Print this page
Sunday, 24 July 2011 07:56

ግብጽን ማን ይመራት ይሆን?

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(1 Vote)

በግብጽ ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ከለቀቁ አምስተኛ ወር አልፏቸዋል፡፡ ሙባረክ ሥልጣን መልቀቃቸውን ባስታወቁበት ወቅት፣ ለ18 ቀንና ለሊት በታህሪር አደባባይ ውሎና አዳራቸውን ያደረጉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ግብፃዊያን ያሳዩት ከልክ ያለፈ ደስታና ፈንጠዝያ አሁን እልም ብሎ በመጥፋት፣ በምትኩ በአገራቸው ከሁለት ወር በኋላ የሚካሄደውን የፕሬዝዳንት ምርጫ በተመለከተ፣ በቀጣይ ግብጽን የሚመራት ማን ይሆን በሚል አሳብ ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡

በሕዝባዊ አመ የተሳተፉት በርካታ ወጣቶች በየጊዜው እየተገናኙ፣ በአገራቸው መፃኢ የፖለቲካ ጉዳይና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር በመመስረት ላይ ሊኖራቸው ስለሚችለው ሚና ይወያያሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ወጣቶቹ በየካፌዎቹ እና መዝናኛ ሥፍራዎች ሰብሰብ ብለው የፖለቲካ ውይይቶች ከጀመሩ በኋላ በሞቀ ክርክርና ጭቅጭቅ ይቋጫሉ፡፡ ሳራ አብዱራህማን የተባለች ወጣት ስትናገር፣ ..በየጊዜው በሚካሄዱ የፖለቲካ ክርክሮች ጭንቅላቴ ሊፈነዳ ነው፤ ከአብዮቱ በኋላ ውስጣዊ ጥንካሬ ያገኘሁና ደስታ የተሰማኝ ቢሆንም፣ ያለማቋረጥ በሚነገሩ የፖለቲካ ወሬዎች ግን በጣም ተጨንቄያለሁ.. በማለት ገልፃለች፡፡
ሞሀን የተባለ ጐልማሳ ሰው ደግሞ ..ወንድ ልጄ በእንግሊዝ የታወቀ ጠበቃ ነው፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ከሕዝባዊ አመ ጋር ለመቀላቀል ወደ ካይሮ መጥቷል፤ የተቀሩት የቤተሰቤ አባላትም አብረውት ነበሩ፡፡ ባለቤቴ ከፖለቲካ በጣም ገለልተኛ የነበረች ቢሆንም ከሕዝባዊ አመ ጋር አብራ ተሳትፋለች፡፡ ከአብዮቱ በኋላም ከጓደኞቿ ጋር የጦፈ ፖለቲካዊ ሙግት ታካሂዳለች.. በማለት ገልጿል፡፡
ሆስኒ ሙባረክ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ግብፃዊያን በተለያዩ ጊዜያት በታህሪር አደባባይ በመውጣት በስልጣን ላይ የሚገኘው ወታደራዊ አስተዳደር፣ ለሚመረጠው አዲስ መንግስት ሥልጣኑን በአግባቡ እንዲያስረክብ ..ከአደራ.. ጭምር አሳስበዋል፡፡ ባለፈው ሳምንትም በታህሪር አደባባይ በመውጣት ሙባረክ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ በመጪው መስከረም ወር የሚካሄደው የፓርላማ ምርጫም ፍትሀዊ እንዲሆን አበክረው ተማጽነዋል፡፡
በሙባረክ አስተዳደር ወቅት ዋነኛው ተቃዋሚ የነበረው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ 35 በመቶ የፓርላማ መቀመጫ እንደሚያገኙ ቢጠበቅም፣ ሙባረክን ለማውረድ በተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ ያለመካፈላቸውና ከሙባረክ መውረድ በኋላም ቢሆን በታህሪር አደባባይ በተካሄደው ሰልፍ አለመታየታቸው ይጠቀሳል፡፡ ኤልጃ ዛራዋን የተባለ አለም አቀፍ የግጭት ቡድን ተወካይ በታህሪር አደባባይ በተገኘበት ወቅት ..የሙስሊም ወንድማማቾቹ እዚህ ካለው ሕዝብ ጋር አብሮ ከመሳተፍ ይልቅ፣ ከሌሎች እስላማዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በግብጽ ውስጥ ትልቅ የእስላማዊ መንግስትን ለመመስረት የሚፈልጉ ይመስላሉ.. በማለት ተናግሯል፡፡  
