Saturday, 15 December 2012 12:55

“ኦፕሬሽን ካተሪን” ከጃንሆይ የልጅ ልጆች ጋር ከኢትዮጵያ ማምለጥ Featured

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

አፄ ኃይለሥላሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ከመንበረ ስልጣናቸው ከወረዱበት ጊዜ ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ለብቻቸው የታሰሩ ሲሆን ቤተሰባቸው ደግሞ በቁም እስር ላይ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜም ብዛታቸው ሃያ አምስት ሆኖ እድሜያቸው ከአንድ እስከ 19 አመት የሚደርስ ሕፃናትና ወጣቶች የሆኑ የጃንሆይ የልጅ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በቁም እስር ላይ ነበሩ፡፡ደርጉ ንጉሳዊ ቤተሰቡ ከርቸሌ እንዲታሰሩ ሲወስን፣ በቁም እስር ላይ የነበሩት ሕፃናትና ወጣቶች ተለቀው ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲኖሩ ፈቀደ፡፡

በዚህ ጊዜ ከተለቀቁት ሕፃናት ልጆች ውስጥ፤ የልዕልት አይዳ ደስታና የልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እንዲሁም የልዕልት ሰብለ ደስታና የደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም ልጆች ይገኙበት ነበር፡፡
ከ12 አመት በታች እድሜ የነበራቸው እነዚህ ልጆች- መነን መንገሻ፣ ሎሊ ካሣ፣ ኮከብ ካሳ፣ እና አምኃ ካሳ የተባሉ ሲሆኑ ሕፃናቱን በጊዜው ያስጠጓቸው አክስታቸው ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የልጆቹ አክስት በገጠማቸው የጤና እክል ሳቢያ ሕፃናቱን መንከባከብ ስለተሳናቸው፣ ልጆቹን በአንድ ላይ የሚያሳድግላቸው ቤተሰብ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡
እነዚህን የንጉሳዊ ቤተሰብ ሕፃናት ተቀብሎ ለማሳደግ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩት፣ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆነ፣ ዴንተንና ጁዲ የተባሉ አሜሪካዊ ሚስዮናውያን ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡ ዴንተን የባፕቲስት ሚሲዮን ዳይሬክተር፤ ባለቤቱ ጁዲ ኮሊንስ ደግሞ በእንግሊዝ ትምህርት ቤት መምህር ነበረች፡፡
አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ ያፈራው የዴንተንና ጁዲ ቤተሰብ፣ አራቱን ሕፃናት በማደጐነት የተቀበለው በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም ነበር፡፡ ከሕፃናቱ ውስጥ ትልቋ የ12 አመት እድሜ ያላት መነን ስትሆን፣ ትንሹ ደግሞ የሁለት አመቱ ሕፃን ሎሊ ካሳ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ቀን ከጣለው ንጉሳዊ ቤተሰብ ጋር ራስን ማነካካት በጊዜው አደገኛ መሆኑን ሚስዮናውያኑ ቢገነዘቡም፣ በልጆቹ ቤተሰብ ላይ በድንገት የደረሰው አደጋ ሕፃናቱን እንዲረዷቸው ገፋፍቷቸዋል፡፡
