Saturday, 08 December 2012 11:00

በኢትዮጵያ የህፃናት ድህነት እየተሻሻለ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

በኢትዮጵያው ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት የድህነት ሁኔታ መሻሻሎች እየታዩበት እንደሆነና ህፃናቶቹ ለዕድሜያቸው በሚመጥን ቁመትና ክብደት ላይ የመድረሳቸው ሁኔታም እየተሻሻለ መምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አራት አገራት (ኢትዮጵያ ህንድ፣ ፔሩ እና ቬይትናም) ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ያለው ያንግ ላይቭስ የተባለው ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳመለከተው የህፃናቱ ቤተሰቦች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መሻሻልን ያመለከተ ሲሆን ይህም ለህፃናቱ ዕድገት መሻሻልና በቂ የምግብ አቅርቦት ማግኘት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ በሁለት ዙሮች ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው በድህነት መሻሻሉ እንቅሰቃሴ በገጠርና በከተማ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በዚህ መሠረትም ከከተማዎች አካባቢ ይልቅ በገጠሮች አካባቢ መሻሻሎቹ ሰፋ ብለው ታይተዋል፡፡ 
በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የተደረገው ይኸው ጥናት በ20 ጥልቅ ጥናት እንዲደርግባቸው በተመረጡ ማህበረሰቦች ላይ የተደረገ ነው፡፡ የጥናት አካባቢዎቹ የተመረጡት በጐላ መልኩ ድሃ የሆኑ ማህበረሰቦችና የምግብ እጥረት ያለባቸውን ወረዳዎችና በአማካኝ ደረጃ ካሉ የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ጋር ሲነፃፀሩ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ቤተሰቦች የተገኙ ህፃናት ለእድሜያቸው የሚመጥን ቁመትና ክብደት ላይ ለመድረስ እንዳይችሉ የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ዋንኛው ችግራቸው መሆኑን ያመለከተው ይኸው ጥናት እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም (በመጀመሪያው ዙር) ጥናት የተካተቱት ህፃናት ሰውነታቸው እጅግ የጫጨና አጫጭሮች እንደነበሩ አመልክቶ በ2009 ዓ.ም (በሁለተኛው ዙር) በተደረገው ጥናት የታየው የህፃናቱ እድገት መሻሻል አበረታች ነው ሲል አመልክቷል፡፡
ይህ ሁኔታ ግን ህፃናቱ መድረስ ከሚባቸው የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ስለማያደርስ ህፃናቱ ተገቢው ቁመትና ክብደት ላይ ለመድረስ እንዲችሉ አልሚ ምግብ ከወዲሁ ማግኘት መቻላቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
ያንግ ላይቭስ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ጥናት የህፃናቱ የዕድገትና የክብደት መጠን መሻሻሎችን ማሳየቱ የቤተሰቦቻቸው የድህነት ደረጃ በመሻሻሉ መሆኑን አመላካች እንደሆነም ገልጿል፡፡

Read 2174 times