Saturday, 08 December 2012 13:33

ጸሊም

Written by  አገኘሁ አሰግድ
Rate this item
(6 votes)

ቆይ እሱና እሷ ምንና ምን ናቸው? ግራ ገብቶታል፡፡
እህቱ አይደለችም፤ ወንድሟ አይደለም፣ ፍቅሯም አይደለም…፡፡ የእሱን ስሜት ያውቀዋል፣ የእሷ ነው ግራ የገባው፡፡ አይኖቿ ውስጥ ፈትሿታል፣ ድርጊቷ ውስጥ፣ ቃላቶቿ ውስጥ…ያው ናት፤ ትናንትም ዛሬም ተመሳሳይ፡፡
ሁሌ ከትምህርት ቤት ሲወጡ አቅፋው ወይ አቅፏት የጦፈ ወሬ እያወሩ ሰፈሯ ድረስ ይሸኛታል፡፡ እስኪመሽና ጨለማ እስኪለብሳቸው ሰፈሯ አብረው ይቆያሉ፡፡ የሰው ጊዜ አልፎ የአራዊት ሲሆን ቅር እያለው፣ ቅር እያላት ይለያያሉ፡፡
ለእሱ ከእሷ ጋር መለያየትን የመሰለ ምሽት፣ እሷን ተለይቶ ከመሄድ የገዘፈ ጨለማ የለም፡፡ ሰፈሩ ሲደርስ ከመሸው በላይ ይመሻል፡፡

