Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 13 August 2011 09:13

የፖላንድ መንገድ - እርምጃ፣ ጊዜ እና ህይወት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
  • ..እንኳን አደረሳችሁ..  ይሻላል ወይስ ..መልካም አዲስ አመት..
  • የወርቅ ፍርፋሪ ብንጠጣም አረማመዳችን አልፈጠነም

የሰዎችን አረማመድና ፍጥነት በማየት፤ ስለ ባህላቸውና አኗኗራቸው ማወቅ፣ ስለባህሪያቸውና አስተሳሰባቸው መናገር ይቻላል? አራት ጋዜጠኞች ሆነን ከሳምንት በፊት የፖላንድ ከተሞችን ስንጎበኝ ነው ጥያቄውን የፈጠርኩት... የተፈጠረብኝ ሳይሆን የፈጠርኩት፡፡ የአስጎብኚዎቻችን እርምጃና ፍጥነት ራሱ... በቀስታ ወደ ኋላ እየቀረንባቸው ምን ያህል ትእግስታቸውን እንደተፈታተንነው! በአገሪቱ ደቡብ ጫፍ ታሪካዊቷን ክራኮ ከተማ ያስጎበኘችን ዶምኒክ የተገናኘን እለት፤ በጉዞ ደክሞን ሊሆን እንደሚችል ነበር የገመተችው፡፡ ግን በማግስቱም ፈጣን አልሆንም፡፡

ከአገሪቱ ሰሜናዊ ጫፍ ግዳንስክና ግዳይና የተሰኙ ከተሞችን ካስጎበኘችን ማርጋሬት ጋርም እኩል አልተራመድንም፡፡ በግዳንስክ ጎልቶ የሚታየው ቤተክርስቲያን አጠገብ ከጎናችን ሆና እየተራመደች ትነግረናለች - አውሮፓ ውስጥ በሸክላ ከተሰሩት ህንፃዎች ሁሉ በግዙፍነቱ ቀዳሚ ነው፡፡ በውስጡ 25ሺ ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ በ14ኛው ክፍለዘመን የተጀመረው ግንባታ በየጊዜው እየተቋረጠ 150 አመታት እንደፈጀበት እየጠቃቀሰች ትረካዋን ትቀጥላለች፡፡ ግን ግማሹ አምልጦናል፡፡ ዞር ብላ ስታይ፤ ከኋላ ቀርተናል፡፡
በፍጥነት ለመራመድ ያልሞከርኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ ደግሞም አላቃተኝም፡፡ ግን፤ ስላልለመድኩት የመሮጥ ያህል እየሆነብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ የስራ ባልደረቦቼና ጓደኞቼ ይሄን ቢያዩኮ፤ ስትራመድ በጣም ትፈጥናለህ እያሉ ማስቸገር ያቆሙ ነበር፡፡
በሁኔታችን ግር ከተሰኘችው ማርጋሬት፣ ማታ አብራን እራት ስትበላ፤ የሬስቶራንቱ ባለቤት የጋበዘን ልዩ መጠጥ የሚያነቃቃን መስሏት ከሆነ ተሳስታለች፡፡ በእርግጥ ሰውዬው ሊጋብዘን አላሰበም ነበር፡፡ ባንኮኒው ላይ ከተደረደሩት መጠጦች መካከል፤ አንዱ ጠርሙስ ለየት ይላል፡፡ ውስጡ ያለው መጠጥ አረቄ ይመስላል - ውሃ ቀለም፡፡ ግን ደግሞ፤ ውስጡ የሚዋልሉ ፍርፋሪ ነገሮች ይታዩበታል፡፡ ወፍራም ሻምፓኝ የመሰለ መጠጥ እንደሆነ የነገረችን ማርጋሬት፤ መጠጡ ውስጥ የሚዋልሉት ነገሮች የወርቅ ፍርፋሪዎች ናቸው አለች፡፡ መቀለዷ አልነበረም፡፡
የሬስቶራንቱ ባለቤት ጠርሙሱን አምጥቶልን እያገላበጥን አየነው፡፡ ..እድሜን ያድሳል.. አለች ማርጋሬት - ይሄ ለቀልድ ነው፡፡ ጠርሙሱን አይተን ከመለስን በኋላ ነው፤ አንዳንድ መለኪያ የተጋበዝነው፡፡ ብር ረክሶ ወርቅ በተወደደበት ዘመን፤ ከወፍራሙ መጠጥ ጋር የወርቅ ፍርፋሪ ማወራረድ? ወርቁ በሚሊግራምም ሳይሆን በማይክሮግራም ከሆነ፤ ብዙም አያስቆጭም፡፡ በዚያ ላይ ይጣፍጣል፡፡ ግን አረማመዳችንን አላፈጠነውም፡፡      
