Saturday, 08 December 2012 11:24

የእኛ ሰው በየመን

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(7 votes)

የአይሻ የሲኦልኑሮ
ካለፈው የቀጠለ 
“ራሴን ቀና አድርገው ውሀውን አጠጡኝ፡፡ ተስገብግቤ የቻልኩትን ያህል ጠጣሁ፡፡ ነፍሴም መለስ ያለች መሠለኝ፡፡ ወዲያው ግን መላ ሰውነቴ በተለይ ደግሞ ከወገቤ በታች እንደእሳት እየተቃጠለ ተበጥሶ የሚወድቅ መሰለኝ፡፡ እንዲችው እንደተቃጠልኩና እንደጮህኩ ውሃ ውሃ ስል ሌሊቱ ነጋልኝ፡፡ ረፋዱ ላይ ሼክ አብዱልቃዊ የተባሉት ጠና ያሉ የመን ሰውዬ መጡ ብለው በሩን ከፈቱት ልክ እንደኛው ሀገር የጠፍር ወንበር አይነት የአባወራ ወንበር ወጥቶላቸውና ስጋጃ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው ቁጭ ብለዋል፡፡ እንደ ሁሉም የመኖች እሳቸውም ወገባቸው ላይ ትልቅ ጌጠኛ ጩቤ ታጥቀዋል፡፡ አባታቸው ወይም የሰፈሩ የጐበዝ አለቃ ናቸው መሰል ሁሉም እየመጣ ለጥ እያለ እጅ እየነሳ እጃቸውን ይስማቸዋል፡፡

“ከዚያ ሁላችንንም ውጡ አሉን፤ ሴቱ ሁሉ እየተነሳ ሲወጣ እኔ ወገቤ ተቆምጦ እንዴት አባቴ አድርጌ ልላወስ? ሁለቱ ሴቶች እንደምንም ደጋግፈው አወጡኝና የቤቱን ግድግዳ አስደግፈው አስቀመጡኝ፡፡ ሁለት የመኖች ሰፌድ በሚመስል የብረት ትሪ ቀጭን ቂጣ እጃቸው እንዳመጣ እየቆረሱ ሲሠጡን፣ አንድ ብጭጭ ያለ ቀይ የመን ደግሞ በደረቱ አስደግፎና አንከርፍፎ ከያዘው ጆሮ የሌለው ትልቅ የብረት ድስት ውስጥ አይብ መሳይ ነገር በማንኪያ እያወጣ ያድላል፡፡ አይብ መሳዩ ነገር በኋላ ሳየው የእውነቱ የአላህ አይብ ሳይሆን ከሰሊጥ የሚሠሩት የቂጣ ማባያ ጣፋጭ ነገር ነው፡፡ እኔ ነኝ እንጂ ያልነካሁት ሴቱ ሁሉ እየተሻማ ነው የበላው፡፡
እኔማ ግራና ቀኝ ጐኔንና ከእምብርቴ በታች ሠቅዞ የያዘኝ ውጋት መተንፈስ እንኳ ከልክሎኝ አፌን በየት አባቴ ልክፈተው፡፡ ትንሽ ቆይተው ደግሞ በትንንሽ ስኒዎች ሻይ ሰጡን፡፡ ሻይውን መቼም እንደምንም ተጣጥሬ ጠጣሁት፡፡
