Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 14:27

የትያትር ቤት መግቢያ ዋጋ ጭማሪ አወዛገበ *ትያትር ቤቶች ጭማሪውን አልተቀበሉትም

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች ላለፉት 10 ዓመታት ለአንድ ሰው የሚከፈለው የትያትር ቤት መግቢያ 15 ብር መሆኑን በመግለፅ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መቶ ፐርሰንት የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን የመንግሥት ትያትር ቤቶች ጭማሪውን ባለመቀበላቸው ውዝግብ እንደተፈጠረ ታውቋል፡፡ “ጭማሪው የተደረገው የአዳራሽ ኪራይ፣ የማስታወቂያና የፕሮዳክሽን እንዲሁም አልባሳትና ቁሳቁስ ዋጋ በመናሩ ነው” የሚሉት የግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች፤ ጭማሪው የተመልካቹን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ብለዋል - “ተመልካች ለለስላሳና ለቀላል ምግቦች ከዚያ ያላነሰ ገንዘብ ያወጣል” በማለት፡፡ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት እና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ጭማሪውን እንደማይቀበሉት ለኢንተርፕራይዞቹ አስታውቀዋል፡፡ 

ባለፈው ረቡዕ ከዋጋ ጭማሪው ጋር በተገናኘ በብሄራዊ ቲያትር ውዝግብ እንደተነሳ ታውቋል፡፡ ”ዕጣ ፈለግ” የተሰኘውን ትያትር “30 ብር አስከፍላችሁ ማሳየት አትችሉም” እንደተባሉ የትያትሩ ደራሲና አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ ትያትር ቤቱ የዋጋ ጭማሪውን የሚገልፅ ደብዳቤ አልደረሰኝም ቢልም የትያትር ኢንተርፕራይዙ ደብዳቤውን ሕዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም ለትያትር ቤቱ ማስገባቱንና በ30 ብር ካላሳዩ ለኪሳራ እንደሚዳረጉ ለጋዜጠኞች መግለፃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ በተፈጠረ ውዝግብ በ30 ብር የምታስከፍሉ ከሆነ ፖሊስ እንጠራለን የሚል ማስፈራሪያ ትያትሩ ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀረው ለትያትሩ ባለቤቶቹ የደረሳቸው ሲሆን ሦስት ተመልካቾች በ30 ብር ትኬት ቆርጠው እንደነበር ታውቋል፡፡ 
በመጨረሻ ግን ተመልካቹ 15 ብር እየከፈለ ገብቷል፡፡ የትያትሩ ደራሲና አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲናገሩ “ተመልካቾቻችንን በማክበርና ከትያትር ቤቱ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ላለማበላሸት ስንል በኪሳራ ለማሳየት ተገደናል፡፡ ጥያቄአችን ግን አልተመለሰልንም” ብለዋል፡፡ በነፃ ገበያ መርህ ዋጋ መቀነስ እና መጨመር መብታችን ነው፤ ትያትር ቤቶችን የሚመለከት አይደለም ያሉት የትያትር ኢንተርፕራይዞች፤ ጥያቄአቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ትያትር ቤትም ከዋጋ ጭማሪው ጋር በተገናኘ በተፈጠረ አለመግባባት ከዕይታ የተስተጓጎለ ትያትር እንዳለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

Read 5823 times