Saturday, 01 December 2012 11:51

ካምፓስና ህይወት

Written by  በሱራፌል መካሻ
Rate this item
(32 votes)

“ልጆች እኔ የሳይኮሎጂ መምህር ነኝ:: እያንዳንዳችሁ በአሁኗ ሰአት ምን እያሰባችሁ እንደሆነ፣ ምን አድርጋችሁ እንደነበር ፣ ከፈለጋችሁም ቁርሳችሁን ምን በልታችሁ እንደመጣችሁ ልነግራችሁ እችላለሁ:: ማነው የሌላ ሰው ስም የጻፈው? ...ጆሮህን ጠምዝዤ ሳላወጣህ ራስህ እኔ ነኝ ብለህ ውጣ!!!” ልቤ ድው ድው ማለት ጀመረ:: በቀዝቃዛው ጠዋት ወበቀኝ:: ግርግር በበዛበት ላይብረሪ ውስጥ ተቀምጫለው:: እኔ ከተቀመጥኩበት ወንበር ፊት ለፊት ትልቅ ጠረጴዛ አለ:: ጠረጴዛው በ1960ዎቹ እንደተሰራ ይነገራል:: በጠረጴዛው ላይ ይሄንን ያህላል ብዬ ለመናገር ቃላት ያጣሁለት ትልቅ መጽሀፍ ተቀምጧል::

ሰውየው ግን ጤነኛ ነው? ማለቴ ይሄንን መጽሀፍ የጻፈው ሰውዬ? ነገሩ ለጽድቅ ነው እንዴ? የተለያዩ ሀሳቦች አእምሮዬን እያስጨነቁት ነው:: ግን ማጥናት አለብኝ:: ምክንያቱም ከ2 ቀናት በኋላ ግራ የገባቸው የዩኒቨርሲቲያችን ምሁራን ቀድመን ብንጠይቃቸው ራሳቸው እንደሚመልሷቸው የምጠራጠራቸውን ጥያቄዎች በፈተና መልክ አቅርበው ፈተና ላይ ትምህርት ይሰጡናል:: “ኤፋችንን” ያከናንቡናል::
ካቀረቀርኩበት ቀና ብዬ መመልከት ጀመርኩኝ:: ብዙው ተማሪ አምሯል (‘ም’ ይጠብቃል):: ከወገቡ ሳይሆን ከአንገቱ አጎንብሶ “ገ” ሰርቶ ይቸክላል:: ለነገሩ እንኳን “ገ” “ቀ” ሰርቶ ቢያጠና አይገርምም፤ ምክንያቱም ከነገ ወዲያ ፈተና ነው:: ከእኔ ጠረጴዛ ፊት ለፊት የተቀመጠው ቴዲ ዝም ብሎ ይቁነጠነጣል:: ምንድነው የሚያቁነጠንጠው ብዬ ዞር ብዬ ባይ ራሴ መቁነጥነጥ አማረኝ:: ጸጉሯን ወደ ፊት ለፊቷ የደፋች ፣ ጆሮዎቿ ላይ ከመኪና ጎማ የሚሰፉ ብረቶችን ያጠለቀች፣ ከንፈሯን በቀይ ቀለም የጀቦነች ፣ ከአፍንጫዋ መጣመም ውጭ ይሄ ቀረሽ የማይሏት ልቅም ያለች ቆንጅዬ ልጅ ዳር ላይ ተቀምጣለች:: በነገራችን ላይ ቴዲን የማውቀው የዛሬ አመት አካባቢ በአንድ ታክሲ አብረን እየሄድን ነጠላ ዜማውን የለቀቀ ሰዐት ነው:: በቃ ድንገት ተነስቶ አለቀሰ:: የለቅሶው መልእክት ባጭሩ ‘እርዱኝ አለበለዚያ እራሴን አጠፋለው’ የሚል ነበር:: እኔና በታክሲዋ ውስጥ የነበርነው አንዳንድ አሮጊቶች ምንድነው ብለን ብንጠይቀው እያለቀሰ በጋቢናው ውስጥ የተቀመጠችውን ቆንጆ ኮረዳ ለመተዋወቅ መፈለጉን ነገረን:: እኔም ለሹፌሩ እንዲያቆም ነግሬው ለልጅቷም ካልተዋወቃት