ደርጉ ሚስዮናውያንን ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ አሜሪካውያንን የስለላ ድርጅቶች አገልጋይ አድርጐ ስለሚጠረጥራቸውና እንቅስቃሴያቸውንም እግር በእግር ስለሚከታተል፣ እኚህ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን ሕፃናቱን በመቀበል ለማሳደግ የወሰዱት እርምጃ ድፍረትን የሚጠይቅ ተግባር ነበር፡፡ ድርጊታቸው ቢደረስበት ኖሮ እጣ ፈንታቸው በ24 ሰአት ውስጥ ከኢትዮጵያ መባረር ሲሆን ልጆቹ ደግሞ ምናልባት እስር ቤት ይወረወሩ ይሆናል፡፡መንግሥት የሚስዮናውያንን እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገደበ፣ ቢሮዎቻቸውንና ማምለኪያ ስፍራዎቻቸውን በመውረስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸውን ኑሮ አስቸጋሪ አደረገባቸው፡፡ በተጨማሪም በስራና በመኖሪያ ቤታቸው ዛቻ ስለሚሰነዘርባቸው፤ ደርግም እነርሱን ከጥቃት ለመከላከል ዳተኝነት በማሳየቱ፣ በገዛ ፈቃዳቸው ኢትዮጵያን እየለቀቁ የሚሄዱ ሚስዮናውያን ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡
ሚስዮናዊው የዴንተንና የጁዲ ቤተሰብም ከፊቱ የተጋረጠበት አደጋ፣ ይኸው ከኢትዮጵያ የመባረር ስጋት ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደርጉ ንጉሳዊ ቤተሰቡን (ከልጀ ልጆቻቸው ጭምር) ሊገድል ይችላል ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ፣ ሚስዮናውያኑ ስለሚያሳድጓቸው ልጆች ክፉኛ እንዲጨነቁ አደረጋቸው፡፡
ይህም ጁዲ ኮሊንስ በድንገት ከኢትዮጵያ የመባረር አደጋ ከመከሰቱ በፊት ልጆቹ ከኢትዮጵያ ሾልከው የሚወጡበትን መንገድ እንድታሰላስል አስገደዳት፡፡
በጊዜው በኢትዮጵያ ሰፍኖ የነበረው ብጥብጥና ግድያም የጁዲ ቤተሰብን ስጋት እውን የሚያደርገው ይመስል ነበር፡፡ ስለሆነም ጁዲ ኮሊንስ በእንግሊዝ አገር በስደት ከሚገኙት የኢትዮጵያ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ጋር ተገናኝታ፣ ልጆቹ ከኢትዮጵያ የሚወጡበትን ስልት ለመንደፍ አቅዳ፣ በሐምሌ ወር 1968 ዓ.ም ከሁለት ልጆቿ ጋር በአሜሪካ በኩል ወደ እንግሊዝ ተጓዘች፡፡
ጁዲ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየችበት ከአሥር አመታት በላይ በሆነ ጊዜ፣ ከንጉሳዊው ቤተሰብ ጋር ተገናኝታ ስለማታውቅ፤ በእንግሊዝ በስደት የነበረውን የጃንሆይ ቤተሰብ የተገናኘችው ራስዋን በማስተዋወቅ ነበር፡፡ በመቀጠልም ደርጉ የጃንሆይን የልጅ ልጆች ሊገድል ይችላል በሚለው ሥጋት ላይ በማተኮር፣ በእንግሊዝ ያለው የልጆቹ ቤተሰብ ከኢትዮጵያ ሕፃናቱን እንዲያወጣቸው ተማፅናለች፡፡
የጁዲ ጥያቄ የድንገቴ በመሆኑ በስደት ያለው ንጉሳዊ ቤተሰብ፣ ሕፃናቱን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ጨርሶ አልተዘጋጀበትም ነበር፡፡ በዚያ ላይ እንዲህ ላለው ተግባር ትልቁን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም፣ በጊዜው እንግሊዝ አገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ሁኔታዎችን እየተከታተለች የባሰ ነገር ከተፈጠረ ወደ ለንደን ተመልሳ እንድትመጣ ተነግሯት፣ ያለ ተጨባጭ እርምጃ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡
ጁዲ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰች ከጥቂት ወራት በኋላ የገባው የ1969 የኢትዮጵያውያን አዲስ አመት ይዞ የመጣው ሰላምና እፎይታን ሳይሆን ሽብርና ደም መፋሰስን ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አዲስ አበባ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ የተሰማው ወሬ፣ ደርግ የጃንሆይን የልጅ ልጆች ሰብስቦ ለማሰር እየተሰናዳ እንደሆነ የሚጠቁም ስለነበር፣ የሚስዮናውያኑ ቤተሰብ እንደገና በጭንቀት ተዋጠ፡፡
