Saturday, 15 December 2012 12:48

የሰሜን ጎንደር የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ከትርጉም ሚካኤል med@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

ውድ አንባብያን! የባለፈው ሳምንት የሰሜን ጎንደር የጉዞ ማስታወሻዬ ላይ የቋራውን አፄ ቴዎድሮስ በተመለከተ የታሪክ ተመራማሪዎችና ፀሐፍት ካስቀመጡልን በተለየ መልኩ የስብሃት ገ/እግዚአብሔር “እነሆ ጀግና” በሚለው መጽሐፍ ማሳየቱን ጠቅሼ በደፈናው ማለፌን ያስተዋሉ አንዳንድ አንባብያን፤ ምነው ከመጽሐፉ ላይ ምሳሌ ጣል ሳታደርግ አለፍክ የሚል ሃሳብ ሰጥተውኛል፡፡ እውነትም ጠቅሼ ማለፉ አግባብ መሆኑን በማመን ከመጽሐፉ ውስጥ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ሰብአዊነትና ማንነት እኔ ሳነባቸው የማረኩኝን ማንነቶቹን የሚመለከቱ አንድ ሁለት ወጎች አቅርቤ ማለፉን አመንኩበት፡፡ እነሆ!!
ክፍል 2

…እቴጌ መነን ካሳን ላኩበት፡፡ እምቢ አልመጣም አለ፡፡ ደጃች ወንድይራድ የሶስት ደጃዝማች የሚያህል ሰራዊት ይዞ ዘመተበት፡፡ ካሳ በሽፍትነቱ ጊዜ አገዛዙን አገሬው ወዶለት ኖሮ፤ አሁን በሙሉ ከተተለት፡፡ ካሳ ጦሩን አፋፍ ላይ አዘጋጅቶ ድንኳኑን ተክሎ ጠበቀ፡፡ ደጃች ወንድይራድ እያስፎከረ - “የኮሶ ሻጭ ልጅ እጁን ቢሰጥ ይሻለዋል” እያሰኘ - መጣ፡፡ 
ካሳ ከደርቡሾች የማረከው የሜዳ መነጽር አለው፡፡
በሱ ያየዋል፡፡
ተዋበች ካሳን፤ “ተኛ ደክሞሃል፡፡ ሲደርሱ እቀሰቅስሃለሁ” ትለዋለች፡፡ የት ሲደርሱ እንደምትቀሰቅሰው አመላክቷት ይተኛል፡፡…
“ታጠቅ! ታጠቅ ደረሱ!” ብላ ቀሰቀሰችው፡፡ ከዚያ ወዲህ የፈረስ ስሙ “አባ ታጠቅ” ሆነ፡፡
ካሳ በቀላሉ ድል አደረገ፡፡ ወንድይራድ ተማረከ፡፡ “ወንድ መሆን ነው እንጂ አስቸጋሪው ወንድይራድ፤ መሳደብ ቀላል ነው፡፡ እኔ እያለሁልህ የወንድ እናት ትሳደባለህ? ብሎ ለቁርስ፤ ለምሳ ለእራት ኮሶ፤ እንቆቆ፤ ቀጨሞ፤ እያጠጣ ወንድይራድን በቁርጠትና በተቅማጥ ገደለው፡፡
አባ ታጠቅ ካሳ ደጃች ወንድይራድን ድል ሲያደርግ ጊዜ እቴጌ መነን እርቅ ጠየቁ፡፡፡ በቋራ ግዛቱ ላይ ደምቢያን ጨመሩለት፡፡ እዚያ ሄዶ ተቀመጠ፡፡
እንግዲህ እቴጌ መነን ቀደም ሲል ደምቢያን ለጐጃም ገዢ ለደጃዝማች ጐሹ ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ አሁን ታዲያ ደጃች ጐሹ” ለምን ግዛቴን ይወስድብኛል? ብለው እቴጌን ቢጠይቁ “መች ሰጥተነው? በጉልበቱ ነው እንጂ የወሰደው” ሲሉ ይመልሱላቸዋል፡፡ ደጃች ጐሹም ይናደዱና “ይህ ውርጋጥ! አሳየዋለሁ!” ብለው ይዘምቱበታል፡፡
