Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 27 August 2011 13:16

ቀውስ ይኖራል፡፡ ግን የራሳችንቀውስ ነው.. ማህታማ ጋንዲ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
አንድ የጫማ ዕደሳ ሥራ ላይ የተሠማራ ጫማ ሰፊ ገበያ አልመጣ ብሎት ይቸገራል፡፡ ስለዚህ ጫማ የማደስ ሥራውን ይተውና ..መድኃኒት አዋቂ ነኝ.. ብሎ የህክምና ሥራ ላይ ይሠማራል፡፡
..ከማናቸውም በመርዝ ከሚመጡ በሽታዎች መከላከያ የሚሆኑ ልዩ  መድኃኒቶች በቅናሽ ዋጋ የሚሰጥ ምርጥ መድኃኒተኛ.. የሚል ሁፍ ይለጥፋል፡፡ (በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል ከእሱ ይሆን የመጣው?) ሰው እንደ ጉድ ይጎርፍለት ጀመር፡፡ እሱም በየዓይነቱ ቅጠላ ቅጠል እያመጣ እየቀመመ፤
..አንተ ይሄንን ከኑግ ጋር በማንኪያ ጠዋትና ማታ ውሰድ.. ይላል፡፡ ታማሚው ይከፍላል፡፡ አመስግኖ ይሄዳል፡፡
ሌላዋ:- ትመጣለች