አረማመዳችን፤ ስለ ጊዜ ካለን አስተሳሰብና ስሜት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሳምንት በዘለቀው የአራት ከተሞች ጉብኝት፤ የቀጠሮ ሰአት ያላሳለፍንበትና ያላረፈድንበት ቀን የለም ማለት ይቻላል - የአስጎብኚዎቻችን ውትወታ ባይለየንም፡፡ የአገሪቱ ቤተመንግስት አጠገብ የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንቱንና የምርጫ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ስንሄድ፤ ሻንጣዬ ውስጥ ፓስፖርት በመርሳቴ አርፍደናል፡፡ አንዱ ከእንቅልፍ ባለመነሳቱ ወይም ቁርስ ባለመብላቱ፤ ሌላኛው በርዶት ጃኬት ሳይደርብ ስለበረደው ወይም ካሜራውን ቻርጅ ሳያደርግ ስላደረ ... በዚህም ሆነ በዚያ የማርፈጃ ምክንያት አይጠፋም፡፡
ደግነቱ፤ መስተንግዶው ፈጣን ነው፡፡ የአገሪቱ ፓርላማም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ህንፃው ውስጥ ለመግባት ካለው የኤሌክትሮኒክስ ፍተሻ በቀር የግቢ በር ላይ ለፍተሻ የሚያስቆም ወይም ፎቶ አታንሱ ብሎ እየከለከለ የሚያጉላላ ሰው የለም፡፡ ሞባይልና ካሜራ ይዞ መግባት አይቻልም ብሎ ጊዜ የሚያጠፋ አላየሁም፡፡ እኛ ስለምናረፍድ እንጂ፤ በጊዜ እንዳንደርስ የሚያደናቅፍ ነገር አላጋጠመንም፡፡ ሰአት ማክበርን በሚመለከት የአፍሪካ ወጣቶች ላይ ጥናት ያካሄደችውን ማልዊና ለማነጋገር ስንሄድም፤ ማርፈዳችንና መዘግየታችን አልቀረም፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልጋል? እንደምናረፍድ አስቀድማ መገመት የሚያቅታት አይመስለኝም፡፡
ማልዊና ዩኒቨሪሲቲ ገብታ የአፍሪካና የኤስያ ባህሎች ላይ ያተኮረ የትምህርት መስክ ለማጥናት የመረጠች ጊዜ፤ ይህንን ተምረሽ ለኑሮ ምን ልትሰሪበት ነው እያሉ ይጠይቋት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ነገር ግን አላማ ይዞ የሚማር ሰው፤ የሚሰራውን አያጣም፡፡ ዛሬ፤ ታስተምራለች፣ በኮንፈረንሶች፣ በአለማቀፍ ዝግጅቶች፣ በጉብኝቶች እየተጋበዘች ጥናቶችንና ማብራሪያዎችን ታቀርባለች፡፡ ስራዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ጊዜ እንደሚያጥራት ማልዊና ገልፃ፤ በቅርቡ በለንደን በሚካሄድ ሰሚናር ጥናት እንድታቀርብ ስለተጋበዘች እየተዘጋጀች እንደሆነ ትገልፃለች፡፡ አፍሪካ ውስጥ በሚታየው የሰአት አከባበርና የጊዜ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ነው ጥናቷ፡፡
ሰአት የማናከብረው፤ የምድር መቀነት እየጠለፈን
ያው እንደተለመደው፤ ቀብር እና ፆም ከመሳሰሉ ነገሮች በስተቀር፤ አብዛኛው ህይወታችን በሰአት የሚመራ አይደለም፡፡ በሰአቱ የሚጀመር የሰርግ ወይም የምረቃ ድግስ፤ በሰአቱ የሚደርስ ሙሽራ ወይም ምግብ አጋጥሟችሁ ያውቃል? አብዛኞቹ እድምተኞችም በጊዜ አይደርሱም፡፡ በሰአት መገኘት አሳፋሪ እየሆነባቸው፤ ለመዘግየት የሚታገሉም ይኖራሉ፡፡ መኪና ማስጠገንም ሆነ ቤት ማስገንባት፣ የተቀደደ ልብስ ማሰፋትም ሆነ ጫማ ማስጣፍ... በጊዜው የሚደርስ ስራ ብርቅ ነው፡፡ በመንግስት መስሪያቤትማ፤ ከቢሮ ቢሮ፣ ከእለት እለት በቀጠሮ ሳይንገላቱ ጉዳይ ለመጨረስ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ዘንድሮ የባሰበትን የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ተመልከቱ፡፡ ታዲያ ይሄ ኋላ ቀርነት አይደለም?
