Saturday, 08 December 2012 13:42

“ባለ ቅኔ ሎሬት”

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehalu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

ማዕረገ ጥበብ ዘፀጋዬ ገብረ መድኅን
“ባለቅኔ ሎሬት” (Poet Laureate) የተሰኘው ማዕረግ የተገኘው ከጥንታዊት ግሪክ (በኋላም ሮማውያን) ጥበበኞችንና አሸናፊዎችን የማክበር፣ የመሾምና የመሸለም ልማድ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ወይራ የባለ ቅኔዎች የበላይ ጠባቂ የሆነው የአፖሎ ቅዱስ ዛፍ ነው ተብሎ በጥንታዊ ግሪካውያን ይታመንበት ስለነበር፣ በተሸላሚዎች አናት ላይ በወይራ ዘለላ የተጐነጐነ አክሊል (Laurel Crown) ይደፋላቸው ነበር፡፡በዘመናዊው የዓለም ታሪክ፤ “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ ሹመት ሆኖ በሥራ ላይ መዋል የጀመረው በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ ውስጥ ሲሆን ማዕረጉም የሚሰጠው የላቀ ሥራ ላበረከተ ባለ ቅኔ ነበር፡፡

ባለ ማዕረጉም ከእንግሊዝ ቤተ መንግሥት የሚቀበለው ደሞዝ በየጊዜው ይቆረጥለት ነበር፡፡
ይህ በእንግሊዝ የተጀመረው “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ የመስጠት ልማድ ሳይስተጓጐል፣ ከሦስት መቶ አመት በላይ በመቀጠል አሁን ያለንበት ዘመን ድረስ ዘልቋል፡፡
አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ከእንግሊዝ “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ ጋር አቻነት ያለው “የኮንግሬስ ቤተ መፃህፍት ባለ ቅኔ” የተባለ ጥበባዊ ሹመት ለሃምሳ አመት ያህል ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1985 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት “ባለ ቅኔ ሎሬት” የተሰኘ ማዕረግ ያቋቋመ ሲሆን፤ ማዕረጉ “በኮንግሬስ ቤተ መፃህፍት የቅኔ አማካሪ” ተብሎ ለሚሾም ሰው የሚሰጥ ነው፡፡ የአሜሪካ “ባለ ቅኔ ሎሬት” በአንዳንድ ብሔራዊ ክብረ በአላት ላይ ቢያንስ አንድ አቢይ ሥራውን እንዲያበረክት የሚጠበቅበት የመንግሥት ደሞዝተኛ ነው፡፡
በእንግሊዝ እንደገና የተጀመረው ባለ ቅኔን በሎሬት ማዕረግ የመሸለም ልማድ ተስፋፍቶ ዛሬ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ስኮትላንድ እና ኔዘርላንድ የጥበብ ታላላቆቻቸውን የሚያከብሩበት ማዕረግ ሆኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ይህንን ማዕረገ ጥበብ ዩኒቨርሲቲዎችና የታወቁ ዓለም አቀፍ ማህበራት አገርና ድንበር ሳይወስናቸው ለጥበበኞች ያበረክታሉ
ምንም እንኳ “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ የመሸለም ልማድና አሰራር ለአገራችን ባእድ ቢሆንም፤ ለባለ ቅኔዎችና ባለ ዜማዎች ልዩ ልዩ ማዕረግ በመስጠት መሾምና መሸለም በቤተ ክህነት አካባቢ የተለመደ ነበር፡፡
