Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 11:28

የቅ/ላሊበላ ደብር ሒሳብ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የሁለቱን ሆቴሎች ባለቤትነት ወደ ገዳሙ ይዞታ የማዛወር ሂደት ተጀምሯል
በወጣው ዜና ‹‹ስሜ ጠፍቷል›› ያሉት የደብሩ አስተዳዳሪ ነዳያኑን ምግብ ከልክለዋል
በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም ሒሳብ በገለልተኛ የውጭ ኦዲተር እንዲመረመርና ‹‹ሀብቱን በሙስና እና ብኵንነት አጥፍተዋል፤ በካህናቱ፣ በሊቃውንቱና በሠራተኞቹ ላይ የአስተዳደር በደል አድርሰዋል፤ ምእመናንን እየዘለፉ ሕዝብንና መንግሥትን አጋጭተዋል›› የሚሉ አቤቱታዎች እየቀረቡባቸው የሚገኙት የገዳሙ አስተዳዳሪ መመህር አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን በሕግ እንዲጠየቁ የቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም አስጎብኚዎች ማኅበር፣ የገዳሙ ካህናት እና ምእመናን ጠየቁ፡፡

በቱሪስት መስሕብነቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዓመታዊ ገቢ የሚያስገኘው የቅዱስ ላሊበላ ደብር፤ የተለያዩ የልማት ተቋማት ቢኖሩትም አስተዳደራቸው በጥቅም በተሳሰሩ የመምህሩ ደጋፊዎች እና ዘመድ አዝማዶቻቸው የሚመራ በመኾኑ ለሙስናና ብኵንነት እንደተጋለጠ ለአዲስ አድማስ የገለጹት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የልማት ተቋማቱ ሒሳብ ፈቃድ ባለው የውጭ ኦዲተር ተመርምሮ ብክነቱ ከተለየ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአስተዳዳሪው ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ እንድትመሠረት ከመጠየቃቸውም ባሻገር የሕዝብንና የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ ለግል ጥቅም በማዋል ከባድ የእምነት ማጉደል በሙስና ወንጀል የሚጠየቁበትም አግባብ እንዲታይ አመልክተዋል፡፡
በአስተዳዳሪው ይፈጸማል ስለተባለው ሙስናና የአስተዳዳር በደል የተመለከተው ዜና ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከተዘገበ በኋላ በሰባት ሚልዮን ብር የገዳሙ ገንዘብ የተገዛውና በግለሰቦች ስም እንደተመዘገበ የተነገረው የይምርሐ ሆቴል ፈቃድን ወደ ገዳሙ የማዛወር ሂደት መጠናቀቁን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በገዳሙ ገንዘብ ቢገነባም የግንባታ ወጪው እና አስተዳደሩ አጠያያቂ ነው የተባለው የቤተ አብርሃም ሆቴል ፈቃድ ዝውውር ደግሞ በመካሄድ ላይ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
የቀድሞው የቼክ አሠራር ተቀይሮ በደብሩ አስተዳዳሪ እና ገንዘብ ያዡ ፊርማ ብቻ ይንቀሳቀሳል የሚባለው የደብሩ ገንዘብ በመምህሩ ትእዛዝ ብቻ ወጪ እንደሚደረግ የሚያስረዱት ምንጮቹ፤ ደብሩ በስጦታ የተረከበው መኪና በገንዘብ እንደተገዛ፣ ከቀረጥ ነጻ የገባ መኪና ቀረጥ እንደተከፈለበት እየተደረገ መግባቱ፣ የቱሪስት ማመላለሻ ነው የተባለው ሚኒባስ ባለቤትነትና የሥራ ፈቃድ እያወዛገበ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ አስተዳዳሪው ከደብሩ ገቢ ለቅርሶች ጥገናና ክብካቤ 15 በመቶ በጀት እንዲያዝ እንደቀረበ የተነገረውን ጥያቄ ያልተቀበሉበትን፣ አብነት ት/ቤቶች በገዳሙ እንዲታቀፉ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተሰጥቷል የተባለውን ትእዛዝ በተደራቢ ሥራነት በማየት ተፈጻሚ ያላደረጉበትን ኹኔታም በዕቅዱ ቅንነት ላይ ለሚያነሡት ጥርጣሬ በማጠናከሪያነት ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል የደብሩን ችግር የዘገበው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለኅትመት ከዋለ ጀምሮ የገዳሙን