Sunday, 24 July 2011 07:52

አፈንጋጩ ጠቢብ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

ዘመኑ ርቆ እንኳ አሁንም ልቡ አጠገባችን ነው፤ ልባችንም ውስጥ እንደ ቁሌት ሽታው ያውዳል፤ ትውልድ ሁሉ ውስጥ ነበር - ወደዚህ ዓለም መጥቶ |Civil Disobedience´N ከፃፈ በኋላ፡፡ የዘመኑ ፈርጦች ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን፣ ናትናኤል ሃውቶርንና ሌሎቹም ጓደኞቹ በኮንኮርድ ጥሩ ጊዜ አጣልፈዋል፡፡

ጽፈዋል፡፡ አንብበዋል አስነብበዋል አሻራ አስቀምጠዋል!በሕንዳዊው ማህተመ ጋንዲ ሕይወትና በሕንድ ፖለቲካ ትልቅ ተጽእኖ የፈጠረ ሩስያዊው የዓለም ደራሲ ሌዎ ቶልስቶይም ..ቶሩ - አነቃቅቶኛል ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል.. ብሎ ያወደሰው ሰው ነው፡፡ እዚያ ብቻ አልቆመም፤ በአሜሪካዊው የጥቁር ሕዝቦች ታጋይ በማርቲን ሉተር ኪንግ ልብም ውስጥ ዳግመኛ ተወልዶ ነበር፡፡ አሜሪካ ውስጥ በማሳቹሴትስ ግዛት ኮንኮርድ የተወለደው ሄነሪ ዴቪድ ቶሩ ቤተሰቦቹ በአብዛኛው መምህራን ነበሩ፡፡ ወንድሙ ጆንና ሁለት እህቶቹ ሥራቸው መምህርነት ነበር፡፡ እናቱ ..ከተማረ ቤተሰብ የመጣሁኝ ነኝ.. የሚል ኩራት ያላት ሽርሽር የምትወድ፣ ዘናጭና አለባበስዋ ደስ የሚል ተናጋሪም ነበረች፡፡ ምግብ ስትሠራም ጣት የሚያስቆረጥም አይነት በመሆኑ ..ማን ይለካካኛል.. ስትል አያምጣው ነው፡፡ በብዙ ኩራት የተሞላችው ..ሚስ ቶሩ.. ልጆችዋ ጥሩ ትምህርት ቤት ገብተው መማር እንደነበረባቸው ታምናለች፡፡
ልጅዋ ሄነሪ ቶሩም ሀርቫርድ ለመግባት ዝግጅት አድርጐ ነበር፡፡ ላቲንና ግሪክም ተምሮ የሚያስፈልገው ሁሉ ተዘጋጅቶለት ስኮላርሺፕ ..ሺፕ አግኝቶ ገባ፡፡ መጽሐፍትን እጅግ ይወድድ ስለነበር ነፍሱ ትጠግብ ዘንድ ጊዜው ደረሰ፡፡ ሀርቫርድ ብዙ ደስ የሚለው ነገር አልነበረም፡፡ መጽሐፍት ግን ሞልቷል፤ የተማሪዎች ቀልድና ኩመካ ጣመው፡፡
ቶሩ መልኩ ሳቢ አይደለም፡፡ ቁመናው አጠር ያለ፣ ረጃጅም እጆችና እግሮች ያሉት፣ አፍንጫው ወደ ከንፈሩ ቁልቁል የተቆለመመ ነው፡፡ በዚያ ላይ አለባበሱም የሀርቫርድን ወግ የጠበቀ አልነበረም፡፡ ተማሪዎች ጥቁር መልበስ ሲገባቸው እርሱ አረንጓዴ ይለብሳል፡፡ ነገረ ሥራው ወፈፌ ነው፡፡ ፈገግታው ግን የዕብጠትና የበላይነት ይታይበት ነበር፡፡
ሀርቫርድ ውስጥ ግሪክ ላቲን፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ አጠና፡፡ ሂሳብና የሥነ ጽሑፍ ጥበብም እንደዚሁ፡፡ የሚነበበውን ብቻ ሳይሆን የማይነበበውን ሁሉ ጠራርጐ አነበበ፡፡ አንድ የእንግሊዝ ገጣሚ ግጥምም አልቀረው፡፡ በየመሀሉም ወደ ትውልድ ቀየው እየሄደ ተፈጥሮን ማድነቅ ቀጠለ፡፡ ተፈጥሮ ሚስቱ ናት፡፡ ያያታል፣ ያደንቃታል፣ ይዘምርላታል፡፡ አንዳንዴም ቀሚስዋን ይገልባል፣ ምስጢርዋን ያነብባል፡፡ ተራራ   ጡቶቿን፣ ሸለቆ ደረቷን፣ ወንዞች የሚፈስሱባት ጭኖቿን ያደንቃል፡፡ እርሱ የማይወድደው ከተማ ነው፡፡ ከአባቱ ጋር ኒውዮርክ እርሳስ ለመሸጥ ሄዶ በጣም አስጠላው፡፡ ለእርሱ ተፈጥሮ ከነድንግልናዋ ነው...
