Saturday, 01 December 2012 13:41

“የሺ ጋብቻ” በሀገር ፍቅር

Written by  አገኘሁ አሰግድ
Rate this item
(3 votes)

ህዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም “ልዩ ድግስ” ተብሎ በተደጋጋሚ በሬዲዮ የሰማነው ዝግጅት የተከናወነበት ዕለት ነበር - “የሺ ጋብቻ” አንድ ወይም ሁለት ጥንዶችን ብቻ ሳይሆን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ጥንዶችን የያዘ የ “ሺዎች ጋብቻ” ነበር፡፡ እነሆ በዚሁ እለት የሺ ጋብቻው እየተካሄደ በነበረበት ተመሳሳይ ሰዓት ብዙ ያልተነገረለት “የሺ ጋብቻ” በሃገር ፍቅር ትያትር ቤት በመከናወን ላይ ነበር፡፡ ይሄኛው የሺ ጋብቻ ግን የተለያዩ ጥንዶችን (ሙሽሮችን) አልነበረም በአንድ ላይ ያሰባሰበው፡፡ ሙሽሮቹ ጥንዶች ሳይሆኑ የሥነፅሁፍ ቤተሰቦች ነበሩ፡፡ 
ፕሮግራሙ የተሰናዳው “በዛጐል ቤተ መፃሕፍት” አዘጋጅነት ነው፡፡ ዛጐል ቤተ መፃሕፍት፣ በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ባለቤትነት የሚመራ ሲሆን የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚታትር ቤተመፃሕፍት ነው፡፡

