Saturday, 24 November 2012 11:54

የገሐነሙ ጉዞ “የእኛ ሰዎች በየመን”

Written by  አልአዛር
Rate this item
(7 votes)

ጠዋት ሁለት ሰአት ከመሆኑ በፊት ሚኪሊላንድ ጐዳና እየተባለ በሚጠራው ከውሃ ልማት ቁልቁል ወደ ቺቺኒያ በሚወስደው መንገድ ላይ፣ አብዛኞቹ ልጅ እግር የሆኑና አዳዲስ ፖስፖርት በእጆቻቸው የያዙ ወጣት ሴቶች አልፎ አልፎ የሚያገኙትን ሰው “አዲሱ ጋምካ” በየት ነው?” በማለት እየጠየቁ ይጓዛሉ፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገራት በቤት ሠራተኛነት ለመቀጠር በየቀኑ ከሚጐርፉት ዜጐቻችን የተወሰኑት መሆናቸውን በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ ሁኔታቸውና ነገረ ስራቸው ያስታውቃል፡፡ እኒህ ከሌሎቹ የአረብ ሀገር ተሰዳጆች የሚለዩት ስደታቸውን መንግስት አውቆት፣ ምናልባትም የሚሠደዱበት ሀገር የመግቢያ ፈቃድ ሰጥቷቸው መሄዳቸው ነው፡፡ የእነዚህኛዎቹ ትልቁ ልዩነት ግን መደበኛ የአየር መጓጓዣ ትኬት ቆርጠው በአውሮፕላን መብረራቸው ነው፡፡

በህገወጥ መንገድ ከሚሠደዱት በሺዎች የሚቆጠሩ የእኛ ሰዎች የጉዞ ሁኔታ ጋር ሲወዳደር የእነዚህኞቹ ጉዞ “በገነት ውስጥ ባሉት መንገዶች” እንደ መጓዝ ሊቆጠር ይችላል፡፡ 
የሆነ ሆኖ አዲሱን ጋምካ አሳዩን እያሉ ገና ከማለዳው ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ሲንጋጉ የሚውሉት “እጩ ህጋዊ የእኛ ሰዎች”፤ በዚያ መንገድ የሚታዩት በሳምንቱ የስራ ቀናት ሁሉ ነው፡፡ ያ መንገድ ከማለዳው እስከ ቀትር ድረስ ባለው ጊዜ ከተራው እግረኛ ይልቅ እኒሁ የአረብ ሀገራት ስደተኞችን ሲያስተናግድ ይውላል፡፡
የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ያ መንገድ ገና በጠዋቱ ያስተናገደው እነኛን የተለመዱ መንገደኞችን ብቻ ሳይሆን አንድ የተለዩ መንገደኛን ጭምር ነበር፡፡ እኒህ የተለዩ መንገደኛም እንደሌሎቹ መንገደኞች “አዲሱ ጋምታ በየት ነው?” በማለት አላፊ አግዳሚውን ጠይቀዋል፡፡ የእኒህ ሴት የአጠያየቅ ቃና ከሌሎቹ ሁሉ በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡
ሴትየዋ እንደሌሎቹ ሴቶች ወደአረብ ሀገር ለመሰደድ የጉዞ ፕሮሰሳቸውን ለማስጨረስ አልነበረም የመጡት፡፡ ልጃቸው የበላው ጅብ አልጮህ ብሎ እንጂ፡፡
