Saturday, 17 November 2012 11:14

የኢትዮጵያ ታላላቆች ዘላለማዊ ማረፊያ Featured

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(5 votes)

መቃብረ ነገሥት ወሰማዕታት
የአርሊንግተን ብሔራዊ መካነ መቃብር በዩናይትድ ስቴስት፣ የዌስት ሚኒስቴር አቤይ መካነ መቃብር በብሪታንያ፣ የታላላቆቻቸው ዘላለማዊ ማረፊያ እንደሆነ ሁሉ በኢትዮጵያም የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የንጉሣዊ ቤተሠቦች፣ የአርበኞች እንዲሁም፣ የሐይማኖት እና የወታደራዊ ባለሥልጣናት ዘላቂ የእረፍት ሥፍራ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ካቴድራሉ እንደ አዲስ ከተመሠረተ ወዲህ ባሉት የሰባ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአፀዱ መካከል በርካታ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ ታላላቆች ለዘላለም አንቀላፍተውበታል፡፡ መንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እዚህ አዲስ አበባ ከተማ፣ ፓርላማው አጠገብ የሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ደብር ነው፡፡ ይህ ደብር የአሁኑን ሥያሜውንና ከመያዙ በፊት መካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም ተቀብተውና ዘውድ ጭነው ከአልጋ ወራሽነት ወደ ንጉሥነት የተሸጋገሩት በዚሁ ደብር ውስጥ በተከናወነ ደማቅ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴ ታህሳስ 15 ቀን 1924 ዓ.ም የአሁኑን ቅርጹንና ሥያሜውን ያሥገኘለትን የአዲስና ዘመናዊ ቤተ ክርስትያን የመሠረት ድንጋይ አኖሩ፡፡ ግንባታው ከውጪ አገር በመጡ ባለሙያዎች ተጀምሮ በመሠራት ላይ እያለ በ1928 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ሰበብ ሥራው ተቋረጠ፡፡ አንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጸሀፊ በነጻነት ማግሥት በወረራው ምክንያት በጅምር ስለቀረው ሕንጻ ሲያትቱ፤ “በዚያን ክፉ ዘመን እንኳን ሠው የሠራው ሕንጻ፤ የእግዚአብሔር ሕንጻ የሆነው ሠው የሚደመሰስበት ጊዜ ነበር” ብለዋል፡፡ 
ሆኖም ይኸው ጅምር ሕንጻ በወረራው ዘመን ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ቆይቶ ግንባታው እንደገና የተጀመረው ፋሺስት ኢጣሊያ ተባርሮ ነጻነት ከተመለሰ በኋላ ሁለት ዓመት ያህል ዘግይቶ በ1935 ዓ.ም ነበር፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ ሥራው መሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ዓመታዊው የሥላሴ ክብረ በዓል በሚከበርበት ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ መሳፍንትና መኳንንት በተገኙበት የተፈጸመ ሲሆን በዕለቱ ካቴድራሉ ሌላ እጅግ ታሪካዊ የሆነ ክንውንን አስተናግዷል፡፡
ይኸውም በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዘመን አገራቸውን ላለማስደፈር በዱር በገደሉ ተሠማርተው ከጠላት ጋር ሲፋለሙ የወደቁትን፤ እንዲሁም በፋሺስቶች የግፍ እርምጃ እየተገደሉ እንደ ጉድፍ የትም የተጣሉትን ኢትዮጵያውያን አፅም አቀባበል የማድረግና የማሳረፍ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ ጥር 13 ቀን 1936 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሥነ ሥርዓቱን እንደሚከተለው ዘግቦት ነበር፡፡ “የኢትዮጵያውያኑ ሠማዕታት አጽም በሳጥን ሆኖ፣ በሀዘን ልብስ መጎናጸፊያ ተሸፍኖ በዚያ ላይ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማን ተጎናጽፎ፣ ስለ ሀገራቸው መድፋቸውን አጥምደው ሲዋጉ መሞታቸውን ለማስረዳት በመድፍ መንኮራኩር በተጠመደ ሠረገላ ላይ አርፎ፤ በስድስት ፈረሶች እየተሳበ፤ አርበኞቹ ዳጃዝማች በቀለ ወያና ደጃዝማች (አሞራው) ውብነህ ተሠማ፣ ፊታውራሪ ፀሐይ እንቁሥላሴና ፊታውራሪ ከበደ ብዙነሽ ያንበሳ ጎፈር አድርገው፤ በእጅ ሥራ የተጌጠ ያንበሳ ለምድ ለብሰው፤ ሁለት ሁለት ላንቃ ያለው ጦር ይዘው፤ ስለ አጽሙ ክብር ሣጥኑ የተጎናጸፈውን ልብስ ጨብጠው ይዘው አጅበዋል፡፡
