Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 15:01

በዋልያዎቹ ስጋት Featured

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በንስሮቹ ጫና፣ በመደብ ጥይቶቹ ጉራ በፈረሰኞቹ ዝምታ ሰፍኗል
መላው ኢትዮጵያዊ በከፍተኛ ጉጉትና ተስፋ በደቡብ አፍሪካ የሚስተናገደውን 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ብሔራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ባገኘው የተሳትፎ እድል በተለያዩ ምክንያቶች አጓጉል እንዳይሆን ስጋቶች ተፈጥረዋል፡፡
29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሊጀመር ስድስት ሳምንታት ቀርተዋል፡፡ በምድብ 3 ከተደለደሉ አገሮች ሶስቱ ናይጄርያ፤ ዛምቢያ እና ቡርኪናፋሶ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተጨዋቾችን በማሰባሰብ እና ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመጓዝ የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ኢትዮጵያ እስካሁን ዝግጅቷን በይፋ አልጀመረችም፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ በአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች የቡድንና የልዑካናቸውን ዝርዝር እስከ ጃንዋሪ 9 እንዲያስታውቁ ቀነ ገደብ አስቀምጧል፡፡ 
በአፍሪካ ዋንጫው እያንዳንዱ ብሄራዊ ቡድን 23 ተጨዋቾች ያለበት ቡድን እና 17 ባለሙያዎች እና ሃላፊዎች የሚካተቱበት ልዑኩን በቀነ ገደቡ እንዲያስታውቅ ያስጠነቀቀው ካፍ ይህን ተግባራዊ በማያደርጉ ተጨዋች የመቀነስ ቅጣት እንደሚያሳልፍ አሳስቧል፡፡
ከሳምንት በፊት ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ በጆሃንስበርግ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ አንዳንድ ነውጠኛ ደጋፊዎች በዛምቢያውያን ላይ ጥቃት ለመፈፀም ሞክረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የውድድሩ አዘጋጆች በፀጥታ እና ደህንነት ዙርያ አስተማማኝ ሁኔታ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥበቃ እና ቁጥጥር ለማድረግ እንደወሰኑ ታውቋል፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች የ24 ሰዓታት ልዩ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ ቡድኖቹ ወደ ስታድዬም ሲሄዱ እና ወደ ማረፊያቸው ሲመለሱ በፖሊስ ጥበቃ እንደሚታጀቡ ሲገልጽ በስታድዬሞችም በጠርሙስ እና ቆርቆሮ የሚሸጡ መጠጦች እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ዳኞች ለአስፈላጊ የውጤት ቅየራ ቁማር እና ሌሎች ጫናዎች እንዳይጋለጡ በሚልም ከብዙሃኑ ተነጥለው የውድድር ሰሞኑን እንዲያሳልፉም በአዘጋጆቹ የተያዘ እቅድ አለ፡፡ ዳኞቹ የሚያርፉበት ሆቴል ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚደረግለት የተገለፀ ሲሆን ወደ ጨዋታዎች ሲጓዙ እና ሲመለሱ በከፍተኛ የፀጥታ ኃይል በመታጀብ ነው ተብሏል፡፡
ስጋት ያጠላባቸው ዋልያዎቹ
የአፍሪካን ዋንጫ ከጀመሩ አራት አገሮች አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ በታሪኳ ለ10ኛ ጊዜ ለመሳተፍ በቅታለች፡፡
