Saturday, 08 December 2012 11:18

“የአዲስ አበባ ሰው ወሮበላ ነው የሚመስለኝ

Written by  የሰሜን ጎንደር የጉዞ ማስታወሻ ከትርጉም ሚካኤል pinumed@gmail.com
Rate this item
(5 votes)

ኅዳር 15 2005 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ ላይ አርሰናል 3 ፉልሃም 3 ምስራቅ በለሳ/ሰሜን ጎንደር የምትል ጽሑፍ ጽፌ ነበር፡፡
አንድ ወዳጄን “አንተ!” ያ ጽሑፌ እኮ ጋዜጣ ላይ ታተመ … አነበብከው?” ብዬ ብጠይቀው “በትግርኛ ነው!” ብሎ ተሳለቀብኝ፡፡
እኔ ግን “ጀማሪ እረኛ ከብት አያስተኛ” ነውና ይኸው ዛሬ ደግሞ ጎንደር ላይ በሰነበትኩባቸው 27 ቀናት ውስጥ፤ በሌሎች ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በ3ቱ ወረዳዎች (ቋራ፤ ምእራብ በለሳና ምስራቅ በለሳ) ከገጠሙኝ ሰዎች፤ የስራ ሃላፊዎች፤ ገበሬዎች፤ የገበሬ ልጆች፤ ባለ ሆቴሎችና አስተናጋጆች ጋር የተለዋወጥኳቸውን ወግና ቁም ነገሮች ፃፍኩ፡፡ ይመቻችሁ!! - በሸገር 102.1 ኤፍ ኤምኛ፡፡

የጉዞዬ ቀዳሚ መዳረሻ ወረዳ ቋራ ናት፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ሀገር እንደመሆኗ በጉዞዬ ውስጥ ቋረኛውን ቴዎድሮስን በአካል የማገኘው እየመሰለኝ ነበር የተጓዝኩት፡፡
የስብሃት ገ/እግዚአብሔርን (ነፍስ ይማር) “እነሆ ጀግና” የምትለውን አነስተኛ መጽሐፍ ያነበበ ሰው፣ ስለ አፄው ብዙ ተመራማሪዎችና የታሪክ ፀሐፍት ካስቀመጡልን ማንነቱና ሰብአዊነቱ ወጣ ባለ መልኩ እንድናየው ያደረገ መጽሐፍ በመሆኑ የኮሶ ሻጭዋን ልጅ፤ ከሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ውጭ ሆኖ የነገሰውን፤ ለዘመነ መሳፍንት ማክተም ተጠቃሽ የሆነውን፤ በጠላት እጅ አልወድቅም ብሎ ራሱን ለሀገሩ ክብር አሳልፎ የሰጠውን ታላቅ መሪ የትውልድ ቦታ የማየት አጋጣሚን የፈጠረልኝ አዕምሮአዊ ጉዞ በመሆኑ ለየት ያለ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡
በዕዝነ አዕምሮዬ ተቀርጾ የነበረው ታዲያ ቋራ ወረዳ አፄ ቴዎድሮስን ያፈራች ሀገር ናት ስትባል እንደው ፋሲል ግንብ ስር ሸጥ - ሸጡንና ጐንደር ዙሪያው ላይ በቅርበት የምትገኝ ቦታ ትመስለኝ ነበር፡
በጉዞዬ የተረዳሁት ግን የአፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታ ከጐንደር 280 ኪ.ሜ አካባቢ “ቸሪጌ ማርያም” መሆኗን ስገነዘብ፣ ከቦታው ቆላነትና ወደ ሱዳን ድንበር እጅግ የቀረበ መሆን አንፃር ሳስተውል፤ “ወይ የአሁኗ ኢትዮጵያ በወቅቱ እስከ ግብጽ ተንሰራፍታ ትገዛ ነበር” አልያም “ያ! ቋረኛ የሱዳኖች መሲህ ሊሆን ይገባ ነበር እንጂ ከዚያ ቆላ መሬት ተነስቶ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብሯል” ቢባል ነገር ፍለጋ እንዳይሆን ስጋት አድሮብኝ ነበር፡፡
ቋራ ደርሰን አንድ ሆቴል አልጋ አገኘንና ባለ 30 እና 40 ብር አልጋ አለ ተብዬ….
