Saturday, 13 August 2011 09:23

ሞሎች እና ብርሐን

Written by  ሌሊሣ
Rate this item
(0 votes)

. . .ምነካው ክፋትን፤ ምነው ሾካካ ሆነ እኩይነት ልጄ?. . . ዘንድሮ የምናየው ክፋት ወይም እኩይነት እንደ ጥንቱ አጥንት ያለው ቆራጥ አይደለም፡፡ እየሳመ የሚናከስ ሰይጣን መጥቶብናል፡፡ ድሮ የምናውቀው ክፋት ክ-ፍ-ት ያለ ነበር፤ በጐ ደግሞ ነጭ በጐ ነበር፡፡ ድንበር አይቀላቅሉም፡፡ ራሱ ከራሱ ጋር አይጣረዝም፡፡ ዘንድሮ እኩይ አላማ የለውም፡፡ ቀፈቱን በነዋይ ከመሙላት በስተቀር፡፡ ጭራ መቁላት እና ሆድ መሙላት እንዲቻል ማንኛውንም ዓይነት ቲያትር መሥራት፡፡ እኩይ፤ ትያትረኛ የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ምናልባት ይሄ አዲሱ የጀርባ አጥንት የሌለው ሾካካ እኩይ ..ክፋት ለክፋትነቱ.. ተብሎ የሚጠራው ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ..ጥበብ ለጥበብነቱ.. እንደሚባለው አይነት መሆኑ ነው፡፡ . . .መብላት ከሆነ ዋናው አላማው፤ በልቶ ሲጠግብ፤ ሌላውን ማስበላት መቻል አለበት፡፡

ዓላማው መብላት ስለሆነ አለማስበላት ዓላማው ሊሆን አይችልም፡፡ የሱ መብላት ከሌላው ሰው አለመብላት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እየበሉ. . . የሚበላ ሞልቶ ተትረፍርፎ በተከመረበት አላስበላም ማለት ክፋት ነው፡፡ ግን ለየት ያለ የክፋት አይነትም ነው፡፡ ክፋት ለራሱ የሚባለው ዓይነቱ፡፡ ክፋት፤ ለአላማ ማስፈሚያነት ሳይሆን አላማም ግብም የሌለው እኩይነት፡፡
የአስፋልት መንገድ መኪና ያላቸውን ብቻ የሚጠቅም፣ የሚያፈጥን፣ የሚያሰለጥን ከሆነ፤ እኔ በእግሬ የምሄደውን ምንም አልጠቀመኝም ማለት ነው፡፡ ባለመኪናዎቹን ብቻ የሚጠቅም መንገድ እኔ ከኪሴ አውጥቼ እንድሠራው የምጠየቅ ከሆነ ግን ክፋት ነው፡፡ ግን ክፋት ነው እንጂ ገና ..ክፋት ለክፋትነቱ.. ንፁህ evil ደረጃ አልደረሰም፡፡ . . . ለባለመኪኖቹ የተሠራው አስፋልት መንገድ፤ የተወሰኑትን የሚያንፈላስስ ሆኖ እኔን ግን ለመኪና አደጋ የሚዳርግ ከሆነ፤ ያኔ ንፁህ እኩይ ደረጃ ደርሷል፡፡ . . .መንገዱ የተሠራው አንዱን ለማሳደጊያ፣ አንዱን ለማጅራት መቺ ለመዳረጊያ ከሆነ. . . መንገዱ እንደ ድሮው ኮረኮንች እና ጭቃማ እንደሆነ ይቀጥልልኝ (እኔ ለራስ ስል) መንገድ መሠራቱ በመንገዱ ለሚያልፉት ወዳሹበት መድረሻ፣ በመንገዱ ውስጥ ለሚኖሩት ደግሞ መንገዱን ተከትሎ በተከፈቱ መሸታ ቤቶች ደንበኛ ለመሆኛ፣ ሥራ ያጣው ኮረዳ አስፋልቱ ሴተኛ አዳሪ አድርጐ እንዲቀጥራቸው መሆኑ ነው እኩይ፡፡ እየሳሙ መንከስ ያልኩት ይሄንን ነው፡፡ ለማልማት ብሎ ማጥፋት፡፡ ነጻነት የሰጡ መስሏቸው ባሪያ ማድረግ፡፡ ቁንጥጫ በጥሩ ክፋት ባለሙያ ከተመዘለገ ህመሙ ቆይቶ ነው የሚሰማው፡፡ ህመሙ መሰማት እና ማንገብገብ የሚጀምረው ከበለዘ በኋላ ቆይቶ ነው፡፡ መቆንጠጥ ለማስተማር ከሆነ ነው እንጂ ለመጉዳት ከሆነማ ልጁንም መርዝ ሰጥቶ መግደል ይሻላል፡፡ እንዳይሞት እንዳይድን የሚያደርግ መድኃኒት ንፁህ እኩይ ነው፡፡. . . የዋህ ከሞተ እኩይ በማን ይጫወታል? የዋህ ምን ይሆናል?!. . . የክፋት መጫወቻ ይሆናል፡፡