መላው ኢትዮጵያዊ በከፍተኛ ጉጉትና ተስፋ በደቡብ አፍሪካ የሚስተናገደውን 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ብሔራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ባገኘው የተሳትፎ እድል በተለያዩ ምክንያቶች አጓጉል እንዳይሆን ስጋቶች ተፈጥረዋል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሰለፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች ዝቅተኛውን የእግር ኳስ ደረጃ የያዘው የኢትዮጵየ ብሔራዊ ቡድን እና በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ባለው ያነሰ ልምድ ለአስከፊ እና አሳዛኝ ሽንፈቶች እንዳይዳርገው እየተባለም ነው፡፡ ውድድሩ ሊጀመር 6 ሳምንታት ሲቀሩት ቡድኑ ዝግጅት እና ልምምድ አለመጀመሩ ፤ ለአቋም መፈተሻ የሚረዱ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አለማድረጉ እና አለማግኘቱ፤ ተጨዋቾችን በማሰባሰብ ብሔራዊ ቡድኑን ለማዋቀር ምንም አለመሰራቱ እና ለአጠቃላይ ተግባራት የሚያስፈልገው በጀት አለመገኘቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሳሳቢ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ ነው፡፡
በብሄራዊ ቡድኑ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዙርያ ለተፈጠሩት ስጋቶች በርካታ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ከበቃ በኋላ ለዝግጅት የሚረዱትን የወዳጅነት ጨዋታዎችን አስመልክቶ ከጋናና አይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ያደርጋል የሚል ዕቅድ ተሰምቶ ነበር፡፡ አሁን ግን ብሄራዊ ቡድኑ ፌደሬሽኑ ባለበት የአቅም ውስንነት በሜዳው ሊያስተናግደው የሚችል የወዳጅነት ጨዋታ ላይኖር ይችላል እየተባለ ነው፡፡ ለወዳጅነት ጨዋታዎቹ ከሜዳው ውጭ በመጓዝ መጋጠም እንደሚኖርበት እየተገለፀ ይገኛል፡፡ ለወዳጅነት ጨዋታዎች ጥያቄ የሚቀርብላቸው አገሮች የኢትዮጵያን አየር ፀባይ ከባድነት በመጥቀስ ሃሳባቸውን እየቀየሩም አስቸግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የገንዘብ ችግር እንዳለበት ማስታወቁም ሌላው ስጋት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት በሦስት ኮሚቴዎች የተዋቀረ ፕሮግራም በመንደፍ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ አንደኛው በፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በአቶ ሳህሉ ገብረወልድ የሚመራው አስተዳደራዊና አቅርቦት ኮሚቴ ነው፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት በአቶ ተካ አስፋው የሚመራው የማርኬቲንግና የጉዞ አመቻች ኮሚቴ ሌላው ነው፡፡ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚመራው ሦስተኛው ኮሚቴ ይሆናል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ያለበትን የገንዘብ ችግር ለማስወገድ በአቶ ተካ የሚመራው ጊዜያዊ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ለስፖርት ኮሚሽን ጥያቄ አቅርቧል፡፡የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የቱንም ያህል የመንግሥት ድጐማ ቢደረግለት ችግሩን ስለማይቃለል በርካታ ቁጥር ያላቸው ኩባንያዎችና ድርጅቶች ለብሄራዊ ቡድኑ በቂ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንዲሰጡ በማግባባት መስራት ይኖርበታል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት ለማጠናከር 50 ሚሊዮን ያህል ብር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በዚህ መሠረትም አምስት የተለያዩ የገቢ ማስገኛ አማራጮች በዕቅድ መያዛቸው ተገልጿል፡፡ የገቢ ማስገኛ መንገዶቹም አጭር የስልክ መልዕክት፣ ኮንሰርቶች፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ እራት፣ ስፖንሰርሺፕ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንደ ቲሸርት፣ ኮፍያ፣ ስካርፍ የመሳሰሉትን