ሰአት ያለማክበር በቀጥታ ከኋላቀርነት ጋር የተያያዘ ነው ለማለት አልፈለገችም - ማልዊና፡፡ ምናልባት እኛን ላለማስከፋት ሰግታ፤ ወይም ደግሞ በአጉል ተቆርቋሪነት ጉድለታችንን ልትሸፋፍንልን እየሞከረች ይሆናል፡፡ እኛን የሚጠቅመን ግን፤ እውነታውን እየመረመረ አፍረጥርጦ የሚነግረንና ከምር እንድናስብበት መነሻ የሚሆነን ሰው አይደለም?
የሆነ ሆኖ፤ ሰአት ያለማክበር ነገር፤ ከምንኖርበት መልክአምድርና ከአየር ፀባይ፤ ከአኗኗር ሁኔታና ከታሪክ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ትገልፃለች ማልዊና፡፡ ለምሳሌ የምድር ወገብ አቅራቢያ በሚገኙ የአፍሪካ አገራት፤ የቀንና የማታ ርዝመት ብዙም አይራራቅም - ወደ ሰሜን ዋልታ የተጠጉ የአውሮፓ አገራት ግን አንዳንዴ፤ የቀን ብርሃን በሌላ ወቅት ደግሞ ጨለማው ለ18 ሰአት ሊቆይ ይችላል፡፡ ማለዳ እንገናኝ፤ አመሻሽ ላይ እንለያይ ብሎ ቀጠሮ መያዝ ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ከአፍሪካዊያን ይልቅ አውሮፓውያን፤ ትክክለኛ ሰአት የመጠቀም ግፊት ይኖርባቸዋል ትላለች ማልዊና፡፡ ብርድና ሙቀት፣ ጎርፍና ማእበል በሚፈራረቅባቸው አካባቢዎች ወይም ከባህር ጉዞ ጋር የተቆራኘ ኑሮ በመሰረቱ ማህበረሰቦችም፤ ጊዜን በትክክል የመቁጠርና ሰአትን በአግባቡ የመጠቀም ግፊት እንደ¸ÃDRÆcW ማልዊና ታስረዳለች፡፡ በእርግጥ ትስስር ይኖረዋል... ነገር ግን
የጊዜ መቁጠሪያ መሳሪያዎችን ለመስራት አስደናቂ ጥረት ከተደረገበት የግሪክ ስልጣኔ በኋላኮ፤ አውሮፓውያን ለ1500 አመታት ያህል ሰአት የመስራት ጉልህ ቁምነገር አልሰሩም - ለዘመናት ባንቀላፉበት በዚሁ የኋላቀርነት ዘመን ለጭፍን እምነቶች እንጂ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ቦታ አልነበራቸውም፡፡ ሰአት የመስራት ጥረታቸውን እርግፍ አድርገው የተዉት፤ የየእለቱ የጨለማና የብርሃን ርዝመት ስለተስተካከለላቸው ነው? ወይስ ብርድና ማእበል ስለጠፋ? አይደለም፡፡ ከ15ኛው ክፍለዘመን በኋላ በአስደናቂ ፍጥነት የሰአት ፈጠራና ስራ የተበራከተውና የተራቀቀውስ፤ የአውሮፓ መልክአምድርና የአየርፀባይ ድንገት ስለተለወጠ ነው? አይደለም፡፡ ማልዊና ተሳስታለች ብዬ አሰብኩ፡፡ ምክንያቱም፤ ብርድና ጨለማ፤ አፍ አውጥቶ ሰአት እንድትፈጥርና ጊዜን በአግባቡ እንድትሰራበት አይነግርህም፡፡  የቀንና የጨለማ ርዝመት መዘበራረቅ፤ የጎርፍና የማእበል መፈራረቅ ኑሮን ቢፈታተንም፤ ምን ብታደርግ እንደሚሻልህ አያማክርህም፡፡ ሰዎች፤ ኑሮ ፈታኝ ሲሆንባቸው ምን ያደርጋሉ?
