነው፡፡ የጥቁር ቆንጆ ነው፡፡ (አንድ ጓደኛዬ ወንድ ቆንጆ አይባልም ይላል፡
መልከ መልካም እንበለዋ፡፡) ስንግባባ ሙሉ ሰአት አልሞላም፡፡ ሙሉ ሰአት ሳይሞላ ሙሉ የህይወት ታሪኩን አጫውቶኝ ጨርሷል፡፡ የህይወት ታሪኩ ሴት መጥበስ ሲጀምር ይጀምራል፡፡ ብዙ ሴቶች አሉ፡፡ ብዙ ታሪኮች አብሯቸው አሳልፏል፡፡ አንዲትም ነገር ደግሞ አይረሳም፡፡

ጳጉሜ ሶስት፣አስራ ዘጠኝ ዘጠና ሦስት፣ ከምሽቱ ሦስት ሰአት፣ ከሶስና ጋር ነበር፡፡ እንዴት እንደሳማት፣ ስንቴ እንደሳማት ያስታውሳል፡፡ ሴት እና ወሬ ይወዳል፡፡
“አንዷ ይህችውልህ” አለኝ የሞባይሉ ግድግዳ ላይ የተለጠፈውን ፎቶ እያሳየኝ፡፡ ፀጉሯን አንጨባራዋለች፡፡ ሰልካካ ናት፡፡ የሚያምሩ አይኖች ነው ያሏት፡፡ ንፁህ ናቸው አይኖቿ፡፡ ጥቁሩ በጣም ጥቁር፣ ነጩ በጣም ነጭ ነው፡፡ ደስ ይላሉ፡፡
“ሌሎችም ፎቶዎች አሉልህ ቆይ--”
ሞባይሉ ውስጥ ያለው የፎቶ ቦርሳ ውስጥ ገብቶ በሷ ስም የተዘጋጀ አልበም ከፈተና
“ይህን እየነካህ እያሳለፍክ እይ” ብሎ ሰጠኝ፡፡
ብዙ ፎቶዎች አሉ፡፡ የራቁት ፎቶዎች ይበዛሉ፡፡ ገንዳ ውስጥ፣ አልጋ ውስጥ፣ እቅፍ ውስጥ፣ እንቅልፍ ውስጥ፡፡
“ደስ ይላል” አልኩ አይቼ ስጨርስ፡፡
“ገና ብዙ አሳይሻለሁ” ከተወወቅን ግማሽ ቀን ሳይሞላ ‘አንቺ’ ይለኝ ጀምሯል… ሴቶች ቢወዱት፣ ቢራቆቱሉት፣ ፎቶ ቢነሱለት አይገርምም፡፡
“ሠራዊት ተጫወት እንጂ” አልኩ ወደ ጓደኛዬ ዞሬ፡፡
እስካሁን ስናወራ የነበረው እኔ እና እንግዳው ልጅ ነን፡፡“እስካሁን የነገረህን ብዙውን ታሪክ አውቀዋለሁ፡፡ ነግሮኛል፡፡
የመጨረሻዋን ልጅ ታሪክ ነው የማላውቀው፡፡ እሱን ሲያወራ እየሰራሁ እየሰማሁት ነበር፡፡ እስኪ ሞባይሉን አቀብለኝ ፎቶዎቿን ልያቸው”
ከፍራሹ ላይ አንስቼ ሰጠሁት፡፡
“ጓደኛ አለህ?” ጠየቀኝ እንግዳው፡፡
“የምን ጓደኛ?”
“የሴት ነዋ!”
አውቄ ነው የምን ጓደኛ ያልኩት፡፡ አሁን ልጁ ገብቶኛል፡፡ ከሴት ሌላ ስለምንም ነገር ማውራት አይፈልግም፡፡
መስማትም የሚፈልገው ስለ ሴት ብቻ ነው፡፡ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያው ሴት፣ ጓደኞቹ ሴቶች፣ ወሬው ስለ ሴቶች…
“አለችኝ”
“How is she?”
“ማለት?”
“I mean is she beautiful? I mean is she hot? Or what?...”
“ቆንጆ የምትባል አይደለችም፡፡ እናም ደግሞ እንደ እምነ በረድ ቀዝቃዛ ናት”
“እያሾፍክ ነው አይደል?”