መሸጥ ናቸው፡፡ አንድ ኩባንያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ለሁለት ዓመት ስፖንሰር ለማድረግ በያዘው ዕቅድ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ሊያገኝ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በበቂ ግዜ ዝግጅታቸውን ለማከናወን በሚያስችል አወቃቀር አለመሰባሰባቸውም ሌላው ስጋት ነው፡፡ በሴካፋ ውድድር በሚሳተፈው የተስፋ ቡድን ኣዳዲስ ተጨዋቾች ለቡድኑ ለማግኘት የተወሰኑ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡ የዋናው ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ወደክለቦቻቸው ተመልሰው ከክልል ክልል በመዘዋወር ጉልበታቸውን እና አቅማቸውን በሚያሟጥጡ የሊግ ጨዋታዎች እየተዳከሙ ናቸው፡፡ 23ቱን የቡድኑን አባላት የመምረጥ ሥራን ዋና አሰልጣኙ ሰውነት ቢሻው እንዳቀዱት ማድረግ አልቻሉም፡፡ አሰልጣኙ በተደጋጋሚ ክለቦችን ማስገደድ የሚችለውም ፌዴሬሽኑ እንደሆነ በመግለፅ በዕቅዳቸው ለመስራት ቡድኑ ቀደም ብሎ እንዲሰባሰብ ጠይቀዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው ከመጀመሩ ቢያንስ ስምንት ሳምንታት ቀደም ብሎ ቡድኑ ቢሰባሰብላቸው ጥሩ ነበር፡፡ አምስት ያህል የወዳጅነት ጨዋታዎች የማድረግ ዕቅድ የነበራቸው ቢሆንም ይህን ግን ማድረግ አልቻሉም፡፡
36ኛው የሴካፋ ታስካር ቻሌንጅ ካፕ ዩሱፍ እና ፍቅሩ
በኡጋንዳ በሚካሄደው 36ኛው የሴካፋ ታስካር ቻሌንጅ ካፕ በሚሳተፈው የተስፋ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሆነውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጨዋቾች ስብስብ ለማጠናከር ይጠቅማል፡፡
በሴካፋ በሞት ምድብ ከኡጋንዳ ከኬንያ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ተስፋ ቡድን ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ የተስፋ ቡድኑ በዓለም ዋንጫና በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች ያልተሰለፉና ለብሔራዊ ቡድኑ ሲሰለፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሆናቸው 14 ተጨዋቾችን አቅፏል፡፡
በዚሁ የተስፋ ቡድን በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በኤስያ ክለቦች የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ልምድ ያለውና ለቬትናም ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው ፍቅሩ ተፈራ፣ በስዊድን ለሚገኝ ክለብ የሚጫወተው ዩሱፍ ሳላህ እና በአሜሪካ የአላባማ ኮሌጅ ለሚገኝ ቡድን ተጨዋች የሆነው አብርሃም ካሣ ይገኛሉ፡፡
በ36ኛው የሴካፋ ታስከር ቻሌንጅ ካፕ ላይ በሞት ምድብ ባለፈው እሁድ የመጀመርያ ጨዋታውን ከደቡብ ሱዳን ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ተስፋ ብሔራዊ ቡድን 1ለዐ ያሸነፈ ሲሆን ግቧን የመብራት ኃይል ክለብ ተጨዋች የሆነው ዮናታን ከበደ አስቆጥሯታል፡፡ በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታው ባለፈው ማክሰኞ ከኡጋንዳ ጋር ተገናኝቶ ደግሞ 1ለ0 ተሸንፏል፡፡
የተስፋ ቡድኑ የምድቡን የመጨረሻ እና ወደ ሩብ ፍፃሜ የማለፍ እድሉን የሚወስንበትን ወሳኝ ፍልሚያ ትናንት ከኬንያ ጋር አድርጓል፡፡
ዩሱፍ ሳላህ