ይህም ዜና ጁዲ ልጆቹ ከኢትዮጵያ የሚወጡበትን መንገድ አጥብቃ እንድትሻ ስላስገደዳት፣ ለሁለተኛ ጊዜ ለዚሁ ጉዳይ ወደ እንግሊዝ ለመጓዝ ትዘጋጅ ጀመር፡፡ ጁዲ ጉዞዋን ከመጀመሯ በፊት ካደረገችው ዝግጅት ቀዳሚው፣ ከባለቤቷ ጋር ስለጉዳዩ ያለችግር በስልክ ለመወያየት የሚያስችላቸውን “ኮድ” ማሰናዳት ነበር፡፡ “ኮድ” እንዲሆን የመረጠችው ቃልም “የካተሪን ኦፕራሲዮን” የሚል ሐረግ ሲሆን “ካተሪን” አራቱን ልጆች፤ “ኦፕራሲዮን” ደግሞ የማስመለጡን ሂደት ይወክላል፡፡
ጁዲ፣ ባለቤቷ ዴንተንና አራቱን የማደጐ ልጆችዋን አዲስ አበባ ትታ፣ በየካቲት ወር 1969 ዓ.ም ከሁለት ልጆችዋ ጋር ወደ ለንደን በመጓዝ፣ ከልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ጋር በልጆቹ ህይወት ላይ ስለተደቀነው አደጋ ተወያይታለች፡፡ በውይይቱም ወቅት የማስወጣቱ እቅድ ጁዲ በምታሳድጋቸው አራት ልጆች ላይ ብቻ ሳይወሰን፣ በአዲስ አበባ ያሉ ተጨማሪ ሌሎች ስድስት የጃንሆይን የልጅ ልጆች እንዲጨምር ንጉሳዊ ቤተሰቡ መፈለጉ ለጁዲ ኮሊንስ ተገልፆላታል፡፡ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተፈለጉት ከልዕልት እጅጋየሁ አስፋወሰን የሚወለዱት ሳሙኤል፣ ራሄል፣ ምህረት፣ አስቴር፣ በክሬና ይስሐቅ የተሰኙት ወጣቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ልጆች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አራቱ የ1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አመፅ ሲጀመር፣ ስለቤተሰባቸው ስጋት ገብቷቸው በውጪ አገር ሲከታተሉት የቆዩትን ትምህርት አቋርጠው ወደ አገራቸው የተመለሱ ነበሩ፡፡
ጁዲ ይህን ግንኙነት ከፈጠረች በኋላ፣ ወደ አሜሪካ ተመልሳ የእቅዱን አተገባበር በቅርብ በመከታተል፣ ከባሏ ከዴንተን ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት መሰረች፡፡ አሁን ቁጥራቸው አስር የደረሰውን የጃንሆይ የልጅ ልጆች ከኢትዮጵያ በምስጢር ለማስመለጥ የሚያስፈልገውን እቅድ የማውጣት፣ ገንዘብና ቁሳቁስ የማደራጀቱ ተግባር በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ይቀለጣጠፍ ጀመር፡፡
በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ ለሚገኘው ለዴንተን አጠቃላይ የማምለጫ እቅዱን ንድፍና አተገባበር የሚያስረዳ አንድ ሰው ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ተደረገ፡፡
ይህ ሰው “ዶክተሩ” የተሰኘ የምስጢር ስም የተሰጠው ሲሆን አራቱን የማደጐ ልጆችና ተጨማሪዎቹን ስድስት የጃንሆይ የልጅ ልጆች ከኢትዮጵያ የሚወጡበትን ስልት፣ ቀንና ስፍራ ለዴንተን በማስረዳት ጥርጊያውን እንዲያቀና ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር፡፡“ዶክተሩ” እሁድ ሰኔ 19 ቀን 1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ዴንተንን አግኝቶ ዝርዝር የማምለጫ እቅዱን ንድፍና በዚያም ውስጥ የዴንተን ሚና ምን መሆን እንዳለበት በማስረዳት ተመልሷል፡፡ በዚህም መሰረት ዴንተን የሚጠበቅበት አስሩን ልጆች በኪራይ መኪና ከአዲስ አበባ አውጥቶ ሶደሬ ማድረስ ብቻ ይሆናል፡፡ ለዚህም የተቆረጠው ቀን ሐምሌ 10 ቀን 1969 ዓ.ም ነበር፡፡ከ15 ቀናት በኋላ ዴንተን ከኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት ኩምቢ ቮልስ ዋገን ተከራይቶ ለጉዞ ዝግጁ በማድረግ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ ዴንተን ቅዳሜ ሐምሌ 9 ቀን 1969 ዓ.