Print this page
Sunday, 24 July 2011 07:29

የአገሬ ፖለቲካና የነጋሶ የሚያፈስ ጣራ

Written by  ልያስ
Rate this item
(0 votes)

በኮረኮንች በአባጣ ጎርባጣ የተሞላው የፖለቲካ መንገድ
ከቤቴ ልወጣ ስል ትጥቅና ስንቄን በቅጡ ማሟላቴን አረጋገጥኩ፡፡ መቅረፀ ድምና ማስታወሻ ደብተር ከጥሩ ብዕር     ጋር ይዣለሁ፡፡ የአንድ የፕሬስ ጋዜጠኛ ዋነኛ መሳሪያዎቹ እኒሁ ናቸው፡፡ የምሄደው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ አዳራሽ የሚያካሂዱትን ሁሉን አቀፍ ክርክርና በመጨረሻም የሚያወጡትን መግለጫ ለመዘገብ ነው፡፡

የፓርቲዎቹ ክርክር ለምን የመጀመርያው እንደተባለ አዕምሮዬ ላቀረበልኝ ጥያቄ ፈጣንና ሁነኛ ምላሽ በማጣቴ የፕሮግራሙን መርሃ ግብር በእጄ ከያዝኩት አዲስ መጽሐፍ (ሰሞኑን የወጣው ..የነጋሶ መንገድ..) መሃል አወጣሁና አፈጠጥኩበት፡፡ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጠኝም አንዳንድ ፍንጮችን አልነፈገኝም፡፡ ለምሳሌ የተሳታፊ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ተወካዮች ተካትተዋል፡፡ የዳያስፖራ ፖለቲከኞችን በተመለከተ በግርጌ ማስታወሻ ላይ የሰፈረው ደቃቅ ጽሁፍ ትኩረቴን ሳበው፡፡ ዳያስፖራ የተባለ ፓርቲ በቅርቡ የተቃዋሚዎችን ጐራ ለመቀላቀል ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ እየጠበቀ እንደሆነ ይገልፃል - ጽሁፉ፡፡ ወዲያው ትዝ ያለኝ ምርጫ ቦርድ ቢፒአርን ተግባራዊ በማድረግ ለአዳዲስ ፓርቲዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚፈጅበትን ጊዜ ወደ ሦስት ቀን ዝቅ ያደርጋል ተብሎ የተናፈሰው ወሬ (አሉባልታ) ነበር፡፡ በሦስት ቀን የፓርቲ ፈቃድ መስጠት ቦርዱን ፈጣን ወይም አዝጋሚ ያስብለው እንደሆነ ለመፍረድ የቀድሞውን አሰራሩን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደመታደል ወይም እንዳለመታደል ሆኖ እስከ ዛሬ የአዲስ ፓርቲዎች የፈቃድ ጥያቄ በምን ያህል ጊዜ ምላሸ እንደሚያገኝ አላውቅም፡፡ ለነገሩ ባውቅ ባላውቅ ምን ይፈይድልኛል አልኩኝና ወዲያው ግን ጋዜጠኝነቴ ትዝ አለኝ፡፡ መለስ ብዬ ደግሞ የመንግስት መ/ቤቶች ለመረጃ ምን ያህል ዝግ እንደሆኑ አሰብኩና የተነሳሳው የጋዜጠኝነት ስሜቴ ውስጤ ሲያንቀላፋ ተሰማኝ፤ የፈለገውን ያህል ጥይት ጋዜጠኛ ብሆን በብረት የተከረቸመ መረጃ እንዴት ፈልፍዬ ማውጣት እችላለሁ? የህዝብ ግንኙነቶቹ በዲሞትፈር ቢያስፈራሯቸውም መረጃ ..የሚደማቸው.. አይነት አይደሉም፡፡ በቢፒአር እስካሁን የታየ ለውጥ የለም፡፡ የአበሻ ጋዜጠኛ ተስፋ አይቆርጥም እንዲሉ እስቲ ደሞ በትራንስፎርሜሽኑ ይለወጡ እንደሆነ እናያለን፡፡
