Print this page
Saturday, 17 November 2012 11:58

ዶክተሯ

Written by  ሱራፌል መካሻ
Rate this item
(4 votes)

አዳማ 3፡15 ጠዋት
ጭንቅላቴ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ቡጢ ያሳረፈበት ይመስል እጅጉን እየከበደኝና እያዞረኝ ነው:: ሙሉ በሙሉ ከእንቅልፌ አልነቃሁም:: ምን ነበር የተፈጠረው?......ምንም የማስታውሰው ነገር የለም:: ከአንገቴ ቀና ብዬ ዙሪያ ገባውን ማየት ጀመርኩ:: ነጭ አንሶላ ለብሼያለሁ:: አንድ ነጭ ጠረጴዛ አልጋው ጎን ተቀምጧል:: በላዩ ላይም ነጫጭ ጠርሙሶች ይታያሉ:: ነጭ አምፖል በርቷል:: ግድግዳው ነጭ ቀለም ተቀብቷል:: ባጠቃላይ ክፍሉ ነጭ ነው:: በልጅነቴ ቤተሰቦቼ “ገነት” የሚባለው ቦታ ይሄን ይመስላል ብለው ከነገሩኝ ጋር ተመሳሰለብኝ:: እውነት ያለሁት “ገነት” ውስጥ ነው እንዴ?

ከደቂቃዎች በኋላ አንዲት ቆንጅዬ ሴት መጣች:: የጸጉሯ ርዝመት ከኤፊል ታወር አይተናነስም ብል ማንም አጋነንክ አይለኝም:: አይኖቿ በጥሩ ሰአሊ የተነደፉ ስእላት፣ ጉንጮቿ ታታሪ ገበሬ ተንከባክቦ ያሳደጋቸው ፖሞች፣ አንገቷ፣ እንትኗ፣ ልዩ ናቸው፡፡ ከንፈሯን ገለጥ ጥርሶቿን ፈልቀቅ ስታደርጋቸው ከጥርሶቿ የሚወጣው ብርሃን ከጸሀይ ሰባት እጥፍ በልጦ አለምን ለማብራት እንደሚበቃ ገመትኩ:: አጠገቤ እየተንሳፈፈች ደረሰች:: “ይቺ ቆንጅዬ የ’ገነት’ አስተናጋጅ ናት እንዴ?” ራሴን ጠየቅኩት:: እንደዚች አይነት ብዙ አስተናጋጆች ካሉ ሁልጊዜ ‘ገነት’ በተስተናጋጆች እንደሚሞላ ለራሴ መላምት አቀረብኩ:: በእርግጠኝነት የት እንደሆነ ባላስታውስም ከዚህ ቀደም ግን የሆነ ቦታ የማውቃት መሰለኝ:: እውነት ይሄ ቦታ ‘ገነት’ ከሆነ ሳንሞት በፊት አንድ ክላስ ተምረን ይሆን? ወይስ አንድ ቀን መንገድ ላይ ለክፌያት ይሆን? ............ወይስ አንድ ቀን ...........? በራሴ ሃሳብ ደነገጥኩኝ:: አምላክ የማስበውን ከነቃብኝ ወደ ሲኦል መወርወሬ ነው ብዬ በፍጥነት ማሰቤን አቆምኩ::