የዚህ ዝግጅት ዓላማ በ2004 ዓ.ም መጽሐፍት ያሳተሙ ደራሲያንንና ደራሲያትን ከአንባቢዎች ጋር ማገናኘት ነበር፡፡ ተሳካለት ይሆን? በ2004 መፃሕፍት ያሳተሙ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አንጋፋና ወጣት ደራሲያንም የዝግጅቱ ተካፋዮች ነበሩ፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ከተገኙት ደራሲያን መካከል አስፋው ዳምጤ፣ አያልነህ ሙላቱ፣ ገስጥ ተጫኔ፣ በድሉ ዋቅጅራ፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ አበባ ሽታዬ፣ ፀሐይ መላኩ፣ የምወድሽ በቀለ፣ አንዷለም አባተ፣ ሰለሞን ሞገስ…በርካታ ናቸው፡፡ ሌሎች ደራሲያንን ሳይጨምር በ2004 መፃህፍት ካሳተሙ ደራሲያን ብቻ አርባ ሁለቱ ተገኝተው ነበር - አርባ ሁለቱ! ከሁለት ሺ አራት ውጪ ያሳተሙ ደግሞ ሌሎች ብዙ…. ደራስያንም ነበሩ፡፡ 
ዝግጅቱ የተከፈተው ለደራሲያኑ ምስጋና በሚያቀርብ ጥዑም ዜማ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍም አልፎ አልፎ የምናያቸው ግጥሞች ከዜማው የተወሰዱ ናቸው፡፡
ለድኩማን ከለላ ነው፣ ለተገፉትም መጠጊያ
ለድምፅ አልባዎቹ ልሳን፣ ለተኙትም ደወል ማንቂያ
አንባቢ ነውና እሱ መጽሐፍ ተንተርሶ አዳሪ
ፍትሕ ነፃነት ናፋቂ፤ ለሰው ልጅ መብት ተቆርቋሪ
ድንቁርናን ገዳይ ጥይት፤ ጨለማውን ደምሳሽ አብሪ….
እያለ ይቀጥላል፣ የዛጐል ቤተመጽሐፍት ወጣቶች ያቀረቡት መዝሙር፡፡
በመቀጠል ንግግር ያደረገው እንዳለ ጌታ ነበር፡፡ አጭር ልቦለድና ግጥሞችም ቀርበዋል፡፡ ገጣሚና ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱም አጭር ንግግር አድርገዋል፡፡ ቤተመፃሕፍቱን ለደገፉ ሰዎች የምስጋና ምስክር ወረቀትም ተበርክቷል፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ግን ከዚህ በፊት ያልታየ ለየት ያለ ልምድ ተዋወቀበት፡፡ በ2004 መፃህፍት ያሳተሙ ደራሲያን ከመጽሐፎቻቸው አምስትም፣ አስርም ቅጂ በማምጣት ለአንባቢዎች አበረከቱ፡፡ የመጽሐፍት ጠበል ጣዲቅ እንበለው ይሆን?
አንባቢ ሆኖ ላስነበበኝ፣ በልሂቃን ሜዳ ላጫወትከኝ
የዕውቀት ትግል ላስታጠከኝ፣ እራሴን እንዳገኝ ላፋለከኝ
መፃሕፍት ከሚሉት ጓደኛ፤ ለምጄ እንድኖር ላደረከኝ
እኔም ዜማ አለኝ ለዚህ ሰው
ክብር ምስጋናዬ ይድረሰው…
…እጣ ይዞራል፡፡ እጣውን ከታዋቂ ደራሲያን አንዱ ያወጣል፡፡ ዕጣው የመጽሐፉን ርዕስ ይዟል፡፡ “አራተኛው ረድፍ ላይ” ይላል እንዳለጌታ፡፡ አራተኛው የመቀመጫ መስመር የወጣው መጽሐፍ ይታደላቸዋል ማለት ነው፡፡ “በእነ - ቢኒያም ወርቁ መስመር፣ መጨረሻው መስመር፣ በእነ አያልነህ ሙላት መስመር…” የመፃህፍት ቡፌ!!
በዕለቱ መጽሐፍ ያልደረሰው ማን ነበር? እርግጥ ነው የመጽሐፍ እደላው የተዋጣለት አልነበረም፡፡ ይህን እንከን አያልነህ ሙላቱ ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙ ሰዓት፣ “ዝግጅቱ ምሁራዊ ነው፤ የመጽሐፍ እደላው ግን ምሁራዊ አይደለም” ሲሉ ገልፀውታል፡፡ አንድም መጽሐፍ ሳይዝ የወጣ ግን አልነበረም፡፡ ስድስትና ሰባትም ይዞ የወጣ ነበር፡፡ ይህንንስ ማን አሠበው?
ተከርችሞ የቆየን በር፤ አስከፍቼው ገብቻለሁ
ፊደል ምትሃት ሆነና፤ ራሴን ወልጄው ኖራለሁ
