Saturday, 15 December 2012 12:57

የእኛ ሰዎች በየመን Featured

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(1 Vote)

ተስፋውን የተነጠቀው ሐፍቶም ግደይ!
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን የስደተኞቹን ትንቅንቅ ማየት እንኳን እንስፍስፍ አንጀት ላለው ሰው ይቅርና ድንጋይ ልብ አላቸው ለሚባሉት የየመን ቤዶይኖችም የሚቻል አይደለምባለፉት ሁለት ሳምንታት የመከራ ታሪኳን የነገረቻችሁ የባቲዋ ታዳጊ አይሻ ኑርሁሴን “አይዞሽ ተስፋ አትቁረጪ!” ለሚሏት ሰዎች ምን ብላ እንደምትመልስላቸው ዘወትር ግራ ይገባታል፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ አይሻ ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አይደለችም፡፡ አስከፊው የየመን ስደት የነገ ተስፋቸውን የነጠቀባቸው፣ የእድሜ ልክ ምኞትና ጉጉታቸውን እንደጉም ካበነነባቸው በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩት ስደተኛ የእኛ ሰዎች ውስጥ አንዷ እንጂ፡፡

ሐፍቶም ግደይንም (የአባቱ ስም የተቀየረ) የመን ለመግባት ባደረገው የስደት ጉዞ የተቀበለውን መከራና ያየውን ፍዳ በወሬ ወሬ ሰምታችሁ አሊያም ራሱ ነግሯችሁ ሲያበቃ፣ ለማጽናናት ብላችሁ “አይዞህ! ሁሉም ነገር ያልፋል፡፡ ተስፋ አትቁረጥ!” ስትሉት ከመቅጽበት አንገቱን በመድፋት፣ ከፍተኛ የቅሬታ ቃና ባለው ድምጽ “ህእ!” ብሎ ፀጥ የሚልባት ሚስጥር በስደት ጉዞው ወቅት የተፈራረቁበት መከራና ፍዳ እንዲሁም የመን ከገባ በኋላ የጠበቀው የስቃይና የፈተና ኑሮ፣ የዘመናት ህልሙንና ተስፋውን ነጥቆ ባዶውን ስላስቀረው ብቻ ነው፡፡ 
በየመን አንዱ ቤት ከሌላኛው ቤት፣ አንዱ ህንፃ ከሌላኛው ህንፃ የሚለየው በዲዛይኑ ሳይሆን በመጠኑ ብቻ ነው፡፡ እንደ ሰንአና ኤደን በመሳሠሉት የየመን ታላላቅ ከተሞች አይናችሁ እስኪታክተው ድረስ የምታዩት የበርና የመስኮት ክፈፋቸው በነጭ ቀለም የተጌጠና አንድ አይነት ዲዛይን ያላቸው፣ ነገር ግን በመጠናቸው ብቻ የተለያዩ ቡናማ ቤቶችና ህንፃዎችን ነው፡፡ የመን ቡናማና ነጭ ቀለማት ብሔራዊ ቀለማቴ ናቸው ብትል ማንም “ምን ነካሽ?” አይላትም፡፡
ስለዚህ የየመንን ከተሞችና መውጫ መግቢያቸውን በሚገባ ካላወቃችሁት በቀር ቤትና ህንፃዎችን ምልክት አድርገው ቢነግሯችሁ አንድን አካባቢ በፍጥነት ለይቶ ለማወቅ በእጅጉ መቸገራችሁ የማይቀር ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ በዋና ከተማይቱ በሰንአ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ከጠፋባችሁ ወዲያ ወዲህ ሳትሉ መሄድ ያለባችሁ ሀዳ፣ ዘብሄሪና ከፍጂ እየተባሉ ወደሚጠሩት የሰንአ ሰፈሮች ብቻ ነው፡፡
