Saturday, 13 August 2011 09:19

ከየት ወዴት...?

Written by  አንዱአለም ቶሎሳ
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ተማሪባለፈው ሳምንት በዕውቀቱ ስዩም፣ ..ፈሪሀ እግዚአብሔር ወይስ ዲሞክራሲ.. በሚል
ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የጻፈው ጽሑፍ የዚህ አጭር አስተያየት የመነሻ     ሀሳብ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሐፊው ምልከታ በሳል ስለነበር ላመሰግነው እወዳለሁ - ብዙ ነገሮችን እንዳስተውል ስላስቻለኝ፡፡
እኔ የምለው፣ ሰሞኑን በዓለማዊ የህትመት ሚዲያዎች የፊት ገፆች ላይ ለምንድን ነው የዲያቆናት ጉዳይ የበዛው እውነት ጉዳዩ ለዚህ የሚያበቃ ሆኖ ነው? ወይስ በሀገሪቱ ውስጥ ለህትመት ሚዲያ የፊት ገጽነት የሚበቁ ርዕሰ ጉዳዮች ስለጠፉ ነው? በእኔ በኩል ግን፣ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ከዲያቆናት አለመግባባት እጅግ በላቀ መልኩ ሚዛን ሊደፉ የሚችሉ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አሉ፡፡

