Saturday, 10 September 2011 11:36

ያኔአችን እና አሁናችን

Written by  ናሆም ሰለሞን
Rate this item
(0 votes)

በቴሌቪዥን መስኮት የሚተላለፉ     የፀረ-ሙስና ማስታወቂያዎች     የታሰበላቸው አላማ አለ፤ ሙስናን
መዋጋት፡፡ ነገር ግን እንደ ተቀባዩ     ሚናቸውም የዛኑ ያህል ይቀያየራል፤ የተነሱበትን ዓላማ ሊቃረን
እስከሚችል ድረስ፤ ማለትም ጥሩ ሙሰኛ በነዚህ ማስታወቂያዎች ሊነሳሳና አዲስ ፀር ሆኖ ሊጨመር እስከሚችል ድረስ በተቀባዩ ሊተረጐሙና ሊፈፀሙም ይችላል፡፡ እነዚህ ማስታወቂያዎች መነገር የለባቸውም ብል ጥቅማቸውንም ልናጣ ነው፡፡ ስለዚህ ይዘታቸው በቅጡ ቢመረመር ዓላማቸውን ሳይስቱ ለተቀባዩ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ይህ ሁፍ ታሪካችንን በዚሁ መነጥር ለመመልከት ያለመ ነው፤ በክርክር ሳይሆን በመካፈል መንፈስ፡፡