እንደዚሁም ከነሱ አጠገብ አራት የጦር ሠራዊት መኮንኖች፣ ሠይፍ ሠይፋቸውን ይዘው ሲጓዙና ከነሱ በስተኋላ በሁለት ኦፊሰሮች ሰፋፊ የአበባ አክሊል ተይዞ በቀኝና በግራ በተገረገረው ሰልፍ መሐልም ሲያልፉ “ሞትስ ለጻድቃን ሕይወት ነው የተባለውን ቃል ያሳስብ ነበር” በማለት ጽፏል፡፡
የሐዘን ማርሽ እየተሰማ በሙሉ ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት የታጀበው የሠማዕታቱ አፅም፣ በቤተ ክርስቲያኑ ዋና መግቢያ ደርሶ ከተቀመጠ በኋላ፣ በካቴድራሉ ምድር ቤት ወደተዘጋጀለት መኖሪያ ገብቶ እንዲያርፍ ተደረገ፡፡
በዚሁ ጊዜም ከኢጣሊያ ወረራ ቀደም ብሎ ያረፈችው የንጉሠ ነገሥቱ ሴት ልጅ ልዕልት ዘነበ ወርቅ አጽምም ወደዚሁ ቤተ ክርስቲያን ፈልሶ፣ ለንጉሣዊው ቤተሠብ በቤተ ክርስትያኑ ውስጥ በተለይ በተዘጋጀውና በቅድሥቱ መሐል በመቅደሱ አንጻር ወደ ታች በልዩ ሁኔታ በታነጸው መቃብረ ነገሥት ውሥጥ አርፏል፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ ግራና ቀኝ ለነዚሁ ሠማዕታት መታሰቢያ የሚሆን ከጥርብ ድንጊያ የተሠራ ሐውልት የቆመ ሲሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ አጼ ኃይለ ሥላሴ ባደረጉት ንግግር “ለንጉሠ ነገሥት ቤተሠባችን ደንበኛ የዕረፍት ሥፍራ እንዲሆን በመሠረትነው የክብር ቦታ በሥራቸውና በመሥዋዕትነታቸው ውለታቸውን ልንመልስላቸው የተገባቸው አገልጋዮች ደንበኛ የርስት ተካፋይ እንዲሆኑ ፈቀድን፡፡
የሚገባቸውን ፈጽመው ማረፋቸውን ስንመሰክርላቸው በአፅማቸው ፊት የክብር ሠላምታ እንሠጣለን” ካሉ በኋላ በመታሰቢያ ሐውልቱ ፊት ለፊት ቆመው ወታደራዊ ሠላምታ አቅርበው ነበር፡፡ በሀውልቶቹ የፊት ገጽ ይህ ግጥም በጥርብ ደንጊያ ላይ ተቀርጾበታል፡፡
ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ
በችንከር ቸንክሮ ሰው እየገደለ
ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ
ማነው እንደ ፋሺስት በሰው ግፍ የዋለ
ሥጋችንን ገድለው ሣይቀብሩ እየጣሉ
ሥማችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ
በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ
እኒህ አስከሬኖች ይመሠክራሉ
ይህንን ታላቅ ሥቃይ መከራና ግፍ
ሲያስታውሰው ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ
አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን
ኢጣሊያ እንደሆነች መርዛም ጠላታችን
እናንት እድምተኞች ዕድለኞች ናችሁ
በኃይለ ሥላሴ ትንሣኤ አገኛችሁ፡፡
በየገደሉና በየጥሻው አጽማቸው ረግፎ ከተገኙት በርካታ ሰማዕታት ውስጥ በየካቲት 1929 ዓ.ም ፋሺስቶችን ሲፋለሙ ተይዘው የተገደሉት የኢትዮጵያ የደቡብ ጦር አዛዥ ራስ ደስታ ዳምጠው አንዱ ናቸው፡፡ በተጨማሪ “ዐይኔ እያየ የምኒልክን አገር ጠላት አይደፍራትም” በማለት በስተእርጅና ዘመናቸው የጎልማሶችን ጀግንነት ተላብሰው ፋሺስቶችን ገጥመው ሲዋጉ የወደቁት ሥመ ጥሩው የዓድዋው ጀግና ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ አጽምም በዚህ ሥፍራ በክብር ካረፉት አርበኞች ውሥጥ ይገኝበታል፡፡
ካቴድራሉ የንጉሣዊው ቤተሠብ ማረፊያ አስቀድሞ የተዘጋጀበት እንደመሆኑ ንጉሠ ነገሥቱ፣ እቴጌና ልዑላን ልጆቻቸው ተራ በተራ አርፈውበታል፡፡ ይኸውም በቅደም ተከተል ልዕልት ዘነበ ወርቅ (በ1936 ዓ.ም)፣ ልዑል መኮንን (በ1949 ዓ.ም)፣ እቴጌ መነን (በ1954 ዓ.ም)፣ ልዑል ሣህለ ሥላሴ (በ1954 ዓ.ም)፣ ልዑል አስፋ ወሰን (በ1989 ዓ.ም)፣ ልዕልት ተናኘ ወርቅ (በ1993 ዓ.ም) አርፈዋል፡፡