እነዚህ ሰፈሮች በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖሩበታል እንደሚባለው የአስራ ስምንተኛው ጐዳና አካባቢ ማለት ናቸው፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ከገቡት አንስቶ የእድሜአቸውን አብዛኛውን ዘመን ከፈጁት ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእነዚህ የሰንአ ሠፈሮች ይኖራሉ፡፡ የምትፈልጉት ሰው በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ ተፈልጐ ካልተገኘ፣ በሰንአ አለመኖሩን ለማረጋገጥ ያላችሁ የመጨረሻ እድል ወደ ሀቢሳ አየር ማረፊያ በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ሄዳችሁ መፈለግ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ላይም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የእኛ ሰዎች የስደት ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡
ወደ ሀቢሳ አየር ማረፊያ የሚወስደውን ይህንን አውራ ጐዳና ለማግኘት ለሰንአ ከተማ እንግዳ ከሆናችሁ፣ የሚቀለው የመኖች ከጥቂት ወራት በፊት “የእድሜ ልክ” ፕሬዚዳንታቸው በነበሩት አሊ አብደላ ሳላህ ላይ ተቃውሞአቸውን ሲገልፁ ወደ ነበረበት በሰንአ እምብርት ላይ ወደሚገኘው ዋናው አደባባይ መጓዝ ነው፡፡
እዚህ አደባባይ ከደረሳችሁ በኋላ ፊታችሁን ወደ ፀሀይ መግቢያ አቅጣጫ አዙራችሁ ከቆማችሁ፣ ሁለት በአንፃራዊነት ሠፋፊና ቀጥ ያሉ አውራ መንገዶችን ማየት ትችላላችሁ፡፡ በስተቀኛችሁ ያለውን ጐዳና ትታችሁ በቅርብ ርቀት ላይ ያለውን ሁለተኛውን ጐዳና ከመረጣችሁ፣ ወደ ሀቢሳ አየር ማረፊያ ይወስዳችኋል፡፡ በስተቀኝ ያለውን ጐዳና ከመረጣችሁ ግን መሄድ የምትችሉት ወደ ከፍጂ ሰፈር ነው፡፡
ወደ ሀቢሳ አየር ማረፊያ የሚወስደውን አውራ ጐዳና ተከትላችሁ ቁልቁል አንድ ሁለት መቶ ሜትር ያህል እንደተጓዛችሁ ታዲያ መደዳውን የተገጠገጡ በርካታ የየመን ምግብ ቤቶችን ታገኛላችሁ፡፡
አንዳንዶቹ ዘመናዊ ምግብ ቤቶች ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን የደከሙ የሚባሉ አይነት ናቸው፡፡ ታዲያ ጠዋት ረፈድፈድ አድርጋችሁና ምሽት ላይ ወደ አምስት ሰአት አካባቢ ወደ እነዚህ የየመን ምግብ ቤቶች ጐራ ብትሉ፣ በየምግብ ቤቶቹ በር ላይ የተኮለኮሉ አካላቸው የኮሰመነና አመዱን የነፋባቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ታገኛላችሁ፡፡
ሀፍቶም ግደይን የምታገኙትም እዚያው ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ እዚያ የተኮለኮሉት የየምግብ ቤቶችን ቆሻሻ ለመድፋትና ትርፍራፊ ምግብ ካገኙ ለመመገብ ነው፡፡
ከሁለቱ አንዱን ካገኙ በጣም አሪፍ ነው፡፡ ትርፍራፊ ወይም ኡፋው ከሆነ የእለት እንጀራቸውን አገኙ ማለት ነው፡፡ ቆሻሻውን ከሆነ ደግሞ ሀቢሳ አየር ማረፊያ ሊደርሱ ሲሉ በስተግራ በኩል ካለው ትልቅ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የብረት ገንዳ ውስጥ ደፍተው ሲመጡ፣ እንደ ምግብ ቤቱ ባለቤት ወይም ሀላፊ ልግስና መጠን ሁለት መቶም ሁለት መቶ ሀምሳም የየመን ሪያል ያገኛሉ፡፡ ቢያንስ ምሳቸውን አሊያም ራታቸውን ሊገዛላቸው ይችላል፡፡ ከቆሻሻው ውስጥ በስህተት የተደባለቀ የምግብ ትራፊ ከተገኘም እሰየው ነው፡፡