የፎቆቹን መብዛት ያየ የሀገሩን ማደግ ያየ እንደሚመስለው ምንም አያጠራጥርም፡፡ ወደ ፎቆቹ የሚወጡት ፎቅ የሚመለከታቸው ናቸው፡፡ ፎቁን ቆመው በዓይን የሚመለከቱ እንጂ የማይመለከታቸው ግን በብዛት አሉ፡፡ በአንድ ሀገር ላይ በአንድ ዓይነት ቋንቋ እና ትውልድ የሚገናኝ ህዝብ መሀል ሁለት ዓይነት ዜጋ ይፈጠራል፡፡ የውስጥ እና የውጭ ዜጋ፡፡ የሞተ እና የኖረ. . . በአንድ ከተማ ላይ አየር እየተጋራ ይጨናነቃል፡፡
. . . ደቀ ሰይጣኖቹ ናቸው የሚንቀሳቀሱት፤ ሲበሉም ተደብቀው፣ ሲያጠፉም በስውር. . . በግልጽ የሚታየው ትያትሩ ብቻ ነው፡፡
ውድ ማለት የቱ ነው? እኩይ ወይም እርኩስ ውድ አይደለም. . .  ውድ ማለት ከራሱ ዋጋ ባሻገር በሌሎች ዋጋዎች እና እሴቶች ላይ በአጠቃላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ማለት ነው፡፡ እኔ የለበስኩት ልብስ እኔን ከብርድ ጠብቆ ከማዘነጥ ባሻገር እኔን ያልሆኑት ሌሎቹ ልብሱን ሲመለከቱ፡- መልካም ስሜት የሚፈጥርባቸው፣ የማይረብሻቸው፣ ለሌላ ዓይነት ስሜት (ወሲባዊም ሆነ አልሆነ) የማይገፋፋቸው፤ ቅናት እና መመቅኘት የማይፈጥርባቸው ሲሆን ብቻ ነው ልብሱን ውድ ብዬ ልጠራው የምችለው፡፡ በለባሹ እና ሳይለብስ የተለበሰውን በሚመለከተው መሀል ያለ በጐ ግንኙነት እስካለ ድረስ እኩይ የሚባለው ነገር አይኖርም፡፡
እነዚህን ፎቆች እና መንገዶች በልብሱ ረገድ አነጻጽረን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡ ልበሱን እንደ ፎቅ የለበሰችው ከተማዋ ብትሆንም ከተማዋ ለበሰች ማለት ግን ከተማዋ ውስጥ የሚኖረው ነዋሪ በሙሉ ከእርቃንነት ስሜት ተላቀቀ ማለት ግን አይደለም፡፡ ከተማዋ ስትለብስ የከተማዋ ነዋሪ በሙሉ የመልበስ እና ከእርቃንነት የመገላገል መንፈስ ቢፈጥርበት ኖሮ የልብሱ (የፎቆቹ እና የመንገዶቹ) ዋጋ ውድ በሆነ ነበር፡፡ በሆነ ነበር ግን አሁን እንደዛ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች ናቸው እንጂ የለበሱት ከተማዋ አሁንም እርቃኗን ናት፡፡ ሁሉንም በእኩል ደረጃ የሚያግባባ አልያም የሚያስተሳስር ዋጋ እስካልተገኘ ድረስ ዋጋ ራሱ የእኩይ ምንጭ ነው፡፡ እኩይ ለእኩይነቱ evil for evils sake የሚፈጠረውም ሲጀመር በዋጋ ምክንያት ነው፡፡ የራስን ዋጋ ብቻ ከፍ በማድረግ እና ከራስ ውጭ ያሉትን የሌሎቹን በማሳነስ ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡
በፊት ከማምንበት ..ሁሉም ለራሱ.. ከሚለው አስተሳሰብ የምህዋር ስርዓቴ እየወጣሁ መሰለኝ፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ ነው፡፡ እኔ ለራሴ ሉአላዊ ሀገር ብሆንም እኔ ተመልካቹን ከራሳቸው አገር ግዛት ሆነው የሚመለከቱኝ ሌሎች. . . ..እነሱዎች.. መኖራቸውን ልክድ አልችልም፡፡ ከካድኩ ደግሞ ክህደቴ የቂል/ዝግ እውቀት ውስጥ ይጥለኛል፡፡ ይህ ውድቀትን ለመኮነን ነው ከመነሻውም የዚህ ጽሑፍ አላማ፡፡ የራስ ብቻ የሆነ ዝግ እውነት እኩይ ነው፡፡ ..እኩይ ለእኩይነቱም.. ትርጉሙ በአጭሩ ይህ የዝግ ዘገምተኛ እውቀት ነው፡፡ ያለውን ነገር እንደሌለ አድርጐ መመልከቻ፣ ማዳመጫ፣ ማሸተቻ እና መቅመሻን መድፈን ቂልነት ነው፡፡ ለቂሉም. . . ለቅሉም አይበጀውም፡፡ ሁለቱም ወድቀው በስተመጨረሻ ይሰበራሉ፡፡ የሚልተን (paradise lost) የእኩይ አይነቶችን እንደ ክህነታቸው ከፋፍሎ በሚከተለው መሠረት ይደረድራቸዋል፡- ዋናው ሰይጣን ሉሲፈር እኩይ የሆነበትን ምክንያት አበጥርጥሮ ይረዳል፡፡ እኩይ ከጥሩው ጋር ያለውን መሠረታዊ ግጭት ብቻ ሳይሆን ከእኩይ ይልቅ መልካሙ የበለጠ ኃይል እና አሸናፊነት እንደሚቀዳጅም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ . . .ከዚህ በመቀጠል ቤልዘባብ አለ፤ የሊቀ ሰይጣኑ አፈ ቀላጤ (mouthpiece). . . አፈ አለቃ እንደማለት፡፡ . . ...ሞሎች..ን (moloch) የምናገኘው በሦስተኛ እርከን ላይ ነው፡፡ ..ሞሎች..፤ የክፋት ለክፋትነቱ ተምሳሌት ነው (a type of evil uncontrolled and unreasonable)
ቢላየል የሚባለው ከዚህ እርከን ወረድ ብሎ የሚገኘው ረቀቅ ያለው የእኩይ ዓይነት ነው ውሸትን እውነት አስመስሎ አግባብቶ የሚያቀርበው፡፡ ከቢላየል ቀጥሎ ማሞን (Mammon) አለ፡፡ ማሞን ቁስ አካላዊ ነው፤ ብልጭልጭ ነገሮችን በድሮው ዘመንም የሚወደው ነው፡፡ በድሮውም የብርሃን ባለሟልነት ዘመኑ፤ ወደ ዋናው ብርሃን ቀና ብሎ ከመመልከት ይልቅ፤ ወለሉ የተሠራበትን የወርቅ ቅብ አጐንብሶ በመቁጠር ጊዜውን ያሳልፍ ነበር፡፡ . . .አደረጃጀታቸው ከላይ እንደጠቀስኩት ነው፡፡ የጥሩውን (good) ከፈለጋችሁ ደግሞ ሚልተን የሚገልው ..ብርሐን.. ብሎ ነው፡፡ ከብርሐን በተቃራኒ ያሉት በሙሉ የጨለማ ደረጃና ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከተዘረዘሩት መሀል ..ሞሎች.. እኩይ ስለእኩይነቱ ያልኩትን ጽንሰ-ሐሳብ በገ-ባህሪ ተላብሶ የሚገኝ ይመስላል፡፡ ንፁህ እርኩስ ነው፡፡ ዋናው መገልገያው ግን ዝቅተኛው እኩይ ነው፡፡ የብልጭልጭ ነገሮች ፍቅር ያለበት - ማሞን፡፡ ሁለቱ ሲቀላቀሉ ..ብርቅርቅ ለብርቅርቅነቱ.. የሚለውን የሰው የገንዘብ እና የወርቅ ፍቅር ይሰጣሉ፡፡እነዚህ ፎቆች ለብርቅርቅ ነገር ፍቅር ተሠርተው የሚመለኩ ከሆነ፤ የእኔን ሀገር እና የሌሎችን የግል ማንነት የሚያጣምር ጥቅም ማግኘት የማይታሰብ ይሆናል፡፡ ለሌላ ሰው ጥቅም እኔ አልገብርም ብዬ ማመ በስተመጨረሻ ደግሞ አይቀርም፡፡ቤተ መጻሕፍት ለሁላችንም እንደ ጥሩ ዋጋ ያለው ነገር ነው የሚታየው፡፡ ታዲያ ግን፡- ቤተ መጽሐፍቱ ውስጥ ያሉት እውቀቶች እና ቁልፎች ለቤተ መጽሐፍት ቤቱ ባለቤቶች እና አስተዳዳሪዎች ብቻ የተፈቀዱ ከሆኑ. . . የቤተ መጻሕፍት ጥቅም ለኔ ምንድነው? ብዬ መጠየቄ አይቀርም፡፡¥m²zN ከእኔ ጋር ከሆነች፡- ቤተ መጻሕፍቱ የመገልገያ ፍቃድ ባላገኝም፤ ችግሩ እንዳላገኝ ካደረጉኝ ሰዎች እንጂ፤ ቤተ መጻሕፍት በመሠረቱ ጥሩ ነገር መሆኑን ግን ማገናዘብ ይቻለኛል፡፡ ቤተ መጻሕፍት እና መጽሐፍቶች በመልካም ሰው ሲያዙ እና ለማንም ሰው ሲፈቀዱ ጥሩ መሆናቸውን ማወቅ አይሳነኝም፡፡ . . .