መጀመሪያ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፊት ለፊት በሚገኘው የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት አካባቢ “ልጄን ያያችሁ?” እያሉ ሲዋልሉ፣ በርካታ ሴቶች “ወደ አዲሱ ጋምካ! ወደ አዲሱ ጋምካ!” እያሉ ሲያወሩና ወደዚያው ሲሄዱ በማየታቸው ነው እስኪ እዚህም ወሬ የሚያውቅ ሰው ባገኝ ብለው የመጡት፡፡
ከጥቁር አንበሳ እስከ ውሃ ልማት ድረስ የመጡትም በእግራቸው ነው፡፡ ከዘሪሁን ህንፃ ትንሽ ወረድ ብሎ የሚገኘውን ኤልሳ ባርና ሬስቶራንት አለፍ እንዳሉ ያገኙትን አንድ በመካከለኛ እድሜ ላይ ያለ የሚመስል ሰውዬ፤ “አዲሱ ጋምካ ወዴት ነው” ብለው ጠየቁት፡፡ መንገዱን እያመለከታቸው ሳለ ድንገት መንታ ቦይ ሰርቶ እየገነፈለ መውረድ የጀመረውን እንባቸውን አየ፡፡
በድንጋጤ ክው ብሎ ምን እንደገጠማቸው እየደጋገመ ቢጠይቃቸውም፣ አንጀታቸው ውስጥ ገብቶ ክፉኛ የሚያንዘፈዝፋቸው ሳግ አላናግር ብሎዋቸው እንዲሁ ማልቀሳቸውን ብቻ ቀጠሉ፡፡
ወደ ላይና ቁልቁል የሚወጣና የሚወርደው መንገደኛ፣ እንደዚያ ባለ አንጀትን በሀዘን በሚያላውስ ሁኔታ በዝምታ የሚያነቡትን ሴትጠ ሲያይ ቆም እያለ “ምን ሆነው ነው?” “ምን ሆኑ?” በማለት በሹክሹክታ እየተጠያየቀ ቀስ በቀስ ከበባቸው፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግን አጀቡ በብዙ እጥፍ አድጐ የጥምቀት ታቦት አጀብ መሰለ፡፡
ሴትየዋ እንባቸው ፈሶ ፈሶ ያለቀ ሲመስልና ያንዘፈዝፋቸው የነበረው ሳግ መለስ ሲልላቸው፣ ምን አይነት ችግር እንደገጠማቸው ለማወቅ በእጅጉ ለጓጓው ሰው ሁሉ “እናንተዬ ልጄን የበላው ጅብ እኮ አልጮህ ብሎኝ ነው! ስደት ብሎ ከጓደኞቹ ጋር ወደ የመን ከሄደ ይሄው ሶስት አመቱ፣ ወሬው የለ፣ ድምጡ የለ… እናንተየ ሞቷል ብሎም የሚያረዳኝ ሰው እንኳ አጣሁ… ይሄው መጋቢያውን አየሁ የሚለኝ ባገኝ ብዬ ካገሬ ከወጣሁ ድፍን ሁለት ወሬ… የወለዳችሁ ፍረዱኝ… መንግስት ወዳገራቸው አግብቷቸዋል ብሎ ሬዲዮኑ ተናግሯል ብለው ነግረውኝ ይሄው የመንግስቱን ቤት ሁሉ እየዞርኩ ብጠይቅ ልጄን አየሁ የሚለኝ አጣሁ፡፡
አባትም እናትም ሆኜ ያሳደኩት አንድ ልጄ ነበረ፡፡ እናንተዬ እንግዲህ ምን ይዋጠኝ… እርም በላ ሆኜ ቀረሁት እኮ!” በማለት ተናገሩ፡፡
እንዲያ የከበባቸው ሰው ሁሉ የበኩሉን አስተያየት መስጠት ጀመረ፡፡ አንዳንዱ “ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄደው ይጠይቁ” ሲል፣ ሌላው ደግሞ “የለም ኢሚግሬሽን ነው መጠየቅ ያለባቸው” ይላል፡፡ ሌሎች ደግሞ “አይ ኦ ኤም ሄደው ካልጠየቁ ሌላ የሚነግራቸው ሰው ሊያገኙ አይችሉም፡፡” ሴትየዋ ግን ኢሚግሬሽን ከተባለው በቀር ሌሎቹ መስሪያ ቤቶች የት እንደሚገኙ የሚያውቁት ነገር ጨርሶ አልነበራቸውም፡፡ እናም ሆድ ባሳቸውና ፈሶ አልቋል የተባለው እንባቸው ድንገት እንደ አዲስ ገነፈለ፡፡
እኒህ ሴት ወይዘሮ የውብዳር ይባላሉ፡፡ በደቡብ ጐንደር ዞን የነፋስ መውጫ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡
የዛሬ አስራ አራት አመት በሞት ከተለዩዋቸው ባለቤታቸው የወለዱት ቀዳሚም ሆነ ተከታይ የሌለውና “አለሜ” እያሉ በቁልምጫ የሚጠሩት አንድያ ልጃቸው የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን በማቋረጥ፣ ከተወሰኑ የሰፈር አብሮ አደጐቹ ጋር በመሆን በህገወጥ መንገድ ወደ የመን ለመግባት የአፋር በረሃን በእግር አቆራርጠው ወደ ጅቡቲ የተጓዙት የዛሬ ሶስት አመት በ2001 ዓ.ም መግቢያ ላይ ነበር፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእነ አለሜ ወሬ ጨርሶ አልተሰማም፡፡ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ስለስደተኞች የሚሠማው ወሬ ግን አንድም ቸር ነገር የለውም፡፡ ግማሹ በሬዲዮ ሰማሁ በቴሌቪዥን አየሁ ብሎ ወደየመን የተሰደዱ ስደተኞች በሙሉ የባህር ውሃ በላቸው ሲል፣ ሌላው ደግሞ ገና እግራቸው የጅቡቲን ድንበር ሳይሻገር የአፋር በረሃ ከረሃብና ከውሃ ጥም ጋር ተባብሮ በአሸዋ ውጦ አስቀራቸው ይላል፡፡
ይህን ወሬ ተከትሎም የወላጅ አንጀት ወደር በማይገኝለት ጭንቀት ተኮማትሮ ኤሎሄ ሲል ይከርማል፡፡ በእንዲህ ያለ ጭንቀትና ጥበት ሶስት እጅግ ረጃጅም የሆኑ የመከራ አመታት ካሳለፉት ወደ የመን የተሰደዱ ስደተኞች ወላጆች አንዷ ወይዘሮ የውብዳር ናቸው፡፡ የጭንቀቱንና የጥበቱን አመታት ከሶስት አመት በላይ መግፋት አልቻሉም፡፡ እናም የልጄን ነገር ቁርጤን አውቄ እርሜን ባወጣ ይሻለኛል ብለው የልጃቸውን ወሬ ለማጠያየቅና ለማወቅ ከነፋስ መውጫ ገጠር ቀበሌ ሲገሰግሱ ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡
ወይዘሮ የውብዳር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የልጃቸውን ወሬ ማግኘት እንጂ የስንቅና መጠለያቸው ጉዳይ እምብዛም አላሳሰባቸውም፡፡ ስለ አዲስ አበባ ነዋሪ ደግነትና ልግስና በተደጋጋሚ ሰምተዋል፡፡ በእርግጥም ያለፉትን ሁለት ወራቶች ያሳለፉት ነዋሪው የሚለግሳቸውን ምጽዋት እየተመገቡና በየደጀሠላሙ እያደሩ ነው፡፡ እንደ እለት ጉርስና ማደሪያቸው ቀና ያልሆነላቸው የልጃቸው የአለሜ ወሬ ብቻ ነው፡፡
የሱን ወሬ ሰማሁ ወይም አየሁት የሚል አንድም እንኳ አልተገኘም፡፡ ዝም ብሎ የውሃ ሽታ ብቻ! ነገ የሚባል ቀንና ተስፋ ጨርሶ የሌለው!