የ28 አመቱ ዩሱፍ ሳላህ አሁን በስዊድኑ ክለብ ሲሪናስካ ኤፍሲ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በአማካይ ስፍራ እና በግራ ክንፍ መስመር በመጫወት የተዋጣለት ዩሱፍ በወጣትነቱ በ3 አማተር የስዊድን ክለቦች ተጫውቷል፡፡ በአዋቂ ደረጃ መጫወት ሲጀምር ደግሞ ከ2006 እኤአ ጀምሮ በሃስልቤይ፤ በቫሱላንድ፤ ሲውዳድ ዴ ሙርሲያ በውሰት፤ ኤአይኬ ከዚያም በኋላ በውሰት ሲሪናስካ ኤፍሲን ከ2 ዓመት በፊት ተቀላቅሎ 65 ጨዋታዎች በማድረግ እና 4 ጎሎች በስሙ በማስመዝገብ የእግር ኳስ ህይወቱን አሳልፏል፡፡ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ በዝውውር ገበያው ያለው የዋጋ ተመን 275ሺ ፓውንድ የሆነው ዩሱፍ በስሪንሰካ ክለብ መጫወት ከጀመረ 9 ወራትን አሳልፏል፡፡
ፍቅሩ ተፈራ
በሶስት አህጉሮች እግር ኳስን በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመጫወት የበቃው ፍቅሩ ተፈራ ለሜሳ በሴካፋ ታስከር ቻሌንጅ ካፕ ቡድኑን በአምበልነት በመምራት እና ድንቅ ብቃት ለማሳየት ችሏል፡፡ ከ2004 እስከ 2006 እኤአ በቅዱስ ጊዮርጊስ 55 ጨዋታዎችን በማድረግ 26 ጎሎች ያገባው ፍቅሩ በፕሮፌሽናል ደረጃ ስኬታማ ልምዶችን በማግኘት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
በ2006 እኤአ ላይ ለ1 ዓመት በደቡብ አፍሪካው ኦርላንዶ ፓይሬትስ ሲጫወት 19 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጎሎች አግብቷል፡፡ ከ2007 እስከ 2009 እኤአ ደግሞ ወደ ሌላው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ በመዛወር በሁለት ዓመት ውስጥ 46 ጨዋታዎች በማድረግ 5 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ፍቅሩ ተፈራ ከዚህ በኋላ አፍሪካን በመልቀቅ ወደ አውሮፓ አቅንቶ ለቼኩ ክለብ ምላዳ ቦሌስላቭ በመፈረም በዚያው አገር ሊግ 9 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በቼኩ ክለብ አጭር ቆይታ የነበረው ፍቅሩ በ2010 እኤአ ላይ ወደ ደቡብ አፍሪካው ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ ተመለሰ፡፡ በሱፕር ስፖርት ዩናይትድ ለአንድ አመት ሲጫወት በ21 ግጥሚያዎች ተሰልፎ 4 ጎሎችን ለማግባት ችሏል፡፡ በ2011 ወደ ኤስያ የተመለሰው አጥቂው ኩፕስ በተባለው የቬይትናም ክለብ 8 ጨዋታዎች ካደረገ በኋላ ወደ ሌላው ታሃናህ ሆዋ ክለብ በመግባት 21 ጨዋታዎች አድርጎ 3 ጎሎችን በማስቆጠር በክለቡ እስከ 11 ወራት ቆይቷል፡፡ ከ2004 እኤአ ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መሰለፍ የቻለው ፍቅሩ ተፈራ 25 ጨዋታዎችን በአገሩ ማልያ አድረጎ ሰባት ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ የ26 ዓመቱ ፍቅሩ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ በዝውውር ገበያው ያለው ዋጋ ተመን እስከ 125ሺ ፓውንድ ነው፡፡
ዋንጫ የሚጠበቅባቸው አረንጓዴዎቹ ንስሮች
የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን አለበት በሚል በአገሪቱ ሚዲያዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብቷል፡፡ ዝግጅቱን ከጀመረ ግን ሁለት ሳምንት አልፏታል፡፡ ከሳምንት በፊት በአሜሪካ ቬንዝዋላን 3ለ1 አሸንፏል፡፡ በቀጣይ ከካተሎኒያ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የማድረግ እቅድ አለው፡፡ የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በሚያደርገው ዝግጅት እስከ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ በጀት እንደያዘ ይገለፃል፡፡ ከሳምንት በፊት ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫን ካሸነፈ ለእያንዳንዱ ተጨዋች 100ሺ ዶላር ቦነስ እንደሚሰጥ በአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቃል ተገብቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ሰሞኑን ለናይጀሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን አድርሰውታል በተባለው መልዕክት ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫን ድል እንዲያደርግ በሁሉም ወገን ትኩረት እንዲኖር ማሳሰባቸው ሲገለፅ አረንጓዴዎቹ ንስሮች ከደቡብ አፍሪካ ዋንጫውን ይዘው መመለስ አለባቸው በሚል ጥሪ እንዳቀረቡ ተነግሯል፡፡ በ1980 እና በ1984 እ.