በልጅነቱ እሁድ እሁድ ቤተክርስቲያን ቀን ስለሚባል ማንም ልጅ ከቤት በማይወጣበት ጊዜ ከተፈጥሮ ጋር ማውራት ለምደዋል፡፡ በነፍሱ አቅፎ እሽሩሩ ማለት መሳም፣ ሱሱ ነበር፡፡ ከአበቦች ጋር መሣቅ፤ ከአእዋፋት ጋር መክነፍ፣ ከእንስሳት ጋር መጃጃል፡፡
ያደገበት ኮርኮርድም የጠቢባን ሠፈር ነበረች፡፡ ኤመርሰንን ጨምሮ ገጣሚያን፣ አሳቢዎችና ምሁራን የነበሩበት ናት፡፡
ሀርቫርድ ከገባ በኋላም የስኮላርሺፕ ተማሪዎች ገንዘብ የሚያገኙበት ጊዜ ይመቻችላቸው ስለነበር ሄነሪ ቶሩም ዕድል ገጥሞት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ያስተምር ነበር፡፡ ካስተማረባቸው ቦታዎች አንዱ ካንቶን ማስቹሴትስ ነው፡፡ ይህ ቦታ ታዲያ ለቶሩ የማይረሳ ብርቅ ጊዜና ጥሩ አጋጣሚ የሚለው አይነት ሆኖለታል፡፡ ብራውንሰን የተባለውን ብዙ ያልተማረ ግን ብዙ የሚያውቅ መምህር ያገኘው እዚህ ነበር፡፡ ይህንን ሰው ቶሩ እጅግ ወደደው፡፡ ከሀርቫርድ ተመሳሳይ ትምህርት ይልቅ የዚህን መምህር ብርቅዬ ሀሳቦች ተራበ፡፡ ብራውንሰንን ..ጥልቅ አሳቢ፤ የተሀድሶው ሰው.. ሲል አደነቀው፡፡ ሀርቫርድ የሚገኘው የተወሰነና የተለመደ መርህና ልምድ ሲሆን፣ ብራውንሰን ግን የለውጥ አዲስ ሀሳብና በተሻለ ዓለም ነፃ አስተሳሰብ እምነትና የጋለ ልብ ያለው ነው ይል ነበር፡፡
ከእረፍት የማስተማር ጊዜ በኋላ ሲመለስ፣ ቶሩ በትምህርቱ ላይ ልቡ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ብዙ ጉጉ መሆን አቃተው፡፡ ሕመምም ሞከረው፡፡ በዚህ ጊዜ መምህሩ ቶሩ ትምህርቱን የማሻሻል ፍላጐት እንደሌለው ለኮሌጁ ሪፖርት አደረገ፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶሩ አሁንም ሕብረተሰቡንና መዋቅሩን መተቸት አልተወም፡፡ ..መኖር ከተስማሚነቱ ይልቅ አስደናቂ፤ ከጠቃሚነቱ ይልቅ ውብ ነው፡፡.. ይል ስለነበር የነገሮች ሥርዓት እንዲለወጥ ይሻል፤ እናም አንድ ሰው ለመኖር በሣምንት አንድ ቀን ሠርቶ ሌላውን ቀን በተፈጥሮ ነፍሱን ማስደሰት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ከወንዝ ጋር እንዲዘምር፣ ከወፍ ጋር እንዲበርር ይጋብዛል፡፡