ምስጋናዬ ላንተ ይሁን፤ በዕውቀት ባህር ላስዋኘኸኝ
መጽሐፍትን ከሚያህል ወዳጅ፤ አስተዋውቀህ ለመራኸኝ
የነፍሴን ዕድፍ እንዳፀዳ፤ በንባብ ፀበል ላጠመከኝ፡፡
እራሳችንና የእራሳችን የሆነውን እኛው ካላከበርነው፣ እኛው ካላመሰገነው ማን ያክብርልን? ማን ያመሰግንልን? ይሄም ፕሮግራም የእኛኑ ደራሲያን እኛው እናመሰግናቸው በሚል ዓላማ የተዘጋጀ ነው፡፡
አንድ ደራሲ ሲጠራ ይነሳል፣ በመጽሐፉ የሚያውቁት አንባቢዎቹ በአካልም ያውቁታል፣ በእጅ ጭብጨባ ያመሰግኑታል፡፡ አዎ…ብዙ ደራሲዎቻችንን ብዙ ጀግኖቻችንን እኮ ሲሞቱ ነው የምናውቃቸው፡፡ በተለይ ደራሲዎቻችንን የሚያሳውቁን የመገናኛ ብዙኅን (በተለይ የኤሌክትሮኒክስ) የሉም፡፡ እነሱ እራሳቸውም ስለማያውቋቸው ይሆን?
“አለማንበብ ይሞቃል” ነበር ያለው የእለቱ መድረክ መሪ፡፡ ትክክል ነው፡፡ አለማንበብ ይሞቃል፡፡ አለማንበብ ውስጥ ዕውቀት የለም፡፡ ዕውቀት በሌለበት ጥያቄ የለም፡፡ ጥያቄ በሌለበት አዕምሮ ስራ የለውም፣ በምንም አይወጠርም፡፡ እንቅልፍ ነው ያለው፡፡ አለማወቅ ውስጥ፤ ሙቀት አለ፡፡ በጊዜ ውስጥ የሚያልፍ ሳይሆን ጊዜ የሚያልፍበት ሙቀት፣ ከንቱ ምቾት! ከምንም የተገኘ፣ ምንም የሆነ ምቾት፡፡ ፕሮግራሙ ከዚህ ከንቱ ምቾት ሊያላቅቀን ነው ጥረት የጀመረው፡፡ ይበል የሚያሰኝ ሥራ ነው፡፡
በዛው በ2004 የታተሙ መፃሕፍትን በፊልም አቀናብሮ ማሳየትስ ቀላል ነገር ነው? ይሄን ያህል መጽሐፍት ታትመው ነበር ብሎ ከመንገር ባለፈ፣ እያንዳንዱን መጽሐፍት በፊልም ተቀናብሮ የቀረበ ሲሆን በፊልሙ ላይ እንዳለጌታ ስለመጽሐፉና ደራሲው መጠነኛ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
ዛጐል ቤተመፃሕፍት እስካሁን ካዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ይሄኛው ልዩ ቀለም ይኑረው እንጂ ሁሉም ድንቅ ናቸው፡፡ የህፃናት ንባብን የሚያነቃቁ ዝግጅቶችን አቅርቧል፣ የግጥም መፅሐፍ አስመርቋል (የበድሉን “እውነት ማለት የኔ ልጅ”) በየሳምንቱ ረቡዕ የቤተመፃሕፍቱ አባላት የሆኑ ፀሐፍትና የንባብ ፍቅር ያላቸው ልጆች እየተገናኙ በንባብ ላይ እንዲወያዩ፣ ጽሑፎቻቸውን ሂስ እንዲደራረጉ፣ ጥልቅ የንባብ ልምድ ያላቸው እንግዶችንም በመጋበዝ መንፈሳቸውን ለማንቃት እየተጋ ያለ ቤተ ንባብ ነው፡፡
ዛሬ የገለፅነውን ዝግጅት ደግሞ የቤተመጽሐፉን ትጋት ለመመስከር ጥሩ ማስረጃ ነው፡ እንዳለጌታ በዝግጅቱ መሃል ሲናገር ከየሺ ጋብቻ ጋር የተፈጠረው መገጣጠም፣ የአጋጣሚ መሆኑን ጠቅሶ፤ ለኛ ግን ይሄ ነው የሺ ጋብቻችን ብሏል፡፡ እውነት ብሏል፡፡ ከዚህ በላይ የሺ ጋብቻ ከየት ይመጣል? አንድ ደራሲ ስንት መፃሐፍት አንብቧል፣ ስንት ደራሲያን በውስጡ አሉ? እልፍ፣ ሺዎች? ታዲያ እኚያ ሁሉ ደራሲዎች በአንድነት ስንት ናቸው? ብዙ ሺዎች - ስለዚህ የሺዎች ጋብቻ!
ይህን መሰሉ ፕሮግራም ወደፊትም እንደሚቀጥል ተነግሮናል፡፡ እሰየው ብለናል፡፡ በመጀመርያው ፕሮግራም ላይ የታዩት እንከኖች ተቀርፈው፣ በቀጣይነት አምሮና ደምቆ እንደሚቀርብ እምነት አለን፡፡
እነሆ መሰናበቻ፤
ምስጋናዬ ላንተ ይሁን፣ ከሞትም መንገድ ላስመለስከኝ
ምስጋናዬ ላንተ ይሁን፣ የዕውቀት ችቦ ላስጨበጥከኝ
ምስጋናዬ ላንተ ይሁን፣ እራሴን ሳምጥ ላዋለድከኝ
እኔም ዜማ አለኝ ለዚህ ሰው
ክቡር ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡

Read 14663 times