ሙባረክ ከመውረዳቸው በፊት በግብጽ ብዙም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልነበሩ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በየጊዜው አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተፈለፈሉ ይገኛሉ፡፡
አመፁን ያካሄዱት ወጣቶች የተለያየ የፖለቲካ አቋምና ርዕዮትን በመከተል እርስ በእርስ ወደ መከፋፈል የደረሱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በርካታ የወጣቶች ፓርቲ ተመስርቷል፡፡ ከተመሰረቱት የወጣቶች ፓርቲ ትልቁ ኮች ፓርቲ (Couch parts) የተባለ ነው፡፡ የወጣቶች አብዮት ሕብረት (Revolution youth union) ሌላኛው የወጣቶች ፓርቲ ሲሆን፣ አብዱላህ ሄልሚ የተባለው የዚህ ፓርቲ መሪም በተለያየ ጊዜያት ከወታደራዊ መንግስት ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያካሂዱና መልካም ግንኙነትም እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል በዕድሜ በገፉት ግብፃዊያን መካከልም ቢሆን ልዩነቶች ተፈጥረዋል - የአክራሪነት አቋምና የዘመናዊነት አቋም በመያዝ፡፡
በግብጽ በሚቀጥለው ለሚካሄደው የፕሬዝዳንት ምርጫ በርካታ ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ዋና ሊቀመንበር እና የኖቤል ተሸላሚ የነበሩት መሐመድ አልባራዲ ሲሆኑ፣ ሌላው በሙባረክ አስተዳደር ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት እንዲሁም የአረብ ሊግ ሊቀመንበር የሆኑት አመር ሙሳ ናቸው፡፡
የሙስሊም ወንድማማቾችን በመወከል የሚወዳደሩት ደግሞ በእስልምና አስተምህሮ  የጠለቀ ዕውቀት እንዳላቸው የሚታወቁት ጠበቃ ሃዘም ሳለ አቡ እስማኤል ናቸው፡፡
ከሙባረክ መንግስት ጋር ግንኙነት ያልነበራቸው ሌሎች ዕጩዎችም ቀርበዋል፡፡
የ74 ዓመቱ አመር ሙሳ እ.ኤ.አ ከ1991 እስከ 2001 ድረስ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉበት  ወቅት፣ በእስራኤል ላይ ባላቸው ጠንካራ ተቃውሞ ምክንያት ምናልባት ከፍተኛ ድምጽ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይገለፃል፡፡ ..በአንዋር ሳዳት የአስተዳደር ዘመን እስራኤል ከግብጽ ጋር እ.ኤ.አ በ1978 ያካሄደችው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት የእስራኤልን ጥቅም ብቻ ያስጠበቀ.. ነው በማለት በታህሪር አደባባይ ሙባረክን ለመቃወም በወጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ አመር ሙሳ ዛሬ እስራኤልን ይቃወሙ እንጂ የግብጽና የእስራኤል የሰላም ስምምነትን ካረቀቀው ቡድን ጋር ስምምነቱን አብረው ማዘጋጀታቸው ይታወቃል፡፡
እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ታላቅ ዲፕሎማት የነበሩት ኢስማኤል ፋሃሚ፣ አንዋር ሳዳት እ.ኤ.አ በ1977 በኢየሩሳሌም ታሪካዊ የተባለውን ጉዞ ሲያካሂዱ፣ በጣም ተበሳጭተው ነበር፡፡ ከእስራኤል ጋር የምናደርገው ስምምነት ግብጽ በአረቡ ዓለም ውስጥ ያላትን የበላይነት ያሳጣታል በሚል ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡  በዚያን ጊዜ የ41 ዓመት ጐልማሳ የነበሩት አመር ሙሳ፤ ከሳዳት ጋር በነበራቸው ወዳጅነት የሰላም ስምምነት እንዲካሄድ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