ራሱን ሊያጠፋ እንደሚችል አስረድቻት አስተዋወቅኋቸው:: እናም በህይወቴ የማልረሳውን አንድ ቁምነገር ሰራሁ:: የሰው ነፍስ አተረፍኩ!!! ከዛ በኋላ ከቴዲ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ችለናል:: እሱ ግን ያ አመሉ አለቅ ብሎት አሁንም አሁንም ይቁነጠነጣል:: የሚነበበውን መጽሃፍ ትቶ የማትነበበውን እሷን ለማንበብ ይሞክራል::
ከቴዲ ጎን ካለው ጠረጴዛ ላይ በቅጽል ስሟ “ክሊዎፓትራ” በመባል የምትታወቀው “ከበቡሽ” ተቀምጣለች:: በነገራችን ላይ ቅጽል ስሟን ያወጣችው ራሷ እንደሆነች አንዳንድ የግቢያችን አሽሟጣጮች እያሽሟጠጡ ይናገራሉ:: ክሊዎፓትራ የመጣችው “ሁለት እጁ’ነሴ” ከሚባለው አካባቢ ሲሆን ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ምዝገባ ላይ ‘አካባቢ’ የሚለው ላይ “two hand cut” ብላ ድንቅ ታሪክ የሰራች ናት:: ዩኒቨርሲቲ በገባች በአመቱ ያደረገችው የመጀመሪያው ነገር የተለያዩ የእናቷንና የራሷን ቀሚሶች እንዲሁም የአባቷን ጋቢዎች ለእኔ ቢጤዎች ማከፋፈል፣ ሁለተኛው ለራሷ ቅጽል ስም ማውጣት ፣ ቅቤ መቀባት ማቆም ፣ ፊቷን ፓውደር መቀባት መጀመር:: ክሊዎፓትራ ደብተሯን ፊቷ አስቀምጣ ታብሰለስላለች:: ምን ሆና ይሆን? ውይ ረስቼው ለካ ሰሞኑን ናቲ የሚባለውን ሙዚቀኛ እንዳፈቀረች እየተናፈሰባት ነው::የሙዚቃ ክሊፕ ማየት የጀመረችው በቅርቡ ስለሆነ አልፈርድባትም:: ፌስ ቡክ ሁልጊዜ እንጠቀማለን የሚሉት እነ ቲቲ አሉ አይደል… እስካሁን ማይክል ጃክሰን አልሞተም እያሉ የሚከራከሩት:: ምንድነው ግን እየሰራው ያለሁት? ለምንድነው የማላጠናው?አእምሮዬ አልረጋጋ ስላለኝ ባዶዬን ከምቆዝም ሻይ እየጠጣሁ ብቆዝም ይሻላል በሚል ወደ ላውንጃችን ሄድኩኝ::
ላውንጃችን ልትወድቅ አንድ እሁድ የቀራት ናት( ዛሬ ቅዳሜ ስለሆነ ነው):: በሁለት ቆርቆሮ፣ በአራት አጣና እና በአንድ ማዳበሪያ ጭቃ ቤት መስራት እንደሚቻል ያሳየን የመጀመሪያው ሰው የላውንጃችን ባለቤት ነው::
ቁጭ ብዬ ስኳር የሚያንሰውን ሻይ ስኳር ማስጨመር ስለማይቻል ብቻ በግድ እየተጋትኩት ሳለ፣ ሰው በምግብ ብቻ እንደማይኖር ያረጋገጡልን ኮስማናውና መላጣው መምህራችን ፕሮፌሰር ጣሰው፣ የአማዞን ጫካ የመሰለውን ጺማቸውን እያፍተለተሉ ወደ ላውንጃችን ገቡ:: አጠገቤ ቁጭ ካሉ በኋላ ከትቢያቸውም ሳይቆጥሩኝ ወደ አስተናጋጁ ዞረው