ሀርቫርድ በቸልተኝነቱ ሊያባርረው ሲል ጣልቃ የገባው ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን ነበር፡፡ ኤመርሰን ያኔ ቶሩን አያውቀውም ግን ስለቶሩ ሰምቷል፡፡ ጐበዝና ተመራማሪ እንደሆነ፡፡ እናም ለኮሌጁ ፕሬዚዳንት አጋዥ ደብዳቤ ፃፈ፡፡ ከሀርቫርድ ጨርሶ ሥራ ሲያጣም ከኤመርሰን አጋዥ ደብዳቤ ተጽፎለት ነበር፡፡ ምክንያቱም ቶሩ ከኮሌጅ ተመርቆ ከሁለት ሣምንታት በላይ መሥራት አልቻለምና ተባርሮ ነበር፡፡ የተባረረው በራሱ ጉዳይ አይደለም፡፡ በሕፃናት የቅጣት ሥነ ሥርዓት ባለመስማማቱ ነው፡፡ ቶሩ ሕፃናት በዱላ መቀጣት የለባቸውም ሲል፣ ትምህርት ቤቱና የትምህርት ቤቱ ኮሚቴ ተጋጩት፡፡ ስለዚህ ትቶላቸው ወጣ፡፡ ቶሩ በዱላ አያምንም፣ በምክርና በነፃነት እንጂ፡፡ በዚያ ላይ አንድ ሥራ ላይ ረጅም ጊዜ የማያቆይ አባዜ አለበት፣ ስልቹ ነው፡፡
ኤመርሰን በበኩሉ ከሀርቫርድ ከጨረሰ በኋላ ቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ትምህርት ቤት ከፍቶ ያስተምር ነበር፡፡ በዚያ ላይ የተወደደ ጠቢብ ነው፡፡ በተለይ ከፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን አገልጋይነት አሻፈረኝ ብሎ ከወጣ በኋላ በጥበቡ ረገድ ጨምሯል ይላሉ ፀሐፍት፡፡ እናም ወዲያውኑ ከታዋቂው ገጣሚ ዊልያም ወርድስ ወርዝና ከሌሎች የጥበብ ሰዎች ጋር ተገናኝቶ በመነቃቃት የተሻለ ውጤት አመጣ፡፡ ቶሩ ኤመርሰንን ይወደዋል፤ ያደንቀዋል፡፡
በዘመኑና ዛሬም ድረስ በአሜሪካ ግጥም ውስጥ ከሚታወቀው ዋልት ዊትማን ጋር ያገናኘውም እርሱ ነው፡፡ የዋልት ዊትማን ግጥም ተቀባይ ባጣ ዘመን አድናቆት ያሰጠው ለአዲስ ጥበብ ልቡ ክፍት የነበረው ኤመርሰን ነው፡፡ ቶሩ ለክርስትና እምነት አክብሮት የለውም ተብሎ ቢወቀስም ኤመርስንን ግን የእግዚአብሔር መንፈስ አብሮት ያለሰው ነው በማለት ያደንቅ ነበር፡፡ ጀምስ ፕሌይስትድ ውድ የተባሉት ፀሐፊ ስለ ኤመርሰን ሲናገሩ ..የወግ ፀሐፊ የነበረው ቶማስ ስተርሊን ማግኘትም እንዲነቃቃ አድርጐታል.. በርግጥም ጥሩ ፀሐፊ፣ አንደበተ ርቱእም ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ ሥነ-ሁፍ ተቆርቋሪ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ስለዚህም ከጐኑ ያሉትን ሁሉ ያበረታታል፡፡ ኤመርስን ..