ካሳ ለደጃች ጎሹ እባክዎን አንጣላ፡፡ “እቴጌ ሊያጋጩን ፈልገው ነው እንጂ ድሮውንም ደምቢያ ወደዚህ ነው፤ ከጎጃም አይደለም” ብሎ ላከባቸው፡፡
አሻፈረኝ ብለው ዘመቱበት፡፡ ካሳ ሊዋጋቸው ቢገደድም እንዳይሞቱ እንዳይቆስሉ ብዙ ጥንቃቄ ወስዶ ነበር፡፡
በጦርነቱ ዋዜማ የደጃች ጐሹ አዝማሪ፤
“ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሳ
ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ”
እያለ ሲዘፍን አደረ
በጦርነቱ ደጃች ጐሹ በጦር ተወግተው ሞቱ፡፡
ያልወደቁትና ያልሸሹት ወታደሮቻቸው አሁንም ለካሳ ገቡለት፡፡
ካሳ ድንኳኑን ጥሎ ዳባውን ለብሶ ለደጃች ጐሹ ሞት ሰባት ቀን ሀዘን ተቀመጠ፡፡ (ደጃች ጐሹ ለካሳ አጐቱ ነበሩና)
በጦርነቱ ዋዜማ የሰደበውን አዝማሪ በነገታው አስጠርቶ ለምን ሰደብከኝ? ቢለው፤
አዝማሪው፤
“አወይ የእግዜር ቁጣ አወይ የአምላክ ቁጣ፤
አፍ ወዳጁን ያማል የሚሰራው ቢያጣ
ሽመል ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ” ሲል መለሰ፡፡
ካሳም “ትክክል ፈርደሃል” ብሎ በሽመል አስደብድቦ አስገደለው፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ወደ ወሎ ለመዝመት ተገደዱ፡፡ ጊሚቢ በተባለ ነፋሻ ስፍራ ከወይዘሮ ወርቂት ጦር ጋር ለረዥም ጊዜ የወሰደ ውጊያ ተካሄደ፡፡ አልተሸናነፉም፡፡
የወይዘሮ ወርቂት የአዝማች ሆነው ደጃች ወልደ ሚካኤል ለአፄ ቴዎድሮስ እንዲህ ሲል ላከባቸው፡፡
“በኔና በእርስዎ ሀጢያት ይህ ሁሉ ሰው ከሚያልቅ፤ እኔና እርስዎ ፍልሚያ እንግጠም፡፡ ያሸነፈ ሁለቱን ሰራዊት ይጠቅልል፡፡”
አንድ ተራ ደጃዝማች እንዴት እንዴት አባቱ ቢደፍር ነው ከንጉሰ ነገስቱ ልፋለም የሚለው?” ብሎ በመናደድ ገብርዬ መልእክተኛውን ሊሰይፈው ሲል፤ አፄ ቴዎድሮስ ክንዱን እየያዙ፤
“ተውኮ ገብርዬ! ወንድን ወንድ ልግጠም ሲል እንዴት መልእክተኛውን ልግደል ትላለህ?” ይሉትና፤ እሺ ነገ ጧት ይዋጣልን፤ ብለው መልስ ይልካሉ፡፡
በኋላ ሲናገሩ አፄ ቴዎድሮስ፤ “እንደዚያች ሌሊት የረዘመብኝና የፈራሁበት ጊዜ አላውቅም” ብለዋል ይባላል፡፡
አይነጋ የለም ነጋ! ሁለቱ ሰራዊቶች ግምባር ለግምባር ተሰለፉ፡፡
ካሳና ወልደ ሚካኤል በየበኩላቸው ጋሻና ጣምራ ጦር ይዘው ፈረስ ላይ ወጡ፡፡ በሩቁ ተፋጠጡ፡፡
“እርስዎ ይወርውሩ” አለ ወልደ ሚካኤል፡፡
“ቆማጣ ቆመጥማጣ፤ አዝዣለሁ አንቺ ወርውሪ!”