“ሴቱ ሁሉ በር ላይ ተሠጥተን ትንሽ እንደቆየን ሼክ አብዱልቃዊ ተነሱና በዚያ አረብኛቸው የሆነ የሆነ ነገር ተናገሩንና ወደ ሰዎቹ ዞረው እጃቸውን በማስጠንቀቅ አይነት እያወዛወዙ ትዕዛዝ መሳይ ነገር ተናገሯቸው፡፡ ሰዎቹም ጐንበስ እያሉ እጅ ይነሳሉ፡፡ ወዲያውም ሁለት የመኖች ደጋግፈው ከፈረሳቸው ላይ አወጧቸውና ሊሄዱ ሲሉ፣ ያ እኔን መጀመሪያ የተገናኘኝ የመን የወሰደብኝን ሃምሳ ዶላር እየሠጣቸውና ወደተቀመጥኩበት በጣቱ እያሳያቸው የሆነ ነገር ነገራቸው፡፡ እሳቸውም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሳቁ በኋላ፣ የሆነ ነገር ነገሩትና ከግቢው ወጥተው ሄዱ፡፡ እሳቸው ለሰውየው የነገሩትን የሰማችው ያቺ አረብኛ የምትችለው ሴት፣ በድንጋጤ ክው ብላ አፏን በእጇ ይዛ “እዋይ!” ካለች በኋላ፣ እኔን በከፍተኛ የፍርሃት ስሜት ትክ ብላ ስታየኝ መላ ሰውነቴን አንዳች አይነት ስሜት ነዘረኝና የሆነ የደገሱልኝ ክፉ ነገር ቢኖር ነው ብዬ በፍርሃት መንዘፍዘፍ ጀመርኩ፡፡
“ቀትሩ በረድ ሲል የጧቱ አይነት ቀጭን ቂጣና ሩዝና ጐመን ያለበት ወፈር ያለ መረቅ (ሾርባ) በነጫጭ ኩባያ እየሞሉ ሰጡን፡፡ ቂጣውን ሳልነካው መረቁን ብቻ አጠገቤ ተቀምጣ የደገፈችኝ ቀጭን የቀይ ዳማ የሆነችው ሴት እያታለለች እንደምንም አስጠጣችኝ፡፡ ከዚያም አንድ አስር የሚሆኑ የመኖች መጥተው ስብስብ እንዳሉ ከመካከላቸው አንደኛው ወደ እኛ ቀረብ አለና የሆነ ነገር ተናገረ፡፡ ያቺ አረብኛ የምትችለው ሴት እጇን አወጣችና ከተቀመጠችበት ተነስታ ከእሱ አጠገብ ሄዳ ቆመች፡፡ ከዚያም እሱ የሚናገረውን በአማርኛ፣ አንዳንዴ ደግሞ ወደ ሆኑ ሴቶች ዞር እያለች በትግርኛ እየተረጐመች ነገረችን፡፡
የመኑ ሰውዬ ከሁለት ቀን በኋላ የጭነት መኪኖች ወደዚህ መንደር ስለሚመጡ መሄድ ወደምትፈልጉበት የአረብ ሀገር ያደርሷችኋል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን በትዕግስት ጠብቁ አለን፡፡
“ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቱ ፊት በመጠኑም ቢሆን ፈካ አለ፡፡ ከእኛ ነጥለው ሌላ ቤት ውስጥ ስላስገቧቸው ወንዶች ሁኔታ ግን ምንም የነገሩንና ያወቅነውም ነገር የለም፡፡
ያንን ቀንና በነጋታውም ቁርስ፣ ምሳና ራታችንን በሰአቱ አቋጥረው አበሉን፡፡ አንዳቸውም ወደነበርንበት ክፍል ትውር ሳይሉ በሠላም ውለን አደርን፡፡ ውጋቱ ትንሽ በረድ ቢልልኝም ከእንብርቴ በታችና ብልቴ በጣም አብጦ ክፉኛ ያቃጥለኝ ነበር፡፡