..አንቺ ይሄንን ከሱፍ ጋር አድርገሽ በየሶስት ቀን ውሰጂ.. ይላታል፡፡ አመስግና ከፍላ ትሄዳለች፡፡
እንዲህ እንዳለ ያ ጫማ ሰፊ ዋና መድኃኒት አዋቂ ተብሎ ዝናው እየገነነ፣ እንደወጥ-ሠሪ ..እጁ አይለወጥም፣ እጁ መድኃኒት ነው፣ እሱ የዳበሰው ሰው ወዲያው ብድግ ነው!.. እየተባለ ጥሩ አድርጎ ራሱን ሸጠ፡፡ አንደበተ-ርቱዕ ስለሆነም አፉ ይጣፍጣል - ሰው ያለውን ሁሉ ይሰማዋል፡፡ ባንድ ጊዜ ዝና አገኘ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በጣም ታመመና እቤት አልጋ ላይ ዋለ፡፡ የአገሩ ንጉሥም፤ ባለሟሎቹን  ጠርቶ
..የዚህን መድኃኒተኛ ዕውነተኛ ችሎታ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ሂዱና ያንን እሱ የመርዝ መከላከያ እያለ የሚሰጠውን መድኃኒት ተቀብላችሁ ከመርዝ ጋር ቀላቅለን ልናጠጣህ ነው ብላችሁ ንገሩትና ውሃ ብቻ ጨምራችሁ ጠጣ በሉት፡፡ ከዚያ ምን እንደሚያደርግ መጥታችሁ ንገሩኝ.. አላቸው፡፡
ባለሟሎቹም በንጉሡ በታዘዙት መሠረት ከመድኃኒቱ ጋር መርዝ ሊያጠጡት እንደመጡ ነገሩት፡፡
መድኃኒተኛው በጣም ደነገጠ፡፡ መርዝ ሊያጠጡት መሆኑን በማሰብም ክፉኛ ተጨነቀ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ሲል ዕውነቱን በመናገር ተናዘዘ
..ጌቶቼ፤ እኔ ምንም ዓይነት የመድኃኒተኝነት ችሎታ የለኝም፡፡ የጫማ ዕደሳ ገበያዬ ሲቀዘቅዝብኝና የኑሮ መላው ሲጠፋብኝ በልቼ የማድርበት አንድ ዘዴ ለመፍጠር ተገደድኩ፡፡ መድኃኒተኛ ሆንኩ፡፡ ህዝቡ ተቀበለኝ፡፡ ቀጠልኩበት.. አለ፡፡
ባለሟሎቹ መድኃኒተኛው ያለውን ወስደው ለንጉሡ ተናገሩ፡፡ ንጉሡ አገሬውን ሰብስቦ፤
..የአገሬው ሰዎች ሆይ! ከእናንተ በላይ ስህተት ላይ የወደቀ ማን አለ? ለዚህ ጫማ ሰፊ አንዳችሁም ጫማችሁን እንዲያድስ አልሰጣችሁም፡፡ የመርዝ ማርከሻ አድርግልን ብላችሁ ግን ነብሳችሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፡፡ ከእንግዲህ ግን ባለሙያ ለዩ፡፡ በስሜት እየተገፋችሁ በወረት አትነዱ.. ብሎ አጥብቆ አሳሰባቸው፡፡
***
አላዋቂ እጅ መውደቅ እርግማን ነው፡፡ ነብሴ በእጅህ ናት ብሎ የአላዋቂ ተገዢ መሆን የከፋ መርገምት ነው፡፡ አንዱ ስላረገው ብቻ ሌላው የሚከተልበት፣ እንደ መንጋ ተከታትሎ ከሚነዱበት ሥርዓት (Herdism) ይሰውር፡፡ ቆም ብሎ የምሄድበት መንገድ ትክክል ነወይ? ከተለመደው መንገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አጥቼ ነወይ? አኪሜስ በእርግጥ መርዙን እያረከሰልኝ ነወይ? ጠንቋይ ለራሱ አያውቅ እንደሚባለው ቢሆንስ? ጫማ ሰፊው ሙያ ወይ ሥራውን ለውጦ አኪም ነኝ ያለው መደበኛ ሙያው አንሶት ነውን? ያገሬው ህዝብ ሙያውን ስላላወቀለት ነውን? ጫማ የሚያሳድስበት ገንዘብ ስላጣ ነውን? አሮጌ ማሳደስ በቃኝ ብሎ ነው?
ለመንገኝነት አስተሳሰብ ወይም ለወረተኝነት አካሄድ ወይም እንደ አዲስ ፕሮጀክት፣  ዕቅድ፣ መመሪያ፣ ሲወጣ እንደፋሽን መከተልና ሳይመረምሩ መቀበል፣ ከተለመደ ቆይቷል፡፡ ይህ የሚከሰተው ከአለማወቅ ወይም ግንዛቤ ከማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ጌታዬ                                                                                                                                                            ያሉት ሁሉ ልክ ነው ከሚል የሎሌያዊነት አመለካከት (Servitude) ሊሆን ይችላል፡፡ ጎረቤቴ ካደረገው ልክ ቢሆን ነው ብሎ ከማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ሆነ ብሎ ስህተትም ቢሆን ልከተለውና ገደል ሲገባ ልየው ከሚል እኩይ ሀሳብም ሊሆን ይችላል፡፡  