ወይዘሮ የውብዳር የአንድ የአለሜ እናት ናቸው፡፡ ወደ የመን በህገወጥ መንገድ የተሰደደው ግን አንድ አለሜ ብቻ አይደለም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በያዝነው አመት ብቻ እንኳ ሃምሳ አንድ ሺ የአለሜ አይነት የእኛ ሰዎች በህገወጥ መንገድ ወደየመን በስደተኝነት ገብተዋል፡፡ እናም ስለስደተኛ ልጆቻቸው ጉዳይ አንዳች አይነት ወሬ አጥተው አንጀታቸውን በድርቡ አስረው ቀንና ሌሊቱን ወዬ ሲሉ የሚያሳልፉ ተጨማሪ ሀምሳ አንድ ሺ እናቶች አሉ ማለት ነው፡፡
የስደት ጉዞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደ የመን የሚደረገው የስደት ጉዞ የገሃነም ጉዞ ነው፡፡ በውስጡ ከሞትም የከፋውን ሞት አጭቆ የያዘ ነው፡፡ እናም የሞት ጥርሶች ያሉት የገሃነሙ ጉዞ በየቀኑ በእጁ የገቡለትን ወደ የመን ተሠዳጅ የእኛ ሰዎች የበላውን ያህል በልቶ፣ እንደ ተአምር በሚቆጠር እድል የተረፉትን በቅድሚያ የሚተፋው ሁዳይዳ፣ ሙካላ፣ ሙካህና ካራዝ ተብለው በሚታወቁ የየመን የቀይ ባህር የጠረፍ ከተሞች ላይ ነው፡፡
እንደ ወይዘሮ የውብዳር ያሉት የስደተኞች እናቶች፤ ከአዲስ አበባ ይልቅ ስለ ልጆቻቸው የተሻለ መረጃ ሊያገኙ የሚችሉት ወደእነዚህ የየመን የባህር ጠረፍ ከተሞች ቢሄዱ ነበር፡፡ ከእነዚህ ከተሞች በበለጠ ሁኔታም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚገኙበት ሁለት የታወቁ ቦታዎች አሉ፡፡ ሆስፒታሎችና እስርቤቶች፡፡ የመን የሚገኙ የተለያዩ እስርቤቶችና ሆስፒታሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን አጭቀው ይዘዋል፡፡ በየመን ወደሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር መስሪያ ቤት ሄዳችሁ “ለመሆኑ በየመን እስር ቤቶች ስንት ኢትዮጵያውያን ስደተኛ እስረኞች እንዳሉ ታውቃለህ” ብላችሁ ብትጠይቁት ምን ሳያቅማማና ጊዜያችሁንም ሳያባክን፣ ሁለት ሺ ኢትዮጵያውያን እስረኞች በተለያዩ የየመን እስር ቤቶች እንዳሉ ይነግራችኋል፡፡
የመረጃው ነገር አስቸጋሪ የሚሆንባችሁ ወደ የሆስፒታሎች ስትሄዱ ነው፡፡ እዚህ ለማወቅ የምትፈልጉትን የመረጃ አይነትና አጠያየቁን በደንብ ማወቅ ይጠበቅባችኋል፡፡
ወደ ሆስፒታሎች በተለይ ደግሞ እንደ ሁዳይዳና ሙካላ በመሳሰሉ የየመን የባህር ጠረፍ ከተሞች ወዳሉ ሆስፒታሎች ሄዳችሁ በሆስፒታሎች ውስጥ ስንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይገኛሉ ብላችሁ ብትጠይቁ፣ “በማቆያ በረዶ ቤት ውስጥ የሚገኙ አስከሬኖች ወይስ ተኝተው እየታከሙ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች?” የሚል መልስ ታገኛላችሁ፡፡ የሁለቱንም መረጃ ግን አስልተው ይነግሯችኋል፡፡
