Saturday, 08 December 2012 11:12

እውነት እቺ አገር የማን ናት?

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(2 votes)

ከስቴድየም መገናኛ የሚሄድ ታክሲ እንዳለ ባውቅም አስር ሠዓት ከሞላ በኋላ በቀላሉ ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ሃያ ሁለት ማዞርያ ብቻ! ትርፍ መክፈል ስላልፈለግሁ እስከ መገናኛ ያለውን መንገድ በእግሬ እለው ጀመር፡፡ ጥቂት መቶ ሜትሮችን እንደተራመድኩ አንድ ወጣት ብቻውን ተቀምጦ አየሁ፡፡ እያለቀሰ ነበር፡፡ (ወንድ ልጅ?) ሲያለቅስ ያሳዝናል፡፡ በግምት ሃያ አራት ዓመት ይሆነዋል፡፡ አማርኛ በትክክል አይችልም፡፡ ሁለተኛ ቋንቋው ስለሆነ፡፡ ጠየም ያለ ልጅ ነው፡፡ ከጣውላ በተሠራ ሰሃን ላይ እያዞረ የሚሸጣቸው መፋቂያዎች በስርአቱ እንደተደረደሩ ናቸው፡፡ እፊቱ አለሁ፡፡ አንዲት መኪና የአስፓልቱን ጥግ እየታከከች መጥታ ቆመች፡፡ ሁለት ወጣቶች ናቸው፡፡ ወንዶች፡፡ መኪናዋን የሚነዳት ወጣት አለቅጥ የለቀቀውን የመኪና ቴፕ ሲቀንስ ሁለተኛው ወጣት የመኪናዋን መስታወት ዝቅ አድርጎ አንገቱን አሰገገ፡፡

ወሬ ፍለጋ፡፡ ጥቂት ብቻ አስተውሎት በዚህ ጽሑፍ የማላሰፍረውን አፀያፊ ቃል ተናገረ፡፡ የሚያለቅሰውን ወጣት የብሔር ስም ጠርቶ አናናቀውና የልጁን ችግር መስማት ጊዜ መግደል እንደሆነ በሚጮህ ድምጽ ለመኪና ዘዋሪ ጓደኛው ተናገረ፡፡ መኪናዋ ተስፈነጠረች፡፡ ሙዚቃዋ እየጮኸ!  
ባለፈው ሳምንት በአንድ ልብ ወለድ መጽሐፍ መነሻነት ‹ኢትዮጵያዊነት የማን እዳ ነው?› ብዬ ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ በድፍረት ለመሰንዘር ያነሣሣኝን ታሪክ ከአፄው ዘመን ጀምሮ የነበረውን ‹‹የምሁራን›› አመጣጥ ነካ ነካ ለማድረግ ሞክሬ ነበር፡፡
ኢትዮጵያዊነት የማን እዳ ነው? በመካከላችን አንድነት የሚኖረው መቼ ነው? መተሳሰብ የሚሰፍነው መቼ ነው? ለየራሳችን ፍላጎት መተሳሰቡን (‹‹የመረዳዳት ባህላችንን››) እናቆየውና የራሳችን የሁላችን ስለምንላት ሀገራችን የጋራ አስተሳሰብ አለን? አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቻችን ከራሳችን ውጭ ማንም ያለ አይመስለንም፡፡ ሀገሪቱም ከእኛ ውጭ አሳቢ እንደሌላት እንድመድማለን፡፡ አለዚያም ሀገሪቱን ረግጠን እና በሀገሪቱ አላግጠን ለማለፍ መለኮታዊ ቅባት እንደተቸረን ይሰማናል፡፡ ይህማ ባይሆን እኩልነታቸውን አስከብረናል በምንልበት ሀገር ዘለፋን አፈናጥረን በመኪና ባልተስከነተርን !