“ልዩነቱ የግል ሻወርና የጋራ ሻወር ይሆን?” ብዬ ስጠይቅ፤
“ዋ! ምን ይላል፡፡ አንተው ባለ 30 ብሩ የድሮው ቤት ነው፤ ባለ 40ው ብር ደግሞ አዲሱ ቤት ነው፡፡”
“ታዲያ እህቴ መታጠብ ፈልጌ ነበር የት ነው የምታጠበው?” ብዬ ጠየቅሁ፡፡
“እረገኝ መታጠቢያ የት ሊኖር ብለህ?! ኸዚያ ገለጉ የሚባል ወንዝ አለ፤ ወርዳችሁ ትታጠቡ እንደሁ እንጂ?”
ወይ ጉድ! መቼም በቀበና፣ በኡራኤል፣ በፒያሳ፣ በመርካቶ በአምባሳደርና በመሳሰሉት የአዲስ አበባ ጓዳዎች ሥር የሚያልፉ ወንዞች የሚያግተለትሉትን የሽንት ቤት ፍሳሽ፤ ግማትና ክርፋት እያስተዋለ ለሚኖር አዲስ አበቤ፤ ወንዝ ወርደህ ታጠብ!! ሲባል ኡ ኡ ያሰኛል!
ያም ሆኖ በቀረበልን ብቸኛ የወንዝ ባኞ (River Shower) አማራጭ መለቃለቃችን ግድ ነበርና ቅያሪ ልብስ፤ ፎጣና ሣሙና ይዘን ወንዝ ስንወርድ ያየነው ትርዒት አስገራሚ ነው፡፡ ለካ፤ የሀገሬው ሰው ወንድ ሴቱ፤ ህፃን አዛውንቱ፤ ከብቱም መኪናውም ነፍሱን ቀዝቀዝ የሚያረገው ገለጉ ወንዝ ውስጥ ነው፡፡ ገለጉ ወንዝ እስከ 70 ሜትር ዙሪያ - ገባውን የሚያደርስ ሆኖ፣ ኮራ ደርበብ ብሎ መሰሰስ እያለ የሚጓዝ ነው፡፡
ውሃ ዋና ሳይችል የገባን ሰው ካገኘ ደግሞ እያሳሳቀ እልም ማለቱ እማይቀር ነው፡፡
ከዚሁ ወንዝ ጋር ተያይዞ በስራ ክራሞቴ በርሚል ተራራ ወደሚባል ጤና ኬላ ስንሄድ፣ ይሄው ወንዝ ከ40 ኪ.ሜ ርቀት በኋላ እንደገና ተጥመልምሎ መጥቶ ጐምለል ሲል አገኘነው፡፡ ታዲያ እዚሁ ወንዝ ላይ በቆላው ሙቀት የተቃጠሉና የነደዱ የአማራ፤ የአዊና የጉምዝ ብሔረሰብ ልጆች ከከብቶቻቸውና ከፍየሎቻቸው ጋር ሲንቦጫረቁ ማየት ራሱን የቻለ የተፈጥሮን ውብ ስጦታ ማጣጣም ነው፡፡
እነዚያ ሁሉ “ኩታራዎች” ሲዋኙ ይቆዩና ከወንዙ ስር ባለች አንዲት ጉብታ ላይ ወጥተው በኮዳቸው ውሃ እየቀዱ፤ እያፈሰሱ የተፈጥሮ ሸርተቴ ሠርተው እርቃናቸውን ይንሸራተታሉ፤ ሲያሻቸው በደረታቸው ይወርዳሉ፤ ደግሞ አፈርና ጭቃው አላንሸራትት ሲላቸው ወንዙ ውስጥ ዘለው ይገባሉ፡፡ ድንቅ ትዕይንትና ውብ ቀለም አለው፡፡
ታዲያ በዚህ መሃል እዚህ አዲስ አበባችን ውስጥ ጓደኝነትና የልብ ወዳጅነት ሲያሻው የሀገሬን የወንዜን ሰውና ዘር የት ነው የማገኘው ለሚል አንዳንድ ባካና ከተሜ፣ ምነዋ እዚህ መጥተህ የቋራን ህዝብ ንጹህ ፍቅር ባየህ ያሰኛል፡፡ ወይ ኢትዮጵያ! የህብረ ቀለም ህዝብ መናኸሪያ!!