የዚህ የሰላም ስምምነት አላማ እ.ኤ.አ በ1967 እስራኤል ከአረቦች ጋር ባካሄደችው ጦርነት ከግብጽ የወሰደችውን የሲና በረሃ መመለስና በግብጽና በእስራኤል ዘላቂ የሠላም ስምምነት ማድረግ፤ በግብጽ በኩል እስራኤል ሉዓላዊ አገር መሆኗን አምኖ መቀበልን ያካተተ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የእስማኤል ፋሃሚ ስጋት አልቀረም፣ ግብጽና እስራኤል መስማማታቸው በርካታ አረብ አገራትን አስኮርፏል፡፡ ነገር ግን አረቦች ግብጽን የሚያክል ታላቅ አረብ አገር የበለጠ መቀየምና ከእርሷ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጥ ለእስራኤል የበለጠ ክፍተት መስጠትና ለእርሷ ጥቃት መጋለጥ መሆኑን በመረዳታቸው የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ከግብጽ ጋር ግንኙነታቸውን ቀጥለዋል፡፡
በሌላ በኩል አመር ሙሳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሆኑ፣ እስራኤል በዌስት ባንክና በጋዛ ሰርጥ አካባቢ ግዛቷን በማስፋፋት አይሁዳዊያንን ሠፋሪዎች በቦታው አስፍራበታለች፡፡ ይህ የእስራኤል እንቅስቃሴ ክፉኛ ያስቆጣቸው አመር ሙሳ፤ ከ30 አመት በፊት የኢስማኤል ፋሃሚ አቋም ትክክል እንደነበረ ተረዱ፡፡ በእስራኤል ላይ ያላቸው አቋም ተቀይሮ ወደ ጥላቻና ቁጣም ተለወጠ፡፡  
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአንድ ከፍተኛ የእስራኤል ዲፕሎማት ጋር በአለም አቀፍ የቴሌቪዥን ሚዲያ በቀጥታ በተካሄደ ክርክር በእስራኤል ላይ ባቀረቡት ነቀፋና ትችት ምክንያት በርካታ አረቦችን ያስደሰቱ ከመሆናቸውም በላይ የግብጽ ድምፃዊያን እርሳቸውን በማወደስ ዘፍነውላቸዋል፡፡ በተለይም ሻባን አብዱልራሚስ የተባለ ግብፃዊ ድምፃዊ፣ ..አና ባካራ እስራኤል.. (እስራኤልን እጠላታለሁ) ..አና ሁበክ አመር ሙሳ.. (አመር ሙሳን እወዳቸዋለሁ) በማለት አዚሞ ነበር፡፡ ሻባን ሙዚቃውን ካወጣ ከአንድ አመት በኋላ በአንድ የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ከአመር ሙሳ ጋር ተገናኝቶ ነበር፡፡ የተጫወተው ሙዚቃ ሙባረክን እንዳስከፋ ለአመር ሙሳ ከገለላቸው በኋላ፣ የግጥሙን ይዘት በማሻሻል ..ሙባረክንም እወዳለሁ.. በማለት አስተካክሎ አሳተመው፡፡ ይሁን እንጂ ለሁለተኛ ጊዜ የታተመው ሙዚቃ እንደመጀመሪያው አልተሸጠም ነበር፡፡ አለመሸጡን ያስተዋሉት ሙሳ፤ ሻባን ሚሊየነር ይሆን የነበረው የመጀመሪያው ሙዚቃ ብቻ ቢሸጥ ነበር በማለት ተናግረዋል፡፡
ናጊ ኤል - ጋትሪፍ ለአራት አመት የአመር ሙሳ ቃል አቀባይ ሆኖ ይሠራ የነበረ ሲሆን፣ ስለ አመር ሙሳ ሲናገር፣ ..እስራኤል በምታደርገው እንቅስቃሴ አመር ሙሳ የሚቃወመው ለማስመሰል ሳይሆን ከአንጀቱ ነው.. በማለት ተናግሮ ነበር፡፡
በእርግጥ የአመር ሙሳ ጽኑ አቋም የበርካታ ግብፃዊያንን ልብ ለመግዛት የቻለ ከመሆኑ ባሻገር Pew Research Center የተባለ ተቋም፤ ሙባረክ ከወረዱ ከሁለት ወር በኋላ ግብጻዊያን በእስራኤል ላይ ያላቸውን አቋም አሰባስቦ ነበር፡፡
