Sunday, 31 July 2011 13:33

መንግሥት

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

.ያለ ዕዳው ዘማች.. ለምን ይሆናል?
ባለፈው ሳምንት በመጠኑ ያስቃኘኋችሁን የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት የዶ/ር ነጋሦን መጽሐፍ አንብባችሁት ከሆነ እሰየው! ለማንኛውም ግን የዛሬ ወጌን ከመጽሐፉ ባገኘሁት አስደማሚ ወግ  ልጀምር አስቤአለሁ፡፡
ዶ/ር ነጋሦ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ አባታቸው ዓይነ ስውሩ ቄስ ጊዳዳ የነገሯቸውን ዓይነተኛ ምሳሌ ነው በመጽሐፉ የጠቀሱት፡፡ በአባታቸው የትውልድ አገር የበርበሬ ነጋዴዎችን ታሪክ ያወሳል - ምሳሌያቸው፡፡

በርበሬ ለመሸመት ገበያ የወጣ ሸማች፣ በነጋዴዎቹ ጩኸት ግራ እንደሚጋባ የነገሯቸው ቄስ ጊዳዳ፤ ..ሁሉም የበርበሬ ነጋዴ የእኔ ያቃጥላል እያለ ስለሚያዋክበው በቅጡ መገብየት ይቸገራል፤ የሆኖ ሆኖ ግን በመጨረሻ የሚፈልገውን የሚመርጠው ገዢው ብቻ ነው.. ሲሉ እዲጫወቷቸው  ገልዋል - ነጋሦ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውነትም ከበርበሬ ነጋዴዎቹ ብዙም የሚለዩ አይመስለኝም፡፡ የማታ ማታ ምርጫው የሕዝቡ መሆኑን ለማስታወስ ያህል ነው እቺን መዝዤ ማውጣቴ፡፡አሁን ወደ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዝለቅ፡፡ እኔ የምለው እቺ የሐምሌ ወር ምነው እሮሮ በዛባት፡፡ ነጋዴው ሁሉ ምሬት በምሬት ሆኗል እኮ! የግብር ክፍያ እጥፍ መሆኑን የሚናገሩ ቅሬታ አቅራቢዎች በርክተዋል፡፡ አስቂኙ ነገር ደግሞ የተገመተውን ግብር ለመክፈል አቅም የለንም የሚል እሮሮ ሲያሰሙ . . . ..ችግር የለም፣ መጀመሪያ ክፈሉና ይመረመራል.. መባሉ እኮ ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ሰሞኑን ደግሞ በየጐዳናው ቡና በፔርሙዝ እያዞሩ የሚሸጡ ሴቶች ፈቃድ እንዲያወጡና የ6 ወር ቅጣት በቀን 200 ብር (ወደ ኋላ ማለት ነው) ይክፈሉ ተብሏል የሚል (ያልተጣራ) ወሬ ሰምቼxlhù”” እንግዲህ ወደ አረቡ አገር ለመሰደድ የሚሰለፉትን እንስቶች ያየ እዚህ አገር ላይ በተገኘው የሥራ ዘርፍ የተሰማሩትን ያበረታታል እንጂ አያዳክምም፡፡ አንዳንድ ነገሮችን እኮ በህግ ብቻ ሳይሆን በህሊና ማመዛዘንንም ያስፈልጋል፡፡ ግራ ቀኙን ማየት፤ የሚጐዳውንና የሚጠቅመውን መለየት የግድ ነው፡፡ ህግ አውጥቶ አገር ላይ የሙከራ ፕሮጀክት ማጧጧፍ ሳይሆን፣ ቀድሞውኑ በቅጡ ማጥናት፣ ከአያሌ ስህተቶችና ፀፀቶች ያተርፋል እላለሁ፡፡ ያለዚያ የዋጋ ቁጥጥሩ ዓይነት ነገር ይፈጠራል- ለሦስት ወር ተግባራዊ ሲሆንና አገር ሲመሰቃቀል ወደ ድሮው መመለስ፡፡ ይሄ ደግሞ እንኳን ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከሚመራ መንግሥት ቀርቶ አምስትና ስድስት ቤተሰብ ከሚያስተዳድርም አባወራ አይጠበቅም፡፡ እኔማ አንዳንዴ ሳስበው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማለት የአዳዲስ ህጐችና ደንቦች ፍተሻ (ሙከራ) ማለት ይመስለኝ ጀምሯል፡፡ ምን ላድርግ?