Saturday, 01 December 2012 11:18

ከኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ የለም Featured

Written by  አበባየሁ ገበያው-
Rate this item
(5 votes)

40/60 የኮንዶሚኒዬም ፕሮጀክት እየተፈተሸ ነው
ዘንድሮ በሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ ላይ ኢህአዴግ የሚያቀርባቸው ዋና ዋና የስትራቴጂ ሃሳቦች ምን ምን ናቸው?
ለምርጫ የተለየ ስትራቴጂ የለንም፡፡ ኢህአዴግ በምርጫ የሚወዳደረው በይፋ አውጥቶ በሚሰራባቸው ስትራቴጂዎች ነው፡፡ የከተማና የገጠር ልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ግንባታ፣ የአቅም ግንባታና የሰላም፣ የውጭ ግንኙነትና የደህንነት ስትራቴጂዎች ናቸው፤ መሠረታዊዎቹ ስትራቴጂዎች፡፡

ህዝቡ በራሱ ተሳትፎና ጥረት፣ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ ቀጣይነት ያለው ፈጣን እድገትን እንዲሁም የሃገሪቱን ህዳሴ ማረጋገጥ የኢህአዴግ አላማ ነው፡፡ በየወቅቱ ያገኘናቸው ድሎችን ታሳቢ በማድረግ፣ ቀጣይ መስራት የሚገቡንን ሃሳቦችን ይዘን፣ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር እየመከርን ተራምደናል፡፡ መንግስትም ድርጅትም የየራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ድሎች የሚመዘገቡትና ችግሮች የሚፈቱት በህዝቡ ተሳትፎ ነው የሚል መሠረታዊ እምነት አስቀምጠናል፡፡ ይህንን እንቀጥልበታለን፡፡ 
ለምርጫ የምንቀርበው መመዘኛዎችን በመለየት ነው፡፡ ጥንካሬዎቻችንና ችግሮቻችንን በግልፅ አውቀን ነው፡፡ “ይሄ ይሄ ጥንካሬያችን ነው፤ እስከዛሬ በዚህ ሁኔታ መጥተናል፡፡ በዚህ ጥንካሬ ውስጥ ደግሞ ይሄ ይሄ ችግር አለብን” እንላለን፡፡ አቅማችን በሂደት እየተገነባ የሚሄድ ነው፡፡ ሃሳቦቻችን ትልልቆች ናቸው፡፡ የተጀመሩ ስራዎቻችን ትልልቆች ናቸው፡፡ ይህን የምንለው ያለ መመዘኛ አይደለም፡፡
የመንግስት አፈፃፀም፣ ፈጣን ልማት ለማምጣት የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ ትልልቅ ድሎችንና ስኬቶችን አስመዝግበናል፡፡ ነገር ግን ሃገራችን እስከዛሬ ከነበረባትና ካለችበት ችግር አንፃር ስናየው በቂ አይደለም ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ከሌሎች አገራትና መንግስታት ጋር ስናነፃፅረውም፤ በብዙ መልኩ በተሻለ ደረጃ ህዝቡን እያንቀሳቀሰና እያሳተፈ የሚሄድ ድርጅት እና መንግስት ነው ያለን፡፡ ከእኛ እምነትና ራዕይ እንዲሁም በፍጥነት ለውጥና እድገት ለማስመዝገብ ካለን ጉጉት አንፃር ስናየው ነው በቂ አይደለም ብለን ችግሮችን የምንፈትሸው፡፡