ዛሬ ይበልጡን ማየት የፈለግሁት እኛ በእድሜአችን ስለምናውቀው ኢህአዴግ የመንግስት አመራር ዘይቤ ነው፡፡ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያን እዳቸው አድርገው ያስቧት እንደሆን ሳምንት ዕድሜ ካለን እንቀጥልበታልን፡፡
ዛሬ ግን መንግስትን እየመራ ያለው ኢህአዴግ፣ ኢትዮጵያ እዳው ነች ወይ? የሚለውን እንመልከት፡፡ ታዲያ ይህ ከፖለቲካ ተንታኝ የቀረበ ትንታኔ አይደለም፡፡
ኑሮን ከሚታዘብ ተራ ጭሮ አዳሪ እንጅ! ኢህአዴግ በዘመኑ ብሄርና ብሄረሰብ የሚሉ ቃላት ላይ የበለጠ ትኩረት አድርጓል፡፡ ታላላቅ ፌስቲቫሎችን እና ልዩ ልዩ የመገናኛ መድረኮችን እያዘጋጀ እርስ በእርስ ለማወዳጀት መጣጣሩም የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ የ ‹‹ኢህአዴግ ህሊና ምጥቀት ማሳያ ›› ተብለው በድርጅቱ ሰዎች የተሞካሹት መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን ተከትሎ መሠረተ መንግስት የሆኑት የሀገሪቱ ብዙኃን መገናኛዎች፣ ከሀገሪቱ ጥግ እስከ ጥግ የነበረውን የሀዘን ድባብ አሳይተዋል፡፡ አዳጊ በሚባሉ አካባቢዎች የታዩ ለቀስተኞች ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ፣ ከዚህ በፊት ያልነበረንን እውቅና በዘመነ ኢህአዴግ ስናገኝ ዋናው ተዋናይ አቶ መለስ ነበሩ የሚል ነው፡፡
በሀገሪቱ የመንግስት እና በአንዳንድ የግል ሚዲያዎች አንድነትን ስለመሰረቱበት ውለታቸው የሚወራላቸው አቶ መለስ ወይም ኢህአዴግ ፣ በውጭ ሚዲያዎችና በአንዳንድ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ደግሞ ሀገሪቱን ለመከፋፈል የተነሱ በብሄሮችና ብሄረሰቦች ላይ መለያየትንና ጥላቻን ያመጡ ሲሏቸው ይደመጣል ፡፡ የተቃውሞ እና የድጋፍ ፖለቲካውን ትተን መሰረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያለንን የአንድነት ብርታት ብንቃኘው ክፍተታችንን ማግኘት የምንችል ይመስለኛል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስለወጠነው ብቻ የህዳሴ ግድብን በጥላቻ ከሚያዩ ተቃዋሚዎች አንስቶ፣ የግል ጋዜጦች ስለሆኑ ብቻ ኢህአዴግን አይወዱም ብለው እስከሚደመድሙ የመንግስት ሰዎች ተዛንቀናል፡፡ ፖለቲካዊ ፍላጎት ምን እንደሆነ፣ ሀገራዊ ፍላጎት ደግሞ ምን እንደሆነ ማወቅ ተስኖን፣ በረባ ባልረባው ስንወዛገብ ሀገሪቷ ሀገራችን አለዚያም ሀገራቸው አልመስለን አለች፡፡
ዛሬ ርእስ ያደረግነው ኢህአዴግ የመንግስትን ስልጣን ሲይዝ፣ “ሀገሪቱ የእኔ እዳ ናት” ብሎ አለዚያም “የራሱን ፍላጎት ለማሟላት” ከሚለው መደምደምያ መለስ በህወሓት ምሰሶነት በብአዴን፣ኦህዴድ እና ደኢህዴን አጃቢነት የተመሠረተውን ግንባር መለስ ብሎ መመልክቱ ይበጃል፡፡ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የተመሠረተው የብሔር ፖለቲካን ያራምዱ በነበሩ የዩንቨርሲቲ ወጣቶች መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ ከተማሪ እንቅስቃሴ በመፍለቃቸው ምክንያት እኒህ ድርጅቶች በሙሉ (ኢህአፓ፣ መኢሶን፤ ህወሓት እና ሌሎችም በድህረ 66 አብዮት የመጡት) ተጣብተዋቸው የኖሩ ድክመቶች የህወሓትም ድክመቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ መሥራች መሪዎች ደግሞ በጊዜው ከቀ.ኃ.ሥ. ዩንቨርሲቲ ተማሪነት ያላለፉ ሆነው መገኘታቸው ከእነዚህ ድክመቶች መኻከል ከፊሎቹ በህወሓት እንቅስቃሴ ውስጥ የበለጠ የጎደሉና የገረሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ፡፡ እነዚህም ችኩልነት፣ ግልብነት፣ ስሜታዊነት፣ ጀብደኝነት የመሳሰሉት ናቸው›› በማለት ሐሳባቸውን የሚሰነዝሩት ዘለዓለም ቁምላቸው ‹‹የኢትዮጵያዊነት እና የአማራነት መለያ ህብር›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ህወሓትን የተመለከተ ጥቅል ሐሳብ እንዲህ ይሰነዝራሉ፡፡
‹‹የወያኔ እንቅስቃሴ ‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው› በሚል ፈሊጥ በምንም ዓይነት መርሆ ራሱን ሳያግት የተባሉት ድክመቶች ኋላ ቀር የሆኑ የጅምላ ደመነፍሳዊ ስሜቶች ከሚገባው በላይ እንዲኮረኮሩና እንዲያራግቡ በማድረግ የዘር ጥላቻን ለማቀጣጠል ተግባር መጠቀሚያ ማድረግ በመቻሉ ብቻ ነው››
እንግዲህ ህወሓት መራሹ መንግሥት ስልጣን ከተረከበበት ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ ከሚነሡት ትችቶች ዋናው የብሔር ፖለቲካ አራማጅነቱ እና የዘር ጥላቻን አስፋፍቷል የሚለው ነው፡፡ ይህን ትችት የሚሰነዝሩት ወገኖች የሀገሪቱ የሲቪል የኃላፊነት ቦታዎች እና ቁልፍ የጦር ሠራዊት ቦታዎች በትግራይ ተወላጆች እጅ ብቻ መውደቁን እንደማስረጃ ሲያነሡ ይደመጣል ፡፡
አሁን ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩን ማለፍ ተከትሎ፣ የሀገሪቱ ፖሊስዎች እና ዕቅዶች በሙሉ በእሳቸው የተሰሩ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ስርዓትን ከመገንባት ይልቅ ጊዜያዊ ማለፊያዎችን ማሰናዳት የበለጠ ይመስላል፡፡ ይህ ሆነ የተባለው ይልቁንም በኢሕአዴግ ሥርዓት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሀገር የዜጎች መሆኗ በምን ይታወቃል?