እናቱ በመቆየቱ ተጨንቀው፣ አባቱ በቁጣ ፊታቸውን ከስክሰው ይደርሳል፡፡ “አይይ…አንተ ልጅ እንደው ቢነግሩህ አልሰማ አልክ አይደል?” እንዳልሰማ ሆኖ ሰላምታ ሰጥቷቸው ከራሱ ክፍል ይገባል፡፡ እሱ እንደው ነገም ከነገ ወዲያም ያው ነው፤ ያውቀዋል፡፡
***
በአንዱ ቀን ከትምህርት ቤት ቀረች፡፡ እንደ መርግ የከበደ ቀን ሆነበት፡፡
የሚተነፍሰው አየር እንኳን ጨነቀው፡፡ ብቻውን ወደ ቤቱ መመለስ ግድ ሆነበት፡፡
መንገዱ እንደቀኑ አልገፋልህ አለው፡፡ ስለ ራሄል ያለውን ብስኩት ስሜት እየኮረሻሸመ …እያጣጣመ የመንገዱን እርቀት ለመርሳት ሞከረ፡፡ ድንገት አንድ ሰው ከፊቱ ተጋርዶ ከመንገዱ ገታው፡፡ ቀና ብሎ አየው፡፡ ቼጉቬራ ከፊቱ ቆሟል፡
ሰዎች “ቼጉቬራ” ብለው ሲጠሩት ሰምቶ እንጂ አውቆት አይደለም፡፡ ፊቱ ስርዝ ድልዝ ይበዛዋል - በቦክስ ተጽፎ፣ በቦክስ የተሰረዘ፡፡ አንዴ ራሔል “ይሄ ልጅ አስተያየቱ በጣም ነው የሚያስጠላኝ” ያለችውን ያስታውሳል፡፡ ከዚህ በላይ አያውቀውም፡፡ ሴቶችን ከሌሎች ወንዶች እጅ ነፃ አውጥቶ የራሱ ለማድረግ የሚታገል እንደሆነ አያውቅም፡፡
ከእሱ ይገዝፋል፡፡
“እንድትተዋት እፈልጋለሁ” አለው፡፡
“ማንን?”
“ራሔልን!” ደነፋበት
“ለምን ሲባል?” በተራው ድምፁን ንዴት ለመቀባት ሞከረ፡፡
“ሰው እንጂ እንዳንተ ያለ ድመት ስለማያስፈልጋት!”
ቢኒያም አልተናደደም፤ “እኔ ግን ከአይጥ ድመት የሚሻላት ይመስለኛል፤ ቢያንስ ከአይጥ ይጠብቃታል”
ቼጉቬራ አይጥ በመባሉ ገነፈለ፡፡ ቡጢ ሰነዘረ፡፡ ቢኒያም በከፊል አረፈበት፣ አፀፋውን መለሰ፡፡ ካንድ በላይ ሳይቃመሱ በቦታው የነበሩ ሰዎች ገላገሏቸው … ገላገሉት፡፡
ከንዴቱ ጋር ቤቱ ገባ፡፡ ንዴቱ አቅበጠበጠው፡፡ በፍጥነት የሱ መሆን እንዳለባት ወሰነ፡፡ … ፃፈላት፡፡ ውብ ቃላት ወረቀቱን አጠቡት፣ የፍቅሩን ልክ አዘነበባቸው፡፡ ቀለለው፡፡ “ነገ እሰጣታለሁ” ሲል አሰበ፡፡
***
በቀጣዩ ቀን መጣች፡፡ ደስተኝነት ያየባት መሰለው፡ … እንደ ተለመደው ወደ ሰፈሯ ሄዱ፡፡ መሸ፡፡ ሰማዩ ይገለባበጣል፡፡ ሰማይ ቤት መላዕክት መብረቅ በመወራወር የሚዝናኑ ይመስላል፡፡ በልቡ ውስጥም ነጐድጓድ ነው፡፡
ፈርቷል፡፡ እሷ የሆነ ነገር ልትነግረው ፈልጋለች፣ እንዴት እንደምትነግረው ነው የቸገራት፡፡ ሊሰጣት ያሰበው ወረቀት እጁ ላይ አለ፡፡
በዚህ ቅዝቃዜ ከእጁ በሚወጣው ላብ ሊበላሽ ነው፡፡ “እቤት ስትገቢ አንብቢው” ብሎ ሰጣት፣ ጨለማ ነው አሁን አታነበውም ብሎ በማመን፡፡
“ምን … እእ… የፍቅር ጥያቄ ነው እንዴ?” በቀልድ ድምፀት ጠየቀችው፡፡
“እ…እ… ጠያቂ ስታጪ ምን ላድርግ” እንደሷው ለመቀለድ ሞከረ፡፡
“ቢኒዬ? ይልቅ አንድ ነገር ልነግርህ ብዬ እኮ…”
“ምን?”
“ከዚህ በፊት አፈቅረው እንደነበር የነገርኩህ፣ ወደ አሜሪካ ሄደ ያልኩህ ልጅ?... ለካ እሱም ተመሳሳይ ስሜት ነበረው፡፡ ከመሄዱ በፊት ለእህቴ በተደጋጋሚ ይነግራት ነበር፣ እሷ ግን አልነገረችኝም፡፡
