Saturday, 08 December 2012 11:47

እንኳን ለልማት ለጦርነትም “መስዋእትነት” እየቀረ ነው

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(5 votes)

“ናይጀርያ በመልሶ ማልማት ለተፈናቀሉ ተንሳፋፊ ት/ቤቶች ሰራች!”
መቼም ባለፉት ሳምንታት በመጪው ግንቦት ወር ስለሚካሄደው የአዲስ አበባ ምርጫ እንደጉድ ያወጋን ይመስለኛል - ፍርሃታችንን፣ ስጋታችንን፣ ተስፋችንን፣ ምኞታችንን፣ ጉጉታችንን፣ ፍላጐታችንን፣ ውዴታችንን፣ ግዴታችንን፣ ኃላፊነታችንን…ስሜታችንን ብዙ አውግተናል፡፡ ብዙ አምተናል፡፡ 
እናም ከዚህ በኋላ ቢያንስ ለጊዜው ብዙም ስለምርጫው የምናነሳው ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሆኖም ሰሞኑን ብልጭ ያለችልኝ አንዲት በዓይነቷ ለየት ያለች ፕሮፖዛል አለችኝና በጨረፍታ ላካፍላችሁ፡፡ እኔ የምለው ግን ---- ስለምርጫ ምናምን ሳወጋችሁ ፍርሃት ይሰማችኋል እንዴ? (ቀልቤ ነግሮኝ እኮ ነው!) ለማንኛውም ግን ዘና ብላችሁ ማውራት-- ማማት--- መሳለቅ-- (መሳቀቅ አልወጣኝም!) መብታችሁ ነው፡፡ እውነቴን እኮ ነው--- ነፃ ሰዎች አይደለንም እንዴ! በዚያ ላይ በገዛ አገራችን ላይ ነን፡፡ ስለዚህ የተሰማንን በነፃነት መግለፅ ህገመንግስታዊ መብታችን ነው! (በታጋዮች መስዋዕትነት የተገኘ!) 
ይኼውላችሁ ፕሮፖዛሉ ምን መሰላችሁ… የምርጫ ቦርድን ኃላፊነት የተመለከተ ነው፡፡ ይኼኔ የቦርዱ ሰራተኞች ምን እንደሚሉኝ አላውቅም --- “ምነው ከላያችን ላይ አልወርድ አልክ!?” ሊሉ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን አልወርድም፡፡ እንዴ--- የህይወታችንን ነገር የያዘ መስሪያ ቤት እኮ ነው! ስለዚህ እቺን መቋጫ የምታበጅ ፕሮፖዛል አንዴ ልንገራችሁና ከዛ በኋላ ዳግመኛ ስለቦርዱ አላነሳም፡፡ በነገራችሁ ላይ ይሄ የፕሮፖዛል ሃሳብ ብልጭ ያለልኝ--- ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትሩ ከኢቴቪ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ባደረጉት (ቤተመንግስት ከገቡ በኋላ ማለቴ ነው) ቃለምልልስ ላይ ምርጫውን ፍትሃዊና ሰላማዊ በማድረግ ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት የፖለቲካ ወግ፣ ፓርቲዎች ከምርጫው ጋር በተያያዘ ወደ ውዝግብና ንትርክ የሚገቡ ከሆነ “እዛው በጠበላችሁ!” እንላቸዋለን ብዬ ነበር (ማስፈራሪያ እኮ አይደለም ማሳሰቢያ ነው!) ጠ/ሚኒስትሩም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዳይጠናቀቅ ለመበጥበጥ የሚሞክሩ ፓርቲዎችን ህዝቡ “እረፉ” ይበላቸው ብለዋል፡፡ (አይገርምም የሃሳብ መመሳሰል!)
አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬ ወዳጆቼ ግን “ጠ/ሚኒስትሩ የተናገሩትን ሰምተህ ነው የፃፍከው አይደል?” አይሉኝ መሰላችሁ! (ኮርጀህ ነው ለማለት እኮ ነው) ይታያችሁ… እኔ ስለምርጫ የፃፍኩት ጠ/ሚኒስትሩ ቃለምልልሱን ከማድረጋቸው ሁለት ሦስት ቀን ቀደም ብሎ ነው፡፡ ለነገሩ ብኮርጅስ… ነውር አለው እንዴ? (የሚበጃችሁን ኮርጁ አልተባለም!) እንዲያ ባይሆንማ አንዳንድ ህጐችን በዲሞክራሲ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት ቃል በቃል አንቀዳም ነበር፡፡ ስለዚህ ማንም ቢኮርጅ ችግር የለውም ለማለት ያህል ነው (ለካድሬ ወዳጆቼ!)
አሁን እንግዲህ የምርጫ ቦርድ ኃላፊነትን በተመለከተ ድንገት ብልጭ አለችልኝ ያልኳችሁን ነገር ልንገራችሁና የምርጫን ጉዳይ ቋጭተን ወደ ሌላ ድንቅና አስደማሚ የፖለቲካ አጀንዳዎች እንለፍ፡፡
(ጦቢያ መቼም አያልቅባት!) አንዳንዴ ስለምርጫ ቦርድ ሳስብ ምን እንደምል ታውቃላችሁ? “እድለ-ቢስ ነው!” (ለሰው ግን አምቼው አላውቅም!) እንዴት በሉኛ… ይኸውላችሁ ለአዳዲስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፈቃድ፣ ሰርተፊኬት፣ ማህተም፣ የውድድር ምልክት ወዘተ የሚሰጠው ቦርዱ ነው፡፡ የፓርቲዎች መገነጣጠልና አለመግባባት ሲፈጠር መ
ፍትሄ የሚሰጠው ማነው? ቦርዱ ነው (አይደለም እንዴ?) አሁን ለምሳሌ የዝነኛውን “ቅንጅት” ፓርቲ ስያሜ በ97ቱ ምርጫ ፓርላማ ለገባው ለአቶ ተመስገን ቡድን የሰጠው ማነው? ቦርዱ እኮ ነው! (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) ምርጫ በመጣ ቁጥር ልቡ እስኪጠፋ የሚፈጋው ማነው? አሁንም ቦርዱ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የአገር ስራ ተሰጥቶት ግን ሲመሰገን ሰምቼ አላውቅም፡፡ እንኳን ተቃዋሚዎች ኢህአዴግም ራሱ እኮ ሲያመሰግነው አልሰማሁም፡፡
(በምስጢር ይመሰጋገኑ እንደሆነ አላውቅም) አሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ… እኔም እንደ ዜጋ ለምርጫ ቦርድ ምስጋና ሳይሆን ወቀሳ ነው ያለኝ (እድለ ቢስ ነው አላልኳችሁም!) ይሄውላችሁ ሰሞኑን ብልጭ ያለልኝ ሃሳብ ምርጫ ቦርድን ፈታኝ ኃላፊነት የሚያሸክም ነው፡፡ ካልቻለ አሁኑኑ ይንገረንና የምርጫ ቦርድን ማኔጅመንት ለፈረንሳይ ወይም ለእንግሊዝ ኩባንያ እንሰጠዋለን (እንደ ቴሌና መብራት ኃይል!) ለማስፈራራት እኮ አይደለም… አማራጮቹን ለመግለፅ ያህል ነው፡፡ እናላችሁ… ምርጫ ቦርድ ከግንቦቱ ምርጫ በፊት ወይም ደግሞ በየአምስት አመቱ ምርጫ ሲካሄድ የሚጣልበት ከባድ ኃላፊነት አለ፡፡ ልክ ነዋ… ኃላፊነት የሚወስድ እየጠፋ እኮ ነው እቺ አገር መቀለጃ የሆነችው፡፡ እንዴ --- ለህይወት ዋጋ የሚሰጥ ጠፋ እኮ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ የፓርቲ ሰርተፊኬት ላይ ፊርማና ማህተም አድርጐ መስጠት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ላቅ ያለ አገራዊ ኃላፊነት ልናሸክመው ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም ግን እደግመዋለሁ፡፡ ይሄን ኃላፊነት ቦርዱ ላይ የመጫን ፍላጎት የለኝም፡፡ (በቀል የፋራ ነው!) እናም --- በደንብ ያስብበትና የማይወጣው ከመሰለው ችግር የለም፡፡ (እድሜ ለውጭ ማኔጅመንት!)