እንደኔ እንደኔ ከሆነ፤ አይደለም ሊጻፍላቸው የሚገባቸው ነገሮች ኖረው ቀርቶ፣ ምንም አንገብጋቢ ነገር ባይኖር እንኳ በአሁኑ ወቅት በየህትመት ሚዲያዎቻችን የፊት ገ ላይ እያነበብናቸው የሚገኙት የዲያቆናት ጉዳይ የፊት ገጽ ሽፋን ሊያገኙ አቅሙ ያላቸው አይመስለኝም፡፡
ለነገሩ አሁን አሁን፣ የሃይማኖት እና የቤተክርስቲያን ጉዳይ መንፈሳዊ መሆኑ ቀርቶ አለማዊ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን በብዙ መልኩ እያስተዋልነው ነው፡፡ ስለዚህም ይመስለኛል የህትመት ሚዲያውም ጉዳዩን እንደ አንድ አለማዊ ጉዳይ በሰፊው እንዲሠራበት የተገደደው፡፡ ይህ በመሆኑ የህትመት ሚዲያዎቻችንን አለመኮነኑ ይመረጣል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን፣ ሚዲያው ለአንባቢው ስለሚደርሰው ርዕሰ ጉዳይ ክብደት እና ቅለት ሊያጤነው የሚገባው ይመስለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ለፊት ገጽነት ሊበቁ የሚችሉትን ጉዳዮች በመምረጡ ረገድ፡፡
የአንድ ቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ወይም ተልእኮ መንፈሳዊ ህይወትን ማቅናት እንጂ አለማዊ ህይወትን ማመቻቸት አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን፣ ሃይማኖት ጨርሶ የአለማዊ ህይወት ማቅኛ መሳሪያ አይደለም ማለት እንዳልሆነ አንባቢዎች እንዱረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ነገሩ የቅደም ተከተል፣ የተልእኮው መጠን ነው እንጂ በእርግጥ ለሁለቱም የሚሆን ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ፣ መንፈሳዊ ህይወትን ከማስቀደም ይልቅ ሃይማኖትን እንደ የዕለት ተዕለት የኑሮ ማቅኛ ብቻ እየተወሰደ መምጣቱን እየለመድነው እንገኛለን፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሊቋጩ የሚገባቸው አለመግባባቶች አለማዊ የህትመት ሚዲያ ላይ ባላየናቸው ነበር፡፡
አንዱን ከአንዱ ለመለየት የተቸገርን ይመስለኛል፡፡ የመንፈሳዊ ህይወት ምግባሩ ምንድን ነው? የአለማዊውስ. . .? በሁለቱ መካከል ፍንትው ብሎ የሚታይ መስመር አለ፡፡ ሲጀመር ቤተክርስቲያን የምትሰብከው እኮ ተቻቻሉ፣ እርስ በእርሳችሁም ተዋደዱ ነው አይደለም እንዴ?! ነው እንጂ! ታዲያ ይህንን እየተሰበክን፣ የአደባባይ ሚስጢር እስኪሆን ድረስ የመምህራኖቻችንን መልካም ያልሆኑ ጉዳዮች ከየጋዜጣው እና ከየመጽሔቱ ማንበብ ነበረብን? ያውም በእኔ እምነት ይህ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳየው፣ የተነሳንበት እና የምንሔድበትን መንገድ መዘንጋታችንን ነው፡፡ ሳናውቀውም ሆነ ፈልገነው፡፡
በእርግጥ በየትኛውም ጊዜና ቦታ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ ተፈጥሮአዊም ነው፡፡ አይደለም ስንቱን ማድረግ የሚቻለው እና ትልቁን የማስተዋል ጋ የተቸረው ሰው ቀርቶ፣ ግዑዝ ነገሮችስ ይገጫጩ የለም እንዴ? ለልዩነት መስፋት ምክንያት የሆኑ አለመግባባቶች ሊጠቡ የማይችሉበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ አይደለም መንፈሳዊ ህይወትን ለሚመሩት ቀርቶ አለማዊ ህይወትን ለሚመሩት ራሱ የሚቻል ነገር ነው፡፡ ትልቁ ብልሃት እና አስተዋይነቱ መቻቻሉና መደማመጡ ነው እንጂ እከሌ እንዲህ አለ፣ እከሊት እንዲህ አለች. . . አይደለም፡፡ ሁሉንም መተው፤ የላይኛውን በማሰብ፡፡ ለነገሩ ይህንን እኔ ራሴ የሰማሁት ከየትም አይደለም፡፡ ከእናንተው ነው፡፡ ታዲያ እኛ እንድናደርገው እየነገራችሁን እናንተ ማድረግ ለምን ተሳናችሁ? ይህ ደግሞ፣ እለት ተዕለት ስለ ነፍሳቸው ለሚታክቱ እና እውነተኛ መንፈሳዊ ህይወትን ለሚመሩት እጅግ በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ ሁላችንስ ተቻችለን ነው እንጂ በመካከላችን ላለመግባባት የሚያስችሉ ልዩነቶች ጠፍተው አይደለም፡፡
ለዚያ ጉዳይ ከሆነ፣ ..ልዩነት ውበት ነው.. እስከተባለ ድረስ፣ ላለመስማማት መስማማት ይቻላል፡፡ ስርዓት ባለው መልኩ ነው ይህ መሆን ያለበት፡፡ የግድ ልዩነትን ለመግለጽ በሚዲያ ላይ መነታረክ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ያውም በመንፈሳዊ ህይወታችን ላይ ጉልህ ሚና በሚጫወቱ ግለሰቦች፡፡ ተዘንግቶ ይሆናል እንጂ መነታረኩ (በግልጽም ሆነ በተዘዋዋሪ) በስንቶች ህይወት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ  ተጽእኖ አለው፡፡
በነገራችን ላይ፣ ማንም ሳይበደልና ሳይነካ እንደው ከመሬት ተነስቶ ለማዳመቅ ነው በየህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚጽፈው ወይም እንዲጻፍ ምክንያት የሚሆነው ከሚል ጭፍንነት ተነስቼ አይደለም ይህንን ለማለት የፈልግሁት፡፡ እርግጥ ነው፤ ችግሮች ይኖራሉ፤ በእርግጥም አሉ፡፡ የኔ ትልቁ ነጥብ ግን መንፈሳዊነቱ፣ መምህርነቱ እንዲሁም አስተዋይነቱ የቱ ላይ ነው? ተግዳሮቶች ባጋጠሙን ቁጥር መነታረኩ ነው? ያልተመቹን ነገሮች በገጠሙን ቁጥር በየህትመት ሚዲያዎች ላይ ማንፀባረቁ ነው? እነዚህ ድርጊቶች በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ላለ፣ አላስተዋይነት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ እንደሚሆን ቀድሞውኑ ይታወቃላ. . .! መቼስ፣ ላወቁና ክርስትናን ጠንቅቀው ያውቃሉ ተብለው ለሚታሰቡት ስለ ክርስትና ማስረዳት እንደ ቂልነት ይቆጠራል እንጂ፣ እንደው ዓለም ለፈጠራት ለገዛ ለባለቤቷ ራሱ አለመመቸቷ ሳይገባቸው ቀርቶ ነው? እንደኔ እንደውም ይህ ድርጊት የስንቱን መንፈሳዊ ህይወት ለማቅናት አቅሙ እና እውቀቱ ካላቸው በጭራሽ የሚጠበቅ ስነ ምግባር አይደለም፡፡

 

Read 3232 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 09:25