Saturday, 01 December 2012 14:00

የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

የዛሬ ስድስት አመት የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጽህፈት ቤት በዋና ፀሀፊው ባንኪሙን የተመራ አንድ ልዩ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡
ስብሠባው ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰአት፣ የፍልስጤሙ ሀማስ ታጣቂዎች ጋዛ ውስጥ በርካታ ሮኬትና ሚሳይል ወደ ተለያዩ የእስራኤል ከተሞች በመተኮስ ሶስት እስራኤላውያን ገድሎ አምስቱን አቆሠለ፡፡ እስራኤልም ወዲያውኑ የአፀፋ እርምጃ በመውሰድ ጋዛን በሚሳይል ክፉኛ መደብደብ ጀመረች፡፡ ድብደባውም የበርካታ ፍልስጤማውያንን ህይወት ሲቀጥፍ ከፍተኛ ንብረትም አወደመ፡፡
የተሠበሠቡት የአረብ ሀገራት መሪዎችም በዚህ አዲስ በተቀሠቀሰው የፍልስጤምና የእስራኤል ግጭት ላይ ከተወያዩ በኋላ ባለ ሁለት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሠባቸውን አጠናቀቁ፡፡

ሁለቱ የአቋም መግለጫ ነጥቦች እንዲህ የሚሉ ናቸው፡፡ አንደኛ፡- በዚህ ስብሠባ ላይ የተካፈሉት ስምንቱ የአረብ ሀገራት የፍልስጤምን ሙሉ አገርነት እውን ለማድረግ ፍልስጤማውያን ለሚያደርጉት ትግል ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሳያቋርጡ ያደርጋሉ፡፡ 
ሁለተኛ አዲስ የተቀሰቀሰውን የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የፍልስጤሙ አስተዳደር ፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ፡፡ ለሚያደርጉት ጥረትና ለሚወስዱት ማናቸውም አይነት እርምጃዎች ግን በቅድሚያ የስምንቱን ድጋፍ አድራጊ ወይም ለጋሽ የአረብ ሀገራት መሪዎች ፈቃድና ስምምነት ማግኘት አለባቸው፡፡ የፍልስጤሙ መሪ መሀሙድ አባስ በተለይ ሁለተኛው ነጥብ አስከፍቷቸውና ተቃውመውት ነበር፡፡ ተቃውሟቸውን ግን ይፋ ማውጣት አልቻሉም፡፡
እንዲህ ካደረጉ ሀገሮች የሚያደርጉላቸው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሊቋረጥባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ሳይወዱ በግድ ተስማምተው ተቀበሉ፡፡
ከዚያም የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስገኘት በእስማኤል ሀንያ የሚመራውንና ጋዛን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረውን ሀማስን “የረባ ነገር ላትፈይድ ይልቅ ፍልስጤማውያንን አታስፈጃቸው፤ ትንኮሳህን አቁም” ሊሉት ቢፈልጉም መቼም ቢሆንም እንደማይሰማቸው ስለሚያውቁ ምናልባት የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁን ገስፀውም ሆነ ተለማምጠው የእራስኤልን የበቀል ዱላ ካስቆሙልኝ በሚል ለእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ለሸሞን ፔሬዝ ደብዳቤ ለመፃፍ ወሰኑና ማርቀቅ ጀመሩ፡፡
እንዲህ ብል ግብጽ ትቀየም ይሆን? እንዲህ ብዬ ብጽፍስ ሳኡዲት አረብና ኳታር በየፊናቸው ምን አይነት ትርጉም ይሠጡት ይሆን? እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር ብጨምርበት ደግሞ ኢራንና ሊባኖስ ምን ሊሉ ይችላሉ? እያሉ ሲያወጡና ሲያወርዱ በሀሳብና በጭንቀትም ሲናውዙ ረጅም ጊዜ ከፈጁ በኋላ ደብዳቤውን አዘጋጅተው ስምንቱ የአረብ ሀገራት እንዲያዩትና እንዲስማሙበት ላኩት፡፡ ፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስ የፃፉት ደብዳቤ ሙሉ ቃል እንዲህ የሚል ነበር፡፡
የዛሬ ስድስት አመት የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፅህፈት ቤት በዋና ፀሀፊው ባን ኪሙን የተመራ አንድ ልዩ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡
“የተከበሩ ሺሞን ፔሬዝ የእስራኤል ፕሬዚዳንት፤ ወንድም ከሆነው የፍልስጤም ህዝብ የወዳጅነት ሰላምታ ይድረስዎት፡፡ ይህን ደብዳቤ የምጽፍልዎ እኛ ፍልስጤማውያን ከአይሁድ ህዝቦች ጋር ያለንን ወንድማማችነት ለመግለጽና እርስዎም ይህንን የወንድማማችነት ስሜት በመረዳት እንዲሁም የእድሜ አንጋፋነትዎትን በመጠቀም የሀገርዎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ የጦር ሀይላቸውንና የታጠቀውን መሳሪያ በመተማመን፣ በከፍተኛ የጠብ አጫሪነት ስሜት በምስኪኑ የፍልስጤም ህዝብ ላይ የከፈቱትን ጦርነት ባስቸኳይ እንዲያቆሙ በቶሎ የተኩስ አቅም ስምምነት እንዲፈረም እንዲያደርጉ ለማሳሠብ ነው፡፡
የተከበሩ ፕሬዚዳንት፡- የፍልስጤምና የአይሁድ ህዝቦች የእርስ በርስ ግጭታቸውን አቁመው ከተባበሩ የቀድሞውን ታላቅነታችንን ለማስመለስና ደህንነታችንን ከሌሎች የመካከለኛ ምስራቅ አረብ ሀገራት ተጽዕኖ ለመከላከል እንችላለን፡፡ የፍልስጤምና የአይሁድ ህዝቦች ቢተባበሩ የጠቅላላው የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የመረጋጋትና የደህንነት ቁልፍ መሆን እንችላለን፡፡
በተጨማሪም የሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ግጭቶች ጦስ ለእኛ እንዳይተርፍ ለመከላከልና የሚጋጩትንም ወገኖች እዚያው በጠበላችሁ ማለት እንችላለን፡፡
የተከበሩ ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬዝ፡- በመጨረሻም ለእርስዎና ወንድም ለሆነው የአይሁድ ህዝብ ደህንነትና ረጅም እድሜ አላህ እንዲሠጣችሁ እየተመኘሁ ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ሠላም የሚያደርጉትን ጥረት ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉበት ከአደራ ጭምር አሳስብዎታለሁ፡፡
ወንድምዎ ሙሀመድ አባስ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንትና የፋታህ የፍልስጤም አርነት ድርጅት ሊቀመንበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ አባስ ደብዳቤያቸውን በስብሠባው በተወሰነው መሠረት የስምንቱን ሀገራት መሪዎች ይሁንታ እንዲያገኝ በቅድሚያ ለግብፁ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲ ካይሮ ተላከላቸው፡፡ ፕሬዚዳት ሙርሲም ደብዳቤውን ካነበቡ በኋላ፣ “የፍልስጤም ህዝብ ያለው ወዳጅነት ከእኛ ከሙስሊሞች ጋር ብቻ እንጂ በተለይ ከእነዚያ የተረገሙ ይሁዲዎች ጋር ጨርሶ ሊሆን አይችልም” በማለት ብስጭት አሉና፣ “የፍልስጤም ህዝብ የወዳጅነት ሠላምታ” ከሚለው ጀምሮ “ይህንን የወንድማማችነት ስሜት በመረዳት” እስከሚለው ድረስ ያለውን የደብዳቤውን ይዘት በያዙት ጥቁር እስክርቢቶ በደማቁ ከደለዙት በኋላ፣ የደለዙበት ምክንያት በይዘቱ ባለመደሠታቸው እንደሆነ የሚገልጽ ቁራጭ ማስታወሻ በማከል፣ ለፕሬዚዳንት ሙሀመድ አባስ መልሰው ላኩላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ አባስም ያንኑ ደብዳቤ ለኢራኑ ፕሬዚዳንት መሀመድ አህመዲን ጃድ ቴህራን ላኩላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት አህመዲነጃድም ደብዳቤውን ተቀብለው ካነበቡት በኋላ “እስራኤልን ከምድረ ገጽ ማጥፋት የኢራን ዋነኛ አላማ መሆኑን እያወቁ ሙሀመድ አባስ ከእስራኤል ጋር ወዳጅነት ለመፍጠር እንዴት ይመኛሉ?” በማለት በንዴት ያዙኝ ልቀቁኝ ካሉ በኋላ፣ ደብዳቤውን አንስተው ፕሬዚዳንት ሸሞን ፔሬዝ የእድሜ አንጋፋነታቸውን በመጠቀም “ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ የከፈቱትን ጦርነት እንዲያቆሙና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረም” የሚለውን ክፍል በእስክርቢቶአቸው ልቅልቅ አድርገው ደለዙት፡፡
ቀጠሉናም ፕሬዚዳት አባስ ለሺሞን ፔሬዝና ለእስራኤል ህዝብ መልካም ምኞታቸውን የገለፁበትን የደብዳቤውን የመጨረሻ ክፍል “ሞት ለእስራኤል! ሞት ለፔሬዝ!” እያሉ ደላለዙትና ለፕሬዚዳንት ሙሀመድ አባስ መልሰው ላኩላቸው፡፡
ፕሬዚዳንት አህመዲነጃድ በዚህ ብቻ አልተወሠኑም፡፡ ወዲያውኑ ስልክ በመደወል “ፍልስጤማውያን እስራኤልን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት አንድ ሠውና አንድ ጥይት እስኪቀር ድረስ መዋጋት እንጂ ከእስራኤል ጋር ሠላም ለመመስረት የሚያስቡ ከሆነ፣ ኢራን የምትሠጣቸውን ከፍተኛ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ታቋርጣለች” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሙሀሙድ አባስን አስፈራሩዋቸው፡፡ ፕሬዚዳንት አባስም በከፍተኛ ጭንቀት ተውጠው ሆዳቸውን ባር ባር ይለው ጀመር፡፡
በመቀጠል ደብዳቤው የደረሳቸው የኢራቁ ፕሬዚዳንት ጃላል ታላባኒ ነበሩ፡፡ ስርዝ ድልዝ የበዛውን ይህን ደብዳቤ ሲያነቡ ነገሩ ግራ ገባቸውና ማድረግ የሚፈልገውን እንዳሻው ያድርገው በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትር አልማሊኪ ሰጧቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አልማሊኪም ያልተሠረዘና ያልተደለዘውን የደብዳቤውን ክፍል ካነበቡ በኋላ፣ “በናቡ ከደነጾር ጊዜ የነበረንን የቀድሞ ታላቅነታችንን ማስመለስ የምንፈልገው እኛ ኢራቃውያን እንጂ ፍልስጤማውያንና ይሁዲዎች አይደሉም” በማለት “የፍልስጤምና የአይሁድ ህዝቦች የእርስ በርስ ግጭታቸውን አቁመው ቢተባበሩ የቀድሞውን ታላቅነታችንን ለማስመለስ…” የሚለውን አረፍተ ነገር ከደብዳቤው ላይ ደህና አድርገው ደለዙና ለፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስ ላኩላቸው፡፡ እሳቸውም ወዲያውኑ ወደ ኩዌት ላኩት፡፡ የኩዌቱ ኤሚር ሼክ ሳባህ አልአህመድ አልጃቢር አልሳባህም ደብዳቤውን ካነበቡ በኋላ፣ “ደህንነታችንን ከሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት ተጽዕኖ ለመከላከል እንችላለን” የሚለውን የደብዳቤውን ክፍል ግጥም አድርገው በሰማያዊ እስኪርቢቶ ከደለዙ በኋላ፣ ልዩ ረዳታቸውን ጠርተው መልሶ ለፕሬዚዳንት አባስ እንዲልከው ሰጡት፡፡ ወዲያውኑም “ይህን ማድረግ የምንፈልገው እኛ ኩዌታውያን እንጂ ፍልስጤማውያን አይደሉም” በማለት ለብቻቸው እያጉረመረሙ ወደ መፀዳጃ ክፍላቸው ገቡ፡፡ ፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስም ደብዳቤውን ባስቸኳይ ወደ ኳታር ዶሀ ላኩት፡፡ የኳታሩ ኤሚር ሼክ ሀማድ አቢን ከሊፋ አልታኒም፣ ድልዝ በድልዝ የሆነውን ደብዳቤ ካነበቡ በኋላ ሌሎቹ መሪዎች እንዳደረጉት እርሳቸውም የማይፈልጉትን አረፍተ ነገር ከመደለዝ ይልቅ መፃፍ የሚፈልጉትን መልእክት ለመፃፍ በመወሰን “የፍልስጤምና የአይሁድ ህዝቦች ቢተባበሩ የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የደህንነትና የመረጋጋት ቁልፍ መሆን ይችላሉ፡፡” ከሚለው አረፍተ ነገር ቀጥሎ “የፍልስጤም ህዝብ እንደ ኳታር ካለ ሀቀኛ ታማኝና ተራማጅ የሙስሊሞች ወዳጅና ደጋፊ ሀገር ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ቢፈጥሩ የአንዳንድ ያረጁ ሀገራትንና መሪዎቻቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ መቋቋምና ነፃነታቸውን በቶሎ መቀዳጀት ይችላሉ” የሚል አረፍተ ነገር ጨመሩበትና ለፕሬዚዳንት አባስ መልሰው ላኩላቸው፡፡
ፕሬዚዳንት አባስም ከኳታሩ ኤሚር የተቀበሉትን ያን ተንከራታች ደብዳቤያቸውን ለሳኡዲ አረቢያው ንጉስ አብዱላህ አብዱላዚዝ አልሳውድ ሪያድ ላኩላቸው፡፡ እርሳቸውም ያን የደተላለዘ ደብዳቤ እያዩ “አሀ! ይቺን መቸም ካለዚያ ከይሲ የኳታር ኤሚር በቀር ያ ደንባራ አባስ እንደሆን አይጽፋትም” ካሉ በኋላ “የፍልስጤምና የአይሁድ ህዝቦች ቢተባበሩ ከሚለው ጀምረው የኳታሩ ኤሚር በእጃቸው ጽፈው የጨመሩትን በሙሉ ግጥም አድርገው በቀይ ቀለም ካጠፉ በኋላ “ሼክ አልታኒ! እንግዲህ ፀጉርህን ትነጭ እንደሆነ አይሀለሁ!” በማለት ደብዳቤውን ለፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስ መልሰው ላኩላቸውና ስልክ በመደወል ከኳታሩ ኤሚር ጋር የጀመሩትን ወዳጅነት ባስቸኳይ ካላቆሙ የሚሠጡትን እርዳታ ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን ከዚች የግማሽ ሀገር የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ላይ እንዳይሰነብቱ እንደሚያደርጓቸው ጠረጴዛቸውን እየደበደቡ ዛቱባቸው፡፡
ፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስ ስልኩን እንደዘጉ ፀሀፊያቸውን ላይላ ሀምዛን ጠሩዋትና ጭንቅላታቸውን በሁለት እጆቻቸው ይዘው “ላይላ በቅርቡ የምሞት ነው ወይስ የማብድ የሚመስልሽ?” በማለት ጠየቋት፡፡
ላይላም፡- “አኡዝቢላሂ! ኧረ እንደዚህ ብለው አያስቡ አቡ አማር! ይህ የሼጣን ሴራ ነው!” በማለት ልዩ ምልክቷ በሆነው ፍልቅልቅ ፈገግታ ተውባ መልስ ከሠጠች በኋላ ወደ ቢሮዋ ተመለሰች፡፡