እኔ የምለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ከምን ደረሰ? አንድ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ዳያስፖራዎችን ሰብስቦ ሲያነጋግር፤ አንዱ ዳያስፖራ ..የትራንስፎርሜሽኑ ጐማ ተንፍሷል.. የሚል አስተያየት መስጠቱ ትዝ አለኝ፡፡ እንዲሁ እንደዛሬው በመሃከላቸው ተገኝቼ ነበር - ለመዘገብ፡፡ አስተያየቱን እንደሰማሁ ዳያስፖራውን ..ደፋር!.. አልኩት (ታዲያ በሆዴ ነው) ..መርዶ ነጋሪ!.. ልለውም ዳድቶኝ ነበር፡፡ ህሊናዬ ግን ..ተው! ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ልሁን አትበል!.. ሲል ገሰፀኝና አርፌ ተቀመጥኩ - (more catholic than the pope ነው ነገሩ) ይሄን ሁሉ የሀሳብ ድር ያደራሁት አእምሮዬ ለጠየቀኝ ጥያቄ መልስ ፍለጋ የፕሮግራሙ መርሃ ግብር ላይ አፍጥጬ ሳለ ነው፡፡ ሌላ ጊዜ እንዲህ ያለውን የታክሲ ላይ ረዥም ጉዞ የምሸውደው በንባብ ነበር፡፡ ..የነጋሶ መንገድ.. የሚለውን የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትን የህይወት (በአብዛኛው የፖለቲካ መንገድ) የሚተርክ አዲስ መጽሐፍ የያዝኩትም ለዚሁ ነው፡፡ ግን ግማሹ መንገድ በሃሳብ አለቀ፡፡ ቀሪውም በከንቱ እንዳያልቅ በመስጋት ቶሎ ብዬ መሃፉን ከፈትኩት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ..መቅደድ.. ጀመሩ - አስደማሚውን የፖለቲካ ታሪካቸውን፡፡ ትላንትና መጽሐፉን ማንበብ ስጀምር የጋዜጣው መግቢያ ላይ (የመንገድ መክፈቻ ይላል ርዕሱ) ያየኋት መስመር ማርካኝ ነበር፡፡ ..የነጋሶ መኖርያ ቤት ጣራ እንደ ፖለቲካው የሚያፈስ ነበር.. ይላል፡፡ ነገሩ በደንብ የገባኝ መጽሐፉን ሳጋምሰው ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ የማስታወቂያ ሚ/ር ሆነው በተሾሙ ጊዜ ዝናብ ሲጥል የቢሯቸው ጣራ አፍስሶ እንደነበር ጠቅሰው የዚያኑ ዕለት በኢቴቪ ዜናው እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ቀጣዩ የሚያፈስ ጣራ የገጠማቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ተሹመው ቤተመንግስት በገቡ ጊዜ ነው፡፡ (ለካስ yቤተመንግስትM ጣራ ያፈሳልና!) የሚያፈሰው ጣራ እስኪታደስ እዚያው ቅጥር ግቢ ወደ ጓሮ የተሰጣቸው ጊዜያዊ መኖሪያ ደግሞ ..የአይጥ መፈንጫ.. ነበር ይላሉ - ነጋሶ፡፡