የየመን ሶስተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ታይዝ የሚገኘው ሆስፒታል በቀን በአማካይ የሠባት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስከሬን ከበረዶው የማቆያ ቤት አውጥቶ ለከተማው ማዘጋጃ ቤት በማስረከብ ለቀብር ያበቃሉ፡፡ በየመን የሚገኙ የእኛ ሠዎች ሆስፒታል ገብተው የሚሞቱንና በማዘጋጃ ቤት አማካኝነት የሚቀበሩትን ወገኖቻቸውን እድለኞች አድርገው ይቆጥሯቸዋል፡፡ የዚህን ምክንያት ስትጠይቋቸው፣ በሀዘንና በድንጋጤ ጉልበታችሁን የሚያብረከክ የስደት ጉዞ ገድል ይተርኩላችኋል፡፡
በአስር ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ታጉረው የፍዳ ህይወት ከሚገፉባቸው የየመን ከተሞች ውስጥ ከመዲናዋ ሰንአና ከወደብ ከተማዋ ኤደን ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የምትጠቀሰው የሀራዳህ ከተማ ናት፡፡ በዚች ከተማ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በያዝነው አመት ብቻ አንድ ሁለት ብሎ ቆጥሮ የመዘገባቸው አስራ ሁለት ሺ ስደተኛ የእኛ ሰዎች ታጉረው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ስደተኞች ወደዚች ከተማ የመጡት ከሳኡዲ አረቢያ ድንበር በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ስለምትገኝ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በቀላሉ መሻገር እንችላለን በሚል ተስፋ ነው፡፡
ይህን ተስፋ ይዘው ወደዚች ከተማ የሚጐርፉትን የእኛ ሰዎች፣ የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ቁጥራቸው አስራ ሁለት ሺ ነው ይበል እንጂ አንዳንድ መጃዎች ትክክለኛ ቁጥራቸው ከሀያ ሺ በላይ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡
እነዚህ ስደተኛ የእኛ ሠዎች እንዳሰቡት ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመሻገር፣ የድንበሩን ጥበቃ ማለፍ ያልቻሉ፣ ወደ ሌላ ሀገርም ሆነ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመመለስም ቤሳቤስቲኒ የሌላቸው ናቸው፡፡ በከተማው የተቋቋመው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ አለመጠን ከመጨናነቁ የተነሳ ስደተኛ የእኛን ሰዎች የምታገኟቸው በየጥጋጥጉ ወድቀው ለነፍስ ማቆያ ቁራሽ ሲለምኑ፣ አሊያም በየምግብ ቤቱ በራፍ ላይ ተኮልኩለው ትራፊ ለመብላት ሲራኮቱ ነው፡፡
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ስደተኛ የእኛ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ተስፋቸውን የጣሉት በአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ላይ ብቻ ነው፡፡ እንደ አለመታደልና ክፉ እጣ ሆኖ ይሄው ድርጅትም እንደነሱው ሁሉ በገንዘብ እጥረት በችጋር የሚጠበብ ነው፡፡ ባለፈው ሁለት ወር ገደማ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከዚሁ ከሀራዳህ የማጐሪያ ካምፕ አውጥቶና በአውሮፕላን አሳፍሮ የላካቸው አሜሪካ ከሚገኙ በጐ አድራጊዎች ባገኘው መጠነኛ የገንዘብ እርጥባን አማካኝነት ነበር፡፡