… እንደነገረችኝ ስላሰበ ዝምታዬ ጨነቀው፡፡ በመሃል የውጪ እድል መጣለት፣ መሄድ ባይፈልግም፣ ከእኔ ሲርቅ እንደሚቀለው አስቦ ሄደ፡፡ ግን እንዳሰበው ስላልሆነ ገና በስድስት ወሩ ተመልሶ መጣ፡፡ ትናንት በጠዋት መጥቶ አገኘኝና ሁሉን ነገር ነገረኝ … በቃ ሁሉ ነገር እንዴት እንደፈጠነ አላውቅም፣ ትናንትናውኑ ቤተክርስትያን ሄደን ተማማልን…” በልቡ ውስጥ መብረቅ ጣለ፡፡ በግንባሩ ላይ ላቡ ተንቸረፈፈ፣ ጨለማ መሆኑ በጀው፡፡ ሰማዩ ማልቀስ ጀመረ፣ እንደሱ ልብ መንሰቅሰቅ ጀመረ፡፡ ባዶነት ባዶ ቦታውን ሲሞላው ይታወቀዋል፡፡ ወረቀቱን ነጥቋት መሮጥ ዳዳው፡፡ ነገ ሲገናኙ እንደምን ዓይኗን ደፍሮ ያያል፡፡ ስሜቱን ሊያሳውቃት አልፈለገም፡፡ በዝናቡ አሳብቦ ለመሄድ ተነሣ፡፡ ለስንብት ሲያቅፋት ገላዋ ከአየሩ በላይ ቀዘቀዘው፡፡
… እጅግ የሚወዱትን ሰው ቀብሮ የመመለስ ስሜት አዝሎ ወደ ቤቱ መንገዱን ተያያዘው፡፡
ነገ ጨነቀው፡፡ ደብዳቤውን ካነበበች በኋላ ለሱ የሚኖራት ግምት…! አዕምሮው ውስጥ ያለውን ስሜት አሽቀንጥሮ ለመጣል ሞከረ፡፡ መሄድ፣ ዝም ብሎ መሄድ፤ በለመደው መንገድ፣ ወደ ለመደው ቤት፡፡ አንዲት መታጠፊያ ላይ ደርሶ ከመታጠፉ ሶስት ሰዎች በላዩ ላይ ተረባረቡበት፡፡
ሁለቱ እጁን አጥብቀው ያዙት፣ ከፊቱ ያለው ኃይለኛ ቡጢ ሆዱ ላይ፣ ቀጥሎ ፊቱ ላይ አሳረፈበት፡፡
ትግል ጀመረ፡፡ አንድ እጁ ነፃ ሆነ፡፡ በቀኙ ያለው ላይ ሰነዘረ፣ አገኘው፡፡ በግራ ላለው ሲሰነዝር ስለት ሰውነቱን ቀዶ ሲገባ አንድ ሆነ፡፡ የጣር ድምፅ ከማሰማቱ አፉ ታፈነ፡፡ ስለቱ ሲነቀል ያለውም ህመም የመወጋት ያህል ነው፡፡ እንደገና ታፋው ላይ … ተነቀለ፡፡
ከመውደቁ በፊት አንድ እጅ ያዘው፣ ወደ ጆሮው ተጠግቶ “ልጅ፣ በፍጥነት ወደ ሲኦል እሺ? ተከፍቶ እየጠበቀህ ነው….” አንሾካሾከለት፡፡
ሰማዩ ብልጭ አለ! በዛው ቅፅበት በብርሃኑ አየው፣ ለየው - ቼጉቬራ ነው፡፡ ለቀቀው፡፡ በጀርባው ወደቀ፡፡ ጥለውት ሄዱ፡፡ ድምፅ ማውጣት አቃተው፡፡ ከማቃሰቱ ጋር ቀረ፣ ባዶ መንገድ ጐዳና ላይ፡፡
***
ነቃ፡፡ ለሰዓታት እራሱን ከሳተበት ነቃ፡፡ ጨለማ ከላይ ወድቋል፡፡ የተኛበት ነገር ይቀዘቅዛል፣ ውሃ ነው፡፡ ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ሃይለኛ ስቃይ ተሰማው፡፡ ሁሉንም ነገር ለማስታወስ ሞከረ፡፡ ጭንቅላቱ ውስጥ የማዞር ስሜት፡፡
በስቃዩ ውስጥ ራሔል ታሰበችው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረባት፣ ያፈቀራትና ያጣት ሴት፡፡ እናቱ ታሰቡት፣ አባቱ፣ ለራሄል የፃፈላት ደብዳቤ … ማሰብ ደከመው፡፡ … አይኖቹን ላለመጨፈን ሲታገል ብርሃን ታየው፡፡ በትግል ቀና አለ - ድንጋጤ!!! መኪና ነው፡፡ ያለው መሃል መንገድ ላይ ነው፡፡
ዳር የሚያደርስ አቅም የለውም፡፡ እንደምንም ለመንቀሳቀስ ሞከረ - ስቃይ!! መኪናው ወደ እሱ እየከነፈ ነው፡፡ የህይወቱ “የመከራ ቅብብሎሽነት” ታየው፡፡ የህይወት ምፀት፣ ወለፈንዴነት ተገለጠለት፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ባለ በሌለ ኃይሉ ተንቀሳቀሰ-ከሲኦል የከፋ ስቃይ! መኪናው ይበልጥ እየቀረበው ነው፡፡ አዕምሮው ውስጥ ራሔል ብቻ ቀረች፡፡ መኪናው ቀረበው፣ ተስፋው ራቀ፡፡ ቀረበው፣ ቀረበው … መኪናው…

Read 4742 times