ኡፋውና የሚደፋው ቆሻሻ በአንድ ላይ ከተገኘ ግን ልዩ ፌሽታ ነው፡፡ ትልቁ ችግርና ፈተና ግን ከእያንዳንዱ ምግብ ቤት የሚገኘው ኡፋ ትንሽ፣ የቆሻሻ መድፊያው የላስቲክ ጀሪካንም አንድ ብቻ መሆንና የእነሱ ቁጥር እጅግ መበርከቱ ነው፡፡
ይህ ከፍተኛ የመጠን ልዩነት ኡፋውን ለማግኘትም ሆነ ቆሻሻውን ወስዶ ለመድፋት በስደተኞቹ መካከል የሚደረገውን ትንቅንቅ እጅግ የከፋ አድርጐታል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን የስደተኞቹን ትንቅንቅ ማየት እንኳን እንስፍስፍ አንጀት ላለው ሰው ይቅርና ድንጋይ ልብ አላቸው ለሚባሉት የየመን ቤዶይኖችም የሚቻል አይደለም፡፡
ሀፍቶም ግደይ ካህራዝ ከተማ ከሚገኘው የስደተኞች መቀበያና ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፕ ወጥቶ፣ ሰንአ ከተማ ከገባበት ካለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ የእለት ተዕለት የስደት ህይወቱን የሚያሳልፈው በዚህ ትንቅንቅ ውስጥ ነው፡፡
የእለት ተዕለት ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ አይነት ግብግብም ከስነልቦና ስቃዩ በተጨማሪ ከፍተኛ የአካላዊ ጉዳት ክፍያ አስከፍሎታል፡፡ የምግብ ቤት ኡፋ ለማግኘትና ቆሻሻ ወስዶ ለመድፋት ተኮልኩለው ይጠባበቁ ከነበሩት የእሱው ቢጤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር ሲታገል ሁለት ጊዜ ከምግብ ቤቶቹ ደረጃ ላይ ወድቋል፡፡ በመጀመሪያው አፍንጫው ተሠበረ፡፡ በሁለተኛው ደግሞ የግራ እጁ ክንድ ሁለት ቦታ ላይ ተሠበረ፡፡ እናም አሁን አፍንጫው ያለማቋረጥ የአፍላ ጉንፋን ንፍጥ አይነት ቀጭን ፈሳሽ ያመነጫል፡፡
የግራ እጁም እንደልቡ አይታዘዘውም፡፡ ይህ የደረሰበት አካላዊ ጉዳት ለሌላ የስነልቦና ጥቃትም ዳርጐታል፡፡ አንዳንድ ስደተኞች ሁሌም ደርቆና ፀድቶ የማያውቀውን አፍንጫውን እያዩ “ንፍጦ” እያሉ ይሰድቡታል፡፡
እንደ ልብ የማይንቀሳቀሰውን እጁን እያዩ ደግሞ “ከርፋፋ ሽባ!” እያሉ ያንጓጥጡታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ልቡ በሀዘንና በብስጭት ያለመጠን እየደማበት በሚሠድቡትና በሚያንጓጥጡት ላይ ክፉ በቀል ለመፈፀም ቢያስብም ሞክሮት አያውቅም፡፡
ግን አስፓልቱ ዳር ሠዋራ ቦታ ይፈልግና ኩርምት ብሎ በመቀመጥ፣ እንደ መርግ የሚከብደውን የልቡን ሀዘንና የሆዱን ብሶት ምርር ብሎ በማልቀስ በትኩስ እንባው ሊያጥበው ይሞክራል፡፡
ሀፍቶም ግደይ በዚህ ጊዜ ነው እዚህ ሄድኩ ብሎ እንኳ ሳይነግራቸውና ሳይሠናበታቸው ከዛሬ አስራ አምስት አመት በፊት የተለያቸው ቤተሠቦቹ ትዝ የሚሉትና በናፍቆታቸው እንደ አዲስ መንቀጥቀጥ የሚጀምረው፡፡
ሀፍቶም ግደይ የየመንን የስደተኝነት እጅግ አስከፊ ኑሮ ለመቋቋም ፈጣሪ የእዮብን ትዕግስትና የሳምሶንን ጉልበት እንዲሰጠው ዘወትር ማለዳ ልመናውን ያቀርባል፡፡ ቀኑን ሙሉ ኡፋ ለማግኘትና ቆሻሻ ለመድፋት ከዚያ ሁሉ ወፈ ሰማይ ኢትዮጵያዊ የሱ ቢጤ ስደተኞች ጋር በሌለው አቅምና በተጐዳ አካሉ ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሲታገል ይውላል፡፡
