Saturday, 01 December 2012 11:48

“ደጎል አደባባይ ዩራኒየም…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው ሊያገባ ሽር ጉዱ ተይዟል፡፡ እናላችሁ…አንድ ቀን አባትየው ሆዬ ምን ብለው ይጠይቃሉ መሰላችሁ…“ለመሆኑ ልጅቷ ልጃገረድ ነች?” እኔ የምለው… አንዳንዱ ሰው ቤቱ ግድግዳ ላይ የሰቀለው ቀን መቁጠሪያ ገና የታህሣሥ ግርግር ጊዜ የነበረው ነው እንዴ? እንዴ… ታዲያ ምን አይነት ጥያቄ ነው! ጥያቄ ሲጠየቅ ይስተዋልልንማ! የምር… ሙቀጫ የሲቲ ስካንን ሥራ ሲሠራ የነበረበት ዘመን ሄዷል እያልን!
ከአንዲት ወዳጄ ስለዚህ ጉዳይ እያወራን ነበር፡፡ (ስለ ‘ሌላ ነገር’ እንዳናወራ ‘ጂ.ፒ.ኤስ.’ ምናምን አሰጋንና ነው፡፡ ቂ…ቂ…) እና ወዳጄ ምን አለች መሰላችሁ… “ለመሆኑ ልጃቸው ራሱ ቨርጂን ነው?” ወዳጄ፣ በ‘ዲፕሎማሲያዊ’ አነጋገር ጥያቄሽ አሪፍ ነው ብለን ብናስብም የአቀራረብ ስህተት አለበት፡፡ እንዴት መሰለሽ…ለወንድ ሲሆን ‘ቨርጂን’ ነው አይደለም የሚባል ነገር የለም፡፡ የሚባለው ምን መሰለሽ… “ዓይኑ በራ ወይ?” ነው የሚባለው፡፡

ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ! “ለካ ዓለም በነገርዬው የሚፋጀው ወዶ አይደለም!…” ከተባለ በፊት ‘ነገሬ ያልተባለ ጉዳይ’ (“እሱን እንኳን ተወው!” ለምትሉ መልእክቱ ደርሶኛል…) ድንገት ታይቶ “የአባ እንትና እንትን፣ እንትን ስትል…” ካስባለ ያው ‘ዓይን በራ’ ማለትም አይደል!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በፊት እኮ እንትን እንትን የሚል ጠረን ያለው ጎረምሳ ሁሉ… ‘ዓይኑ የሚበራው’ የቅዳሜ ስሁር ዕለት ነበር፡፡ አሁን ልጄ…ከፍጥነቱ የተነሳ መቼ እንደሚበራም እየጠፋን ነው፡፡ ነገርዬው ‘ማተርኒቲ ዋርድ’ ምናምን ውስጥ ‘የሚጠፋበት’ ዕድል አለው እንዴ!
የ‘ዓይን መብራት’ ነገር ካነሳን አይቀር…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ! የዳያስፖራው ወዳጄ ያ ‘ዓይንህ የበራበት’ እሪ በከንቱ ፈረሰልህ እኮ! (በእርግጥ የእሪ በከንቱ ስም አሰጣጥና አንተ “ለእሪታ የሚቀርብ ድምፅ…” ያሰማህበት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን እኔ ምስክር እቆምልሀለሁ!)
እኔ የምለው…እገረ መንገዴን የመፍረስ ነገር ካነሳን… ግራ እየገባን ያለ ነገረ አለ፡፡ ምነው ከተማችን ውስጥ ‘ማፍረስ’ በዛሳ! ግንባታ አሪፍ ነው፡፡ ግን… ቢገነባም እኮ ድፍን ከተማ መተራመስ አለበት እንዴ! ከአንድ ቦታ አንድ ቦታ ለመሄድ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ የምር እኮ አንዳንዴ… አለ አይደል… ተኝታችሁ በተነሳችሁ ቁጥር የሆነ አካባቢ ወይ ፈርሶ ወይ ታጥሮ ስታገኙት…በቃ፣ ሂሳቡ አልገጥም ይላችኋል፡፡ አንዳንድ አካባቢ እኮ… የመፍረስ ፍጥነቱ “የኢንዶኔዥያው ሱናሚ ሳንሰማው ገብቶ ሳንሰማው ወጣ እንዴ!” ያሰኛል፡፡ እኛ ትንሽ ነገር ሁሉ ስለሚለምድብን ማፍረስ ከለመደብን ልክ አይመጣም፡፡ ነገ የትኛውን ምሰሶ እየነቀነቅን እንደሆነ አናውቅማ! አሀ…የእኛ የራሳችን ምሰሶ ቢሆንስ! “እናቴ ምን አለ በእንትኑ ጊዜ እንትን ባልሽኝ…” አይነት የሲንግል ዘፈን ግጥም የሚመስል ነገር ማጉረምረም ይመጣል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የዘመንና የአገር ነገር በደንብ ያልገባቸው ምስኪን አባት “ለመሆኑ ልጅቷ ልጃገረድ ነች?” ብለው አረፉላችሁ፡፡ “ብር አምባር ሰበረልዎ…” እኮ በ“እንደ አብረሀም” ሲተካ መጠርጠር ነበረባቸው፡፡ ልክ ነዋ…“እስቲ አምጣው የእንትኑን ሸማ እንድንስማማ…” የሚል ዜማ “ተከልክሎ ነው ወይ የቀረው…” ብለው መጠርጠር ነበረባቸው፡፡
እንዴ…ኤፍ.ኤሞቹ እንኳን እኮ የማዶናን “ላይክ ኤ ቨርጂን” ካሰሙ ሰነበቱ! ‘የሚያውቁት ነገር’ ቢኖር አይደል! የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንድ “ነገር የገባኝ ነኝ…” የሚል ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ… “‘ቨርጂን’ የሚባል ነገር ከመፈለግ ደጎል አደባባይ ዩራኒየም መፈለግ ይሻላል፡፡” (እዚህ አገር እንደሁ ዘንድሮ ምንም ነገር ጫፍ ከተያዘ ‘ርብርብ’ ነውና…ይቺ “በጋዜጣ ላይ ተጥፋለች…” ተብሎ ደጎል አደባባይ ተቆፍሮ እንዳያድር ፍሩልኝ፡፡ )
የምር ግን…ፍሬሽ (‘ቨርጂን’ ማለትም ይቻላል) ነገር እየናፈቀን ነው፡፡ ልክ ነዋ…ፍሬሽ ሰላጣ እንኳን እያጣን የኮንትሮባንድ ፎጣ የመሰለ ነገር እየገዛን እኮ ነው፡፡ ፍሬሽ ነገር እየጠፋ ሲሄድ ደግሞ…አለ አይደል… ሁሉ ነገር ሞቅ ሞቅ ይሆንና ማጣፊያው ያጥራል፡፡ ስሙኝማ…በሁሉም ነገር ‘ሞቅ ሞቅንማ’ እንዴት እንደተካንንባት! እኔ የምለው…ለዚህ፣ ለዚህ ነገር ጊነስ ‘ቡክ ኦፍ ሬከርድስ’ ላይ ቦታ ያልተሰጠው እነሱ ‘ስለማይደርሱብን’ ነው እንዴ!
እናማ ያልተሞከሩ ‘ፍሬሽ’ ሀሳቦች እጥረት ሰንጎ ይዞናል፡፡
ይቺን ስሙኝ…ሰውየው በቃ ‘ላቩን’ ለእሷዬዋ ለመግለጽ ምን ይላታል መሰላችሁ… “ላንቺ ስል ዓለም ጥግ ድረስ እሄዳለሁ፣” ይላታል፡፡ እሷዬዋም ምን አለችው መሰላችሁ… “ውይ ደስ ሲል! ግን ዓለም ጥግ ሄደህልኝ እዛው ቆይ፣ አትመለስ፡፡” በቃ የሆነ ጠቃሚነቱ ያበቃበት ነገር ይኖራላ! እሱ ዓለም ጥግ ደርሶ እሰኪመጣ ‘ይሞታል’ እንዴ!
ሌላው ሰውዬ ሌላዋን እንትናዬ ምን ይላታል መሰላችሁ… “እወድሻለሁ፣ እኔን ማግባት አለብሽ…” ይላታል፡፡ እሷዬዋም “እኔ አልወድህማ! ሌላ ሴት መፈለግ አለብህ፡፡ ሌላ ቆንጆ ሴት ፈልግ፣” ትለዋለች፡፡ እሱ ምን ቢላት ጥሩ ነው…“እኔ ቆንጆ ሴት አልፈልግማ! አንቺን ነው የምፈልገው፡፡” አሪፍ አይደል!
አትወጂኝም ያልከው የጠላሁህ የታል
ያለኝ አንድ አንጀት ነው ተኝተህበታል፡፡
የሚባል የላቭ አይነት ነበር፡፡ ቪላ የለ፣ መኪና የለ፣ የአይ ፓድ ስጦታ የለ፣ የ140 ብር ክትፎ የለ በቃ….“አንዷ አንጀቴ ላይ ያለኸው አንተ፣ ምን ትፈልጋለህ!” ማለት ብቻ፡፡ እንትናዬ… አንዷ አንጀትሽ ላይ ስንት ሰው አለ? ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…አሉ ስንላቸው ‘እየተሰወሩ’ ያስቸገሩን ነገሮች በዝተዋል፡፡ እናማ…“ለመሆኑ ልጅቱ ልጃገረድ ነች?” የሚለው ነገር ለሌላም ይሠራል፡፡ ‘ፍሬሽ’ ነገር እየጠፋ ነዋ!
