አሴዋ
ዛሬም እየዋ
ገባልህ የዋንጫ ዋ!
ትግልህ የተጫዋች እልክ
ድልህ የተመልካች ልክ፡፡
ይሄዋ አሴ ያልከው ሆነ
አድማስህ ድሉን ዘገነ
ፕሬስና ኳስ ተካነ
በእጅ የተፃፈው ቃል ሁሉ፣ በግር የተፃፈ ወርቅ ሆነ!!
..ህዝብ ሲያውቅ እኔም አውቅ.. እንዳልክ፤
እንካ ዋንጫውን ተረከብ፣ ሲያሸንፍም አንተ አሸነፍክ!!
ዛሬ ህልምህን ዕውን አረክ
ደግ አረክ! አሴ ደግ አረክ!
አሴዋ
ዛሬም እየዋ
ገባልህ የዋንጫ ዋ!
ተረካቢህ አያሳፍር፣ ድፍን - ታታሪ ጨዋ፡፡
ተንቀለቀለ ቀንዲሉ፣ ያድማስህ ድምር ደመራ
ጋመ ንብርብሩ ፍም፣ አንተኑ በእሳት ሊጠራ!
ቀን ይጠብቃል እንጂ፣ ድል የትጉህ እጅ ነው
ወትሮም ካድማስ ጎህ ይቀዳል፣ ጎርፍም የዥረት ጅራፍ ነው
ከእያንዳንዱ ድል ጀርባ፣ አንዳንድ ጀግና ካለ
አንተ ነህ አሴ ልባሙ፣ ህልምህ በድል የተኳለ!
ተስፋህ ንፍ አያቅምና፣ ገና ይበራል ቀንዲሉ
አድማስህ ኬላ የለውም፣ ገና ይሰፋል ፀዳሉ፡፡
..ህዝብ ሲያውቅ እኔም አውቅ.. እንዳልክ
እንካ ዋንጫውን ተረከብ፣ ሲያሸንፍም አንተ አሸነፍክ!!
(ለአሴዋ ለአዲስ አድማስ ተጫዋቾችና ድል ለሚገባቸው ሁሉ)
ሐምሌ 28 2003 ዓ.ም