ም ጧት፣ አራቱን የማደጐ ልጆቻቸውንና ስድስቱን የአክስቶቻቸውን ልጆች በመኪናው ይዞ፣ አስፈሪውን የአዲስ አበባ የፍተሻ ኬላ በማለፍ በሰላም ሶደሬ ደረሰ፡፡ ምሽቱንና ሌሊቱንም በሶደሬ መዝናኛ ስፍራ ያለምንም ችግር አሳለፉ፡፡እሑድ ሐምሌ 10 ቀን 1969 ዓ.ም የወራት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው “የካተሪን ኦፕራሲዮን” የሚከናወንበት እለት በመሆኑ፣ ዴንተን በአይኑ እንቅልፍ ሳይዞር ነበር የነጋው፡፡ በእቅዱ መሰረት ከጠዋቱ ልክ ሦስት ሰዓት ከመሆኑ በፊት ዴንተን ከአስሩ ልጆች ጋር ከሶደሬ መዝናኛ ወጥቶ ጥቂት ከተጓዘ በኋላ ገላጣ ሜዳማ ስፍራ ሲያገኝ መኪናውን አቁሞ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ገና ከመኪናው ሳይወርድ አንድ አነስተኛ አውሮፕላን ሲያንዣብብ፤ ሁለተኛ አውሮፕላንም ሲከተለው ተመለከተ፡፡ አውሮፕላኖቹ በተከታታይ መሬት ላይ እንዳረፉም ዴንተንና አስሩ ህፃናትና ወጣቶች ከመኪናው ወርደው በፍጥነት በሁለቱ አውሮፕላኖች ውስጥ ገብተው በረራው ተጀመረ፡፡አውሮፕላኖቹ መንገደኞቹን ይዘው ለጥቂት ሰአታት በመብረር፣ መሐል ኬንያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሰዋራ ስፍራ ላይ አርፈው እንግዶቻቸውን ሲያወርዱ፣ አስፈሪውና አደገኛው “የካተሪን ኦፕራሲዮን” የመጀመሪያው ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ እርግጥ ሆነ፡፡ ዘመቻውን በአሜሪካ ስትከታተል የቆየችው ጁዲ ኮሊንስ፤ መልካሙን ዜና እንደሰማች፣ በማግስቱ ወደ ኬንያ የበረረች ሲሆን ናይሮቢ እንደደረሰችም ልጆቹን ወደ አሜሪካ ለመውሰድ የሚያስፈልገውን ተግባር በተራዋ ማቀለጣጠፍ ጀመረች፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ለጃንሆይ የልጅ ልጆች ቪዛ በመስጠት የማስመለጡ ተግባር ተሳታፊ ሆኖ እንዲገመት ስላልፈለገ፣ እንግዶቹ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ከልክሏቸዋል፡፡ይሁን እንጂ በኬንያ የስዊድን ኤምባሲ፣ አስሩ ልጆች ወደ ሀገሩ እንዲገቡ ቪዛ ስለሰጣቸው፣ ሐምሌ 22 ቀን 1969 ዓ.ም ዴንተን፣ ጁዲና አስሩ ልጆች በምሥራቅ አፍሪካ አየር መንገድ ወደ ስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በረሩ፡፡ በስቶክሆልም ሁለት ሳምንታት ከቆዩ በኋላ፣ በጊዜው በአውሮፓ የአሜሪካ ስደተኞች መቀበያ በነበረው ምዕራብ ጀርመን ሲዘዋወሩ ቆይተው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡ጁዲና ዴንተን ከእውነተኛ መንፈሳዊ ሰዎች የሚጠበቀውን ርህራሄ ማሳየት የጀመሩት የደርግን እርምጃ ሳይፈሩ ልጆቹን ተቀብለው በማሳደግ ሲሆን፤ የፍቅራቸውን ፍፁምነት ያመለከቱት ደግሞ ራሳቸውን ፍፁም አደገኛ ለሆነ ሁኔታ አጋልጠው፣ ልጆቹን ከኢትዮጵያ ለማውጣት በመወሰናቸው ነበር፡፡በጃንሆይ የልጅ ልጆች ላይ ያንዣበበውን አደጋ ተረድተው ማስመለጡን የነደፉትና ያቀነባበሩት በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ምንም ልምድ የሌላቸው ሚስዮናውያን ባልና ሚስቶች መሆናቸው ድርጊቱን ከተመሳሳይ ታሪኮች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ይህም ገድል አ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም (Code Word – Catherine) በሚል ርእስ በመፅሐፍ ታትሞ ሲቀርብ፣ እንደ ጣፋጭ ልቦለድ በርካታ አንባቢያንን ለማስደሰት በቃ፡፡

 

br /

Read 4126 times Last modified on Wednesday, 19 December 2012 07:21