Saturday, 17 November 2012 11:36

ዲያስፖራ ገበሬዎች

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

ከአዲስ አበባ በ194 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ ነን፡፡ ሥፍራው በደቡብ ክልል የጉራጌ ዞን አብሽጌ ወረዳ ቦረር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ይሰኛልአካባቢው ሞቃታማ የአየር ንብረት ቢኖረውም ለምለም አፈሩ የሰጡትን የሚቀበል፣ የተከሉበትን የሚያሣድግ ለም ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ሥፍራ ለመገኘታችን ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ለክልሉ ሰማንያ በመቶ (80%) የሚሆነውን የምርጥ ዘር ፍላጐት የሚሸፍነውን የእርሻ ልማት ለመጐብኘት ሲሆን፣ የእርሻ ልማቱ ባለቤቶች ለአመታት ኑሮአቸውን መስርተው የኖሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎች ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ የቆዩና ወደ አገራቸው ተመልሰው በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዲያስፖራዎች ናቸው፡፡

ዲያስፖራው እምብዛም ባልደፈረው የግብርና ዘርፍ በመሰማራት፣ በዘመናዊ የግብርና
አሠራር በመጠቀም ለእርሻ ሥራ ግብአት የሚሆኑ ምርጥ ዘሮችንና ለኤክስፖርት የሚመጥኑ ሰብሎችን በማምረት ተግባር ላይ የተሰማሩት የእነዚህ ዲያስፖራ ገበሬዎች ጉዳይ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወልቂጤ ከተማ ብቅ ያለ እንግዳ ስለነዚህ ዲያስፖራ ገበሬዎችና ስለ እርሻ ልማቱ ሳይሰማ አይመለስም፡፡ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻቸው በግለሰቦች ደረጃ እየተሠራ ያለ ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል፡፡
በመሀመድ አወል እርሻ ልማት፣ በቦረር እርሻ ልማትና በሶፊያ ዑመር እርሻ ልማት ሥር የለማው የእርሻ ማሣ ከ790 ሄክታር በላይ ነው፡፡ አባት አቶ መሀመመድ አወል፣ እናት ወ/ሮ ሶፊያ ዑመርና የአብራካቸው ክፋይ የሆነው ልጃቸው ዑመር መሀመድ፣ አቶ ኤልያስ ከድር ከተባለ ባልንጀራው ጋራ በጋራ ያቋቋሙት የእርሻ ልማት በዚህ ኩታ ገጠም በሆነ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራን በስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራው አምራቹን እምብዛም ተጠቃሚ ስለማያደርግና ምርት ሂደቱ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በበርካታ ኢንቨስተሮች ዘንድ የማይመረጥ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ በምርጥ ዘር ማባዛት ሥራ ወቅት በከፍተኛ ጥንቃቄና በዕለት ተዕለት ክትትል ከለማ የእርሻ ማሣ ላይ በሄክታር ከ15-20 ኩንታል ምርጥ ዘር የማግኘት እድል ሲኖር፣ ለምግብነት ከሚውለውና በአነስተኛ እንክብካቤና በቀላል የአመራረት ዘዴ ከሚለማ የምግብ እርሻ ማሣ ላይ በሄክታር ከ70-80 ኩንታል ምርት ለመገኘት መቻሉ በርካታ ባለሃብቶች ከምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ተገልለው የምግብ እህል ማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ዲያስፖራ ገበሬዎች የእርሻውን ሥራ ከማሣ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሠራርን በመጠቀም ሠርተው በአጭር ጊዜ ሊደርስ የሚችልና ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለውን ምርጥ ዘር በማምረት ለገበሬው እያደረሱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዘመናዊ ግብርና አሠራርን የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና፣ የፀረ አረም መድሃኒቶች አጠቃቀምን ለአርሶ አደሩ በማስተማር ህብረተሰቡ በዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎች የመጠቀም ልምድን እንዲያዳብር ያስተምራሉ፡፡ አባት አቶ መሀመድ አወል የጀመሩትን የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ልጃቸው ዑመር መሀመድ ከአሜሪካ መጥቶ ተከትሎታል፡፡ ዑመር እጅግ ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኝበትን ሥራውንና የተደላደለ ዘመናዊ የውጭ አገር ኑሮውን ጣጥሎ አገሩ በመግባት ኤልያስ ከድር ከተባለ ኢንቨስተር ጓደኛው ጋር ያቋቋመው ቦረር እርሻ ልማት በ225 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ ዑመር በዚህ የእርሻ ማሳ ላይ በዘመኑ አዲስ የተባለውንና እጅግ በጣም ምርታማ በመሆኑ ተመራጭነቱ ከፍ እያለ የመጣውን BH-540 የበቆሎ ዝርያ በማምረት ለአርሶ አደሩ የዘር ምንጭ በመሆን እየሰራ ነው፡፡ የእርሻ ልማቱ በክልሉ በዚህ BH-540 በተባለው የምርጥ በቆሎ ዝርያ ብዜት ሥራ ብቸኛው መሆኑንና ከፍተኛውን የአቅርቦት ተግባርም በማከናወን ላይ የሚገኝ መሆኑን የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ዓመት የእርሻ ልማቱ ባሣየው እንቅስቃሴና በዘር ማብዛት ሥራ ውስጥ ባበረከተው አስተዋፅኦ የዞኑ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቢሮ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ሲል መርጦ ሸልሞታል፡፡
ባለፈው ሣምንት መጨረሻ የእርሻ ማሣውን ለመጐብኘት ከሥፍራው የታደመው ቡድን በማሣው ላይ ባየው ነገር መገረሙን መደበቅ አልቻለም፡፡ ለመኪና መሄጃ መንገድ መሀል ለመሀል እየተወ ግራ ቀኙን ይዞ በመስመር የተተከለው የምርጥ ዘር በቆሎ፣ የሸንብራና የበርበሬ እርሻ ለአይን ያታክታል፡፡ አይኑን ወደ ሩቅ አሻግሮ ለመመልከት የሞከረ ሰው፣ በተንጣለለ ሜዳ ላይ የሚዘናፈልና ለዓይን የሚያሣሣ ሰብል ማየት አይደለም፡፡ አርሶ አደሩን እንጂ ባለሃብቱን ተጠቃሚ ባለማድረጉና ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ በዘር ብዜት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች እምብዛም የማያመርቱት BH-540 የተባለው የበቆሎ ዝርያ እዚህ በስፋት ይመረታል፡፡ ሰማንያ በመቶ የሚደርሰው የክልሉ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት የሚሸፈነውም በዚሁ እርሻ ነው፡፡ የደቡብ ክልል እርሻ ልማት ድርጅት ምርጥ ዘሩን ከእነ አቶ ዑመር መሀመድ በ1350 ብር ሂሣብ እየተረከበ ለአርሶ አደሩ በሽያጭ ያከፋፍላል፡፡ ይህ ዋጋ ባለፉት ዓመታት የተሰጠ ዋጋ በመሆኑና በየጊዜው እየጨመረ ከሚሄደው የሰው ኃይል ክፍያ፣ የነዳጅ ዋጋ እና የማዳበሪያና የፀረ አረም መድሃኒቶች ዋጋ ጋር ፈፅሞ የሚጣጣም አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ዲያስፖራ ገበሬዎቹ ከምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ወጥተው በአጭር ጊዜ በሚደርሰውና ብዙም ድካም በማይጠይቅ ሁኔታ በዘመናዊ መልክ ሊመረት ወደሚችለው ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን የማምረት ተግባር ላይ እንዲሰማሩ የሚያስገድድ ሁኔታ እየፈጠረባቸው ነው፡፡ በምርጥ ዘር የበቆሎ ዝርያ አቅርቦት በደቡብ ክልል ብቸኛ የሆነው ይህ የእርሻ ልማት ድርጅት ሥራውን ቢያቋርጥ በአርሶ አደሩና በአገሪቱ ላይ ሊከሰት የሚችለውን ቀውስ ለመረዳት ብዙ ምርምር አያስፈልግም፡፡