“አይደለም”
ዞሮ ጓደኛውን ማለት ጓደኛችንን አየው፡፡ እውነቴን እንደሆነ ጭንቅላቱን ነቅንቆ አሳየው፡፡
“ትወዳታለህ?”
“በጣም”
“ንገረኝ በናትህ ስለሷ”
“ረዥም ነው፡፡ ባወራህም የምትገባ ልጅ አይደለችም፡
እስኪ አንተ ስለ ቴሌ ንገረኝ፡፡ ምን ክፍል ነው የምትሰራው?”
ስለ ቴሌ፣ ስለ ስራው ትቶ ሌላ የሴት ጨዋታ አወራኝ፡
ሲጨርስ፡-
“ቆይ ፍቅር ላንተ ምንድ ነው?” አልኩት ልጁን፡፡
ሰራዊት እንዲህ አይነት ወሬ ይመቸዋል፡፡ ከወንበሩ ተንደርድሮ መጥቶ ፍራሽ ላይ ተቀላቀለን፡፡
እኔ እና እሱ ስንከራከር ስንጯጯህ መሸ፡፡ ልጁ አንድም ነገር አልተናገረም፡፡ “Love is love of values” አጃኢብ ነው የሆነበት፡፡
እንዲያ እያልን ነበር ስንከራከር ያመሸነው፡፡ በመጨረሻ ለመጠጥ ወጣን፡፡
ሠራዊት ከልጁ ጋር አብሮ አደግ ናቸው፡፡ አሁን ሠራዊት አሪፍ ስራ ይዟል፡፡
አሪፍ ኑሮ እየኖረ ነው፡፡ ታዲያ ይሄን እውነታ የትውልድ መንደሩን ሰው ሁሉ ጋብዞ ማሳየት አይችልም፡፡
እንደ ጌዲዮን አይነት ወሬኛ ሰው የታቀደውን ያሳካል፡
አዋዋላችንም ምስክር ነበር፡፡ ምሳ የት በላን? ሰመርላንድ፡፡ በምን ስንቅም ዋልን? በሃይላንድ፡፡ ሲጋራ ለጉድ ተጨሰ፡፡ አሁን እንግዲህ ለጨብሲ ምን እንደሚጠብቀን መጠርጠር ቀላል ነው፡፡ ውስኪ፣ ቤሉስ… ምናምን፡፡ አንዳቸውም አይመቹኝም፡፡
ለኔ ከቢራ ውጪ መጠጥ የለም፡፡ መስከሬ የሚታወቀው፡- “እግዚአብሔርም በስምንተኛው ቀን ቢራን ፈጠረ” ማለት ስጀምር ነው፡፡
ሠራዊት “እኔ የምጠጣውን ጠጡ” ማለት ስለሚወድ አንድ አምስቱን ቢራዎቼን እቤት ጠጥቼ ነው ከተማ የወጣነው፡፡ ብላክ ሌብል ወረደ፡፡ አንድ ጠርሙስ ጨረስን፡፡
ሁለተኛውን ጠርሙስ ይዘን እየዞርን ጠጣን፡፡ ለእንስቶች ቢራ እየጋበዝን ደነስን፡፡
እኔ ቤት ነው የነቃነው፡፡ስንት ሰአት እንደገባን፣ እንዴት እንደገባን ምንም የማስታውሰው ነገር የለም፡፡
የስልክ ጩኸት ነው የቀሰቀሰኝ፡፡ ከቀኑ ስድስት ሰአት ሆኗል፡፡
“አቤት እማዬ?”
“አንተ ደህና ነህ?!”
“ደህና ነኝ”
“ታዲያ ምን ሆነህ ነው በዛ ሌሊት ስትደውል የነበረው?! ደሞ ሲደወልልህ አታነሳም፡፡ ቤተሰቡን አመስከው እኮ”
“እኔ? መች ደወልኩ?”
ሰራዊት ሳቁን ለቀቀው፡፡
“ምንድነው?” አልኩት፡፡ ስልኩን እንድዘጋው በምልክት ነገረኝ፡፡
“ቆይ እማዬ መልሼ እደውልልሻለሁ” ዘጋሁት፡፡
“ምንድነው?”