ካህናትና ሠራተኞች በመሰብሰብ እንዲሁም በመንግሥታዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት በዜና ዘገባው ስማቸው መጥፋቱን እየገለጹ የሚገኙት የገዳሙ አስተዳዳሪ መምህር አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን÷ ገዳሙ በቋሚነት የሚረዳቸውን 65 የከተማውን ድኾች ምግብ እንዳይሰጣቸው በማገድ ነዳያኑ ዘገባውን በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር እንዲቃወሙ በማስገደድ ‹‹እያስራቧቸው ነው›› ይላሉ - ምንጮቹ፡፡
አስተዳዳሪውን የተቃወሙና በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራቸው የተባረሩ፣ ማስጠንቀቂያና የደመወዝ ቅጣት የተወሰነባቸው ካህናት እና ሠራተኞች፤ ከንስሐ አባቶቻቸው የተለዩ ምእመናን፣ ከገዳሞቻቸው የተባረሩ መነኰሳትና መነኰሳዪያት፣ ከሰበካ ጉባኤ አባልነትና አመራርነት የተባረሩና እንደሚባረሩ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ምእመናን ቁጥር ከሰባ እንደማያንስ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት የደብሩ ምንጮች÷ ምእመናን በአጠቃላይ እና የተወሰኑ ደጋፊዎቻቸው በተለይ የዜናውን መረጃ ሰጥተዋል ተብለው በሚጠረጠሩ ምእመናን ላይ አካላዊ ጥቃት እንዲያደርሱ በልዩ ልዩ ቅስቀሳዎች በመገፋፋት ላይ መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በነገው ዕለት ከቅዳሴ በኋላም የዜና ዘገባው ካስከተለው ውጤት ጋራ የተያያዘ ነው በተባለ ጉዳይ ካህናቱ፣ ምእመናኑና ጥቂት የከተማው አስተዳደር ባለሥልጣናት በቅ/ላሊበላ ደብር ዐውደ ምሕረት ስብሰባ መጠራታቸውን የከተማው ነዋሪዎች ጥሪው ተላልፎበታል የተባለውን ደብዳቤ በምንጭነት በመጥቀስ ለዝግጅት ክፍሉ ተናግረዋል፡፡ መምህሩ ከፍተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው በአስተዳዳሪነት ከተቀመጡበት ቅ/ላሊበላ ደብር ይልቅ በአዲስ አበባ በየቀኑ ብር ሁለት መቶ አበል እየታሰበላቸው ምንጩ ሳይታወቅ እንዳሠሯቸው በሚነገርባቸው ቤቶች የሚያሳልፉት ጊዜ ይበልጣል ያሉት ምእመናኑ÷ አባ ገብረ ኢየሱስ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ማንንም ሳያስፈቅዱ ወደ አሜሪካ ሄደው ለሁለት ወራት መቆየታቸውን በማስታወስ አሁን በተፈጠረው የአስጎብኚዎች ማኅበር፣ የካህናትና ምእመናን ግፊት ምክንያት ከተጠያቂነት የሚሸሹበት ኹኔታ እንዳይኖር ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ የቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም ከንጉሥ ላሊበላ ዘመን ጀምሮ የሚጠራበትን የሊቀ ካህንነት ክብር እንደያዘ “መምህር” ተብሎ በሚጠራና በድንግልና በመነኮሰ ካህን እንዲተዳደር ሥርዐት መሠራቱን፣ መምህሩ በሞት በሚለይበት ወይም ደግሞ በዕድሜ ገፍቶ ማስተዳደር ሲሳነው ከካህናቱ መካከል በካህናቱ ጉባኤ ይመረጥና ሹመቱ በቀደመው ዘመን በንጉሠ ነገሥቱ በኋላም በፓትርያሪኩ ሲጸድቅ የገዳሙ አስተዳዳሪ (መምህር) እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ በአስተዳዳሪነት የቆዩት አባ ገብረ ኢየሱስ እንዳሉባቸው በሚዘርዝሯቸው በርካታ የሥነ ምግባር ችግሮች ምክንያት ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በሕግ እንዲጠየቁ የሚሹት ካህናቱና ምእመናኑ÷ የቅ/ላሊበላ አብያተ መቅደስን በቀጣይነት የሚያስተዳድረው መምህር አመራረጥና አሿሿም ከቦታው ታላቅ አገራዊ ፋይዳና ዓለም አቀፋዊ ደረጃ፣ ሕዝቡ ከካህናቱና ከአብያተ መቅደሱ ጋር ፈጥሮት ከቆየው ቤተሰባዊነት አኳያ በመንፈሳዊም ሆነ በዘመናዊ ትምህርት ከፍ ያለ ደረጃ ያለው፣ በሥነ ምግባሩ የታወቀና አርኣያ መሆን የሚችል ሰው መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

Read 3952 times