ባለፈው ረቡዕ ከዋጋ ጭማሪው ጋር በተገናኘ በብሄራዊ ቲያትር ውዝግብ እንደተነሳ ታውቋል፡፡ ”ዕጣ ፈለግ” የተሰኘውን ትያትር “30 ብር አስከፍላችሁ ማሳየት አትችሉም” እንደተባሉ የትያትሩ ደራሲና አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ ትያትር ቤቱ የዋጋ ጭማሪውን የሚገልፅ ደብዳቤ አልደረሰኝም ቢልም የትያትር ኢንተርፕራይዙ ደብዳቤውን ሕዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም ለትያትር ቤቱ ማስገባቱንና በ30 ብር ካላሳዩ ለኪሳራ እንደሚዳረጉ ለጋዜጠኞች መግለፃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ በተፈጠረ ውዝግብ በ30 ብር የምታስከፍሉ ከሆነ ፖሊስ እንጠራለን የሚል ማስፈራሪያ ትያትሩ ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀረው ለትያትሩ ባለቤቶቹ የደረሳቸው ሲሆን ሦስት ተመልካቾች በ30 ብር ትኬት ቆርጠው እንደነበር ታውቋል፡፡
በመጨረሻ ግን ተመልካቹ 15 ብር እየከፈለ ገብቷል፡፡ የትያትሩ ደራሲና አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲናገሩ “ተመልካቾቻችንን በማክበርና ከትያትር ቤቱ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ላለማበላሸት ስንል በኪሳራ ለማሳየት ተገደናል፡፡ ጥያቄአችን ግን አልተመለሰልንም” ብለዋል፡፡ በነፃ ገበያ መርህ ዋጋ መቀነስ እና መጨመር መብታችን ነው፤ ትያትር ቤቶችን የሚመለከት አይደለም ያሉት የትያትር ኢንተርፕራይዞች፤ ጥያቄአቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ትያትር ቤትም ከዋጋ ጭማሪው ጋር በተገናኘ በተፈጠረ አለመግባባት ከዕይታ የተስተጓጎለ ትያትር እንዳለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