ቀኑ ተገባዶ ፀሐይዋ ምድሪቱን ለጨለማው አስረክባ ዘወር ስትል ግን የሀፍቶም ልብና መልክ ልክ እንደ ምሽቱ መጥቆር ይጀምራል፡፡ ይሄኔ መላ የሰራ አካላቱ በከፍተኛ ፍርሃትና ወደር የለሽ ጭንቀት መራድ ይጀምራል፡፡ ምናለ ባይመሽ? ፀሐይቷስ ምናለ ባትጠልቅ? እያለ የጭንቀትና የጥበት ምኞቱን የሚመኘው ከዚህ መራራ ፍርሃትና ጭንቀት ለአንድ ቀን እድሜም እንኳ ቢሆን እፎይ ብሎ ለማሳለፍ ነበር፡፡
የዚህ ዋነኛ መነሾው ደግሞ የቀን ውሎው ያለመጠን መክፋቱና የትናንትና ጐምዛዛ ህይወቱ ከነግሳንግሱ የትዝታን ፈረስ ጭኖ፣ ፀሐይዋ የብርሃን እግሯን ገና ከመሰብሰቧ ከተፍ ብሎ መላ አካሉን ክፉኛ እየለበለበ ስለሚያሳድረው ነው፡፡ ነገሩ በዚህ ብቻ ቢያበቃላት ኖሮ እሱም አምላኩን ተመስገን ለማለት አንድ ጥሩ ምክንያት ባገኘ ነበር፡፡
ለዚህ ግን አልታደለም፡፡ ነገሩ የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል እንደሚባለው አይነት ነው፡፡ ጐምዛዛው የትናንትና ትዝታው ክፉኛ እያንገላታው ማደሩን ያወቀው ፀፀትም ያን የማይጠግብ መጋዝ ጥርሶቹን አግጥጦ፣ ችጋር ክፉኛ አጐሳቁሎ ነጭ አመዱን የነፋበትን ኮስማና ሰውነቱን ሲያነክተው ያድራል፡፡
ይህን እንዲህ ነው ተብሎ በቃላት የማይነገር ስቃይ መቋቋም ሲያቅተው፣ ሀፍቶም ግደይ በውድቅት ሌሊት መላ አካሉ እንደ አንዳች ነገር እየተንዘፈዘፈ ህቅ ብሎ ተንሰቅስቆ ያለቅሳል፡፡ በዚህ ጊዜም ቢሆን ወደ ሀቢሳ አየር ማረፊያ በሚወስደው አውራ ጐዳና ጥግ ላይ የተበጣጠሰ ካርቶን አንጥፈው አጠገቡ ከተኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚያገኘው አንዳች አይነት የማጽናኛ በጐ ቃላት ሳይሆን ከቀን ጀምሮ ሲሠማው የነበረውን ዘለፋና እርግማን ብቻ ነው፡፡ “እንግዲህ ጀመረው ይሄ ሽባ! ምነ እንዲያው አላህ ይዞህ በሄደ” “ዝም አትልም አንተ የሞትክ! እንዲያው ካንተ ማላዘን የሚገላግለን ነገር ይጥፋ? ውሻ! የሰው ውሻ!” በቃ ይህንን ብቻ ነው፡፡
እንደዚህ አይነት ስድቦች ለሀፍቶም አዲስ አይደሉም፡፡ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የረባውንም ያልረባውንም ሰበብ እያደረጉ፣ በየቀኑ ስለሚሰድቡት ስድቦቹን ጆሮው በደንብ አድርጐ ለምዶዋቸዋል፡፡
ጨርሶ መልመድ ያቃተው ነገር በየቀኑ የሚቀበለው ክፉ ስድብ የሚፈጥርበትን ወደር የለሽ የስነልቦና ስብራት ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለመቋቋም የሚያስችል ትዕግስትም ሆነ ጥንካሬ እስከዛሬ ድረስ ማግኘት አልቻለም፡፡ በራሱ ብዙ የማደሪያና የመዋያ ቦታውን በመለዋወጥ እነዚያን የሚስድቡትን ሰዎች ለመራቅ ሞክሯል፡፡ የሆድ ነገር ግን ሆድ ይቆርጣል፡፡ እናም ነፍስን በህይወት ለማቆየት የሚረዳውን የእለት ኡፋውን ለማግኘትና ከቀናውም ቆሻሻ በመድፋት ጥቂት ሪያሎችን ለማግኘት የግዱን ወደዚሁ ቦታ ተመልሶ ይመጣል፡፡ ትቷቸው፣ ሸሽቷቸው የሄደው ሰዎችም እንደተዋቸው ሆነው ይጠብቁታል፡፡ ሁሉም ነገር የነበረውን ሂደት እንደያዘ መጓዙን ይቀጥላል፡፡ ስድቦቹም ጭምር፡፡