“ና እስኪ አስተናጋጅ ........ አንድ አጥሚት አምጣልኝ” አሉት:: አስተናጋጁ ለመሳቅ ቢዳዳም ክብር መስጠት እንዳለበት ስለተረዳ የሚሸጥ አጥሚት እንደሌለና አጥሚት ለመግዛት በመሞከር የመጀመሪያው ሰው እሳቸው እንደሆኑ በመግለጽ ስማቸው በUNESCO በቅርስነት እንዲያዝ ለማድረግ በትጋት እንደሚሰራ ሊነግራቸው ካሰበ በኋላ ሃሳቡን ትቶት “የለም” በማለት አቆመ::
ፕሮፌሰር አንድ ሁለቴ ካሳሉ በኋላ “ ታዲያ ለጉንፋን የሚሆን ምን አላችሁ?” ሲሉት እኔም አጋጣሚውን ተጠቅሜ ማንነቴን ላሳያቸው በማሰብ “ ቀሽር ጥሩ ነው ፕሮፌሰር” አልኩኝ:: “በል ጎሽ ቀሽር አምጣልኝ” ካሉት በኋላ ወደ እኔ ዞረው ወሬ ጀመሩ::
“መነጽሬን ስላላደረኩ አልለየሁህም እንጂ ተማሪዬ እንደሆንክ እርግጠኛ ነኝ” አሉኝ:: እኔም የልብ ልብ ተሰምቶኝ ከአፋቸው ቀበል አድርጌ “አዎን ፕሮፌሰር የሶስተኛ አመት ተማሪዎ ነኝ” አልኩኝ ደረቴን ነፋ አድርጌ:: “እና ከነገ ወዲያ ፈተና ተቀምጦልህ ዛሬ እዚህ ከኔ ጋር ወሬህን ትቀዳለህ?” እየተናደዱ ጠየቁኝ::
“አይ ፕሮፌሰር...”
“አይ ይለኛል እንዴ?ምን አይነት ጠማማ ትውልድ ነው ያለው ባካችሁ? እኛ በናንተ እድሜ እንኳን ሻይና ቀሽር ቀርቶ ንጹህ የቧንቧ ውሃ የምናየው ከስንት አንዴ ነው:: የፈተና ጊዜማ ጋቢያችንን ለብሰን ኩራዝ አብርተን እንደምናጠና ስነግርህ በኩራት ነው::...” ሰውየው ምን ነካቸው? እርግጥ ነው ድሮ መብራት አልነበረም:: አሁንም ቢሆን አለ ብሎ በድፍረት ለመናገር ይከብዳል::
ልዩነቱ በነሱ ዘመን ኩራዝ ነበር:: የኛ ዘመን ላምባዲናችን እንቅልፋችን ነው:: ፕሮፌሰር ለየት ያለ ነገር በመናገር ይታወቃሉ::የመጀመሪያ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለን በመጀመሪያው የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍለጊዜ ገብተው ራሳቸውን ካስተዋወቁን በኋላ፣ ስለትምህርቱ አንዳንድ ነገሮች ነገሩንና “ስማችሁንና የመታወቂያ ቁጥራችሁን ጻፉና ፈርሙ” ብለው አንድ ወረቀት ሰጡን:: እኔም አንድ ክላስ የቀጣ ጓደኛዬን ስም ጽፌ ፈረምኩለት:: ሊወጡ ሲሉ ቆጠሩን:: ሲቆጥሩን አንድ ትርፍ መጣ::
“ልጆች እኔ የሳይኮሎጂ መምህር ነኝ:: እያንዳንዳችሁ በአሁኗ ሰአት ምን እያሰባችሁ እንደሆነ፣ ምን አድርጋችሁ እንደነበር ፣ ከፈለጋችሁም ቁርሳችሁን ምን በልታችሁ እንደመጣችሁ ልነግራችሁ እችላለሁ:: ማነው የሌላ ሰው ስም የጻፈው? ...ጆሮህን ጠምዝዤ ሳላወጣህ ራስህ እኔ ነኝ ብለህ ውጣ!!!” ልቤ ድው ድው ማለት ጀመረ:: በቀዝቃዛው ጠዋት ወበቀኝ::