በዚህ መሠረት 54 በመቶ የሚሆኑት በግብጽና በእስራኤል መካከል የተካሄደውን የሰላም ስምምነት የሚቃወሙ ሲሆን፣ 36 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስምምነቱ እንዳለ እንዲቀጥል የሚፈቅዱ ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ምንም አይነት ድምጽ አልሰጡም ነበር፡፡ አንድ ምዕራባዊ ዲፕሎማት ስለ ሙሳ ሲናገሩ፤ ..የአመር ሙሳ ታላቅነት ምንጩ ሙሳ የግብጽ ብቻ ሳይሆን ራሱን አረባዊ ብሔርተኛ ..ምስል.. እንዳለው አድርጐ በመመልከቱ ነው.. ሲሉ ገልጿቸው ነበር፡፡
ናጊ ኤል ጋትሪፍ አያይዞ ሲገልጽ፤ አመር ሙሳ ምናልባት በሚቀጥለው ምርጫ ቢያሸንፍና በግብጽና በእስራኤል መካከል የተካሄደው የሰላም ስምምነት እንዲቋረጥ ቢያደርግ አብዛኛው ግብፃዊ የሚከፋበት አይሆንም በማለት ተናግሯል፡፡
ይሁን እንጂ አመር ሙሳ የሚያስተቻቸውና የሚያስነቅፋቸው ነገር አልጠፋም፡፡ ሙሳ ምንም እንኳ በሙባረክ አስተዳደር ተቃውሞ በተነሳበት ወቅት ከሕዝባዊ አመፀኞቹ ጋር በመቀላቀል ሙባረክን የተቃወሙ ቢሆንም፣ ከአንድ አመት በፊት ከግብጽ ቴሌቪዥን ጋር በተካሄደ ቃለ መጠይቅ ሲናገሩ፣ ..ከሙባረክ ጋር እጅግ የጠበቀ ወዳጅነት አለን፤  እርሱን ከረጅም አመት በፊት እንደማውቀው ሁሉ ለምርጫ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ምን ማድረግ እንዳለበት በደንብ እገልጽለታለሁ፡፡ እኔም እርሱን ነው የምመርጠው.. በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ባለፈው ጥር ወር በስዊዘርላንዷ ከተማ በዳቮስ በተካሄደ አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ላይ አመር ሙሳ ተገኝተው ነበር፡፡ በወቅቱም በግብጽ ሕዝባዊ አመጽ የተቀጣጠለበትና ሙባረክ ከስልጣን እንዲወርዱ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ስለነበረ፣ አመር ሙሳ በስዊዘርላንድ ሆነው ወሬውን እንደሰሙ፣ ስብሰባው ገና ከመጀመሩ ጥለው ወደ ካይሮ ተመለሱ፡፡
ካይሮ እንደደረሱም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ግብፃዊያን የታህሪር አደባባይን አጨናንቀውት ነበር የደረሱት፤ ወዲያውም ለሙባረክ ስልክ በመደወል ስለ ሰልፈኞች ነግረዋቸው ነበር፡፡  
..ሚስተር ፕሬዝዳንት፣ ይህ አብዮት ነው፤ ምንም አይነት ደም መፋሰስ የለበትም፤ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የሚሉትን ሁሉ ይስሟቸው እና ምላሽ ይስጡ.. በማለት እንዳናገሯቸው ለሰልፈኞቹ ገልፀውላቸው ነበር፡፡  
ነገር ግን በርካታ ጋዜጦች ሙሳ ከሰልፈኞቹ ጋር ቢቀላቀሉም ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ ለውጥ እንዲመጣ እንጂ ሙባረክ ከስልጣን እንዲወርዱ መጠየቅ አይኖርባችሁም በማለት ለማግባባት ይሞክሩ እንደነበር ጋዜጦቹ ጠቅሰው ሙሳን በመተቸት ጽፈዋል፡፡
ሙሳም ምላሽ ሲሰጡ፤ ተቃዋሚዎቻቸው ያስወሩባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  
በሰኔ ወር በተካሄደ ጥናት፤ አመር ሙሳ 25 በመቶ ድምጽ ያላቸው ሲሆን፣ መሀመድ አልባራዲ ደግሞ 5 በመቶ ብቻ ድምጽ አግኝተዋል፡፡ የተቀሩት ተወዳዳሪዎች ደግሞ በጣም አነስተኛ ድምጽ እንዳገኙ ተገልል፡፡ በመጋቢት ወር አመር ሙሳ 40 በመቶ ድምጽ የነበራቸው ሲሆን፣ በሰኔ ወር ላይ ያገኙት ድምጽ መውረዱ ሲታይ፣ አመር ሙሳ በብዙ አቋማቸው የሚወደዱ ቢሆንም ለሙባረክ የነበራቸው ታማኝነትና ድጋፍ ግን የሚያገኙትን ድምጽ እየቀነሰባቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ 57 በመቶ የሚሆነው ግብፃዊ ምንም ድምጽ ያልሰጠ ሲሆን፣ ይህም የፉክክር መድረኩ በጣም ክፍት በመሆኑ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ጠንክረው እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ማርክ ያኒች ሲናገሩ፣ እስካሁን ያለው ውጤት ሙሳ እንደሚያሸንፉ የሚያሳይ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ግን አይደለም በማለት ገልዋል፡፡