በየምግብ ቤቶች በር ላይ አሰፍስፈው ትርፍራፊ ለመብላት ሳይሆን ለመቅመስ ሲራኮቱ ከሚውሉት ስደተኛ የእኛ ሰዎች ውስጥ ታዲያ ሞላ የተባለ የአማራ ክልል ተወላጅ ይገኝበታል፡፡ የአስራ አምስት አመት ታዳጊ የሆነው ሞላ፣ የአስራ አምስት አመት ልጅ መሆኑን የሚመሰክር አንዳችም ነገር የለውም፡፡ የስደቱ የገሀነም ጉዞና አሰቃቂው የስደተኝነት ኑሮው ሁሉንም ነገሩን ነጥቆ በልቶበታል፡፡ ፀጉሩ ሸብቷል፡፡ አይኖቹ ሞጭሙጨዋል፡፡
ረሀብ በምህረት የለሽ ምላሹ ያጐሳቆለው ሰውነቱ ጐብጧል፡፡ ከእርዛቱ መክፋት የተነሳ መላ አካሉን የሸፈነው በአንድ እጅግ አዳፋ የትልቅ ሰው ኮት ነው፡፡ ባለፈው አመት የካቲት ወር ላይ “ለመሆኑ የስደቱን የገሀነም ጉዞ እንዴት አመለጥከው?” ተብሎ ተጠይቆ ነበር፡፡ የሞጨሞጩትንና ህይወት አልባ የሆኑትን አይኖቹን መሬት ላይ ተክሎ በግራ እግሩ አውራ ጣት አሸዋውን እየጫረ የዚያን አሠቃቂ የስደት ጉዞ ገድል መተረክ ጀመረ -
“ከሠሜን ወሎ ተነስተን ያን አሰቃቂ የስደት ጉዞ የጀመርነው በአፋር በረሀ ላይ ነው፡፡ በአፋር በረሀ አንድ ቀን ተኩል ያህል እንደተጓዝን ቀማኞች አገኙንና ክፉኛ ከደበደቡን በኋላ፣ የያዝነውን ገንዘብ እንዳለ ዘርፈው ጥለውን ሄዱ፡፡ በዚያ ዘግናኝ በረሀ ለአንድ ሳምንት ያህል በእግራችን ተጓዝን፤ አብረውን ሲጓዙ ከነበሩትውስጥ ሁለት ሴቶችና አንድ ከእኛ በእድሜ በለጥ የሚል ሰውዬ በውሀ ጥም የተነሳ መራመድ አቅቷቸው ወደቁ፡፡ ይደርሱብናል ብለን ብንጠብቃቸውም ሳይመጡ ቀሩ፡፡ አንደኛዋን ልጅ “እስኪ እንያቸውና እናምጣቸው ትንሽ ውሀ እሰጥሀለሁ” ስትለኝ እሺ ብያት አብሬያት ወደ ሁዋላ ተመልሰን ሄድን፡፡ ትንሽ እንደሄድን አሸዋው ላይ አንድ ሰው ወድቆ አየን፡፡ ቀርበን ስናየው ያ ትልቁ ሰውዬ ነው፡፡
ሰውነቱን ትልልቅ ጉንዳኖች ወረውታል፡፡ እሷ አንተየ! እያለች ደጋግማ ብትጠራውም አልመለሰላትም፡፡ ወዲያው ልጅቱ “እኔን አፈር ይብላኝ” እያለች ወደ ታች መሄድ ስትጀምር እኔም ተከተልኳት፡፡ ወዲያውኑ ግን ሁለቱን ሴቶች አሸዋው ላይ ወድቀው አገኘናቸው፡፡ ብንጠራቸው አይሰሙም፡፡ ዘመዴ ናት ያለቻትን ልጅ እጅ ይዛ ብትጐትታትም አትሰማም፡፡ እሷ የዘመዷን እጅ ይዛ ስትጐትት አይቼ፣ እኔም ሌላኛዋን ሴት ጐትቼ ለማንሳት ብዬ እጇን ስይዘው ግርር ብሎ እንደ በረዶ ይቀዘቅዛል፡፡
በዚያ በረሀ ሠውነቷ እንዲያ መቀዝቀዙ በጣም ያስገርማል፡፡ ልጅቱ “እኔ ካፈሩ ልግባልሽ!” እያለች እያለቀሰች አሸዋውን ስታለብሳት ዘመዷ መሞቷ ገባኝ፡፡ ከዚህ በፊት የሞተ ሰው አይቼ ስለማላውቅ በጣም ከመደንገጤና ከመፍራቴ የተነሳ ሽንቴ አመለጠኝ፡፡ ከዚያ ይህችኛዋንም አሸዋውን እንደ ነገሩ አለበስናትና ተመለስን፡፡