ከ”ባለ ቅኔ ሎሬት” ጋር የሚቀራረብ ኢትዮጵያዊ ማዕረገ ጥበብ (Literary Title) “ብላቴና ጌታ” የተሰኘውና በንጉሠ ነገሥቱ ለሲቪሎች ብቻ የሚሰጥ ከፍተኛ ሹመት ነበር፡፡ ዝክረ ነገር የማዕረጉን ደረጃ ሲተነትን፤ “በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በልዩ ልዩ ክፍል ላሉ ሹማምንት፤ ለሚኒስትርነት ደረጃ ለደረሱና ስሜታቸውም ወደ ሥነ ፅሁፍ ጥናት ላዘነበለ የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው” በማለት ይገልፀዋል፡፡
ከአገራችን የጥበብ አውራዎች መካከል አንጋፋ የሆነው ፀጋዬ ገብረ መድኅን በዚህ “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ ከአስር ዓመት በላይ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ ማዕረጉ የተገኘበት አግባብ እና ሁኔታ በግልፅ ባለመታወቁ ፀጋዬን ለአሉባልታ ዳርጐታል፡፡ እንዲያውም አንድ መፅሐፍ ፀጋዬ ራሱን በራሱ ነው “ባለ ቅኔ ሎሬት” በማለት የሾመው ማለቱን የዛሬ አራት አመት ግድም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡
ጋሼ ፀጋዬ ሕይወቱ በ1998 ዓ.ም ከማለፉ በፊት የነበሩትን አሥር አመታት ያሳለፈው ሕክምናው በኢትዮጵያ የማይገኝ ሕመምን ለመታከም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ስለ ሰብእናው እና ሥራዎቹ የፃፉትን ለማንበብ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ስላልነበረ፣ ለጥያቄው ጥርት ያለ መልስ ከራሱ ከፀጋዬ ገብረ መድኅን ለማግኘት ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሰነዶች ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሰጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ለፀጋዬ ገብረ መድኅን በ”ባለ ቅኔ ሎሬት ማዕረግ” መጠራት ምክንያት የሆነው በዓለም አቀፍ የባለ ቅኔ ሎሬቶች ሕብረት የአለም ባለቅኔዎች ጉባኤ (United Poets Laureate International – World Congress of Poets) ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም በፊሊፒንስ ዋና ከተማ ሚኒላ ውስጥ የተመሰረተው የዚህ ዓለም አቀፍ ማህበር አላማ፤ በጥበብ (በተለይም በቅኔ) አማካይነት አለም አቀፋዊ ወንድማማችነትንና ሰላምን ማራመድ ነው፡፡
ማህበሩ በሁለት አመት አንድ ጊዜ በሚያካሂደው የአለም ባለቅኔዎች ጉባኤ ላይ ከመላው አለም የተሰባሰቡ ባለ ቅኔዎች ሥራዎቻቸውን ለጉባኤው ያቀርባሉ፤ እርስ በእርስም ስለ ቅኔ ይወያያሉ፣ ከዚህ በተጨማሪም ቅኔን የተመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች በጉባኤው የሚቀርቡ ሲሆን ለምርጥ ባለ ቅኔ ደግሞ የምስክር ወረቀት፣ ሜዳልያ እና የተከበረው ባለ የወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል (Golden Laurel Crown) ይበረከትለታል፡፡
ከሐምሌ 14 ቀን እስከ ሐምሌ 18 ቀን 1989 ዓ.ም በእንግሊዝ አገር፣ ባኪንግሀምሻየር ክፍለ ግዛት፣ ሀይ ዋይኮምብ ከተማ ውስጥ በተካሄደው አሥራ አምስተኛው የዓለም ባለ ቅኔዎች ጉባኤ ላይ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን “ኤዞፕ” የተሰኘውን ቅኔውን ከማሰማቱም ሌላ “Poetry Conquered Darkness and the World was Saved” በሚል ርእስ ጥናታዊ ፅሁፍ ማቅረቡ ታውቋል፡፡