የሆቴሉ ባለቤት፤ ወጣት፣ ተግባቢና ነቄ ናት፡፡ 3000 ህዝብ አካባቢ በሚኖርባት፣ ነገር ግን ከፍተኛ የሰሊጥ ገንዘብ በሚንቀሳቀስባት፣ ትንሽ ወረዳ ውስጥ ዲኤስ ቲቪ (DS TV) ማሳያ ክፍል አላት፤ ቢራ ትሸጣለች ወዘተ፡፡
ታዲያ አንድ ሮብ ቀን ሥራ ጨረስኩና “ወንዝ - ባኞ” ወርጄ ታጠብኩና ጥላ ስር አረፍ ባልኩበት፤ ያችው የሆቴል ባለቤት ነጭ ባዶ ወረቀት ይዛ መጣችና…
“ንሳማ አንተ፤ ዛሬ ማታ ኳስ አለ አሉ ፃፍልኝማ?”
“ማንና ማን ይጫወታል?” አልኳት፡፡
“ኧረ እንጃልኝ እነማን ናቸው ዛሬ ይጫወታሉ ያልክ አንተ?” ወደኋላ ዞር ብላ ጠየቀች፡፡
“ማንቸስተር ኸ ቼልሲ ነው ሚጫወት” ፖሊስ - ልብስ የለበሰ አንድ ወጣት መልስ ሰጠ፡፡
“በል ጣፈውማ”
“ስንት ሰዓት ላይ ነው ጨዋታው?”
“እረዲያ ዝም ብለህ በሶስት ተኩል በለውማ፡፡ ኋላ ምነዋ ያልለጠፍሽ እንዳይሉ ብዬ እኮ ነው!”
እየገረመኝ ፃፍኩና ሠጠኋት፡፡ የሆቴሏ በር ላይ ወስዳ ለጠፈችው፡፡
ሌላው የቋራው አስገራሚ አጋጣሚ የኢቲቪ የአዲስ አበባ የተመልካች ድርቅ በቋራ ነዋሪ የተካሰ ይመስላል፡፡ “እረ ከኢቲቪ በላይ ከቴም ምን ልናይ?” ያለ እስኪመስል “ዜናና የሰው ለሰው ድራማ” ለማየት ወደ ሆቴሉ የሚመጣው ሰው ብዛት የሚደንቅ ነው፡፡
በቆይታዬ እንደተረዳሁት ለዚህ ምክንያቱ ሁለት ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ወረዳዋ የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶ የተጠናቀቀላት ቢሆንም የቤት ቆጣሪ (ባልቦላ) ጠብቁ ተብለው እየተጠባበቁ በመሆኑ ጀነሬተር ባላቸው እኔ እንደገባሁበት ሆቴል ዓይነት ውስጥ ካልሆነ በቤታቸው ቴሌቪዥን ማየት የማይችሉ በመሆናቸው ሲሆን፤ ሌላውና አስገራሚው ምክንያት ግን የ2፡00 ሰዓት ዜና ላይ የየዕለቱን የቢዝነስ ዘገባ በተለይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (የECEXን) የሠሊጥ መግዣ ዋጋ ነዋሪው አጽንኦት ሰጥቶ የሚከታተል በመሆኑ ነው፡፡
በአንድ የዜና አጋጣሚ ታዲያ ከሆቴሉ ባለቤት ጐን ቁጭ ብዬ ዜና ስከታተል (የሰሊጥ እርሻ እንዳላት ልብ ይሏል)
“ዛሬ በዋለው የአለም ገበያ ዋጋ የአንድ ኩንታል ሰሊጥ መሸጫ ዋጋ 1850 ብር መሆኑን ከ ECEX ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡”
“ሰማህልኝ አንተ የ ECEXን ስራ? የዛሬ ወር 2300 ሲገዛው የሰነበተውን ሠሊጥ የአዝመራ መሰብሰቢያ ወቅት ደረሰ ብሎ 1850 ብር ያስገባው? ኧረ የመድኃኔዓለም ያለህ!! አሄሄ! ሚሸጥለትን ያገኝ መስሎት! አይ ሞኞ!!”
ጨዋታዋ ኮረኮረኝና “ስለECEX መረጃው አለሽ እንዴ?” ጥያቄ አቀረብኩ፡፡
“እኔን ነው?”