“ዳኒ እየተሻለህ ነው አይደል?” ድምጿ የመላእክትን ድምጽ ይመስላል:: እቺን መቼም ‘አይደለም’ ብሎ ማሳፈር ይከብዳል:: ‘አዎን’ የሚለውን ቃል ላወጣ ስል ደነገጥኩኝ:: እንዴ ዳኒ የኔ ስም ነው እንዴ? አዎን አዎን የሚል መልስ ከአእምሮዬ መጣልኝ:: ግን ቅሬታው ሊለቀኝ አልቻለም:: ቢሆንም ባይሆንም ብዬ በመጨረሻ “አዎን እየተሻለኝ ነው” አልኳት:: ምን አሞኝ እንደነበር ትዝ ባይለኝም!! “ምነው ቅዝቅዝ አልክብኝ… ማን እንደሆንኩ ግን አስታወስከኝ?” “አዚ ነሻ!” ቃላቱ ከአፌ ተስፈንጥረው ወጡ:: ወዲያውኑ መልሼ “ይቅርታ ዶ/ር አዜብ” አልኳት:: ፊቷ ላይ የእርካታ ፈገግታ ይታያል:: “በል ይቺን ዋጥና ወደቤታችን እንሂድ” ሁለት ነጭ እንክብሎችን ከውሃ ጋር ሰጠችኝ:: ስውጣቸው በፊት ያልነበረኝን ብርታት ሰጡኝ:: ለመራመድ ግን በሷ መታቀፍ የግድ ነበር::
ግንቦት 2061 ዓ.ም
‘ገነት’ን መስሎኝ ከነበረው ግዙፍ ሆስፒታል ከወጣው ወር አለፈኝ:: በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ የአዚ እንክብካቤ ልዩ ነበር:: ለእኔ ያላትን ፍቅር ጥልቀትም ተገንዝቤዋለሁ:: እኔ ካልበላሁ እሷ እህል ባፏም አይዞር! ብቻዬን ወደ ውጪ እንድወጣ አትፈቅድልኝም:: ብወጣ ራሱ ተመልሼ እስክገባ ድረስ ስልኳ ስራ አያቋርጥም፤ ደጋግማ ትደውላለች:: እኔ ካልተኛው የእሷ እንቅልፍ የውሃ ሽታ ይሆናል:: አቤት የፍቅራችን ከአድማስ መስፋት! እነዛ ትምቡክ ትምቡክ የሚሉትን ከማር የሚጣፍጡ ከንፈሮቿን ከከንፈሬ ስታገናኛቸው፣ እነዛ ውብና ለስላሳ እጆቿን በወገቤ መሃል እያንሸራሸረች ‘አፈቅርሀለው’ ስትለኝ እኔም መልሼ ‘አፈቅርሻለው’ ስላት አቤት ደስታዋ! I mean አቤት ደስታችን!! በዝግታ ተጀምሮ ወደ ሰማይ አስመነጥቆን፣ በክዋክብቶች መሃል ቤታችንን አሰርቶን፣ ጨረቃን አሳቅፎን መልሶ ደግሞ አቀዝቅዞን፣ ወደ ምድር የሚያወርደንን ውብ ዜማ ራሳችን ደርሰን ራሳችን እናዜመዋለን:: ፍቅር ሰርተን ፍቅር በልተን ፍቅር ጠግበን እንኖራለን:: በዚህ ጊዜ ሁለታችንም የምንለው ነገር አለ..........”አቤት መሞት ባይኖር!!!”
አንዳንዴ ሳስበው በህይወታችን የሚከሰቱት ነገሮች በፈረቃ የሚከናወኑ ይመስለኛል:: ይሄ ባይሆን ኖሮ አዚ አንዳንዴ ከፍቷት አላያትም ነበር:: ይሄ ባይሆን ኖሮማ እኔን እያየች እንባዋ አይኗ ላይ ግጥም አይልም ነበራ:: በህይወቷ ውስጥ የሚያስከፋት አንድ ነገር ያለ ይመስለኛል:: ሁልጊዜ ምክንያቷን እጠይቃታለሁ:: ሁልጊዜም መልሷን ትነግረኛለች:: የሁልጊዜው ምላሽም “ ዳኒዬ እኔ’ኮ ከልቤ ስለማፈቅርህ ሳይህ ታሳሳኛለህ… ለዛ ነው የማለቅሰው” የሚለው ነው:: የወሬያችንንም አጀንዳ ከማይረቡ ነገሮች ዓለምን ሊቀይሩ ወደሚችሉ ቁምነገሮች ትቀይረዋለች ከንፈሮቼን ሳም ሳም በማድረግ:: ከእሷ የእለት ከእለት እንክብካቤ ጋር ጤንነቴ ስለተመለሰ፣ አሁን እኔ እና እሷ ተቃቅፈን ወደ ከተማ መውጣት፣ ሲኒማ መመልከት፣ ወክ ማድረግ ጀምረናል::ትናንትናዬ ግራ የገባው ትናንትና ነው:: ከብርሃንነቱ ይልቅ ጨለማነቱ ሚዛን የሚደፋ ትናንትና! አዜብ ፍቅረኛዬ ናት:: ግን መቼና የት እንደተዋወቅን፣ መቼና እንዴት ፍቅር እንደጀመርን፣ መቼ መኪና እንደገዛንና ቤት እንደሰራን ምንም ትዝ አይለኝም:: አንድም ጓደኛስ የለኝም እንዴ? በምን ስራስ እየተዳደርኩ ነበር የምኖረው?........ አእምሮዬ ስዕል እንደምችል ሲነግረኝ፣ ሸራዬን ወጥሬ ብሩሹን ከቀለሙ አዋህጄ አጣምሬ፣ ነፍስ የሚያለመልም ውብ ስዕል ልሰራ ብሞክር እጄ አሻፈረኝ ብሎ ዶሮ የሞነጫጨረው አስመሰለብኝ:: አእምሮዬ ትችላለህ ብሎኝ እንዴት እጄ እንቢ ሊለኝ ቻለ?
ሰኔ 2061 ዓ.ም
አዚ አሳ አምሮኛል ስላለችኝ ሆቴል ልንበላ እየሄድን ነው:: በመኪና መሄድ ስለሰለቸን በዛውም ተፈጥሮን ለማድነቅ በሚል በእግራችን መንገዱን ተያያዝነው:: በድንገት ከፊታችን ሁለት ወጣቶች መጡ:: “ኧረ ሶል የጠፋ ሰው! ምን ሆነህ ነው እንዲህ ዲስአፒር ያደረግኸው?” አለኝ አንዱ:: ከመቅጽበት ሁለቱም እቅፍ እቅፍቅፍ አድርገው ሰላምታ ሰጡኝ:: ሁለቱንም ላስታውሳቸው ሞከርኩ፤ ግን ምንም ጠብ ሊልልኝ አልቻለም:: “ሶል ግን ስልካችን እያለህ ይሄን ያህል ጊዜ ለምን እንዳልደወልክ አልገባኝም?” አለኝ ሁለተኛው:: አሁን እንደተሳሳቱ ገባኝ:: ”ይቅርታ እኔ ሶል የምትሉት ሰው አይደለሁም ተሳስታችኋል!” “ሶል በእውነት ሙድ ያዥ ሆነሻል:: የተበደርሽኝን 1500 ብር ረስተሽው ነው? ለሱ ብለሽ ሰፈር እንደቀየርሽ ተነቅቶብሻል” ተሳሳቁ:: አዚ ንዴቷ በጣም ገነፈለ:: “ይቅርታ የኔ ወንድሞች እሱ የምትሉት ሰው አይደለም… ተመሳስሎባችሁ ሊሆን ይችላል” አለች:: “ምን እያልሽ እንደሆነ አልገባኝም:: እኔ ሶልን ልረሳው?” “እናንተም ምን እያላችሁ እንደሆነ አልገባኝም:: እሱ እኮ ዳንኤል ነው:: የፈለጋችሁት ብር ከሆነ ግን እንኩ” ብላ ከቦርሳዋ የ2000 ብር ቼክ ፈርማ ሰጠቻቸውና እጄን እየጎተተች መንጨቅ መንጨቅ እያለች መራመድ ጀመረች:: እስክንርቅ ድረስ በድንጋጤ ክው ብለው እየተመለከቱን ነበር:: “ታውቂያቸዋለሽ እንዴ?” ራሷን በአሉታ ነቀነቀችው:: “እና ታዲያ እንዴት 2000 ብር ትሰጪያቸዋለሽ?” “ዳኒዬ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሰው እያየን ከምንጨቃጨቅ እቺን ብር ሰጥቼያቸው ብንገላገላቸው አይሻልም? ብር ፈልገው ነው እንጂ አንተን የት አውቀውህ ነው አበደርንህ ምናምን የሚሉት” ሌሎች ነገሮችን እያዋራች አረሳሳችኝ:: መንገዳችን ተገባዶ ወደ ሆቴሉ ደረስን:: ባለ 5 ኮኮብ ሆቴል ነበር:: በአንዲት ጠይም ቆንጅዬ አስተናጋጅ ተስተናገድን:: በጣም የሚጣፍጠውን አሳ ጣታችንን እስክንቆረጥም ድረስ በላነው:: በላዩ ላይ ደግሞ ቀይ ወይን!........... አስተናጋጃችን ግን በጣም ትገርማለች:: ፈገግታዋ፣ መቅለስለሷ፣ ጥቅሻዋ በዛብኝና ግራ ገባኝ:: ቢያንስ ቢያንስ ፍቅረኛ እንዳለኝና ከሷ ጋር ልዝናና እንደመጣሁ አታስብም እንዴ? አይ የዘንድሮ ሴቶች..........አይናውጣ ሆነዋል ማለት ነው አልኩኝ:: እኔና አዚ ጨርሰን ስንወጣ ለመስተንግዶዋ 50 ብር ቲፕ ሸጎጥ አደረግኩላት:: እሷም ትንሽዬ ወረቀት የኮት ኪሴ ውስጥ ወሸቅ አደረገችልኝና አንድ ፈገግታ በነጻ መረቀችልኝ:: አዚ እንዳትከፋ በሚል የሆነውን አልነገርኳትም:: እቤት እንደደረስን በችኮላ መጸዳጃ ቤት ገብቼ አስተናጋጇ የሰጠችኝን ወረቀት ገለጥኩት::
“ሶልዬ የኔ ፍቅር ስልክህን ዘግተህ ድንገት ከተለየኸኝ ወዲህ አንተን ለመፈለግ ያላደረግኩት ጥረት አልነበረም:: አንተ ግን ውቅያኖስ ውስጥ የተጣለች ሳንቲም መስለህ ደብዛህ ጥፍት አለ:: ሶልዬ ዛሬ ሳይህ ፍቅረኛዬን አገኘሁት ብዬ ልጠመጠምብህ ነበር:: ግን እኔን ችላ ማለትህንና ከጎንህ የነበረችውን ቺክ ሳይ በቃ ሌላ ጠብሶ ነው እኔን ያልፈለገኝ ብዬ አሰብኩ:: ለመሆኑ ግን ልብህ እንዴት እኔን ሊረሳ ቻለ? ያን ሁሉ የፍቅር ጊዜያትን አሳልፈን እንደማንተዋወቅ ታልፈኛለህ? የሆነ ሆኖ እኔ ሁልጊዜ የምፈልገው ያንተን ደስታ ነውና መልካም የፍቅር ጊዜን እንድታሳልፍ ተመኘሁልህ:: ምናልባት ሃሳብህን የምትቀይር ከሆነ ስልኬ 0980 …ነው:: ያንተው ዮርዲ”
ደነገጥኩኝ:: እንዴት የሚያሰቅቅ ነገር ነው? እኔ ዳኒ ነኝ፤ ዛሬ ግን ሁለት ሰዎች ሶል ብለው አናገሩኝ:: አንዷ ከነመፈጠሯም ጭምር የማላውቃት ሴት ደግሞ የድሮ ፍቅረኛዬ ነበርክ፣ የኔ ፍቅር ምናምን የሚል ደብዳቤ አሻረችኝ:: ቆይ ምንድነው እየተደረገ ያለው? እንዴ እሺ እኔ ማነኝ?