ኤ.አ ለሁለት ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫን ያሸነፈችው ናይጀሪያ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአገሪቱ መገናኛ ብዙሐን ለዋንጫ መጠበቋ ተጨዋቾቹንና አሰልጣኙን ከፍተኛ ጫና ውስጥ በመክተት ውጤታማነታቸውን እንዳይፈታተነውም እየተሰጋ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት ባቀረበው የቦነስ ክፍያ መሰረት በየጨዋታው 5ሺ ዶላር በአበል መልክ የሚታሰብላቸው ተጨዋቾቹ በምድባቸው የሚያደርጓቸውን 3 ጨዋታዎች ካሸነፉ በነፍስ ወከፍ 30ሺ ዶላር ቦነስ ይከፈላቸዋል፡፡ የሩብ ፍፃሜን ካለፉ 15ሺ ዶላር፤ ግማሽ ፍጻሜን ካለፉ 20ሺ ዶላር፣ ለዋንጫ ከበቁ 30ሺ ዶላር ለናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ ሊታሰብ እቅድ ተይዟል፡፡
የ50 ዓመቱ የናይጄርያ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ለብሄራዊ ቡድኑ ባለፈው 1 ዓመት ከ50 በላይ ተጨዋቾችን ከአገር ውስጥ እና ከአውሮፓ ሊጎች በመጥራት የቡድኑን ስብስብ ለማጥናት ሞክሯል፡፡
በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ናይጄርያን ወክለው የሚሰለፉ 23 ተጨዋቾችን በሙሉ በመለየት በሚቀጥለው ሁለት ሳምንት ይፋ ለማድረግ እንደሚችል ስቴፈን ኬሺ ያስታወቀ ሲሆን የአገሪቱ ሚዲያዎች የቼልሲዎቹ ቪክቶር ሞሰስ እና ጆን ኦቢ ሚኬል ፤ ግብ ጠባቂው ቪንሰንት ኢንዬማ፤ ኢኬቹኩ ኡቼ እና አምበል የነበረው ጆሴፍ ዮቦ በእርግጠኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዛቸው እንደማይቀር እየገለፁ ናቸው፡፡
ሻምፒዮናነታቸውን ለማስጠበቅ የተማመኑት የመዳብ ጥይቶቹ
የ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ዛምቢያ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ እንደምትሰለፍ አሰልጣኙ እና ተጨዋቾቹ በተደጋጋሚ እየገለፁ ናቸው፡፡
ለአፍሪካ ዋንጫው የመጨረሻ ዝግጅትን በህንድ ልታደርግ የነበረችው ዛምቢያ ባልተገለፁ ምክንያቶች ይህን ዕቅድ በመሠረዝ እዚያው አገሯ ላይ በመሠረተችው ካምፕ ለመዘጋጀት እንደወሰነች ታውቋል፡፡ የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን የወዳጅነት ጨዋታ ከሳምንት በፊት ከደቡብ አፍሪካ ጋር ጆሃንስበርግ በሚገኘው ሶከር ሲቲ ስታድዬም አድርጐ 1ለ0 አሸንፏል፡፡ በቀጣይ ከሳውዲ አረቢያ፣ ታንዛኒያ እና ከኖርዌይ ጋር የመጫወት ዕቅድም አለው፡፡
የዛምቢያው አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ቡድናቸው ምድብ 3ን በመሪነት በማጠናቀቅ ሻምፒዮናነቱን ሊያስጠብቅ እንደሚችል ተስፋ እንደሚያደርጉ ሰሞኑን ሲናገሩ ለአፍሪካ ዋንጫው በሚደርገው ዝግጅት 6 ሳምንታት በቂ ጊዜ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ስለ ዝግጅታቸው ድምፃቸው የጠፋው ፈረሰኞቹ
ቡርኪናፋሶ ስለአጠቃላይ ዝግጅቷ ብዙም ያልተዘገበላት አገር ሆናለች፡፡ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ያደረገችው ቡርኪናፋሶን ሁሉም የምድብ 3 ቡድኖች ትኩረት ቢነፍጓትም በፈረንሳይ ሊጐች ያሉ ተጨዋቾችን በማሰባሰብ በዝምታ ዝግጅቷን ቀጥላለች፡፡ ቡርኪናፋሶ ከሳምንት በፊት ደግሞ በሞሮኮ ከዲሪፖብሊክ ኮንጎ ጋር ተገናኝታ 1ለ0 ማሸነፍ ችላለች፡፡

Read 10186 times Last modified on Monday, 03 December 2012 13:45