በአንድ ክፍለ ከተማ ነው አሉ፡፡ ነዋሪዎች ለፈቃድ እደሳና ለግብር ክፍያ በብዛት ተሰልፈዋል፡፡ በወረፋው መብዛት የተፈጠረውን ግርግር ፈር ለማስያዝ ሲሞክር የነበረ ፖሊስ፣ አንድ አረጋዊ ይገፈትርና ይወድቃሉ (አውቆ በድፍረት ይሁን ሳያውቅ በስህተት አልተረጋገጠም) በፖሊሱ ህገወጥ ተግባር የበሸቁ ሰዎች ጉዳዩን ለአለቃው ይጠቁማሉ፡፡ አለቅየው ነገሩን ቦታው ድረስ መጥቶ ከመረመረ በኋላ ምን አለ መሰላችሁ? ..ፖሊሱ የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው.. ብሎት እርፍ!
እንግዲህ ስለአገልግሎትም አይደል የጀመርነው . . . እንቀጥላ! የህዳሴው ግድብ ሊሰራ ነው ተብሎ መወራት ከጀመረ ወዲህ የመብራት ኃይል መ/ቤት የተለመደ ማን አለብኝነቱን ገፍቶ የቀጠለበት ይመስላል፡፡ በማንኛውም ሰዓት መብራት እልም ይላል - ባሰኘው ሰዓት ይመጣል፡፡ በእርግጥ የ80 ቢሊዮን ብር ግዙፍ ግድብ አባል ላይ እንደሚገነባ እናውቃለን - ቦንድም ገዝተናል፡፡ ይሄም ቢሆን ግን መብራት ኃይል ደንበኞቹን ለማንገላታት በቂ ሰበብ የለውም፡፡ መብራታችንን ከቤታችን ድንገት እልም ሲያደርግብን ምናለ ይቅርታ እንኳን ቢጠይቅ? ኧረ ጡር ደግ አይደለም፡፡ በእርግጥ ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ መብራት ኃይልን ፕራይቬታይዝ ማድረግ ነበር፡፡ መንግስት ወደ ፊት መብራት ኃይል የብር ማተምያ ማሽን ይሆናል ብሎ አስቧል መሰለኝ አላስነካም ብሎ አንቆ ይዞታል፡፡ አልሰማ አለን እንጂ መንግስት ዝም ብሎ አስተዳደሩ ላይ ብቻ ቢያተኩርና የቀረውን ነገር ሁሉ ወደ ግል ቢያዞር ከዚህ ሁሉ ወቀሳ በዳነ ነበር - ግን ለጊዜው መንግስት አልመሰለውም፡፡ እስከዚያው ታዲያ የሚያዋጣው እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ሳይሆን መወትወት ነው፡፡ እስኪመስለው ድረስ መወትወት. . . ብዙ ጊዜ፡፡
እዚሁ ጋዜጣ ላይ የኒዮ ሊበራሊስት አቀንቃኞች የሚመስሉ ፀሐፍት፤ መንግሥት ቢዝነስ አይሆነውም ሲሉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ኒዮ ሊበራሊስት ቢሆኑም ነገርየው እውነት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ በቅርቡ ጊዮን ሆቴል ሄዶ የደረሰበትን እንግልት ሲነግረኝ ..ጊዮን ለግል ባለሃብት ተሸጧል ሲባል ሰምቼ ሄጄ ጉድ ሆንኩልህ.. አለኝ - በማዘን፡፡ ምን ገጠመህ? አልኩት፤ የደረሰበትን ለመስማት ጓጉቼ፡፡ ወዳጄ እንደነገረኝ ወደ ጊዮን ጐራ ያለው የ3 ዓመት ልጁን ይዞ ነው - ለማዝናናት፡፡ ልጁም ወደ ህፃናት መዝናኛው ሥፍራ ሲደርስ በደስታ ፈነደቀ - በኮይን የሚንቀሳቀስ ሞተርሳይክል፣ ፈረስ፣ ሄሊኮፕተር ወዘተ ላይ ጉብ ብሎ ለመጫወት የህፃን ልቡ እየተጣደፈች፡፡ አባት እንደምንም አሳምኖ ወደ መክፈያው ሥፍራ መውሰድ ነበረበት - ልጁን፡፡ ሆኖም ከገንዘብ ተቀባይዋ የተሰጠው ምላሽ አባትን የሚያሰቅቅ ነበር፡፡ የህፃናት መጫወቻ ማሽኖቹ አይሰሩም ነው የተባለው፡፡ እስቲ አስቡት . . . ይሄንን ለ3 ዓመት ህፃን ልጁ ምን ብሎ ሊያስረዳው ወይም ሊያሳምነው ይችላል? ወዳጄ ከካሸሯ ጋር ትንሽ በመጨቃጨቁ ባለሙያዎቹን ጠያይቃ ሞተር ሳይክሉ ብቻ እንደሚሰራ ተነገረው፡፡ የሁለት ኮይን ሂሳብ ከፍሎ ልጁን ሊያጫውት ወደ ማሽኑ አመራ፡፡ ሞተር ሳይክሉ ግን አይሠራም፡፡ ቢዝነስ በመንግስት ሲያዝ ይሄው ነው - አይሰራም፤ አይነቃነቅም፡፡ መንግስት ቢዝነስ እንዳይሳካለት ተረግሞ ግን XNÄYmስላችሁ! በቃ ፊልዱ አይደለም ስላችሁ - የህዝብ አስተዳደር ሌላ፤ ቢዝነስ ሌላ! ለዚህ ነው ወዳጄ ..