“አዎ እህቴ?”
“ዋ! ምን ጅል ነው አንተ ECEXን ታውቂዋለሽ ወይ ይበለኝ? ኸዚያ አንድ ወንበር አለኝ”
“እውነትሽን ነው?”
“ኋላስ አንተው ቀላል ሰው አርገኸኝ ኖረሃል! “ዶ/ር እሌኒ ሸራተን እራት ጋብዛኝ ኑራ እኮ ነው!”
“አዲስ አበባን ታውቂዋለሽ ማለት ነው?”
“እንግዲያ!”
“ታዲያ ለምን ወደ አዲስ አበባ መጥተሽ ንግድ ምናምን አትሞክሪም? ቤትም ገዝተሽ ልጆችሽን እዛ ብታስተምሪ ጥሩ ይመስለኛል”
“እረ መከራዬ! እኔ ነኝ አዲስ አበባ የምኖር? እንደው ውነቱን ንገሪኝ ካልከኝ ሙላው የአዲስ አበባ ሰው ወሮበላ ነው ሚመስለኝ!
“እንዴ የአዲስአባ ሰውማ ይሄን ያህል ወሮበላ አይደለም!” ምነው እናቴ” ወሮበላ መባሌ እየከነከነኝ ሳለ ቀጠለች፡፡
“ኧረ እንጃልኝ አንተው! እንዲያው ሰዉ ዝም ብሎ ችኩል ነው፡፡ በዚህ ብትሄድ ክልብ! ክልብ! በዚያ ብትሄድ ክልብ! ክልብ! ከቴም እረፍት የማያውቅ፡፡
መቼ ነው በዛ ሰሞን እህቴ ወደ ገርጂ ቤት ልትገዛ አስባ ኑራ እንዲያው አብሬያት ብሄድ የደላላ መአት በዜት ሊያላውሰን፡፡ ታዲያ አንዱ መጣልህና “እዚህ እኔ ጋ ያለው ቤት ስፋቱ 300 ካ.ሜ ነው፤ ቪላ ነው፤ የግንብ አጥር አለው፤ ያለቀለት ነው” ብሎህ ሲያበቃ ሄደ … ብታየው ምኑ ከምኑ ተገናኝቶ ብቻ በአንድ ገጥ ሰርቪስ ቤቶች ያሉት ነው፤ እንኳን ግንብ አጥር ሊኖረው የቆርቆሮ አጥሩ በወጉ ያልተከወነ ሁኖ ታገኘዋለህ፡፡ ሌላው ይመጣልህና “እኔ ጥሩ ቤት አለኝ” ይልህና በሌላ መንገድ ወስዶ ያነ የቀደመው ደላላ ያሳየህ ቤት ውስጥ ወስዶ ይዶልሃል፡፡ ደሞልህ አንዱ ይመጣና “ቤት ፈልጋችሁ ነው?” ይልሃል
“አዎን” ትለዋለህ፡፡
“ለሌላ ደላላ ነግራችኋል?”
“ምኑን ነው የምንነግር አንተ?” ብትለው
“አይ ሌላ ደላላ ከሰማ ኮሚሽኔ ዝቅ ስለሚል ብዬ ነው”
“እረ እኛ ምኑን አውቀነው ብለህ ዝም ብለህ ቤቱን አሳየን” ብለነው አብረን መሄድ፡፡
ኋላልህ እንዳይነገረው የተባለ ደላላ ይመስለኛል በሌላ ዙሮ ቆይቶ ኑሮ “ምን ቆርጦህ ነው ሳትነግረኝ የምትመጣ?” ብሎ እንዲያው ሊፋጁ!
“ዋ! ትተናቸው ሄድነ፡፡”
“እስኪ አሁን ያገኙትን አብረው ቢካፈሉ ምን ነበር?” እግዜሩስ መች ይወደው ብለህ እንዲያው አጋሰስነትና ሆዳምነት እንጂ፡፡ ኋላማ ምንም ላይረቡ ቢያተክሩነ “አንቺ እንዳረግሽ አርጊው” ብዬ ትቻት ወደ ሃገሬ መጣሁ፡፡ ኧረ ግምኛ ነው አንተ የአዲስ አበባ ሰው! ፈሪሃ እግዜሩም የሌለው፡፡” (ይቀጥላል)

Read 4512 times