ከመቅጽበት ጉሮሮዬ ደረቀ:: ምላሴም ከትናጋዬ ጋር ተጣብቆ አልላቀቅ አለኝ:: መደንገጥ ለካ እንዲህ ቀላል ነው::
“አንተ ልጅ ከ1 እስከ 3 እስክቆጥር ካልወጣህ እኔ ፕሮፌሰር ጣሰው አይደለሁም :: አንድ…” ወደ ሁላችንም እያፈራረቁ ተመለከቱ:: ምላሴ መንተባተብ ጀመረ:: አጉተመተምኩ::
“ሁለት!” እግሬ እየተብረከረከ ከለቅሶ በማይተናነስ ድምጽ “ እኔ ነኝ ፕሮፌሰር...እ...ልጁ አሞት ስለቀረ ነው:: በውነት ፕሮፌሰር ሰይጣን አሳስቶኝ እንጂ እንዲህ አይነት ነገር አድርጌ አላውቅም::እኔ እኮ...” አላስጨረሱኝም፡፡
ከክፍል አስወጡኝ:: በዩኒቨርሲቲ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወላጅ አምጣ በማለት አዘዙኝ:: ወላጆቼ ከሺህ ኪሎሜትር በላይ እርቀው እንደሚኖሩ ስገልጽላቸው “ቀይ ባህር ውስጥ ናቸው እንዴ ?” በማለት ተሳለቁብኝ::
በኢሜይልም ቢሆን ሪፖርት እንዲያደርጉላቸው አዘዙኝ:: ያኔ እንዲህ ታለፈ:: አሁን ደግሞ ፕሮፌሰር ከጎኔ ቁጭ ብለው ትኩሱን ቀሽራቸውን እየጠጡ እኔን መውቀሳቸውን ቀጥለዋል:: አቦ በደከማቸው!!
ፕሮፌሰር ደክሟቸው ሳይሆን ስልክ ተደውሎላቸው ጥለውኝ ሄዱ:: ከአንድ ሰአት በላይ አባክነውብኛል:: ለማንኛውም ወቀሳቸውን በጥናቴ ድባቅ ልመታው እየሮጥኩ ወደ ላይብረሪ ገባሁ:: ወደ ቦታዬ ስጠጋ...አበስኩ ገበርኩ የሚያሰኝ ነገር አየሁ:: አይኔን ማመን አልቻልኩም:: በእውኔ ነው በህልሜ?...በቁንጅናዋ በግቢያችን አንደኛ የተባለላት ውቧ፣ቆንጆዋ፣ቢዩቲፉሏ ሳምሪ እኔ ከምቀመጥበት ወንበር ፊትለፊት ተቀምጣለች:: እውነት ለመናገር እሷን ለመተዋወቅ ያላደረግሁት ጥረት አልነበረም:: ዛሬ ግን...ወይኔ ጉዴ! ዛሬ አይን ላይን እየተያየን ልናጠና ነው::
ለነገሩ እኔ እንዳለሁ ስላላወቀች ነው እንጂ ብታውቅማ ኖሮ...? ልቤ ልትፈርጥ ደረሰች:: ደሞ ዛሬ እንዴት አባቷ አምሮባታል! ወንድ ልጅ ኮስተር ሲል ነው የሚያምርበት ብዬ ራሴን እንደምንም አደፋፈርኩና ኮስተር ብዬ ወንበሬን ስቤ ተቀመጥኩ:: ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ንግስቲቱ ጉሮሮዋን አጸዳችና
“ሳላስፈቅድህ ካንተ ፊት ለፊት በመቀመጤ ይቅርታ:: ካንተ ጋር እያወራን እንድናጠና ፈልጌ ነበር:: ይከፋሃል?”
አቤት የተሰማኝ ደስታ:: በልቤ “ሳምሪ ታስተፌስህ ልበ ሰብእ” አልኩኝና ቃላት እያማጥኩ ማውራት ጀመርኩ::
“ሳምሪ እኔ...”

Read 34656 times