ወልደ ሚካኤል ወረወረ፡፡ ከሸፈ፡፡ ካሳ ወረወረ፡፡ ወጋው፤ ከፈረሱ ላይ ከነበለው፡፡
ጋልቦ ደርሶ የጦሩን አወጋግ ቢመለከት ጦሩ ሰውዬውን ከመውጋትም አልፎ በስቶ ግማሹ ያህል በጀርባው ወጥቶ ይታያል፡፡ “ምንኛ ብፈራ ነው እንዲህ የበሳሁት?” አለ ካሳ በመገረም፡፡ (እንዲህ ደፍሮ “ፈራሁ” ለማለት ምን ያህል ጀግንነት ይጠይቃል? የካሳን ያህል፡፡)
(“እነሆ ጀግና” ገፅ 27-30)
ታዲያ ውድ አንባቢያን የአፄ ታዎድሮስን ማንነት ከስብሀት መፅሃፍ ላይ ይቺን ታህል ጨልፌ ካስቃኘኋችሁ፤ ቅዱስ መፅሐፉ “ንግባ አኸ ሀበ ጥንተ ነገር” ይላልና ወደ ቀደመው ወጋችን እንመለስ፡፡
የቋራ መብራት አቅርቦትን በተመለከተ ደግሞ የራሷ ድራማ አላት፡ ወትሮም ከአዘዞ ወደ መተማ ስንጓዝ መቼም የመንገዱ ድሎትና ስፋቱ አይጣል ነው፡፡ ምስጋና ለመንግስታችን፡፡ ታድያ ከጐንደር 150 ኪ.ሜ ተጉዘን ሸዲ የምትባል ከተማ ላይ ስንደርስ ወደ መተማ መስመር የሚወስደውን አስፋልቱን መንገድ ወደ ቀኝ ትተን በስተግራ በኩል ወደ ቋራ የሚወስደውን 110 ኪ.ሜ የፒስታ መንገድ ተያያዝነው፡፡ ታዲያ ከፀሃዩ ንዳድና ወበቅ በተጨማሪ ይሄን ቋረኛ እንደ ችቦ አጭቀው የሚያልፉና የሚያገድሙ አይሱዙና ኤፍኤስአር መኪኖች የሚያለብሱንን አቧራ እየረገምንና እያራገፍን ስንጓዝ፤ የቆዳቸው ንጣት እንደ መስታወት የሚያብረቀርቅ ከብቶችን እያየን ስንደመም፤ በመንገዳችን አንዳንዴም በግራ አንዳንዴም በቀኝ እየተዘረጉ የሚገረምሙንን የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እያስተዋልን ቋራ ወረዳ ገባን፡፡
ቋራ ወረዳ ስንደርስ ታዲያ “ሞባይል ቻርጅ እናደርጋለን” የሚሉ የሱቅ የጨርቅ ላይ ማስታወቂያዎች ሲበረክቱብኝ ጊዜ “ይህቺ ወረዳ መስመሩ ተዘረጋላት እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይል አላገኘችም?” የሚል ጥርጣሬ አደረብኝ፡፡ በነገራችን ላይ ሞባይል ቻርጅ ማድረጊያ ሱቆች ውስጥ በሰፊ ጠረጴዛ ላይ 150-200 ሞባይሎችን ቻርጅ ለማድረግ የተዘጋጁ ሶኬቶችን ተመልክቼ ጉድ ብያለሁ፡፡
እናላችሁ ወደ ማደሪያዬ (ማደሪያ እንጂ ሆቴል ለማለት ይከብዳል) ገባሁና ሞባይል ባትሪ ቻርጅ ለማድረግ በማሰብ “ሶኬት ይኖር ይሆን?” ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡
“ልትቻርጅ ነው?” (ቻርጅ ልታደርግ ነው)
“አዎ እናቴ”
“እንግዲህማ ማታ ጄነሬተር ሲለኮስ ካልሆነ መች መብራት አለ ብለህ?”