የፈጣን እድገቱ ሚስጥር በየደረጃው ማህበረሰቡን ለማንቀሳቀስ መቻላችን ነው፡፡ መንግስት ብቻ የሚሠራበት ሳይሆን፤ የሚያመቻችበትና የጐደለው የሚያሟላበት ነው፡፡ ዋናው የልማት አቅም ህዝብ ነው፤ ይህ የልማት አቅም ተደራጅቶ ውጤት የሚያመጣበት አቅጣጫ መፍጠራችን ነው የስኬቱ ሚስጥር ብለን እንወስዳለን፡፡ እንከን የለውም፤ የሚሻሻሉ ነገሮች የሉትም ማለት አይደለም፡፡ ከአቅምና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ፡፡ ይህን ደግሞ በሂደት ለውጥ ራሱ እየፈታው ይሄዳል፡፡ ህብረተሰቡ ነው፤ ራሱ ባመጣው ለውጥም ህብረተሰቡ ይለወጣል፤ የህብረተሰቡ አተያይና አቅም እየተገነባ ይሄዳል፡፡
ስለዚህ ህብረተሰቡ አካባቢውን ይቀይራል፤ አካባቢው ህብረተሰቡን ይለውጠዋል፡፡ ይህን መስተጋብር ግምት ውስጥ ያስገባ፤ ጥንካሬያችንና ድክመታችንን በሚዛን የሚያስቀምጥ አቅጣጫ ይዘን ነው ለምርጫ የምንቀርበው፡፡ ስኬታችንን አጋነን፤ ችግሮቻችንን አንኳሰን ለማቅረብ አንፈልግም፡፡ በምርጫ ወቅትም ሆነ አልሆነ፤ ኢህአዴግ ሁልጊዜ ስኬቶችን በልኩ ያስቀምጣል፡፡
በተለይም ለአዲስ አበባ ምርጫ ተሻሽለውና ተስተካክለው የሚቀርቡ ስትራቴጂዎች ይኖራሉ?
በስትራቴጂ ደረጃ አዲስ ስትራቴጂ እንቀይሳለን ብለን አናምንም፡፡ የተጀመሩት ስትራቴጂዎች በጣም ረጅም ርቀት የሚያራምዱን ናቸው፡፡ ሌሎች እየመጡ የሚማሩባቸውና በአርአያነት የሚወስዷቸው ስትራቴጂዎች አሉን፡፡ በእርግጥ በምንፈልገው ልክ ሁሉን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ካለን ራዕይ አንፃር ሲታይ ገና ረጅም ርቀት መሄድ አለብን፡፡ ግን የአቅጣጫ ለውጥ አይጠይቀንም፡፡ የያዝነውን አቅጣጫ በፍጥነት የማስፋትና የማሳደግ ጥረት ነው የሚያስፈልገን፡፡ መሻሻል ሲባልም ይህን ማለታችን ነው፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ የከተማ ስትራቴጂያችንን ብንወስድ፤ አንድ ዋና ነጥብ ማንሳት እንችላለን። በከተማ የአብዛኛው ህዝብ ገቢው አነስተኛ ነው፡፡ አብዛኛውን የከተማ ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው በምንድን ነው ከተባለ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን የኢኮኖሚ ልማት መስኮች እንዲሰማራ በማመቻቸት ነው፡፡ ብድር የሚያቀርቡ፣ ስልጠና የሚሰጡ፣ አመለካከትን የሚቀርፁ ተቋማት እንዲበራከቱ በማድረግ መንግስት ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ዋናው አቅጣጫ ይሄው ነው፡፡ በዚህም አቅጣጫ፤ ሰዎች ወደ ስራ እየገቡና ህይወታቸው እየተቀየረ ነው፡፡
ይሄ ማለት ግን ችግሮች የሉም ማለት አይደሉም፡፡ በሚፈለገው መልክ ተደራጅተው ያልገቡና በሚፈለገው ልክ ለውጤት ያልበቁ ማህበረሰቦች አሉ፡፡ ለዚህ ምን አይነት አዲስ አቅጣጫ ያስፈልጋል ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ እስከ አሁን ስኬት ባስመዘገብንበት አቅጣጫ ውስጥ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ አንዱ ነጥብ፣ የፈፃሚዎችን፣ የመንግስትን አቅም ይበልጥ ማጠናከር ነው፡፡ መንግስት አመቻቾች በጉዳዩ ላይ እምነትና እልህ እንዲያድርባቸው፤ በዚህም አቅማቸው ተገንብቶ በተጨባጭ ህዝቡ ጋ ደርሰው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ በመንግስትና በድርጅት በኩል ያለውን እምነት ህብረተሰቡ ተቀብሎ ይጠቅመኛል ብሎ እንዲጓዝ ማድረግ ካልቻልን በምንፈልገው ፍጥነት መሄድ አንችልም፡፡ ለዚህ ኮሙዩኒኬሽን ያስፈልጋል፡፡