የቦረር እርሻ ልማት ባለቤት አቶ ዑመር መሀመድ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገረው፤ ለአሥራ አንድ አመታት ኑሮውን ከመሰረተባት አሜሪካ ወደ አገሩ መጥቶ ለመሥራት የወሰነው ከስድስት አመታት በፊት ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አባቱ የተሰማሩበትን የእርሻ ሥራ ሊመለከት በሁኔታው እጅግ ተመሰጠ፡፡ ይህ ሁሉ እያለን ስማችን በዓለም መዝገበ ቃላት በረሃብና በድርቅ መገለፁ አሣዘነው፡፡ አገሬ ገብቼ መሥራት አለብኝ ሲልም ወሰነ፡፡ ጊዜ ሣያጠፋ እጅግ ዘመናዊና የተደላደለ ኑሮን የሚኖርባትን አሜሪካ ተሰናብቶ አገሩ ገባ፡፡ እንደሱው የባዕድ አገር ኑሮ በቃኝ ብሎ አገሩ ከገባ ኤልያስ ከድር ከተባለ ሌላ ዲያስፖራ ጋር በመሆን እዛው ከአባቱ እርሻ ጋር ኩታገጠም የሆነ መሬት ከዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ ወስዶ ዘመናዊ እርሻውን ሀ ብሎ ጀመረ፡፡ ከኤልያስ ከድር ጋር የጀመሩትን ይህንኑ የእርሻ ልማትም ቦርት የእርሻ ልማት የሚል ሥያሜ ሰጡት፡፡ የእርሻ ማሳቸው ከዓመት ዓመት የሚያሳየው ውጤትና የአካባቢው ለምነት ሞራል ሰጣቸው፡፡ ዛሬ የቦረር እርሻ ልማት 18 ቋሚ፣ 150 ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቀጥሮ የሚያስተዳድር ሲሆን ከ400 ለሚበልጡ የቀን ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ከተንጣለለው የእርሻ ማሣ ዘንድሮ ከወትሮው የተሻለ የምርጥ ዘር ምርት ይጠበቃል፡፡
አቶ ዑመር መሀመድ ያለውን አቅምና እውቀት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀምና የእርሻ ሥራውን በሥፋት ለማከናወን የመሬት ጥበትና የምርጥ ዘር ዋጋ አነስተኛነት ማነቆ እንደሆኑበት ይናገራል፡፡ በዚህ የእርሻ ማሣ ላይ ያለ ሥራ የቀረ ሥንዝር መሬት አይታይም፡፡ የምርጥ ዘር እርሻ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ጥንቃቄ ውስጥ በማሣዎች መካከል መኖር የሚገባው ከ300-400 ሜትር ክፍተት እነ ዑመር የምርጥ ዘር ማባዛት ሥራውን በፈለጉት መጠን እንዳይሠሩ አግዷቸዋል፡፡ ለዚህም የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸው የእርሻ መሬት እንዲሰጣቸው ለዞኑ የኢንቨስትመንት ቢሮ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ጥያቄያቸው በዞኑ የሥራ ኃላፊዎች እየታየ እንደሆነና በቅርቡም ምላሽ እንደሚሰጥበት ኃላፊዎቹ ነግረውናል፡፡
የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ መርሻ በዞኑ ውስጥ ከ230 በላይ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ይህንን የእርሻ ልማት ተወዳዳሪ የሌለው ነው ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡
ኃላፊው ከባድና እልህ አስጨራሽ ነው ባሉት በምርጥ ዘር ማባዛት ሥራ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙትን እነዚህ ባለሃብቶች፣ የመደገፉንና የማበረታታቱን ተግባር ዞናቸው እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከክልሉ የምርጥ በቆሎ ዝርያ አቅርቦት ሰማንያ በመቶ የሚሆነው በእነዚህ ባለሃብቶች የሚሸፈን መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የምርጥ ዘር ፍላጐቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምራ መሀመድ በበኩላቸው፤ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩት እነዚህ ባለሀብቶች እያከናወኑት ያለው ሥራ ከዞኑ አልፎ በክልልና በአገር ደረጃም ትልቅ ውጤት ያለው ሥራ ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ በምርጥ የበቆሎ ዝርያ በዚህን ያህል መጠን የሚያመርት አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ምራ፤ ባለሃብቶቹ የምርጥ ዘር ዋጋ ማነስና ከእህል ምርት ጋር ሲነፃፀር የዘር ምርት ውጤት አናሣ መሆን ከዘር ብዜት ሥራ እንዳያስወጣቸው አንዳንድ የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እነ ዑመር መሀመድ ከበቆሎ ዘር ብዜት ሥራ በተጨማሪም የጤፍ፣ የሽንብራና የቦሎቄ ምርጥ ዝርያዎችን በማምረት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስና አርሶ አደሩ ውጤታማ የሆነ የግብርና ሥራ እንዲያከናውን ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ገልፀውልናል፡፡ ለምግብነት የሚውሉ የቦሎቄ፣ የሽንብራና የበርበሬ ምርቶችን ግን አሁንም እያመረቱ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡ በተንጣለለው የእርሻ ማሳቸው ላይም የተጠቀሱትን የሰብል አይነቶች የማየት ዕድሉ ገጥሞናል፡፡
እነዚህ ዲያስፖራ ገበሬዎች እያከናወኑት ያለው የእርሻ ተግባር በአገር ደረጃ ትልቅ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው ያሉት የጉራጌ ዞን አስተዳደሪው አቶ ይግለጡ አብዛ፤ ባለሃብቶቹ ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያበረከቱት ያለውን ትልቅ አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲገፉበት ዞኑ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነቱን ጠቁመዋል፡፡ በአንዳንድ ባለሃብቶች የተለመደውና ለኢንቨስትመንት የያዟቸውን መሬቶች አጥሮ የማስቀመጥ ልማድ በዞናቸውም አልፎ አልፎ እንደሚስተዋል የጠቆሙት ኃላፊው፤ እንዲህ ያሉት ባለሃብቶች የወሰዷቸውን መሬት እንዲመልሱ በማድረግ እንደነ ዑመር ላሉ ውጤታማ ሥራ ለሚሰሩ ባለሃብቶች እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከስድስት ባለሃብቶች መሬት መንጠቃቸውንም ዞን አስተዳዳሪው ነግረውናል፡፡ ትልቅ ራዕይና ዓላማን ይዞ ወደ አገሩ የመጣው ወጣቱ ኢንቨስተር፤ ከእርሻ ሥራው በተጨማሪ ከቤተሰቦቹ ጋር በሆቴል ሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታል ለመገንባት ሙሉ የህክምና ቁሣቁሱን ከውጭ አገር አስመጥቶ የቦታ ርክክብ በማድረግ ግንባታውን ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተገልፆልናል፡፡

Read 4442 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 12:04