“አልነገርኩህም ለካ --- ይህ በሽተኛ ልጅ እኮ ሲሰክር የሰው ስልክ እየወሰደ ከኤ እስከ ዜድ ያሉት ቁጥሮች ላይ ይደውላል፡፡ ሚስኮል ያደርጋል፡፡ ያንተን ስልክ ሌሊት ይዞት አይቻለሁ”
ስልኬ ጮኸ፡፡ ሰራዊት ይስቃል፡፡ ልጁ ተከናንቧል፡፡ እሱም እየሳቀ ነው፡፡
“ደም ሳቅ!”
ስልኬ በድጋሚ ጮኸ፡፡ የእናቴ ነፍስ አባት ናቸው፡፡ “ለምን ስልኩን አታጠፋውም” አለኝ ሠራዊት፡፡
የስልኩ ማጠራቀሚያ ውስጥ ገባሁ፡፡ ሲም ካርዱ ሙሉ ነው፡፡ 250 ቁጥሮች ይዟል፡፡ የቀረውን ማጠራቀሚያ አየሁት፡፡ 110 ስልኮች አሉት፡፡
360 ቁጥሮች ላይ ደውሏል፡፡ የተደወሉትን ስልኮች አየሁ፡፡ የተደወሉልኝንም አየሁ፡፡ ያልተደወለለት ሰው የለም፡፡ እናቴ፣ የእንጀራ እናቴ፣ አባቴ፣ የእንጀራ አባቴ፣ ወንድሜ የእናቴ ልጅ፣ ወንድሞቼ የአባቴ ልጆች፣ የወንድሞቼ እህቶች፣ የእህቶቼ ወንድሞች፣ የእህቶቼ እህቶች፣ የወንድሞቼ ወንድሞች፣ …አለቆቼ፣ ጓደኞቼ፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ ሆስፒታል፣ ጋራዥ፣ ፀጉር ቤት….
ወጥቼ ፊቴንም ንዴቴንም ታጥቤ መጣሁ፡፡
አልተቆጣሁም፡፡ ሲስቁ አብሬ ሳቅሁኝ፡፡ምሳ ከእንቁጣጣሽ ሆቴል አስመጥተን በላን፡፡ ሀይለኛ ሀንግኦቨር ነው፡፡
በማስታገሻ ኪኒን የሚመለስ አይደለም፡፡ መጠጣት ጀመርን፡፡
“ጌዲዮን?”
“አቤት”
“ከሁሉም የምትወዳት ሴት የትኛዋን ነው? ከእስከዛሬዎቹ?”
“This one.” ብሎ ሞባይሉን ከፍቶ አሳየኝ፡፡
መሸም፡፡ ሁለተኛም የስካር ቀን ሆነ፡፡ ሠራዊት እና ጓደኛው ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ሦስት ሰዓት ሆኗል ከምሽቱ፡፡
የልጅቷን ስልክ ከጌዲዎን ስልክ ደብቄ ወስጃለሁ፡፡
አልጋ ላይ ተንጋልዬ ደወልኩላት፡፡ መስመሯ ተይዟል፡፡
ደግሜ ሞከርኩ፡፡ ተይዟል፡፡ ጌዲዮን ጋር ደወልኩ፡፡ የሱም ተይዟል፡፡ እያወራት መሆን አለበት፡፡ የባሰ እልህ ያዘኝ፡፡ አንድ ሰዓት ያለማቋረጥ ተያዘ፡፡ አንድ ሰአት ሙሉ ያለማቋረጥ ሞከርኩ፡፡ በመጨረሻ ጠራ፡፡ በአንዴ አነሳችው፡፡
“ሄለው ጌዲ ካርድ ጨርሰህ ነው?”
“ጌዲ አይደለሁም”
ዝም ብዬ በቀል ነው እንጂ የፈለግሁት፣ ምን ልላት እንደደወልኩ አልተዘጋጀሁም፡፡ ምኑ በቀል እንደሆነም ግራ ገባኝ፡፡
“ማነህ ታዲያ?” ድምጿ በጣም ለስላሳ ነው፡፡ ክሬም እንደበዛበት አይነት ኬክ፡፡
“ገምቺ እስኪ”
“እስኪ ትንሽ አውራ፡፡ እንድሰማህ---”
“ምን ላውራ?”