መለወጥና ማደግ የማይፈልግ፣ ኑሮው እንዲሻሻልለት የማይፈልግ ህብረተሰብ የለም፡፡ ወደተሻለ ኑሮ ለመጓዝ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንዴት ነው መሻገር የምችለው? የሚለው ጥያቄ አለ። በመፍትሄ አቅጣጫው ላይ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የድርጅትና የመንግስት አመራሮች በየደረጃው ስራ የመጥላት አተያይን ለመቅረፍ እየሰራን ነው፡፡ አጠገቤ ያለውን ነገር ሰርቼ ጥሪት መቋጠር አለብኝ የሚል እልህና እምነት መፈጠር አለበት፡፡ ከወጣቱ መጀመርና ወላጆች ይህን እንዲደግፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ወላጆች፣ “የኔ ልጅ ይሄን አይነካም ያን አይነካም” ከሚል አመለካከት ወጥተው ወጣቶችን ለሥራ ሲያበረታቱ፤ የስራ ፍቅር እየጐለበተ ይመጣል። የተገኘውን ሰርቶ የመቆጠብና ጥሪት የመቋጠር ባህል እየዳበረ ይመጣል፡፡ ይሄ ግን በቀላሉ አይመጣም። ጥረትን ይጠይቃል። ዛሬ ትንሽ እየበሉ ነገ ከፍ የሚሉበት አመለካከት መገንባት ጊዜን ይጠይቃል፡፡ በመንግስት ፍላጐት ብቻም አይሳካም፡፡ በህብረተሰቡ የግንዛቤ ደረጃም ወሳኝ ነው። ስለዚህ በአመለካከት የተለወጡትን የማበረታታት፤ ሌላውም ከእነዚህ ትምህርት እንዲወስድና በስፋት ተደራጅቶ ወደ ተግባር የማሰማራት ስራ ይጠይቃል፡፡
የከተማ ልማት አንዱ ስትራቴጂ ይሄ ነው። የሁሉም ስትራቴጂዎች አላማ፣ ህዝብን መጥቀም ነው፡፡ ኢህአዴግ፣ ብዙሃኑ በየትኛው ስትራቴጂ ይጠቀማል የሚለውን ያስባል፡፡ ከሌላ ቦታ ከሌላ ሰው የተገኘ ሃብት የማካፈል ጉዳይ አይደለም፡፡ ራሱ ሰርቶ ኑሮውን እንዲለውጥና እንዲሻሻል የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ የሶሻል ስቴት አይነት የማህበራዊ ደህንነት ስራ አይደለም።
ከሃብታሞች ትንሽ እየሸረፍንና ለድሃው እያቃመስን ሁሉም ተቻችሎ ይበላል የሚል አስተሳሰብ አይደለም። ሃብታሙ እየሠራ ሃብት እንዲፈጥር እንደግፍ፤ አነስተኛ ገቢያ ያለውም በራሱ ጥረትና ለእድገቱ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ልክ እንዲጠቀም እንደግፈው፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ የሥራ እድል መፍጠር ነው - ባለው አቅም ላይ በመመስረት፡፡ በእጃቸው ያለው አቅም ላይ ድጋፍ ተጨምሮበት ብዙ ዜጎች መስራት ጀምረዋል፡፡
ጐዳና ላይ የነበሩ ሰዎች፣ ይህችን ሰርቼ፣ ይህችን ቆጥቤ፣ ሃብት አፍርቼ... ኑሮዬን እቀይራለሁ፣ ነገ ቤት አሰራለሁ፤ ከነገ ወዲያ ትዳር እይዛለሁ ወደ ማለት መምጣት ጀምረዋል፡፡ መንግስት ባይደግፋቸውና ባያመቻችላቸው ከአረንቋ መውጣት የሚያቅታቸው ዜጐችም ትንሽ ደግፎ በእግራቸው መሮጥ እንዲጀምሩ ማድረግ ነው። አዝሎ መሄድ ሳይሆን እንዲሮጡ ሜዳውን የመጥረግ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ህብረተሰቡ አውቆ መጠቀም ጀምሯል፡፡ ይሄ ፍላጐት ተፈጥሯል፡፡ ቀሪው ምንድነው ካልን፣ የማስፋት ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በህብረተሰብ ዘንድ ለምን እንዲህ አይነት የግንዛቤና የተነሳሽነት ጅምር ተፈጠረ ከተባለ፤ ሰው ኑሮውን ምን ያህል መቀየር እንደሚችል በተጨባጭ ከተለወጡ ሰዎች በማየቱ ነው። ኢህአዴግ እነዚህን ለውጦች ለማስመዝገብ ውጤታማ ስትራቴጂዎችንና አቅጣጫዎችን ይዞ ሲሰራ የነበረው፤ ለአንድ ጊዜ የምርጫ ዘመቻ ብቻ አይደለም፡፡ የድርጅቱ መሠረታዊ እምነትና አቅጣጫ ስለሆነ ነው፡፡ የመንግስት እምነትና ፖሊሲ ሆኗል፡፡ ለበርካታ ዘመናት የተከማቸውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቅረፍ ከተሞቻችንንና የህዝቦቻችንን ኑሮ መቀየር የኢህአዴግ አላማ ነው፡፡
በመንገድ፣ በሃይል አቅርቦት፣ በስልክ እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች የኢህአዴግ ቁርጠኝነት በወዳጁም በባላንጣውም የሚታወቅ ነው፡፡ ይሄም ከተሞቻችንን እየቀየራቸው ነው፡፡ መንገዱ ሲሻሻል፤ መንገዱ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች እየተቀየሩ ይሄዳሉ። ሰዎች ለገበያ ያላቸው ቅርበት እየጨመረና ኑሯቸው እየተሻሻለ ይመጣል፡፡ አስር ሰዓት የሚፈጀው ጉዞ ወደ ሶስት ወይም አራት ሰዓት የሚያጥርበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጢሻ የነበሩ መንገዶች ወደ ዘመናዊ ትልቅ አስፋልት ሲቀየሩ፤ ኩስስ ብለው የቆዩ ቤቶች መቀየር ይጀምራሉ፡፡
በማህበራዊውም ዘርፍ ተመሳሳይ ነው። አሁን በየመንደሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ በዜጐች ላይ ኢንቨስት እያደረግን ነው፡፡ እውቀትና ክህሎት ያለው፣ አመለካከት የተቃናና ስራ ወዳድ የተማረ ዜጋ ማፍራት፤ ጥሮ ግሮ መኖር የሚፈልግ ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ወንዱንም ሴቱንም የሚጠቅሙ፤ ለጥቂቶች ሳይሆን ብዙሃኑን የሚያነቃንቁ የልማት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
በከተማ ከሚነሱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የኮንዶሚኒየም ግንባታ ነው። በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተነስቶ ነበር። በዘንድሮው ምርጫም 40/60 የቤቶች ፕሮጀክት እየተነሳ ነው። ነባሩ የኮንዶሚኒየም ግንባታ አፈፃፀሙ የታቀደለት ያህል አለመሆኑ አንድ ነጥብ ነው፤ እስካሁን በአዲስ አበባ ለነዋሪ የተላለፉት 80ሺ ቤቶች ናቸው። አዲሱ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ አለመጀመሩ፣ በዚያ ላይ መካከለኛ ገቢ ያለውን ህብረተሰብ ሳይሆን ቀድሞ ለቆጠበና ሙሉ በሙሉ መክፈል ለሚችል ዲያስፖራ ዕድሉ የሚያደላ ነው የሚል ትችቶች ተፈጥረዋል። ከዚህ አንፃር እንደ 97ቱ ምርጫ ኢህአዴግ የአዲስ አበባ ምርጫ አያሰጋውም?
