Saturday, 01 December 2012 10:47

የታክሲ ተጠቃሚዎች ከአቅማችን በላይ ክፍያ እየተጠየቅን ነው አሉ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

ከቦሌ ድልድይ ተነስተው በተለያዩ አቅጣጫዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች በሚያስከፍሉት እጥፍ ታሪፍ ተገልጋዮች መማረራቸውን ገለፁ፡፡ የታክሲ ሹፌሮች እንደሚሉት፤ በቦሌ መንገድ ሥራ የተነሳ የሚጓዙበት ርቀት በመጨመሩ እየጠየቁት ያለው ክፍያ አግባብ ነው፡፡ የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት በበኩሉ፤ ታክሲዎቹ ያደረጉትን የታሪፍ ጭማሪ እንደማያውቅና ህገወጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከቦሌ ድልድይ ኮሜርስ መስመር የሚሠራው የታክሲ ሹፌሩ ዳዊት ሀይሌ፤ ዋናው መንገድ እየተሠራ በመሆኑና ተለዋጭ ተብሎ የተዘጋጀው መንገድ የመኪና እቃ ስለሚሰብር በአትላስ ሆቴል መንገድ እንደሚጠቀምና 7 ብር እንደሚያስከፍል ገልጿል፡፡

አዲሱ 
መንገድ ኪሎ ሜትሩ ስለሚጨምር እና መንገዱ አንድ ብቻ በመሆኑ በሚፈጠረው ጭንቅንቅ ለረጅም ሰአታት እንደሚቆሙ የጠቆመው ዳዊት፤ እነዚህ ሁሉ የሚያስከትሉትን ወጪዎች ለማካካስ ተጨማሪ ክፍያ ለመጠየቅ መገደዳቸውን ይናገራል፡፡ከቦሌ አራት ኪሎ አምስት ብር እንደሚያስከፍል የገለፀው ሌላው የታክሲ ሹፌር ስንታየሁ ተሾመም፤ ታሪፍ መጨመራቸው ትክክለኛ እንደሆነ ያምናል፡፡ የመንገዱ መርዘምና የትራፊክ መጨናነቁ ለዋጋው መጨመር ምክንያት እንደሆነም ገልጿል - ስንታየሁ፡፡ ከቦሌ ድልድይ አውቶቢስ ተራ የሚሠራው ዳንኤል ይሄይስ ደግሞ 10 ብር ነው የሚያስከፍለው፡፡ ዳንኤልም ምክንያቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሔው የመንገዱ ተሠርቶ ማለቅ ብቻ መሆኑን የሚናገረው ዳንኤል፤ እስከዛው ድረስ ግን ተገልጋዩ ታክሲ አጥቶ ከሚሰቃይ ተጨማሪውን ክፍያ ከፍሎ መገልገሉ ይሻለዋል ብሏል፡፡ የታክሲ ሹፌሮች ለታሪፍ ጭማሪው ሌላው ምክንያት ነው ብለው የሚያቀርቡት፣ የተራ አስከባሪዎች ከታሪፍ ውጪ ማስከፈል ነው፡፡ ለተራ አስከባሪዎች በአንድ ጉዞ ከሁለት ብር እስከ ሦስት ብር ድረስ እንደሚከፍሉ የሚናገሩት የታክሲ ሹፌሮች፤ አንከፍልም ቢሉ ዘለፋና ቦክስ እንደሚገጥማቸው ገልፀው ችግሩን ለማን ማመልከት እንዳለባቸው እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡ የታክሲ ተገልጋዮች በበኩላቸው የታሪፍ ጭማሪው ኑሮአቸውን እንዳቃወሰው ይገልፃሉ፡፡ አቶ ሀሌሉያ አበባው ከቦሌ ድልድይ ሜክሲኮ የሚጓዘው ታክሲ ተጠቃሚ ሲሆን 2.70 ከነበረው መደበኛ ታሪፍ 

ወደ 5 ብር ከፍ ማለቱ ክፉኛ እንደጐዳቸው ይናገራሉ፡፡ ከቦሌ ድልድይ አውቶብስ ተራ የዘወትር

ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ሀቢባ አብዱልከማል ደግሞ በፊት በቀን አስር ብር ለትራንስፖርት ያወጡ

እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ግን ወጪያቸው ከ20-23 ብር እንደደረሰ ይናገራሉ፡፡ በመንገድ ብልሽት

እያሳበቡ ሹፌሮች የሚጨምሩት ታሪፍ ተገልጋዩን ከእቅድ ውጭ እንዳደረጉትና ገቢና ወጪው

እንዳልተመጣጠነ ጠቁመው፤ መንግስት ለችግሩ መፍትሄ እንዲያበጅ ጠይቀዋል - ወ/ሮ ሃቢባ፡፡

የአዲስ አበባ የመንገድና ትራንስፖርት ትራንስፖርት ኦፕሬሽን ማኔጅመንት የስራ ሒደት ባለቤት አቶ

ወጋየሁ አሠፋ በበኩላቸው፤ ጭማሪው እጅግ የተጋነነና መ/ቤቱ የማያውቀው ህገወጥ ታሪፍ መሆኑን

ገልፀው፣ መንገዱ በመቆፈሩ ምክንያት ታክሲዎች መንገድ ቀይረው ቢሠሩም የመ/ቤቱ ባለሙያዎች

ቦታው ድረስ ሄደው ርቀቱን መለካታቸውንና ከቀድሞው ኪሎ ሜትር አለመብለጡን ጠቁመው፤

መ/ቤታቸው ምንም አይነት የታሪፍ ጭማሪ አለማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ተገልጋዩ ከታሪፍ ውጪ

እንዲከፍል ሲጠየቅ በየቦታው ለሚገኙት የቀጠና ስምሪት ተቆጣጣሪዎችና ለትራፊክ ፖሊሶች

በመንገር ችግሩን መፍታት እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ቦሌ ድልድይ ያገኘነው የታክሲ ረዳት መለሰ

አለሙ ለተራ አስከባሪዎች ያልተገባ ክፍያ አልከፈልም በማለቱ ተደብድቦ እንደሚያውቅ ይናገራል፡፡

በፊት ለሚከፍሉት ክፍያ ደረሰኝ ይቆረጥላቸው እንደነበር የሚናገረው ረዳቱ፤ አሁን ግን ደረሰኝ

እንደሌለና ይሄንም የሚቆጣጠር አካል አለመኖሩን ይገልፃል፡፡
የቦሌ ድልድይ ተራ አስከባሪዎች ታምራት ተፈራ፣ እዩብ ካሳ እና ፀጋዬ ኪሮስ በበኩላቸው፤ ከታሪፍ

ውጪ የሚያስከፍል ተራ አስከባሪ የለም ይላሉ፡፡ “ነገር ግን መጐዳታችንን የሚያዩ ሹፌሮች

ጨምረው ሊሠጡን ይችላሉ፤ እኛ ግን አናስገድዳቸውም” ብለዋል፡፡ “ታክሲዎች ትርፍ ሲጭኑ እና

ከታሪፍ ውጪ ሲያስከፍሉ እንኳን እኛ ተጨማሪ ክፍያ አልጠየቅንም” የሚሉት ተራ አስከባሪዎቹ፤

ትኬት ካላለቀ በስተቀር ተቆርጦ እንደሚሰጥ ይናገራሉ፡፡ ችግር የሚፈጥሩባቸው የማህበራት ሀላፊዎች

እንደሆኑ ጠቁመው፤ የጫኑበትን አንከፍልም በማለት እንደሚጨቃጨቁና ያለ ተራቸው እንደሚጭኑ

ተራ አስከባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

Read 2901 times