እንደመንደርደሪያ የተጠቀምኩት ሃሳብ በያኔያችን እና በአሁናችን መሃል ያለውን ግንኙነት ለመዳሰስ ስለሚጠቅም ነው፡፡ ይህን ግንኙነት መነሻዬ ላይ በተጠቀሰው መነጥር ብናየው፣ በተቃርኖ ላይ የተመሰረተ ነው ለማለት የሚያስቸግር አይሆንም፡፡ ጉዞው በተወሰኑ አዎንታዊ እርምጃዎች ግን በብዙ የቁልቁለት ሩጫዎች፤ በጥቂት ድሎች ግን በእልፍ ሽንፈቶች የታሸ፤ ያኔ ብለን ስናወራ ውስጣችንን በሚያላሽቁ መዝገቦች፤ ሐውልቶች፣ ወዘተ የተለበጠ፤ አሁን ብለን ስንል በሚያሸማቅቁ እውነታዎች የተሞላ ነው፡፡
ተቀባዩ እንዴት ተረጐመው? እንዴትስ ተገበረው?
አሁን ስለ ኢትዮጵያ ስንጠየቅ፤ ..የሰው ልጅና የቡና መጀመሪያ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ መገኛ ወዘተ.. ልንል መዝገብ ለመግለጥ በመትጋት የዚህን ጉዞ አሉታዊ ገታዎች አውጥቶ ለመናገር ድፍረት የማጣት ሁኔታ ውስጥ ወድቀናል፡፡ በቅርብ በጊዜያችን እንደ ቀድሞው ውስጥን የሚያላሽቁ ክስተቶችን ለማምጣት በእኛም፣ ከእኛም በፊት ባለፍንበት መንገድ ምክንያት ብዙም እንደ ልብ የሚያራምድ ሁኔታ እንዳይፈጠር ሆኗል፡፡ በያኔያችን ውስጥ አዎንታዊነትን አጥብቆ የመሻት መንፈስ የመነጨው ባሁናችን ካለው የዛ አሉታዊነትን ከሚያወርሰው ልመት ለመዳን ካለን ደመነፍሳዊ ፍላጐት ነው፡፡ ታሪክ እንደ አደንዛዥ እ ከእውነታው መደበቂያ፤ ..ነበርን..ን ከ..ነን.. ማምለጫ አድርገን የቁልቁለት ግልቢያችን ላይ ተጨማሪ ማቀጣጠያ ሆኖ ከጥቅሙ ጉዳቱ መዝኖ፣ ቢቀር ባይነገረን የሚያስብል ሆኗል፡፡ ኩራት ተጭኖን ከአሁናችን ሲያቆራርጠን፣ ከ..ነበርን.. ማጥ ከትቶ ሲያላቁጠን፤ ዝም አልን፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ካለንበት ችግር ለመውጣት ለሚደረጉ ጥረቶች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ገደበን፡፡ ደግመን ለመስራት በማንችለው ሳይሆን በማንፈልጋቸው የያኔያችን ፈርጦች በማድከም አስተኛን፤ ታላቅነት የሚመለስበት ሳይሆን የሚወራበት ልዥቀት ውስጥ ገባን፡፡ እኛ ተቀባዮቹ ያኔያችንን ወደ ቅድስና በተጠጋ ክብደት፤ ከአክብሮት ባለፈ እምነት በራሳችን ላይ ጫንነው፡፡ ታሪክን ያኔ የነበሩት ወገኖች እንደሰሩት በመዘንጋት እንደተአምር ወደ ማየት የመኮላሸት ጫፍ ደረስን፡፡
በእኔ ሃሳብ የታሪክ መዝገቡ በራሱ ምንም ነው፤ አክሱም፣ ላሊበላ፣ የፋሲል ግምብ ድንጊያ ናቸው፤ አባይ ወንዝ ነው፡፡ ግን እኛ ስንይዘው አክሱም፣ ላሊበላ፣ የፋሲል ግምብ ትርጉም አላቸው፡፡ ተምሳሌት ናቸው፤ እንዴት ተሰሩ? ሲጠየቅ እና ሲታወቅ የልምድ መቅሰሚያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አባይ መስኖ የሚያለማ፣ ሃይል የሚተፋ ወንዝ ይሆናል፡፡ ከፈለግን ደግሞ አባይን የምሳሌ እና የቅኔ ምንጭ፤ አክሱም፣ ላሊበላ፣ የፋሲል ግምብን ዛሬያችንን መርሸያ መሳሪያ ብቻ ልናደርጋቸው እንችላለን፡፡ እንደ መጀመሪያው ምሳሌ የፀረ-ሙስናውን ማስታወቂያ ከፈለግን ወንጀል መማሪያ (ሙስናን ማስታወቂያ) ካሻን መከላከያ (ፀረ-ሙስናን ማስተዋወቂያ) ማድረግ እንደምንችል ሁሉ በተመሳሳይነት ለታሪክ ባለን አቀራረብ ላይ የሚታውን ያኔውን የማግዘፍ፣ ከማክበር ያለፈ መፍራት፣ ለዛሬ መቋምያ ብቻ ሆኖ ..ያኔ ይገርምሃል አንደኛ ነበርን!.. በሚል መኩሪያ ብቻ አድርጐታል፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬስ ለሚለው ጥያቄ ዝምታን አስከትሏል፡፡ታሪክ ካለፈው መማሪያ እና መንገድ ከፋች ከመሆን ይልቅ አድካሚ የእንቅልፍ ክኒን የሆነበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ታሪካችንን ለዛሬ መነሻችን ለአሁኑ ..ትልቅ እንሆናለን.. ውጥናችን መሳሪያነት ካላዋልነው፣ የተኬደውን መንገድ አንጥረን ካላየንበት፣ ውድቀቱን ካልተናገርነው፤ ሽቅብ ተኪዶ ቁልቁል የመውረዱን ምስጢር ካልተረዳን፤ ለምን? እንዴት? ካላልነው፤ የሦስት ሺህ አመት ሳይሆን የአምስት ቀን መንገድም ብዙ ሊኮራበት ይችላል፡፡ ነገር ግን በቀጣዩ ቀናት ለሚደረገው ጉዞ ልምድ ካልተቀመረበት በስተቀር አሁንም ..ይገርምሃል ከአምስት ቀን በፊት አንደኛ ነበርን.. ብለን ዛሬ ለተገኘንባት ለስድስተኛዋ ቀን መለገሚያ ካረግነው፤ ባይነገር ይሻላል ከሚያስብል ሁኔታ ከመውደቅ አያድነንም፡፡ አክሱም የማይደገም የአንድ ጊዜ ተአምር አይደለም! የአባይ ልጅ በጥማት አይሞትም! ለማለት የስልጣኔያችን ምስጢር ሊፈታ ግድ ነው!
ታላቅ ነበርን፤ በነበርም አንቀርም፤ ዳግም ታላቅ ለመሆን ከታሪክ ክፉና ደጉን፤ ኩራትና እፍረቱን፤ መርገምና ትሩፋቱን ጨምቀን ጠጥተን እንነሳ፡፡

 

Read 4549 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:37