አያሰጋውም፡፡ በመሠረቱ፣ ከኢህአዴግ ውጭ እንደዚህ ዓይነት ስትራቴጂዎችንና ፕሮጀክቶችን ሊያስብ የሚችል ሌላ ፓርቲ የለም፡፡ እንከን አለበት ከተባለምኮ፤ በጥሩ መንገድ እየሄደ ያለው ኢህአዴግ እንከኑን አስተካክሎ እንዲራመድ ማድረግ ነው አሁን ያለው አማራጭ። አንዲት ነገር ነጥሎ በማንሳት ሳይሆን፣ ሁለገብ በሆነ አቅጣጫ ህብረተሰብን ከስረ መሰረቱ የሚያነቃንቅና የሚጠቅም ፖሊሲ ያለው ሌላ ፓርቲ የለም፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ እንከኖቹን ራሱ ገና ሲፈጠሩ ቀድሞ ያገኛቸዋል፤ ለማስተካከልና ለማረም ይሰራል፡፡ የጐደለ ካለ ህብረተሰቡን ሙሉልኝ እያለ ይጠይቃል፡፡ ሁለገብ ፖሊሲ የያዘ፣ የራሱን ስህተት ቀድሞ የሚያወጣና የሚያርም፣ በጐደለው ደግሞ ህዝቡን ሙሉልኝ የሚል ሌላ ፓርቲ የለም።
በ1997 ዓ.ም የነበረው ሁኔታ አሁን ያለው ሁኔታ የለያያል። ኢህአዴግ አሁን የሚሠራባቸው ሃሳቦቹንና አቅጣጫዎቹን በፖሊሲ ደረጃ አስቀምጦ ወደተግባር ለመለወጥ ገና ሀ ያለበት ደረጃ ነበር ያኔ፡፡ ፖሊሲው ለምርጫ ሊባል የቀረበ ዘመቻ ቢሆንስ የሚል ጥርጣሬ በወቅቱ ቢፈጠር አይገርምም። አሁን እሱን አልፈነዋል፡፡ በአለፉት ዓመታት በተጨባጭ ኢህአዴግ ከምን ተነስቶ የት እየሄደ እንደሆነ ህብረተሰቡ አይቷል፡፡ የኢህአዴግ ፖሊሲ ለምርጫ ዘመቻ ተብሎ የቀረበ ሳይሆን፤ ብዙሃኑን እንደሚጠቅም ታምኖበት የተቀመጠ እንደሆነ በተግባር ታይቷል። በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችና የሚሻሻሉ ነገሮች የሉትም ወይ ከተባለ ይኖሩታል፡፡ ጥሩ ነው ተብሎ የታሰበው አቅድ፤ በኋላ ሲታሰብ ያልተፈለገ ተደራቢ ውጤት ያመጣ ይሆናል፡፡ እና ምን እናደርጋለን? ያዝ አድርገን እንፈትሸውና ሃሳቦችን አስተካክለን እንገፋበታለን።
ለምሳሌ የኮንዶምኒዬሙን ጥያቄ እንመለከት። በነባሩ የኮንዶሚኒዬም ፕሮጀክት፤ ዜጎች 20% ብቻ ቆጥበው 80% በመንግስት ብድር ይሸፈናል፡፡ አሁን ደግሞ 40% ለሚቆጥቡ ዜጎች 60% በመንግስት ብድር እየተሸፈነ እንሰጣለን እያልን ነው፡፡ አርባ በመቶ የቆጠቡ ዜጎች ከፍለው ኮንዶምኒዬም ሲረከቡ፤ እነሱ በከፈሉት ገንዘብ ተጨማሪ ኮንዶምኒዬሞችን መስራት ይቻላል - ለሌላውም እንዲዳረስ። ምንም ያልቆጠበ ሰው ከሌላው ቀድሞ ያለ በቂ ክፍያ ኮንዶምኒዬም ከወሰደ ግን፤ ተጨማሪ ቤቶችን ለመገንባት የሚረዳ የቁጠባ ገንዘብ አይኖርም። ከመንግስት እንጂ ከህብረተሰቡ የሚመጣ ገንዘብ ይቋረጣል። የቁጠባ አመለካከትን ይሰብራል። ለመንገድም፣ ለኤሌክትሪክም፣ ለዩኒቨርስቲም ለሁሉም ግንባታ ከመንግስት ካዝና መጠበቅ፤ ብዙ ርቀት አያራምደንም። ዞሮ ዞሮ የመንግስት እጅ ማጠሩ አይቀርም፡፡