እኛ ‘ጠሀፊ’ ነን የምንለው ‘ፍሬሽ’ ሀሳብ የለን…ሙዚቀኞች ፍሬሽ ሀሳቦች የሏቸው… ‘ቦተሊከኞች’ ፍሬሽ ሀሳብ የላቸው… ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም ነገር… አይደለም ለአገልግሎት ሊበቃ ለ‘ሪሳይክሊንግ’ እንኳን የማይመቸው እየተግበሰበሰ ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ… የሆነች ነገር ትዝ ብላኝ ነው፡፡ ሰውየው ቶማስ የሚባለው ጓደኛው ‘ዲታ’ ነው፡፡ እንትንዬው ደግሞ ቶማስን በአካል አታውቀውም፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ምን ይላታል መሰላችሁ… “የእኔ ፍቅር እወድሻለሁ፡፡ የእኔ እንድትሆኚ እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ቶማስ ሀብታም አይደለሁም፣ እንደ ቶማስ ቪላ ቤት የለኝም፣ እንደ ቶማስ ቆንጆ መኪና የለኝም፡፡ ግን የእኔ ፍቅር እወድሻለሁ፣ ያለ አንቺም መኖር አልችልም፣” ይላታል፡፡ እሷዬዋ አዳመጠችና ምን አለችው መሰላችሁ… “የእኔ ፍቅር፣ እኔም እወድሀለሁ፡፡ ግን ላስቸግርህና…የቶማስን አድራሻ ልትሰጠኝ ትችላለህ?” በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ ይሏችኋል የዚህ አይነቱ ነው፡፡
ይቺን የድሮ ቅኔ ስሙኝማ…
አንገት የለሽም ወይ አዙሮ የሚያይ
ሲመሽ ብር ብለሽ ትሄጃለኝ ወይ?
አሪፍ አይደል! ሲመሽ “ብር ብለው…” የሚሄዱ ስለበዙ ይኸው ድፍን ከተማው ቺቺኒያ ሆኖ ሊያርፍ አይደል እንዴ! የምር አስቸጋሪ ነገር አለ…አንዳንድ እንትናዬዎች እንትናዬዎቻቸውን “ሄደሽ ፍራንክ ፈላልገሽ ነይ…” ይሉዋታል የሚባለው ነገር በርክቷል ነው የሚባለው፡፡ ይህ ነገር እውነት ከሆነ… አለ አይደል… ከዚህ የባሰ የሞራል ዝቅጠት ይኖራል?! የ‘ወሬ’ አገር፣ የ‘ፉከራ’ አገር፣ የ‘ዲስኩር’ አገር ሆነና ውስጥ ውስጡን ሞራል እየመነመነ ለምሳሌነት የሚበቃ እየጠፋ ሲሄድ… የምር አስቸጋሪ ነው፡፡
እግረ መንገዳችንን…የሁሉም ነገር መለኪያ ‘ፈረንካ’ የሆነበት ዘመን ውስጥ ጥልቅ ብለን የገባን አይመስላችሁም! አብሮ አድጌ፣ አበ ልጄ፣ የአክስቴ ልጅ…ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ ወዳጅነት ለመዳበርና ለመፍረስ ወሳኙ አብሮ የተኖረበት ዘመን ሳይሆን ‘ፈረንካ’ ብቻ ሆኗል፡፡ “ከሌለህ የለህም” ማለት ዘንድሮ ነው፡፡ የእኔ ቢጤ ከርፈፍ ያሉ እንትናዎች እንትናዬዎቻቸውን ከዓይናቸው ስር የሚሞጨለፉት ፈረንካቸው ከቦምቦሊኖ አላልፍ እያለ ነው፡፡
(ስሙኝማ…ቦምቦሊኖ እንኳን ከአቅሟ እንዲህ ኪሳችንን ትፈታተን! በቀደም የቀለጠው መንደር ለአንድ ቡና በወተትና ለአንድ የ‘ረበር ፕላንቴሽን’ የምታስታውስ ቦምቦሊኖ ሀያ አራት ብር የተቆነደደ ወዳጄ ‘ሬቮሉሽን’ ሊጀምር ምንም አልቀረው!)
ፈረንካ…ወደ ሮቦትነት እየለወጠን ነው፡፡ እንደ ሞሏቸው ከመንቀሳቀስ በቀር ራሳቸውን ችለው አያስቡማ! ራሱን ችሎ የሚያስብ ሰው ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ “ይሄ ነገር ሄዶ፣ ሄዶ ገደል እንዳይሆን…” ማለቱ ደግ ነው፡፡ መተባበርና እኔን… መባባል ሲጠፋ የማያሳስበንማ!
እናማ… ‘አልቦ ዘመድ’ ላይ ብርሀኑ ድንቄ የጻፏትን ስሙኝማ
“ብቻህን ለመቆም ተዘጋጅ፣
ልጅ፣ ወንድም፣ እህት፡ ዘመድ የሚባሉ ነገሮች የምቾት ጊዜ አጫፋሪዎች ናቸው፡፡” ይሄ ዘመናችን ይህንን አባባል ሙሉ ለሙሉ እውነት ሊያደርገው የቀረበ አይመስላችሁም?!
እናላችሁ… ሰውየው “ለመሆኑ ልጅቷ ልጃገረድ ነች?” ማለታቸው እንዳሳዘኑኝ ነገር…የምር ባገኛቸው “ደጎል አደባባይ ዩራኒየም ይፈልጉ…” እላቸው ነበር፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 18359 times