“ዳኒዬ ምነው ፈለግከኝ እንዴ?” “አዎን ዶ/ር አዜብ እኔ ማን እንደሆንኩ እንድትነግሪኝ እፈልጋለሁ::” “ዳኒ ነሃ! ደግሞ ማንን መሆን ፈለግህ?” “ሶልን........እስኪ እንቺ ይሄን ደብዳቤ አንብቢው” የዮርዲን ደብዳቤ ሰጠኋት:: ተቀብላኝ አነበበችው:: ከዛም ዝም አለች:: “ አንድ ነገር ተናገሪ እንጂ!” ሳላስበው አምባረቅሁባት:: ቀስ በቀስ እንባዋ ተንጠባጠበ አለቀሰች አለቃቀሰች ብቻዋን እያጉተመተመች:: በጣም አሳዘነችኝ:: “ምን ሆንሽ?” “ዳንኤል ወይም ሰለሞን what ever! የኔ በደል ከምትገምተው በላይ ነው:: እኔ እጄ በኅጥያት ደም የተጨማለቀ ከንቱ ነፍሰገዳይ ሐኪም ነኝ:: ነገሮች እኔ ባሰብኳቸው አቅጣጫ ሳይሆን በራሳቸው መንገድ እየሄዱ ከአቅሜ በላይ እየሆኑ ነው:: እናም አሁን እውነቱን መናገር አለብኝ:: oh my God!” ምን እንደተፈጠረ ምንም ሊገባኝ አልቻለም:: አዜብ ራሷን መቆጣጠር እያቃታት ነው:: ይሄን ያህል ከባድ ምስጢር ይኖር ይሆን እንዴ? “ እስኪ አዜብ የሆንሽውን ቀስ ብለሽ ንገሪኝ:: እኔ ምንም ብታወሪ ለመስማት ዝግጁ ነኝ::” “ይሄውልህ ስሜ ዶ/ር አዜብ ሲሆን በሙያዬም ኒውሮ ሰርጂን ነኝ:: ዳኒ የሚባል ቆንጆ ፍቅረኛ ነበረኝ::” ምን እያወራች ነው? ነበረኝ? እሺ አሁንስ? “አንተን የማውቅህ ጭንቅላቴን አመመኝ ብለህ እኔ ጋር ለመታከም የመጣህ ጊዜ ነው:: ቁመናህ፣ መልክህ፣ ፈገግታህ፣ ጨዋታህ በቃ ሁለመናህ ሳበኝ:: በጭንቅላትህ ውስጥ ካንሰር የወጣብህ መሆኑንና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ እንደሆነ በሰከንዶች ውስጥ ባለን ምርጥ የቴክኖሎጂ መሳሪያ አወቅሁኝ:: ይህንንም ላንተ ሳልነግርህ ችግርህን በራሴ ለመፍታት በወኔ ተነሳሳሁ:: ይሄን እንዳደርግ የገፋፋኝ ታዲያ ከህክምናው ስነምግባር በላይ አንተን እያፈቀርኩህ መምጣቴ ነበር::” “ታዲያ እኔ ማነኝ?” በጭንቀት ጠየቅኳት:: “አንተ ሰለሞን ትባል ነበር!” “ምን?” “እባክህን አታቋርጠኝ:: ሁሉን ነገር ከሰማህ በኋላ ፍርዱን ያኔ ትሰጠኛለህ::” ጭንቅላቴን በመነቅነቅ መስማማቴን ገለጽኩላት:: “ዳኒን ነፍስና ስጋዬ እስኪነጣጠሉ ድረስ አፈቅረው ነበር:: ምን ያደርጋል ታዲያ! ከባድ የልብ በሽታ ነበረበት:: እየጠናበት ሄዶም በመጨረሻ እኛ ሆስፒታል እንዲተኛ ሆነ” እምባዋ መንጠባጠቡን አብዝቶ ቀጠለ:: “ሆስፒታል ሆኖ ሲያንገበግበው የነበረው ጉዳይ አንድ የጀመራትን ስዕል ሳይጨርስ መተኛቱ ነበር:: እውነቴን ልንገርህ እሱ ለእኔ ከሊዎናርዶ ዳቬንቺ የበለጠ፣ ከፓብሎ ፒካሶ የሚልቅ ምርጥ ሰዓሊ ነበር:: በሰዓቱ ስራዎቼ እሱን ማስታመምና የአንተን ጉዳይ መከታተል ነበር:: ነገር ግን የአንተን ካንሰር በቀዶ ጥገና ህክምና ለማውጣት በተዘጋጀንበት ቅጽበት ዳኒዬ እንደሞተ ነገሩኝ::”