ትክክለኛውን አቅጣጫ ከተገነዘብነው ግን፤ እስካሁን የቆጠበው ዜጋ ቤት ሲወስድ፣ እሱ በከፈለው ገንዘብ ቤት እየተገነባ አሁን እየቆጠበ ላለው ይደርስለታል። ይሄኛው በከፈለው ገንዘብ ደግሞ ወደፊት መቆጠብ ለሚጀምር ቤት ይሰራለታል፡፡ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። አለበለዚያ ግን የመንግስት አጆች ይታሰራል፡፡ በመንግስት ካዝና ብቻ እንስራ ከተባለ፤ ያለውን ገንዘብ በትኖ ከጨረሰ በኋላ ስራው ይቆማል፤ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ብዙሃኑን በቀጣይነት መጥቀም የሚቻለው፤ የቁጠባ ባህሉን ማጐልበትና የቆጠበውን ማበረታታት ሲቻል ነው፡፡
እኔ በመቶ ፐርሰንት ቆጥቤ እያለሁ አንድ ፐርሰንት ላልቆጠበ ሰው ቤት ከተሰጠው፣ መቆጠቤ ትርጉም አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ለቆጠበ ሰው የቅድሚያ እድል ቢያገኝ ግን፣ ሌላውም ለመቆጠብ ይነሳሳል፤ ተጨማሪ ቤቶችን የመገንባት አቅምም ይጨምራል። በጐ መንፈሱ ይሄው ነው፡፡ ያልተፈለገ ውጤቱ ደግሞ፤ ጥያቄው ላይ እንደተጠቀሰው ዲያስፖራ ወይም የተሻለ ገንዘብ የያዘ ዜጋ ይጨመርለታል፤ ገንዘብ የሌለው ዜጋ ደግሞ በችግሩ ውስጥ የሚቀጥልበት ነገር ያመጣል የሚል አተያይ አስከትሏል፡፡ እንዴት እናጣጥመው?
አሁን የተለምነው አቅጣጫ በአንድ በኩል የቁጠባ ባህልን የሚያሳድግ ትክክለኛና ልማታዊ የሆነ አቅጣጫ ነው፡፡ ለሁሉም የሚጠቅም አቅጣጫ ነው፡፡ በሌላ በኩል ገንዘብ ያለው ተጨማሪ ሃብት የሚያገኝበትና እጅ ያጠረው የማያገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ ሌላ ጉዳት አለው ማለት ነው፡፡ ቀስ ብሎ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ያዝ አድርጐ መንግስትም እንየው ቀስ ብለን እንግባበት ያለበት ምክንያት ይሄው ነው፤ መንፈሱ ግን የተቀደሰ ነው፡፡
ይቀጥላል

Read 4319 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 15:15