የኮንኮርድ ሰው.. እያለ የሚጠራው ሄነሪ ዴቪድ ቶሩ፤ በ14 አመት ያህል ታናሹ ቢሆንም ከኤመርሰን ጋር ኮከቡ ገጥሞ ነበር፡፡ ስለዚህም ኤመርሰንን ፍለጋ - መኖሪያቸውን ኮንኮርድ ካደረጉ ሰዎች ጋር በመሆን “Transcending club” በሚል መጠሪያ ክበብ አቋቁመው ነበር፡፡ በዚያው ክበብ ስም “The Dial” የሚል ስያሜ ያለው ተወዳጅ መሄት ማሳተም ጀመሩ፡፡ ይህም መሄት ለአራት አመታት ያህል በህትመት ዘለቀ፡፡ እዚያ ክበብ ውስጥ የነበሩ ሰዎችም “Simple living and high thinking” የሚል መርህ ነበራቸው፡፡ በቡድኑ ውስጥ ክርክርና ውይይት ይደረጋል፤ ግጥም ይነበባል፤ አዳዲስ ሀሳቦች ይንሸራሸራሉ፡፡ የራሳቸው አለም የራሳቸው ፀሐይ፣ የራሳቸው ሕግ ነበራቸው፡፡ የፍቅርና የጥበብ ሕግ ማለቴ ነው፡፡
በመጽሔቱ ላይ ቶሩ ስለ ኤመርሰን ፏል፤ ከካርሊሊ ጋር እያነፃፀረ ስለ ኤመርሰን ፍቅር፤ ጓደኝነት፤ ሀይማኖትና ገጣሚነት እንዲሁም ሃያሲነት ጠቅሷል፡፡ ታዲያ ከግጥምና ከሃያሲነት ችሎታው ይልቅ ሌሎች ችሎታዎቹ እንደሚበልጡ አሳይቷል፡፡ ኤመርስን ዛሬም ሲነበብ ስለ ግጥም የፃፋቸው መጣጥፎች ተአምር ያህል ናቸው - ውብና ጣፋጭ!
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጓደኛው ዴቪድ ሃስኪን እንደሚለው፤ ቶሩ ኮሌጅ በነበረ ጊዜ ድም አወጣጡ ሳይቀር የኤመርሰንን እየመሰለ ነበር፤ እንደ ኤመርሰን አይኑን እንደ መጨፈንም ያደርገው ነበር፡፡ ሃስኪን ሲቀልድ ..አፍንጫውም የኤመርሰንን ሊመስል ሞካክሮ አይቻለሁ.. ብሎታል፡፡ በንፋስ ሽውታ የዛፎች ቅርንጫፎች ዳንስ ነፍሱን የሚያስደንሳት ቶሩ፤ በአበቦች ውበት በወንዞች ዜማ የሰከረ ነበር፡፡ እርሻ ይወዳል፤ ገበሬ መሆን ግን አይፈልግም፡፡ የላሞች ድም ደወል ከቤተክርስቲያን መረዋ ይልቅ ይማርከዋል፡፡ ተፈጥሮን ከነድንግልናዋ ይወድዳል! ሳትነካካ... ሳትገሰስ፡፡ ሳይንስ እንደ ግጥም ይመስጠዋል፡፡ ብቻውን መሆን ይወዳል፤ አፈንጋጭ እንደሆነም ያውቃል፤ የሀርቫርድ ተማሪዎችም ይህንን ያውቃሉ፡፡ ..ሰው ከሰዎች ጋር ሲሆን ብቻውን ከሆነበት ጊዜ ይልቅ ብቸኝነት ይሰማዋል.. ይላል፡፡ በዚህ ሀሳብ ኤመርሰንም ይስማማል፡፡