ምዕራባዊያን በግብጽ እንደ ሙስሊም ወንድማማቾችና ሌሎች እስላማዊ ኃይሎች ስልጣን ከሚይዙ ይልቅ ለአመር ሙሳ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ የሚናገሩት ማርክ ያኒች፣ ነገር ግን በሕዝባዊ አመ የተሳተፉት ወጣቶች፤ የሙባረክ አገዛዝን የሚያስታውሳቸውን ሙሳን እንደገና ሊመርጡ ይችላሉ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ምናልባት አመር ሙሳ የሚያገኙት ድምጽ፣ በነሀሴ ወር እያሽቆለቆለ ከመጣ፣ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ሰፊ ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል የሚገል አሉ፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾቹ ፓርቲ ተወካይ የሆነው ሙሀመድ ሞርሲ ሲገልጽ፣ በሙባረክ አስተዳደር ወቅት እስላሞች አለአግባብ ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል፡፡ አሁን ግን ከፍተኛ የፓርላማ መቀመጫ የሚኖረው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ነው በማለት ገልጾአል፡፡
የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ከፍተኛ የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄደ ሲሆን፤ እስልምናን ለመምረጥ “Yes” የሚለውን ምልክት እንዲጠቀሙ ለደጋፊዎቹ አሳውቋል፡፡
በግብጽ ከወራት በኋላ ምርጫ ሊካሄድ ዝግጅት እየተካሄደ ባለበት በዚህን ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋምና ርዕዮት የበለጠ እየሰፋ መሄዱ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ ሕዝባዊ አመን ያካሄዱ ወጣቶች የታገልነው ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማምጣት ነው በማለት የእስልምና ሕግን ብቻ በግብጽ ለማስፈን ደፋ ቀን የሚሉትን እንደ ሙስሊም ወንድማማቾች ያሉትን እስላማዊ ኃይሎች ..ያካሄድነውን አብዮት ሊቀሙን አይገባም.. በማለት እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ከፍተኛ ድምጽ ያገኛሉ የተባሉት ግብጻዊው የኖቤል ተሸላሚ የተጠበቀውን ያህል አላገኙም፡፡ አመር ሙሳም ቢሆኑ ከሙባረክ አስተዳደር ጋር ባለችው ንክኪ ምናልባት አሁን ያላቸውን ድምጽም ሊያጡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ ግብጽ በአረቡ አለም ባላት ታላቅ ስምና ከእስራኤል ጋር ባላት የጂኦ ፖለቲካ ግንኙነት እንዲሁም በምዕራባዊያን ዘንድ ከሚሰጣት የላቀ ቦታ አንፃር በጥቅምት ወይም በህዳር ወር የሚካሄደው ምርጫ ከፍተኛ ትኩረትን መሳቡ የማይቀር ነው፡፡ ግብጽን ማን ይመራት ይሆን? የሚለውም ጥያቄ በዚያን ጊዜ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል፡፡

 

Read 5543 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 08:06