በዚህ መሠረት ይህችን ሀገር ላለፉት 21 ዓመታት ሲመራት የቆየው ኢህአዴግ እና ርዕዮተ ዓለሙ፣ በአንድ ሰው ላይ የተንጠለጠለ ነበር፡፡ በግንባሩ ውስጥ ቦታ አላቸው የሚባሉት አራቱ ድርጅቶች ይቅሩና አዛዥ ናዛዥ ነው የሚባለው ህወሓት ይቆይና የዚህች ሀገር አስተዳደሪ የአቶ መለስ ጭንቅላት ነበር ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡ ይህ በመሆኑ ምን በጎና ክፉ ጎኖች ሊኖሩት ይችላሉ?
የአንድ ግለሰብ ኃይለኛ ተጽዕኖ ወይም ከፍ ያለውን የሥራ ኃላፊነት መውሰድ፣ በመሪው ድርጅት ወይም በተመሪው ሀገርና ሕዝብ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የእነ ፕሉቶን ፍልስፍና ርቀን መጥቀስ ሳይገባን፣ ከመለስ በፊት የነበሩትን ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም እና አስተዳደራቸውን ብሎም ሀገራዊ ውጤቱን መመልከት ይቻላል፡፡
መንግሥቱ ኃ/ማርያም ቁጡ መሪ ነበሩ፡፡ ዘመናቸውም አብዮተኝነት ነበር፡፡
ግልፍተኝነት፡፡ ከውይይት ይልቅ ጥይት የሚቀድምበት፡፡ ተመሪው ሁሉ የእሳቸው ተከታይ አልነበረምን? እንኪያስ ያ ሁሉ ዜጋ በጥይት ባልተላለቀም ነበር፡፡
ይህ የአንድ ግለሰብ አመራር በመንግሥት ውስጥ የራሱ ተጽእኖ እንዳለው ለመመልከት ያመጣነው ምሳሌ ነበርና እንዳመጣን እንመልሰው፡፡ ወደ መለስ ዘመን ስንመጣ ደግሞ በዘመናቸው ሲደነቁም ሲወገዙም የኖሩ ስራዎችን ሠርተው ማለፋቸው የሚታወቅ ነው፡፡
የተነሳንበትን ነጥብ ስንመለከት ግን ሀገሪቱን የዜጎች ሀገር ሊያደርጓት ቀርቶ፣ የኢህአዴግ እንኳ እንዳላደረጓት “ብቻቸውን ሲሰሩ ኖሩ” የሚለው የድርጅታቸው ምስክርነት በቂ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚይዟቸው አቋሞች እና የሚያራምዷቸው ሐሳቦች አስደሳች እና አኩሪ ሆነው የሚታወሱት በርካታ ጊዜ ነው፡፡
(ይህ በብዙ የብዙኃን መገናኛዎች እየተደጋገመ ስለሆነ መድገሙ አልታየኝም ) ከዚህ በተረፈ ግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባለ የአስተዳደር ዘይቤ ያመጡት መለስ ዜናዊ መሆናቸውን ለመመስከር የሚያዳግተን አይሆንም ፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ይሁን በሌሎች ልሂቃን ተቀባይነት የተነፈገው የሚመስለውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ (ልማታዊ መንግስት) የተባለ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ያመጡት አቶ መለስ ቢሆኑም፣ ለሀገሪቱ ከዚህ የተለየው አካሄድ ሁሉ እንደማይበጃት ከምርጫ ዘጠና ሰባት ክርክር አንስቶ እስካሁንም እየተቀነቀነ ይገኛል፡፡
ይህ በአቶ መለስ ዕውቀትና ብቃት ላይ የተንጠለጠለ ርዕዮተ ዓለም መጨረሻው ወይም መድረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ወደፊት የምንመለከተው ጉዳይ ይሆናል ፡፡
አቶ መለስ በገነቡት ሥርዓት ውስጥ እንከኖች እንደነበሩ ቢያንስ ከተቃዋሚዎች አንደበት ነጋ ጠባ እንሰማለን፡፡
አንዳንዶቹን እኛም እናውቃቸዋለን፡፡ ፓርቲያቸውም አይክደውም፡፡ በየቀበሌውና በየወረዳው እንዲሁም በየክልሉ እንደ “ማፍያ” መደራጀት የቀራቸው “የመንግስት ሌቦች” እና በዝባዦች መኖራቸውን ማንም አይክድም ፡፡ ልማታችንን የጎተቱት እነማን ሆኑና? ዛሬም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉት የስልጣን እርከኖች በአንድ ብሔር አባላት የተያዙ እንደሆኑ ሀሜት ይናፈሳል፡፡
