Saturday, 24 November 2012 11:21

ኢቢኤስ ተመልካች በትዕግስት እንዲጠብቀው ጠየቀ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ስርጭት ለሦስተኛ ጊዜ መቋረጡን ድርጅቱ አስታወቀ፡፡ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን አለምአቀፍ ማኔጅመንት እንዳስታወቀው፤ ጣቢያው ሁለት ጊዜ ከአረብሳት እንዲወርድ ከተገደደ በኋላ በዩተልሳት 7 ዌስት (EUTELSAT 7W) በድጋሚ ስርጭቱን ቢጀምርም ከ14 ቀናት በኋላ የአዲሱ የሳተላይት መስመር (በዩተልሳት 7 ዌስት’ የስርጭት መስመር በፍሪኩዌንሲ 10815) ከህዳር 5 ቀን 2005 ማለዳ ጀምሮ ካልታወቀ አቅጣጫ በተደረገ ከፍተኛ የሳተላይት ሲግናል ማዛባትና “ጃሚንግ” ከዩተልሳት የስርጭት መስመር እንዲወርድ ተደርጓል፡፡

ከአቅማችን በላይ በሆነና ሰሚ ባጣነው ህጋዊ ያልሆነ እርምጃ መደበኛ ስርጭታችን ተስተጓጉሏል” ያለው ጣቢያው፤ በተደጋጋሚ እና በተመሳሳይ ሁኔታ ተጠቂ መሆኑን ገልፆ “ተመልካቾች የተለመደውን ድጋፋችሁን እና ትእዕግስታችሁን እንዳትነፍጉን” ብሏል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ስርጭት እንደሚመለስም ኢቢኤስ አስታውቋል፡፡
በአረብ ሳት ለሁለት ጊዜያት፣ ከዚያም በኋላ በዩትልሳት ለሶስተኛ ጊዜ የተቋረጠው የቴሌቭዥን ጣቢያው ብቸኛ ገቢው ከማስታወቂያው የሚያገኘው በመሆኑ ስርጭት ከሌለው ለኪሳራ መዳረጉ የማይቀር ነው ያሉት የድርጅቱ ተወካይ፤ አላማችን ስርጭቱ እንዲቀጥል መፍትሄ ማፈላለግ እንጂ ጣቢያውን መዝጋት አይደለም ብለዋል፡፡ ኢቢኤስ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በብሮድካስት ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምና ቀልጣፋ አሰራር በመከተል አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞችን እንዳቀረበ የጠቆመው የድረገፅ መረጃው፤ በመላው ዓለም በአጭር ጊዜ ውስጥ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ተመልካቾችን እንዳፈራ ያመለክታል፡፡
ድርጅቱ ጥቅምት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ላይ በድረገፁ ይፋ ባወጣው መግለጫ፤ የአረብ ሳት የሳተላይት ኩባንያ መስከረም 15 ቀን 2005 ዓ.ም የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስርጭትን ያለምንም ማስጠንቀቅያ ከሳተላይት ማውረዱን አመልክቶ፤ የእርምጃው መንስኤ ከደቡባዊ የኤርትራ ምድር አቅጣጫ በተላከ የሳተላይት ሲግናል ማዛባትና እቀባ ወይም “ጃሚንግ” ምክንያት መሆኑን አብራርቷል::
ጣቢያችን ለ25 ቀናት ተቋርጦ የነበረው ስርጭቱ እንዲመለስ ከብዙ ድርድር እና ክርክር በኋላ ጥቅምት 7ቀን 2005 ወደ መደበኛ የአየር ስርጭቱ ቢመለስም፣ በሚያሳዝንና ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ አየር በተመለስን በሶስት ቀናት ውስጥ አረብሳት ከኤርትራ ደረሰብኝ ባለው የሲግናል መዛባት እና ቀረበብኝ ባለው አቤቱታ ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ የሳተላይት ስርጭቱ እንደተቋረጠበት ድርጅቱ ገልጿል:: ሁለተኛውን እርምጃ ለየት የሚያደርገው የአረብሳት ከኤርትራ መንግስት የኢንፎርሜሽን መስርያ ቤት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስርጭት ከአረብሳት እንዲቋረጥ ተፅፎ ተላከልኝ ባለው ደብዳቤ ላይ ተመስርቶ በድጋሚ ስርጭታችንን ማቋረጡ ነው የሚለው ማኔጅመንቱ፤ የአቤቱታ ደብዳቤው የኢቢኤስ ፕሮግራሞችን ሁሉን አቀፍ የአስተማሪነትና የአዝናኝነት ሚና በመካድ በደፈናው ግጭትን የሚቀሰቅሱ አሉታዊ ፕሮግራሞችን ያቀርባል የሚል መሆኑ ነው ብሏል፡፡ አቤቱታው መሰረተቢስ መሆኑን ለአረብሳት ደጋግሞ እንዳሳወቀ ገልጿል፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያው በአሜሪካ ህግ የተቋቋመ የግል የቴሌቪዥን ኩባንያ ከመሆኑም በላይ ፖለቲካዊ ይዘት ላላቸው ዜናዎችም ሆኑ ፕሮግራሞች ትኩረት እንደሌለው የጠቆመው ማኔጅመንቱ፤ ባለፉት ሁለት አመታት ከማናቸውም ሃገራት፣ መንግስታትና ቡድኖች ምንም አይነት አቤቱታ እንዳልቀረበበት እና ከማናቸውም ወገኖች ጋር በሰላም የመስራት አላማ እንዳለው ጠቅሶ፤ ይሄን ሁሉም አካላት እንዲረዱለት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል፡፡

Read 2990 times