በየጊዜው ለሚለዋወጠው የሕዝብ ዕድገት ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠትና የፖሊሲ ውሳኔ ለውጥ ለማድረግ ጥሩ መረጃ (ዳታ) በጣም አስፈላጊ ነው ያሉት የዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ ተወካይ፤ የሚሠራና የሚተማመኑበት ወቅታዊ፣ ባህላዊ ጠቀሜታ ያለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማነፃፀር ፖሊሲ ለመቅረጽና ለፕሮግራም ልማት ትግበራ ክትትልና ምዘና ጥሩ መረጃ በጣም ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
ገንዘብ ፈንድ በማድረግና በማኔጅመንት ተጨባጭ ውጤትና ለማስመዝገብና ተጠያቂነትን ለማስፈን መረጃ በሁሉም የዩ ኤን ኤጀንሲዎች ጠቃሚ መሆኑን ተወካዩ ገልፀው፤ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምርምር በማድረግ የልማት ተሳትፎ የልማት ውጤትን ምን ያህል እንደሚጐዳና እንደሚጠቅም ለመረዳት መረጃ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በብዙ የአፍሪካ አገሮች የትምህርትና የጤና መረጃዎችን በማሰባሰብ ጥሩ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ የጊዜ አጠቃቀምን ጨምሮ በፆታ ጉዳዮች ፣ በሴቶች ላይ በሚፈፀም ጥቃትና የሥራ ቅጥርን በተመለከተ መረጃዎችን ማጠናቀር ገና ብዙ እንደሚቀር ገልፀዋል፡፡
በዓሉን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከተመድ የሥነ ሕዝብ ጽ/ቤትና ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስታቲስቲክስ ዘርፍ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ኤጀንሲው ላለፉት 50 ዓመታት ያደረገው የሥራ እንቅስቃሴና ያለፈባቸውን የዕድገት ደረጃዎች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ቀርቧል፡፡