Saturday, 01 December 2012 11:42

ኢትዮጵያዊነት የማን ዕዳ ነው?

Written by  በደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(1 Vote)

“ማጆሪስ”ን እንዳነበብኩት
“ይህ ትውልድ በራሱ ላይ ነው ያመጸው……” የሚለውን የአንድ ዶክተር ንግግር ሳነብ ወዳለፈው ዘመን ትውልድ ማንነትና ምንነት መመልከት እፈልጋለሁ፡፡
ጠጅና ጮማ የቀፈት መሙያ መሆኑ ታምኖበት የምቾትና የባለጸግነት መለያ በሆነበት በዚያ ዘመን ጥቂቶች ፊደል መቁጠር ጀምረው ነበር፡፡ ፊደል ከቆጠሩት ጥቂቱ ነፍስ ማወቅ ሲጀምሩ ‹‹ኢትዮጵያ የእኛ ዕዳ ናት›› የምትል ጉርምርምታን ማዜም ጀምረው ነበር፡፡
የግሪካዊውን ስመጥር ፈላስፋ የፕሉቶን ንግግር (every state is a community of some kind, and every community is established with a view to some good) የምናውቅ የዚህ ትውልድ አባላት፤ የያኔዎቹ ‹ኢትዮጵያዊነት የኛ ኃላፊነት ነው›› ሲሉ አንድ መስመር ታይቷቸው እንደሆነ መገመታችን የማይቀር ነው፡፡


የያኔው ትውልድ አባላት ግን ያን አላደረጉም፡፡ የሚፈልጉት፣ የሚመኙት፣ የሚያደርጉት ሁሉ ትኩስ ብረት ምጣድ ላይ እንደተበተነ ተልባ እየተንጣጣ በየአቅጣጫው ተበተነ፡፡
ያ ዘመን ሀገሪቱን ለመረከብ ሳይሆን ራሱን ወንበር ላይ ለማውጣት የሚታትር የበዛበት ነበር፡፡
የፓርቲዎቹ የስልጣን ጥማት ከመደብ ትግል እስከ ትጥቅ ትግል፣ ከመጨነቅ እስከመታጠቅ፣ ከመገደል እስከመግደል ያሉ ወገኖች ግራና ቀኝ የታማቱበት የሁካታ ዘመንን ወለደ፡፡
ደርግን ተከትሎ በህወሃት እየተመራ አዲስ አበባ የገባው የታጋዮች ፓርቲም ቢሆን ሀገሪቱን የራሱ ዕዳ አድርጎ አልተቀበለም ሲባል አልሰማንም፡፡ ያጸደቀው ህገመንግስት የራሱን የመከፋፈል እና የመገነጣጠል ምኞት የሚያሳካ፣ የሚከተለው ፖሊሲ እና ስትራቴጅ የራሱን የሃይል ሚዛን የሚጠብቅበት፣ ስልጣን አያያዙና መዋቅሩ የራሱን ዙፋን የሚንከባከብበት እንጅ ሀገሪቱን ሀገር ለማድረግ የቀየሰው አይደለም እየተባለ ከመታማት አልዳነም፡፡
እነዚህ የፖለቲካ ነፋሶች በነፈሱበት ዘመን ሁሉ ሥነ ጽሑፋችን ምን ፋይዳ ነበረው? ብሎ መጠየቅ የዚህን ዳሰሳ ፀሃፊ ሐሳብ ለመከተል ይጠቅማል፡፡
የአጼው ዘመን ጸሀፊያን ያን ያህል እንዲደፍሩ ባንጠብቅም፣ የደርግ ዘመን ጸሐፍት የሳንሱርን ቀንበር ሰብረው ለማለፍ የሚያስችል ወኔ እንደነበራቸው ባንገምትም በሦስቱም ዘመናት ስለለነበሩ ጸሐፍት የኢህአዴግ ዘመን ላይ ሆነን ትዝብታችንን መግለጽ እንችላል፡፡