“በመንገዳችን ላይ ግን እኮ የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶ አይቼ ነበር፡፡ ገና አልጀመረም ማለት ነው?”
“ይኸውልህ ወንድም ዓለም! በ1997 ምርጫ ሲቃረብ ኢህአዴግ መንገዱን ሰራልነ፤ በባለፈው ምርጫ ደግሞ መስመሩን ዘርግተውታልኝ፤ ደግሞ በሚመጣው ምርጫ ባልቦላ ሰጥተውነ መብራት እናበራ እንደሁ እንጂ መንግስትስ ይሄን ኹሉ ባንደዜ ከየት ያመጣው ብለህ? እረ ተመስገን ነው አንተዬ”
(ንግግሯ የምሬት ሳይሆን የተቆርቋሪነት መንፈስ አሳየኝና)
“ለመሆኑ ባለፈው ነሀሴ ወር ላይ ጠቅላይ ሚንስትራችን ሲሞቱ ምን አላችሁ?” አልኳት፡፡
“እረ እንዴት ያለው ሰው መጣብኝ ዋ! ነጠላችነን ዘቅዝቀን አለቀስነ፤ ደረታችነን መታነ እንጂ ኋላማ ምን ልናደርግ ብለህ?”
“አይ እንደው አንዳንድ የውጭ ሀገር ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች በየክ/ሃገሩ የኢህአዴግ ካድሬዎች ህዝቡን በማስፈራራት አደባባይ ወጥቶ እንዲያለቅስ አድርገዋል የሚል ነገር ሰምቼ ነበር፡፡ እውነት ነው?”
“እረ በቤዛይት አለም! ይልቅ ዋዛ ፈዛዛውን ትተህ ልብ ብለህ ስማ ልንገርህ፡፡ ህዚህ ወረዳ ሰፊ የሰሊጥ እርሻ አለ፡፡ አሁን ዛዲያ ኢንቨስተሩ ብትል፤ ቋረኛው ብትል፤ ሰፋሪው ብትል እረ አልፎ አልፎም የመንግስት ሰራተኛውም እኮ መሬት እየተከራየ፤ እያሳረሰ ሰሊጥ የማይሸጥ የለም፡፡ ዛዲያ ይሄነን እንድናገኝ ያደረገ ሰው ሞተ ቢባል ኸቤቱ ወጥቶ የማያለቅስ ሊኖር ብለህ ነው?” “ይልቅ! የአዲስ አባ ሰው እድለኛ ነው አንተው፡፡ ኸቤተ መንግስት ገብቶ ኸሬሳው ላይ ተደፍቶ አልቅሷልኝ እኮ፡፡ እኛ ነነ እንጂ እርማችንን ሳናወጣ የቀረን፡፡”
“ሃዘን በርትቶባችሁ ነበር ማለት ነው?”
“እረ አፈር ልብላለት! እንደው አለምዬ! እሱ ሞቶ ቀረ እንጂ እኛማ ምን ልንሆን ብለህ?”
“እንዴት?”
“ይህው አሁን እኔ ትንሽ የሰሊጥ እርሻ አለችኝ፤ ጐንደር ቤት አለኝ፤ ሁለቱ ልጆቼ ኸዚያ ነው ሚማሩ፤ ትራክተር አለኝ፡፡ ከቴም ተይህ በላይ መለስ ዜናዊ ምን ሊያረግልኝ ኑሯል? ተዎው ወንድማለም ግፍ እንዳይሆን፡፡
“በዓመት ስንት ኩንታል ሰሊጥ ታመርቺያለሽ?”
“ትንሽ ነው አንተው!”
“አሁን አምና ስንት ኩንታል ሸጥሽ?”
“ትንሽ ነው አንተዬ፡፡ አንድ 300 ኩንታል ነው፡፡ (300 ኩንታልን በ2000 ብር ምቱት እንግዲህ)
“እንዲህም አርጐ ትንሽ የለ?”
(ይቀጥላል)

Read 3374 times