“ልክ በሶስተኛው ቀን ግን ያልጠበቅነው መአት መጣብን፡፡ የመኖቹ ገና በጠዋቱ ተሰብስበው መጡና በሩን ከፍተው አይናቸው ያያትን ሴት እያስነሱ እዚያው ወለሉ ላይ እያንደባለሉ መገናኘት ጀመሩ፡፡ ትንሽ በረድ ያለላቸው ሁለት ትላልቅ የጭነት መኪናዎች ወደ ግቢው እንደገቡ ነበር፡፡ በጭነት መኪናዎቹ ተሳፍረው የመጡት አንድ ስምንት የሚሆኑት የመኖች ከጩቤያቸው ሌላ ጠመንጃም ታጥቀዋል፡፡
ፊታቸውን አይናቸው ብቻ ሲቀር በጨርቅ ተሸፋፍነዋል፡፡ በጣም ያስፈራሉ፡፡ ከእነሱ አንደኛው ወደ እኛ ክፍል ገባ ሲል ሶስት የመኖች ሶስቱን ሴቶች ወለሉ ላይ ጥለው እየተናገኙዋቸው ነበር፡፡ የሆነ ነገር ጮክ ብሎ እየሳቀ ከተናገረ በኋላ በእግሩና በያዘው ሸምበቆ መታ መታ አድርጐ አስነሳቸውና ሴቱን ሁሉ አንድ ባንድ እየቆጠረ ወደ በሩ ተጠግቶ ወደቆመው አንደኛው የጭነት መኪና ላይ እንድንሳፈር አደረገ፡፡
ሁለት ሴቶች ደጋግፈው በማንሳት ከክፍሉ ውስጥ ቢያስወጡኝም ከጭነት መኪናው ላይ ግን ቢያረጉ ቢሠሩኝ እግሬን ማንሳት አቅቶኝ መሳፈር ሳልችል ሰውነቴ እየተንዘፈዘፈ ብቻዬን እንደቆምኩ ቀረሁ፡፡
“ሴቱን ሁሉ የጫነው የጭነት መኪና ከግቢው ለመውጣት መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ ሌላኛው የጭነት መኪና እኛ ከነበርንበት ክፍል በጀርባ በኩል ብቅ አለ፡፡ ከእኛ ተለይተው የወሰዷቸውን ወንዶች በሙሉ አጭቋል፡፡ ያጐቴን ልጅ ሽፋ አልቃድርን እንዴት ሁኖ እንደሆነ ለማየት ብዬ ከወዲያ ወዲህ ባይኔ እያማተርኩ ብፈልገውም ማየት አልቻልኩም፡፡
ሆድ ብሶኝ ተንሰቅስቄ እያለቀስኩ ያባት የናትህ ውቃቢ ይከተልህ፣ እሱ አላህ እንዳለ ይጠብቅህ እንጂ እንግዲህ እያልኩ ፍጥርቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ “ሴቱንና ወንዱን ሁሉ የጫኑት የጭነት መኪናዎች ተከታትለው ከግቢው እንደወጡ እኔና ግቢውን እንዲጠብቁ ተብለው የቀሩት ሠባት የመኖች ብቻ ቀረን፡፡ ከቶ እኔን ምን ሊውጠኝ ነው ብዬ ገና ማሰብ ከመጀመሬ ያ ሁሉ የመን እየተንጋጋ መጥቶ ሰፈረብኝ፡፡
ቀድሞ የያዘኝ የመን አሸዋው ላይ ጥሎ መጀመሪያ እንደተገናኘኝ በታጠቀው ስለታም አስፈሪ ጩቤ ከደረቴ ጀምሮ እስከ ብልቴ ድረስ አርዶ የጣለኝ ነበር የመሠለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ምን እንዳደረጉኝ ምን እንደሆንኩኝ አላስታውስም፡፡ ይሄውልሽ እንግዲህ የእኔ ነገር የቀረው እንዲህ ሆኖ ነው፡፡ ግን እኮ ገና አስራ ስድስት አመቴ ነው!”