እነዚህ አስተሳሰቦች በአገርም፣ በአህጉርም፣ በሉልም ደረጃ የሚሠሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ግን በዚህ በመጠቀም ዝናን የሚያካብቱ ከአገሬው በላይ ያሉ ንጉሦች፣ መሪዎች፣ ኃላፊዎችና አለቆች ይኖራሉ፡፡ የአገሬው መራብ፣ መቸገር፣ በኑሮ መማቀቅ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ዝና ወዳዴ የሚባሉ ሰዎች ህልማቸው ሁሉ በዝና የተሞላ ነው፡፡ ሮማዊውን ሴናተር ሲሴሮን ጠቅሶ ሞንታኝ የተባለ ፀሐፊ እንደ¸lN-
..ዝናን የሚቃወሙ ሰዎች እንኳን ቢሆኑ፣ ስለአቋማቸው በሚጽፉት መጽሐፍ ላይ ስማቸው እንዲኖር ይፈልጋሉ - ዝናን የሚቃወሙ ዝነኞች ይሆናሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው የገበያ ጉዳይ ነው፡፡ ዋና ዋና ኤኮኖሚያዊ ጥቅሙን ለማንም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ዝናን ግን ቢሞቱ አያጋሩም፡፡..
ከዓለም ጋር የምንሟገተው፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አቋም የምንወስደው፣ ጐረቤት አገር የምንረዳው፣ ለዝና ሳይሆን ለሀገራችን ጥቅም መሆን አለበት፡፡ አገራችን በዝነኝነቱ ስትታወቅ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ዕድገቷና የህዝቧ አኗኗር ግን ከዚያ ጋር አልሄደላትም፡፡ አለመታደል ነው፡፡ አንድ ወጣት ቻይናዊ፤ ምዕራባውያን አንድን መንግሥት ስለመደገፍ የሚሰብኩትን ስብከት እንዲህ ሲል ይሞግታል፤
..ሱዳን ውስጥ ያለ አምባገነን የምንደግፈው ነዳጁን ለማግኘት እንዲቻል ነው ትሉናላችሁ፤ የሜዲቫል ንጉሣዊ ሥርዓት ያለውን የሳውዲ አረቢያ መንግሥትስ የምትደግፉት ስለምን ነው?..
ዛሬ ብቅ ብቅ እያሉ የመጡት የእስያና የላቲን አገሮች ምዕራቡ ዓለም ውስጥ ይግቡ እንጂ በራሳቸው መንገድ ሥርዓቱን እየቃኙ ነው፡፡ የራስ መተማመን መልዕክቱም ለኛም ነው፡፡ ..እኛ አሜሪካኖች፤ ሌሎችን ለውጥን አትፍሩ፤ ከእኛ ተማሩ ስንል ቆይተን. . . አሁን ስናከብራቸው የነበርናቸውን ነጻ ገበያን፣ ንግድን፣ ካገር አገር መንቀሳቀስን ነፃነት እና ቴክኖሎጂያዊ ለውጥን መፍራትና መጠራጠር ጀመርን  እያሉ ነው (ፋሪድ ዘካርያ).. አለም እየተከፈተ አሜሪካን እየተዘጋች ነው - በራሷ ጨዋታ፡፡ ከሀገራችን ጋር በአንድ ይቆጠሩ የነበሩት የእስያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ዛሬ የት ናቸው? እኛ የት ነን? የኋላ ቀርነትና የድህነትን መርዝ ማርከሻ ስንፈልግ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በጫማ ሰፊ አሮጌ እደሳና በመድኃኒት አዋቂ ቤተ-ሙከራ መሃል ሆነን ብዙ ዳክረናል፡፡ መፈክር በማስነገር በፖለቲካ መር አካሄድ ብዙ ፎክረናል፡፡ እጃችን አፈር ጨብጦ ዕድገት ለማምጣት ግን ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ሙስናችን ዛሬም ለከት አጥቷል፡፡ ንግዳችን በራሳችን ሻጥርም በሌሎች ሸርም ውሉ በማይታወቅና ግቡ በማይነበይ ኤኮኖሚያዊ ዘመቻ ውስጥ ይዳክራል፡፡ በስታቲስቲካዊ አሀዝና በስትራቴጂ ብዛት መልካም ዝና አለን፡፡ ዝና ግን፤ አንድ ያልታወቀ ገጣሚ፤ ..ዝና.. በሚል G_Ñ-
..ዝናኮ እንደንብ ነው
ዜማ አለው
መውጊያ አለው
ቀን የጨለመ እለት
በሮ እሚጠፋበት
ጉድ ነው! ክንፍም አለው!!..
ቀሪው አገር ነው፡፡ አገሬው ነው፡፡ ዝና አላፊ ጠፊ ነው እንደማለት ነው፡፡
ገበያ ካጣ ጫማ ሰፊና አለሙያው ከሚያክመን አዋቂ ይሰውረን እንጂ አንድ ቀን ራስን መቻል አይቀርም፡፡ ራስን በራስ ማከምን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ራስ ከመግዛት የተሻለ ነገር የለም፡፡
በጥንቶቹ ቀናት የእንግሊዝ የመጨረሻው ጌታ ለታላቁ የህንድ መሪ ለማህተመ ጋንዲ ..እኛ ህንድን ለቀን ትተናችሁ ከወጣን ቀውስ ይፈጠራል.. ይለዋል፡፡ ጋንዲም ..አዎ ቀውስ ይኖራል ግን የራሳችን ቀውስ ነው.. አለው፡፡ በሌሎች እጅ ወድቆ ነጻ ናችሁ ከመባል የራስን ቀውስ ማስታመም ይሻላል እንደማለት ነው፡፡ ይህን በልቦናችን ያኑርልን፡፡

 

Read 7210 times Last modified on Saturday, 27 August 2011 13:25

Latest from