እነሆ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ካቴድራሉ ኦፊሴላዊ የንጉሣዊ ቤተሰብ እና የአርበኞች ብሔራዊ መካነ መቃብር በመሆን አገልግሎቱን ጀመረ፡፡ ይኸው ልማድ ሳይቋረጥ ቆይቶ የደርግ መንግሥት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ የካቴድራሉ መካነ መቃብር የተለመደ አገልግሎቱን ሲያበረክት ቆይቷል፡፡
ባለፉት 84 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተነሱት ሶስት መሪዎች ሁለቱ (ዐፄ ኃይለ ሥላሴና አቶ መለስ ዜናዊ) ያረፉት በዚህ ካቴድራል ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን ሳይጨምር የሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቀብር በቤተ ክርስትያኑ ተፈጽሟል፡፡
ሶስቱ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሲሆኑ እነሱም ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተ ወልድ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን እና ልጅ ሚካኤል እምሩ ናቸው፡፡
ይህ ታሪካዊ ካቴድራል በሐገራችን በተለያየ ጊዜ የተነሱ ብጥብጦች ሳቢያ የተገደሉ ባለሥልጣናት ማረፊያም ሆኗል፡፡
በታህሳስ 1953 ዓ.ም በክቡር ዘበኛው አዛዥ በጀነራል መንግሥቱ ንዋይ በተመራው መፈንቅለ መንግሥት ሳቢያ በግፍ ከተገደሉት 19 ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የንግድ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ እና ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ ያረፉት በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውሥጥ ነው፡፡
ደርግ በግፍ የጨፈጨፋቸው በተለምዶ “ስልሳዎቹ” በመባል የሚታወቁት ቀደምት ሠማዕታት አፅም ከጅምላ የመቃብር ጉድጓድ ወጥቶ እንደገና በክብር ያረፈው በዚሁ ካቴድራል ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ከንጉሣዊ ቤተሠብ፣ ከአርበኞችና የመንግሥት መሪዎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት እና የቤተ ክህነት መሪዎች አርፈውበታል፡፡
በዚህ ጎራ ከሚመደቡት መንፈሳዊ መሪዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ተክለ ሐይማኖት እና በቅርቡ ከዚህ ዓለም ያለፉት አቡነ ጳውሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ይገኙበታል፡፡
ካቴድራሉ በጥበብ ሥራቸው ከሙያ ጓደኞቻቸው ልቀውና መጥቀው በመገኘት ያንጸባራቂ ገድል ባለቤት የሆኑ የጥበብ ታላላቆችን በአፀዱ ሥር አሳርፏል፡፡ በዚህ ዝርዝር ከሚቀመጡት ውስጥ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድሕን፣ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ አርቲስት አስናቀች ወርቁ እና ደራሲ ስብሀት ገብረ እግዚአብሔር በቀዳሚነት ይገኙበታል፡፡
ጊዜ ሲቀያየር የሚለዋወጡት መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ የቦታ አገልግሎትም ጭምር እንደመሆኑ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ካቴድራሉ በመካነ መቃብሩ የሚያስተናግደው አርበኞችን ብቻ መሆኑ ቀርቶ ባለሥልጣናትን፣ አርቲስቶችን፣ ደራሲያንንና የፖለቲካ ሰዎች በመሆኑ በሂደት ሥፍራው ወደ ብሔራዊ መካነ መቃብርነት ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሆኖም ካቴድራሉ ያለው መሬት ውስን እንደመሆኑ፤ በሥፍራው የሚቀበሩትን ሰዎች ማንነት የሚወስን ደንብ ተዘጋጅቶ ከለላ ካልተደረገለት፣ ሥፍራው ወደ ተራ የሠፈር መካነ መቃብርነት ደረጃ ዝቅ ብሎ ታላላቆችን የምናሳርፍበት ቦታ እንዳይጠፋ ስለሚያሰጋ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊያስቡበት ይገባል፡፡

 

Read 6585 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:35