እምባዋ እንደ አባይ ጅረት እየተጥለቀለቀ ይወርዳል:: ንዴቷን በግድ እየተቆጣጠረች እንደሆነ ያስታውቅባታል:: የጠየቅኳት ጥያቄና እያወራችው ያለው ነገር ተዛምዶው አልገባ ብሎኝ ጭጭ ብዬ እያዳመጥኳት ነበር::
“ዳኒን በምንም አይነት ሁኔታ ቢሆን ማጣት አልፈለግሁም ነበር:: ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ:: ሃሳቡ ሰውነቴን ንዝር አደረገኝ ግን ጊዜዬን ማባከን አልፈለግኩም:: ወዲያው ለረዳቴ ነገርኩት፤ እሱም በሃሳቤ ተስማማ:: በሰለሞን ውስጥ ዳንኤልን እንዳይ ደግሞም ሁለቱንም ሳላጣ ለመኖር ብቸኛው አማራጭ brain transplantation ነበር:: የዳኒን brain ወደ ሶል skull ውስጥ መጨመርና ነርቮቹን መቀጣጠል፣ አርተሪና ቬይኖቹን ቶሎ ማገናኘት ብሎም ሶልም ዳኒም ሳይሞቱ እንዲኖሩ ማድረግ! Brain transplantation ድሮ ድሮ የማይቻልና የማይታሰብ እንደሆነ ይነገራል:: አሁን ግን it’s just a simple procedure. እኔም በስራው ጎበዝ ከሚባሉት ኒውሮ ሰርጂኖች መሃል አንዷ ነበርኩ:: የሚያሳዝነው አዕምሮውን ከዳኒ አውጥቼ ወደ አንተ ጭንቅላት እስካስገባው ድረስ የባከኑት ጥቂት ደቂቃዎች ጥቂት ኒውሮኖችን እንዲሞቱ ስላደረጋቸው አዕምሮው የዳኒን ሙሉ ነገር አያስታውስም:: እንግዲህ ለዚህ ነው ሰዎች መንገድ ላይ ሲያዩህ ሶል ብለው የጠሩህ ይሄ ነው ሃጥያቴ የአንተንም የሌሎችንም በተለይም የውድ ፍቅረኛህን የዮርዳኖስን ህይወት ማመሰቃቀሌ፣ ራስ ወዳድነቴ ሁለት ሰው አፍቅሬ ሁለቱንም ሳላጣ ለመኖር የነበረኝ ፍላጎት ይሄን ሁሉ አስደረገኝ:: ካሁን በኋላ ከፈለግክ በእጆችህ ሲጥ አድርገህ መግደል፣ ከፈለግክም ፖሊስ ጠርተህ ማሳሰር ትችላለህ:: ህይወቴን በእጅህ ላይ አኑሬያለሁ::”
ኑዛዜዋን ጨረሰች:: እኔ ደግሞ ማሰብ ጀመርኩ:: ምን እንደማደርጋት ግራ ገባኝ:: ይቺ ሴትዮ ህይወቴን እንዲህ አመሰቃቅላው ምን ባደርጋት የአንጀቴ ይደርስ ይሆን? የመግደያ መንገዶችን ማሰብ ጀመርኩ:: ወዲያው ደግሞ ከሆስፒታል ጀምሮ የዋለችልኝን ውለታ አስታወስኩ:: ለፍቅር ብላ የከፈለችው መስዋእትነት ነው ብዬ ልተዋት? ካሁን በኋላ ስሜስ ማን ሊሆን ይችላል? ዳንኤል ወይስ ሰለሞን? ሰውስ መጠራት ያለበት በመልኩ ነው ወይስ በአእምሮው? ብቻ አንድ ውሳኔ ላይ እስክደርስ ድረስ ከዶክተሯ ራቅ በማለት ጸጥ ረጭ ያለ ቦታ ፈልጌ ለመቀመጥ እግሮቼን ማንቀሳቀስ ጀመርኩ::

 

Read 5762 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 12:14