እኔ የምላችሁ ---- የቦርዱን ኃላፊነት “Suspense” አደረግሁት አይደል? (ሆቢዬ ነው!) እናላችሁ… ምርጫው ሊጀመር አንድ ቀን ሲቀረው ቦርዱ ከስታቲስቲክስ ቢሮ ጋር ይፈራረማል፡፡ ምን አትሉም --- የህዝብ እርክክብ ነዋ፡፡ ሁልጊዜ በምርጫ ማግስት ህዝብ እየጠፋብን ተቸገርን እኮ፡፡
እኛ አገር ብቻ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ በቃ በየአፍሪካ አገሩ ምርጫ ካለ ህዝብ ይጎድላል፡፡ ስለዚህ የእኔ ፕሮፖዛል ለዚህ ችግር ፍቱን መፍትሄ ነው፡፡ (በጥናት ባይረጋገጥም!) እንዴት መሰላችሁ ----- ስታቲስቲክስ ቢሮ ከምርጫው ቀደም ብሎ የቆጠረውን ህዝብ ለምርጫ ቦርድ ያስረክባል፡፡ ከዚያስ? ድምፅ ከተሰጠና ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ አሸናፊው ይፋ ይሆን የለ! ያኔ የምርጫ ቦርድ ስራ ተጠናቀቀ ማለት ነው፡፡ ግን እርክክብ ይቀረዋል፡፡ ቦርዱ ከስታቲስቲክስ ቢሮ ቆጥሮ የተረከበውን ህዝብ ቆጥሮ ያስረክባል፡፡ አንድ እንኳን ከጎደለ ቢሮው አይረከብም፡፡
ይሄን ያህል ነው ያስረከብኩህ ብሎ “ውለዳት!” ይለዋል፡፡ መቼም ቦርዱ እንዴት ያለ ጭንቅ ውስጥ እንደሚገባ ካሁኑ ታየኝ (እድሉ ነዋ!) መቼም ከምርጫ በፊትና በኋላ ህዝብን ቆጥሮ የመረካከብን ፋይዳ ለእናንተ አልነግራችሁም፡፡ አያችሁ… “በወሊድ ምክንያት አንዲትም እናት አትሞትም”፣ “በኤችአይቪ አንድም ሰው አይሞትም” እየተባለ አይደል፡፡
ለምን ቢባል---ገዳይነታቸው ይታወቃላ፡፡ በፖለቲካ ደግሞ “የስልጣን ሽኩቻ” የተባለ ገዳይ ቫይረስ አለ፡፡ ልክ እንደኤችአይቪ መድሃኒት ያልተገኘለት፡፡
በእርግጥ እነኦባማ አገር መድሃኒቱ ከተገኘ ቆየት ብሏል፡፡
ችግሩ ግን የነሱ መድሃኒት ለአፍሪካ ቫይረስ አይሆንም፡፡
እንደውም ያስፋፋዋል፡፡ እናም ትክክለኛው መድሃኒት በአፍሪካውያን የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ተፈልስፎ እስኪገኝ ድረስ ሰውን ከሞት ለማዳን በምርጫ ሰሞን እየቆጠሩ መረካከብ ጊዜያዊ መከላከያ ይሆናል ይላል- ፕሮፖዛሌ (የፖለቲካ ኮንዶም ቢኖርማ ግልግል ነበር!) እናላችሁ ---- የዘንድሮ ምርጫ መሪ ቃል “በምርጫ የተነሳ አንድም ዜጋ አይሞትም፣ አይታሰርም፣ አይዋከብም፣ አይሰደድም” የሚል ሲሆን የዚህን መሪ ቃል ኮፒራይት ለምርጫ ቦርዱ በነፃ አበርክቻለሁ፡፡ እሱ እንግዲህ ይተግብረው፡፡ እኔ የምላችሁ---- የጐዳና ላይ ነውጥ ተፈጠረ ብሎ ጥይት ከመተኮስ አስቀድሞ ነውጡን መከላከል አይሻልም? (ወጪውም እኮ ይቀንሳል!)
በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ለትንሹም ለትልቁም “መስዋእትነት” የሚለው ነገር አይመቸኝም (ፈሪ ሆኜ እኮ አይደለም!) መስዋዕትነት ሲባክን ስለማልወድ ነው (ግፍ ነዋ!) ደግሞም እኮ በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ነን! አንዳንዴ ግን ኢህአዴግ “መስዋእትነት” የሚላቸው ነገሮች ያስቁኛል (ማለቴ ደስ ይሉኛል!) ለምሳሌ አንድ የኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣን እንደሰሞኑ ዓይነት ትላልቅ የክላስተር ስልጣን አግኝቶ፣ እናንተ አገር አማን ነው ብላችሁ--- “ሹመት ያዳብር!” ብትሉት ምን እንደሚል ታውቃላችሁ…ፊቱን ከስክሶ “መስዋእትነት እኮ ነው!” ይላችኋል (በምን ሂሳብ?)
እኔ የማይመቸኝ ምን አይነት መስዋእትነት መሰላችሁ… ለምሳሌ ልማት ያለመስዋእትነት አይመጣም ምናምን ሲባል በመስዋዕትነት ማሾፍ ይመስለኛል፡፡ እንዴ… በሰለጠነው አለም እኮ እንኳን ለልማት ለጦርነትም የሚከፈለው መስዋእትነት እየቀረ ነው (እድሜ ለቴክኖሎጂ!) እናላችሁ… አንዳንድ የልማት ካድሬዎች አንዳንዴ የሚናገሩትን አያውቁትም፡፡
ለምሳሌ መልሶ ይለማል የተባለ አካባቢ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ የራሱን ወሰን ለማስከበር ቢከራከር ምን እንደሚሉት ታውቃላችሁ? “ፀረ ልማት!” እኛ ደግሞ የምንለው ምን መሰላችሁ… ማንም መስዋእትነት ሳይከፍል (ያለ አግባብ ሳይፈናቀል፣ ተገቢው ካሳ ተሰጥቶት፣ ሰብአዊ መብቱ ተጠብቆ ወዘተ) አገር መልማት ትችላለች፡፡ አገር ስትለማ እኮ ህዝብም መልማት አለበት (ልማቱ ለህዝቡ መስሎኝ!) ኢህአዴግ ያለመስዋእትነት ልማት ማምጣት አልችልም ካለ ግን ቶሎ ይንገረን - ሌላ አማራጭ አለ፡፡ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቱን ለውጭ ማኔጅመንት ሰጥቶ መገላገል ይቻላል፡፡
በነገራችሁ ላይ በናይጄሪያም እንዲሁ እንደኛ አገር መልሶ ማልማት አለ አሉ - ሰሞኑን በቲቪ እንደሰማሁት፡፡
እናላችሁ--- ልማቱ እስኪለማ ዜጎችም መልማት እንዳለባቸው የገባቸው “ነቄዎች” በጀልባ ላይ ተንሳፋፊ ት/ቤቶች እየከፈቱ ነው (ህፃናት አገር እስክትለማ ሳይማሩ መጠበቅ የለባቸውማ!) ለማንኛውም ኢህአዴግ መስዋዕትነትን የሙጥኝ ከሚል ጥበብና ብልሃትን ይማር!! የጥበብ ዘመን ያምጣልን!!

Read 3317 times