የዛን ቀን አስፈሪ ቅዠት ሲያሰቃየኝ አደረ፡፡ የዛች የሞተችው ልጅ እጅ አሁንም አሁንም እየታየኝ በፍርሀት ስንዘፈዘፍ ነጋልኝ፡፡ “ለአንድ ሳምንት ያህል በእንዲህ ያለ ሁኔታ በበረሀው ከተጓዝን በኋላ ታጁር ተራራ ላይ ደረስን፡፡ ከዚያ ትንሽ እንረፍ አልንና ባገኘነው ላይ ጋደም አልን፡፡ ወዲያው ግን የለቅሶ ድምጽ ሰምቼ ዘወር ስል፣ አጠገቤ የተኛው ሰውዬ እየተንሰቀሰቀ “አወይ ልጆቼ!” እያለ ያለቅሳል፡፡ ከሱ አጠገብ የተኛችው ወጣት ሴት ደግሞ “ስለነፍስ! ውሀ! ውሀ! እያለች ታቃስታለች፡፡ በእኔ ግርጌ በኩል የተጋደሙት ሁለቱ ወጣቶች ብቻ በፀጥታ ተኝተዋል፡፡ አይናቸው ግን አልተከደነም፡፡ “ጉዞ እንጀምር ተነሱ ሲባል እነዚያን ወጣቶች ተነሱ ብላቸዉ መልስ ሳይሠጡኝ ዝም ብለው ትክ ብለው ያዩኛል፡፡ መሞታቸውን የተረዳሁት መንገድ የሚመራን ሰውየ አይናቸውን ሲከድነው ብቻ ነው፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ጅቡቲ እስክንደርስ ድረስ በርካታዎቹ ሲሞቱ አየሁ፡፡ መንገዳችን የሞት መንገድ ነበር፡፡ እኔ ከሞት እንዴት እንዳመለጥኩ አላውቅም፡፡ ምናልባት ቀኔ ስላልደረሰ ይሆናል…” የአስራ አምስት አመቱ ሞላ ገሀነሙን የየመን የስደት ጉዞ የተጓዘው በእንዲህ ያለ ሁኔታ ነው፡፡ የየመንን መሬት እግሩ ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሠቦቹ ጋር ጨርሶ ተገናኝቶ ስለማያውቅ፣ የቤተሠቦቹን ጭንቀት መገመት መቼም ቢሆን አይከብድም፡፡ የሞላ እናት ከአለሜ እናት የሚለዩት ምናልባት የልጃቸውን ወሬ ፍለጋ እንደ ወይዘሮ የውብዳር ወደ አዲስ አበባ ያልመጡ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ለሞላ ያንን እጅግ አሰቃቂ ጉዞ ማጠናቀቁ ያስቀረለት ነገር ቢኖር የበረሀውን ንዳድ ብቻ ነው፡፡ በጉዞው ወቅት አብረውት ሲጓዙ የነበሩና በረሀብና በውሀ ጥም የበረሀው አሸዋ ላይ በየቦታው ድፍት ብለው የቀሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መላ ሁኔታ በየእለቱ በህልሙ እየመጡበት በክፉ ቅዠት ሲንዘፈዘፍ ማደሩ እንደሁ ዛሬም አልቀረለትም፡፡
የዚህ ምስኪን ልጅ ፈተና ይሄ ብቻ ቢሆን እንደ እድለኛ በተቆጠረ ነበር፡፡ ረጅሙን አስፈሪ ቅዠታም ሌሊት የማለዳው ንጋት ሲገላግለው፣ ከጠዋት እስከ ምሽት ለነፍስ ማቆያ ብቻ የሚበጅ ቁራሽ ለማግኘት የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ይቀበለዋል፡፡ እናም የየእለት ህይወቱ ልክ እንደ በረሀው ጉዞ ያለ ነው፡፡ ህይወትን ለማቆየት ከሞት ጋር የሞት የሽረት ግብግብ መግጠም፡፡ የአይሻ ኑርሁሴን፣ የሀፍቶም ግደይ፣ የግርማ በዳዳና የኑርሀሴን ሽፋ (የአባታቸው ስም ተቀይሯል) እናቶችስ በአሁኑ ወቅት በልጆቻቸው ነገር እንዴት ሆነው ይሆን? እነ አይሻና እነ ሀፍቶምስ የገሀነሙን ጉዞ ተጉዘው የሀራዳህን የስደተኞች መጠለያ ለማጣበብና ለአስፋልት ዳር ህይወት የበቁት እንዴት ነው? ታሪኩ ልክ እንደ ገሀነሙ ጐዳና ማለቂያ የለውም፡፡

Read 3723 times Last modified on Saturday, 08 December 2012 14:08