እኔ መጽሐፉን አዘጋጅ ብሆን ኖሮ |yቤተመንግስት አይጦች ምን አይነት ናቸው?.. የሚል ጥያቄ ለዶ/ር ነጋሶ አነሳ ነበር፤ ምክንያቱም አይጦቹ እዚያው ነዋሪ ከሆኑ ከተራው የአይጥ ሠራዊት መለየታቸው አይቀርም ብዬ ነው፡፡ ቤተመንግስት ገብቶ የሚቆይ እንጂ እዚያው የሚቀር የለምና ፕሬዚዳንት ነጋሶም ከኢህአዴግ ጋር ..በማይረባ ነገር ተጋጭተው.. ቃል ኪዳናቸውን አፈረሱና በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው እንደለቀቁ ይነግሩናል - በመጽሐፋቸው፡፡ የሚያፈስ ጣራ የሚከተላቸው የሚመስሉት ነጋሶ፤ መንግስት የጡረታቸው አካል አድርጐ ..ያሻራቸው.. የመኖርያ ቤት ጣራም ዝናብ ሲዘንብ ያፈስ እንደነበር መሃፉን ላዘጋጀው ጋዜጠኛ ዳንኤል አውግተውታል፡፡ በዚህም ቢበቃቸው ጥሩ ነበር፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጣቸውም ሰፊ ግቢ ያለው ትልቅ መኖርያ ቤት ጣራው የሚያፈስ መሆኑን ተናግረዋል (እዚሁ ጋዜጣ ላይ ዜናው መዘገቡንም አስታውሳለሁ) እውነትም ጋዜጠኛው ጥሩ አስተውሏል፡፡ የነጋሶ የፖለቲካ ህይወትና መንግስት የሚሰጣቸው መኖሪያ ቤት ጣራ ሲያፈስ ነው የኖረው፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መቼ ደህና ጣራ ተገጥሞለት ያውቅና ነው? በራሴ ሃሳብና በመሃፉ ተወስጄ መውረጃዬን እንዳለፍኩ ያወቅኩት ወያላው ..ደንበኞቻችን የዛሬው ፕሮግራም በዚሁ ተጠናቋል.. ብሎ ሲሳለቅብኝ ነው፡፡ ለካስ ተሳፋሪው ሁሉ ወርዶ የቀረሁት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ከታክሲው ስወርድ ደግሞ የጉዞው የመጨረሻ ጣቢያ ድረስ መምጣቴን ተረዳሁ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ስንት አመት የተጓዙበትን ጐርበጥባጣ የፖለቲካ መንገድ እኔ በአንዴ ፉት ልላት በመቋመጤ የተፈጠረ ነው በሚል ግለ-ሂስ ሰጥቼ በሌላ ታክሲ የመልስ ጉዞ አደረኩኝ፡፡ የነጋሶን የፖለቲካ ታሪክ ሳነብ ወቅታዊው የፖለቲካ ሁነት (የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያካሂዱትን ውይይት) ሊያመልጠኝ ነበር ስል በራሴ ላይ ቀላለድኩና ሰዓቴን ስመለከት ትንሽ ተጽናናሁ፡፡ መርሃ ግብሩ እንደሚለው ውይይቱ የሚጀመረው 9 ሰዓት ላይ ነው፤ አሁን ገና 8፡30 ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ታሪክ ሊያጠኑ ወደ ጀርመን ሲሄዱ ቦሌ አየር ማረፊያ የሸኛቸው ዲማ ነገዎ ያላቸውን በመጽሐፉ አስታውሰዋል ..