Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 24 July 2011 07:08

ልጅና ቀራጭ ችግር አያቅም!..

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አንድ ልብስ ሰፊ ይሄዳል፡፡ ከዚያም፤
..ይሄውልህ ይሄን ምን የመሰለ ሙሉ ሱፍ እንደተሰፋ ገዝቼ እጅጌው ረዘመብኝ፡፡ ስለዚህ ይሄንን
እጅጌትንሽ እንድታሳጥርልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ይመስልሃል?.. ሲል ይጠይቀዋል፡፡..
ልብስ ሰፊውም፤ ..የለም ይሄ ማሳጠር ላያስፈልገው ይችላል፡፡ ዝም ብለህ ክንድህን እዚህ እክርንህ ጋ አጠፍ ማድረግ
ነው፡፡ አየኸው እጅጌህ ወደ ውስጥ እንደገባ?.. ይለዋል፡፡

ሰውዬው የተባለውን ካደረገ በኋላ በመስታወት ሲያየው ኮሊታው ደሞ ወደ ማጅራቱ ተሰቅሏል፡፡
ስለዚህ፤
..ኮሊታዬ ደግሞ አላግባብ ወደ ማጅራቴ ወጣብኝ ይሄው ግማሽ ጭንቅላቴን ሸፈነውኮ! ምን ይሻላል?..
ሲል ጠየቀው፡፡
ልብስ ሰፊውም፤ የሰውዬውን ጭንቅላት ወደ ኋላ ቀና እያደረገ፣ ..በቃ ጭንቅላትህን ወደ ኋላ እንዲህ
ቀና አድርገህ ስትለጥጠው ልክ ይገባል.. ይለዋል፡፡
ሰውዬው፤
..አሁን ደግሞ ግራ ትከሻዬ በሶስት ኢንች ያህል ከቀኝ ትከሻዬ ወደ ታች ወረደ..
ልብስ ሰፊው፤
..ችግር የለም፡፡ ከወገብህ በኩል ወደ ግራ ጠመም በል፡፡ ልክ ይገባል፡፡.. ሰውዬው እንደተባለው ወደ ግራ
ከወገቡ ተጣመመ፡፡
ልብስ ሰፊውም፤
..አሁን ትክክል ሆነሃል፡፡ ሱፉም ልክክ ብሏል፡፡ ገንዘብህን ከፍለህ መሄድ ትችላለህ.. አለው፡፡
ገንዘቡን ከፍሎ ሲወጣ የሰውዬው ቅር እጅግ አስገራሚ ሆነ፡፡ የግራ ክርኑ ተንጋዶ ወደ ወጪ ወጥቷል፡፡
ጭንቅላቱ ወደ ኋላ ተገትሯል፡፡ ወገቡ ወደ ግራ ጥምም ብሏል፡፡ ለመራመድ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ
ግራና ቀኝ እግሩን እያጠላለፈ እየተወለጋገደ ነው፡፡
እንዲህ እየተወለጋገደ በመሄድ ላይ ሳለ ሁለት መንገደኞች ያዩታል፡፡ አንደኛው፤
..ያን ምስኪን ሽባ ሰውዬ ተመልከተው፡፡ አንጀቴን ነው የበላው፡፡ አያሳዝንም?..
ሁለተኛው፤
..ያሳዝናል፡፡ ግን በጣም የሚደነቀው ልብስ ሰፊው ነው፡፡ ይሄ ሱፍ ልብስ ለዚህ ውልግድግድና ጥምም
ላለ ሰው እንዲስማማ አድርጎ ሙሉ ሱፍ እንዲለብስ ማድረግ ትልቅ ጭንቅላት ይጠይቃል፡፡ ያ ልብስ ሰፊ
ሊቅ መሆን አለበት!!.. አለ፡፡

