Saturday, 08 December 2012 11:07

33ቱ ፓርቲዎች የምክትል ጠ/ሚኒስትሮቹን ሹመት ተቃወመ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(4 votes)

ኢራፓ “ስርአቱ ይስተካከል እንጂ ሹመቱን አልቃወምም” ብሏል
በቅርቡ በአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ቀርቦ የፀደቀው የሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሹመት ህገመንግስቱን የሚፃረር ነው ሲሉ በአዳማ ከተማ ፔቲሽን ተፈራርመው ለምርጫ ቦርድ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡ 33 ፓርቲዎች ተቃወሙ፡፡
ኢራፓ በበኩሉ የኢህአዴግ ስርዓት ይስተካከል እንጂ ከህገመንግስት ውጭ ቢሆንም ለአገር እስከጠቀመ ድረስ ሹመቱን አልቃወምም ብሏል፡፡

የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሁለት ባለስልጣናትን በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ማዕረግ ለፓርላማ አቅርበው ማፀደቃቸው ህገመንግስቱን የጣሰ ተግባር ነው ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡ ባለፉት ጊዜያትም በጥድፊያና ከህገመንግስቱ ጋር በሚፃረር መልኩ የወጡት የፀረሙስና የመያዶች የፕሬስና የፀረ ሽብር አዋጆች ሁኔታው ቀጣይ እንጂ አዲስ ነገር አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል - በመግለጫቸው፡፡ “የአጀንዳው አቀራረብም ሆነ የሹመቱ አፀዳደቅ ከፓርላማው የአሰራር ስነስርዓት ጋር ያልተጣጣመና በተለመደው ጥድፊያ የተከናወነ ነው አጀንዳው ለፓርላማ አባላት በተለመደው አሰራር መሰረት ያልተሰራጨ ከመሆኑም በላይ በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ከህገመንግስቱ አንፃር ሳይመረመርና ሳይታይ መፅደቁ ይህን ያረጋግጣል” ብለዋል ፓርቲዎቹ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም በተለያዩ ጊዜያት የህገመንግስቱን ድንጋጌዎች የሚጥሱ አምዶችን ተቀብሎ ማፅደቁን ፓርቲዎቹ ጠቁመው፤ አሁንም ከዚህ ድርጊቱ ሳይቆጠብ በህገ መንግስቱ አንቀፆች 74፣ 75 እና 76 ሀገሪቱ አንድ ምክትል ጠ/ሚኒስትር እንደሚኖራትበግልጽ ቢቀመጥም ከህገመንግስቱ ውጪ ሌሎች ሹመቶችን ተቀብሎ ማጽደቁ ህገመንግስቱን መጣስ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
ገዢው ፓርቲና መንግስት ለተፈጠረው ኢ-ህገመንግስታዊ ድርጊት “የተሾሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሳይሆኑ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የሚሰሩ ኃላፊዎች ናቸው” በማለት የሰጠው ማስተባበያ የቃላት ጨዋታ ከመሆን አያልፍም ያለው የፓርቲዎቹ መግለጫ” ተሿሚዎቹ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ሳይሰጣቸው በሚኒስትርነት ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የየዘርፎቹ አማካሪዎች መሆን ይችሉ እንደነበር ገልጿል፡፡
ፓርቲዎቹ ህገመንግስቱን አክብረው የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው ያሏቸውን አስፈፃሚ አካሉና ፓርላማው የተፈጠረውን ህገመንግስታዊ አካሄድ በአስቸኳይ እንዲያርሙ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ በበኩሉ፤ የኢህአዴግ ስርዓት ይስተካከል እንጂ ሹመቱ ከህገመንግስት ውጭ ቢሆንም ለአገር እስከጠቀመ ድረስ እንደማይቃወም ገልጿል፡፡የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ “ኢህአዴግ የፈለገውን ሲያደርግና ሲሠራ የቆየ ቢሆንም መልካም ጐኖችን እንዳሉት መካድ የለብንም” በማለት ኢህአዴግ በተሻለ መንገድና በአብሮነት በመጓዝ ከሠራና ለአገር እድገትና ለውጥ በአንድነት ከተራመድን ከህገመንግስቱ ውጪ የሚሠሩትን አገራዊ ጥቅሞች በሙሉ ፓርቲያቸው እንደሚደግፍ አስታውቀዋል፡፡

Read 2562 times