መፀለይን ወይም ለጣኦት መስዋእት ማቅረብን አልያም፤ ለጎሳ መሪዎችና ለመንግስት አቤት ማለትን የሚመርጡ ይኖራሉ - ..ሰው ደካማ ሚስኪን ነው፤ ህይወታችን በሌሎች ሰዎችና  በመለኮታዊ ሃይሎች እጅ ነው.. ብለው የሚያምኑ ከሆነ፡፡
ዘወትር እያማረሩ መኖርን ወይም በእውር ድንብር መሰደድን፤ አልያም እንደ አብዛኞቹ የኤስኪሞ ተወላጆችና እንደጨለማው ዘመን አውሮፓውያን ያለመፍትሄ የኑሮ ችግርን ተሸክሞ ለመኖር መምረጥም  ይቻላል - ..ሰው ተስፋ የለሽ ሚስኪን ነው.. ብሎ በማመን፡፡  ወይም በዘመነ ሬነሰንስና በዘመነ ኤንላይትመንት እንደነበሩት አውሮፓውያን፤ ደቂቃና ሴኮንድ ጭምር የሚቆጥር ሰአት ለመስራት መምረጥ ይቻላል - ..ሰው አእምሮውን ተጠቅሞ ህይወቱን እየመራ ኑሮውንና መንፈሱን ማበልፀግ የሚችል ጀግና ነው.. በሚል ሳይንሳዊ አስተሳሰብ፡፡
የሰአት አከባበርና የጊዜ አጠቃቀም ዝንባሌዎች፤ ከመልካምድርና ከአየር ፀባይ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው የሚለው ሃሳብ ስህተት ከሆነ፤ እንደገና መመርመርና ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ ምናልባት፤ አረማመዳችንና የጊዜ አስተሳሰባችን፤ በአጠቃላይ ስለ ህይወትና ኑሮ ካለን አስተሳሰብና ስሜት ጋር የተያያዘ ቢሆንስ?
..እንኳን አደረሳችሁ.. እና ..መልካም አዲስ አመት..
በኢትዮጵያ የ20ኛው ክፍለዘመን ታሪክ ላይ የምትመራመረው ፖላንዳዊቷ ሃና፤ ከሁሉም በላይ ጊዜንና ህይወትን በተመለከተ በአገራችሁ ያለው አስተሳሰብ ጎድቷችኋል ብላ ታስባለች፡፡ በየአመቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሁለት ወር እየከረመች ጥናት የምታካሂደው ሃና፤ አማርኛ እንደምትችል መስማቴን ስነግራት፤ ..ቲንሽ፣ ቲንሽ.. አለች እየሳቀች፡፡ መናገር ቢከብዳትም፤ መስማትና አንብባ መረዳት ግን ትችላለች፡፡ ገና ወጣች ስለሆነች፤ ለመለማመድ ብዙ ጊዜ አላት፡፡ ዶክተር መሆኗን አልነገርኳችሁም መሰለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ላይና የአማርኛ ቋንቋ ላይ በምታካሂዳቸው ጥናቶች ነው፤ ስሟ ላይ ፒኤችዲ የሚል ቅጥያ የተጨመረላት፡፡ እንግዲህ በዋርሶ ዩኒቨርሲቲ፤ ስለኢትዮጵያ የምትመራመር አይደለች? ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡
..በጥንታዊ ስልጣኔ ስሟ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፤ ለዘመናት በኋላቀርነት የተተበተችበት ምክንያት፤ ከባህልና ከአስተሳሰብ ጋር የተያየዘ ይሆን?.. ብዬ ጠየቅኳት፡፡ በቅርቡ የንግስት ዘውዲቱንና የንጉስ ሃይለስላሴን ሹክቻ የሚዳስስ መፅሃፍ ያሳተመችው ወጣቷ ሃና፤ ትንሽ ብታመነታም መልስ ለመስጠት ወደኋላ አላለችም፡፡ የአንድን አገር ታሪክ ከሚወስኑ ነገሮች መካከል፤ ባህልና አስተሳሰብ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብላ እንደምታሰብ ዶ/ር ሃና ጠቁማ፤ ጊዜንና ህይወትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ያስተዋለችው አስተሳሰብና ባህል ወደኋላ የሚያስቀር እንደሚመስላች ነገረችኝ፡፡ እንዴት?