“ቆይ ማን እንደሆንክ ለምን አትነግረኝም?”
“ራስሽ ገምቺ”
“ሄኒ! አንተ ብሽቅ! አንተ ነህ አይደል?!”
“ሄኒም አይደለሁም፡፡ ብሽቅም አይደለሁም፡፡ ሌላ ገምቺ”
“ኾኾ… ዛሬ ደሞ ምን አይነቱ መጣ ባካችሁ?!”
“ስንት አይነት ታውቂያለሽ?”
“ወይ ማንነትህን ንገረኝ ወይ ስልኩን ልዝጋው”
“ዝጊው”
“የእውነት?!”
“የእውነቴን ነው ማፊ”
“ማፊ?”
“ምነው?”
“ማፊ የሚሉኝ እኮ ጥቂት ሰዎች ናቸው”
“ስንት ናቸው? እነ ማናቸው?”
“ቆይ አንተ ማነህ?”
“እንዴት እንደረሳሽኝ ገርሞኛል”
“በናትህ ንገረኝ፡፡ ማነህ?”
“ስለረሳሽኝ ገርሞኛል”
“የሚገርምህ እንዲህ አይነት ድምፅ ያለው ሰው አላውቅም፡፡ ከዚህ በፊት ሰምቼው ቢሆን ይህን ድምፅ አልረሳውም፡፡ በዚህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስልኬን ማን ሰጠህ?”
“እራስሽ”
“እኔ?”
“እራስሽ”
“ግን ደግሞ እኮ እንዲህ አይነት ድምፅ ፈፅሞ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ማፊ ነው ያልከኝ? ቆይ ስሜ ማነው?”
“ምዕራፍ”
“የግቢ ልጅ ነህ አይደል?”
“አይደለሁም”
“ታዲያ የት ነው እምታውቀኝ፡፡ አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ… ተገናኝተን የምናውቅ ቢሆን ኖሮ ይህን ድምፅ አልረሳውም፡፡ ድምፅህ! እሺ የት ነው የምማረው?”
“ሃርቫርድ”
“በናትህ አትቀልድ”
“እሺ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፡፡ ስድስት ኪሎ”
“እሺ ምንድነው የማጠናው?”
“አስትሮኖሚ”
“በናትህ አትቀልድ፡፡ እያስጨነከኝ ነው”
“ማኔጅመንት”
“ወይኔ!!” የጉጉት ሲቃ ለስላሳ ድምጿ ውስጥ አለ፡፡ (ጌዲዮን ወሬኛ እንደሆነ እና ያልነገረኝ ነገር እንደሌለ አታውቅም፡፡)
“በናትህ እኔ ግን አውቅሃለው?”
“ታውቂኛለሽ”
“ቆይ አብረን ሆነን እናውቃለን?”
“በደንብ”
“እሺ በጣም የምወደው ምግብ ምንድነው?”
“ፒዛ”
“ወይኔ ጉዴ! ታዲያ ይሄን ድምፅ እንዴት እረሳዋለሁ?”
“ይኼውልሽ ማፊ እንዳትጠራጠሪ ሌላ ምልክት ልንገርሽ፡፡ ግራ ጡትሽ ላይ ሽታ አለ፡፡ ቀኝ ጭንሽ ላይ ትልቅ የማሪያም ስሞሽ!”
“እ-ን-ዴ-ኤ! ኧረ ባባትህ! ወጥተን እናውቃለን?”
“አዎ”
“ባባትህ፣ በናትህ፣ ባባትህ ልታሳብደኝ ነው፡፡ እኔ እና አንተ ወጥተን እናውቃለን?”
“አዎ አልኩሽ እኮ”
“እና ታዲያ?”
“ሰክረሽ ነበር”
ዝም አለች፡፡
“አልነካሁሽም፡፡ አቅፌሽ ተኛሁ፡፡ ጠዋት ሳትነቂ ስሜሽ ወደ ስራ”
“እምትገርም ሰው ነህ፡፡ አብሮኝ አድሮ ሳይነካኝ ያደረ ሰው አላስታውስም፡፡ ማን እንደሆንክ ለምን አትነግረኝም ግን?” የተናደደች ትመስላለች፡፡
“ይህን ጥያቄ ትተሽ ለምን ሌላ አናወራም?”