ጊዮን ለግል ባለሃብት ተሸጧል ሲባል ሰምቼ ሄድኩና ጉድ ሆንኩልህ.. ያለኝ፡፡ መንግስት የማያገባው ውስጥ እንዲህ እየገባ በራሱም በህዝቡም በአገርም ላይ ችግርና ትርምስ ሲፈጥር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ? ..ያለዕዳው ዘማች..፡፡ ሆቴል ላስተዳድር ሲል . . . ያለዕዳው ዘማች፤ ዘይትና ሳሙና ሲቸረችር . . . ያለዕዳው ዘማች፤ ቢራና ድራፍት ልነግድ ሲል . . . ያለዕዳው ዘማች . . . ወዘተ ወዘተ .  
ቢዝነስ የመንግስት ሙያ አይደለም . . . አያምርበትም፡፡ ያምርብኛል ብሎ እልህ ሲጋባ ደግሞ ውጤቱ ኪሳራ፣ ብክነት፣ ትርምስ . . . ይሆናል፡፡
እንግዲህ ኑሮአችንን መከራ የሚያደርጉብን አያሌ ችግሮች በአብዛኛው ሰው ሰራሽ (መንግስት ሰራሽንም ያካትታል) እንደሆኑ ከተሞክሯችን መገንዘብ ችለናል. . . አይደል! በአገራችን እያሰለሰ የሚከሰተው ድርቅና ረሃብ ለምሳሌ በከፊል የተፈጥሮ በከፊል ደግሞ የሰው ሰራሽ ችግሮች ውጤት ይመስሉኛል፡፡ የኑሮ ውድነት ግን ፈሞ የተፈጥሮ አደጋ ነው ሊባል አይችልም - የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት እንጂ፡፡ የፖሊሲው ብቸኛ ባለቤት ደግሞ ሁሌም መንግስት ነው፡፡ ፖሊሲ ፕራይቬታይዝ ተደርጐ አያውቅማ! እስቲ የኑሮ ውድነቱን የተመለከተ ትንሽ ወግ ቢጤ ላካፍላችሁ፡፡ ኑሮ ውድነቱን ብቻ ሳይሆን ወጉንም እንካፈል ብዬ ነው!
አንዷ የሥራ ባልደረባዬ አስቤዛ ለመሸመት ወደ ሱፐር ማርኬት ሄዳ ሳለ፣ ሁለት አባ ወራዎች ሚስታቸውን ተክተው ገበያ ወጥተው አገኘቻቸው፡፡ ሁለቱ አባወራዎች የቤት አስቤዛ ሸመታ የወጡት ሚስቶቻቸው ላይ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነው - በየጊዜው የሚጠየቁት የቤት ወጪ በመናሩ፡፡ ለነገሩ አባወራዎቹ ጥሩ ዘይደዋል፡፡ ሚስቶቻቸውን ሲጠራጠሩ ከሚኖሩ ለራሳቸው እውነቱን አውቀውት ከኑሮ ውድነቱ ጋር መጋፈጥ ይሻላቸዋል፡፡ ወጌን በዶ/ር ነጋሦ ..የነጋሦ መንገድ.. እንደቀደስኩት በዚያው መጽሐፍ ባሳርገውስ?
አብዮታዊ ደሞክራሲ ስለተባለው የኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የሚያወሱት ዶ/ር ነጋሦ፤ የቃል ማብራሪያ ከጠ/ሚኒስትሩ ማግኘታቸውን ጠቅሰው የሚነበብ መጽሐፍ ግን አልጠቆሙኝም ሲሉ ሀቁን ተንፍሰዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሦ 10 ዓመት ሙሉ በኢህአዴግ መታለላቸውን የሚገልበት የመጽሐፉ ክፍልም አስደማሚ ነው - እሳቸው በሶሻሊዝም ጐዳና ላይ ነን ሲሉ ኢህአዴግ ነፍሴ ..የምንመራው በነጭ ካፒታሊዝም ነው.. ብሎ ገላገላቸውና የእህል ውሃቸው ማብቂያ ሆነ - አሳዛኝ ክስተት ይሏል ይሄ ነው፡

 

Read 3551 times Last modified on Sunday, 31 July 2011 13:40