የቶሩ ከተፈጥሮ ጋር መፋቀርና ብቸኛ የመሆን ምርጫ ወደ ዋልደን ጫካዎች እንዲገባ አድርጐታል፡፡ በዚያም በ28 ዶላር ከ12.5 ሳንቲም መኖሪያ ቤት ሰርቶ ለሁለት አመታት ከሁለት ወር ኖሯል፡፡ አንድ ማንኪያ፣ አንድ ቢላ፣ አንድ ሳህን ይዞ የሀርቫርዱ ምሩቅ በጫካ ውስጥ ሲፍና ሲያሰላስል ቆይቷል፡፡ ..ዋልደን.. የተባለው ጽሁፍም የዚህ ኑሮ ውጤት ነው፡፡
ኤመርሰን ወደ አውሮፓ ሲሄድ ቶሩ ቤት እንዲኖር አድርጐት ነበር፡፡ ይሄኔ ደግሞ ቶሩ መሐፉን የማሳተም ህልም አርግዞ ነበር፡፡ ግና በቀላሉ አልተሳካለትም፡፡ ኤመርሰን ለአሳታሚዎች ደብዳቤ ቢፍለትም አሳታሚዎች በቀላሉ አልተቀበሉትም፡፡ ሁሉም አሻፈረን አሉ፡፡ በኋላ ሄነሪ ዴቪድ ቶሩ የማይወድደውን ነገር አደረገ፡፡ ብድር ገብቶ የአበባ ስዕል ያለበት ቡኒ ሽፋን ያለው መሐፍ አሳተመ፡፡ ዋጋው አንድ ዶላር ከ25 ሳንቲም ነበር፡፡ “The week” ስለ ወንዞች ፍቅር፣ ስለደኑ፣ ስለመስኩ የሚያወራ መጽሐፍ፣ የማይገለጠውን የቶሩን ወንድም የጆንን ፍቅርም ይዞ ነበር፡፡ በቲቢ በሽታ የሞተው ወንድሙ ሰቀቀን፣ ቶሩን በእጅጉ ጐድቶት እንዳለፈ ይነገራል፡፡ “The Dial” በተባለው መሄት ላይ የታተሙት የቶሩ ግጥሞችም በመሐፉ ተካትተው ነበር፡፡
ገበያ ላይ የወጣው መሐፍ ግን አድናቂም መራቂም አላገኘም፡፡ የቶሩና የኤመርሰን ወዳጅ የሆነ አንድ ሰው፣ ኤመርሰን ስለ መሐፉ በመሄት ላይ እንዲፍ ጠየቀው፡፡ ኤመርሰን ግን ጓደኛው መሆኑ ስለሚታወቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፡፡ ይልቁኑ ጨካኝ የሚባለው ሃያሲ ሎዌል ወቀሰው፤ ደቆሰው፡፡ ቶሩ ይህንን ሁሉ ትዛዜ በሳቅ አሳልፎ በመንግስትና ሕብረተሰብ ልምድ ላይ ያለውን ተቃውሞ ቀጥሎ “Civil Disobedence”N በ1849 አሳተመ፡፡
ሕንዳዊው ማህተመ ጋንዲ በ1907 ዓ.ም አነበበው፡፡ ከዚያም ..ኢንዲያን ኦፒኒየን.. በሚለው መሔት ታተመ፡፡ ሕንዶች ለነፃነታቸው ተጠቀሙበት፡፡ አሜሪካዊያንም ለጥቁሮች ነፃነት ታገሉበት፡፡ ቶልስቶይ በፍቅር ወደቀበት፡፡ ኢትዮጵያዊያን በ1997 ዓ.ም ሞካከሩት፡፡ ሄነሪ ዴቪድ ቶሩም ከህብረተሰቡ ድድር ግድግዳ ጋር እየተጋጨ፣ እየደማ፣ ኖረ፡፡ ከዚያም በኋላ ቆይቶ ሞተ፡፡ ሀሳቡ ግን በሁላችንም ልብ ውስጥ ዛሬም እየፈሰሰ ነው... ሁፎቹም... ያወራሉ!... ትውልድም ያደምጣቸዋል... የተፈጥሮ ዜማ... የሕዝብ ቁስሎችና ውበቶች!...

 

Read 5696 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 07:54