“ድምፅህ ያምራል” አተነፋፈሷ ተለውጧል፡፡
“ደጋገምሽው”
“የምሬን ነው፡፡ እንዲህ አይነት ድምፅ ሰምቼ አላውቅም” ዝም አልኩ አፍሬ፡፡
“ድምፅህ!” አለች አሁንም በዛ ድምጿ፡፡
ተላመድን፡፡ድምጼን ወዳዋለች፡፡ እሷ እንደምትለው እኔ እስክደውልላት በነበረው ህይወቷ የእኔ አይነት ድምፅ ሰምታ አታውቅም፡፡
“አመሰግናለሁ” አልኳት፡፡
“ምንም አይደል የኔ ባለ ሸጋ ድምፅ!”
“ያንቺም ድምፅ በጣም ይገርማል፡፡ የሴት ድምፅ ነው፡፡ የባለጌ ሴት ድምፅ!”
“አውቃለሁ፡፡ ይልቅስ አንድ ነገር ላስተምርህ”
“እባክሽ… Please.”
በጣም ይገርማል፡፡ እንዲህ አይነትም ነገር አለ እንዴ? ፍቅር በስልክ አስተማረችኝ፡፡
ሱስ ሆነብኝ፡፡
“አሁን በደንብ ስለለመድክ አንተ ነህ ወሬውን የምትጀምረው” አለችኝ አንድ ቀን፡፡
“ታዛዥ ነኝ”
“አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት”
ጀመርኩ፡፡
“ስልኩን በየትኛው እጅሽ ነው የያዝሽው?”
“በግራዬ”
“ቀኝ እጅሽስ?” ነገረችኝ፡፡ እንዲያ እያልን ቀጠልን፡፡
አንድ ቀን፡- የተለመደውን መግቢያ ካወራን በኋላ
“ንከሰኝ” አለችኝ፡፡
“የቱ ጋ?”
“አንገቴ ላይ”
“ይኸው”
“በደንብ ነዋ”
“እነሆ ንክሻ በደንብ!”
ስትጮህ ጊዜ፣ በጣም ስትጮህ ጊዜ ደንግጬ ስልኩን ዘጋሁት፡፡
በነጋታው እሷ ደወለች፡፡
“ትላንት ምን ሆነሽ ነው?”
“በጣም እኮ ነው የነከስከኝ”
“ሴትዮ በስልክ እኮ ነው!”
“እና ታዲያ?”
“አያምም ብዬ ነዋ!”
“ሌሎቹ የምናወራቸው ነገሮች እውነተኛ ስሜት ይፈጥሩ አይደል?”
“በደንብ!”
“ይኼም እንደዛው ነው!”
“ይገርማል!”
“በደንብ እንዲገርምህ ዛሬ ስካርፍ አድርጌ ነው የዋልኩት፡፡ ቁስሉን ለመሸፈን”
“የምር?”
“የምር!”
አመንኳት፡፡
ሌላ ቀን፡-
“ሁሌ ሴትዮ ትለኝ አይደል? ስትለኝ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ ዛሬ ሰውዬ ልበልህ”
“በይኝ”
“ሰውዬ?”
“አቤት የእኔ እመቤት”
“የወር አበባዬ ከቀረ ቆየ፡፡ ሦስት ወር ሆነው፡፡ ተመረመርኩ፡፡ እርጉዝ ሆኛለሁ”
“በእውነት?”
“በእውነት!”
“ከማን?”
“የምን ከማን አለው? ከአንተ ነዋ!”
“ሴትዮ በስልክ እኮ ነው”
“እና ታዲያ?”
“አይሆንማ!”
“ሆኗላ!”
“ሴትዮ?!”
“ወዬ የኔ ውድ”
“እና ምን ተሻለ?”
“እንጋባ!”
ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡
አብረን ሆነን ተመረመረች፡፡
እርጉዝ ነች፡፡
ማን ነበር She is beauty ያለው? Beautiful ማለት ጠፍቶት አልነበረም፡፡
ይህቺ የኔዋ ጉድም ቆንጆ ሳትሆን ቁንጅና ነች፡፡ ተጋባን፡፡

Read 84436 times