Saturday, 08 December 2012 11:05

የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤትና ሌሎች 28 ተከሳሾች ጉዳይ ለብይን በድጋሚ ተቀጠረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

ህገመንግስቱንና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በህገወጥ መንገድ ለማፈራረስ ሙከራ ሲያደርጉ ተይዘዋል በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድና ሌሎች 28 ተከሳሾች ጉዳይ ለብይን በድጋሚ ቀጠሮ ተሰጠው፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ከትናንት በስቲያ ለብይኑ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው ተከሳሾቹ ሳይቀርቡ በዳኞች ፅ/ቤት ነበር፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች ተከሳሾች በእለቱ በችሎት በመቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጥ መስማት እንደሚገባቸው በመግለፅ ሊቀርቡ ያልቻሉበት ምክንያት እንዲገለፅላቸው ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሾች በችሎት ፊት ቀርበው ፍ/ቤቱ የሚሰጠውን ትእዛዝና ሌሎች ጉዳዮች የመስማት መብት እንዳላቸው የጠቆሙት ዳኛው፤ በቀጣይ ቀጠሮዎች ተከሳሾቹ እንዲቀርቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የእምነት ነፃነትን በመቃረን ከራሳቸው አክራሪ አስተሳሰብና አስተምህሮት ውጪ በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ እምነትና ሃይማኖት መኖር የለበትም በሚል ሃይማኖታዊ መንግሥት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱና ሲያስተባብሩ ተይዘዋል በሚል ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበባቸው እነዚሁ ተከሳሾች፤ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን የክስ ተቃውሞ ዐቃቤ ሕግ ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው ሲል ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ ተቃውሞ ላይ እንደገለፁት፤ ደንበኞቻቸው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ተይዘው መታሰራቸውንና ከሕግ አግባብ ውጪ በተገኘ ማስረጃ ተከሰው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ህጋዊነት የጐደለው አሰራር ነው ብለውታል፡፡ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የቀረበውን ክስ የማየት ስልጣን የለውም ሲሉ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት የተከሳሾች ጠበቆች፤ የክሱ ተነጣጥሎ መቅረብም በደንበኞቻቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው በመጠየቅ ተቃውሞአቸውን ህዳር 13 ቀን 2005 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ነበር፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችን ተቃውሞ የተቀበለው ፍርድ ቤቱም፤ ዐቃቤ ሕግ ለተቃውሞው ምላሽ እንዲሰጥ ለህዳር 21/2005 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ዐቃቤ ሕግ በፅሁፍ አቅርቦ ለፍ/ቤቱ በንባብ ያሰማው የተቃውሞ ምላሽ እንደሚያመለክተው፤ ፍርድ ቤቱ በወንጀል ህጉም ሆነ በፀረ ሽብርተኝንት አዋጁ መሰረት ተጠርጣሪዎቹ የተከሰሱበትን አይነት የወንጀል ክስ የማየት ስልጣን እንዳለው ገልፆ፤ በዝርዝር ለቀረቡት የክስ ተቃውሞዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ መዝገብ ከ29 ተጠርጣሪዎች አንዷ በመሆን በዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበባቸውና በኦሮሚያ ክልል አክራሪነትን አስፋፍተዋል የተባሉት የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ ክስ ከሌሎች ተከሳሾች ተነጥሎ እንዲቀርብ በጠበቃቸው አማካኝነት የቀረበውን ጥያቄ ዐቃቤ ሕግ የወንጀሉ ዓላማ አንድ መሆኑንና ክሱ ተነጥሎ ሊታይ እንደማይገባ ለፍርድ ቤቱ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
በተከሳሾች ጠበቆች የቀረበውን የክስ ተቃውሞና በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን ምላሽ የተቀበለው ፍርድ ቤቱ፤ ግራ ቀኙን መርምሮ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለህዳር 27/2005 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረትም በችሎት ላይ ተገኝተው የሚሰጠውን ብይን ለማዳመጥና ተከሳሾቹን ለማየት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፍርድ ቤቱ ቢገኙም በእለቱ ተከሳሾቹ ባለመቅረባቸው ምክንያት አብዛኛዎቹ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ተስተውለዋል፡፡
በአስራ አንድ ጠበቆቻቸው የተወከሉት ተከሳሾች፤ ወደ ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸው ምክንያትም ከፀጥታ ኃይል ማነስ ጋር በተያያዘ ምናልባት በችሎቱ አካባቢና በፍርድ ቤቱ የፀጥታ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት እንደሆነም ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመውናል፡፡ የተከሳሾቹ አስራ አንድ ጠበቆች በዳኛው ፅ/ቤት ተገኝተው ለብይን የተሰጠውን ተለዋጭ ቀጠሮ ተቀብለው ሄደዋል፡፡
ታህሳስ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠበቆችና በዐቃቤ ሕግ የቀረቡትን ጉዳዮች መርምሮ ብይን ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

Read 2471 times