ለተደጋጋሚ ጊዜ የሞከረው ሽሽት እውር ቢሸፍት ከጓሮ አያልፍም የተባለው አይነት የሆነበት ሀፍቶም፤ ፈጣሪው ከዚህ አጥንት የሚሠነጥቅ ስቃይ ገላግሎ እፎይ እንዲያስብለው ወይ ተሳዳቢዎችን አለበለዚያም እሱን በሞት እንዲወስደው አጥብቆ ተመኝቶም፣ ተማጽኖም የስለት እጣን ቋጥሮም ያውቃል፡፡ ሁሉም ግን ባዶ ነው፡፡ ተሳዳቢዎቹ ዛሬም አሉ፡፡ እሱም ይሄው አለ፡፡ ይህን በከፍተኛ ስቃይ የተሞላ ክፉ አዙሪት መቋቋም ከአቅሙ በላይ ሲሆንበትና ነገር አለሙ ሁሉ ድፍን፣ ጭልም ሲልበት ፈጣሪው የከለከለውን የእለት ሞቱን በገዛ ራሱ፣ በገዛ እጁ ሊሞተው ለበርካታ ጊዜ በቁርጠኝነት ወስኖ ነበር፡፡ ለሶስት ጊዜ ያህልም ሞክሮታል፡፡ እንዲያ የተመኘው ጐምላላው ሞት ግን ሀፍቶምን በጄ ሊለውና ሊታረቀው አልፈለገም፡፡
አጥብቆ በተመኘውና በፈለገው ቁጥር የዚያኑ ያህል ይሸሸዋል፡፡ የዛሬ ሁለት አመት ሚያዝያ ስምንት ቀን፣ ሊደፋ ከተሸከመው የቆሻሻ ጀሪካን ውስጥ በቢጫ ሞላላ የፕላስቲክ ጠርሙስ ግማሽ ያህል የተሞላ ፈሳሽ ነገር አገኘ፡፡
“ተመስገን! በረኪና ተገኘ!” አለ፡፡ “ከዚህ ሁሉ ስቃይ ይሄ በረኪና ይገላግለኛል!” በጉያው ሸጉጦ ይዞ ወደሚያድርበት አስፋልት ዳር አመራ፡፡ ከዚያ ፈጣሪው ነፍሱን እንዲቀበላት አደራ ካለና ሶስት ጊዜ ካማተበ በኋላ በአንድ ትንፋሽ ግጥም አድርጐ ጠጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ራሱን ያገኘው ሰንአ አደባባይ አጠገብ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት በሚወስደው መንገድ በስተግራ በኩል ባለው የመጀመሪያ መታጠፊያ ጠርዙ ላይ በሚገኘው የሼክ መንሱር አብደላ መለስተኛ ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡
በገዛ ትውከትና አይነምድሩ ክፉኛ ተበክሎ እየተፈራገጠ ሲያጣጥር ድንገት ያዩት ሁለት የሰንአ ቀይ ጨረቃ አባላት ነበሩ ወደዚያ መለስተኛ ሆስፒታል በመውሰድ ህይወቱን ያተረፉት፡፡
የፕላስቲኩ ባለ ቢጫ ቀለም መሆንና ቅርፁ የበሪኪና ላስቲክ ቢመስለውም በውስጡ የያዘው ፈሳሽን ግን በረኪና ሳይሆን የብረት ቀለም መበጥበጫ “አኳራጅ” ነበር፡፡
በሁለተኛ ሙከራው ታንቆ ለመሞት ፈልጐ ሁለት ጊዜ ቢሞክርም ሊታነቅበት የሞከረው ገመድ ሁለቴም ተበጥሶ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ ገመዱ የላጠው አንገቱ ግን ክፉኛ ቆስሎበት ሲያሰቃየው ከርሟል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ያደረገው ሙከራ ሊሳካለት ነበር፡፡ አስፓልቱ ዳር አብረውት ከሚተኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል የቲቢና የወባ በሽተኛ ስለነበር በየእለቱ የሚወስደው በርካታ መድሀኒቶች ነበሩት፡፡
አንድ ምሽት ላይ ያለማቋረጥ የሚያስለው ሳል፣ ትንሽ ጋብ ብሎለት እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርገው፣ ሃፍቶም ቀስ ብሎ መድሃኒቶቹን በሙሉ ከሠረቀው በኋላ፣ በጥድፊያ እጁ እንዳመጣለት ክኒኖቹን መዋጥ፣ ፈሳሽ መድሃኒቶቹን ደግሞ ብልቃጦቹን እየከፈተ በአንድ ትንፋሽ መጨለጥ ጀመረ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 2870 times Last modified on Wednesday, 19 December 2012 07:29