አንተ ሂድና ታሪክ ተማር፤ እኛ ታሪክ እንሰራለን.. ማናቸው ታሪክ እንደሰሩ ፍርዱን ለታሪክ ባለሙያዎች (ተመራማሪዎች) ትተን እንለፈው፡፡ የአራት ኪሎ ቤተመንግስት መግቢያ በር ላይ በርቀት ግርግር ተመለከትኩና ውይይቱ ገና አለመጀመሩ ስለገባኝ እርምጃዬን ቀነስኩ፡፡ እየቀረብኩ ስሄድ ግን አንድ ቦታ ተሰብስቦ የቆመ የመሰለኝ የሰው ግርግር ወደተለያዩ አቅጣጫዎች እየተበታተነ መሆኑን ተረዳሁኝ፡፡ አሁንም ለሌላ ጊዜ ተላለፈ ማለት ነው - አልኩኝ ለራሴ፡፡ እንዳሰብኩት ከሆነ ለሦስተኛ ጊዜ መተላለፉ ነው ማለት ነው፡፡ ወደ ቤተመንግስቱ በር ልደርስ ትንሽ ሲቀረኝ የማውቃቸውን የግሉ ፕሬስ ጋዜጠኞች (በድሮ ስማቸው ..በሬ ወለደ.. ወይም Gutter press) አገኘሁና ወደ ውስጥ ተያይዘን ዘለቅን፡፡
በመድረኩ ላይ የሚታወቁም የማይታወቁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሰይመዋል፡፡ በቅርቡ በይፋ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚሆነው የዳያስፖራ ፓርቲ ተወካዮችም ተደርድረዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ..ኢህአዴግ.. የሚለውን ስሙን አሳንሶ ..አውራ ፓርቲ.. የሚለውን ቅጽል ስሙን አጉልቶ ቀርቧል፡፡ የመድረኩ መሪ የእለቱን የውይይት (ክርክር) ርዕስ ሲያስተዋውቅ ..ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲÃêE ሥርዓት አለመዳበር ሰበቡ ምንድን ነው?.. የሚል እንደሆነ ከተናገረ በኋላ እንደ ፓርላማው አፈ-ጉባኤ ከተወሰነው የንግግር ጊዜ ማለፍ እንደማያስቀጣ አስታውቆ የመጀመርያ እድሉን ከ2002 ምርጫ በኋላ ራሱን ..አውራ ፓርቲ.. ብሎ ለሰየመው ኢህአዴግ ሰጠው፡፡ (አንዳንዴ ኢህአዴግ ራሱን አውራ ያለው አባወራ ለማለት ይሆን እላለሁ) የኢህአዴግ ካድሬዎች እየተፈራረቁ ለአገሪቱ ሰራንላት ያሉትን ልማትና ግንባታ ከዘረዘሩ በኋላ በአገሪቱ ዲሞክራሲÃêE ሥርዓት እንዳይዳብር ያደረገው ደርግ እንደሆነ በመጥቀስ እንደ ጉድ ወረዱበት፡፡ በመቀጠል ተራው የዳያስፖራ ነበር፡፡ ለዲሞክራሲ ሥርዓቱ አለመዳበር ዋናው ሰበቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው በማለት ተጠያቂ አድርጐ ወነጀላቸው፡፡ ምክንያቱን ሲገልም በጋራ ተባብረው ገዢውን ፓርቲ ከማዳከም ይልቅ እርስ በርስ መናቆራቸውንና መጠላለፋቸውን አስቀመጠ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የክርክር አቋም በሁለት ጐራ ሊከፈል ይችላል፡፡ አንደኛው ጐራ ዲሞክራሲ ላለመዳበሩ ተጠያቂው ራሱ ገዢው ፓርቲ ነው ሲል ..አውራውን ፓርቲ.. ነቀፈ፡፡ ሁለተኛው የተቃዋሚ ጐራ ግን ብዙዎችን ያስገረመ በአይነቱ ለየት ያለ ሊሰኝ የሚችል አቋሙን በይፋ ተናገረ - ለዲሞክራሲ ሥርዓቱ አለመዳበር ሰበቡ ራሱ ህዝቡ ነው አለ - በድፍረት፡፡