አዲስ አመት መባቻ ላይ የምንጠቀምባቸውን አባባሎች በምሳሌነት ታነሳለች - ሃና፡፡  ..መልካም አዲስ አመት.. ወይም ..አስደሳች አዲስ አመት.. ከሚሉ አባባሎች ይልቅ፤ ..እንኳን አደረሳችሁ.. የሚል አባባል ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡ የወደፊቱ ህይወትና የወደፊቱ ጊዜ ላይ ሳይሆን፤ ያለፈው ህይወትና ጊዜ ላይ ምን ያህል እንደምናተኩር የሚጠቁም ምሳሌ ነው፡፡ ..እንኳን አደረሳችሁ.. በሚለው አባባል ውስጥ፤ ..የወደፊቱን ህይወት ደግሞ ሲደርስልን ወይም ሲደርስብን፤ ሲከሰትልን ወይም ሲከሰትብን እናየዋለን ... እስከዚያው ተቀምጦ ከመጠበቅ ሌላ፤ በሰው ሚስኪን አቅም ምን ማድረግ ይቻላል!.. የሚል ስሜት የሚኖር አይመስላችሁም? ..በሰው ሚስኪን አቅም ምንም ማድረግ አይቻልም ብሎ.. የሚያስብ ሰው፤ ፈጠን ፈጠን ብሎ የመራመድ ልምድ አያዳብርም - ..የት ለመድረስ ብሎ ይፈጥናል!..፡፡ ሰአት የማክበርና ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ዝንባሌ አይገነባም - ..ደግሞ በሰው ደካማ አቅም መቻኮልና ማቀድ ምን ለመፍጠር!..፡፡ ..ሰው በተፈጥሮው አቅመ ቢስ ደካማ ነው.. የሚል እምነት በተስፋፋበት አገር፤ ፈጥኖ የመራመድ፣ ሰአት የማክበርና ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም አስተሳሰብም ሆነ ዝንባሌ የሚያዳብሩ ሰዎች ጥቂት ቢሆኑ አይገርምም፡፡ ሌላኛው አማራጭ መንገድ፤ አየን ራንድ እንደምትለው፤ ..ምን ደረሰብኝ ወይም ምን ይከሰትብኛል?.. ከሚለው ጥያቄ ይልቅ፤ ..ምን አደረስኩ ወይም ምን እንዲከሰት አደርጋለሁ?.. የሚለው ጥያቄ ላይ ያተኮረ መንገድ ነው፡፡ ..ሰው በተፈጥሮው፤ አእምሮውን ተጠቅሞ እውቀት እያዳበረ፤ የህይወት አላማው የመምረጥና አላማውን የማሳካት አቅም አለው.. ከሚል ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ጋር የተሳሰረ መንገድ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ..እንኳን አደረሰህ.. ከማለት ይልቅ፤ ..መልካም አዲስ አመት.. የሚል አባባል ለምን ተመራጭ እንደሚሆነ አስቡት፡፡ ..አላማ ከመረጣችሁና ከሰራችሁ፤ አዲሱን አመት አስደሳችና መልካም እንዲሆን ማድረግ ትችላላችሁ.. የሚል መልእክት የያዘ አባባል አይመስላችሁም?

 

Read 5287 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 12:52