በተለይ ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን የታተሙ መጻህፍትን (ታሪክና እውነት ቀመስ የሆኑ) ለግል አለዚያም ለዘመን ጥቅም ሲባል የሚደረቱ የክስ፣ የወቀሳ፣ የስድብ፣ የጥላቻ፣ የምንፍቅና፣ የብልግና መጻህፍት በርክተው እናገኛለን፡፡ ከዚህ አልፎ ፖለቲካዊ፤፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወይም ማህበራዊ ጉዳዮችን ለመዳሰስ የሚነሱ መጻህፍት በጭፍንነት ተሞልተው፣ በተከበበ አጥር ዙርያ ሲንደፋደፉ እናስተውላለን፡፡ የፈጠራ ድርሰቶች ደግሞ ብዙ ጊዜ ሀገራዊነት ማጠንጠን ተስኗቸው በማይረባ ርእሰ ጉዳይ ሥር ሲርመሰመሱ እናስተውላለን፡፡
በሀገሪቱ አንድ አደጋ አለ.. ይህን አደጋ ደግሞ የሚቋቋም የሀገር ውስጥ ቡድን አለ፤ በሚል ልብ ለማንጠልጠል የሚሞከርበት አጻጻፍ የተስተዋለባቸው ሁለት ያህል ዓመታትን መለስ ብለን እየቆጠርን ወዲህ ብንመጣ የሁለት እጃችንን ጣቶች ብዛት ሊበልጧቸው ይችላሉ፡፡ ጥላሁን ብርሃኑ የጻፈው “ማጆሪስ” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ ከዚህ ትዝብት የሚያመልጥ ሆኖ ባላገኘውም በብዙ መልኩ ጠንካራ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ከላይ የሰፈሩት አንቀጾች በሙሉ ወደ ማጆሪስ ለመንደርደር የተከተቡ ናቸው፡፡‹‹ትውልዱ በራሱ ላይ ነው ያመጸው›› “ማጆሪስ”ን ሲያነቡ ሐሳባቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡
‹‹ሀገር የእኛ ዕዳ ናት›› የሚል መፈክር ያነገበው ቡድን፣ በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱን ሽቅብ ለማስወንጨፍ ያቀደውን ቢመለከቱ! ሀገሪቱ መልማት አለባት፡፡ መከተልም ያለባት የልማት መንገድ የዚህ ዓይነት አይደለም ብለን ለመቃወም ብዙዎቻችን ወንበር ላይ ያለውን ኢህአዴግን ማጥላላት የመጀመርያ እርምጃ እናደርገዋለን፡፡
ይህን በማድረጋችንም ራሳችንን ጀግና እና አብዮተኛ አድርገን የምንቆጥር ጥቂት አይደለንም፡፡ ታላቁ ነጥብ ግን የገዥውን ፓርቲ ድክመት መተንተኑ ላይ ሳይሆን የተሻለውን መንገድ መቀየሱ ላይ ነው፡፡ እልፍ የሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲመሰረቱና ሲበተኑ አስር ባልሞሉ አመታት ውስጥ ብዙ ታዝበናል፡፡
የጥላሁን ብርሀኑ “ማጆሪስ” የሚያጓጉ ሀገራዊ እቅዶችን አስቀምጧል፡፡ እነዚህን እቅዶች የነደፉት ‹‹ዘ ዳይመንድስ››፤ የስልጣን ወንበር ላይ ለመውጣት ሲሯሯጡ አይደለም የሚተርከው፡፡ መንግስትን እየመራ ካለው ፓርቲ ጋር ሆነው ‹‹ማጆሪስን›› እውን ሊያደርጉ ሲታትሩ እንጂ፡፡ የጥላሁን ምኞት መልካም እቅድን ነድፎ ብቻ ዝም የሚል አይደለም፡፡ አሁን አሁን አታካች የሆኑ ገዥውን ፓርቲ የመወረፍ አባዜን በመራቅም ብቻ አይደል፡፡ ኢህአዴግ ለተቃዋሚዎች እድል ሰጥቶ የሀገሪቱ ጉዳይ ከልብ በመነጨ ቅንነት ሲያማክር የሚያልም ድርሰትም ነው፡፡
ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልፈልግም፣ መሳተፍ አልፈልግም፣ ፖለቲካ አልጽፍም ይህ የፖለቲከኞች ሥራ ነው፣ ወዘተ. እየተባለ ማህበራዊ ሕይወታችን ሳይቀር ከፖለቲካ አልለይ ብሎ ፍርሃት በቀፈደደን በዚህ ጊዜ ሥነ ጽሑፋዊ ለዛውን ሳያጣ ለፖለቲከኞች የሚሆንን መንገድ መጠቆም ብርታት ነው፡፡
ተቃዋሚዎች፣ ገዥው ወይም ይመለከተናል የሚሉ ከዚህ መጽሀፍ ሐሳብ ላይ ተነስተው አንድነትን ቢያጠነክሩ ሀገሪቱ በፕሮፓጋንዳና በዜና ብቻ ሣይሆን በእውነትና በተግባር ትሰለጥን ትበለጽግማለች፡፡
‹‹በመኻል ኢትዮጵያ ቀድሜ የጠቀስኳቸውን ተፋሰሶች በመገደብና በመጥለፍ በባሌ፣ በአርሲ፣ በሸዋና በጎጃም ትላልቅ ሜካናይዝድ የሆነ ግብርና ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ አሁንም በደቡብና በኦሮሚያ እንዲሁም በድሬዳዋና በጋምቤላ አካባቢ ያለውን የቡናና የሻይ ምርት በዘመናዊ መልኩ በማሳደግ አሁን ካለው የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት በሁለት ሺ ፐርሰንት ምርቱና አግሮአንዱስትሪው እንዲመጥቅ ጥረታችንን ጨርሰናል” (39) “ማጆሪስ” ይህን የመሰሉ አንቀጾችን ስላሰለፈ አይደለም ጠንካራ ነው የምለው፡፡ ተምረው እንዳልተማሩ የሚሆኑ ምሁሮቻችን የዚህ ሐሳብ ባለቤት እንደሆኑ መመኘቱ ነው ታላቁ ነገር፡፡
በጽሑፌ መነሻ እንደገለጽኩት በአጼው ዘመን ፊደል ቆጥረው በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተለያይተው እስከዛሬ ቂምና ጥላቻን የሚዘሩ ‹‹ከእኔ ውጭ ለዚች ሀገር የሚጠቅም የለም፤ ከእኔ ሀሳብ ውጭ ለዚች ሀገር የሚበጅ የለም›› የሚሉ ‹‹ ምሁሮች›› እስካሁን ያለው ትውልድም እርስ በእርስ እንዳይግባባና ‹‹ሀገር›› የምትባለዋን በአንድነት እንዲያስባት አላስችል ብለዋል፡፡
በምሁራን በኩል ወጥ የሆነ ስሜት የለንም፡፡
አንዳንዶች ጥላቻቸው የጽንፍ ነው፤ አንዳንዶች ፍርሃታቸው የጽንፍ ነው፤ አንዳንዶች ውሸታቸው የጽንፍ ነው፡፡ “ማጆሪስ” ግን እነዚህን ሁሉ የዘመን እከኮች ከሀሳባቸው ጋር ወደ ጎን ትቶ ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል እቅድ ሲነድፍ ይታያል፡፡ ቢሆን ይህ ፍቱን እሳቤ ይመስላል፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊያን ፕሮፌሰሮች፣ የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪዎች፣ የፖለቲካ ጠበብቶች፣ የህክምና ዶክተሮች፣ የኮምፒዩተር ሳይቲስቶች፣ የግብርና ባለሙያዎች ፣የምህንድስና ጠበብቶች በዚች በቁርጥ ቀን ይፋ ለሚሆነው የታላቅነት ራዕይ በራቸውን ዘግተው ቀንና ሌሊት በምርምር ሥራቸው ላይ ተጥደው በሃያ ዓመት ጉዞ ዛሬ ላይ ደርሰዋል›› (35)
