Saturday, 24 November 2012 11:33

“ሆላንድ ካር” በኪሣራ ተዘጋ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ከሆላንድ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠም ሥራውን የጀመረው ሆላንድ ካር በከፍተኛ ኪሣራ መዘጋቱ ይፋ ሆነ፡፡ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ታደሰ ተሰማ ከአገር መውጣታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሰሞኑን ካሉበት አገር ሆነው የኩባንያውን መዘጋት በስልክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡ 
ለኩባንያው መዘጋትም ዋንኛው ምክንያት የደረሰባቸው ከፍተኛ ኪሣራና ከዘመን ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ ለመክፈል አለመቻላቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ “ዛሬ ቀኑ ለእኔ እጅግ የሚያሳዝን ቀን ነው፡፡ ብዙ ራዕይ ነበረን፣ ብዙ ገንዘብም አፍስሰን ነበር፡፡

ሆኖም እንዳሰብነው ሊሆንልንና ሊሣካልን ባለመቻሉ ኩባንያችን እንዲዘጋ ግድ ሆኗል፡፡” ሲሉ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የደረሰባቸውን ኪሣራና የገንዘብ እጥረት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ገልፀዋል፡፡ 
ከዘመን ባንክ የወሰዱት ከፍተኛ የብድር ገንዘብ መክፈያ ጊዜ በማለፉ ኩባንያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌላ መፍትሔ እስካላመጣ ድረስ ባንኩ ኩባንያውን በጨረታ መሸጡ የማይቀር መሆኑንም ኢንጅነር ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ላለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ ኪሣራ ሲያስተናግድ መቆየቱን የተናገሩት ኢንጅነር ታደሰ፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ18-20 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ኪሣራ እንደደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡
የድርጅቱን ሠራተኞች የወደፊት እጣ ፋንታ አስመልክተው ሲናገሩም፤ ኩባንያው በደረሰበት ከፍተኛ ኪሣራ ሲዘጋና ምርትና ሽያጭ ሲያቆም ለሠራተኞቹ ደመወዝ መክፈል ስለማይችል ሠራተኞቹ ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደሚገደዱ አረጋግጠዋል፡፡
ይህ ሁኔታ በምን መልኩ እንደሚከናወን ግን ገና ያልታወቀ ጉዳይ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከኩባንያው ጋር የአዳዲስ መኪኖች ውል ፈጽመው ገንዘብ የከፈሉና መኪኖቻቸውን ያልተረከቡ 180 የሚደርሱ ደንበኞችን ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩም፤ ደንበኞቻችን መፍትሔ የሚያገኙበትን ዘዴ እየሰራን ነው፡፡
ምን አይነት መፍትሔ እንደሚሆንና በየትኛው መንገድ መፍትሔውን እንደምንሰጥ በ10 ቀናት ውስጥ ለደንበኞቻችን እናሳውቃለን ብለዋል፡፡ ከአገር ስለወጡበት ጉዳይና ወደ አገራቸው መቼ እንደሚመለሱ ለቀረበላቸው ጥያቄም “ከአገር የወጣሁት አንዳንድ መጨረስ ያሉብኝን ጉዳዮች ለመጨረስና በአንዳንድ ችግሮች ላይ መፍትሔ ለማፈላለግ ነው፡፡ ወደ አገሬ መመለሴ የማይቀር ቢሆንም መቼ እንደሚሆን ግን አላውቅም፡፡
በአጭር ጊዜም እመለሳለሁ ብዬ አላምንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኩባንያው ላለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ መኪና የመገጣጠም ሥራ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን እስከአሁን ድረስ በርከት ያሉና የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን የቤት መኪኖች በመገጠጣጠም ለደንበኞቹ ሲያስረክብ ቆይቷል፡፡
.ኤ.አ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ደግሞ “አሃዱ” የተሰኘ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ለሙከራ አምርቶ ያስመረቀ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

Read 3522 times