አይሻ ኑርሁሴን ታሪኳን እንዲህ ከተረከችው በኋላ በረጅሙ ተንፍሳ ፀጥ አለች፡፡ እንባዋ ግን መንታ ቦይ ሰርቶ፣ ያን ያለአቅሟ የተሸከመችው መከራና የተቀበለችው ወደር የለሽ አስከፊ ፍዳ መላ ወዙን ምጥጥ አድርጐ ያከሰለውን ጠይም ፊቷን እያጠበ ያለማቋረጥ ይፈስ ነበር፡፡
የመኖቹ እስክታክታቸው ድረስ ለሰባት እየተፈራረቁ ሲደፍሯት ከቆዩ በኋላ፣ ስትደክምባቸውና የሞተች ሲመስላቸው መሸትሸት ሲል ጠብቀው ከሁዳይዳ ከተማ መዳረሻ አውራ መንገድ ዳር ላይ ጥለዋት ተመለሱ፡፡ በሞትና በህይወት መካከል ሆናና ከአንገቷ እስከ እግሯ ድረስ በደም ተነክራ ስታጣጥር ያገኟት አንዲት አሮጊት የመናዊት ለነፍሴ ብለው ከወደቀችበት አንስተው ለከተማው ቀይ ጨረቃ ቢሮ አስረከቧት፡፡ የቀይ ጨረቃ ቢሮውም የአቅሙን ያህል መጠነኛ የህክምና እርዳታ ካደረገላት በኋላ፣ የተሻለ ህክምና ብታገኝ በሚል የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ያቋቋመው ትልቁ የስደተኞች ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፕ ወደሚኝበት የሃርዳህ ከተማ ተላከች፡፡ ሆኖም ግን አይሻ የመኖቹ በተደጋጋሚ የፈፀሙባት የቡድን አስገድዶ መድፈር የፌስቱላ በሽተኛ ስላደረጋት ከካምፑ አቅም በላይ ነበርና እንደታሰበው በደንብ ሊረዳት ሳይችል ቀረ፡፡
አይሻ ሽንቷን መቆጣጠር አለመቻሏ የፈጠረባት አቻ የለሽ የቅስም ስብራትና የስነልቦና ቀውስ በቀረው እንጥፍጣፊ አቅሟ ልትሸከመው የምትችለው ስላልሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ራሷን ለመግደል፣ ሞክራ ነበር፡፡ አንዱም ግን አልተሳካላትም፡፡
በመጨረሻም የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕን ለቃ በመውጣት፣ ራሷን ከመላው የሰው ልጆች ሁሉ በማግለል እግሯ ወደ መራት የሃርዳህ ከተማ አውራ ጐዳና ጥግ ላይ ኑሮዋን አደረገች፡፡
ለልመና የምትዘረጋውን እጇን ያየና ለነፍሴ ያለ የሚጥልላትን ምጽዋትና ቁራሽ ቂጣ ሲገኝ እየቀመሰች የታጣ ቀንም አንጀቷን አጥፋ ተኮራምታ እያደረች ኑሮዋን ትኖረዋለች - የልጅነት ህልሟን የልጅነት ምኞቷን በየመን አሸዋ ውስጥ ቀብራ፡፡
ሼክ አብዱልቃዊ የተባሉት የሁዳይን መንደር አዛውንት የአካባቢው የየመን ቤዶይን ጐሳ መሪ ሲሆኑ በሶማሌ የህገወጥ ስደተኛ አጓጓዥ ጀልባዎች በየቀኑ እየተጫኑ በሁዳይዳ የጠረፍ አሸዋ ላይ የሚደትን በመቶዎች የሚቆጠሩና እጅግ የሚበዙት ኢትዮጵያውያን የሆኑ ህገወጥ ስደተኞችን ባሠማሯቸው ህገወጥ የጐሳ አባሎቻቸው አማካኝነት እያገቱ የሚዘርፉና ለሌሎች ህገወጥ ሰው አስተላላፊዎች የሚሸጡ ቀንደኛ ወንጀለኛና የወንጀለኛ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ከነአይሻ ጋር አግተዋቸው የነበሩትን ሁለት የጭነት መኪና ሙሉ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ጥቂት ኤርትራውያን ወንድና ሴት ስደኞች የት እንዳደረሷቸው ለማወቅ የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር እስከ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ እልህ አስጨራሽ ትግል ቢያደርጉም አንዳቸውም አልተሳካላቸውም፡፡
የአይሻ ነገር እንዲህ ሆነ፡፡ ለመሆኑ የእነ ሃፍቶም ግደይና የሌሎቹ እጣ ፋንታስ እንዴት ሆኖ ይሆን? (ይቀጥላል)

Read 3695 times Last modified on Saturday, 08 December 2012 14:13