እኔ ይሄን እንደሰማሁ ብልጭ ብሎብኝ ነበር፡፡ በእጄ ላይ የነበረውን ቴፕ ወደ ተቃዋሚዎቹ ልወረውር ምንም አልቀረኝም - ሆኖም በደህና ጊዜ አንዱ ጥግ የወሸቅኳትን ቁራጭ ትዕግስት ተጠቅሜ ራሴን ዲሞክራሲÃêE እንቅስቃሴ እንደምንም መግታት ቻልኩኝ፡፡ ሰይጣን አሳስቶኝ መቅረፀ ድምፁን ወደ መድረኩ ብወረውር ኖሮ ጆርጅ ቡሽ ላይ ጫማውን እንደወረወረው ጋዜጠኛ እታሰር እንደሆነ ባላውቅም |ለዲሞክራሲW አለመዳበር ሰበቡ ህዝቡ ነው.. ላሉት ውንጀላ ጥሩ ማስረጃ እሆንላቸው እንደነበር ፈሞ አልጠራጠርም፡፡
የምሰራበት ጋዜጣ ቢሮ ስገባ የሥራ ባልደረባዬ አግኝቶኝ በጥያቄ አጣደፈኝ፡፡ የማይቀርልኝ መሆኑን ስረዳ የቻልኩትን ያህል አጠር አድርጌ በአራት ኪሎ ቤተመንግስት በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉትን ነገርኩት፡፡ ትክ ብሎ እያየኝ በጥሞና ሲያዳምጠኝ የቆየው የሥራ ባልደረባዬ በምን አይነት ፈጣን ጀት ኮሎምቢያ እንደገባ አላውቅም፡፡ ከኮሎምቢያ የቆዳ ምርት ውጤቶችን ይገዙ የነበሩ የውጭ ነጋዴዎች የምርቱ ጥራት በየጊዜው እየቀነሰ መምጣቱ ያሳስባቸውና ችግሩን ለመመርመር ኮሎምቢያ ድረስ መጥተው ባለድርሻ አካላትን ያነጋግራሉ፤ መጀመሪያ የሄዱት የቆዳ ጃኬትና ጫማ አምራቾች ጋር ሲሆን ለምርቱ ጥራት መቀነስ ምክንያቱን ሲጠይቁ ጥፋቱ ያለው ከቆዳ አልፊዎቹ እንደሆነ ተነገራቸው፡፡
በቀጥታ ቆዳ አልፊዎቹ ጋር ሄደው ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እዚህም ጥፋቱ የእኛ አይደለም ተባሉ፡፡ ታዲያ የማነው? ብለው ጠየቁ፡፡ የቄራዎቹ ነው አሉ - አልፊዎቹ፡፡ ..እነሱ ለሥጋው እንጂ ለቆዳው ግዴላቸውም.. ከሚል ወቀሳ ጋር፡፡ ሰዎቹ አልታከቱም፡፡ ቄራ ሄዱ፡፡ ቄራዎቹ ደግሞ ጥፋቱ ያለው አርቢዎቹ ጋ ነው የሚል ምላሽ ሰጧቸው፡፡ አሁን በአንድ ነገር እርግጠኛ ነበሩ፡፡ አርቢዎቹ ወደ የትም ጣታቸውን ሊቀስሩ አይችሉም ብለው ተማምነዋል፡ እዚያ እንደደረሱ ግን እምነታቸውን የሚያፈራርስ ምላሽ አገኙ፡፡
..ለቆዳው ጥራት መቀነስ ተጠያቂዎቹ ከብቶቹ ራሳቸው ናቸው.. አሉ - አርቢዎቹ
..እንዴት?.. ግራ ተጋብተው ጠየቁ ሰዎቹ
..ሽቦ ላይ እየሄዱ ይታከካሉ.. የአርቢዎቹ ምላሽ ነበር፡፡
የሥራ ባልደረባዬ ይህቺን የኮሎምቢያ ግሩም ምሳሌ ከየት እንዳገኛት ስላልነገረኝ እኔም ምንጭ መጥቀስ አልቻልኩም፡፡ ምንጭ ላለመጥቀሴ ግን ተጠያቂው ወይም ጥፋተኛው የሥራ ባልደረባዬ እንደሆነ እወቁልኝ፡፡
ማስታወሻ - በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያካሄዱት ክርክር በእውን የተካሄደ ሳይሆን ምናብ ወለድ መሆኑን ልገል ፈለግሁና በእውን ቢካሄድ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ህሊናዬ ሹክ ሲለኝ ሃሳቤን ገታሁት፡፡

 

Read 3819 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 07:36