ፕሬዚዳንት መሀሙድ አባስ ከራስ ፀጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በሸፈናት ፈካ ያለ ቡናማ ቀለም ሠፊ ድርያ ውስጥ እንኳ ሆኖ እንደ አንዳች ነገር እየተውረገረገ የተመልካቹን ስሜት በቀላሉ የሚገዛውን ሰውነቷን ከኋላዋ እየተመለከቱ “አንቺ የታደልሽ! ሰማይ ምድሩ ከፍ ዝቅ ቢል እንደሁ ስሜት አይሰጥሽ!” አሉና ደብዳቤውን መልሳ ለሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ቤይሩት እንድትልከው አዘዟት፡፡
ደብዳቤው የደረሳቸው የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ሚሻል ሱሌይማን ከፍተው እንዳዩት መጀመሪያ የተሰማቸው ስሜት ድንጋጤ ነበር፡፡ ሳይሠረዝና ሳይደለዝ የቀረው የፕሬዚዳት መሀሙድ አባስ ደብዳቤ፤ “በተጨማሪም የሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ግጭቶች ጦስ ለእኛ እንዳይተርፍ ለመከላከልና የሚጋጩትንም ወገኖች እዚያው በጠበላችሁ ማለት እንችላለን” የሚለው ብቻ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሚሸል ሱሌይማንም ጥቂት ካሠቡ በኋላ እንዲህ አሉ፤ “የሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ግጭት ጦስ የተረፈን እኛን ሊባኖሳውያንን እንጂ ፍልስጤማውያን ምናቸው ተነካ?” እናም “የሌሎች ሀገራት የግጭት ጦስ ለእኛ እንዳይተርፍ” የምትለዋን ክፍል እርሳቸውም በጥቁር ቀለም ደልዘው ካጠፉ በኋላ ደብዳቤውን ወደ መጣበት መልሰው ላኩት፡፡
በመጨረሻ ደብዳቤው የተላከላቸው የዮርዳኖሱ ንጉስ ዳግማዊ አብዱላህም ፍልስጤሞችን ሆነ በግጭት የተጠመዱ ሌሎችንም እዚያው በጠበላችሁ ማለት ያለበት ማህሙድ አባስ ሳይሆን እኛ ዮርዳኖሳውያን ነን በማለት የቀረችውን አረፍተ ነገር ደልዘው ካጠፉ በኋላ፣ ደብዳቤውን ወደ ዌስት ባንክ መልሰው ላኩት፡፡ ፕሬዚዳት ማህሙድ አባስም ፀሀፊያቸውን ላይላን “ያልተላከለት የሀገር መሪ አለ ወይ?” በማለት ጠይቀዋት ሁሉም እንደ ደረሳቸውና ይጨመርና ይቀነስ ያሉትን አድርገው መላካቸውን አረጋገጡ፡፡
ከዚያም የመሪዎቹን አስተያየት ያን ስምንት ሀገራት ዞሮ የተመለሰውን ደብዳቤያቸውን በጥድፊያና በጉጉት ተሞልተው ከፈቱት፡፡ ወዲያውኑ ግን በድንጋጤ ክው ብለው ቀሩ፡፡
በእስራኤልና በሀማስ መካከል የተጀመረውን አውዳሚ ወታደራዊ ግጭት እንዲያስቆሙላቸውና የተኩስ አቁም ስምምነት ባፋጣኝ እንዲፈረም እንዲያደርጉላቸው በማሰብ ለእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ለሺሞን ፔሬዝ የፃፉትና እርዳታ የሚያደርጉላቸው የአረብ ሀገራት አስተያየታቸውንና ይሁንታቸውን እንዲሠጡበት የላኩት ደብዳቤ በመጨረሻ እሳቸው ጋ ሲደርስ የያዘው መልእክት እንዲህ የሚል ብቻ ነበር፡- “የተከበሩ ሺሞን ፔሬዝ የእስራኤል ፕሬዚዳንት፡- ወንድምዎ ማህሙድ አባስ፡- የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንትና የፍልስጤም አርነት ድርጅት ፋታህ ሊቀመንበር” በቃ!
“ያ አላህ! ያ አላህ!” ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ መጮህ ጀመሩ፡፡
“ያ ኡዝቢላሂ! እነኛ የተረገሙ ይሁዲዎች ይህን ሰውዬ በቃ አሳበዱት ማለት ነው?” አለች ላይላ ፍልቅልቅ እንዳለች፡፡

Read 3492 times