የዓለም ባለ ቅኔዎች አሥራ አምስተኛ ጉባኤ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን በአገሩ ቋንቋና በእንግሊዝኛም ጭምር ያበረከታቸውን ግጥሞች፣ ቅኔዎች እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን በመመርመር፤ ስራዎቹም የሰው ልጅን እኩልነት፣ ነፃነት፣ ወንድማማችነትና ፍቅር አበክረው የገለጡ መሆናቸውን ተረድቶ ባለ ቅኔ ሎሬት የሚያገኘውንና የተከበረውን ባለ ወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል ሸልሞታል፡፡
እስከዚያን ጊዜ ድረስ ይህንን ባለ ወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል ከተሸለሙት ታዋቂ የአለም ባለ ቅኔዎች መካከል የአሜሪካው ባለ ቅኔ ሎሬት ሮበርት ትንስኪ፣ የሩስያው ኢጐር ሚኮሌሴንኮ፣ የፈረንሳዩ አሲት ቻክሮቮርቲ እና የእንግሊዙ ጆን ዋዲንግተን ፌዘር እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጥበብና በህይወት ጐዳና ላይ ሲጓዝ በቀዳሚ ሥራው ገና በልጅነቱ “ወጣት ደራሲ” የተሰኘው ፀጋዬ ገብረ መድኅን፤ በተከታታይ ባቀረባቸው ድንቅ ሥራዎቹ ምክንያት ገና በ29 አመት እድሜው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅትን በረከት እንዳገኘ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ማዕረጉና ያገኘው ክብር እረፍት የነሳቸው ተመልካቾች ባገኙት መድረክ ሁሉ ሲተቹት ኖረዋል፡፡ ፀጋዬ ይህንን አስመልክቶ ሲናገር፤
“…የአርመኖች እናት ‘ሂድ ልጄ፤ ከቤት ውጣና መንገዱን አቋርጠው፤ ሰው ሥም ያወጣልሀል’ አለችው ይባላል፡፡ በ13 አመቴ አምቦ ትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ የመጀመሪያ ቴአትሬን (የንጉሥ ዳዮኒስየስ ፍርድ የተሰኘውን) ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አቀረብኩላቸው፡፡ ተከትሏቸው መጥቶ የነበረው ጋዜጠኛ፤ በሳምንቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‘ፀጋዬ ገብረ መድኅን የሚባል ወጣት ደራሲ’ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቴአትር አቀረበላቸው ብሎ ዘገበ፡፡ ከቤቴ ወጥቼ መንገድ ሳቋርጥ ስም ወጣልኝ ማለት ነው እንጂ፤ እኔ በዚያን እድሜዬ ‘ደራሲ’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንኳ አላውቅም ነበር፡፡ ይሄ ስም ይገባዋል ብለው ያመሰገኑኝ መምህራን ነበሩ፤ አይገባውም ብለው የታዘቡኝም ነበሩ…”
“…እኔ ከገጠር ሜጫ ምድር ከገበሬና ከመለስተኛ ነጋዴ ቤተሰብ መጥቼ፣ አዲስ አበባ በምኒልክ ከተማ ብዙ የሥነ ፅሁፍ ታላላቅ ሰዎች በታወቁበት፣ በደረጁበትና ሥር በሰደዱበት መሀል ገብቼ፣ ገና በ29 አመቴ ስሸለም፣ የነፍሳቸውን መክሊት እንደወሰድኩባቸው ያህል፣ በተለይ ጐምቱዎቹ የሥነ ፅሁፍ አባቶች ያደረሱብኝን የምቀኝነት ቁስል በቁጭት ሳስተውለው… እንኳንስ ሊያማርረኝ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምክር ነበር የጠቀመኝ” ብሎ ነበር፡፡