ምሁራን ሆኑም አልሆኑም፣ ፖለቲከኞች ሆኑም አልሆኑም፣ ቀራጮች ሆኑም አልሆኑም ባለሙያዎች ሆኑም አልሆኑም፤ እጅጌ ለማስተካከል ሰውዬውን አጣመው መልቀቃቸው ደግ ነገር አይደለም፡፡ ስህተት ለማረም ሌላ የተጣመመ ስህተት መሥራት የለብንም፡፡ ክርኑን ለማዳን አንገቱን መገተር፣ አንገቱን ለማዳን ወገቡን ማጣመም፤ በመጨረሻም ሰውዬው እንዳይራመድ አርጎ ማሽመድመድ ከቶም አያሳድገንም፡፡ አንድ የአገራችን ፀሃፊ እንዳለው፤
..የአበሻ ንግድ
የሌላውን ሥራ ማሽመድመድ፡፡
የአበሻ መኪና አነዳድ
በሌላው መንገድ መገድገድ፡፡.. እንዳይሆን ነገረ-ሥራችን፤ ቀና እንሁን፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሚከተን፡፡ ሌሎች ካላለቀሱ እኔ አልስቅም ዓይነት አስተሳሰብ ቢያንስ ሳዲዝም ነው - በሌሎች ሥቃይ መደሰት፡፡ ሁሉን ጥቅም በሀሰት ሰነድ፣ በአየር - ባየር ገፈፋ ካላገኘሁ የሚል ስግብግብ እንዳለ ሁሉ ንፁህ ነጋዴ መኖሩን በቅጡ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡  ለሀገር በሚጠቅም መንገድ ሂሳቡን የሚሠራ ቢሮና ሠራተኛ እንዳለ ሁሉ፣ ያለማምታታትና ያለግል ኪስ የማይንቀሳቀስ መኖሩንም ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ የመንግሥት ላይሆን እንደሚችል ሁሉ፤ የግልም የግል ላይሆን ይችላል፡፡ በአገራችን የቤት ልጅ መበደልና ..እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን ማረጋገጥ.. የተለመደ ነገር ነው፡፡ ..እያንዳንዱ ትውልድ የዱላ ቅብብል የሚጫወትበት እያልን..  የአንድ ትውልድ ብቻ መጫወት እንዳናደርገው መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለገቢ ፍትሐዊነት እየተናገርን ገቢውንም ፍትሁንም እንዳናጣ እናስብ፡፡ The Holy Roman Empire was neither Holy nor Roman nor an Empire እንደተባለው እንዳይሆን (የተቀደሰችው የሮማ ግዛተ - ነገሥት፤ ቅድስትም፣ ሮማዊም፣ ግዛተ - ነገሥትም አልነበረችም፤ እንደማለት ነው)
ታዋቂው ፀሀፌ - ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን በአንደኛው ተውኔቱ ውስጥ ..አንዲት የዱር አውሬ፣ ልጅ በመውለጃዋ ሰሞን ልን ትበላለች አሉ፣ ምጥ የጠናባት እንደሆን.. የሚለን ለዚህ ነው፡፡
መልካም እንቅልፍ ለመተኛት መልካም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከግፍ መራቅ ያሻል፡፡ ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ ሸር መራቅ ይገባል፡፡ በፈረንጅ አገር አንድ ሰው ለአገሩ አገር ውስጥ ገቢ እንዲህ የሚል ማስታወሻ ፎ ነበር :- ..የከፈልኩትን ታክስ አጭበርብሬ የከፈልኩ ስለሆነ እንቅልፍ መተኛት አቃተኝ፡፡ ገቢዬን ዝቅ አድርጌ አስገምቼ ነው፡፡ ስለዚህ የ150 ዶላር ቼክ ልኬላችኋለሁ፡፡ ይህም ሆኖ እንቅልፍ እምቢ እሚለኝ ከሆነ ግን ቀሪውን እልክላችኋለሁ፡፡..
ቼኩን በእጁ ያስገባው፤ የአገር ውስጥ ገቢ ሠራተኛውም ..እኔም ቀሪዋን እስክትልክ እንቅልፍ የሚወስደኝ አይመስለኝም.. ብሎ ፃፈለት፡፡ እንቅልፍ ከሚያሳጣ ዘመን ይሰውረን! አንድ የኢትዮጵያ አጎት ደግሞ የእህታቸው ልጅ ይሄንንም ግዛ ይሄንንም ግዛ እያለ  ..አዬ፤ ልጅና ቀራጭ ችግር አያቅም.. አሉ ይባላል፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርብን፡፡

 

Read 6858 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 07:12