መጽሐፉ በዘመናዊ ትምህርት የሠለጠኑ ምሁራንን ከየዘርፉ አሰባስቦ ስለሀገር እንዲያስቡ ማድረጉ ሙገሳን ፍለጋ አይመስለኝም፡፡ ልብ ያለው ልብ እንዲል እንጂ፡፡
ኢትዮጵያን መረከብ፣ ማሳደግ፣ ማበልጸግ የእኛ ዕዳ እንጅ የማንም አይደለም፡፡ የማስተዳደር የመፖትለክ ሥራውን ግን እኛ አንፈልግም የሚል የተማረ ዜጋ ማየት አስደሳች ነው፡፡ የተማርነው ሀገር ጥሎ ለመሰደድ ሳይሆን፣ የተማርነው ዘር እየተቋጠርን የቆየ ቂም ልንቀሰቅስ ሳይሆን፣ የተማርነው ወንበርና ጉቦ ፍለጋ ለመኳተን ሳይሆን፣ የተማርነው የግል ሆድን ለመሙላት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ለመረከብ ነው ብሎ የተነሳ የቅን ምሁራን ስብስብን መሠረት ያደረገው “ማጆሪስ” ይበል የሚያሰኝ የታሪክ አወቃቀር አለው፡፡
በተለይ ምዕራፎቹ ሊጠቃለሉ ሲሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚያጣድፍና ልብ የሚያንጠለጥል ሁነት አምጥቶ ልብን መስቀል የመጽሐፉ መለያ ይመስላል፡፡
አንድን ጉዳይ እየተረከ ቆይቶ በምእራፉ ማጠቃለያ ላይ የሚደንቅ ግን የማይጣረስ ሁነት በማምጣት የአንባቢን ልብ ያንጠለጥላል፡፡
በእርግጥ የተነሳሁት የ”ማጆሪስ”ን ሀሳብ ከመውደድ፣ ወድጄም ለዚህኛው ትውልድ የለውጥ ኃይልነት ማስረጃ እንዲሆነኝ ከመፈለግ ነው፡፡ ከዚህ ያለፈውን ሥነ ጽሑፋዊ አካሄድ በጥልቀት ልተነትን አልሞከርኩም ፡፡
ሐሳቡን መውደዴ ግን ሐሳቦቹ የተገለጹበትን ቃላት ማጤን ላይ ተጽእኖ አድርጎብኛል ማለት አልችልም፡፡ በጥላሁን አጻጻፍ ላይ የቃላት እንደወረደነት አስተውየበታለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሀገራዊ ጉዳዮች ሲነሱም ስነ ጽሑፋዊ ውበት ቅድሚያ ሊሠጠው እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ ምሳሌ እንውሰድ፤
‹‹በመጨረሻ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ቃለ መሃላ የሚገቡበት ሰዓት ደርሶ ሁሉም በአንድ ትንፋሽ በፍጹም ጉጉት ተቁነጠነጡ፡፡
የግብርና የሃይድሮ ፓወር የመንገድ የባቡር ሀዲድ የኮንስትራክሽን በርካታ ግንባታ እቅዶች በመጽሐፉ ተካተዋል፡፡ ሁሉም በልቡ የሃምሳ ዓመቷ ኢትዮጵያ ለማዬት ፈጣሪው እድሜ እንዲሰጠው በልቡ ናፈቀ›› (269-270)
በ”ማጆሪስ” ውስጥ አልፎ አልፎ ደንቀፍ የሚያደርጉ ሥነ ጽሑፋዊ ለዛ የራቃቸው የሚመስሉ አረፍተ ነገሮች ይገጥሙናል፡፡ አሁን አሁን በብዙዎቻችን ዘንድ ችላ የተባለ የመሰለው የፊደል ግድፈትም በ”ማጆሪስ” ውስጥ ይስተዋላል፡፡
በጥቅሉ ግን የጥላሁን ብርሃኑ “ማጆሪስ” የዚህን ትውልድ ህልምና ፍላጎት የሚገልፅ ይመስለኛል፡፡ ቀሪውን ለአንባቢያን ፍርድ ትቼዋለሁ፡፡

Read 3239 times