ሳይሳነኝም ግን ቤተ መጽሐፍት እኔ ልጠቀምባቸው ስላልቻልኩ ማንም መቻል የለበትም፤ ያልኩኝለት፤ ንፁህ እኩይ ሆኛለሁ፡፡ ..እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል.. ያለችው አህያ የዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ እኔ እስከኖርኩ ሌላው ይሙት፤ ከማለት ጋር ተቃራኒ ቢመስልም አስተያየቱ፤ ግን በቅርበት ከተመለከትናቸው ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ ሁለቱም እኩይ ለአኩይነቱ ናቸው፡፡ ግለሰብነት እውነት ነው፤ ግን ግለሰብነት ብቻውን አይደለም፡፡ ከማህበረሰባዊነት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ አንዱ ቢሞት፤ ለሞተው ሰውዬ ሁሉም ነገር አብሮት እንደሚሞት ቢታወቅም. . . ለሚኖሩት ግን የሱ መሞት እነሱን እንደ¥YgD§cW እሱ እና እነሱ በአንድነት ያውቃሉ፡፡ ልዩነታቸው ከምንም ነገር በፊት መሠረታዊ ቢሆንም፤ አንድነታቸው ግን አንደኛው በሚያደርገው ተግባር ጊዜ እና ቦታ ሌሎቹንም ስለሚያስተሳስር እሱ እነሱን በጭራሽ አይመለከቱኝም ሊል አይቻለውም፡፡የነጻነት (ፍትህ) ጥያቄ በሰው ልጅ አስተዳደር ላይ የሚነሳው የተሻለ ቦታ ላይ (ወይም ሰርዶ ላይ) የተቀመጠው (እሱ) እንደሚግጠው ወይም ለራሱ ምቾትን እንደሚፈልገው ሌሎችም ፍላጐት እንዳላቸው መዘንጋቱ ላይ ነው፡፡ ለእሱ ምቾት ማግኘት ሳይሆን ለራሳቸው ምቾት ማጣት ምክንያቱ ..አንተ ነህ.. ብለው ይከስሱታል፡፡. . . ከከሰሱት በኋላ ደግሞ አይቀርም፤ ይከሰክሱታል፡፡ እኩይ ለእኩይነቱ እንዳለ ሁሉ ማካካሻው ወይም ማርከሻው ..ጥሩ ለጥሩነቱ.. መኖሩ አይቀርም፡፡ (መኖር አለበት!. . . በከፍተኛ ሥልጣን ወይንም የብቃት ደረጃ ላይ ተሰይሞ አይተን ባናውቅም!)፡፡ ጥሩን ማድረግ፡- ጥቅም ወይም ትርፍ ስላለው. . . ወይም መንግሥተ ተተኪ አልያም መንግስተ ሰማይ መግቢያ ትኬት ብቻ ስለሚሆን ሳይሆን. . . ጥሩ ማድረግ መደረግ ብቻ ሳይሆን፤ ጥሩ ለሰው ልጅ እውነተኛ ልኩ በመጠኑ የተሠራለት ብቸኛ እውነቱ እና ከፍተኛ ማንነቱ ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ ጥሩ ብርሃን ነው፤ ወደ ላይ መውጣት ነው፡፡ እኩይ በተለያየ ደረጃ እየዘቀጠ ወደ ታች መውረድ እንደሆነው፡፡ ጥሩ የሆነ የሰው ልጅ ስለ እምነትም ሆነ ከሰው የበለጠ የፈጣሪ ግዛት ማውራት የለበትም፡፡ ሰውን ራሱን ፈጣሪ አድርጓል፡፡ ስለ ጥሩነት ሐልዮት ከመስበክ ጥሩ ማድረጉ ወይም መሆኑ ለሰው የመጨረሻው የእድገት ደረጃው ነው፡፡ ጥሩ ማድረጉ ወይም መሞከሩ ደግሞ የሰውን የመጨረሻ ልክ ለመሙላት የሚያደርገው ሙከራ ይሆንለታል፡፡

 

Read 3506 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 09:25