ሐዋሳ ከተማን አስመልክቶ ጥያቄ ተነሥቷል፣ከደቡብ ኢትዮጵያ የተፈናቀሉት አማሮች መጠጊያ ማጣታቸው እስካሁንም እያነጋገረ ይገኛል፣ ኦጋዴን ውስጥ ያልተፈታ ችግር አለ፣ የኑሮ ውድነት ዜጎችን አስጨንቆ ይዟል፣ ከተሞች በምእራባዊያን ባሕል ተወረዋል ፣ የትምህርት ጥራት ችግር አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፣ ሥራ አጦች በርክተዋል ፣ ካድሬ መሆን የመኖርያ ፈቃድ ከመሰለ ቆይቷል፣ የመኖርያ ቤት እጥረት አሳሳቢ ነው፣ ሃይማኖታዊ አክራሪነት የሁልጊዜ ስጋት ነው፣ የፕሬስ ነጻነት አለ የሚሉ የሉም ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳለ በተደጋጋሚ ይስተጋባል፣ ቋንቋን፣ መሬትን፣ ባሕልን ወዘተ የተመለከቱ ጥያቄዎች ዘወትር ይነሣሉ፡፡ ለእነዚህ እና መሠል ጉምጉምታዎች ቀጥተኛ እና ቀና የሆኑ መልሶችን መስጠት የሚቻለው አስተዳደር ቢመጣለት ሕዝቡ ደስታውን አይችለውም፡፡ በዚያኛው ትውልድ ውስጥ አቋመ ጠንካራ ነበር የሚባልለት ኢህአፓ፣ ደርግ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያደረገውን ጦርነት ይቃወም ነበር (ለሶማሊያ ይረዳ ነበር?) ኢህአዴግም ከአሁኗ ሶማሊያ ጋር ያደረገው ጦርነት ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ውጭ በሌሎች ተቃውሞ የገጠመው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
የዚህ ሁሉ ምንጩ ቢያንስ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገሪቱን የጋራ አድርገን አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ስላቃተን ይመስለኛል፡፡ (ቢንላደን ለሁሉም አሜሪካዊያን እንጅ ለቡሽ አሊያም ለኦባማ ብቻ ጠላት እንዳይደለ ልብ ይሏል)
በርካታ ኀዘንተኞች “የመለስን ራዕይ እናሳካለን፣ የጀመሩትን እናስጨርሳለን” የሚሉ ትላልቅ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ ማስተዋላችን አስደሳች ቢሆንም አንዳንድ ሕዝብ ሲያጉረመርምባቸው የነበሩ ጉዳዮች በእርጋታ ሊጤኑ እንደሚገባቸው መረዳት መልካም ነው፡፡ በየጊዜው የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች የጩኸት ሰበብ የሆኑ የተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦች፣ ክልከላዎች፣ አፈናዎች ወዘተ---በአዲሱ ተተኪ አስተዳዳሪ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡
በመጨረሻ ቀደም ብዬ ያነሳሁትን ጥያቄ ደግሜ በማንሳት ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡ እቺ ሀገር የማን እዳ ናት? የተቃዋሚዎች ወይስ የኢህአዴግ? የእኛ የዜጎች ሁሉ ወይስ የጥቂት ባለጊዜዎች? እውነት እቺ አገር የማን ናት? በደንብ አስበን በደንብ መክረን በደንብ አገናዝበን ለራሳችን መልስ ልንሰጥበት የሚገባ ሁነኛ ጥያቄ ነው፡፡
ያኔ ብቻ ነው “እቺ አገር የአንድ ፓርቲ እዳ ናት ወይስ የሁላችን እዳ?” ለሚለው ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ የምንችለው፡፡ ግዴለም ብንወያይም እኮ አይጎዳንም!

Read 4160 times