ባለ ቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን በኋለኛው የእድሜው ዘመን፤ በተለይም ሕክምናውን አሜሪካ ውስጥ በመከታተል ላይ ሳለ ስላገኘው እውቅናና ሽልማት በተለይ ለጦቢያ መፅሔት በየካቲት ወር 1997 ዓ.ም በሰጠው ቃለ መጠይቅ፤
“…ዛሬም ብዙ ምሁራንና አለም አቀፍ ታዋቂ ድርጅቶች በብዙ የሙገሳ ስሞች ይጠሩኛል፡፡ ስሜን እየካቡ ደብዳቤዎች ይፅፉልኛል፡፡ ሽልማቶችም የምስክር ወረቀቶችም ይሰጡኛል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሦስት አመት (በ1994 ዓ.ም አካባቢ) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ፤ ልዑል ኤርምያስ ሳህለ ስላሴ ‘የብላቴን ጌታ ማዕረግ ሸልሜሀለሁ’ ብሎ ደብዳቤ ፅፎልኛል፡፡
በተሸለምኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ብዙዎች ቢመርቁኝም ጥቂቶች ደግሞ በምቀኝነት ቅር የሚላቸው አሉ፡፡
አበሻ ቤት ደግሞ ምቀኝነት በሽ በሽ ነውና ነገሩ አያስደንቅም” ብሎ ነበር፡፡
ፀጋዬ ገብረ መድኅን ለሂስና ትችት አዲስ አልነበረም፤ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በህይወቱ ዘመን ሁሉ ሲፈታተነው የኖረው አሉባልታ፣ ምቀኝነት እና ተንኮል ነበር፡፡
እሱም “መሰደብ ሳይሆን በስራው መነቀፍ ለኪነ ጥበብ ሰው እድሉ ነው፤ ስድብ ግን ከጋዜጠኝነት ወግ፣ ከሂስም ወግ የራቀ ነው” ሲል ከዛሬ 45 አመት በፊት ለመነን መፅሔት ተናግሮ ነበር፡፡
እንግዲህ የፀጋዬ “የባለ ቅኔ የሎሬት” ማዕረግ የፈለቀበት ምንጭ ከዚህ በላይ በተገለፀው መልክ ቀርቧል፡፡ ይህም ምናልባት “ፀጋዬ ራሱን በራሱ ነው ‘ሎሬት’ ያለው” ለሚለው ከእውነት የራቀ ክርክር መልስ በመሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለጥያቄው እልባት ይሰጠው ይሆናል፡፡
የጥበብ ታላላቆቻችን የታሪክ መሰረቶቻችን ስለሆኑ ልናከብራቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ በእውቀቱ ስዩም በአንድ ግጥሙ እንዳለው፣ “ዛሬ ነብይ በአገሩ አይከበርም፤ ነገ ደግሞ ነብይ ባገሩ አይፈጠርም” ይሆንና ኢትዮጵያችን የታላላቆች ምድረ በዳ እንዳትሆን ያሰጋል፡፡
የምናስበው ወደ ፊት ለሚነሱት ጠቢባኖቻችን እንጂ እንደ ፀጋዬ ገብረ መድኅን አይነቶቹ ወፍራም ቆዳ ያላቸው ጀግኖቻችንማ “ያበሻ ምቀኝነት” የተባለውን ክፉ ጠባያችንን ተቋቁመው ታላላቅ ሥራዎች አበርክተውልን አልፈዋል፡፡ፀጋዬ ገብረ መድኅን ከግማሽ ምእተ አመት በላይ በጥበብ አለም ውስጥ በቆየበት ጊዜ ላበረከታቸው ስራዎቹ “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ የሚበዛበት አይደለም፡፡ ለዚህ ሰው እስካሁን የገዛ አገሩ ከሰጠችው ሽልማት ይልቅ በባህር ማዶ የተቀበላቸው ሽልማቶች በእጥፍ ይበልጣሉ፡፡ በሰለጠነው አለም እንደተለመደው ማዕረጐች በመስጠት፣ አደባባዮችን፣ መንገዶችን፣ ቤተ ጥበባትን በስሙ በመሰየም ወይም የመታሰቢያ ሀውልት በማቆም፣ አሁንም ፀጋዬ ገብረ መድኅንን ልናከብረው እንችላለን፡፡ ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎቻችንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊያስቡበት ይገባል፡፡

 

Read 6342 times Last modified on Saturday, 08 December 2012 13:50